ስንት ሰዓት ተሰቀለ? በስንተኛው ቀንስ ተነሳ? ለሙስሊሞች ሙግት የተሰጠ ምላሽ

ስንት ሰዓት ተሰቀለ? በስንተኛው ቀንስ ተነሳ?

ለሙስሊሞች ሙግት የተሰጠ ምላሽ

ሰሞኑን አንድ ሰለምቴ ነኝ ባይ ሙስሊም አፖሎጂስ የክርስቶስን ስቅለት በተመለከተ የጻፈውን ጽሑፍ አንዳንድ ወገኖች ሲቀባበሉት አይቼ ነበር፡፡ ጸሐፊው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተጻፉትን ዘገባዎች በማጋጨት “አልተሰቀለም” የሚለውን እስላማዊ የታሪክ ስህተት ለማጽደቅ ይሞክራል፡፡ እርሱ ያልተገነዘበው አንድ ነገር ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት መሆኑ ቀርቶ መጽሐፍ ቅዱስ የሚባል መጽሐፍ እንኳ ባይኖር እስልምናን ከታሪካዊ ስህተቱ ማዳን የሚችልበት ዕድል አለመኖሩን ነው፡፡ የክርስቶስ ስቅለት በመጀመርያውና በሁለተኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ በኖሩት የግሪክ፣ የሮም፣ የአይሁድና የክርስቲያን ጸሐፊያን የተዘገበና የተረጋገጠ በመሆኑ የክርስቶስን ስቅለት የሚክዱ ሙስሊሞች ከታሪክ መዛግብት ጋር ይላተማሉ፡፡ የክርስቶስን ስቅለት የሚክድ በሊቃውንቱ ዓለም ቦታ የሚሰጠው የታሪክ ምሑር ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችን ግን ከክርስቶስ ስቅለት ከ600 ዓመታት በኋላ ወደ ዋሻ ገብቶ በመውጣት የክርስቶስን ስቅለት በተመለከተ ለብዙ ትርጎሞች የተጋለጠ የተምታታ ንግግር የተናገረውን የሙሐመድን ቃል እውነት ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማይባጥጡት ተራራ የለም፡፡ ይህንን ለማድረግ ከሚጣጣሩባቸው መንገዶች መካከል አንዱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ስቅለትና ስለ ትንሣኤ የተጻፈውን ዘገባ እርስ በርስ ማጋጨት ነው፡፡ ይህ ጸሐፊ እንዲህ በማለት ይጀምራል፡-

የአዲስ ኪዳን ምሁር ሄርማን ቻርለስ በ 1890 AD ሲናገሩ፦ 5,800 የሚደርሱ የአዲስ ኪዳን ግሪክ እደ-ክታባት ይገኛሉ፤ እነዚህ እደ-ክታባት እርስ በእርሳቸው የቃላት ሆነ የትርጉም ልዩነት አላቸው፤ ለምሳሌ በሳይናቲከስና በቫቲካነስ እደ-ክታባት መካከል የ 3,036 የቃላትና የትርጉም ልዩነት አላቸው ብለዋል፤ ይህ ልዩነት የመጣው የአዲስ ኪዳን ስረ-መሰረት”netion” ስለሌለና አሁን ያለት እደ-ክታባት የቅጂዎች ቅጂ ስለሆነ እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ፤ ይህ ልዩነት ጤናማ አለመሆን ብቻ ሳይሆን የክርስትናን ዶግማ ክፉኛ ይፈታተናል፤ ምክንያቱም እነዚህን አራት ወንጌላት ሃዋርያት አለመፃፋቸው ብቻ ሳይሆን በእነርሱ የዳቦ ስም የገለበጡት ፅሁፍም ችግር ስላለበት ነው፤ እስቲ ይህንን ልዩነት ዛሬ በስቅለቱ ዙሪያ ያሉትን ዘገባዎች እንመልከት፦

