አብርሃምና አምልኮተ ጣዖት – ትርጉም አልባ የቁርኣን ትረካ

አብርሃምና አምልኮተ ጣዖት 

ትርጉም አልባ የቁርኣን ትረካ

“ሌሊቱም በእርሱ ላይ ባጨለመ ጊዜ ኮከብን አየ፡፡ «ይህ ጌታዬ ነው» አለ፡፡ በጠለቀም ጊዜ፡- «ጠላቂዎችን አልወድም» አለ፡፡ ጨረቃንም ወጪ ኾኖ ባየ ጊዜ፡- «ይህ ጌታዬ ነው» አለ፡፡ በገባም ጊዜ፡- «ጌታዬ (ቅኑን መንገድ) ባይመራኝ በእርግጥ ከተሳሳቱት ሕዝቦች እኾናለሁ» አለ፡፡ ፀሐይንም ጮራዋን ዘርግታ ባየ ጊዜ፡- «ይህ ጌታዬ ነው፡፡ ይህ በጣም ትልቅ ነው» አለ፡፡ በገባችም ጊዜ፡- «ወገኖቼ ሆይ! እኔ ከምታጋሩት ሁሉ ንጹሕ ነኝ» አለ፡፡ «እኔ ለዚያ ሰማያትንና ምድርን ለፈጠረው (አምላክ) ቀጥተኛ ስኾን ፊቴን አዞርኩ፡፡ እኔም ከአጋሪዎቹ አይደለሁም» (አለ)፡፡ወገኖቹም ተከራከሩት፡፡ «በአላህ (አንድነት) በእርግጥ የመራኝ ሲኾን ትከራከሩኛላችሁን በእርሱም የምታጋሩትን ነገር አልፈራም፡፡ ግን ጌታዬ ነገርን ቢሻ (ያገኘኛል)፡፡ ጌታዬም ነገሩን ሁሉ ዕውቀቱ ሰፋ፡፡ አትገነዘቡምን» አላቸው፡፡” (ሱራ 6፡76-80)

ይህንን ትረካ ልብ ብሎ የተመለከተ ሁሉ እውነተኛ ታሪክ ከመሆን ይልቅ ተረት መሆኑ ይገባዋል፡፡ አብርሃም የከዋክብትን መታየትና መጥለቅ እንዲሁም የጨረቃና የፀሐይን መውጣትና መግባት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ብዙ ሺህ ጊዜ የተመለከተ ሰው ሆኖ ሳለ ከዕለታት አንድ ቀን እነዚህ የህዋ አካላት ሲወጡና ሲገቡ ተመልክቶ እያንዳንዳቸውን በየተራ “ይህ ጌታዬ ነው” ብሎ እስኪያመልካቸው ድረስ እንዴት አዲስ ሊሆኑበት ቻሉ? አብርሃም እስከዚያች ዕለት ድረስ የነዚህን ብርሃናት መውጣትና መጥለቅ አላስተዋለም ነበርን?

