መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ! ለአቡ ሀይደር የተሰጠ መልስ

መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ!

ለአቡ ሀይደር የተሰጠ መልስ

ኡስታዝ አቡ ሀይደር እንደተለመደው የእስልምናን የክፍለ ዘመናት ሽንቁር ለመድፈን ጥረት አድርጓል፡፡ ሙሐመድ “የሚወርድለትን” መገለጥ የሚጠራጠር ከሆነ ከእርሱ በፊት ቅዱሱን መጽሐፍ የሚያነቡትን ወገኖች ሄዶ እንዲጠይቅ የተነገረው ቃል ትርጉሙ ክርስቲያኖች እንደሚያስቡት አይደለም የሚል ሙግት አቅርቧል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ይህንን ሙግት እንፈትሻለን፡፡ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡፡

አቡ ሀይደር

መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ!!

“ወደ አንተም ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን እነዚያን ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ፡፡ እውነቱ ከጌታህ ዘንድ በእርግጥ መጥቶልሃል፡፡ ከተጠራጣሪዎቹም አትሁን፡፡” (ሱረቱ ዩኑስ 1094)

የዚህን አንቀጽ መልእክት በአግባቡ ለመረዳት ወገኖቻችን አልታደሉም፡፡ በተሳሳተ መንገድ ተረድተው መልክቱን ለነሱ ሊያደርጓትም ቋመጡ፡፡ በድፍረትም እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፡

በዚህ አንቀጽ መሠረት ቅዱስ ቁርኣን ለሙስሊሞች፡ በእምነታቸው ጥርጥር ከገባባቸው መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ዘንድ ሄደው በመጠየቅ እውነቱን መረዳት እንደሚችሉ መጠቆሙን እንረዳለን!!፡፡

ውይ ስታሳዝኑ…. እኔ የምለው፡እንደው ትክክለኛ ትርጉሙንና መልእክቱን ከማየታችን በፊት፡ እናንተ እንዳላችሁት ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ›› አንባቢዎችን እንድንጠይቅ ከሆነ ቁርኣኑ የሚገፋፋን፡ ለምን ከናንተ በፊት የነበሩትን አይሁዶቹን አንጠይቅም? ለምን ወደናንተ መምጣት አስፈለገ? ወይስ ቅድሚያ ወደናንተ እንድንመጣ ፈልጋችሁ ነውን?

ደግሞስ እናንተን ነው ቢባል እንኳ ማንን ነው የምንጠይቀው? ካቶሊክን? ኦርቶዶክስን? ፕሮቴስታንትን? ኢየሱስ ብቻ (only jesus) የሚሉትን? የይሆዋ ምስክሮችን (Jihovah witness)?…..? እኮ ማንን? እንጠይቃችሁ ዘንድ ንገሩና! በስም ከፋፍለን የጠራናችሁ በመሐከላችሁ የእምነት ልዩነት መኖሩ የታወቀ ስለሆነ ነው፡፡ ደግሞስ በየትኛው ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ›› መሰረት ላይ ሆናችሁ ነው የምትጠየቁት? 66 ወይስ 73? ወይንስ 81? ደግሞስ የየትኛው ዓመት እትም? ምረጡልና!!

መልስ

የሙስሊም ሰባኪያን አስተሳሰብ በጣም ደካማ ስለመሆኑ ከላይ የተጻፈው ሐሳብ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ለነዚህ ሁሉ ችግሮች ምላሽ መስጠት ያለበት እስልምና እኮ ነው! መጽሐፉን የሚያነቡትን ወገኖች እንድትጠይቅ ያዘዘው ማን ነው? አላህ አይደለምን? ማንን መጠየቅና የትኛውን መጽሐፍ እንደሆነ ለይቶ ሊነግርህ የሚገባው “ጠይቅ” ያለህ አላህ እንጂ እኛ አይደለንም፡፡ ስለዚህ ከላይ የዘረዘርካቸው ክፍፍሎችና የቀኖና ልዩነቶች እንደ ችግር የሚወሱ ከሆነ እነዚህ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ “ሒድና ጠይቅ” ያለው አላህ ኃላፊነቱን ይወስዳል፡፡ ስለዚህ አላህ “ጠይቅ” ያለው ክርስቲያኖችን ወይስ አይሁድን? የትኛውን የክርስትና ቤተ እምነት፣ የትኛውንስ ቀኖና ነው? ምላሹን አላህን ጠይቀው፡፡

አላህ “ጠይቅ” ብሎ ያዘዘው አይሁድን ቢሆን ወይም ክርስቲያንን፣ አንዱንም ሆነ ሁሉንም የክርስትና ቅርንጫፎች፣ ባለ 66ቱም ሆነ ሌሎች ቀኖናዎች፣ አንድ ነገር በጣም ግልፅ ነው፤ በሁሉም መንገድ እስልምና ውድቅ ነው! ይሁዲም ሆነ የትኛውም የክርስትና ቅርንጫፍ እስልምናን አያጸድቅም፡፡ የትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና የሙሐመድን አስተምሕሮ አይደግፍም፡፡ ደግሞም እስልምና የክፍፍልና የቀኖና ችግር የሌለበት ይመስል ጉዳዩን ማጋነንህ በጣም ይገርማል፡፡ ለመሆኑ በእስልምና ስንት ቤተ እምነት ነው ያለው? ስንት ዓይነት ቁርኣንና የቁርኣን አተረጓጎም ነው ያለው? አንድ ሰው እስልምናን መቀበል ቢፈልግ በካፊርነት ከሚፈራረጁትና እርስ በርስ እየተገዳደሉ ከሚኖሩት የእስልምና ቅርንጫፎች መካከል የቱን ቢመርጥ ነው ጀነት የሚገባው?

ክርስቲያኖች የተለያዩ ቀኖናዎች እንዳሏቸውና ቤተክርስቲያንም የተወሰኑ የአፖክሪፋ መጻሕፍትን ከአዲስ ኪዳን ማግለሏ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን የቀደሙት ሙስሊሞችም ተመሳሳይ ችግር እንዳጋጠማቸውና ተመሳሳይ ተግባር መፈፀማቸውም እውነት ነው፡፡ በመጀመርያዎቹ የእስልምና ዘመናት የተለያዩ የቁርኣን ቀኖናዎች ነበሩ፡፡ የኡበይ ቢን ከዕብ ቁርኣን 116፣ የአብደላህ ኢብን መስዑድ 111፣ የኡሥማን 114 ሱራዎች ነበሯቸው፡፡ ልዩነቱ ኡሥማን አንዱን ቀኖና ብቻ መርጦ ሌሎቹን ሕገ ወጥ ማድረጉና ክርስቲያኖች ግን ያንን ማድረግ አለመቻላቸው ነው፡፡ በዚህ ዘመን እንኳ ሐፍስ፣ ዋርሽ፣ አል ዱሪ፣ ቃሉን፣ ወዘተ. የተሰኙ ብዙ ልዩነቶችን የሚያሳዩ ከ 24 ያልተናነሱ የአረብኛ የቁርኣን ንባቦች ይገኛሉ፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሚጠቀሙት የሐፍስ ቁርኣን በ1924 የግብፅ ካይሮ ኦፊሴላዊ ቁርኣን ተደርጎ የታወጀ ሲሆን ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን የተደረገው በ1985 ዓ.ም. በሳዑዲው ንጉሥ ፈሐድ አማካይነት ነበር፡፡ በወቅቱም አንድ ዓይነት ሳይሆን ወደ አምስት ዓይነት የሚሆኑ የሐፍስ ቁርአኖች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ለማወቅ እዚህ ጋ እና እዚህ ጋ ጠቅ ያድርጉ፡፡

