የአቡበክር ቁርአንን የማሰባሰብ ሂደት ከጥርጣሬ የፀዳ ነበርን?

ሙስሊም ወገኖች ለቁርአን በትክክል ተጠብቆ መቆየት እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት ሌላው ነጥብ በኸሊፋ አቡበክር ዘመን በአንድ ጥራዝ መሰብሰቡን ነው፡፡ ቁርአንን በቃላቸው ያጠኑ ብዙ ሰዎች በየማማ ጦርነት (ሐርበ ሪዳ) በማለቃቸው ምክያት በስጋትና በችኮላ የተፈፀመውን ይህንን የማሰባሰብ ሒደት ፍፁም ከጥርጣሬ የጸዳና ቁርአን ላይ ለውጥ አለመደረጉን ባረጋገጠ መንገድ የተሠራ በማስመሰል ይናገራሉ፡፡ እውነቱ ግን ከዚያ እጅግ የራቀ ነው፡፡ የአቡበክርን የማሰባሰብ ሒደት በከፍተኛ ጥርጣሬ እንድንመለከት የሚያደርጉ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ተከታዩ ጽሑፍ ለሐሰን ታጁ መጽሐፍ ከሰጠነው ምላሽ ላይ የተወሰደ ነው፡፡

ሐሰን ታጁ ቁርአን በነቢዩ ዘመን በአንድ ጥራዝ ለምን እንዳልተሰበሰበ ሲገልፁ “በየጊዜው በመውረድ ሂደት ላይ ስለነበርና ጽሑፉ ስላልተጠናቀቀ ነው” ይላሉ (ገፅ 19)፡፡

ቀደም ሲል እንደገለፅነው የቁርአን ሁለት ሦስተኛው በመሐመድ ዘመን በጽሑፍ መጠበቁን የሚያመለክት የረባ ማስረጃ የለም፡፡ ሆኖም ቁርአን በመሐመድ ዘመን በአንድ ጥራዝ ያለመሰብሰቡ ምክንያቱ ሐሰን ታጁ የጠቀሱት ብቻ አይደለም፡፡ አል-ሱዩጢ የተሰኙ ሙስሊም ሊቅ እንዲህ ይላሉ፡-

“ነቢዩ መሐመድ የተወሰኑ ሕግጋትንና ንባባትን የመሻር ሐሳብ ስለነበራቸው ቁርአንን በአንድ ጥራዝ አልሰበሰቡትም፡፡”[1]

ቁርአንን ለመጀመርያ ጊዜ በአንድ ጥራዝ እንዲሰበሰብ ያደረጉት ኸሊፋ አቡበክር ሲዲቅ ነበሩ፡፡ አቶ ሐሰን ቁርአን በአቡበክር ዘመን የተሰበሰበበትን ሂደት ሲገልፁ፡- “ሐርበ ሪዳ” በተሰኘ የአመፅ ጦርነት ምክንያት የማማ በተባለ ቦታ በርካታ የነቢዩ ባልንጀሮች የሞቱበት ሁኔታ መከሰቱን፤ ከነዚህ መካከል በቁርአን ሊቅነታቸው የታወቁ 70 ያህል ሶሐቦች መሞታቸውን፤ የቁርአን አዋቂዎች ሞተው ያለቁ እንደሆን ቁርአንን ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ሂደት ሊቋረጥ መቻሉ ዑመርን እንዳሰጋው፤ ስለዚህ ቁርአን የተጻፈባቸው ቁሳቁሶች ሁሉ በኸሊፋው ኃላፊነት ስር እንዲሰበሰቡ ሐሳብ እንዳቀረበ፤ በዚህም መሠረት የማሰባሰቡን ሂደት “ምግባረ ሰናይ” የነበረው ዘይድ በበላይነት እንዲመራው እንደተመረጠና ይህንኑ እንዳከናወነ አትተዋል (ገፅ 20-22)፡፡ ነገር ግን በማሰባሰቡ ሂደት ወቅት የነበረውን አጨቃጫቂ ሁኔታና ሸፍጥ ሳይገልፁ አልፈዋል፡፡ በአቡበክር ዘመን የተደረገው ቁርአንን የማሰባሰብ ሂደት አጠራጣሪ የሚሆንባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ፡-