ርዕሱ ስለ ክርስቶስ ስቅለት ሆኖ ሳለ ወደ ቴክስቹዋል ክሪቲሲዝም መዝለልህ አስገራሚ ነው፡፡ የክርስቶስን ስቅለት ከዚህ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም፡፡ የዘመናችን ዕውቅ ቴክስቹዋል ክሪቲክና የሙስሊሞች ተወዳጅ የክርስትና ተቃዋሚ ባርት ኤህርማን እንኳ የክርስቶስን ስቅለት አጥብቆ ያምናል፣ የክርስቶስን ህልውና በሚክዱ ወገኖች ላይም ሲሳለቅ በተደጋጋሚ ይታያል፡፡ የክርስቶስን ስቅለት ከቴክስቹዋል ክሪቲሲዝም ጋር አገናኝቶ ሲክድና አጠራጣሪ አድርጎ ሲመለከት አንድም ጊዜ አልታየም፡፡ ስለ ቴክስቹዋል ክሪቲሲዝም እንነጋገር ከተባለ ራሱን በቻለ ርዕስ መነጋገር ይቻላል፤ በዚያውም በቶፕካፒና በሰመርቃንድ ቁርአኖች መካከል ስለሚገኙት ከ 2000 በላይ ስለሆኑት ልዩነቶች፣ በሰነዓ የቁርኣን ማኑስክሪፕቶች ውስጥ ስለሚገኙት ስርዝ ድልዞች፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የተሰራጨው የአረብኛ ቁርኣን የሐፍስ ቅጂ ስለመሆኑና ሐፍስ ደግሞ ሐሰተኛ ሰው በመሆኑ ምክንያት እርሱ የዘገባቸው ሐዲሶች ተቀባይነት ስለማጣታቸው፣ በዚህ ዘመን በዓለም ላይ ከ26 በላይ የአረብኛ ቁርአኖች ስለመኖራቸውና በሺዎች የሚቆጠሩ ልዩነቶችን ስለማሳየታቸው፣ ወዘተ. ታብራራልናለህ፡፡ ኦሪጅናሉም ቁርኣን ከኡሥማን የማቃጠል ዘመቻ ተርፎ እንደሆን ታረጋግጥልናለህ፡፡ የማይገናኝ ነገር በማገናኘት ማምታታት ለመግባባት ስለማይጠቅመን እንዲህ ያለ አካሄድ ብትተው ጥሩ ነው፡፡

ነጥብ አንድ

“የቤተ መቅደስም መጋረጃ”

የሉቃስ ዘጋቢ ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ ህይወቱን የሰጠው የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ከተቀደደ በኃላ እንደሆነ ይተርካል፦

ሉቃስ 23፥45-46 “የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ”። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፦ አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ።

የማቴዎስ ዘገቢ ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ ህይወቱን የሰጠው የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ከመቀደዱ በፊት እንደሆነ ይተርካል፦

ማቴዎስ 27፥ 50-51 ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ። እነሆም፥ “የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ”፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤

ጥያቄአችን፦ የቱ ትረካ ነው ትክክል? ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ ህይወቱን የሰጠው የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ከተቀደደ በኃላ እንደሆነ የሚተርክልን የሉቃስ ዘጋቢ ወይስ ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ ህይወቱን የሰጠው የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ከመቀደዱ በፊት እንደሆነ የሚተርክልን የማቴዎስ ዘጋቢ?

አሁን እንዲህ ያለ ጥያቄ አንድን ታሪካዊ ክስተት ለማስተባበል የሚቀርብ ነው? ሲጀመር እነዚህ ነገሮች ሁሉ የተከናወኑት በአንድ ጊዜ (Simultaneously) በመሆኑ በየትኛውም ቅደም ተከተል ብትጽፋቸው ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡ የቤተ መቅደስ መጋረጃ የተቀደደው ኢየሱስ ነፍሱን በሰጠበት በዚያው   ቅፅበት ነበር፡፡ ሙግትህ ሚዛን አይደፋም፡፡ ቅደም ተከተል ሊያሳስብህ የሚገባው እንዲህ ፈጣን የሆኑ ክስተቶች በተስተናገዱበት ሁኔታ ሳይሆን ክስተቶቹን በቅደም ተከተላቸው መሠረት ማየት በአጠቃላይ ታሪካዊ ሒደቱ ተዓማኒነት ላይ ተፅዕኖ በሚያመጣበት ሁኔታ ነው፡፡ ትርጉም ያለው የጊዜ ልዩነት (significant time gap) በሌለበትና የክስተቶቹ ቅደም ተከተል በአጠቃላይ ታሪኩ ተዓማኒነት ላይ ተፅዕኖን በማያመጣበት ሁኔታ በአጉሊ መነፅር ግጭትን መፈለግ ተቀባይነት የለውም፡፡

