የመናዊው አቡ አል-ፈት፤ የጨለማው ዘመን ሻማ
አባ ዕንባቆም (የልደት ስማቸው አቡ አል-ፈት) በ1489 ዓ.ም እ.ጎ.አ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የመናዊ ሙስሊም ሲሆኑ እስላማዊ መጻሕፍትን ለብዙ ዘመናት ካጠኑ በኋላ ክርስትናን የተቀበሉ ሰው ነበሩ። ወደ ኢትዮጵያ እንዲጓዙ መለኮታዊ ራዕይ እንደተገለጠላቸውና በባርነት በየመን በነበሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን ስለ ክርስትና እንደተነገራቸው ታሪካቸው ያስረዳል። እኚህ ታላቅ ሰው የደብረ ሊባኖስ ገዳም አስተዳዳሪ ከመሆን ጀምሮ ከሊቀ ጳጳሱ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ እስከሆነው እስከ እጨጌነት የደረሱ እንዲሁም የኢትዮጵያ ገዳማት ሁሉ አስተዳዳሪ ለመሆን የበቁ ሰው ነበሩ። ክርስትናን ከተቀበሉ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነበር ግራኝ አሕመድ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ ጥቃት የጀመረው። በዚህ ጊዜ አባ ዕንባቆም ግራኝ አሕመድ ለግድያ ከሚፈልጋቸው ሰዎች መካከል አንዱ በመሆናቸው ምክንያት በስውር ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ የተረፉትን ክርስቲያኖች ያፅናኑ፣ እስልምናን የተመለከቱ ጽሑፎችንም ያዘጋጁ ነበር።
የአባ ዕንባቆም ክርስትና የተፈተነ ክርስትና ነበር። ከግራኝ ወረራ አስቀድሞ ለንጉሥ ልብነ ድንግል ታማኝ አልሆኑም በሚል ሙስሊሞች ወደሚበዙበት ጉንጫ ወደ ተባለ አካባቢ ለቅጣት የተሰደዱ ቢሆንም ብዙ ሙስሊሞችን ወደ ክርስትና ማምጣት ችለው ነበር። እኚህ አስገራሚ ሰው “አንቀጸ አሚን” የሚል የክርስትናን እውነትነትና የእስልምናን ሐሰትነት የሚገልጽ ምሑራዊ መጽሐፍ የጻፉ ሲሆን የመጽሐፉን የመጀመርያ ጽሑፍ በአረብኛ በማዘጋጀት ለግራኝ በመላክ የክርስቶስን ወንጌል ነግረውታል። አባ ዕንባቆም የአረብኛ፣ ግዕዝ፣ ቅብጥ፣ እብራይስጥ፣ ሦርያንኛ፣ አርመንኛ፣ ፖርቹጊስ እና የጣልያን ቋንቋዎችን ጠንቅቀው የሚያውቁ ባለ ታላቅ አእምሮ ነበሩ። የዮሐንስ አፈወርቅን የእብራውያን አንድምታ ወደ ግዕዝ የተረጎሙት እርሳቸው ነበሩ። ስለ እኚህ ሰው ስንቶቻችሁ ሰምታችኋል? ታሪካቸውን ስትሰሙ ምን ተሰማችሁ? https://en.wikipedia.org/wiki/Enbaqom