  1. የመጀመርያው መታወቅ ያለበት ጉዳይ ቢኖር ስለዚህ የማሰባሰብ ሂደት የሚናገሩት ድርሳናት በወቅቱ የተጻፉ ሳይሆኑ ነገሩ ከተከሰተ ከክፍለ ዘመናት በኋላ የተጻፉ መሆናቸው ነው፡፡ ዘጋቢዎቹ ምንም ያህል ቅኖችና ሐቀኞች ቢሆኑ ታሪኩ በጊዜ ርዝመት መበረዝ መቻሉ የሚያከራክር አይደለም፡፡ በዚህ ሂደት ወቅት አስደንጋጭ የሆኑ ጉዳዮች ሳይዘገቡ የመታለፋቸው ሁኔታ እጅግ ሰፊ ነው፡፡ ታሪኩ መቀየሩን ከሚያሳዩ ማስረጃዎች መካከል አንዱ በአቡበክር ዘመን ቁርአን በወረቀት ላይ እንደተጻፈ መነገሩ ነው፡፡ ነገር ግን ሐቀኛ በሆኑት የታሪክ መዛግብት መሠረት ሙስሊሞች ፐፓይረስ የተሰኘውን ከደንገል የሚዘጋጅ መጻፍያ መጠቀም የጀመሩት በዑመር ዘመን ግብፅን ከወረሩ በኋላ ነበር፡፡ ወረቀት በሙስሊሞች ጥቅም ላይ የዋለው ደግሞ አቡበክር ካለፉ ከመቶ ሃምሳ ዓመታት በኋላ ሰመርቃንድ በተሰኘ ቦታ ነበር፡፡ በባግዳድ ወረቀትን ማምረት የተጀመረው በስምንተኛው ክፍለ ዘመን መገባደኛ በቻይናውያን እርዳታ ነበር፡፡[2]
  2. ቁርአንን በአንድ ጥራዝ የማሰባሰብ ሂደት ለመጀመርያ ጊዜ በአቡበክር ትዕዛዝ በዘይድ አማካይነት እንደተከናወነ በእስላማዊ ድርሳናት ውስጥ ቢነገርም[3] ይህንን የሚጣረስ ሌላ ዘገባ አለ፡-

“ኢብን ቡራይዳህ እንዳስተላለፉት፤ ለመጀመርያ ጊዜ ቁርአንን በሙሳሂፍ (ጥራዝ) የሰበሰበው የአቡ ሁዛይፋህ ባርያ የነበረውና ነፃ የወጣው ሰሊም ነበር፡፡”[4]

(ሰሊም ቁርአንን እንዲያስተምሩ በነቢዩ መሐመድ ሥልጣን ከተሰጣቸው አራት ሰዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡)[5]

እንግዲህ ሙስሊም ምሑራን ሁለት እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ዘገባዎችን ተጋፍጠዋል፡፡ ከሁለቱ አንዱ የግድ ውሸት መሆን አለበት፡፡ ቁርአንን በአንድ ጥራዝ የሰበሰበው የመጀመርያው ሰው ማነው? የሚለውን ቀላል ጥያቄ ከጥርጣሬ በጸዳ ሁኔታ መመለስ ያልቻሉ ድርሳናት ሌሎች ትርክቶቻቸው አስተማማኝ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

3. በመሐመድ ዘመን በቁርአን ውስጥ የተካተቱ ነገር ግን ዘይድ ያስወገዳቸው ክፍሎች ነበሩ፡፡ እስላማዊ ድርሳናት እንዲህ ሲሉ ይናዘዛሉ፡-

“አብዱላህ ቢን አባስ እንዳስተላለፉት፤ ኡመር ቢን ኸጧብ በአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ምስባክ ላይ ተቀምጠው እንዲህ አሉ፡- ‹‹አላህ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) በእውነት ላካቸው፤ መጽሐፍንም አወረደላቸው፤ በእርሳቸው ላይ በተወረደው ውስጥ በድንጋይ የመውገር አንቀፅ ነበር፡፡ አነብንበነዋል፣ በትውስታችን ውስጥ መዝግበነዋል እንዲሁም ተረድተነዋል፡፡ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በድንጋይ ወግሮ የመግደልን ቅጣት ይተገብሩ ነበር፤ ከእርሳቸው በኋላ እኛም ተመሳሳይ ነገር እንፈፅም ነበር፡፡ በጊዜ ሂደት ሰዎች ‹በአላህ መጽሐፍ ውስጥ የውግረትን ሕግ አላገኘንም› በማለት በአላህ የተደነገገውን ይህንን ድንጋጌ ችላ እንዳይሉ እፈራለሁ፡፡ ዝሙትን የሚፈፅሙ ባለትዳር ወንዶችና ሴቶች በማስረጃ ከተረጋገጠ፣ እርግዝና ከተፈጠረ ወይም ከተናዘዙ እንዲወገሩ በአላህ መጽሐፍ ውስጥ የተቀመጠ ግዴታ ነው፡፡››”[6]

