“አብርሃም ሳይወለድ እኔ ነኝ!”
ለሙስሊም ሰባኪ ስሁት ሙግት ምላሽ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነቱን ገልጦ ከተናገረባቸው አጋጣሚዎች መካከል አንዱ ዮሐንስ 8፡58 ላይ ይገኛል፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው።” በጥቅሱ ውስጥ “እኔ አለሁ” የሚለው በግሪክ ἐγὼ εἰμί (ኢጎ ኤይሚ) የሚል ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙ “እኔ ነኝ” (I Am) የሚል ነው። ጌታችን በተናገረበት አውድ አባባሉ ያልተቋረጠ ዘላለማዊ ኑባሬን የሚያመለክት ሲሆን በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያሕዌ እግዚአብሔር አምላክነቱንና ዘላለማዊነቱን ለፍጥረቱ ሲያሳስብ ይህንን ንግግር ይጠቀማል። ይህ ንግግር የኢየሱስን መለኮትነት የሚገልፅ ቢሆንም የሐሰት መምህራን በተለያዩ መንገዶች ለማስተባበል ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ። በዚህ ጽሑፍ አንድ ሙስሊም ሰባኪ ያቀረባቸውን ሙግቶች የምንፈትሽ ይሆናል።
ማሳሰብያ፦ የፊደል ግድፈቶች ሁሉ የእርሱ ናቸው።
አብዱል
መግቢያ
አበይት ክርስቲአናት ማለትም ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ አንግሊካንና ፕሮቴስታንት ይህንን ጥቅስ ተመርኩዘው የኢየሱስ አምላክነት አሊያም የእርሱን ከመወለዱ በፊት ያለውን ቅድመ-ህልውና ለማመልከት ይጠቀሙበታል። እውን ይህ ጥቅስ የኢየሱስ አምላክነት አሊያም የእርሱን ከመወለዱ በፊት ያለውን ቅድመህልውና ያሳያልን?
እኛ ሙስሊሞች ደግሞ በተቃራኒው አያሳይም ብለን የተለያየ ሙግት እናቀርባለን፦
መልስ
እናንተ ሙስሊሞች ቁርአናችሁ ሃይማኖታችሁን በተመለከተ እንኳ ጥርጣሬ ሲያድርባችሁና ግራ ስትጋቡ ክርስቲያኖችን መጠየቅ እንደሚገባችሁ የሚመክራችሁ ሆኖ ሳለ መጽሐፍ ቅዱስን ለክርስቲያኖች እንድታብራሩ ማን ሥልጣን ሰጣችሁ? “ወደ አንተም ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን እነዚያን ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ፡፡ እውነቱ ከጌታህ ዘንድ በእርግጥ መጥቶልሃል፡፡ ከተጠራጣሪዎቹም አትሁን፡፡” (ሱረቱ ዩኑስ 10፡94)። ለበለጠ ማብራርያ መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ! በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ጽሑፍ ያንብቡ።
አብዱል
- የሰዋስው ሙግት
ኢጎ ኤይሚ ἐγὼ εἰμί የሁለት ቃላት ውቅር ሲሆን ኢጎ እኔ ማለት ሲሆን ባለቤት ተውላጠ-ስም subjuctive pronoun ነው፣ ኤይሚ ደግሞ ነኝ ሲሆን አያያዥ ግስ linking verb ነው፣ ይህን የሰዋስው ሙግት ይዘን ሁለት ነጥቦችን እንዳስሳለን፦
ነጥብ አንድ
ኢጎ ኤይሚ ሆ ኦን ἐγὼ εἰμί ὁ ὢν
አበይት ክርስቲአናት ዘጸ 3:14 ላይ ኢጎ ኤይሚ እኔ ነኝ የሚለውን ቃል ከግሪክ ሰፕቱአጀንት(LXX) ትርጉም ይወስዱና ከዮሐንስ 8:58 ጋር አዛምደው ኢየሱስን ሙሴን ሲያናግር የነበረውን ያህዌህ ለማድረግ ሲዳዳቸው ይታያል፣ ይህ አካሄድ ሁለት ክፉኛ ችግሮች አሉበት፦