በተጨማሪም የሙስሊሞች የቀኖና ችግር በቁርኣን ብቻ የተገደበ ሳይሆን ሐዲስንም ይጨምራል፡፡ የሐዲስ መጻሕፍት ሃይማኖታዊና ሌሎች ጉዳዮችን ለመወሰን የሚያስችሉ የሙሐመድ ታሪኮች ሲሆኑ በእስልምና በጣም ወሳኝ ናቸው፡፡ የሐዲስ መጻሕፍት የእስልምና ቀኖና አካል ናቸው፡፡ ሆኖም የትኛው ሐዲስ መካተት እንዳለበት በሙስሊሞች መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ትልቅ አለመግባባት አለ፡፡ ሱኒና ሺኣ የተለያዩ ሐዲሳት ያሏቸው ሲሆን ጭራሹኑ ሐዲስን የማይቀበሉ ሙስሊሞችም አሉ፡፡ ስለዚህ የእስልምና ቀኖና እስከ ዛሬ ድረስ ያልተዘጋና ተለዋዋጭ ነው፡፡ ሙስሊሞች በራሳቸው ቀኖና እስከ ዛሬ ስላልተስማሙ ነገሮችን ማጋነን ማቆም ያስፈልጋቸዋል፡፡

አቡ ሀይደር

ወደ ሐቁ ስንመጣ ግን የቅዱስ ቁርኣኑ መልእክት በፍጹም ይህን አያረጋግጥም፡፡ እነሱ የተረዱትን ሀሳብ የሚገልጽ ነገር በቅርቡም ሆነ በሩቁ በቃሉ ውስጥ አይገኝም፡፡ እንዴት? የሚሉ ከሆነና፡ ቀጥተኛ ትርጉሙን መረዳት የሚሹ ከሆነ ማብራሪያውን ከልብ ይከታተሉ፡፡ እውነቱንም ለመረዳት አላህ ያግዘን፡፡ ልባችንንም ያስፋልን፡፡

1. ጥቅላዊ ማብራሪያ፡

የአንቀጹ መልእክት፡የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነቢይነትና ወደሳቸው የሚወርድላቸው መለኮታዊ ራእይ (ቅዱስ ቁርኣን) ከአላህ ዘንድ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የሌለበት መሆኑን እና በዚህ ጉዳይም ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንደማይጠራጠሩና፡ ‹‹ቢጠራጠሩ እንኳ›› ከሳቸው በፊት የነበሩትን የቀደምት መለኮታዊ መጽሐፍት ሊቃውንቶችን በመጠየቅ እውነተኝነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚችሉ ነው፡፡ ምክንያቱም፡የሳቸው ነቢይነትም ሆነ፡ የቅዱስ ቁርኣን አምላካዊ ቃልነት በመጽሐፎቹ ኦርጂናል ቅጂ ላይ እንደተጠቀሰ ሊቃውንቶቹ ያውቃሉና!!፡፡

ስለዚህም ‹‹እውነቱ ከጌታህ ዘንድ በርግጥ መጥቶልሀል፡፡ በመሆኑም ከተጠራጣሪዎች አትሁን!›› በማለት፡ እቅጩን በመንገር ጉዳዩን ይደመድመዋል፡፡

አለቀ ደቀቀ፡፡ እውነቱ ያለው እዚሁ ነው፡፡ እዛ እውነት አለና ሂደህ ጠይቅ! የሚል ቃልም ሆነ ፊደል ማግኘት አይቻልም፡፡ ሊቃውንቶቹን ጠይቅ! የተባለው፡ እነሱን እንኳ ብትጠይቃቸው አንተን በሚገባ ያውቁሀል፡፡ ነቢይነትህንም ሆነ የሚወርድልህ ራእይ ከአላህ ዘንድ መሆኑን ይመሰክራሉ ነው፡፡ ይኸው የጌታ አላህ ምስክርነት፡

እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ወንዶች ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (ሙሐመድን) ያውቁታል፡፡ ከነሱም የተለዩ ክፍሎች እነርሱ የሚያወቁ ሲኾኑ እውነቱን በእርግጥ ይደብቃሉ፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2146)፡፡

“እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (ሙሐመድን) ያውቁታል፡፡ እነዚያ ከእነርሱ ውስጥ ነፍሶቻቸውን ያከሰሩት እነርሱ አያምኑም፡፡” (ሱረቱል አንዓም 620)፡፡

ይህ ነው እውነታው! ከዛ ውጪማ እውነቱን ለማወቅ ከፈለግህ፡ እነሱን ሄደህ ጠይቅ ለማለት ከሆነ፡ በዚያው አንቀጽ ውስጥ ‹‹እውነቱ ከጌታህ ዘንድ በእርግጥ መጥቶልሃል›› በማለት አስረግጦ መናገር ለምን አስፈለገው?

የቃሉ መልእክት ግን፡እነዚያን ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ብትጠይቃቸው የአንተን ነቢይነትም ሆነ የሚወርድልህን ራእይ (ቅዱስ ቁርኣን) ከአላህ ዘንድ የመጣ መሆኑን ይናገራሉ ነው፡፡ ደግሞም ሊቃውንቶቹ ለሐቅ ያደሩ፡ እውነቱ ሲነገራቸው አምነው የተቀበሉ፡ እንደ ዐብዱላህ ኢብኑ ሰላም (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደ ዐብዱላህ ኢብኑዐምር ኢብኑልዓስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) አይነቶቹን እንጂ፡ ለምድራዊ ጥቅማቸው ሲሉ እውነቱን በሀሰት የለወጡ፡ የመጽሐፉን ትክክለኛ መልእክት የደበቁና፡ በመጽሐፉ ላይ እጃቸውን ያስገቡትን አይደለም፡፡ እነዚህን ክፍሎችማ ሄዶ መጠየቅ ለጥመት እንጂ ለምሪት እንደማይጠቅም በሌላ አንቀጽ እንዲህ ይገልጸዋል፡

“ከመጽሐፉ ባለቤቶች የሆኑ ጭፍሮች ነፍሶቻቸዉን እንጂ የማያሳስቱ ሲሆኑ ሊያሳስቱዋችሁ ተመኙ ግን አያውቁም” (ሱረቱ አሊዒምራን 369)፡፡

መልስ

ከላይ የሚገኘው ሐተታ የሙሐመድ መገለጥ በትክክል ከሰማይ የመጣ ነው በሚል ተቀባይነት በሌለው ቅድመ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የኡስታዙ ማብራርያ ሲጠቃለል ሦስት ነጥቦችን የያዘ ነው፡፡ የመጀመርያው ጠይቅ የተባለው ሙሐመድ ነው የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው እንዲጠይቅ የተነገረው ስለተጠራጠረ ሳይሆን ቢጠራጠር በሚል ሐሳብ ነው፤ ሙሐመድ መገለጡን አይጠራጠርም፡፡ ሦስተኛ እንዲጠይቅ የተነገረው የእርሱ ስም በኦሪጅናል መጽሐፍት ላይ እንደሚገኝ የሚያውቁትን ሊቃውንት ነው፡፡ አንድ በአንድ እንያቸው፡፡

የመጀመርያው ነጥብ አያከራክረንም፡፡ “ጠይቅ” የተባለው ሙሐመድ ቢሆን ወይም አጠቃላዩ ሕዝበ ሙስሊም የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ነቢይ የተባለው ሙሐመድ መጠየቅ ካስፈለገው የእርሱ ተከታዮች ከእርሱ ስለማይበልጡ ፍለጋውን ተከትለው መጠየቅ ግድ ይላቸዋል፡፡ ነገር ግን የቁርኣን ተፍሲሮችን ስንመለከት በሙሐመድ ተመስሎ የተነገረው መልእክት ሕዝበ ሙስሊሙን የተመለከተ ነው፡፡ የኢብን አባስ ተፍሲር እንዲህ ይላል፡-

The Prophet (pbuh) did not ask nor was he ever in doubt about the Qur’an. Rather, Allah was addressing with these words the people of the Prophet.

