የአትናቴዎስ የሃይማኖት መግለጫ
- ለመዳን የሚፈልግ ሁሉ ከሁሉም ነገር አስቀድሞ የሁሉ የሆነች የቤተ ክርስቲያን ሃይማኖትን እውነተኛ አድርጎ ሊቀበል ያስፈልገዋል።
- ንጹሕና ሙሉ አድርጎ ያልጠበቀው ሁሉ ያለ ጥርጥር የዘላለም ጥፋት ይደርስበታል።
- በሦስትነቱ አንድነቱን፥ በአንድነቱም ሦስትነቱን አምነን አንድ አምላክን እናመልካለን። ይህም እውነተኛ የክርስትና ሃይማኖት ነው።
- ይህንንም የምናደርገው አካላቱን ሳንደባልቅ መለኮታዊ ህልውናውንም ሳንከፍል ነው።
- ምክንያቱም የአብ አካል ለብቻው የወልድ ለብቻው፥ የመንፈስ ቅዱስም ለብቻው ስለሆነ ነው።
- ሆኖም የአብ፥ የወልድና የመንፈስ ቅዱ መለኮት አንድ ነው፥ ክብሩ ሥልጣኑም እኩል ሆኖ ይኖራል።
- ወልድ በህልውናው እንደ አብ ነው፥ መንፈስ ቅዱስም እንደዚሁ ነው።
- አብ አልተፈጠረም፥ ወልድ አልተፈጠረም፥ መንፈስ ቅዱስም አልተፈጠረም።
- አብ ወሰን የለውም፥ ወልድ ወሰን የለውም፥ መንፈስ ቅዱም ወሰን የለውም።
- አብ ዘላለማዊ ነው፥ ወልድ ዘላለማዊ ነው፥ መንፈስ ቅዱስም ዘላለማዊ ነው።
- ቢሆነም ዘላለማዊ የሚሆን አንድ እንጂ ሦስት አይደሉም።
- ያልተፈጠረና ወሰን የሌለው ሦስት እንዳልሆነ እንደዚሁም ያልተፈጠረና ወሰን የሌለው አንድ ነው።
- እንዲሁም አብ ሁሉን የሚችል ነው፥ ወልድ ሁሉን የሚችል ነው፥ መንፈስ ቅዱስም ሁሉን የሚችል ነው።
- ቢሆንም፥ ሁሉን የሚችል አንድ አንጂ ሦስት አይደሉም።
- ስለዚህ አብ አምላክ ነው፥ ወልድ አምላክ ነው፥ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው።
- ሆኖም አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አይደሉም።
- ስለዚህ አብ ጌታ ነው፥ ወልድ ጌታ ነው፥ መንፈስ ቅዱስም ጌታ ነው።
- ሆኖም አንድ ጌታ እንጂ ሦስት ጌቶች አይደሉም።
- ምክንያቱም የክርስትና እምነት እውነተኛነት እያንዳንዱ አካል አምላክና ጌታ መሆኑን እንድናምን እንደሚያስገድደን ሁሉ የክርስትና ሃይማኖት ሦስት አማልክት ወይም ሦስት ጌቶች እንዳንል ይከለክለናል።
- አብ በማንም አልተሠራም፥ አልተፈጠረም፥ አልተወለደምም።
- ወልድ ከአብ ተወለደ እንጂ አልተሠራም አልተፈጠረምም።
- መንፈስ ቅዱስ አልተሠራም፥ አልተፈጠረም፥ አልተወለደምም፥ ነገር ግን ከአብ የሚሠርጽ ነው።
- ስለዚህ አብ አንድ ስለሆነ ሦስት አብ አይደለም፥ ወልድም አንድ አንጂ ሦስት ወልድ አይደለም፥ መንፈስ ቅዱስም አንድ እንጂ ሦስት አይደለም።
- ከሦቱ አካላት አንዱ ከሌላው ቀዳሚነት ወይም ደኃሪነት የለውም፤ አንዱም ከሌላው የሚበልጥ ወይም የሚያንስ አይደለም።
- ስለሆነም፥ ሦስቱ አካላት በእኩልነትና በዘላለማዊነት አንድ ናቸው። ከዚህ የተነሣም ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው ሦስቱ አካላት በአንድ መለኮት አንድ አምላክም በሦስት አካላት ይመለካል።
- ለመዳን የሚፈልግ ሁሉ ስለ ሥላሴ እንደዚህ ማሰብ ይገባዋል።
- ከዚህም ሌላ የዘላለምን ደኅንነት ለማግኘት የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ መገለጽ በእውነት ማመን አስፈላጊ ነው።
- ምክንያቱም ትክክለኛው እምነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ አምላክም ሰውም መሆኑን አምነን ማስታወቅ ነው።
- እርሱም ከዘመናት አስቀድሞ ከአብ የተወለደ አምላክ ከእናቱም በሥጋ በዓለም የተወለደ ሰው ነው።
- የሚያስብ ነፍስ ያለችውና የሰውን ሥጋ የለበሰ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው።
- በአምላክነቱ ከአብ ጋር የተካከለ፥ በሰውነቱም ከአብ ያነሰ ነው።
- አምላክም ሰውም ቢሆንም አንድ ክርስቶስ እንጂ ሁለት ክርስቶስ አይደለም።
- አንድ ነው ስንል ግን የሰውን ሥጋ ለበሰ እንጂ መለኮት ወደ ሥጋ አልተለወጠም።
- በእርግጥ አንድ የሆነውም በባሕርያት መደባለቅ ሳይን በአካል አንድ በመሆኑ ነው።
- ምክንያቱም የሚያስብ ነፍስና ሥጋ አንድ ሰው እንደሆኑ ሁሉ አምላክና ሰው በክርስቶስ አንድ ናቸው።
- እርሱም ለደህንነታችን ሲል መከራ የተቀበለ፥ ወደ ሲኦል የወረደ፥ ከሙታን የተነሣ፤
- ወደ ሰማይ የወጣ፥ በአብ ቀኝ የተቀመጠ፥ በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ከዚያ የሚመለስ ነው።
- በመምጣቱ ጊዜም ሰዎች ሁሉ በሥጋ ተነስተው ስለ ሥራቸው መልስ ይሰጣሉ።
- መልካም የሠሩ ወደ ዘላለም ሕይወት ክፉ የሠሩም ወደ ዘላለም እሳት ይገባሉ።
- ይህ እውነትኛው የክርስትና እምነት ነው። ይህን የማያምንና አጥብቆ የማይዝ ሊድን አይችልም።