አንደኛ ዘጸ 3:14 ላይ ያለው ኢጎ ኤይሚ ሆ ኦን ὁ ὢν እርሱ Who የሚል አምልካች ተውላጠ-ስም Demonstrative pronoun አለው፣ ዮሐንስ 8:58 ግን ሆ ኦን የሚል አምልካች ተውላጠ-ስም የለውም።
መልስ
ዮሐንስ 8፡58 ከዘጸአት 3፡14 ጋር ተያያዥ ቢሆንም ይበልጥ የሚመሳሰለው ኢሳይያስ ውስጥ ከሚገኙት ጥቅሶች ጋር ነው። ተከታዮቹ ጥቅሶች ውስጥ “እኔ ነኝ” የሚለውን የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም “ኢጎ ኤይሚ” በማለት ነው የሚያስቀምጠው፦
“ይህን የሠራና ያደረገ፥ ትውልድንም ከጥንት የጠራ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር፥ ፊተኛው በኋለኞችም ዘንድ የምኖር እኔ ነኝ።” (ኢሳ. 41፡4)
“እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ የእስራኤልም ቤት ቅሬታ ሁሉ፥ ከሆድ ያነሣኋችሁ ከማኅፀንም የተሸከምኋችሁ፥ ስሙኝ። እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ፥ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ፤ እኔ ሠርቻለሁ እኔም አነሣለሁ፤ እኔ እሸከማለሁ እኔም አድናለሁ።” (ኢሳ. 46፡3_4)
“ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፤ እኔ ነኝ፤ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ።” (ኢሳ. 48፡12)
በሌሎች የብሉይ ኪዳን ክፍሎችም ውስጥ በርካታ ተመሳሳይ ጥቅሶች ይገኛሉ። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት የሚደግፉት ሐሳብም የጌታችን አነጋገር ከእነዚህ ጥቅሶች ጋር የተያያዘ ነው የሚል ነው። በማስከተል እንደምንመለከተው ጌታችን ኢየሱስ እየተናገረበት ከነበረው አውድ አንጻር “ኢጎ ኤይሚ” የሚለው አባባል አምላክነቱን ያሳያል፤ ስለዚህ “ሆ ኦን” የሚለውን መጨመር አለመጨመር ምንም ለውጥ አያመጣም። በግሪክ ቋንቋ “ὁ ሆ” ውሱን መስተኣምር ስትሆን “ኦን ὢν” ደግሞ የ “ኤይሚ εἰμί” ያሁን ጊዜ ቦዝ አንቀጽ (present participle) ነው። በግሪክ ቋንቋ ያሁን ጊዜ ቦዝ አንቀጽ ቀጣይነት ያለው ወይም ተደጋጋሚ ድርጊትን የሚያሳይ ነው። “ኦን” የሚለውም ሆነ “ኤይሚ” የሚለው የአሁን ጊዜን አመልካች በመሆናቸው በትርጉም ደረጃ አንድ ናቸው። ጌታችን ለአብርሃም የተጠቀመውን መፈጠርን የሚያመለክተውን ቃል ለራሱ አለመጠቀሙ ወይም የ “ኤይሚ” አላፊ ጊዜን አመልካች የሆነውን “ኤሜን” የሚለውን ቃል አለመጠቀሙና ያልተቋረጠ ኑባሬን የሚያመለክተውን “ኤይሚ” የሚለውን ቃል መጠቀሙ አብረሃም ከመወለዱ በፊት ጅማሬ የሌለው ኑባሬ እንዳለው ያመለክታል። Robert M. Bowman Jr. (1995). Jehovah’s Witnesses Jesus Christ &The Gospel of John. Grand Rapids, MI: Baker Book House, p. 114-116.
አብዱል
ሁለተኛው ችግር ደግሞ አንድ ሰው ኢጎ ኤይሚ እኔ ነኝ ማለቱ አምላክነትን ያሳያል ከተባለ ኢጎ ኤይሚ እኔ ነኝ ብለው የተጠቀሙ ብዙ ሰዎች ናቸው፣ እነርሱስ አምላክ ናቸውን?