“ነቢዩ ጠይቀው አያውቁም፤ ቁርኣንንም ተጠራጥረው አያውቁም፡፡ ይልቁኑ አላህ በነዚህ ቃላት እየተናገረ ያለው የነቢዩን ሕዝብ ነው፡፡” ምንጭ

ከአፍታ በኋላ እንደምንመለከተው በዚህ ተፍሲር ውስጥ ሙሐመድ ጠይቆ እንደማያውቅና ቁርኣንን ተጠራጥሮ እንደማያውቅ የተነገረው ሐሰት ቢሆንም ትዕዛዙ ሕዝበ ሙስሊሙን የተመለከተ እንደሆነ መገለጹ የኡስታዙን አቋም ውድቅ ያደርጋል፡፡

“እንዲጠይቅ የተነገረው የሙሐመድ ስም በኦሪጅናል ጽሑፎች ውስጥ እንደሚገኝ የሚያውቁትን ሊቃውንት ነው” የሚለው አባባል ትርጉም አልባ ነው፡፡ ሙሐመድ ስሙ ተጠቅሶ የሚገኘው በዘመኑ በነበሩት አይሁድና ክርስቲያኖች እጅ በሚገኙት መጻሕፍት ውስጥ የነበረ መሆኑን ያምን የነበረ ሲሆን “ኦሪጅናሉ ውስጥ ነበር አሁን ግን ጠፍቷል” የሚለው አመለካከት የዘመንኛ ሙስሊሞች እንጂ የሙሐመድ አይደለም፡፡ በእጃቸው የነበረው መጽሐፍ ደግሞ የኦሪጅናሉ ቅጂ እንጂ ኦሪጅናሉ አይደለም፡፡ በሰባተኛው ክፍለ ዘመንም የነበሩትም ሆነ በዚህ ዘመን በእጃችን የሚገኙት መጻሕፍት በመጀመርያዎቹ ጸሐፍት ብዕርና ብራና በእጃቸው የተጻፉ ሳይሆኑ እነርሱ ከጻፏቸው ላይ እየተገለበጡ እዚህ የደረሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ በሙሐመድ ዘመን የነበሩት ወገኖች በሙሴና በሌሎች ነቢያትና ሐዋርያት እጅ የተጻፉት እነዚያው መጻሕፍት በእጃቸው ላይ የነበሩ ይመስል “የሙሐመድ ስም በኦሪጅናል ጽሑፎች ውስጥ እንደሚገኝ…” ብሎ ማለት ዕውቀት አጠርነት ነው፡፡ ሙሐመድ በዘመኑ በአይሁድና ክርስቲያኖች እጅ ስለነበሩት መጻሕፍት እንጂ ስለ በኩረ ጽሑፎች እየተናገረ አልነበረም፡፡ ሌሎች ነጥቦቹ በማስከተል ስለተደገሙ የምንመለከታቸው ይሆናል፡፡

አቡ ሀይደር

2. ዝርዝር ማብራሪያ፡

መልእክቱ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንና፡ በአንቀጹ ላይም ሊተላለፍ የተፈለገው መልእክት፡ ወገኖቻችን ካሰቡትና ከቋመጡለት ነገር ጋር ምንም ግኑኝነት እንደሌለው ለማወቅ ይረዳ ዘንድ፡ በኃይለ ቃል እየከፈልን እንመልከተው፡፡

1. ‹‹ወደ አንተም ካወረድነው›› በሚለው ኃይለ ቃል ውስጥ፡ ከጌታ አላህ ዘንድ ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የወረደ መለኮታዊ ራእይ መኖሩን በቀላሉ እንረዳለን፡፡ ይህም ራእይ ‹‹ቅዱስ ቁርኣን›› ነው፡፡

እኛ ቁርኣንን ባንተ ላይ ማውረድን እኛው አወረድነው።” (ሱረቱደህር (ኢንሳን) 7623)፡፡

መልስ

ጥቅሱ ቁርኣን ትክክል ነው የሚል ቅድመ ግንዛቤን መያዙ ግልፅ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ቅድመ ግንዛቤ ማረጋገጫ ያስፈልገዋል፡፡ ለሙሐመድ መገለጡን የሰጠው አካል ለዚህ የሚሆን ማረጋገጫ ከሙሐመድ በፊት መጽሐፉን በሚያነቡት ወገኖች ዘንድ እንደሚገኝ እየነገረው ነው፡፡ ለሙሐመድ የወረደለት ራዕይ መለኮታዊ መሆን አለመሆኑ የሚረጋገጠው ከእርሱ በፊት ከነበረው መጽሐፍ ጋር ከተስማማ ብቻ ነው፡፡ ጥያቄው መሆን ያለበት የሙሐመድ መገለጥ እውን እንደተባለው ከቀደመው መጽሐፍ ጋር ይስማማልን? የሚል ነው፡፡ መልሱ ግልፅ ነው፡፡

አቡ ሀይደር

ከዛም ይቀጥልና፡

2. ‹‹በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን›› በማለት ደግሞ አንድን ነገር እንዲያደርጉ ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡ ማረጋገጫው ምንድነው? የሚለውን ኋላ ላይ እንመለስበታለን፡፡ ‹‹በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን›› ማለት ግን፡ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) መጠራጠራቸውን የሚያመላክት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቃሉ የሚናገረው ‹‹በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን›› እያለ እንጂ፡ ‹‹በመጠራጠር ውስጥ ነህና›› እያለ አይደለም፡፡

ብትሆን› (if) የሚለው ቃል Conditional sentence ነው፡፡ ሊከሰትም ላይከሰትም የሚችል፡ በሁኔታዎች የሚወሰን አያያዥ (conjunction) የሆነ ቃል ነው፡፡

አጠቃላይ ሀሳቡ፡ወደ ‹‹አንተ ካወረድነው መጽሐፍ (መለኮታዊ ራእይ) ብትጠራጠር እንኳ›› ለማለት ነው፡፡ ታዲያ ምን ይሁን? ከተባለም፡

ዓረፍተ ነገሩ አኳሆናዊ (Conditional) መሆኑ እውነት ቢሆንም ሁሉን አዋቂ የሆነው አምላክ የሙሐመድን መፃዒ ሁኔታ ስለሚያውቅ ሙሐመድ እስከ ፍፃሜው ሳይጠራጠር የሚኖር ከሆነ እንዲህ ያለ ትዕዛዝ መስጠት አያሻውም፡፡ ከአኳሆናዊ ንግግሩ በማስከተል “ከተጠራጣሪዎቹም አትሁን” የሚለው ጠንካራ ማስጠንቀቂያ የሙሐመድን ልብ አለመርጋት ጥሩ አድርጎ ያሳያል፡፡

“ሙሐመድ መገለጡን ተጠራጥሮ አያውቅም” የሚለው አባባል ከሙሐመድ የቀደመ ታሪክ አንፃር ፍጹም ቅጥፈት መሆኑ ግለ ታሪኩን ከሚያውቅ ሰው ሁሉ የተሰወረ አይደለም፡፡ ሙሐመድ መገለጡ ሲመጣለት ከመጠራጠርም አልፎ ሰይጣን እንደያዘው ስጋት አድሮበት ነበር፡፡ መገለጡ ከሰማይ እንደመጣለት በስንት መከራ ያሳመኑት ሚስቱ ኸዲጃና ወረቃ የተሰኘ ክርስቲያን አጎቷ ነበሩ፡-

