ወለድ ኢ-ፍትሃዊ ነውን? በመጽሐፍ ቅዱስስ ተከልክሏልን?

ወለድ ኢ-ፍትሃዊ ነውን? በመጽሐፍ ቅዱስስ ተከልክሏልን?

አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ወለድን እንደሚከለክልና እስላማዊውን “የወለድ አልባ” የባንክ ሥርዓት መቃወማችን ትክክል አለመሆኑን ለማሳየት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ሲጠቅሱ ተመልክተናል፡፡ በነገራችን ላይ በርዕሱ ላይ የጻፍነው ጽሑፍ ብዙ ወገኖች እጅ ገብቶ የመወያያ ርዕስ በመሆኑ ምክንያት ሙስሊም አፖሎጂስቶች መልስ ለመስጠት እየዳከሩ ይገኛሉ፡፡ http://www.ewnetlehulu.net/am/whats-wrong-with-islamic-bank/ አራት ግልፅ ነጥቦችን በማስቀመጥ አቋማችንን እናሳውቃል፡-

  1. “እስላማዊውን” የፋይናንስ ሥርዓት በአገራችን ውስጥ መዘርጋት ምን መዘዞች እንዳሉትና ለምን እንደማያስፈልግ በቀደመው ጽሑፋችን ውስጥ በዐሥር ነጥቦች አሳይተናል፡፡ ሙስሊም ሰባኪያን ከዐሥሩ ነጥቦች መርጠው እየተሟገቱ የሚገኙት “ቁርአናችን አይፈቅድም” በሚለው ላይ ነው፡፡ “ይፈቅዳል ወይንስ አይፈቅድም?” በሚለው ላይ እነርሱ ራሳቸው አልተስማሙም፡፡ ሙስሊሞች ሁሉ ያልተስማሙበትን የጥቂት አክራሪዎችን አቋም የብዙኀኑ ሕዝበ ሙስሊም አቋም አስመስሎ “እስላማዊው አቋም ይህ ነው” ብሎ ማለት ተቀባይነት የለውም፡፡
  2. በእስላማዊው የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ወለድ የለም የሚለው አባባል ግልፅ ቅጥፈት ነው፡፡ እስላማዊ ባንኮች “ወለድ” የሚለውን ቃል ላለመጠቀም ከተበዳሪዎች የሚቀበሉትን ወለድ “ኪራይ” “ትርፍ” ወዘተ. እያሉ ቢሰይሙም ዞሮ ዞሮ ከወለድ ጋር የሚመጣጠን አንዳንዴም የበለጠ ገንዘብ ያስከፍላሉ፡፡ ለዚህ ነው ከገዛ ሊቃውንቶቻቸው መካከል አንዱ እንዲህ ሲል የጻፈው፡- “ዋነኛ የገንዘብ ማንሸራሸርያ ስልታቸው በሆነው በሙራባሃ የገንዘብ ልውውጥ ውስጥ በግዢና በሽያጭ ዋጋዎች መካከል ያለው ልዩነት የሚሰላው ከወለድ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ሲሆን እርሱም ገንዘብ በጊዜ ውስጥ ባለው ዋጋ ነው፡፡ የበለጠ ግልፅ በሆነ መንገድ ለማስቀመጥ ያህል፣ እስላማዊ ባንኮች 95% በሆነው የገንዘብ ልውውጣቸው ውስጥ ወለድን የሚያስከፍሉ ሲሆን በእስላማዊ ካባ የተሸፈነ ነው፡፡ በተለያዩ ሽፍንፍን ዘዴዎች ወለድን ማስከፈላቸው ምርቶችን ለማድበስበስ የታለመ ሲሆን እስላማዊ ባንኮች በማጭበርበርና በማታለል አለመታመንን ያበረታታሉ፡፡ በአላህ ፊት የከፋው ኃጢአት የትኛው ነው? በግልፅ ወለድን ማስከፈል ወይንስ በማጭበርበር ተግባራት ውስጥ ተሳታፊ መሆን?” Muhammad Saleem, Islamic Banking – a $300 Billion Deception (Xlibris, 2005), 68-69.
  3. መጽሐፍ ቅዱስ ወለድን ይከለክላል የሚለው አባባል በአንድ ጎኑ ሲታይ እውነት ቢሆንም በሌላ ጎኑ ግን ውሸት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወለድን የሚከለክሉት ጥቅሶች ለእስራኤላውያን በተሰጡት የብሉይ ኪዳን ትዕዛዛት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በጭፍን ወለድን የሚከለክሉ አይደሉም፡፡ በብሉይ ኪዳን መሠረት እስራኤላውያን አንዳቸው ከሌላቸው ወለድን እንዳይቀበሉ ቢታዘዙም በውጪ አገራት ሰዎች ግን ወለድን መቀበል እንደሚገባቸው ተነግሯቸዋል፡- “ለወንድምህ በወለድ አታበድር፤ የብር ወይም የእህል ወይም የማናቸውንም ነገር ሁሉ ወለድ አትውሰድ። ለእንግዳው