ዮሐ 9:9 ሌሎች። እርሱ ነው አሉ፤ ሌሎች። አይደለም እርሱን ይመስላል እንጂ አሉ፤ እርሱ። እኔ ነኝ ”ἐγὼ εἰμί ”አለ።
ሐዋ 10:21 ጴጥሮስም ወደ ሰዎቹ ወርዶ። እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ ”ἐγὼ εἰμί ”፤
1ሳሙ 4:16 ሰውዮውም ዔሊን። ከሰልፍ የመጣሁ እኔ ነኝ ”ἐγὼ εἰμί ” ፥ ዛሬም ከሰልፍ ኮበለልሁ አለ። ግሪክ ሰፕቱአጀንት(LXX)
2ሳሙ.20:17፤ ወደ እርስዋም ቀረበ፤ ሴቲቱም። ኢዮአብ አንተ ነህን? አለች። እርሱም። እኔ ነኝ ”ἐγὼ εἰμί ” ብሎ መለሰላት። ግሪክ ሰፕቱአጀንት(LXX)
መልስ
የሙስሊሙ ሙግት በእጅጉ የተሳሳተ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቦታ “እኔ ነኝ” የሚለውን ቃል የተጠቀመው ምን ዓይነት ህልውና እንዳለው ለማመልከት እንጂ ከላይ ከተጠቀሱት ጥቅሶች ጋር በሚመሳሰል መንገድ አይደለም። የአይሁድ ጥያቄ “ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን?” የሚል እንደነበር ልብ ይሏል (ቁ. 57)። ስለዚህ ጥያቄው ኢየሱስ አብርሃም ከመወለዱ በፊት ነበረ ወይስ አልነበረም? የሚል ነው። ጌታችን ለጥያቄው ምላሽ ሲሰጥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ” በቀጥተኛ ትርጉሙ “እኔ ነኝ” በማለት ነበር። ይህም የሚያሳየው ከአብርሃም ልደት በፊት ህልውና ያለው መሆኑን ነው። ሙስሊሙ ሰባኪ ይህንን እውነታ ከስሌቱ ውጪ በማድረግ ነው እየሞገተ ያለው። ለዚህ ነው ስሁት ሙግት ነው ያልነው።
አብዱል
ነጥብ ሁለት
ኤህዬህ አሸር ኤህዬህ אֶֽהְיֶ֖ה אֲשֶׁ֣ר אֶֽהְיֶ֖ה
ዘጸ 3:14 እግዚአብሔርም ሙሴን፦ ኤህዬህ አሸር ኤህዬህ אֶֽהְיֶ֖ה אֲשֶׁ֣ר אֶֽהְיֶ֖ה አለው እንዲህ ለእስራኤል ልጆች። «ኤህየህ אֶֽהְיֶ֖ה » ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ አለው።
የዘጸ 3:14 ያለው ኤህየህ אֶֽהְיֶ֖ה እኔ ነኝ ሁለት ጊዜ የመጣ መሆኑ ከግሪክ ሰፕቱአጀንት ኢጎ ኤይሚ እኔ ነኝ ይለያል፣ ከዛም ባሻገር ለኖርማር የምንጠቀምብበት እኔ ነኝ በዕብራይስጥ አኒ ሁ אָֽנֹכִי֙ ነው፣ በዚህም የቋንቋ ሙግት የተነሳውን እሳቤ ፉርሽ ይሆናል፣ ኢየሱስ በአረማይክ እኔ ነኝ የሚለውውን ቃል ምን ብሎ እንደነበር የሚያሳይ ስረ-መሰረትnetin ስለሌለ የተነሳውውን እሳቤ ድምጥማጡን ያጠፋዋል፣ ምክንያቱም ኢየሱስ ሆነ ነቢያት ግሪክ ተናጋሪ አልነበሩም፣ አንዱ አምላክ ሙሴን ሲያናግር የነበረው በዕብራይስጥ እንጂ በግሪክ አልነበረም፣ አይ እኔ ነኝ በዕብራይስጥ አኒ ሁ ለአምላክነት መስፈርት ነው ካችሁን እንግዲያውስ ብዙ ሰዎች እኔ ነኝ በዕብራይስጥ አኒሁ ብለው የተጠቀሙ ናቸው፣ እነርሱስ አምላክ ናቸውን?