….ነቢዩም እንዳሉት “መልአኩም በጉልበት ያዘኝና አስጨንቆ ከአቅሜ በላይ ጨመቀኝ፡፡ ከዚያም ለቀቀኝና አንብብ አለኝ፡፡ እኔም መልሼ “እኔ ማንበብ አልችልም አልኩት፡፡” ይሄኔ እንደገና ያዘኝና መቋቋም ከምችለው በላይ ጨመቀኝ፡፡ ከዚያም ለቀቀኝና እንደገና አንብብ አለኝ፡፡ እኔም በድጋሚ ማንበብ አልችልም አልኩ፡፡ እርሱም ለሦስተኛ ጊዜ ይዞ መቋቋም ከምችለው በላይ ጨመቀኝና ለቀቀኝ ከዚያም እንዲህ አለኝ፡- “አንብብ በጌታህ ስም፡ ሁሉን በፈጠረው፡፡ ሰውንም ከረጋ ደም በፈጠረው፡፡ አንብብ ጌታህም ታላቅ ነውና… (ሱራ 96፡15) የአላህ መልእክተኛም መገለጡን ተቀብሎ ሲመለስ ኸድጃ ጋር እስኪገባ ድረስ በፍርሃትና የአንገቱ ጡንቻዎቹ በመንቀጥቀጥ ይብረከረኩ ነበር፡፡ እርሷ ጋ ሲደርስም “ሸፍኑኝ ሸፍኑኝ” አለ፡፡ እነርሱም ፍርሃቱ እስኪለቀው ድረስ ሸፈኑት፡፡ እርሱም “ከድጃ ሆይ ምን እየሆንኩ ነው; ብሎ ጠየቃት፡፡ የገጠመውንም ነገር ሁሉ ከነገራት በኋላ “የሆነ ነገር ሳልሆን አልቀርም” አላት፡፡ ኸድጃም መልሳ “በፍፁም፤ በአላህ! አንተ ታላቅ መልካም የምሥራች ያለብህ ነህ፡፡ አንተ ከዘመዶችህ ጋር መልካም ግንኙነት እስካለህ ድረስ፤ እውነትን እስከተናገርክ ድረስ፤ ድሆችንና ምስኪኖችን እስከረዳህ ድረስ፤ እንግዶችንም በአክብሮት እስካስተናገድክ ድረስ አላህ በፍፁም አይጥልህም” አለችው፡፡ ነገር ግን ከጥቂት ቀናት በኋላ ዋራቃ ሞተ፤ መለኮታዊውም መገለጥ ለጊዜው ቆመ፡፡ ከዚህም የተነሳ ነቢዩ እጅግ አዘነ፡፡ ብዙ ጊዜም ራሱን ከትልቅ ተራራ ጫፍ ላይ ፈጥፍጦ ሊገድል እንደሞከረና ራሱን ሊወረውር ወደ ተራራው በደረሰ ቁጥር ገብርኤል ይገለጥለትና “ሙሐመድ ሆይ በእርግጥ አንተ የአላህ መልእክተኛ ነህ” ሲለው ልቡ እንደሚረጋጋና እንደሚሰክን ከዚያም ወደ ቤት እንደሚመለስ ሰምተናል፡፡ የመገለጡ መምጣት በዘገየ ቁጥር እንደበፊቱ ያደርግ ነበር፡፡ ወደ ተራራው በቀረበም ቁጥር ገብርኤል ከዚህ በፊት እንዳለው ይለው ነበር፡፡ (ሳሒህ አል-ቡኻሪ 9.111)

የአል-ዙቤይር ኢስማኢል ቢን ሐኪም ከኸድጃ ሰምቶ እንደ ነገረኝ ኸድጃ የአላህን መልእክተኛ እንዲህ አለቻቸው፡- የአጎቴ ልጅ ሆይ በዋሻው የተገለጠልህ ወደ አንተ ሲመጣ ልትነግረኝ ትችላለህ? አዎን እችላለሁ አሏት፡፡ እርሷም ሲመጣ ንገረኝ አለቻቸው፡፡ ገብርኤል በመጣ ጊዜ ወደእኔ መጥቶ የነበረው ይኸውና መጥቷል አሏት፡፡ የአጎቴ ልጅ ተነሳና በግራ ጭኔ ላይ ተቀመጥ አለቻቸው የአላህ መልእክተኛም ተቀመጡ፡፡ እርሷም ታየዋለህን? አለቻቸው፡፡ እርሳቸውም አዎን አሏት፤ ዙርና በቀኝ ጭኔ ላይ ተቀመጥ አለቻቸው፤ እርሳቸውም ተቀመጡ፡፡ እርሷም አሁን ታየዋለህን? አለቻቸው አዎን አሏት፤ አሁንም ልብሷን ገለጥ አድርጋ ወደላይኛው ጭኔ ከፍ ብለህ ተቀመጥ አለቻቸው፤ እንደገና ተቀመጡ፡፡ እርሷም አሁን ታየዋለህ? አለቻቸው፤ አዎን አሏት፤ አዎን ባሏት ጊዜ ጭኗ ላይ ከፍ ብለው እንደተቀመጡ መሸፈኛዋንና የለበሰችውን ጠቅላላ ልብሷን አወላልቃ እራቁቷን በመሆን አሁን ታየዋለህን? አለቻቸው፤ አላየውም አሏት፤ እርሷም የአጎቴ ልጅ ሆይ ልብህ ይረጋጋ ደስም ይበልህ፤ በአላህ እርሱ መልአክ እንጅ ሰይጣን አይደለም አለቻቸው፡፡ (Muhammad Ibn Ishaq, The Life of Muhammad, translated by A.Guillaume, p. 107)

ስለዚህ ሙሐመድ የገዛ መገለጡን ተጠራጥሮ አያውቅም የሚለው ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ነቢይ እንደሆነ ከተነገረው ዕለት አንስቶ ከፍተኛ ጥርጣሬ ያደረበት ሲሆን ከዚህ ጥርጣሬ ነፃ የሆነበት ጊዜ ያለ አይመስልም፡፡ ሳሂህ አልቡኻሪ ሐዲስ ውስጥ እንደተዘገበው ወረቃ ከሞተ በኋላ ጥርጣሬው ስላየለበት ከተራራ ላይ ራሱን ወርውሮ ለመግደል ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም ጂብሪል እየመጣ ነቢይ መሆኑን ማሳሰብ ያስፈልገው ነበር፡፡ ነቢይነቱን ባይጠራጠር ኖሮ ራሱን ለመግደል መሞከር ለምን አስፈለገው? ጂብሪልስ ነቢይነቱን ማሳሰብ ለምን አስፈለገው? ይህ ታሪክ በአል-ጦበሪ መጽሐፍ ውስጥም ይገኛል (The History of al-Tabari: Muhammad at Mecca, translated by W. Montgomery Watt and M.V. McDonald 1988, Volume 6, p. 76)፡፡