ነጥብ ሁለት

“በሰቀሉትም ጊዜ”

ቅድሚያ የአራቱ ወንጌላት ተራኪዎች ጊዜን የሚቆጥሩት በዕብራውያን አቆጣጠር ብቻ መሆኑ ሊጤን የሚገባው ጉዳይ ነው፤ የሮማውያን አቆጣጠር አንዳንዶች ይጠቀሙ ነበር የሚለው ቅጥፈት የታሪክ፣ የአውድና የባህል ማስረጃ የለውም፤ ይህ ቅጥፈት ግጭትን ለመደበቅ ሆን ብሎ ግምታዊ ነው፤

የሮማውያን የሰዓት አቆጣጠር አንድ ዓይነት ብቻ እንዳልነበረ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። በዚያን ዘመን ከፀሐይ መውጣት የሚጀምር አቆጣጠ ብቻ ሳይሆን ከአይሁድ የተለየና ከእኩለ ሌሊት የሚጀምር የሰዓት አቆጣጠር ይከተሉ እንደነበር የታወቀ ነው፤ ይህ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ሮማዊ የታሪክ ጸሐፊ በነበረው በአረጋዊው ፕሊኒ ሳይቀር ተዘግቧል (Pliny the Elder, Natural History 2:77)፡፡ ዮሐንስ ደግሞ ወንጌሉን ጽፎ የነበረው ከሮማውያን ዋነኛ ማዕከላት መካከል አንዷ በነበረችው በኤፌሶን ከተማ ከሆነ ሮማውያን ከሚጠቀሟቸው አቆጣጠሮች መካከል ከእኩለ ሌሊት የሚጀምረውን አቆጣጠር መጠቀም ይችላል። በወንጌሉ ውስጥ ይህንን የሮማውያን አቆጣጠር መጠቀሙን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ካሉ የክርስቶስን ስቅለት በተመለከተ የሮማውያንን አቆጣጠር አልተጠቀመም የሚያስብል ምን ምክንያት ይኖራል?

ለምሳሌ ማርቆስ የዕብራዊያን አቆጣጠሩ ኢየሱስ ተሰቀለ የተባለበት በዕብራውያን 3 ሰአት ነው ይለናል፦

ማርቆስ 15፥25 “”በሰቀሉትም ጊዜ” “”ሦስት ሰዓት”” ነበረ።

ማርቆስ 15፥33 “ስድስት ሰዓትም”” በሆነ ጊዜ፥ እስከ “”ዘጠኝ ሰዓት”” በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።

34 “”በዘጠኝ ሰዓትም”” ኢየሱስ፦ ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤

በዚህ ሁለም ይስማማል፤ ኢየሱስ ተሰቀለ የተባለው ከ ቀኑ ጠዋት 3 ሰአት ነው፤ ከዮሐንስ ዘገባ ጋር ፍጭቱን ከማየታችን በፊት ዮሐንስ የሚጠቀመው የዕብራውያን አቆጣጠር መሆኑን በአፅንኦትና በአንክሮት እንመልከት፦

ዮሐንስ 1፥40 መጥታችሁ እዩ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ “አሥር ሰዓት” ያህል ነበረ።

ይህ ዮሐንስ የሮማውያንን አቆጣጠር መጠቀሙን ከሚያሳዩ አጋጣሚዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ አንዳንድ ተርጓሚዎች የተጠቀሰው ሰዓት ከሰዓት በኋላ አሥር ሰዓት እንደሆነ ቢገምቱም በግሪኩ ንባብ ጠዋት ይሁን ከሰዓት አልተነገረም፡፡ አስር ሰዓት (ከኛ አቆጣጠር ጋር ተመሳሳይነት ባለው የአይሁድ አቆጣጠር ከጠዋቱ አራት ሰዓት) የተባለው የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ከኢየሱስ ጋር የተገናኙበት ሰዓት በመሆኑ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ተገናኝተው ቀኑን ሙሉ አብረውት እንደ ዋሉ መናገር ይቻላል፡፡ የአማርኛው ትርጉም ግልፅ ባይሆንም ኪንግ ጀምስና ሌሎች ትርጉሞች ሰዓቱ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን ያገኙበት ሰዓት መሆኑን በሚያመለክት መንገድ ተርጉመውታል፡-

