አስገራሚዎቹ የአላህ መሐላዎች

አስገራሚዎቹ የአላህ መሐላዎች

ሰዎች የሚምሉት የተናገሩት ቃል እውነት መሆኑን ወይንም የገቡት ቃል እንደማይለወጥ ማረጋገጫ ለመስጠት ነው፡፡ ስለዚህ በመሐላቸው የሚጠሩት ማንኛውም ነገር ወይንም አካል ከቃላቸው የሚበልጥ ዋጋ ሊኖረው ይገባዋል፡፡ በመሐላ የምንጠራው ስም ከፍ ባለ ቁጥር የቃላችንም ክብደት በዚያው መጠን ይጨምራል፡፡ ሰዎች ሊምሉበት የሚችሉት የመጨረሻው ትልቅ ስም የፈጣሪያቸው ስም ነው፡፡ ይህ መሐላ እጅግ ከባዱ ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ከእርሱ የሚበልጥ ምንም ነገር ባለመኖሩ ሲምል በራሱ ይምላል እንጂ በፍጡራን አይምልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡-

“ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፥ አትመለስም፦ ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፥ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ።” (ኢሳ. 45፡23)

“እናንተ በግብጽ ምድር የምትኖሩ ይሁዳ ሁሉ፥ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ በግብጽ ምድር ሁሉ በሚኖር በይሁዳ ሰው ሁሉ አፍ ስሜ ከእንግዲህ ወዲህ፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ተብሎ እንዳይጠራ፥ እነሆ፥ በታላቅ ስሜ ምያለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡” (ኤር. 44፡26)

“እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ። በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ እያበዛሁም አበዛሃለሁ ብሎ፥ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ፥ በራሱ ማለ፡፡” (ዕብ 6፡13-14)

እግዚአብሔር አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በገዛ ራሱ ስምና ክብር እንጂ በሌላ ፍጥረት ሲምል አይታይም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ከመሐላ ትርጉም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህም ቀደም ሲል እንደገልጽነው መሐላ ቃላችን የማይለወጥ መሆኑን ማረጋገጫ ለመስጠት ከቃላችን የሚበልጥ ስም የምንጠራበት የመጨረሻው ንግግር በመሆኑ ነው፡፡

“ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጠው ይምላሉና፥ ለማስረዳትም የሆነው መሐላ የሙግት ሁሉ ፍጻሜ ይሆናል” (ዕብ. 6፡16)፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በፍጡራን የሚምል ከሆነ የቃሉን ክብር ወደ ፍጡራን ደረጃ አውርዶታል ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ከክብሩና ከግርማ ሞገሱ ጋር የማይሄድ በመሆኑ እግዚአብሔር አምላክ በፍጡራን አይምልም፡፡

የእስልምና ሃይማኖት መመርያ የሆነው ቁርኣን ግን ከቃሉ ክብደትና ከግርማው ጋር በማይመጣጠን ሁኔታ አላህ በፍጥረታት መማሉን ይነግረናል፡፡ አላህ ከማለባቸው ፍጥረታት መካከል የሚበዙቱ እንኳንስ ለፈጣሪ ይቅርና ለሰው ልጆች እንኳ የማይመጥኑ ለመሐላ ቃል የማይበቁ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በቁርኣን ከተጠቀሱት የአላህ መሐላዎች መካከል የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፡-

በሙሐመድ ዕድሜ፡- 15:72 “በዕድሜህ እንምላለን”

በብዕር፡- 68:1 “በብርዕ እምላለሁ በዚያም መልአኮች በሚጽፉት”

በመካ ከተማ፡- 90:1 “በዚህ አገር በመካ እምላለሁ”

በፈረሶች፡- 100:1 “እያለከለኩ ሩዋጮች በኾኑት ፈረሶች እምላለሁ”

በወጋገን፡- 84:16 “በውጋገኑ እምላለሁ”

በፕላኔቶች፡- 81:15 “ተመላሾችም በሆኑት ዐዋድያት እምላለሁ”

በረፋድ፡- 93:1 “በረፋዱ እምላለሁ”

በሌሊት፡- 92:1 “በሌሊቱ እምላለሁ በጨለማው በሚሸፍን ጊዜ”

በፀሐይ 91:1 “በፀሐይና በብርሃኗ እምላለሁ”

በጎህ፡- 89:1 “በጎህ እምላለሁ”

በሌሊት ሰማይ፡- 86:1 “በሰማዩ፣ በሌሊት መጪውም እምላለሁ”