በሌላ የቁርኣን ጥቅስ እንደተገለጸው በአንድ ወቅት ሙሐመድ በአላህ ላይ ለመዋሸት ተቃርቦ ነበር፡-

“እነሆ ከዚያም ወደ አንተ ካወረድነው ሌላን በኛ ላይ ትዋሽ ዘንድ ሊፈትኑህ በእርግጥ ተቃረቡ፤ ያን ጊዜም ወዳጅ አድርገው በያዙህ ነበር። ባላረጋንህም ኖሮ ወደነሱ ጥቂትን (ዝንባሌ) ልትዘነብል በእርግጥ በተቃረብክ ነበር። ያን ጊዜ የሕይወትን ድርብ (ቅጣት) የሞትንም ድርብ (ቅጣት) ባቀመስንህ ነበር፤ ከዚያም ላንተ በኛ ላይ ረዳትን አታገኝም ነበር።” (ሱራ 17፡73-75)

ሙሐመድ በአላህ ላይ ለመዋሸት እስኪቃረብ ድረስ ጥርጣሬው የገዘፈ እንደነበር ከዚህ ጥቅስ እንገነዘባለን፡፡ መቼስ አንድ ሰው ከእውነተኛው አምላክ ዘንድ መገለጥን እየተቀበለ መሆኑን በሚያውቅበት ሁኔታ ለመዋሸት ያስባል ሊባል አይችልም፡፡ ሙሐመድ ግን በሚገለጥለት ጉዳይ ላይ ሙሉ መተማመን ስላልነበረው ከመገለጡ ሐሳብ በመውጣት ለመዋሸት ተቃርቦ ነበር፡፡ ስለዚህ ሙሐመድ መገለጡን ተጠራጥሮ አያውቅም የሚለው የሙስሊሙ ሰባኪ አባባል ሐሰት ነው፡፡

አቡ ሀይደር

አጠቃላይ ሀሳቡ፡ወደ ‹‹አንተ ካወረድነው መጽሐፍ (መለኮታዊ ራእይ) ብትጠራጠር እንኳ›› ለማለት ነው፡፡ ታዲያ ምን ይሁን? ከተባለም፡

3. ‹‹እነዚያን ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ›› በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል፡፡ የመጽሐፉን አንባቢዎች ጠይቅ የሚለው ሀሳብ የሚያያዘው፡ ወደ አንተም ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን ከሚለው የቁርኣኑ ቃል ጋር እንጂ፡ እውነትን ከፈለግህ ከሚል የፈጠራ ወሬ ጋር አይደለም፡፡ ታዲያ ከየት አምጥታችሁ ነው፡ እውነቱን ከፈለጋችሁ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያነቡትን ጠይቁ! ይላል ቁርኣናችሁ የምትሉን?

መልስ

ጠይቅ የተባለው ጥርጣሬውን በእምነት የሚተካ እውነት እንዲያገኝ አይደለምን? መጽሐፉን በሚያነቡት ወገኖች ዘንድ አስተማማኝ እውነት እንዳለስ አያሳይምን? የተገለጠለት ጉዳይ እውነት መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥየቃም ሆነ አዲስ እውነት ለማግኘት የሚደረግ ጥየቃ ያው ዞሮ ዞሮ እውነትን ለማወቅ የሚደረግ ጥየቃ ነው፡፡ ስለዚህ “እውነትን ከፈለግህ” የሚለው መረዳት “የፈጠራ ወሬ” ሊባል የሚችለው በምን ሒሳብ ነው?

ሙስሊሙ ሰባኪ በቁርኣንና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል ግልፅ ግጭት መኖሩን ያውቃል ስለዚህ ቁርኣን ትክክል ነው የሚል ቅድመ ግንዛቤ ስላለው “ጠይቅ” በሚለው ትዕዛዝ ምክንያት ከተፈጠረው ቅርቃር የሚወጣበትን መንገድ ለማግኘት እየተፍጨረጨረ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ጂምናስቲክ ከመሥራት ተቆጥቦ ጉዳዩን በሚዛናዊና በሰከነ መንገድ ለተመለከተ ሰው እውነታው ግልፅ ሆኖ ይታየዋል፡፡ ሙሐመድ ጥርጣሬ ካደረበት የመጽሐፉን ሰዎች እንዲጠይቅ የነገረው አካል የመጽሐፉ ይዘት ከእርሱ መገለጥ ጋር እንደማይስማማ የማያውቅ አለበለዚያም እያወቀ የመጽሐፉን ይዘት የማያውቀውን ሙሐመድን ለማታለል ተናግሮ መሆን አለበት፡፡ ከሁለት አንዱ ነው፡፡ የመጽሐፉ ይዘት ከመገለጡ ጋር እንደማይስማማ እያወቀ “ጠይቅ” ካለው ተናጋሪው ሐሰተኛ ነው፡፡ የመጽሐፉን ይዘት የማያውቀውን መሃይሙን ሙሐመድን ለማታለል (ሙሐመድ መገለጥን እየሰጠው ያለው አካል ከቀደሙት ነቢያት የተለየ እንዳልሆነ እንዲያስብ ለማድረግ) ተናግሮ ከሆነ ደግሞ አታላይ ነው፡፡ ወጣም ወረደ ሙሐመድም ሆነ ሙስሊሞች ጥርጣሬ ካደረባቸው የመጽሐፉን ሰዎች እንዲጠይቁ ታዘዋል፡፡ ስለዚህ ጥርጣሬ ያደረበት ማንኛውም ሙስሊም መጽሐፉን የሚያነቡትን ወገኖች የመጠየቅ ሃይማኖታዊ ግዴታ አለበት፡፡ ሳይጠይቅ ከቀረ ሃይማኖቱ ያስቀመጠበትን ግዴታ ባለመወጣቱ ምክንያት በቁርኣን ላይ ያምጻል፡፡ የቁርኣንን ትዕዛዝ ተቀብሎ ከጠየቀ ደግሞ መጽሐፉ ከቁርኣን ጋር እንደማይስማማ ስለሚረዳ እስልምናን ይተዋል፡፡ ስለዚህ ሙስሊሞች አጣብቂኝ ውስጥ ናቸው፡፡ የእስልምናን ሐሰትነት ሳይመሰክሩ ከአጣብቂኙ የሚወጡበት መንገድ ዝግ ነው፡፡

አቡ ሀይደር

ከላይ በጥቅላዊ ማብራሪያው ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፡ የመጽሐፍቱን ሊቃውንቶች ብትጠይቃቸው እንኳ በመጽሐፉ ውስጥ በኦርጂናል ይዘቱ የአንተ ነቢይነት እንደተነገረ ያውቃሉ፡ እነሱም ይመሰክራሉ እያለ ነው፡፡

ወገኖቻችን! ‹‹ከአንተ በፊት›› የሚለው ኃይለ ቃል የናንተን ምኞት ከንቱ አያስቀረውምን?

ቅዱስ ቁርኣን እየተናገረ ያለው፡– ‹‹ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ›› በማለት እንጂ፡ ከአንተ በኋላ የሚመጡትን ጠይቅ አላለም፡፡ አሁንስ ገባችሁ?

መልስ

ስለ ኦሪጅናል ቀደም ሲል መልስ ተሰጥቶበታል፡፡ ‹‹ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ›› ሲል በሙሐመድ ዘመን ስለነበሩት ነው ወይስ ስለ ሞቱት ነው እየተናገረ ያለው? በሙሐመድ ዘመን ስለነበሩት ነው፡፡ በሙሐመድ ዘመን የነበሩት ሊቃውንት ያነቡ የነበሩት ደግሞ በኛ እጅ ካለው መጽሐፍ የተለየ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ከዚያ በፊትም ሆነ በዚያ ዘመን የነበሩትን የብራና ጽሑፎች አይቶ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ስለዚህ የምናነበው መጽሐፍ አንድ እስከሆነ ድረስ እኛንም ሆነ እነርሱን መጠየቅ ልዩነቱ ምንድነው? ትዕዛዙ በሙሐመድ የተገደበ እንዳልሆነ በተፍሲሮች ተነግሯል፡፡ ስለዚህ እኛን ልትጠይቁ ዘንድ ግድ ይላችኋል፡፡

አቡ ሀይደር

4. ‹‹እውነቱ ከጌታህ ዘንድ በእርግጥ መጥቶልሃል ከተጠራጣሪዎቹም አትሁን›› በማለት አንቀጹ በሚያምር አገላለጽ ተደመደመ፡፡ አላሁ አክበር!