“He saith unto them, Come and see. They came and saw where he dwelt, and abode with him that day: for it was about the tenth hour.” (KJV)

He said to them, “Come and you will see.” So they came and saw where he was staying, and they stayed with him that day, for it was about the tenth hour. (ESV)

He said to them, “Come, and you will see.” So they came and saw where He was staying; and they stayed with Him that day, for it was about the tenth hour. (NASB)

“Come and you’ll see,” He replied. So they went and saw where He was staying, and they stayed with Him that day. It was about 10 in the morning. (HCSB)

ከነዚህ ትርጉሞች በተለየ መንገድ የተረጎሙ ቢኖሩም አሥር ሰዓት ከተገናኙና አብረውት እንደዋሉ ከተነገረ በሮማውያን አቆጣጠር ጠዋት አሥር ሰዓት (በአይሁድ አራት ሰዓት) እንጂ ከሰዓት በኋላ ሊሆን አይችልም፡፡

ዮሐንስ 4፥6 በዚያም የያዕቆብ ጕድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጕድጓድ አጠገብ እንዲህ ተቀመጠ፤ “”ጊዜውም ስድስት ሰዓት”” ያህል ነበረ።

ድካም ያለበት ቀትር ስድስት ሰአት የዕብራውያን አቆጣጠር እንጂ የሮማውያን አቆጣጠር አይደለም፤ ምክንያቱም የሮማውያን ስድስት ሰአት የዕብራውያን ከምሽቱ 12 ሰአት አሊያም ከጎህ 12 ሰአት ነው፤

በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 4 ላይ የተጠቀሰው ስድስት ሰዓት ቀትር ስድስት ሰዓት እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ቢታመንም ማስረጃ የለውም፡፡ በሮማውያን አቆጣጠር ምሽት ስድስት ሰዓት (በአይሁድና በእኛ ደግሞ ምሽት አስራ ሁለት ሰዓት) እንዳይሆን የሚያደርገው ምንም ነገር የለም፡፡ በጠራራ ፀሐይ ውኀ ለመቅዳት መሄድ ያልተለመደ ስለሆነ (ዘፍ. 24፡11) ብዙ ሰባኪዎች የሳምራዊቷን ሴት በዚያ ሰዓት ውኀ ለመቅዳት መሄድ ሲያብራሩ ጥሩ ታሪክ ስላልነበራት ከሰዎች ዕይታ ለመሰወር በማሰብ ሰዎች ውኀ ለመቅዳት የማይሄዱበትን አሳቻ ሰዓት እንደመረጠች በመናገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተባለ ታሪክ ፈጥረዋል፡፡ ይህ ግን ማስረጃ ሊቀርብለት የማይችል ግምት ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ ደክሞት በውኀ ጉድጓድ አጠገብ መቀመጡ ቀኑን ሙሉ መጓዙን የሚያመለክት ሲሆን ፀሐይ ስታዘቀዝቅ ውኀ ለመቅዳት መሄድ ደግሞ የተለመደ ነበር፡፡ ስለዚህ በዚህ ስፍራ ላይ 6 ሰዓት የተባለው በኛና በአይሁድ አቆጣጠር እኩለ ቀን 6 ሰዓት ሳይሆን ከሮማውያን አቆጣጠሮች መካከል በአንዱ መሠረት 6፣ በኛና በአይሁዶች አቆጣጠር ደግሞ አመሻሽ 12 ሰዓት አካባቢ ነበር፡፡ ይህ እንደ ሮበርት ገንድሪ እና ጆን ክላርክ ያሉ ታላላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት የሚደግፉት ሐሳብ ነው። (Gundry, R.H., Commentary on the New Testament. Verse-by-Verse Explanations with a Literal Translation; pp. 354, 365, 371, 451) (Clark, G.W., The Gospel of John (A People’s Commentary; Philadelphia, PA: American Baptist Publication Society 1896; p. 41)

