እግዚአብሔር ይጸጸታል ወይንስ አይጸጸትም?
ዘፍጥረት 6፡6 “እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ በልቡም እጅግ አዘነ” ይላል፡፡ እግዚአብሔር እንደ ደካማው ፍጥረት እንደሰው ባደረገው ይጸጸታልን? በመሠረቱ “ጸጸት” ማለት አንድ ሰው አንድን ድርጊት ያደርግና በኋላ ያደረገው ድርጊት በጠበቀው መልኩ ሳይኾንለት ሲቀር ነው፡፡ ይህ ለሰው የተገባ ባሕርይ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው አስቀድሞ የነገርን ፍጻሜ ማወቅ አይችልምና፡፡ አምላክ ግን ኹሉን የሚያውቅ ጌታ ስለሆነ በሚሠራው ሥራ አይጸጸትም፡፡ ታዲያ “አምላክ ሰውን በመፍጠሩ ተጸጸተ” ማለት አግባብነት አለውን? ሰውን ሲፈጥር ሰው ምን እንደሚያደርግ አስቀድሞ አያውቅምን? የማያውቅ ከሆነ ኹሉን አዋቂ አይደለም ማለት ነው፡፡ ታድያ ይህ አምላክ መኾን ይችላልን? ወይስ ይህ የአምላክ ሳይኾን የሰው ቃል ነው?
ተከታዮቹ ጥቅሶች ተያያዥ ናቸው፡-
1ኛ ሳሙኤል 15፡35 “ሳሙኤል ሳኦል ቢያለቅስለትም እንኳን እስከ ሞተበት ዕለት ድረስ ዳግመኛ ሊያየው አልሄደም፡፡ እግዚአብሔርም ሳኦልን በእስራኤል ላይ በማንገሡ ተጸጸተ” ይላል፡፡ አምላክ ይጸጸታልን? ፈጣሪን ይጸጸታል ማለት ድፍረት አይኾንምን?
አሞፅ 7፡1-6 “ጌታ እግዚያብሔር በእሳት ሊፈርድ ተዘጋጀ ፤ እሳቱም ታላቁን ጥልቅ አደረቀ ፤ ምድሪቱንም በላ ፡፡ ከዚያም በኃላ ፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እንድትተወው እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ይህን እንዴት ሊቋቋመው ይችላል? ታናሽ ነው እኮ አልሁ፡፡ እግዚአብሔር ስለዚህ ነገር ተጸጸተ ፤ ጌታ እግዚአብሔር፤ “ይህም ደግሞ አይፈፀምም” አለ” ይላል ፡፡ አምላክ ይጸጸታልን?
መልስ፡- መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ተጸጸተ” ሲል እንደ ሰው ያለ ጸጸት አለመኾኑን በሌሎች ቦታዎች ላይ ግልፅ አድርጓል፡-
“ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም፡፡” (ዘኍ. 23፡19)፡፡
“የእስራኤል ኃይል እንደ ሰው የሚጸጸት አይደለምና አይዋሽም አይጸጸትምም አለው፡፡” (1ሳሙ. 15፡29)፡፡
በነዚህ ቦታዎች ጸጸትን ለማመልከት የገባው የእብራይስጥ ቃል “ናኻም” የሚል ሲሆን በተለያዩ አውዶች ውስጥ የተለያዩ ትርጉሞች አሉት፡፡ ለምሳሌ ያህል ተከታዮቹን ጥቅሶች ተመልከቱ፡-
“እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ (ናኻም)፡፡” (ዘጸ. 32፡14)
“ግብፃውያንስ፦ በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ (ናኻም)፥ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ፡፡” (ዘጸ. 32፡12)
“እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፥ ስለ ባሪያዎቹም ያዝናል (ናኻም)” (ዘዳ. 32፡36)
“ምሕረትህ ለመጽናናቴ (ናኻም) ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባሪያህ ይሁነው፡፡” (መዝ. 119፡76)
“እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳልና (ናኻም)፥ ባሪያዎቹንም ይረዳልና፡፡” (መዝ. 135፡14)
“በሸለቆው ውስጥ ያሉ የለዘቡ ድንጋዮች እድል ፈንታሽ ናቸው፥ እነርሱም ዕጣሽ ናቸው፤ ለእነርሱም የመጠጥ ቍርባን አፍስሰሻል፥ የእህልንም ቍርባን አቅርበሻል፡፡ እንግዲህ በዚህ ነገር አልቁጣምን (ናኻም)?” (ኢሳ. 57፡6)
“አጽናኑ (ናኻም)፥ ሕዝቤን አጽናኑ (ናኻም) ይላል አምላካችሁ፡፡” (ኢሳ. 40፡1)
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደ ሰው እንደማይጸጸት ከነገረን፤ ናኻም የሚለው የእብራይስጥ ቃል ደግሞ በብዙ መንገዶች ሊተረጎም ከቻለ (መራራት፣ መመለስ፣ ማዘን፣ መጽናናት፣ መፍረድ፣ መቆጣት)፤ ጠያቂው እግዚአብሔር “እንደተጸጸተ” የሚናገሩትን ጥቅሶች አጥብበው መተርጎማቸው ትክክል አይደለም፡፡ ዘፍጥረት 6፡6 እና 1ሳሙኤል 15፡35 ላይ የሚገኙት ጥቅሶች እግዚአብሔር ማዘኑን ለመግለፅ የተነገሩ ሲሆኑ አሞፅ 7፡1-6 ላይ የሚገኘው ደግሞ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ሊፈፅመው ከነበረው ፍርድ መታቀቡን ያመለክታሉ፡፡