1ሳሙ.4:16፤ ሰውዮውም ዔሊን። ከሰልፍ የመጣሁ እኔ ነኝ ”’אָֽנֹכִי֙ ” ፥ ዛሬም ከሰልፍ ኮበለልሁ አለ።
2ሳሙ.20:17፤ ወደ እርስዋም ቀረበ፤ ሴቲቱም። ኢዮአብ አንተ ነህን? አለች። እርሱም። እኔ ነኝ ””אָֽנֹכִי֙ ” ብሎ መለሰላት።
መልስ
በመጀመርያ ደረጃ የግሪክ ሰብቱጀንት “ኢጎ ኤይሚ ሆ ኦን” በማለት ነው የተረጎመው። ይህም የእብራይስጡን ሐሳብ በትክክል የሚገልጽ ነው። የግሪክ ሰብቱጀንት በክርስቶስና በሐዋርያቱ ዘመን በስፋት ጥቅም ላይ ሲውል የነበረ ትርጉም በመሆኑ የጌታ ሐዋርያት ሲጠቀሙበት ነበር። ስለዚህ ጥያቄው እነርሱ በተጠቀሙበት ትርጉም የእብራይስጡ ሐሳብ ምን ተብሎ ተወከለ? የሚል ነው። አረማይክም ቢሆን እንደ ግሪኩ ሁሉ የእብራይስጥ ትርጉም እንጂ ከእብራይስጥ ጋር አንድ ባለመሆኑ ክርስቶስ ጌታችን በአረማይክ ሲናገር እብራይስጡን ወደ አረማይክ በመተርጎም ነው ሊሆን የሚችለው። ስለዚህ የግሪኩ ትርጉም ለአምላክ ጥቅም ላይ የዋለውን አባባል የወከለበትን መንገድ ዮሐንስ ከነገረን የእብራይስጡን ማጣቀስ የሚኖረው ፋይዳ ኦሪጅናል ቃሉ ምን እንደሆነ ከማወቅ የዘለለ አይሆንም።
በሁለተኛ ደረጃ በእብራይስጥ ብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር አምላክ “አኒሁ” (እኔ ነኝ) ብሎ የተናገረባቸው በርካታ ጥቅሶች የሚገኙ ሲሆን ሰብዓ ሊቃናት “ኢጎ ኤይሚ” በማለት ተርጉመውታል (ኢሳ. 41፡4፣ 43፡10-13፣ 46፡4)። ስለዚ በሙስሊሙ ሰባኪ አባባል “ለኖርማር” (ኖርማል ለማለት ነው) ጥቅም ላይ የሚውለው የእብራይስጥ ቃል “አኒሁ” በብሉይ ኪዳን ውስጥ ለእግዚአብሔር በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ስለዋለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠቀመው በብሉይ ኪዳን ለእግዚአብሔር ጥቅም ላይ የዋለውን ቃል ነው ማለት ነው። አባባሉን ሰብዓውያን መጠቀማቸው ምንም ለውጥ አያመጣም ምክንያቱም ጌታችን የተጠቀመበት አጠቃቀም ዘላለማዊ መሆኑን በሚያመለክት አውድ እንጂ እንደ ሰብዓውያን አይደልምና።
አንዱ አምላክ ሙሴን ሲያናግር የነበረው በእብራይስጥ በመሆኑና ነቢያት ግሪክኛ ተናጋሪ ባለመሆናቸው ግሪኩ ተቀባይነት የለውም ከተባለ ተመሳሳይ የሙሴ ታሪክ በአረብኛ ቁርአን ውስጥ ስለሚገኝ አረብኛውም ተቀባይነት የለውም ማለት ነው? ይህ የሙስሊሙ ሰባኪ ሙግት ለግሪኩ ሠርቶ ለአርብኛው የማይሠራበት ምክንያት ምንድነው? እንዲህ ያለ ሙግት እስልምናን ጭምር የሚያፈርስ ማስተዋል የራቀው ሙግት ነው።
አብዱል
የአውድ ሙግት
ዮሐ 8.56-58 አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው። አይሁድም። ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት። ኢየሱስም፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ ἐγὼ εἰμί አላቸው።
ኢጎ ኤይሚ ἐγὼ εἰμί እኔ አለሁ የሚልም ፍቺ ይኖረዋል፣ ይህም ጥቅስ ቢሆን የኢየሱስን ከመወለዱ በፊት ያለውን ቅድመ-ህልውና ኣያሳይም ብዬ ክፉኛ እሞግታለሁኝ፣ ምክንያቱም አብርሃም ኢየሱስ የተወለደበትን ቀን በእውነቱ አይቶታል ወይ? ነጥቡ ያለው እዚህ ጋር ነው፣ አይ አብርሃም ኢየሱስ ያየው በተስፋ ቃል ከተባለ፣ በተመሳሳይ የአይሁድ ጥያቄ፦ ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? ነበር፣ አብርሃም ኢየሱስ በተስፋ ቃል አይቶ ከተደሰተ ኢየሱስም አብርሃምን በተስፋ ቃል ደረጃ አይቶታል፣ ምን ኣብርሃም ብቻ አብርሃም ሳይወለድ ሄኖክ፣ ኣቤልና ኖህ አይተውታል፦
