የመጀመርያዎቹ የእጅ ጽሑፎች አለመኖራቸው የመጽሐፍ ቅዱስን ተዓማኒነት ይቀንሳልን?

የመጀመርያዎቹ የእጅ ጽሑፎች አለመኖራቸው የመጽሐፍ ቅዱስን ተዓማኒነት ይቀንሳልን?

ተከታዩ ጽሑፍ ለሐሰን ታጁ መጽሐፍ ከሰጠነው ምላሽ የተወሰደ ነው፡፡

አቶ ሐሰን “የማመሳከርያው መጥፋት” በሚል ርዕስ ስር እንዲህ ይላሉ፡-

አሁን በምድር ላይ ያሉ ወንጌሎችን ከኦሪጅናል ጸሐፊዎች ስራ ለማመሳከር እንዳይሞከር በባለቤቶቹ የእጅ ጽሑፍ የተጻፉ መጽሐፍት ከምድረ ገጽ ጠፍተዋል፡፡ ሁሉም የወንጌል መጽሐፍት ከግሪክ የተቀዱ ናቸው፡፡ አሳሳቢው ነገር ግን ይህም የግሪክ እናት መጽሐፍ መጥፋቱ እና የክርስቲያኑ ዓለም ያለ ማጣቀሻ መቅረቱ ነው፡፡ (ገፅ 42)

ይህንን አባባል ይደግፍልኛል ያሉትን ሐሳብ እንደተለመደው ከኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ ላይ ጠቅሰዋል (ገፅ 42-43)፡፡ ነገር ግን በጽሑፋቸው ውስጥ ሁለት ሐሰተኛ ምልከታዎች ይገኛሉ፡፡ የመጀመርያው ወንጌላት በቀዳሚነት በግሪክ ቋንቋ ሳይሆን በሌላ ቋንቋ የተጻፉ በማስመሰል መናገራቸው ነው፡፡ ይህ አባባላቸው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ዕውቀት እንደሌላቸው አመላካች ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መጀመርያ የተጻፉት በግሪክ ቋንቋ እንደሆነ ለማወቅ ምሑራንን መጥቀስ አያሻም፡፡ አቶ ሐሰን እኔ ወደማገለግልባት ቤተ ክርስቲያን እሑድ ጠዋት በመምጣት የሰንበት ትምህርት የሚማሩትን ህፃናት ቢጠይቁ በጥሩ ሁኔታ ሊያስረዷቸው ይችላሉ፡፡

ሁለተኛው ደግሞ በኩረ ጽሑፉ ከሌለ አንድ መጽሐፍ ተዓማኒነት እንደሚጎድለው በማስመሰል መናገራቸው ነው፡፡ እውነት ነው የአዲስ ኪዳን በኩረ ጽሑፎች ዛሬ በእጃችን አይገኙም፡፡ የተጻፉባቸው ቁሶች እስከ እኛ ዘመን መቆየት ለመቻል እንደ ቁምራን ባለ ከባቢያዊ ሁኔታው ለዚህ ምቹ በሆነ ስፍራ መቀመጥ ነበረባቸው፡፡ እንደርሱ ባለመሆኑ በዘመን ርዝማኔ የተፈጥሮ ሂደት ሰለባ ሆነዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ምክንያት የአዲስ ኪዳንን መጻሕፍት ተዓማኒነት የሚጠራጠር ምሑር የለም፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ዕድሜ ያለው የመጀመርያው ጽሑፍ የተጻፈበት ቁስ ተጠብቆ ለዚህ ዘመን የበቃ አንድም ጥንታዊ መጽሐፍ መጥቀስ አይቻልም፡፡ ቁርአን እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ከተጠናቀቀ ከስድስት ክፍለ ዘመናት በኋላ የተጻፈ ቢሆንም የመጀመርያዎቹ ጽሑፎቹ ጠፍተዋል፡፡ ጽሑፎቹ በተፈጥሯዊ ምክንያቶች ጠፍተው ቢሆን ኖሮ አሳሳቢ ባልሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን በኡሥማን ትዕዛዝ እንዲቃጠሉ በመደረጋቸው ምክንያት የሆነ ዓይነት ሸፍጥ አለመኖሩን ሙስሊሞች እርግጠኛ መሆን አይችሉም፡፡

ምሑራን የአንድን ጥንታዊ መጽሐፍ ተዓማኒነት ለማረጋገጥ ነፃ በሆነ መንገድ የተገለበጡትን ኮፒዎች ብዛት፣ ጥራትና በመካከላቸው የሚገኘውን ስምምነት ይገመግማሉ እንጂ የመጀመርያው ጽሑፍ የግድ መገኘት አለበት አይሉም፡፡ እንደርሱ ዓይነት መመዘኛ ቢጠቀሙ ኖሮ ከጥንት መጻሕፍት መካከል አንዱም ተዓማኒ ባልሆነ ነበር፡፡

በኮፒዎች ብዛት አዲስ ኪዳን ከእርሱ በፊትም ሆነ በኋላ ከተጻፉት ጥንታውያን ጽሑፎች ጋር ሊነፃፀር በማይችልበት ሁኔታ በእጅጉ የላቀ በመሆኑ ለተዓማኒነቱ አስተማማኝ ዋስትና ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ዕውቅ ክርስቲያን አቃቤ ዕምነት የሆኑት ፕሮፌሰር ጆሽ ማክዱዌል እንዲህ ይላሉ፡-