ሌሎች ሊቃውንት ደግሞ የዮሐንስ አጻጻፍ የአይሁድን የተከተለ እንደሆነ የሚያምኑ ሲሆን የጥንት ሰዎች ሰዓትን በዋና ዋና ክፍሎች ማለትም ማለዳ፣ ሦስተኛው ሰዓት፣ ስድስት ሰዓት፣ ዘጠኝ ሰዓት እና ምሽት በማለት ይከፋፍሉ ነበር። ስለዚህ በነዚህ ሰዓታት መካከል ያሉትን ጊዜያት ብዙ ጊዜ ወደ አንዱ በማስጠጋት ይቆጥራሉ። ለምሳሌ ያህል ጊዜው ጠዋት 4:30 ከሆነ ማርቆስ ወደ 3 ሰዓት በማስጠጋት ዮሐንስ ደግሞ ወደ ቀኑ 6 ሰዓት በማስጠጋት መጻፍ ይችላሉ። ይህ እንደ ዘመናችን ሰዓትን በትክክል የሚያሳዩ መቁጠርያዎች ባልነበሩበት በዚያን ዘመን ፍጹም ተቀባይነት የነበረው ጉዳይ ነበር።

ይህን ሃቅ ይዘን የዮሐንስ ዘጋቢ ጋር ኢየሱስ ስድስት ሰአት ላይ እንኳን ሊሰቀል ይቅርና ገና ህዝቡ ስቀለው እያሉ ይጮኹ እንደነበር ይተርካል፦

ዮሐንስ 19፥14-15 ለፋሲካም የማዘጋጀት ቀን ነበረ፤ “ስድስት ሰዓትም” የሚያህል ነበረ፤ አይሁድንም፦ እነሆ ንጉሣችሁ አላቸው። እነርሱ ግን፦ አስወግደው፥ አስወግደው፥ “”ስቀለው”” እያሉ ጮኹ።

ጥያቄአችን፦ የቱ ትረካ ነው ትክክል? በሰቀሉት ጊዜ 3 ሰአት ነበረ ብሎ የሚተርከው የማርቆስ ዘጋቢ ወይስ 6 ሰአት ላይ ገና አልተሰቀለም ብሎ የሚተርከው የዮሐንስ ዘጋቢ?

የቱን ሃቅ ይዘህ ነው እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረስከው? አይሁድ ኢየሱስን ወደ ጲላጦስ የወሰዱት በሮማውያን አቆጣጠር ማለዳ 6 ሰዓት ማለትም በአይሁድ አቆጣጠር ጠዋት 12 ሰዓት ነበር፤ በአይሁድ አቆጣጠር 3 ሰዓት ላይ ተሰቀለ፡፡ ኢየሱስ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ ለፍርድ ከቀረበ 3 ሰዓት ላይ ተሰቀለ ቢባል ምንም ግጭት አይፈጥርም፡፡  ዮሐንስ የሮማውያንን አቆጣጠር መጠቀሙን ከምንም ዓይነት ጥርጣሬ በጸዳ ሁኔታ እንድናምን የሚያደርገን ማስረጃ እዚያው በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ይገኛል፡-

ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው።” (ዮሐንስ 20፡19)

በአይሁድ የሰዓት አቆጣጠር መሠረት ቀን የሚቆጠረው ከምሽት በኋላ ነው፡፡ ስለዚህ እሑድ ከ 12 ሰዓት በኋላ ሰኞ ነው፡፡ ዮሐንስ የአይሁድን የሰዓት አቆጣጠር ቢጠቀም ኖሮ “ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ…” ከማለት ይልቅ “ያም ቀን ካለፈ በሳምንቱ በሁለተኛው…” ማለት ነበረበት፡፡ ነገር ግን በሮማውያን የሰዓት አቆጣጠር ቀጣዩ ቀን የሚጀምረው ከእኩለ ሌሊት በመሆኑ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ሲገለጥ ገና እሑድ ነበር ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የተገለጠው ፀሐይ ከገባችና በአይሁድ አቆጣጠር ሁለተኛው ቀን ከገባ በኋላ መሆኑን ሉቃስ 24፡19-40 ላይ ከሚገኘው ተጓዳኝ ትራኬ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ጥቅስ ዮሐንስ የሮማውያንን አቆጣጠር መጠቀሙን ከጥርጣሬ በጸዳ ሁኔታ ያረጋግጥልናል፡፡ ስለዚህ ያንተ ሙግት ቦታ የሚሰጠው አይደለም፡፡

ነጥብ ሶስት

“ሶስት ቀን”

