ኤል-ጊቦር – አስደናቂው ትንቢትና የሙስሊም ሰባኪያን ክህደት

ኤል-ጊቦር

አስደናቂው ትንቢትና የሙስሊም ሰባኪያን ክህደት

የጌታችንን ልደት መታሰብያ በዓል ምክንያት በማድረግ ሙስሊም ወገኖች በማሕበራዊ ሚድያ ሲቀባበሉ የነበሩት አንድ ጽሑፍ ደርሶኝ ነበር፡፡ ጽሑፉ የተዘጋጀው የቋንቋ ምሑር ለመምሰል በሚጥር ነገር ግን መሳሳት በማይሰለቸው አንድ ሰለምቴ ነኝ ባይ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን የሚያውቁ ወገኖች ቦታ ሊሰጡት የሚችሉት ዓይነት ሙግት በውስጡ አይገኝም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ወንድሞች መልስ እንድሰጥበት በጠየቁኝ መሠረት ለሙስሊም ወገኖቻችንና መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ጠንቅቀው ለማያቁ ክርስቲያኖች ጥቅም ስል መልስ ልሰጠው ወስኛለሁ፡፡ ጸሐፊው እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-

ኃያል አምላክ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኛ በሆነው፡፡

2274 አላህን ተገቢ ክብሩን አላከበሩትም፡፡አላህ በጣም ኃያል አሸናፊ ነው፡፡

ብዙ ዐበይት ክርስትና፦አምላክ ተወልዷልብለው ከሚጠቅሷቸው አናቅጽ መካከል ይህ ጥቅስ ነው፦

ኢሳይያስ 96 ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።

ሕጻንየሚለው ኃይለቃል ይሰመርበት። የዚህን ጥቅስ ዐውደንባብ ስመለከት ይህ ሕጻን በወቅቱ የተወለደ ሕጻን ነው፦

ኢሳይያስ 716 ሕፃኑ ክፉን ለመጥላት መልካሙን ለመምረጥ ሳያውቅ የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት አገር ባድማ ትሆናለች።

ኢሳይያስ 84 ሕፃኑ አባቱንና እናቱን መጥራት ሳያውቅ የደማስቆን ሀብትና የሰማርያን ምርኮ በአሦር ንጉሥ ፊት ይወስዳልና

ኢሳይያስ 83 “ወደ ነቢይቱም ቀረብሁ፤ እርስዋም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች

ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልናየተባለው ሕጻን ነቢይቱ የወለደችው ወንድ ልጅ እንደሆነ ፍትውና ቁልጭ አርጎ ያሳያል።

መልስ

ተመልከቱ ይህ ጸሐፊ የጥቅሱን አውድ ከቆረጠ በኋላ አንድና ሁለት ምዕራፎችን ወደ ኋላ ተመልሶ ሌሎች ጥቅሶችን በመጥቀስ አዲስ አውድ ለመፍጠር ሞክሯል፡፡ በተለይም ኢሳይያስ 8፡3 ከኢሳይያስ 9፡6 ጋር የአውድ ቁርኝትም ሆነ የሐሳብ መመሳሰል የለውም፡፡ ይህ ጸሐፊ ግን አንባቢያንን ለማሳሳት በኢሳይያስ 9 ምንባብ ውስጥ ከላይና ከታች የሚገኙትን ሐሳቦች ከቆረጠ በኋላ ከምዕራፍ 7 እና 8 ቆንጥሮ በመውሰድ የተለያዩ ምንባቦችን አንድ ላይ ሰፍቶ አዲስ አውድ ፈጥሯል፡፡ ይህ ዓይን ያወጣ ማጭበርበር ነው፡፡

