ኢየሱስ አለመሰቀሉን የሚያመለክቱ ጥንታዊ መዛግብት ይገኙ ይኾንን?

ኢየሱስ “አለመሰቀሉን” የሚያመለክቱ ጥንታውያን መዛግብት ይገኙ ይኾንን?

አንዳንድ ሙስሊሞች የክርስቶስን ስቅለት የሚያስተባብል ማስረጃ ያገኙ መስሏቸው የኖስቲሲዝምን ጽሑፎች ሲጠቅሱ እየተመለከትን ነው፡፡ በኢየሱስ ምትክ ሌላ ሰው ተሰቅሏል የሚለው ግምት በእስልምና የተጀመረ አይደለም፡፡ ኖስቲሳውያን የተሰኙ የእምነት ቡድኖች ይህንን ያምኑ ነበር፡፡ ኖስቲሲዝም (Gnosticism) በሁለተኛውና በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ተከታዮችን አፍርቶ የነበረ የኑፋቄ ቡድን ሲሆን አጀማመሩንና የተጀመረበትን ዘመን በተመለከተ በሊቃውንት መካከል ስምምነት የለም፡፡ አንዳንዶቹ ከአይሁድ ኑፋቄያዊ ቡድኖች የተገኘ እንደሆነ ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ ክርስቲያናዊ አውድ ይሰጡታል፡፡ ሙሉ በሙሉ አረማዊ ስረ መሠረት እንዳለው የሚናገሩ ሊቃውንትም አሉ (Geisler, Encyclopedia of Christian Apologetics; p. 504)፡፡ ኖስቲክ (Gnostic) የሚለውን ቃል ለመጀመርያ ጊዜ የተጠቀመው ሄንሪ ሞር የተሰኘ በ17ኛው ክ.ዘ. የኖረ ሰው ሲሆን “ዕውቀት” የሚል ትርጉም ካለው ኖሲስ (Gnosis) ከሚለው የግሪክ ቃል የተዋቀረ ነው (Britannica, Encyclopedia of World Religions; p. 380)፡፡  ኖስቲሲዝም በተሰኘው እምነት ስር የሚመደቡ ብዙ ቡድኖች የሚገኙ ሲሆን ከክርስትና የሚለዩዋቸው ዋና ዋና ትምህርቶቻቸው የሚከተሉት ናቸው፡-

  • የብሉይ ኪዳን አምላክ ከአዲስ ኪዳን አምላክ የተለየ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን አምላክ ክፉና ውሱን ሲሆን የአዲስ ኪዳን አምላክ ሁሉን ቻይ ነው፡፡
  • ፍጥረት የተፈጠረው በሶፍያ (ጥበብ) ውድቀት ምክንያት ነው፡፡
  • ቁስ የተባለ ሁሉ ክፉ ነው፡፡
  • ኢየሱስ በሥጋ አልመጣም፣ በመስቀል ላይ አልሞተም፣ ትክክለኛው ኢየሱስ መንፈስ ነው፡፡
  • የመንፈስ ትንሣኤ እንጂ የሥጋ ትንሣኤ የለም፡፡ (Geisler, p. 504)

ስለ ኖስቲሳውያን ከጥንት ቤተ ክርስቲያን አበው ጽሑፎች ብዙ መረጃዎችን የምናገኝ ሲሆን በ1945 ዓ.ም. ነጅ ሐማዲ በተባለ ቦታ የኖስቲሳውያን እምነቶች የተንጸባረቁባቸው ብዙ መጻሕፍት በመገኘታቸው ምክንያት ስለ እነርሱ ያለን መረጃ ከፍ ብሏል፡፡ ከነዚህ መጻሕፍት መካከል “የቶማስ ወንጌል” የተሰኘው መጽሐፍ ይገኝበታል (Britannica, Encyclopedia of World Religions; p. 380)፡፡  በቁርኣን ውስጥ የሚገኘው ኢየሱስ በህፃንነቱ ከጭቃ ወፍ ሠርቶ ስለማብረሩ የሚናገረው ታሪክ ከዚህ ወንጌል ላይ የተወሰደ ነው (The New Testament Apocrypha, vol. 1, rev. ed. by W. Schneemelcher, trans. R. McL. Wilson, Westminster / John Knox, 1991, p. 444)፡፡

