የኡሥማን ቁርኣንን የማረም ሒደት ከጥርጣሬ የፀዳ ነበርን?

የኡሥማን ቁርአንን የማረም ሒደት ከጥርጣሬ የፀዳ ነበርን?

ተከታዩ ጽሑፍ ሐሰን ታጁ ቁርአን በኸሊፋ ኡሥማን ዘመን የተሰበሰበበትን በብዙ አጠራጣሪ ክንውኖች የተከበበውን ሒደት ከጥርጣሬ የጸዳ ለማስመሰል በመጽሐፋቸው ውስጥ ላሰፈሩት ሙግት የሰጠነው ምላሽ ነው፡፡

ሐሰን ታጁ በኡሥማን ዘመን ስለተደረገው ቁርአንን የማረምና የማስተካከል ሥራ ያቀረቡት ሐተታ በአሳሳች ምልከታዎች የተሞላ ነው፡፡ ኡሥማን ቁርአንን ለምን ማረም እንዳስፈለገው ሲገልፁ እዲህ ብለዋል፡-

የእስልምና ግዛት እያደር እየሰፋ፤ ለአረብኛ ቋንቋ እንግዳ የሆኑ ሕዝቦች የሙስሊሙን ኡምማህ እየተቀላቀሉ ሄዱ፡፡ በዚያ ወቅት ቁርአን በመጽሐፍ መልክ ተዘጋጅቶ ያልተበተነና በቃል የሚተላለፍ በመሆኑ የንባብ ስልት ለአዳዲስ ሰላሚዎች ማስቸገሩ እና ልዩነትም መፈጠሩ አልቀረም፡፡ በአርመንያና በአዘርቤጃን ዘመቻ ላይ የተሳተፈው ሁዘይፋህ ቢን አልየማን በቁርአን የንባብ ስልት ላይ የተከሰተውን ልዩነት ማስተዋሉ አልቀረም፡፡ በዚህ ሳቢያ የደረሰውን መወዛገብም አስተዋለ፡፡ እናም ኡሥማን ዘንድ በመቅረብ እንዲህ ሲል ተማፀናቸው፡- ‹‹ሕዝበ ሙስሊሙ ልክ እንደ አይሁዶችና ክርስቲያኖች በሃይማኖት መጽሐፉ ከመወዛገቡ በፊት አንዳች መላ ዘይዱ፡፡›› (ገፅ 22-23)

ሙስሊሙ ማሕበረሰብ በቁርአን ላይ መለያየት የጀመረው ለአረብኛ ቋንቋ እንግዳ የሆኑ ሕዝቦች በመስለማቸው ምክንያት ብቻ ሳይሆን በዋናነት የመሐመድ ባልደረቦች ይጠቀሟቸው የነበሩ የተለያዩ እርስ በርሳቸው የማይስማሙ ቁርአኖች በመሰራጨታቸው ነበር፡፡ የኢራቅና የሦርያ ሙስሊሞች ለጂሃድ በአርመንያና በአዘርባጃን ድንበር ላይ በተገናኙ ጊዜ ‹ትክክለኛው የቁርአን ቅጂ የቱ ነው?› በሚለው ጥያቄ ላይ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ከሦርያ የመጡ የሁምስ ሙስሊሞች የአል ሚቅዳድ ኢብን አል-አስዋድን ቅጅ ይቀበሉ የነበረ ሲሆን የተቀሩት የሦርያ ሙስሊሞች ደግሞ የኢብን ከዕብን ቅጂ ይከተሉ ነበር፡፡ በኢራቅ የነበሩት የበስራ ሙስሊሞች የአቡ ሙሳን ንባብ ይከተሉ የነበረ ሲሆን የኩፋ ሙስሊሞች ደግሞ የኢብን መስዑድን ይከተሉ ነበር፡፡[1] ስለዚህ የመለያየቱ አብይ መንስኤ የተለያዩ የቁርአን ቅጂዎች መሰራጨት እንጂ የአረብኛ ቋንቋ ችግር አልነበረም፡፡ የኡሥማን ዓላማ የግጭት መንስኤ የሆኑትን እነዚያን የተለያዩ የቁርአን ቅጂዎች በማስወገድ ወጥ የሆነ የንባብ ሥልት ያለውን አንድ ቅጂ ማዘጋጀት ነበር፡፡