ዕብ.11:13 እነዚህ ሁሉ (ኣብርሃም፣ ሄኖክ፣ ኣቤልና ኖህ) አምነው ሞቱ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፥
አስተዋላችሁልኝ? አብርሃም ሳይወለድ ሄኖክ፣ ኣቤልና ኖህ ኢየሱስን በተስፋ ቃል አዩትና ተሳለሙት እንጂ በህልውናማ ደረጃ መቼ ነበርና አይተው ይስሙታል? የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና የሚለው ይሰመርበት፥ አይሁድም። ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት። አብርሃም ሳይወለድ ሄኖክ፣ ኣቤልና ኖህ ኢየሱስ አይተው ከተሳለሙት ኢየሱስ አብርሃምን ብቻ ሳይሆን አብርሃም ሳይወለድ ሄኖክን፣ አቤልን፣ ኖህን አይቷል፣ የኢየሱስና የአብርሃም፣ ሄኖክ፣ አቤል፣ ኖህ መተያየት ፍካሬአዊ እንጂ እማሬአዊ እንዳልሆነ ሁሉ ኢየሱስም አብርሃም ከመወለዱ በፊት መኖሩ በተስፋ ቃል እንጂ በህልውና አይደለም፣ ይህን በቀላሉ ለመረዳት አንድ ሳይወለድ በፊት በተስፋ ቃል ይኖር የነበረ ሰው ለናሙና እናቅርብ፦
ዕብ 7:9-10 ይህንም ለማለት ሲፈቀድ፥ አሥራትን የሚያስወጣ ሌዊ እንኳ በአብርሃም እጅ አሥራትን ሰጥቶአል፤ መልከ ጼዴቅ በተገናኘው ጊዜ ገና በአባቱ ወገብ ነበረና።
ሌዊ የኣብሃም የልጅ ልጅ ልጅ ነው፣ ኣብርሃም ደግሞ ቅድመ-ኣያቱ ነው፣ ነገር ግን ሌዊ ሳይወለድ በፊት ለመልከ ጼዴቅ አሥራትን ሰጥቶአል፣ ሌዊ እንኳ በአብርሃም እጅ አሥራትን ሰጥቶአል የሚለው ይሰመርበት፣ ያኔ ሌዊ የት ነበር ? ስንል በኣብርሃም ወገብ ነበረና፣ በአባቱ ወገብ ነበረና የሚለው ይሰመርበት፣ ታዲያ ሌዊ በምን ደረጃ ነበር ስንል በህልውና ሳይሆን በተስፋ ቃል ነው፦
ዕብ.7:6 ትውልዱ ከእነርሱ የማይቈጠረው ግን ከአብርሃም አሥራትን አውጥቶአል፥ የተስፋ ቃል የነበረውንም ባርኮአል።
የተስፋ ቃል የነበረውንም የሚለው ይሰመርበት። ሌዊ በኣብርሃም ወገብ የተስፋ ቃል ሆኖ ለመልከ ጼዴቅ አሥራትን ከሰጠ፣ ኢየሱስ በኣቤል፣ በሄኖክ፣ በኖህ ወገብ ሆኖ በተስፋ ቃል ደረጃ ቢኖር ምን ያስደንቃል? ኢየሱስ የነቢያት የተስፋ ቃል ዘር አይደል እንዴ፦
ሐዋ.13:23 ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ።
መልስ
ከላይ የሚገኘው “ሙግት” የተለያዩ ሐሳቦችን በማደበላለቅ የተፈጠረ ለአቅመ ሙግት የማይበቃ ቧልት ነው። ሲጀመር ጥያቄው አብርሃም በተስፋ ደረጃ ኢየሱስን አይቶታል አላየውም፤ ሌሎች ነቢያትስ በተስፋ አይተውታል አላዩትም? የሚል ሳይሆን ኢየሱስ አብርሃምን አይቶታል አላየውም? የሚል ነው። አብርሃም ኢየሱስን ያየው በተስፋ ነው ብንል እንኳ በተስፋ ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ ስለማንመለከት ከአብርሃም በኋላ የተወለደው ክርስቶስ በተስፋ አብርሃምን አይቶታል ማለት ትርጉም አይሰጥም። ወደ ኋላ የምንመለከተው ወይ በትዝታ ወይም ደግሞ በታሪክ ነው። ጌታችን አብርሃምን እንዳየው ሲናገር አብርሃም ሳይወለድ በፊት በመኖሩ ምክንያት መሆኑን ግልጽ አድርጓል፤ ስለዚህ አብርሃምን ያየው በአብርሃም ዘመን በመገኘት በገሃድ ነው።