እነዚህ የእምነት ቡድኖች ከክርስትና ያፈነገጡ ሲሆኑ ኢየሱስ ትክክለኛ የሰው አካል እንዳልነበረው የሚያምኑ ናቸው፡፡ ትክክለኛ የሰው አካል ካልነበረው ደግሞ ሊሰቀል አይችልም፡፡ ባሲለደስ የተሰኘ የሁለተኛው ክፍለ ዘመን ኖስቲሳዊ የቀሬናው ስምዖን በኢየሱስ ምትክ መሰቀሉን ጽፏል፡፡ በዚህም መሠረት ስምዖን ሲሰቀል ኢየሱስ አጠገባቸው ቆሞ ሲስቅ ነበር፡፡ ንፁህ ሰው ሲሰቀል ሳለ ኢየሱስ ደግሞ መንፈስ ስለሆነ ስለማያዩት ቆሞ ሲስቅ አስቡት፡፡ እንዲህ ያለውን ተረት ከማስረጃ በመቁጠር የሚያናፍሱ ሙስሊሞች ሕሊናቸውን ከወዴት ጥለውት ይሆን? በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ማኒ የተሰኘ ሦርያዊ ሰው ኢየሱስ ከሞት ያስነሳው የናይን ከተማ መበለት ልጅ በምትኩ መሰቀሉን ጽፏል (Geisler, p. 147)፡፡ እነዚህ ግምቶች እንደ እስላማዊው ግምት ኹሉ በሥነ መለኮታዊ ፍላጎት ላይ የተመሠረቱ ሲሆኑ ምንም ዓይነት ታሪካዊ መሠረት የሌላቸው ከንቱ ተረቶች ናቸው፡፡ በወንጌላት ውስጥ ከተጻፉት የዐይን ምስክሮች ዘገባዎች ጋር ይጣረሳሉ (ማቴዎስ 27፣ ማርቆስ 14፣ ሉቃስ 23፣ ዮሐንስ 19)፤ እንደዚሁም ከቀዳሚያን የሮም፣ የአይሁድና የግሪክ ዘገባዎች ጋር ይጣረሳሉ፡፡ በአንደኛው ክፍለ ዘመን በክርስትና ወዳጆችም ሆነ ባላንጣዎች የተጻፈ ክርስቶስ መሰቀሉን የሚክድ ቅንጣት ታክል ዘገባ የለም፡፡ በኢየሱስ ቦታ ሌላ ሰው መተካቱን የሚናገሩ በኖስቲዝም ተፅዕኖ ያደረባቸው ግለሰቦች የጻፏቸው ጽሑፎች ከ150 ዓመታት በኋላ ነበር መታየት የጀመሩት (Geislere, p. 147)፡፡

ኖስቲሳውያን ኢየሱስ የሚዳሰስ አካል እንደሌለው ስለሚያምኑ ሊሰቀል አይችልም ይላሉ፤ ነገር ግን ደግሞ የስቅለቱ ትዕይንት መፈፀሙን መካድ ስለማይችሉ በምትኩ ሌላ ሰው መሰቀሉን በመናገር ደካማ እምነታቸውን ከታሪካዊ ዘገባ ጋር ለማስታረቅ ሞክረዋል፡፡ ኖስቲሳውያን የዚህ ዓለም ፈጣሪ ክፉ አምላክ (ዲያብሎስ) እንደሆነ ያስተምራሉ፡፡ ሙስሊሞች ኢየሱስ የሚዳሰስ አካል እንዳልነበረው የሚያምኑትንና ፈጣሪያቸው ሸይጧን መኾኑን የሚያስተምሩትን የእምነት ቡድኖች ግምት የክርስቶስን ስቅለት ከሚያሳዩት የተትረፈረፉ ዘገባዎች ይልቅ እንደ ተዓማኒ ማስረጃ መቁጠራቸው በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ “የጨነቀው ዱቄት ከንፋስ ጋር ይወዳጃል” አሉ!

ቅዱስ ቁርኣን