የታላቁ እስክንድር አፈታሪክና የቁርኣን ኩረጃ

የታላቁ እስክንድር አፈታሪክና የቁርኣን ኩረጃ

በወንድም ትንሣኤ


የሙስሊሞች ነቢይ ሙሐመድ ነቢይነቱን ሰዎች እንዲቀበሉለት ከተጠቀማቸው ሙግቶች መካከል አንዱ ከኖረበት ቦታና ጊዜ ርቀው የተከሰቱ ሁነቶችን በመዘገብ ይህ ከፈጣሪ ካልተገለጠ በቀር የሚቻል አይደለም የሚል አመክንዮ ማቅረብ ነው። ሙሐመድ ፈጣሪ ገልጦልኝ ዘግቤያቸዋለሁ ካላቸው ታሪኮች አንዱ በአረቡ ምድር ዙልቀርነይን (ባለ ሁለት ቀንዱ) በመባል የሚታወቀው የታላቁ እስክንድር ታሪክ ይጠቀሳል። በቁርኣን መሰረት ይህ ሰው መጀመሪያ ወደ ምዕራብ ቀጥሎም ወደ ምስራቅ አቅጣጫ በመጓዝ ፀሐይ የምትጠልቅበትንና የምትወጣበትን ቦታ ከማግኘቱ በተጨማሪ ወደ ሰሜን በመጓዝ “መናገር የማይችሉ” ሕዝቦችን አግኝቶ እነዚህን ሰዎች የእጁጅ እና መእጁጅ ከተሰኙ ወራሪዎች ለመጠበቅ ታላቅ ግድብ ሠርቷል (18:83-100)።

ይህ አፈታሪክ ሙሐመድ እንዳለው መለኮታዊ መገለጥ ሳይሆን በሰባተኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ እንደተጻፈ ከሚገመተው “የታላቁ እስክንድር ድንቅ ስራዎች” ከተሰኘው የሲሪያክ አፈታሪክ እንደተገለበጠ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። የሁለቱን ዘገባዎች ጥልቅ መመሳሰል ለማስተዋል አንባቢው ከስር የተቀመጠውን የሲሪያክ አፈታሪክ በቅንፍ ከተቀመጡት የቁርዓን አያዎች ጋር እያስተያየ እንዲያነብ ይመከራል።

ይህ ቴትራድርሃም የተሰኘ የግሪኮች ሳንቲም ላይ የተቀረጸ የታላቁ እስክንድር ምስል ሊሲማኾስ በተባለ ቦታ የተገኘ ሲሆን በ297-281 ቅድመ ክርስቶስ ገደማ የተሠራ ነው። በቁርኣን ውስጥ እንደተጠቀሰው ሁሉ እስክንድር ቀንዶች እንዳሉት ተደርጎ ተስሏል።

በዚህ አፈታሪክ መሠረት ታላቁ እስክንድር የምድርን ጫፎች ለማየት ይወስንና ከጉዞው በፊት ወደ ፈጣሪ ይጸልያል። ፈጣሪውንም “ቀንዶች እንዲያበቅልለትና ምድር ላይ ስልጣን እንዲሰጠው” ይለምናል (18:84)። በመርከብ ጉዞ ላይ ሳለም አንድ መርዛማ ባሕርን ለመሻገር የፈራው እስክንድር ይህንን መንገድ በመተው “ፀሐይ የምትጠልቅበት ብሩህ ውኅ” የሚታይበትን አቅጣጫ ይከተላል (18:86)፤ ከዚህ ተነስቶም ፀሐይን በመከተል “ፀሐይ የምትወጣበትን” ምስራቃዊ ጫፍ ያገኛል (18:90)። በአፈታሪኩ መሠረት ፀሐይ በምትወጣበት ሰዓት በአካባቢው የሚኖሩት ሰዎች በሃሩሩ እጅግ ከመቃጠላቸው ብዛት ዋሻ ውስጥ ወይም ውኅ ውስጥ ይደበቁ ነበር (18:90)። በመቀጠልም እስክንድር ወደ ሰሜን አቅጣጫ ይጓዝና የእጁጅና ማእጁጅ በተባሉ ነገሥታት የሚመሩ ክፉ ወራሪዎች ያስቸገሯቸውን ሕዝቦች ያገኛል። ታላቁ እስክንድር የሰዎቹን ችግር ሲገነዘብ ከእነርሱ ጋር በመተባበር “ነሃስና ብረት በመጠቀም” ታላቅ ግድብ ይሰራላቸዋል (18:94-96)። በስተመጨረሻም ይህ ግድብ የዓለም ፍጻሜ ሲደርስ እንደሚፈርስና በዚያ ጊዜም ህዝቦቹ “ከፊሉ በከፊሉ እንደሚቀላቀሉ” (Fall upon each other) ትንቢት ይናገራል (18:98)። [1]