የሌዊ ለመልከ ጼዴቅ አሥራትን መክፈል የሙስሊሙን ሙግት የሚደግፍ አይደለም ምክንያቱም በአብርሃም ወገብ ውስጥ ሆኖ አሥራትን እንደከፈለ የተነገረው የአብርሃም ዘር በመሆኑ ምክንያት አብርሃም የፈጸመው ተግባር ለእሱም ተቆጥሮለታል በሚል ስሌት ነው። የዕብራውያን ጸሐፊ ያቀረበውን አጠቃላይ ሙግት ስንመለከት አብርሃም በሥልጣን ከመልከ ጼዴቅ በታች ሆኖ አሥራትን ስላወጣለት አሥራት የሚወጣለት ሌዊም ከመልከ ጼዴቅ ያንሳል ስለዚህ የሌዊ ዘር ከሆነው ከአሮን የላቀ የክህነት ሥልጣን ያለው እንደ መልከ ጼዴቅ ያለ ካህን ያስፈልገናል እርሱም ክርስቶስ ነው የሚል ነው። ምንም እንኳ ክርስቶስ ራሱ ከአብርሃም ዘርና ከይሁዳ ነገድ ቢሆንም የክህነት ሥልጣኑ እንደ አሮን ሳይሆን እንደ መልከ ጼዴቅ የሆነበት ምክንያት ኢ-ሟቲ ሕይወት ያለው በመሆኑ እንደሆነ ዕብራውያን 7፡15 ላይ ተጽፏል። በዕብራውያን ጸሐፊ መሠረት ክርስቶስ ጌታችን ሁሉን የፈጠረ መለኮት እንጂ ፍጡር አይደለም (ም. 1)።
ሌላው መታወቅ ያለበት ነገር የአብርሃም ኢየሱስን ማየት በተስፋ ቃል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በገሃድም ጭምር መሆኑ ነው። በዘመነ ብሉይ ጌታ በተለያየ መልክ ለሰዎች ይገለጥ ነበር። ለምሳሌ ያህል ለአብርሃም ከተገለጡት ሦስቱ እንግዶች መካከል አንደኛው ጌታችን መሆኑን ብዙ የነገረ መለኮት ሊቃውንት የሚስማሙበት እውነታ ነው (ዘፍጥረት 18)። በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ከኖረው ከዮስቶኒዮስ ሰማዕት ጀምሮ የነበሩት አበው ቃሉን ሲረዱ የነበሩት በዚሁ መንገድ ነበር። የአብርሃም ኢየሱስን ማየት በተስፋ ቃል ነው ቢባል እንኳ የኢየሱስ አብርሃም ሳይወለድ በፊት መኖር በተስፋ ቃል ሳይሆን በኑባሬ ስለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። በመጀመርያ ደረጃ በተስፋ ቃል መኖሩን ለማመልከት “ኢጎ ኤይሚ” የሚል አባባል የተጠቀመ ማንም የለም። ቃሉ የተጠቀሰበት ቦታ ላይ ሁሉ አካላዊ ኑባሬን ለማመልክት ብቻ ጥቅም ላይ ውሎ እንመለከታለን። ለዚህ ማስረጃ ሙስሊሙ ሰባኪ ራሱ የጠቀሳቸውን ጥቅሶች መመልከት ይቻላል። ሙስሊሙ ሰባኪ የተጠቀመው ሙግት ከመቶ አመታት በፊት የተተወ ያረጀ ያፈጀ ሙግት ነው፤ ምክንያቱም በግሪክ “ኢጎ” የሚለው ጠንካራ አነጋገር ኢየሱስ ራሱ በማንነቱ ዘላለማዊ ህልውና እንደነበረው የሚያሳይና በሌላ መንገድ ሊተረጎም የማይቻል መሆኑ ነው። (Bowman. Jehovah’s Witnesses & Jesus, p. 113)። ለዚህ ነው ለዘብተኛ ምሑራን እንኳ ሳይቀሩ ቃሉ የክርስቶስን አካላዊና ዘላለማዊ ህልውና እንደሚያመለክት አምነው የተቀበሉት። ለምሳሌ ያህል በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐተታ እንዲህ ይላል፦
Since Abraham is the most important figure for the Jews, they now ask how Jesus can have met him. Jesus answers with an ego eimi formula different from that in w. 24 and 28, because it is part of a normal sentence. He contrasts Abraham’s birth with his own sovereign being that transcends time. One might compare Ps 90:2, ‘Before the mountains were brought forth… you are God.’ Jesus has been able to see Abraham because he was before him. This assertion is considered as a blasphemy and therefore the Jews want to stone him (Lev24:16).