በወለድ አበድረው፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር በሥራህ ሁሉ ይባርክህ ዘንድ ለወንድምህ በወለድ አታበድር።” (ዘዳግም 23፡19-20) ያለ ወለድ ማበደር የሚለው ፅንሰ ሐሳብ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ድኾችን አለመበደልና መርዳት ከሚል ፅንሰ ሐሳብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በሒደቱ ውስጥ ድኾች እንዳይበደሉ የተሰጠ ትዕዛዝ እንጂ ወለድ መቀበል ኃጢአት ወይንም ኢ-ፍትሃዊ ስለሆነ አይደለም የተከለከለው፡፡ እንደርሱ ቢሆን ኖሮ ከባዕዳን ወለድ መቀበል ባልተፈቀደ ነበር፡፡
  4. ወለድን ማስከፈል ኢ-ፍትሃዊ ነው የሚለው የአላዋቂዎች አባባል ነው፡፡ ማንኛውም ስለ ምጣኔ ኃብትና ስለ ገንዘብ መሠረታዊ ዕውቀት ያለው ሰው ይህ ሃቅ አይጠፋውም፡፡ የገንዘብ ዋጋ የሚሰላው በጊዜ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የዛሬ ዐሥር ዓመት የነበረው የ100,000 ብር ዋጋና ዛሬ ያለው ዋጋ እኩል አይደለም፡፡ ምናልባትም ከግማሽ በላይ ዋጋው ወርዶ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው የዛሬ ዐሥር ዓመት ያበደረው ወይንም ባንክ ያስቀመጠው ገንዘብ ዛሬ ያለ ምንም ጭማሪ ተመላሽ ቢሆንለት ኪሳራ ውስጥ ይገባል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ገንዘብ በጊዜ ውስጥ ያለውን ዋጋ እንዲሁም ተያያዥ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ወለድ መቀበል ፍትሃዊ እንጂ ኢ-ፍትሃዊ አይደለም፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ለድኻ ጎረቤቶቻችን በእምነት ቢመስሉንም ባይመስሉንም በወለድ አናበድርም፡፡ ይህ የህሊናና የክርስቲያናዊ ስነ ምግባር ጉዳይ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን እንዲያውም ብድር ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ስናበድር እንደሚመለስልን ተስፋ በማድረግ ሳይሆን እንደ ስጦታ እንድናበድር ነው የሚያስተምረን (ሉቃስ 6፡35)፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ማሰብያ አእምሮ ስለሰጠን ገንዘባችንን ባንክ ስናስቀምጥ ወለድ የመቀበል ፍትሃዊ መብታችንን እንጠቀማለን፤ ምክንያቱም ተቋማቱ በገንዘባችን ለመጠቀም የተደራጁ ነጋዴዎች እንጂ ድኾች አይደሉምና፡፡ ፍትሃዊ ወለድ ከሚያስከፍሉ የፋይናንስ ተቋማትም እንበደራለን፤ ምክንያቱም ድኻ አደጎችን ለመርዳት የተቀመጡ እጓለ ሙታን አይደሉምና፡፡ ድኾችን መርዳትን ታሳቢ ያደረገውንና በእስራኤላውያን መካከል ብቻ የተወሰነውን የብሉይ ኪዳንን የወለድ ክልከላ ሕግ ከዚህ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም፡፡ ሙስሊም የፋይናንስ ተቋማትም ቢሆኑ ይህንን ሊካድ የማይችል የምጣኔ ኃብት እውነታ ስለተገነዘቡ “ወለድ” የምትለዋን ስም ላለመጠቀም በተለያዩ ዘወርዋራ ዘዴዎችና ስያሜዎች ከወለድ ጋር የሚመጣጠን አንዳንዴም የሚበልጥ ክፍያን ያስከፍላሉ፡፡ ቀደም ባለው ጽሑፋች እንደገለፅነው የእስላማዊ ፋይናንስ ተቋማት ዓላማ የወለድ ጉዳይ አይደለም፡፡ አጀንዳቸው ክርስቲያኑንም ሆነ ሙስሊሙን የማይጠቅም ሙስሊሞችን ከሌላው ማሕበረሰብ ለመነጠል ያለመ ዓለም አቀፍ የአክራሪዎች አጀንዳ ነው፡፡ ስለዚህ በፅኑ እናወግዛለን፡፡

 

የእስላማዊ ባንክ አሉታዊ ገፅታዎች