ይህ ዘገባ ከቁርኣን ታሪክ ጋር የሚመሳሰል ብቻ ሳይሆን በቃላትና ሐረጋት ደረጃ እንኳ አንድ ዓይነት ነው። በሁለቱም ታሪኮች መሠረት እስክንድር ቀንድ ያለውና ምድር ላይ ሥልጣን የተሰጠው ተደርጎ ቀርቧል፤ ፀሐይ የምትወጣበትንና የምትጠልቅበትን የምድር ጫፍም ተመልክቷል። ከዚህ ባለፈም የእጁጅና ማእጁጅ የተባሉ ወራሪዎችን ለመከላከል ከነሃስና ብረት የተሠራ ግድብ አኑሮ ግድቡ በዓለም ፍጻሜ እንደሚፈርስ ትንቢት ተናግሯል። ይህንን መመሳሰል ያስተዋሉት የሥነ-ሃይማኖት ታሪክ አጥኚው ጋብሬል ሬይኖልድስ “ቁርኣን ውስጥ የሚገኘው ሁሉም የታሪኩ ክፍል ማለት ይቻላል እጅግ በሚደንቅ ሁኔታ የሲሪያክ አፈታሪኩ ውስጥ በበለጠ ግልጽና ሰፋ ባለ መልኩ ይገኛል” ይላሉ።[2]

በእርግጥም ይህ አስገራሚ መመሳሰል ተራ አጋጣሚ ሊሆን እንደማይችል ግልጽ በመሆኑ ሦስት አማራጭ ሐሳቦች ይቀሩናል። ወይ ይህ የሲሪያክ አፈታሪክ ከቁራኣን የተቀዳ ነው፤ አልያም ሁለቱም አንድ ምንጭ አላቸው ወይም የቁርኣን ደራሲ በቀጥታ ከዚህ አፈታሪክ ኮርጇል።

በእጃችን የሚገኘው ታሪካዊ ማስረጃ የመጀመሪያዎቹን ሁለት አማራጮች አይደግፍም። እንደ ሬኒንክ ያሉ በዘርፉ ሰፊ ጥናት ያካሄዱ ምሁራን እንደሚገልጹት ይህ አፈታሪክ የተጻፈው ሮማውያን ከፋርሶች ጋር ያደረጉት ጦርነት ማብቂያ (628-630AD) አካባቢ ነው።[3] የአፈታሪኩ ዋና አላማ የጦርነቱ ድል የሮማውያን ክርስቲያኖች እንደሚሆንና ይህም በታላቁ እስክንድር ሳይቀር ቀድሞ የተተነበየ እንደሆነ ማስረዳት ነው። ጋብሬል ሬይኖልድስ እንዲያውም የእስክንድር ወደ ሦስቱ አቅጣጫዎች (ጉዞው የመስቀል ቅርጽ እንዳለው ልብ ይሏል) መጓዝ የታሪኩ ጸሐፊ ሊያስተላልፍ የፈለገውን “የመጨረሻ የክርስቲያኖች ድል” ያመለክታል ይላሉ።[4]

ታዲያ እስልምናም ሆነ ቁርኣን ገና በደንብ ባልታወቁበት ሰዓት የሶርያ ክርስቲያኖች ይህንን ታሪክ ከቁርኣን ይገለብጣሉ ብሎ ማሰብ የሚመስል አይደለም። የአፈታሪኩ ደራሲ ቁርኣንን ለማንበብ/ለመስማት ያለው ዕድል አናሳ መሆኑንና ታሪኩን ለመገልበጥ ምንም ዓላማ ሊኖረው እንደማይችል ስናገናዝብ ድርሰቱ ከቁርኣን የተኮረጀ አለመሆኑ ግልጽ እየሆነ ይመጣል። ይህ ብቻ ሳይሆን ጋብሬል ሬይኖልድስ እንደሚሉት የሲሪያኩ አፈታሪክ ከቁርኣን ገልብጦ ቢሆን ኖሮ ከአረብኛ እንደተተረጎመ የሚጠቁሙ ቃላትና ሐረጋት ይኖሩት ነበር።[5] ይህ አፈታሪክ በሲሪያክ ክርስቲያኖች የተፈበረከበት ግልጽ የፖለቲካ አላማ መኖሩ የአፈታሪኩ ጸሐፊ ከሌላ መጽሐፍ ገልብጦ እንዳልወሰደው የሚያስረግጥ ሌላ ማሳያ ነው።

