ዳዊት የገደለው ሠራዊት ብዛት ስንት ነው?

ዳዊት የገደለው ሠራዊት ብዛት ስንት ነው?

ንጉሥ ዳዊት የገደለውን ሠራዊት ብዛት በተመለከተ በተከታዮቹ ጥቅሶች መካከል ግጭት መኖሩን የሚናገሩ አንዳንድ ወገኖች አሉ፡-

ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት መቶ ሰረገለኞች አርባ ሺህም ፈረሰኞች ገደለ፤ የሠራዊቱንም አለቃ ሶባክን መታ፥ እርሱም በዚያ ሞተ። (2ሳሙ. 10፡18)

ይህ ጥቅስ ከተከታዩ ጋር ይጋጫል ተብለናል፡-

ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት ሺህ ሰረገለኞች፥ አርባ ሺህም እግረኞች ገደለ፥ የሠራዊቱንም አለቃ ሾፋክን ገደለ። (1ዜና 19፡18)

ይህንን ልዩነት አንዳንድ ምሁራን የእጅ ጽሑፉን የገለበጡ ሰዎች የግልበጣ ስህተት እንደሆነ ቢናገሩም ይህንን የማይቀበሉና የአረዳድ ችግር ብቻ እንደሆነ የሚናገሩ ሌሎች ደግሞ አሉ፡፡ በዚህም መሠረት 2ሳሙ. 10፡18 ላይ የተዘገበው የሰረገሎች ብዛት ሲሆን 1ዜና 19፡18 ላይ የተዘገበው የሰረገለኞች ብዛት ነው፡፡ የኪንግ ጀምስ ትርጉም የመጀመርያውን “and David slew the men of seven hundred chariots” (ዳዊት የሰባት መቶ ሰረገላዎችን ሰዎች ገደለ) በማለት ያስቀመጠ ሲሆን ሁለተኛውን ጥቅስ “David slew of the Syrians seven thousand men which fought in chariots” (ዳዊትም ከሶርያውያን በሰረገሎች የሚዋጉ ሰባት ሺህ ሰዎችን ገደለ) በማለት ያስቀምጣል፡፡ በዚህ መሠረት 2ሳሙ. 10፡18 በሰባት መቶ ሰረገሎች ላይ ስለተቀመጡ ተዋጊዎች የሚናገር ሲሆን 1ዜና 19፡18 ደግሞ የተዋጊዎቹ ብዛት ሰባት ሺህ መሆኑን ይነግረናል፤ ስለዚህ ግጭት የለም፡፡

እግረኞቹንና ፈረሰኞቹን በተመለከተ እነዚህ እንደ እግረኛም እንደ ፈረሰኛም የመዋጋት ስልጠናና ድርሻ ስለነበራቸው አንዱ ጸሐፊ እግረኞች ሲላቸው ሌላው ደግሞ ፈረሰኞች ብሏቸዋል፡፡ ውጊያው ለተወሰኑ ቀናት የተደረገ በመሆኑ እነዚህ ወታደሮች አመቺ ሲሆን በፈረስ አመቺ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ በእግር ቢዋጉና እግረኛ ወይንም ፈረሰኛ ተብለው ቢጠሩ ምንም ችግር የለውም፡፡ ይህ የዘጋቢዎቹ ምርጫ ነው የሚሆነው፡፡

ለማንኛውም የግልበጣ ስህተት ነው ቢባል እንኳ ሙስሊም ወገኖች እንዲህ ያሉ ከዋና አስተምሕሮዎች ጋር ያልተያያዙ ጥቃቅን ጉዳዮችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እያወጡ ከሚተቹ ቁርአናቸውን ቢመረምሩና ቢያርሙ ያዋጣቸዋል ባይ ነን፡፡ ሊቃውንቶቻቸው ለመደበቅ ቢሞክሩም በቁርኣን የእጅ ጽሑፎች ውስጥ በቅርቡ የተገኙት ከ 4000 በላይ ሆን ተብለው የተደረጉት ለውጦች (intentional changes) ለዓለም ሕዝብ ይፋ ሆነዋልና፡፡ ይህንን አስመልክቶ ዶ/ር ዳንኤል አለን ብሩቤከር የተሰኙ የቁርኣን ጽሑፎች ሊቅ Corrections in Early Quran Manuscripts: Twenty Examples በሚል ርዕስ የጻፉትን መጽሐፍ ማንበብ በቂ ነው፡፡ እኚህ ሊቅ በጥናት ካገኟቸው 4000 ልዩነቶች መካከል ሃያዎቹን በናሙናነት በመጽሐፍ ያሳተሙ ሲሆን ሌሎቹንም በተከታታይ ለንባብ እንደሚያበቁ ይጠበቃል፡፡


የመጽሐፍ ቅዱስ ግጭቶች?

ቁርኣን ግጭቶች