ከእስላማዊ ድርሳናት ከምናገኛቸው መረጃዎች በመነሳት የኡሥማን የእርማት ሥራ እጅግ አጠራጣሪ የሚሆንባቸውን ብዙ ምክንያቶች መጥቀስ እንችላለን፡-

  1. የኡሥማን ቅጂ በአቡበክር ዘመን በዘይድ ተዘጋጅቶ በዑመር እጅ በነበረውና የዑመር ልጅ ሐፍሷ[2] በወረሰችው ጥራዝ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡[3] የዚያ ጥራዝ የአሰባሰብ ሂደት እጅግ አጠራጣሪ መሆኑን ቀደም ሲል ተመልክተናል፡፡
  2. ዘይድ የመሐመድ ጸሐፊ የነበረ ቢሆንም ቁርአንን እንዲያስተምሩ በመሐመድ ዕውቅና ከተሰጣቸው አራቱ አነብናቢዎች መካከል አልነበረም፡፡ አራቱ አነብናቢዎች አብዱላህ ኢብን መስዑድ፣ ሰሊም፣ ሙዓዝና ኡበይ ቢን ከዕብ ነበሩ፡፡[4] ቁርአንን እንዲያስተምሩ በመሐመድ ዕውቅናና ሥልጣን የተሰጣቸው ግለሰቦች እያሉ ዘይድ ለዚህ ሥራ መመረጡ ጥያቄን ያጭራል፡፡
  3. ቁርአንን የማነብነብ ብቃቱ በመሐመድ የተመሰከረለትና ቁርአንን እንዲያስተምር ተሹሞ የነበረው ኢብን መስዑድ[5] ከኮሚቴው ውስጥ እንዲገለል ተደርጎ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳም ቅሬታውን እንዲህ በማለት ገልፆ ነበር:-

“ሙስሊሞች ሆይ! ቁርአንን እንዳልጽፍ እኔን በማግለል እስልምናን ስቀበል [ገና ሳይወለድ] በአባቱ አካል ውስጥ በካፊርነት ለነበረው ሰው [ለዘይድ] ኃላፊነት ተሰጠ፡፡”[6]

ኢብን መስዑድ ያቀረበው ይህ ቅሬታ ተገቢ ነበር፡፡

4. ኢብን መስዑድ በኡሥማን ትዕዛዝ በዘይድ ተዘጋጅቶ የነበረውን ቁርአን ጨምሮ ሕዝበ ሙስሊሙ የተጭበረበረ ንባብ የሚከተል መሆኑን በማሳወቅ በግልፅ ተቃውሟል፡፡[7] የኩፋ ሕዝቦች በኡሥማን ውሳኔ የፀደቀውን አዲሱን ቁርአን እንዳይቀበል አድርጓል፡፡[8] በዚህም ምክንያት የኩፋ ሕዝብ አል-ሐጃጅ ኢብን ዩሱፍ አል-ሣቃፊ ሥልጣን እስከያዘበት ዘመን ድረስ የኢብን መስዑድን ቁርአን ተቀብሎ ኖሯል፡፡[9]

5. ኡሥማን በቁረይሽ ዘዬ ከተጻፈው አዲሱ ቁርአን ውጪ ሌሎች ቁርአኖችን በማቃጠል እንዲወድሙ በማድረጉ በዘመኑ በነበሩት ሙስሊሞች ዘንድ ተነቅፏል፡፡ “ቁርአንን የቀደደ ሰው” እስከመባልም ደርሷል፡፡[10]

6. ኡሥማን የቀደሙትን ቁርአኖች አቃጥሎ የእርሱን ብቻ ኦፊሴላዊ በማድረጉ ምክንያት የመረጃ ስወራ አለመኖሩን እርግጠኞች ሆነን መናገር አንችልም፡፡