ወደ ሁለተኛው አማራጭ ስንመጣ ሁለቱ ዘገባዎች ከአንድ የቀደመ ምንጭ እንደተቀዱ ማሰብ ከባድ ነው። የሲሪያኩ አፈታሪክ የተፈበረከው በዘመኑ የነበረውን ጦርነት ክርስቲያኖች እንደሚያሸንፉ ለማመልከት በመሆኑ ታሪኩ ከዚያ በፊት ባሉ ምንጮች መዘገቡ ስሜት አይሰጥም። ሬይኒንክ እንደሚሉት “የሲሪያኩ አፈታሪክ የተፈበረከው ለዚህ ዓላማ ብቻ ከሆነ በቁርኣንና በአፈታሪኩ መካከል ያለው መመሳሰል ሁለቱም በቀደመ ምንጭ ላይ ተመሥርተው በመጻፋቸው ምክንያት የመጣ ሊሆን አይችልም።”[6]

በመሆኑም የቀረው ብቸኛ አማራጭ እንደ ቫን ብሌደል እና ፒተር ቢቴንሆልዝ ያሉ ምሁራን እንደሚሉት የቁርኣን ደራሲ ታሪኩን በእርግጥም ከዚህ አፈታሪክ በመገልበጥ እንደወሰደው መደምደም ነው።[7][8] ምንም እንኳን አንዳንድ ምሁራን ከአፈታሪኩ የድርሰት ጊዜ በመነሳት ታሪኩ መካ ደርሶ የቁርኣን ደራሲ ሊሰማው ይችላል የሚለውን ሐሳብ ቢጠራጠሩትም ታሪኩ ግን ቁርኣን በተደረሰበት ሰዓት የአረቡ ምድር ውስጥ በደንብ ሊታወቅ የማይችልበት ምክንያት አይኖርም። አረቦች ከቀድሞ ጀምሮ በሮማውያንና ፋርሶች ጦርነት በወታደርነት መሳተፋቸው የታሪኩን ወደ አረቡ ሕዝብ የመስፋፋት ዕድል ይጨምረዋል። “ከዙልቀርነይንም ይጠይቁሃል” የሚለው የቁርኣን ንግግርም በሙሐመድ ዙሪያ በነበሩ አረቦች ዘንድ የዙልቀርነይን ታሪክ ይታወቅ እንደነበር ያመለክታል። በተለያዩ ተፍሲሮች መሰሠረት ይህ አያህ የወረደው አይሁዶች ሙሐመድን “የአለም ጫፍ ድረስ ስለተጓዘው ሰው” ጠይቀውት ስለነበረ መነገሩ ታሪኩ በእርግጥም በአረቡ ምድር ይታወቅ እንደነበር የሚያሳይ ሌላ ማስረጃ ነው።[9] ለዚህም ነው ቫን ብሌደል “አፈታሪኩ በስፋት ይታወቅ እንደነበር መጠራጠር ይከብዳል” የሚሉት።[10]

ጽሑፋችንን ስናጠቃልል ይህ አፈታሪክ በሶሪያ ክርስቲያኖች የተፈበረከበት ጊዜያዊና ፖለቲካዊ አላማ ቢኖረውም የቁርኣን ደራሲ ግን ይህንን አላማ ባለመገንዘቡ ምክንያት ትርክቱን ቀጥታ ከዚሁ ምንጭ በመገልበጥ ከእስላማዊ ዕይታ አንጻር ትርጉም የለሽ የሆኑ ዘገባዎችን ሊዘግብ ችሏል። የመጽሐፉ ሰዎች (አይሁዶች) ሙሐመድን ለመፈተን ስለ ታላቁ እስክንድር ቢጠይቁትም ሙሐመድ ግን አዲስ ታሪክ ከመናገር ይልቅ በዙሪያው ባሉ አረቦች ቀድሞም ይታወቅ የነበረውን አፈታሪክ በማስተጋባት ሐሰተኛ ነቢይነቱን አስመስክሯል። ሙስሊም ወገኖች ይህንን ግልጽ ኩረጃ አስተውለው የቁርኣንን ሰው ሠራሽነት ይቀበሉ ይሆን? ወይስ ይህ አስገራሚ መመሳሰል ተራ ግጥምጥሞሽ እንደሆነ ይነግሩናል?


[1] Gabriel Reynolds, The Quran in its historical context, Page 178-180.

[2] Ibid. 181.

[3] G.J.Reinink, Alexander the Great , page 160-162.

[4] Gabriel Reynolds, The Quran in its historical context, Page 185.

[5] Ibid. 189.

[6] G.J.Reinink , Alexander the Great , page 152.

[7] Van Bladel, Alexander legend in the Quran, page 197-198.

[8] Peter Bietenholz, Myths and Legends in Historical Thought from Antiquity to the Modern Age, page 122-123.

[9] Tafsir Ibn Kathir , Surah 18:83.

[10] Gabriel Reynolds, The Quran in its Historical Context, Page 191.


ቁርኣን