ከ5,686 በላይ የሚሆኑ የታወቁ የአዲስ ኪዳን የግሪክ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች አሉ፡፡ በተጨማሪም 10,000 የላቲን ቩልጌቶችና ሌሎች 9,300 ቀዳሚያን ቅጂዎች፣ በአጠቃላይ ከዚያ ካልበለጡ ወደ 25,000 የሚሆኑ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች አሉ፡፡ ከጥንት መዛግብት መካከል አንዱም እንኳ ይህንን ያህል ቁጥርና የማረጋገጫ ብዛት ወደ ማስመዝገብ የቀረበ የለም፡፡ በንፅፅር 643 የእጅ ጽሑፎች ብቻ ያሉት የሆሜር ኢሊያድ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ (Josh McDowell, Evidence That Demands a Verdict, p. 34)

ከነዚህ እውነታዎች በመነሳት ለአቶ ሐሰን ተከታዮቹን ጥያቄዎች እናቀርባለን፤ በማስረጃ የተደገፈ ምላሽም እንዲሰጡን እንጠይቃቸዋለን፡-

  1. የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ዕድሜ ያለው በኩረ ጽሑፉ (autograph) ተጠብቆ ያለ አንድ መጽሐፍ ይጥቀሱልን፡፡
  2. በእጅ ጽሑፎች ሥልጣን ከመጽሐፍ ቅዱስ የላቀ ጥንታዊ ጽሑፍ የሚያውቁ ከሆነ ይጥቀሱልን፡፡
  3. የመጀመርያው ጽሑፍ መኖሩ ተመራጭ መሆኑን ከማመን በዘለለ አንድ ጥንታዊ መጽሐፍ ተዓማኒ ለመሆን የመጀመርያው ጽሑፍ መኖሩን እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያነሳ አንድ የታሪክ ምሑር ይጥቀሱልን፡፡
  4. በመሐመድ ዘመን ከተጻፉት ቀዳሚያን የቁርአን ጽሑፎች መካከል እስከ እኛ ዘመን የኖረ አንድ ቁራጭ እንኳ ካለ ያሳዩን፡፡
  5. በመሐመድ ዘመን የተጻፉትን ማሳየት ካልቻሉ ጥያቄውን ቀለል እናድርግሎት፡፡ በአቡበከር ዘመን ተሰብስቦ በሐፍሷ ቤት ተቀምጦ የነበረው ሙሳሒፍ ካለ ያሳዩን፡፡
  6. እርሱንም ማድረግ ካልቻሉ አሁንም እናቅልልሎት፡፡ ከኡሥማን አምስቱ ኮፒዎች መካከል እስከዚህ ዘመን የዘለቀ ካለ ያሳዩን፡፡
  7. ኡሥማን ቀዳሚያን ጽሑፎችን የእሳት ሲሳይ ማድረጉን በዚሁ መጽሐፍዎ ገፅ 25 ላይ አምነዋል፡፡ የሐፍሷ ቅጂ በማርዋን መቃጠሉን ቢክዱም በማስረጃ አስደግፈን ቅጥፈትዎትን አጋልጠናል፡፡ ስለዚህ የቁርአን ጽሑፎች እንደ መጽሐፍ ቅዱስ በተፈጥሯዊ ሂደት ሳይሆን ሆነ ተብለው እንዲወድሙ የመደረጋቸው ምክንያት ምስጢር ለመደበቅ የተደረገ ሸፍጥ አለመሆኑን በማስረጃ ያረጋግጡልን፡፡

አቶ ሐሰን ኦሪጅናል ቁርአን አለመኖሩን ልባቸው እያወቀ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ ያለውን ሙግት ማቅረባቸው የግብዝነት መገለጫ ካልሆነ ሌላ ምን ይባላል? የገዛ ንግግራቸውን ወደ ራሳቸው ብንመልስና እንዲህ ብንላቸውስ ይቀበሉ ይሆን?

አሁን በምድር ላይ ያሉት ቁርአኖች ከኦሪጅናል ጸሐፊዎች ሥራ ለማመሳከር እንዳይሞከር በባለቤቶቹ የእጅ ጽሑፍ የተጻፉት መጽሐፍት ከምድረ ገጽ ጠፍተዋል፡፡ ሁሉም የቁርአን መጽሐፍት በአረብኛ ቋንቋ የተጻፉ ናቸው፡፡ አሳሳቢው ነገር ግን ይህ የአረብኛ እናት መጽሐፍ በኡሥማንና በማርዋን​ ዘመን ተቃጥሎ መጥፋቱና የሙስሊሙ ዓለም ያለ ማጣቀሻ መቅረቱ ነው፡፡

“ከመስታወት በተሠራ ቤት ውስጥ የምትኖር ከሆነ በሌላ ሰው ላይ ድንጋይ አትወርውር” የሚለው የፈረንጆቹ አባባል ልብ ላላቸው ሙስሊሞች ጥሩ ምክር ነው፡፡

 

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ

መጽሐፍ ቅዱስ