በከዋክብት መጥለቂያዎች፡- 56:75 “በክዋክብትም መጥለቂያዎች እምላለሁ”

በሰማይ፡- 86:11 “የመመለስ ባለቤት ብሆነችው ሰማይም እምላለሁ”፤ 85:1 “የቡርጆች ባለቤት በሆነችው ሰማይ እምላለሁ”፤ 51:7 “የከዋክብት መንገዶች ባለቤት በሆነችው ሰማይ እምላለሁ”

በኮከብ፡- 53:1 “በኮከብ እምላለሁ በገባ ጊዜ”

በጨረቃ፡- 74:32 “ከክሕደት ይከልከሉ፤ በጨረቃ እምላለሁ”

በጡር ጋራ፡- 52:1 “በጡር ጋራ እምላለሁ”

በበለስና በዋይራ፡- 95:1 “በበለስና በዘይት ወይራ፣ እምላለሁ”

በሰው ነፍስ፡- 75:2 “ራሷን ወቃሽ በሆነች ነፍስም እምላለሁ”

በዕለተ ትንሣኤ፡- 75:1 “አይደለም፤ በትንሣኤ ቀን እምላለሁ”

በጊዜያት፡- 103:1 “በጊዜያቱ እምላለሁ”

በመላእክት፡- 77:6 “ምክንያትን ለማስወገድ፣ ወይም ለማስፈራራት፣ ጣይዎች በሆኑት መላእክት እምላለሁ”፤ 79:5 ነገርንም አስተናባሪዎች በሆኑት መላእክት እምላለሁ”

በቁርኣን፡- 50:1 “በተከበረው ቁርኣን እምላለሁ”፤ 38:1 “የክብር ባለቤት በሆነው ቁርኣን እምላለሁ”

በራሱ፡- 15:92 “በጌታህም እንምላለን”፤ 92:3 “ወንድና ሴትን በፈጠረውም አምላክ እምላለሁ”፤ 16:63 “በአላህ እንምላለን”

አላህ በነዚህ ሁሉ ነገሮች ከማለ በኋላ አንድም ነገር እንዳይቀረው የፈለገ ይመስል በሚታዩትና በማይታዩት ነገሮች ሁሉ ሲምል ይገኛል፡- 69:38-39 “በምታዩትም ነገር እምላለው። በማታዩትም ነገር።”

የቁርአኑ አላህ ሲምል አይመርጥም፡፡ የራሱን ስም ጨምሮ ለመሐላ የማይገለገልበት ስም የለም፡፡ በሰማይና በምድር ውስጥ የሚገኝ ሰዎች ሊያዩት የሚችሉትም ሆነ የማይችሉት የትኛውም ፍጥረት አይቀረውም፡፡ እንዲህ ያለ መሐላ ለፈጣሪ ቃል ክብር የማይሰጥ፣ ቃል ተቀባዩን የማያስተማምንና የመሐላን ትክክለኛ ትርጉም የሳተ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

ይህ የቁርአኑ አላህ መሐላ ከእስላማዊ የተውሒድ አስተምሕሮ ጋር ይጋጫል፡፡ በእስላማዊ የተውሒድ አስተምሕሮ መሠረት በአላህ ስም ካልሆነ በስተቀር በሌላ ፍጥረት ስም መማል ይቅርታ የሌለው የሺርክ ኃጢአት ነው፡-

ዑመር እንዳወራው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- “አንድ ሰው የሚምል ከሆነ በአላህ ስም ብቻ ይማል፡፡” ቁረይሾች በአባቶቻቸው ይምሉ ነበር ነገር ግን ነቢዩ “በአባቶቻችሁ አትማሉ” ብለዋል፡፡ (Sahih Al-Bukhari, Volume 5, Book 58, Number 177)

ለምንድነው ይህ የተባለው? በሙሐመድ እምነት መሠረት ለመሐላ ብቁ የሆነው የአላህ ስም ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን የሰው ልጆች በአላህ ስም ብቻ በመማል ክብርን እንዲሰጡትና በሌላ ቢምሉ ከኃጢአት እንደሚቆጠርባቸው የደነገገው ሙሐመድ በቁርኣን ውስጥ አላህ ከግዑዛን ፍጥረታት ጀምሮ በሚታዩትና በማይታዩት ፍጥረታት ሁሉ እንደማለ በመግለፅ ይህንን መርህ እንደጣሰ ይነግረናል፡፡ ምናልባት ሙስሊም ሰባኪያን ይህ መርህ ለሰው እንጂ ለአምላክ እንደማይሠራ ይነግሩን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለመሐላ ብቁ የሆነው የአምላክ ስም ብቻ ከሆነ አላህ ከራሱ ውጪ ባሉት ፍጡራን ሲምል ፍጡራን ለመሐላ ብቁ የሚሆኑበት አመክንዮ የለም፡፡ ሰዎች በስሙ ብቻ ምለው ለቃላቸው ክብደት እንዲሰጡ ያዘዘው አምላክ መልሶ ደግሞ በፍጡራን በመማል ቃሉን አያቃልልም፡፡