ወደሳቸው ይወርድ የነበረው መለኮታዊ ራእይ፡እውነቱ እኔው ራሴ ነኝ! ካለ፡ ሌላ እውነት ፍለጋ እንዴት ይኬዳል?

ስለዚህ እውነቱ እዚሁ ቁርኣን ውስጥ ነው ያለው፡፡ ‹‹ብትጠራጠር እንኳ እነሱን ጠይቅ›› ማለቱ፡ እውነትን ፍለጋ ወደነሱ ሂድ! ከማለት ጋር ምንም ግኑኝነት የለውም፡፡ ግኑኝነቱ፡ እነሱም ቢሆኑ ብትጠይቃቸው የአንተን ነቢይነት በሚገባ ስለሚያውቁ ይነግሩሀል ነው፡፡

መልስ

ውሸት ነዋ! የሙሐመድ አስተምህሮና መጽሐፍ ቅዱስ ልዩነታቸው የጨለማና የብርሃን ያህል ነው፤ ስለዚህ ለሙሐመድ መገለጥን የሰጠው አካል “ብትጠራጠር ሂድና ጠይቅ ያረጋግጡልሃል” ብሎ ማለቱ ሙሐመድን እያታለለ መሆኑን አለበለዚያም የመጽሐፍ ቅዱስን ይዘት አለማወቁን ያሳያል፡፡ ሆኖም ይህ አንቀፅ ከፈጣሪ ነው የሚል ማንኛውም ሰው አንቀፁን የመታዘዝ ግዴታ አለበት፡፡ ቢታዘዝ ቁርኣን ሐሰት መሆኑን የሚያውቅበትን ዕድል ያገኛል፤ ባይታዘዝ ደግሞ ይህ አንቀፅ ከፈጣሪ አለመሆኑን አምኗል አለያም ከፈጣሪ እንደሆነ አምኖ አመፀኛ ሆኗል፡፡ በዚያም ሆነ በዚህ ይህ አንቀፅ ለእስልምና የጎን ውጋት እንደሆነ ይኖራል፡፡

አቡ ሀይደር

5. የአላህ ነቢይም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ይህ አንቀጽ በወረደላቸው ግዜ፡ የመጽሐፉን ሰዎች ሄደው አልጠየቁም፡፡ ባይሆን በተቃራኒው እንዲህ ነበር ያሉት፡

‹‹ አሹክኩ ወላ አስአል›› ‹አልጠራጠርም አልጠይቅምም፡፡

(ተፍሲሩጠበሪይ፡ ጃሚዑል በያን ሱረቱ ዩኑስ 94 ቁጥር 17893-17894)፡፡

እኛም የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ተከታይ የሆንን ሙስሊሞች፡ እሳቸውን በመከተል አንጠይቅምም ደግሞም አንጠራጠርምም፡፡

መልስ

ለሙሐመድ መገለጡን የሰጠው ባዕድ መንፈስ ሙሐመድን የማታለል ዓላማ ይዞ ይህንን ቃል ከነገረው ተሳክቶለታል ማለት ነው፡፡ አንዳንድ አጭበርባሪ ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ ተዓማኒነትን ለማግኘት የአንድ ትልቅ ሰው ስም ጠርተው “ካላመንከኝ እገሌን ጠይቀው!” በማለት ሰዎችን ማታለላቸው የተለመደ ነው፡፡ አልፈውም “አሁን ደውዬ ላገናኝህ? እንዲያውም ናና አብረን ሄደን እናናግረው! ወዘተ” በማለት በራስ መተማመን ያላቸው ሊያስመስሉ ይችላሉ፡፡ እንደ ሙሐመድ ያለ ያልተማረ ሰው ደግሞ ያንን ከልክ ያለፈ “በራስ መተማመን” እንደ እውነተኛነት መለክያ በመውሰድ “በቃ አልጠይቅም፤ አምኜሃለሁ” በማለት ለአጭበርባሪው ወጥመድ እጅ ይሰጣል፡፡ አስተዋይ ሰው ግን “ጠይቅ ካልክ እሺ ብጠይቅ ደስ ይለኛል፤ ባንተ ላይ ያለኝን መተማመን ይጨምርልኛል እንጂ አይጎዳኝም” በማለት የሰውየውን እውነተኛነት ወደ ማረጋገጥ ይሄዳል እንጂ እንደ ሙሐመድ ለዚያውም ነፍስን በሚያክል ጉዳይ  ላይ ‹‹ላ አሹክኩ ወላ አስአል›› ‹አልጠራጠርም አልጠይቅምም› በማለት ከራሱም አልፎ የተከታዮቹን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል የሞኝ ውሳኔ አይወስንም፡፡ ስለዚህ እኛ ጠይቁ ብለን እንመክራችኋለን፡፡ ጥርጣሬያችሁን በ “አላሁ አክበር” ፉከራ ለመደበቅ ከምትሞክሩ እውነት የቀደሙት መጻሕፍት የሙሐመድ መገለጥ ትክክል መሆኑን ያረጋግጡ እንደሆን ጠይቁና እዩ!

ሙሐመድ ጠይቆ አያውቅም የሚለው አባባል ሐሰት መሆኑ መታወቅ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ በሐዲሳት እንደተዘገበው ሙሐመድ በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ በቶራህ ውስጥ ምን እንደተጻፈ ሲጠይቅ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል በአንድ አጋጣሚ የእርሱን ማንነትና መምጣት የሚገልፅ ነገር በቶራህ ውስጥ ይኖር አንደሆን አንድን አይሁዳዊ ጎልማሳና ሌላ ወጣት አይሁዳዊ ጠይቆ ነበር፡፡ ጎልማሳው አይሁዳዊ ምንም ነገር እንደሌለ የመለሰለት ሲሆን ወጣቱ ግን አዎንታዊ ምላሽ እንደሰጠ ተነግሯል፤ ነገር ግን በትረካው ውስጥ ወጣቱ አይሁዳዊ ሙሐመድ በየትኛው የቶራህ ክፍል እንደተጠቀሰ አልገለጸም፡፡ ሙሐመድ በቶራህ ውስጥ ተጠቅሷል የሚለው ሐሰት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ትረካው ግን “ጠይቆ አያውቅም” የሚለውን የሙስሊሙን ሰባኪ አባባል ውድቅ ያደርጋል፡፡ (Tafsir Ibn Kathir Part 9 of 30: Al A’raf 088 To Al Anfal 040, Translation By Muhammad Saed Abdul-Rahman, p. 57)፡፡ በሌላ አጋጣሚም እንዲሁ አመንዝሮችን ስለመውገር በቶራህ ውስጥ ምን እንደተጻፈ ጠይቆ ተረድቷል፡፡ (Sahih al-Bukhari, Volume 8, Book 82, Number 809)፡፡ ስለዚህ ሙሐመድ ጠይቆ ያውቃል፡፡ ጠይቆ አያውቅም የሚለው ዓይን ያወጣ ክህደት ነው፡፡ እርሱ ከጠየቀ ደግሞ የዘመናችን ሙስሊሞች ከእርሱ ስለማይበልጡ መጠየቅ ያስፈልጋቸዋል፡፡