“ለአይሁድ አብርሃም ወሳኝ ስብዕና በመሆኑ ኢየሱስ እንዴት ሊያየው እንደቻለ ጠየቁት። ኢየሱስም ቁጥር 24 እና 28 ላይ ከሚገኘው ለየት ባለ ኢጎ ኤይሚ በሚለው ቀመር መለሰላቸው፤ ምክንያቱም ያኛው የመደበኛ ዐረፍተ ነገር አካል ነውና። የአብርሃምን ልደት ከጊዜ በላይ ከሆነው ከገዛ ራሱ ሉኣላዊ ኑባሬ ጋር አነጻጸረ። መዝሙር 90፡2 ላይ “ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ” ከሚለው ጋር ማነጻጸር ይቻላል። ኢየሱስ አብርሃምን ማየት ችሏል ምክንያቱም ከአብርሃም በፊት ነበረና። ይህ አባባል የክህደት ስድብ ተደርጎ ስለሚቆጠር አይሁድ ሊወግሩት ፈለጉ (ሌዋ. 24፡16)።” John Barton & John Muddiman: The Oxford Bible Commentary, Oxford University Press, 2001, p. 977-978
ይህ ሐተታ በጣም ለዘብተኛ በሆኑ ሊቃውንት የተጻፈ ቢሆንም የጥቅሱን ትክክለኛ ትርጓሜ አስቀምጧል፡፡ ሙስሊሙ ሰባኪ በሊቃውንት ዘንድ ቦታ የሌለው ደካማ ሙግት ይዞ ነው እየሞገተ ያለው።
ሁለተኛ የዮሐንስ ወንጌል የኢየሱስን ቅድመ ህልውና ሲገልጽ ለመጀመርያ ጊዜ አይደለም። በዮሐንስ መሠረት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ፍጥረት የነበረ ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረ አምላክ ነው፦
“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።” (ዮሐንስ 1፡1-2
“ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” (ቁ. 9-12)።
“ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” (ቁ. 14)
በወንጌሉ መሠረት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ልደቱ ከአብ ጋር በሰማይ የነበረ፣ ከአብ የወጣና ከሰማይ የወረደ እንጂ ከልደቱ በኋላ መኖር የጀመረ አይደለም፡-
“እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል?” (ዮሐንስ 6፡62)
“ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።” (ዮሐንስ 3፡13)
“ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና።”(ዮሐንስ 6፡38)
መጥምቁ ዮሐንስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ከእርሱ የላቀ እንደሆነ ሲመሰክር እንዲህ አለ፡-
“ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው።” (ዮሐንስ 3፡31)
በሌላ ቦታ መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስ ከእርሱ በፊት የነበረ መሆኑን እንዲህ ሲል መስክሯል፡-
“ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ፦ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ።” (ዮሐንስ 1፡15)
“አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው።” (ዮሐንስ 1፡30)
መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን በስድስት ወር የሚበልጠው ሆኖ ሳለ ከእርሱ በፊት እንደነበረ መናገሩን ያስተውሏል!