አንዳንድ ሙስሊም ሰባኪያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በመጥቀስ እግዚአብሔር አምላክ በፍጡራን እንደማለ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ የሚጠቅሱት ጥቅስ እንደሚከተለው ይነበባል፡-

“እግዚአብሔር በያዕቆብ ክብር እንዲህ ብሎ ምሎአል፦ ሥራቸውን ሁሉ ለዘላለም ምንም አልረሳም።” (አሞፅ 8፡7)

“The Lord hath sworn by the excellency of Jacob, Surely I will never fnetet any of their works.” (KJV)

በዚህ ስፍራ “ክብር” ተብሎ የተጠቀሰው ቃል የእብራይስጥ አቻ “ገዖን” የሚል ሲሆን “ክብር፣ ግርማ፣ ሞገስ፣ ትምክህት፣ ትዕቢት፣ ኩራት” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ ይህ ቃል የእግዚአብሔርን ክብር ለማመልከት በተደጋጋሚ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅም ላይ ውሏል (ዘጸ. 15፡7፣ ኢዮብ 37፡4፣ ኢሳ. 2፡10፣ 2፡19፣ 2፡21፣ 24፡14፣ ሚክ. 5፡4)፡፡ ከዚህም በመነሳት በዚህ ቦታ የያዕቆብ ክብር፣ ግርማ፣ ሞገስ፣ ኩራት፣ የተባለው ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት በአንድ ድምፅ የሚስማሙበት እውነታ ነው፡፡

“The Lord hath sworn by the excellency of Jacob — That is, by himself” (Benson Commentary)

“By the excellency of Jacob – that is, by Himself who was its Glory, as Samuel calls Him “the Strength” 1 Samuel 15:29 or the Glory of Israel. Amos had before said, “God sware by His Holiness” and “by Himself” or “His soul.” (Barnes’ Notes on the Bible)

“Lord hath sworn by the excellency of Jacob—that is, by Himself, in whom Jacob’s seed glory [Maurer]. Rather, by the spiritual privileges of Israel, the adoption as His peculiar people [Calvin], the temple, and its Shekinah symbol of His presence. Compare Am 6:8, where it means Jehovah’s temple (compare Am 4:2).” (Jamieson-Fausset-Brown Bible Commentary)

“By the excellency of Jacob; by himself, for God cannot swear by any greater, and he is called the excellency of Jacob, Psalm 47:4.” (Matthew Poole’s Commentary)

“The Lord hath sworn by the excellency of Jacob,… Not by the ark, as R. Japhet; nor by the temple, as Kimchi; but by himself; which sense Kimchi also mentions, and Aben Ezra; the God of Jacob and his glory, the most excellent of all Jacob’s enjoyments, and of whom he had reason to boast and glory; see Amos 6:8.” (Gill’s Exposition of the Entire Bible)

“The pride of Jacob may be Jehovah Himself (cf. 1 Samuel 15:29)” (Cambridge Bible for Schools and Colleges)

“The Excellency of Jacob. This is a title of God himself, as in Hosea 5:5Hosea 7:10, where it is rendered “pride.” Thus the Lord is said to swear by his holiness (Amos 4:2), by his soul (Amos 6:8; comp. 1 Samuel 15:29). So here he swears by himself, who is the Glory and Pride of Israel; as truly as he is this, he will punish.” (Pulpit Commentary)

ስለዚህ ይህ ጥቅስ እግዚአብሔር በፍጡራን ስለመማሉ ማሳያ ሊሆን አይችልም፡፡

አንዳንድ ሙስሊም ሰባኪያን ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ በራሱ ስለማለ አላህ በፍጡራን ቢምል ምን ችግር አለው? የሚል አስቂኝ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ የሚጠቅሷቸው ጥቅሶች የሚከተሉት ናቸው፡-

“በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለኝ በእናንተ ትምክህት እየማልሁ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕለት ዕለት እሞታለሁ።” (1ቆሮንቶስ 15፡31)