በአንድ ዘገባ መሠረት ዑመር ይህንን አንቀፅ በዘይድ ወደሚመራው ኮሚቴ ባመጣ ጊዜ ዘይድ ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም፤ የሰጠው ምክንያት ደግሞ ከዑመር ውጪ ሌላ ምስክር ስላላገኘ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡[7] ነገር ግን ይህ አንቀፅ የቁርአን አካል እንደነበር የመሐመድ ሚስት አይሻ መመስከሯ ተነግሯል፡፡[8] ዘይድ ቁርአንን ሲሰበስብ በጽሑፍ ሊገኝ ያልቻለው በፍየል ስለተበላ መሆኑም ተዘግቧል፡፡[9]

ይህ አንቀፅ በመሐመድ ዘመን የቁርአን አካል እንደነበር በመናገራቸው ዑመርና አይሻ ቅጥፈት ፈጽመው ይሆን? ከአራቱ ኸሊፋዎች መካከል አንዱና የመሐመድ የቅርብ ወዳጅ የነበረው ዑመር እንዲሁም የነቢዩ ሚስት አይሻ የሰጡት ምስክርነት ካልታመነ የማን ምስክርነት ሊታመን ነው? በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሌሎች ብዙ የቁርአን ክፍሎች አለመካተታቸውን እንዴት እርግጠኛ መሆን ይቻላል?

4. በየማማ በተደረገው ጦርነት ወቅት ከሞቱት ሰዎች ጋር የጠፉ የቁርአን አናቅፅ እንደነበሩ እስላማዊ ትውፊቶች ይመሰክራሉ፡፡ ይህ ማለት ሁሉም የቁርአን ክፍሎች በሁሉም አነብናቢዎች እኩል በሆነ ሁኔታ አልተሸመደዱም ነበር ማለት ነው፡፡ ይህንን የሚያረጋግጡ ድርሳናት እነሆ፡-

ኢብን አቢ ዳውድ የሚከተለውን አስተላልፈዋል፡- “ብዙ የወረዱ የቁርኣን ጥቅሶች በየማማ ጦርነት ላይ በሞቱት ብዙ ሰዎች ይታወቁ ነበር … ከጦርነቱ በተረፉት ሰዎች ግን አይታወቁም ነበር እንዲሁም በጽሑፍ አልሠፈሩም ነበር፡፡ ቁርኣን ሲሰበሰብ አቡበክር፣ ዑመርም ሆነ ኡሥማን አያውቋቸውም ነበር፡፡ ከእነርሱ በኋላ በነበረ አንድም ሰው ጋ ማግኘት አልተቻለም፡፡”[10]

አል-ሱዩጢ፣ ኢትቃን በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ ተከታዩን ማስጠንቀቅያ አስፍረዋል፡- “ከእናንተ መካከል ማንም ሰው ሙሉውን ቁርኣን አግኝቼዋለሁ ብሎ መናገር የለበትም፡፡ የቁርኣን አብዛኛው ክፍል የጠፋ ሆኖ ሳለ ሁሉን አውቃለሁ ብሎ መናገር እንዴት ይቻላል? ከዚህ ይልቅ የተረፈውን አግኝቼዋለሁ ብሎ ይናገር፡፡”[11]

በዚህ ሁሉ ችግሮችና ውዝግቦች የታጀበው የአቡበክር ቁርአንን የማሰባሰብ ሂደት ተዓማኒነት ሊኖረው የሚችለው በምን መስፈርት ነው? 


[1] Al Suyuti. Al Itqan fi `ulum al Qur’an; p. 378; Cited in: The Qur’an Dilemma; Former Muslims Analyze Islams Holiest Book. 2001, Vol. 1, p. 49

[2] The Qur’an Dilemma. Vol. 1, p. 51

[3] Ibn Abi Dawud, Kitab al-Masahif, p. 5

[4] Al Suyuti. Al-Itqan; p. 135

[5] Sahih al-Bukhari, Volume 6, Book 61, Number 521

[6] Sahih Muslim, 17:4194

[7] Al Suyuti. Al Itqan;  p. 385;፤ Cited in: The Qur’an Dilemma; Vol. 1, p. 52

[8] Sahih Muslim, book 8, no. 3421

[9] Sunan Ibn Majah; 3፡9፡1944

[10] Al Suyuti. Al- Itqan fi `ulum al Qur’an; part 2, p. 25; Cited in Ibn Warraq. Which Koran?: Variants, Manuscripts, Linguistics; Prometheus Books, 2011, p. 24

[11] Al Suyuti. A- Itqan fi `ulum al Qur’an; part 2, p. 25; Cited in: Ibn Warraq. Which Koran?; p. 24


በኡስታዝ ሐሰን ታጁ ለተጻፈ መጽሐፍ የተሰጠ መልስ

ቅዱስ ቁርአን