7. ኡሥማን አዲሱን ቁርአን ኦፊሴላዊ በማድረግ ሌሎችን ቢያቃጥልም የሐፍሷን ቁርአን ሳያቃጥል በመመለሱና በሌሎች አነብናቢዎች የተዘጋጁትን ቁርአኖች በሙሉ ሳያጠፋ በማለፉ ምክንያት ሌሎች የቁርአን ቅጂዎች በድጋሚ ችግር መፍጠራቸው አልቀረም፡፡ የእነዚህ ንባቦች የተወሰኑ ክፍሎች ኢብን አቢ ዳውድ አል ሲጂስታኒና አቡ አል-ፈሥ ዑሥማንን የመሳሰሉ ጥንታውያን ሙስሊም ሊቃውንት በጻፏቸው መጻሕፍት ውስጥ ተጠብቀዋል፡፡ እነዚህ ልዩነቶች ሲገመገሙ በቁርአን ውስጥ ከፍተኛ ለውጦች መደረጋቸውን ያመለክታሉ፡፡[11]

8. ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተገኙት ከኡሥማን ቁርአን ላይ እንደተገለበጡ የሚነገሩት ጥንታዊ የቁርአን ጽሑፎች እርስ በርሳቸው የማይመሳሰሉ ሲሆኑ ብዙ ግጭቶች በመካከላቸው ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ጽሑፎች ማየት የሚፈልግ በግርጌ ማስታወሻው ላይ የተሰጡትን ድረ-ገፆች በመጎብኘት ፎቶግራፎቹን ማግኘት ይችላል፡፡[12]

ከላይ ከጠቀስናቸው ነጥቦች አኳያ ሐሰን ታጁ የቁርአን አሰባሰብ ጥርጣሬን ሊያጭሩ ከሚችሉ ነገሮች የፀዳ መሆኑን ለማሳየት በመጽሐፋቸው ውስጥ ገፅ 18-27 ያሠፈሯቸው ሐሳቦች በሙሉ ውድቅ ናቸው፡፡ ቁርአን በመሐመድ ዘመንም ሆነ በኸሊፋዎች ዘመን በትክክል መጠበቁን እንድናምን የሚያስችል ማስረጃ የለም፡፡ በእስላማዊ ድርሳናት ውስጥ ሰፍረው የሚገኙት ማስረጃዎች ከዚያ በተፃራሪ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡


[1] The Qur’an Dilemma; Vol. 1, p. 52

[2] ሐፍሷ የሁለተኛው ኸሊፋ የዑመር ኢብን አል-ኸጧብ ልጅ ስትሆን ከነቢዩ መሐመድ ሚስቶች መካከል አንዷ ነበረች፡፡

[3] Sahih al-Bukhari, vol. 6, bk 61, no. 510

[4] Sahih al-Bukhari, Vol. 6, Bk 61, no. 521

[5] Ibid.

[6] Ibn Abi Dawud al-Sijistani. p. 24-25; Cited in: The Qur’an Dilemma; Vol. 1, p. 54

[7]  Ibn Sa’d’s Kitab al-Tabaqat al-Kabir, English translation by S. Moinul Haq, M.A., PH.D assisted by H.K. Ghazanfar M.A. [Kitab Bhavan Exporters & Importers, 1784 Kalan Mahal, Daryaganj, New Delhi- 110 002 India], Volume 2, p. 444

[8] Nöldoke, Tarikh al-Qur’ān 280, 339; Cited in: The Qur’an Dilemma; Vol. 1, p. 54

[9] Encyclopedia of the Qur’ān Vol. 1, p. 348; Cited in: The Qur’an Dilemma; Vol. 1, p. 54

[10] Ibn Warraq. The Origins of the Koran: Classic Essays on Islam’s Holy Book; Prometheus Books, Amherst NY, 1998, p. 102

[11] The Qur’an Dilemma; Vol. 1, p. 59

[12] http://www.qurantext.net

www.answering-islam.net/PQ/A1.htm#AppendA


በኡስታዝ ሐሰን ታጁ ለተጻፈ መጽሐፍ የተሰጠ መልስ

ቅዱስ ቁርአን