ኢየሱስ የአላህ ነብይ ነው አይዋሽም፤ መቼም አራቱ ወንጌላት ላይ ያሉት ቃላት አይደለም የኢየሱስ ይቅርና የመጀመሪያዎቹ ፀሃፊያን ያልሆኑ ንግግሮች በእማኝነትና በአስረኝነት ማቅረብ ይቻላል፤ ነገር ግን ነጥባችን እርሱ አይደለም፤ ኢየሱስ ተናገረ ተብሎ የተቀጠፈበት ነገር እርስ በእርሱ ይጋጫል፤ እንደ ማርቆስ ዘጋቢ ኢየሱስ ይነሳል የተባለው “ከሦስት ቀንም “”በኋላ”” ተብሎ ነው፤ ልብ አድርጉ “በኃላ” የሚለው መስተዋድድ በአራተኛው ቀን አሊያም በአምስተኛው ቀን ሊሆን ይችላል፤ ግን ሶስኛውን ቀን አይጨምርም፦

ማርቆስ 8፥31 የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፥ ሊገደልም “ከሦስት ቀንም “”በኋላ”” ሊነሣ” እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር።

የማቴዎ ዘጋቢ ደግሞ ኢየሱስ ይነሳል የተባለው “በ”ሦስተኛውም ቀን”” ተብሎ ነው፤ ልብ አድርጉ “በ” የሚለው መስተዋድድ ሶስተኛውን ቀን ብቻ የሚያመለክት ነው፦

ማቴዎስ 16፥21 ከዚያን ቀን ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ “”በሦስተኛውም ቀን” ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር።

ጥያቄአችን፦ የቱ ትረካ ነው ትክክል? ኢየሱስ ይነሳል የተባለው “ከሦስት ቀንም “”በኋላ”” ነው ብሎ የሚተርከው የማርቆስ ዘጋቢ ወይስ ኢየሱስ ይነሳል የተባለው “በ”ሦስተኛውም ቀን”” ነው ብሎ የሚተርከው የማቴዎስ ዘጋቢ?

በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ለነበረ አይሁዳዊ “በሦስተኛው ቀን” እና “ከሦስት ቀን በኋላ” የሚሉት አባባሎች ልዩነት አልነበራቸውም፡፡ ይህንን ለመረዳት የአይሁድ መሪዎች ለጲላጦስ የተናገሩትን ማየት በቂ ነው፡-

“ጌታ ሆይ፥ ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ፦ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን። እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም፦ ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት።” (ማቴ. 27፡63-64)

የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስ ከሦስት ቀን በኋላ እንደሚነሳ መናገሩን ያስታወቁ ሲሆን መቃብሩ ግን እንዲጠበቅ የጠየቁት እስከ ሦስተኛው ቀን ነው፡፡ ስለዚህ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ለነበሩት አይሁድ ከሦስት ቀን በኋላ ማለት አራተኛው ወይንም አምስተኛ ቀን ማለት ሳይሆን እስከ ሦስተኛው ቀን ማለት ነው፡፡ በዚያን ዘመን በነበሩት አይሁድ አቆጣጠር ደግሞ ማንኛውም የቀን ክፍል እንደ ሙሉ ቀን ስለሚቆጠር [1] አርብ ፀሐይ ከመግባቷ በፊት አንድ ቀን፣ ፀሐይ ከገባች በኋላ እስከ ቅዳሜ ምሽት ሁለተኛው ቀን፣ ከቅዳሜ ምሽት እስከ እሑድ ማለዳ ሦስተኛው ቀን ይሆናል፡፡ ቀጣዩ ቀን የሚገባው ፀሐይ ከገባች በኋላ ነው፡፡ ከዛሬ 2000 ዓመታት በፊት የነበረውን አነጋገር ወደ ራሳችን ዘመን አምጥተን በኛ ባሕልና አነጋገር መተርጎም ለስህተት ይዳርጋል፡፡


[1] https://www.jewishencyclopedia.com/articles/5007-day


እስልምናና የመሲሁ ስቅለት

ስለ ስቅለት እስላማዊ ብዥታ

ክርስቶስ ተሰቅሏልን? በአሕመድ ዲዳት እና ጆሽ ማክዱዌል መካከል የተደረገ ሙግት፡፡