ከላይ በሚገኘው የቁርኣን ትረካ መሠረት በመጀመርያው አጋጣሚ ሌሊቱ ሲጨልም አብርሃም ቀና ብሎ ኮከቡን ተመልክቶ “ይህ ጌታዬ ነው” በማለት አመለከው፡፡ ነገር ግን ኮከቡ ሲጠልቅ “ጠላቂዎችን አልወድም” በማለት ሐሳቡን ቀየረ፡፡ በማስከተል ደግሞ ጨረቃ ስትወጣ ተመልክቶ “ይህ ጌታዬ ነው” በማለት ማምለክ ጀመረ፡፡ እዚህ ጋ አንድ ጥያቄ እንጠይቅ፡፡ አብርሃም ኮከቡን ማምለክ የተወው ለምንድነው? መልሱ “ስለጠለቀ” የሚል ነው፡፡ ታድያ አብርሃም ጨረቃን ማምለክ ሲጀምር መጥለቁን አያውቅም ነበርን? አብርሃም የጨረቃን መውጣትና መጥለቅ ብዙ ሺህ ጊዜ የተመለከተ በመሆኑ እንደምትጠልቅ ያውቃል፡፡ ነገር ግን በቁርኣን ትረካ መሠረት የጨረቃን መጥለቅ ተመልክቶ ማምለክ ማቆሙ ተነግሮናል፡፡ ትረካው በዚህ አያበቃም፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ፀሐይ ስትወጣ ተመልክቶ “ይህ ጌታዬ ነው ይህ በጣም ትልቅ ነው” በማለት ፀሐይን ማምለክ እንደጀመረ ይነግረናል፡፡ ቀደም ሲል ኮከብና ጨረቃ መውጣታቸውን ተመልክቶ ካመለካቸው በኋላ መግባታቸውን ሲመለከት አምላክ አለመሆናቸውን ተረድቶ ሁለቱንም ማምለክ ያቆመው አብርሃም፤ ከዚያ ቀደም ፀሐይ ስትጠልቅ አይቶ የማያውቅ ይመስል እርሷንም ማምለክ ጀምሮ ልክ ስትጠልቅ አምላክ አለመሆኗን ተረድቶ “ወገኖቼ ሆይ! እኔ ከምታጋሩት ሁሉ ንጹሕ ነኝ” በማለት ተናገረ፡፡ የፀሐይን መውጣትና መጥለቅ ዕድሜ ልኩን ሲያይ የኖረ ሰው እንዲህ ይሞኛል ብሎ ማሰብ ከዚያ የባሰ ሞኝነት ነው፡፡

ይህ ጥቅስ ሌላ ጥያቄም ያስነሳል፡፡ አብርሃም የጨረቃን መግባት ተመልክቶ አምላክ አለመሆኑን ከተረዳ በኋላ “ጌታዬ (ቅኑን መንገድ) ባይመራኝ በእርግጥ ከተሳሳቱት ሕዝቦች እኾናለሁ” በማለት እንደተናገረ ተጽፏል፡፡ ቀደም ሲል አብርሃም የኮከብና የጨረቃን መግባት ተመልክቶ አማልክት አለመሆናቸውን አረጋግጧል፡፡ ታድያ አሁን ቅኑን መንገድ እንዲመራው ተስፋ ያደረገው ጌታ ማን ነው? አብርሃም እነዚህን ሐሰተኛ አማልክት ከሚያመልክ መጀመርያውኑ “ቅኑን መንገድ እንዲመራው” ተስፋ እያደረገ ያለውን ይህንን አምላክ ማምለክ ይችል አልነበረምን? ነገር ግን የቁርኣን ጸሐፊ አብርሃም የፀሐይን መጥለቅ የማያውቅ ይመስል ለሦስተኛ ጊዜ የተታለለ በማስመሰል ስሎልናል፡፡ ከዚህ ሁሉ የምንረዳው ይህ ታሪክ ምናባዊ ፈጠራ እንጂ እውነተኛ ታሪክ አለመሆኑን ነው፡፡ ፈጠራው ምናልባት ለህፃናት ይመጥን እንደሆን እንጂ ለአዋቂዎች የሚመጥን አይደለም፡፡

በጥቅሉ ስንመለከት በቁርኣን ውስጥ የሚገኘው የአብርሃም ታሪክ በ2ው ክፍለ ዘመን ረቢ ሂያ በተሰኘ የአይሁድ ረቢ የአምልኮተ ጣዖታትን አደገኛነት ለማስተማር በሚል የተፈጠረ በሚድራሽ ውስጥ የሚገኝ ምሳሌ ሲሆን እውነተኛ ታሪክ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ለቅዱሳት መጻሕፍት ባይተዋር የነበረው የቁርኣን ደራሲ ግን ምሳሌውን እውነተኛ ታሪክ አድርጎ በማቅረብ ስህተት ሠርቷል፡፡ ውድ ሙስሊሞች፤ ይህንን ነው ከሰማይ የወረደ መገለጥ የምትሉት?

ቅዱስ ቁርኣን