አቡ ሀይደር

6. ኢማሙል ቡኻሪይ በዘገቡት ሶሒሕ ሐዲሥ ላይ ደግሞ፡ እንዲህ የሚል ግሳፄ ተቀምጧል፡

ﻋَﻦْ ﻋَﺒْﺪِ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﺑْﻦِ ﻋَﺒَّﺎﺱٍ ﺭَﺿِﻲَ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻋَﻨْﻬُﻤَﺎ، ﻗَﺎﻝَ : ” ﻳَﺎ ﻣَﻌْﺸَﺮَ ﺍﻟﻤُﺴْﻠِﻤِﻴﻦَ، ﻛَﻴْﻒَ ﺗَﺴْﺄَﻟُﻮﻥَ ﺃَﻫْﻞَ ﺍﻟﻜِﺘَﺎﺏِ، ﻭَﻛِﺘَﺎﺑُﻜُﻢُ ﺍﻟَّﺬِﻱ ﺃُﻧْﺰِﻝَ ﻋَﻠَﻰ ﻧَﺒِﻴِّﻪِ ﺻَﻠَّﻰ ﺍﻟﻠﻪُ ﻋَﻠَﻴْﻪِ ﻭَﺳَﻠَّﻢَ ﺃَﺣْﺪَﺙُ ﺍﻷَﺧْﺒَﺎﺭِ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ، ﺗَﻘْﺮَﺀُﻭﻧَﻪُ ﻟَﻢْ ﻳُﺸَﺐْ، ﻭَﻗَﺪْ ﺣَﺪَّﺛَﻜُﻢُ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﺃَﻥَّ ﺃَﻫْﻞَ ﺍﻟﻜِﺘَﺎﺏِ ﺑَﺪَّﻟُﻮﺍ ﻣَﺎ ﻛَﺘَﺐَ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻭَﻏَﻴَّﺮُﻭﺍ ﺑِﺄَﻳْﺪِﻳﻬِﻢُ ﺍﻟﻜِﺘَﺎﺏَ، ﻓَﻘَﺎﻟُﻮﺍ : ﻫُﻮَ ﻣِﻦْ ﻋِﻨْﺪِ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻟِﻴَﺸْﺘَﺮُﻭﺍ ﺑِﻪِ ﺛَﻤَﻨًﺎ ﻗَﻠِﻴﻠًﺎ، ﺃَﻓَﻼَ ﻳَﻨْﻬَﺎﻛُﻢْ ﻣَﺎ ﺟَﺎﺀَﻛُﻢْ ﻣِﻦَ ﺍﻟﻌِﻠْﻢِ ﻋَﻦْ ﻣُﺴَﺎﺀَﻟَﺘِﻬِﻢْ، ﻭَﻻَ ﻭَﺍﻟﻠَّﻪِ ﻣَﺎ ﺭَﺃَﻳْﻨَﺎ ﻣِﻨْﻬُﻢْ ﺭَﺟُﻠًﺎ ﻗَﻂُّ ﻳَﺴْﺄَﻟُﻜُﻢْ ﻋَﻦِ ﺍﻟَّﺬِﻱ ﺃُﻧْﺰِﻝَ ﻋَﻠَﻴْﻜُﻢْ ” ﺭﻭﺍﻩ ﺍﻟﺒﺨﺎﺭﻱ 2685.7522.7523

ዐብዱላህ ኢብኑዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዲህ ይላል፡

እናንተ ሙስሊሞች ሆይ! በነቢዩ ላይ የተወረደላችሁ መጽሐፍ (ቁርኣን) ከአላህ ዘንድ የመጣ አዲስ (ያላረጀ) ሆኖ ሳለ፡ እናንተም ያልተበረዘና የሰው እጅ ያልገባበት ሆኖ እያነበባችሁት፡ የመጽሐፉን ሰዎች (አይሁዶችና ክርስቲያኖች) እንዴት ትጠይቃላችሁ? አላህም (በቁርኣኑ) የመጽሐፉ ሰዎች መጽሐፉን በእጃቸው እንደበረዙትና እንደቀየሩት፣ ከዛም የተበረዘውን ጥቂትን ምድራዊ ዋጋ ለመሸመት፡ ይህ ከአላህ ዘንድ የመጣ ነው እንዳሉ ነግሯቹኋል፡፡ እንግዲያውስ ወደናንተ የመጣላችሁ ዕውቀት እነሱን ከመጠየቅ አይከለክላችሁምን? በአላህ ይሁንብኝ! ከነሱ ውስጥ አንድም ሰው ወደናንተ ስለወረደው ሲጠይቁአችሁ በፍጹም አላየንም (ታዲያ እናንተ እነሱን እንዴት ትጠይቃላችሁ?)”

(ቡኻሪይ 2685 7522 7523)፡፡

አዎ! ልንጠይቃቸውም አይገባም! ትክክለኛው ሀሳብ ይህ ነው ወላሁ አዕለም፡፡

ጌታህ በመካከላቸው በትክክል ፍርዱ ይፈርዳል፤ እርሱም አሸናፊው ዐዋቂው ነው። በአላህም ላይ ተጠጋ፤ አንተ ግልጽ በሆነው እውነት ላይ ነህና።” (ሱረቱነምል 2779)፡፡

መልስ

ከኢብን ዐባስ ጋር የተያያዘው ሐዲስ የቁርኣንን ጥቅስ የተረጎመበት መንገድ ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ ትክክል ነው ከተባለ ቁርኣን አንዱ ቦታ ላይ “ሂድና ጠይቅ” ብሎ በሌላ ቦታ ላይ ደግሞ “መጽሐፋቸው የተበረዘ ነው” የሚል ከሆነ እርስ በርሱ ይጋጫል ማለት ነው፡፡ በርግጥ የጥቅሱን አውድ የምንመለከት ከሆነ ኢብን ዐባስ መሳሳቱ ግልፅ ይሆንልናል፡፡ ሐዲሱ የሚጠቅሰው የቁርኣን ክፍል እንዲህ ይነበባል፡-

“(አይሁዶች) ከነሱ የኾኑ ጭፍሮች የአላህን ቃል የሚሰሙና ከዚያም ከተረዱት በኋላ እነርሱ እያወቁ የሚለውጡት ሲኾኑ ለናንተ ማመናቸውን ትከጅላላችሁን? እነዚያንም ያመኑትን ባገኙ ጊዜ «አምነናል» ይላሉ፡፡ ከፊላቸውም ወደ ከፊሉ ባገለለ «ጊዜ አላህ በናንተ ላይ በገለጸላቸሁ ነገር እጌታችሁ ዘንድ በርሱ እንዲከራከሩዋችሁ ትነግሩዋቸዋላችሁን? አታውቁምን?» ይላሉ፡፡ አላህ የሚደብቁትንና የሚገልጹትን የሚያውቅ መኾኑን አያውቁምን? ከነሱም መጽሐፉን የማያውቁ መሃይማናን አሉ፡፡ ግን ከንቱ ምኞቶችን (ይመኛሉ)፤ እነርሱም የሚጠራጠሩ እንጂ ሌላ አይደሉም፡፡ ለነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉና ከዚያም በርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «ይህ ከአላህ ዘንድ ነው» ለሚሉ ወዮላቸው፡፡ ለነርሱም ከዚያ እጆቻቸው ከጻፉት ወዮላቸው፡፡ ለነሱም ከዚያ ከሚያፈሩት (ኃጢኣት) ወዮላቸው፡፡” (አል-በቀራ 2፡175-179)