“እናንተ ደግሞ ትምክህታችን እንደምትሆኑ እንዲሁ ትምክህታችሁ እንድንሆን፥ በከፊል ስለ እኛ እንዳስተዋላችሁ ፈጽማችሁ ታስተውሉት ዘንድ ተስፋ አደርጋለሁ። (2ቆሮንቶስ 1፡14)

ሁለቱን ጥቅሶች በማገጣጠም “ጳውሎስ ‹ትምክህታችሁ እኛ ነን› ብሎ ተመልሶ ‹በእናንተ ትምክህት እየማልሁ› በማለት በራሱ ምሏል” ይላሉ፡፡ ይህ በሦስት ምክንያቶች ስህተት ነው፡፡ አንደኛ ጳውሎስ ፍጡር በሆነው በራሱ ማንነት ስለማለ አላህ በፍጡራን ቢምል ችግር የለውም የሚለው አመክንዮ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሁለተኛ ጳውሎስ በራሱ ምሎ ከሆነ ለገዛ ንግግሩ የሰጠውን ዋጋ የሚያሳይ ነው፡፡ ቢያንስ ከራሱ ባነሰ ነገር አልማለም፡፡ አላህ ቃሉ ከፍጡራን በላይ እንደሆነ የሚገነዘብ ከሆነ በፍጡራን መማል የለበትም ምክንያቱም ቃሉ ከፍጡራን በላይ ነውና፡፡ ሦስተኛ በትርጉም ችግር ምክንያት እንጂ 1ቆሮንቶስ 15፡31 ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አልማለም፡፡ በቦታው የተጠቀሰው የግሪክ ቃል “ኔ” የሚል ሲሆን “ማረጋገጥ” ተብሎ ቢተረጎም ይበልጥ ትክክል ይሆናል፡፡ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “አረጋግጣለሁ” በማለት ተርጉሞታል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለት ተዕለት መግባቢያችን ውስጥ ቃላችን “አዎን” እና “አይደለም” እንዲሆን እንጂ መሐላ አስፈላጊ አለመሆኑን አስተምሯል፡-

“ደግሞ ለቀደሙት፦ በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፥ አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው።” (ማቴ. 5፡33-36)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ፍጥረትና ግዛት ውስጥ ባለ በማንኛውም ነገር መማል ትክክል አለመሆኑን አስተምሯል፡፡ ይህ ማለት ግን በምንም ሁኔታ መማል አይቻል ማለት አይደለም፡፡ እርሱ ራሱ ሊቀ ካህኑ በመሐላ በጠየቀው ጊዜ መሐላውን በማክበር ምላሽ ሰጥቷል (ማቴ. 26፡63-64)፡፡ ቅዱሳንም የጌታን ስም ጠርተው ሲምሉ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ታይተዋል (ሐዋ. 21፡23-26፣ ሮሜ 9፡1፣ ገላ. 1፡20፣ ራዕይ 10፡5-6)፡፡

መሐላ በክርስትና እጅግ ጥብቅ ጉዳይ ነው፡፡ በሁሉም አጋጣሚ የእግዚአብሔርን ስም በመጥራት ማቃለል በአሥርቱ ትዕዛዛት ከተከለከሉት ተግባራት መካከል አንዱ ነው፡-

“የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና” (ዘጸአት 20፡7)፡፡

እስልምና በመሐላ ላይ ያለው አቋም በእጅጉ የላላ ነው፡፡ ሙስሊሞች የአምላካቸውን ስም ጠርተው መተማመን እንኳ እስከማይችሉ ድረስ “ወላሂ (በአላህ እምላለሁ)” እያሉ በእንቶ ፈንቶ ጉዳዮች መማል የባሕላቸው አካል ነው፡፡ ከአንድ ደካማ ክርስቲያን ይልቅ አንድ ጠንካራ የሚባል ሙስሊም በሆነው ባልሆነው በአምላኩ ስም እየማለ የአምላኩን ስም ሲያቃልል ይውላል፡፡ ሙሐመድ በብዙ ሐዲሳት ውስጥ መሐላ በማያስፈልግባቸው ጉዳዮች በመማል መጥፎ ምሳሌ ሆኗቸዋል፡፡ አምላካቸው አላህም ግርማ ሞገሱን በማይመጥኑ በግዑዛንና በጥቃቅን ፍጥረታት በመማል ቃሉን አቃሏል፡፡ አላህ የተባለው ይህ የሙሐመድ አምላክ በራሱ ብቻ ከሚምለው የነቢያት አምላክ ከያሕዌ እግዚአብሔር ምንኛ የተለየ ነው!

 

ቅዱስ ቁርኣን