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ ዓለም አለመሆኑን እንዲሁም ከልደቱ በፊት የነበረ መሆኑን የተናገረበት አጋጣሚ የዮሐንስ ወንጌል 8 ላይ ይገኛል፡-
“ኢየሱስም ደግሞ፦ እኔ እሄዳለሁ ትፈልጉኛላችሁም በኃጢአታችሁም ትሞታላችሁ እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አላቸው። አይሁድም፦ እኔ ወደ ምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም ማለቱ ራሱን ይገድላልን? እንጃ አሉ። እናንተ ከታች ናችሁ፥ እኔ ከላይ ነኝ፤ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፥ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም። እንግዲህ፦ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤ እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና አላቸው። እንግዲህ፦ አንተ ማን ነህ? አሉት። ኢየሱስም፦ ከመጀመሪያ ለእናንተ የተናገርሁት ነኝ።” (ዮሐንስ 8፡21-25)
እንግዲህ በዚህ አውድ ውስጥ ነው ጌታችን እንዲህ ሲል የተናገረው፦
“አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው። አይሁድም፦ ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት። ኢየሱስም፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው። ስለዚህ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ።” (ዮሐንስ 8፡56-59)
ጌታችን ከአብርሃም በፊት መኖሩን የተናገረው በቀጥተኛ ንግግር ባይሆንና ተምሳሌታዊ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ያለ ንግግር በመናገር በአይሁድ ዘንድ ድንጋጤ እንዲፈጠር ባላደረገ ነበር። እነርሱም ሊወግሩት ድንጋይ ባላነሱ ነበር።
አብዱል
መደምደሚያ
እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል የኣብርሃምን የወገቡ ፍሬ፣ የዳዊትን የሆዱ ፍሬ፣ የማርያም የማህጸና ፍሬ ኢየሱስን አመጣ እንጂ እግዚአብሔር ጋር ሆኖ እየረዳና እያገዘ የሚኖር አምላክ አልነበረም ፦
ኢሳይያስ 44:24 ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ ከእኔ ጋር ማን ነበረ?
ዘዳ.32:39፤ አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤
ዘዳ 32:12 እግዚአብሔር ብቻውን መራው፤ ከእርሱም ጋር ሌላ አምላክ አልነበረም።
እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ማን ነበረ እያለ, ነቢያትም ከእርሱ ጋር ሌላ አምላክ አልነበረም እያሉ ተመልሰን ለምንድን ነው ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር ኣብሮ ነበረ የምንለው?
ስለዚህ ዮሐ 8:58 የኢየሱስ አምላክነት አሊያም የእርሱን ከመወለዱ በፊት ያለውን ቅድመ-ህልውና ከቶ ኣያሳዪም።
መልስ
እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ማንም እንዳልነበረ ተናገሮ ሳለ ኢየሱስ ከእርሱ ጋር እንደነበረ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚናገሩበት ምክንያት ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃልና ጥበብ ስለሆነ ነው። የሙስሊሞች ስህተት የሚመነጨው ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ኢየሱስ ማንነት የሚሰጡትን ይህንን ምስክርነት ካለማስተዋል ነው። እግዚአብሔር አብ ከእርሱ ጋር ማንም እንዳልነበረ ሲናገር አሕዛብ አማልክት ናቸው የሚሏቸውን ጣዖታት ታሳቢ በማድረግ እንጂ የእርሱ ቃልና ጥበብ የሆነውን ኢየሱስን እንዲሁም የእርሱ ኃይል የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ታሳቢ በማድረግ አይደለም። ኢየሱስ እግዚአብሔር አብ ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረበት ቃልና ጥበብ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት እንዲህ ይመሰክራሉ፦
“እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ። ከጥንቱ ከዘላለም ጀምሮ ተሾምሁ ምድር ከመፈጠርዋ አስቀድሞ። ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፥ የውኃ ምንጮች ገና ሳይፈልቁ። ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፥ ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድሁ፥ ምድሪቱንና ሜዳውን ገና ሳይፈጥር የመጀመሪያውንም የዓለም አፈር። ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ፥ በቀላያት ፊት ክበብን በደነገገ ጊዜ፥ ደመናትን በላይ ባዘጋጀ ጊዜ፥ የቀላይን ምንጮች ባጸና ጊዜ፥ ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፥ የምድርን መሠረት በመሠረተ ጊዜ፥ የዚያን ጊዜ እኔ በእርሱ ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ፤ ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፥ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ።” (ምሳሌ 8፡22-30)
“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።” (ዮሐንስ 1፡1-2)
“እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል።” (ቆላስይስ 1፡15-17)
“ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ኹሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ኾኖ፥ ኹሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” (ዕብራውያን 1፡1-3)
“ደግሞ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ኹሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል፡፡” (ዕብራውያን 1፡10-12)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ አምላክ ነው። ውድ ሙስሊም ወገኖቻችን፤ የሕይወት ምንጭ ወደሆነው ወደ እርሱ ትመጡ ዘንድ ጥሪ እናቀርብላችኋለን። እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦
“መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” (የሐዋርያት ሥራ 4፡12)