የጥቅሱ አውድ እንደሚናገረው እነዚህ ወገኖች ከአይሁድ ወገን የሆኑ የተወሰኑ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የተወሰኑ ሰዎች ሙስሊሞችን ሲያገኙ እስልምናን የተቀበሉ ይመስላሉ ነገር ግን እውነተኛ አማኞች አይደሉም፡፡ ከእነርሱ ወገን የሆኑ መጽሐፉን የማያውቁ መሃይማን ደግሞ አሉ፡፡ ከአውዱ እንደሚታየው ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ መጽሐፉን በእጆቻቸው የሚጽፉትና ከአላህ ዘንድ እንደሆነ የሚናገሩት እነዚህ ሐሰተኛ ወገኖች ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ትክክለኛውን መጽሐፍ አያውቁትም ነገር ግን ሌላ መጽሐፍ በእጃቸው በመጻፍ ይሸጣሉ፡፡ በዚህ ስፍራ መጽሐፍ ሻጮቹ ክርስቲያኖች አይደሉም፤ አይሁድ ናቸው፡፡ ከአይሁድም ሁሉም አይሁድ አይደሉም፤ የተወሰኑት ናቸው፡፡  እነዚህ ደግሞ እስልምናን የተቀበሉ የሚያስመስሉ ነገር ግን ከልባቸው ያላመኑ ናቸው፡፡ ይህንን ተግባር የሚፈፅሙት ደግሞ ሁሉም ሳይሆኑ ከእነርሱ መካከል የተወሰኑ መሃይማን ናቸው፡፡ የሚጽፉት መጽሐፍ ምን እንደሆነ ባይገለጽም መጽሐፍ ቅዱስ ሊሆን አይችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ኮፒዎች የተሰራጨና በሊቃውንቱ እጅ የሚገኝ በመሆኑ ምክንያት ጥቂት አይሁድ ለዚያውም እስልምናን እንደተቀበሉ የሚናገሩ ለሙሐመድ ቅርበት የነበራቸው ወገኖች ሊለውጡት የሚችሉት አይደለም፡፡ ስለዚህ አቡ-ሃይደር የጠቀሰው የኢብን ዐባስ ትርጓሜ የጥቅሱን አውድ የሳተ ነው፡፡ የተሳሳተ ሐሳብ በማንም ተነገረ በማን ስህተት እስከሆነ ድረስ ስህተት ነው፡፡

ይህንን አባባል ከኢብን ዐባስ እንደተላለፈ አድርጎ ያቀረበው አል-ቡኻሪ በሌላ ሐዲስ ደግሞ ይህንን የሚጣረስ ከኢብን ዐባስ የተላለፈ ሌላ ሐሳብ ያቀርብልናል፡፡ ዕውቁ ሙፈሲር ኢብን ከሢር እንዲህ ጠቅሶታል፡-

“… አል ቡኻሪ እንደዘገበው ኢብን አባስ እንዲህ ብሏል፤ ‹የዚህ አያ ትርጉም የሚከተለው ነው፡- … ከአላህ ፍጥረታት መካከል ማንም የአላህን ቃላት ከመጻሕፍቱ ውስጥ ማስወገድ አይችልም፡፡ ግልፅ ትርጉማቸውን ያጣምማሉ ማለት ነው፡፡› ወሃብ ኢብን ሙነቢህ እንዲህ አለ ተውራት እና ኢንጂል ልክ አላህ በገለጣቸው ሁኔታ ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ ከውስጣቸው አንድም ፊደል አልተወገደም፡፡ ነገር ግን ሰዎች ራሳቸው በጻፏቸው መጻሕፍት ላይ ተሞርኩዘው በመጨመርና ውሸት በሆነ አተረጓጎም ሌሎችን ያሳስታሉ፡፡” … የአላህ መጻሕፍት ግን እስከ አሁን ተጠብቀው ይገኛሉ፤ ሊለወጡም አይችሉም፡፡ (Tafsir Ibn Kathir – Abridged, Volume 2, Parts 3, 4 & 5, Surat Al-Baqarah, Verse 253, to Surat An-Nisa, verse 147, First Edition: March 2000, p. 196)

እዚሁ ተፍሲፍ የግርጌ ማስታወሻ ላይ እንዲህ የሚል እናገኛለን፡-

“ቃሉን ያጣምማሉ ማለት ትርጉሙን ይለውጣሉ ወይም ያጣምማሉ ማለት ነው ከየትኛው የአላህ መጻሕፍት ውስጥ አንድ ቃል እንኳ መለወጥ የሚችል የለም፡፡ ይህ ማለት በተሳሳተ መንገድ ይተረጉማሉ ማለት ነው፡፡”

ስለዚህ የቱ ነው ትክክል? ሙስሊሞች ባይወዱትም ትክክለኛው ትርጓሜ የኋለኛው ነው፡፡ ሙሐመድ አንድ ጊዜም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ መበረዙን ተናግሮ አያውቅም፡፡ ይልቅስ ሥልጣኑን ተቀብሎ አክብሮት ይሰጠው ነበር፡፡ ሱናን አቡዳውድ ላይ ደግሞ እንዲህ የሚል ሐዲስ እናነባለን፡-

“… ለአላህ መልእክተኛ (ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁንና) ወንበር አመጡላቸው፤ ተቀመጡበትም፡፡ ከዚያም ተውራት አምጡልኝ አሉ፤ አመጡላቸውም፡፡ ከዚያ ከወንበሩ ላይ ተነስተው ተውራትን አስቀመጡና እንዲህ አሉ፡– በአንተ እና አንተን በገለጠው አምላክ አምናለሁ፡፡” Sunan Abu Dawud, Book 38 (Kitab al Hudud, i.e. Prescribed Punishments), Number 4434

ኢብን ከሢር ደግሞ አላህ ስላዘዘው ሙሐመድ ይህንን ማድረጉን ይናገራል፡፡ (Tafsir Ibn Kathir (Abridged) Volume 3, Parts 6, 7 & 8)

ሙሐመድ ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምሕሮ ጋር የሚጋጭ መገለጥ አምጥቶ ሳለ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚደግፈው ማሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስን ይዘት አለማወቁን ያሳያል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡትን ሰዎች ሄዶ እንዲጠይቅና የገዛ መገለጡን እንዲያረጋግጥ አላህ እንደነገረው የተናገረውም ባለማወቁ ምክንያት ነው፡፡ አንድ ሙስሊም ይህንን ቃል እንደ ፈጣሪ መገለጥ ከተቀበለ መታዘዝ ይኖርበታል፡፡ ከታዘዘ ደግሞ ቁርኣን ሐሰት መሆኑን ይገነዘባል፡፡ ካልታዘዘ በቃሉ ላይ አምጿል ወይም ደግሞ እውነት መሆኑን አልተቀበለም ማለት ነው፡፡ ሙስሊም ሰባኪያን የፈለገ ያህል ጥቅሱን ቢለጥጡ፣ ቢጨምቁ ወይም ቢጠመዝዙ ይህንን የሃይማኖታቸውን የዘመናት ሽንቁር መድፈን አይቻላቸውም፡፡ የአቡ ሀይደር ጽሑፍም የሚያረጋግጥልን ይህንኑ ነው፡፡

 

እስላማዊ አጣብቂኝ :- መጽሐፍ ቅዱስ ከተበረዘ ቁርኣን ዋሽቷል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ካልተበረዘ ቁርኣን የፈጣሪ መጽሐፍ አይደለም!

መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟልን? ማን በረዘው? ለዶ/ር ሙሐመድ ዓሊ አልኹሊ የተሰጠ ምላሽ

ተውራትና ኢንጅል መጽሐፍ ቅዱስ ናቸውን?

መጽሐፍ ቅዱስ