ኢየሱስን የሰቀሉት ሰዎች ኃጢኣተኞች ናቸው ወይንስ አይደሉም?
አንዳንድ ሙስሊሞች “ኢየሱስን የሰቀሉት ሰዎች ኃጢኣተኞች ናቸው ወይንስ አይደሉም?” በሚል ጥያቄ ግራ ሲጋቡ ስለታዘብን ተከታዩን ምላሽ ልንሰጣቸው ወደድን፡፡
በእርግጥ እነዚህ ወገኖች “The end justifies the means” ወይንም ደግሞ በሀገርኛ “የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው” የሚል ዓይነት ፍልስፍና ባለው የእስልምና አስተምህሮ የተቃኘ ዕይታ ስላላቸው እንጂ ይህ እንደ ጥያቄ ሆኖ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይም አልነበረም፡፡ በእስልምና አንድ ሙስሊም የሚፈፅመው መጥፎ ተግባር ውጤቱ ለሙስሊሙ ማሕበረሰብ ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ የሠራው መጥፎ ሥራ ሳይሆን ውጤቱ ነው የሚታይለት፡፡ ይህንን ጉዳይ በተለይም ለመልካም ውጤት ሲባል ውሸትን ከመናገር አስፈላጊነት ጋር አያይዘው ብዙ ሙስሊም ሊቃውንት በስፋትና በጥልቀት ያስተምራሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል አል-ገዛሊ የተሰኘ የመካከለኛው ዘመን ሙስሊም ፈላስፋ እንዲህ በማለት ጽፏል፡-
“ንግግር ዓላማን የማሳክያ መንገድ ነው፡፡ እውነትን በመናገርና በመዋሸት በሁለቱም መንገዶች ምስጋና የተገባው ግብ ከተመታ በመዋሸት ማሳካት የተፈቀደ አይደለም ምክያቱም መዋሸት አስፈላጊ አይደለምና፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱን ዓላማ ማሳካት የሚቻለው እውነት በመናገር ሳይሆን በመዋሸት ከሆነና ያ ግብ የተፈቀደ ግብ (ሐላል) ከሆነ በመዋሸት ግቡን መምታት የተፈቀደ ነው… እንዲሁም ግቡን መምታት ግዴታ ከሆነ በመዋሸት ግቡን መምታት ግዴታ ነው፡፡” (‘Umdat al-Salik “The Reliance of the Traveller”, see section ‘LYING’)
ነገር ግን በክርስትና አንድ ሰው የሥራው ውጤት ብቻ ሳይሆን የልቡ ፍላጎት (Intention) እና የተጠቀመበት መንገድም ጭምር ይታያል፡፡ አይሁድ ኢየሱስ እንዲሰቀል ለሮማውያን አሳልፈው ሲሰጡት በብሉይ ኪዳን ትንቢት የተነገረለት ከሰማይ የመጣ የእግዚአብሔር ልጅ፣ መሲህ መሆኑን በመካድና እርሱን ለማጥፋት በማሰብ ነበር፡፡ ስለዚህ ኃጢኣተኞች ናቸው፡፡ በወቅቱ የይሁዳ አስተዳዳሪ የነበረው ጳንጥዮስ ጲላጦስ የተሰኘው ሮማዊ ገዢ ሊፈታው ቢፈልግም “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን!” በማለት ጮኸው ነበር (ማቴ 24፡25)፡፡ ያንን ከተናገሩ ከ37 ዓመታት በኋላ በራሳቸው ላይ የጠሩት እርግማን ደርሶባቸዋል፡፡ አይሁድ እርሱን ለሮማውያን አሳልፈው በመስጠታቸው ምክንያት እንደሚፈረድባቸው ጌታ ኢየሱስ እራሱ ተናግሯል (ዮሃ 19፡11)፡፡ የዚህም ምክንያቱ የኢየሱስ መሰቀል እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የተፈፀመ ባለመሆኑ ሳይሆን ቀደም ሲል እንዳልነው በአይሁድ ክፉ የልብ መሻትና ክህደት ምክንያት ነው፡፡
