መሐመድና ጥቁር ሴት
የዘረኛ ሰው የህልም ትርጓሜ
መሐመድ ለጥቁሮች ከፍተኛ ንቀት እንደነበረውና የዘረኝነት አንድምታ ያላቸውን ንግግሮች መናገሩን እንዲሁም አድሏዊ ተግባራትን መፈፀሙን ከዚህ ቀደም ተመልክተናል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ይህንኑ የሚያጠናክር ተጨማሪ ማስረጃ እናስነብባችኋለን፡፡ ተከታዮቹ ዘገባዎች ሙስሊሞች ከቁርአን ቀጥሎ ከፍተኛ ቦታ በሚሰጡት ሳሂህ አል-ቡኻሪ በተሰኘው የሐዲስ ስብስብ ውስጥ የሚገኙ ናቸው (“ሳሂህ” ማለት የታመነ ወይም ትክክለኛ ማለት ነው)፡-
አብደላህ እንዳወራው ነቢዩ እንዲህ አሉ፣ “(በህልም) አንዲት ፀጉሯ ያልተበጠረ ጥቁር ሴት ከመዲና በመውጣት በመሐኢዓ ማለትም በአል-ጁፋ ስትቀመጥ አየሁ፡፡ የመዲና የበሽታ ወረርሽኝ ወደዚያ ቦታ (አል-ጁፋ) መዛመቱ ነው ብዬ ተረጎምኩት፡፡” (ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 9፣ መጽሐፍ 87፣ ቁጥር 161)
ነቢዩ በመዲና ሆነው ስላዩት ህልም አብዱላህ ቢን ዑመር እንዳወራው፤ ነቢዩ እንዲህ አሉ “(በህልም) አንዲት ፀጉሯ ያልተበጠረ ጥቁር ሴት ከመዲና በመውጣት በመሐኢዓ ስትቀመጥ አየሁ፡፡ የመዲና የበሽታ ወረርሽኝ ወደ መሐኢዓ ማለትም ወደ አል-ጁፋ የመዛመቱ ምልክት ነው ብዬ ተረጎምኩት፡፡” (ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 9፣ መጽሐፍ 87፣ ቁጥር 162)
ተመሳሳይ ዘገባ ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 9፣ መጽሐፍ 87፣ ቁጥር 163 ላይ ይገኛል፡፡
እንዲህ ያለ ንግግር በአንድ ተራ ሰው ቢነገር አቅልሎ ማለፍ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከፈጣሪ ዘንድ የተላከ እንደሆነ በተነገረለት “ነቢይ” መነገሩና በመንፈሳዊ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ መገኘቱ ጉዳዩን በቸልታ እንዳናልፈው ያስገድደናል፡፡ የዘረኝነት ምስል ከሳች የሆኑ መሰል ንግግሮች በቢሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ሲደመጡና ለክፍለ ዘመናት ሲነገሩ የሚያሰርፁት ዘረኛ አመለካከት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህንን ንግግር የሰማና አምኖ የተቀበለ ሰው ፀጉሯ የተንጨባረረ ምስኪን ጥቁር ሴት ሲመለከት የሚፈጠርበትን መጥፎ ስሜት ማሰብ አያዳግትም፡፡ ፈጣሪ ጥበበኛና ሁሉን አዋቂ በመሆኑ እንዲህ ያለ አደገኛ መዘዝ ያለውን ሕልም አያሳይም፡፡ የበሽታ ወረርሽኝ ከአንዱ ወደ ሌላ ቦታ መዛመቱን “ለነቢዩ” ማሳየት ቢፈልግ የሆነ ዓይነት አስፈሪ አውሬ ወይም ዕብድ ውሻ ሊያሳየው እየቻለ ሴትን የመሰለች የከበረች ፍጥረት “ጥቁርና ፀጉሯ የተንጨባረረ” የሚል ዘረኛ መግለጫ አክሎ ማሳየት ለምን አስፈለገ? በዚህ ህልምና በፍቺው ውስጥ የመሐመድ ዘረኛ አመለካከት እንጂ የፈጣሪ ጥበብና ዕውቀት አይታይም!
መሐመድ ለጥቁሮች የነበረው ንቀት በእስልምና የሰው ልጆች እኩል ናቸው የሚለውን ተረት ውድቅ የሚያደርግ ማስረጃ