በእግዚአብሔር ሉኣላዊ ሥልጣን የሚያምን ሰው እግዚአብሔር ሰዎች ለክፉ በማሰብ የሠሩትን ሥራ ለበጎ መጠቀም እንደሚችል ማመን አይከብደውም፡፡ አይሁድ ያሰቡት ሌላ ቢሆንም እግዚአብሔር ግን ዘላለማዊ ዓላማውን ለማስፈፀም ተጠቅሞበታል፡፡ ለምሳሌ ያህል ሙስሊሞችም ሆኑ ክርስቲያኖች የሚያውቁትን የኢዮብን ሕይወት እንወሰድ፡፡ ሰይጣን ኢዮብን ሲፈትነው ሊያጠፋው በማሰብ ነበር ነገር ግን እግዚአብሔር የኢዮብን እምነት ለመግለጥና ለሰው ልጆች ሁሉ ምሳሌ ሊያደርገው እንዲሁም ኢዮብን ወደ በለጠ ክብር ለማምጣት ተጠቅሞበታል፡፡ የኢዮብ መፈተን ውጤቱ ለበጎ መሆኑ ሰይጣንን ከክፋቱ ነፃ አያደርገውም፡፡ ሰዎችም ሆኑ ሰይጣን ለክፋት ያሰቡትን መንገድ የገዛ ዓላማውን ለማስፈፀም በመጠቀም የክፋት ግባቸውን ማክሸፍ የእግዚአብሔር ሉኣላዊ ሥልጣን ነው፡፡ አይሁድ ኢየሱስን ለማጥፋት ነበር ለሮማውያን አሳልፈው የሰጡት ነገር ግን የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ዓላማ አልተረዱም ነበር፡፡ እነርሱ ለክፉ ያሰቡትን እግዚአብሔር ግን ለበጎ በመጠቀም የዓላማው ማስፈፀምያ አድርጎታል፡፡ ክብር ለስሙ ይሁን!
ሙስሊም ወገኖቻችን የዚህን ሙግት ከንቱነት መረዳት ይችሉ ዘንድ ተከታዩን እምነታቸውን እንዲያውጠነጥኑት እንጠቁማቸዋለን፡፡ አንድ ሙስሊም በአላህ መንገድ በጂሃድ እየታገለ ሳለ ቢሞት በቀጥታ ወደ ገነት ይገባል የሚል እምነት የብዙ ሙስሊሞች ነው፡፡ ስለዚህ አንድን ሙስሊም ጂሃዲስት በመግደል በቀጥታ ወደ ገነት እንዲገባ የሚረዳው ሰው ጂሃዲስቱን በመግደሉ ኃጢኣተኛ ነው ወይንስ አይደለም? ለምን?
በአሁኑ ዘመን ክርስቶስ እንዳልተሰቀለ የሚያምኑ ብቸኛ ሕዝቦች ሙስሊሞችና የእነርሱ ትምህርት ተፅዕኖ ያሳደረባቸው ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ቁርኣን ኢየሱስ እንዳልተሰቀለ በመናገር በዘመኑ ከነበሩት የታሪክ ምንጮች ሁሉ ጋር ስለተጋጨ ይህንን የቁርኣን ቅጥፈት ለማስተባበል ሙስሊሞች ያልተጠቀሙት መንገድ የለም፤ እስከ ዛሬ ድረስ አልተሳካላቸውም እንጂ፡፡ የክርስቶስ ስቅለት በነቢያት የተተነበየ (ኢሳይያስ 53)፣ በደቀ መዛሙርቱ የተዘገበ (አዲስ ኪዳን) እና በመጀመርያው ክፍለ ዘመን የታሪክ ምንጮች የተረጋገጠ (ጆሲፈስ፣ ፕሊኒ ትንሹ፣ ማራ በር ሴራፒዮን፣ የባቢሎናውያን ታልሙድ፣ ወዘተ) እውነታ ነው፡፡ ሙሐመድ ግን ነገሩ ከተፈፀመ ከ600 ዓመታት በኋላ ወደ ሒራ ዋሻ ገብቶ በመውጣት “ክርስቶስ አልተሰቀለም” አለ፡፡ ማስረጃው ደግሞ “መልአክ ተናገረኝ” የሚል ነበር፡፡ ውሸታሙ ማነው? የክርስቶስን ስቅለት አስቀድመው የተነበዩት ነቢያት፣ መሰቀሉን አይተው የመሰከሩት ሐዋርያት፣ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን የነበሩት የታሪክ ሊቃውንት ወይንስ ከ600 ዓመታት በኋላ ወደ ዋሻ ገብቶ በመውጣት ይህንን ሁሉ ማስረጃ የካደው ሙሐመድ? መልሱን ለህሊናችሁ፡፡