ኢሳይያስ 7፡7፡14-16 ድንግል አማኑኤልን ስለመውለዷ የሚናገር ሲሆን በብዙ ክርስቲያን ሊቃውንት መሠረት ድርብ ፍፃሜ (double fulfillment) ያለው ጥቅስ ነው፡፡ ይህ ማለት በኢሳይያስ ዘመን ለነበሩት ወገኖች የራሱ ትርጉምና አፈፃፀም የነበረው ሲሆን ፍጹማዊው የትንቢቱ ምልዓት ግን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተዓምራዊ ልደት ነው፡፡ ኢሳይያስ 7 እና 9 ላይ የተጠቀሰው ህፃን አንድ መሆኑ ለጸሐፊው ሙግት ምንም የሚፈይደው ነገር የለም ምክንያቱም ትንቢቱ ድርብ ከሆነ ከኢሳይያስ 9 ጋር መመሳሰል የሚችለው በቀዳሚ ፍፃሜው ሳይሆን በሁለተኛው ፍፃሜው ብቻ ነውና፡፡  ኢሳይያስ 7 መሲሁ ከድንግል እንደሚወለድ የሚናገር ሲሆን ኢሳይያስ 9 ደግሞ ስለ ማንነቱ (አምላክ ስለ መሆኑ) ይናገራል፡፡ ሁለቱም መሲሃዊ ትንቢቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን ምዕራፍ 8፡1-4 የሚናገረው ነቢዩ ኢሳይያስ ስለወለደው ልጅ ሲሆን የአሦር ንጉሥ በደማስቆና በሰማርያ ላይ የሚፈፅመውን ወረራ ለማመልከት ስሙ ማሔር-ሻላል-ሐሽ-ባዝ (ምርኮ ፈጠነ፥ ብዝበዛ ቸኰለ) ተብሎ እንዲጠራ እግዚአብሔር ለነቢዩ ለኢሳይያስ ትዕዛዝ ሰጥቶታል፡፡ የዚህ ህፃን ሌላኛው ስም አማኑኤል ሊሆን እንደሚችልና የመጀመርያው የትንቢቱ ፍፃሜ ሊሆን እንደሚችል ግምት ቢኖርም ኢሳይያስ 9 ላይ የሚገኘው ትንቢት በዚህ መንገድ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ትንቢቱ ራሱን የቻለና በመሲሁ ልደት ብቻ ሊፈፀም የሚችል ነው፡፡ “ህፃን” የሚል ቃል በሦስቱም ቦታዎች ላይ ስለተጠቀሰ” ብቻ ሁሉንም አንድ ማድረግ የሚያስኬድ ሎጂክ አይደለም፡፡ “ህፃን” የተባለ ሁሉ አንድ ሰው ይመስል ጸሐፊው ሕጻን የሚለው ኃይለቃል ይሰመርበት” የሚል ማሳሰብያ መስጠቱ የማሰብ አቅሙን የሚያስገመግም ያላዋቂ ንግግር ነው፡፡

ጸሐፊው ይቀጥላል፡-

ይህ ሕጻን የማዕረግ ስሙ፦ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃየሚል ነው፥ እነዚህ አራት ስም የሁለት ውሕደት ስም“compound Noun” ናቸው።

መልስ

ይህ ጸሐፊ ራሱን የቋንቋ ምሑር ለማስመሰል ይሞክራል ነገር ግን የማዕርግ ስም (Title) ምን ማለት እንደሆነ አያውቅም፡፡ እነዚህ ስሞች የህፃኑ የማዕርግ ስሞች እንደሆኑ ከተቀበለ የህፃኑ ማንነት ገላጭ መሆናቸውን ተቀብሏል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ “መቶ አለቃ፣ ዶክተር፣ ካፒቴን፣ ንጉሠ ነገሥት፣ ወዘተ.” የሚሉት የማዕርግ ስሞች ናቸው፡፡ መሰል ቃላት ተቀፅላ የሆኑለት ሰው የተጠቀሰው ሙያ፣ ሥልጣን ወይንም ማንነት ባለቤት እንደሆነ የሚያመለክት ነው፡፡ ከተፀውዖ ስምም በላይ የማዕርግ ስሞች የአንድን ሰው ሁኔታ ይገልፃሉ፡፡ አንድ ሰው የተፀውዖ ስሙ “ንጉሥ” ሆኖ በትክክለኛ ማንነቱ ግን ንጉሥ ላይሆን ይችላል፡፡ “ንጉሥ” የሚል የማዕርግ ስም ያለው ሰው ግን በትክክል “ንጉሥ” መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ድንቅ “መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ” የሚለው የህፃኑ ማዕርግ መሆናቸውን ጸሐፊው ስለተቀበለ አምላክነቱን ተቀብሏል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የክርክሩ ነጥብ ምንድነው?

በማስከተል ይህ የዞረበት ጸሐፊ “የማዕርግ ስም” ብሎ ቀደም ሲል የመደባቸውን ቃላት “የተፀውዖ ስም” ከሚል ዕይታ አንፃር ሌላ ትርጉም ለመስጠት ይሞክራል፡፡ እንዲህ ይላል፡-

አጉራ ዘለል መረዳት ያላቸው ሰዎችኃያል አምላክየሚለውን ለአምላክነቱ ከተጠቀሙየዘላለም አባትየሚለውን ለአብነቱ መጠቀም ነበረባቸው፥ ምክንያቱምኤል” אֵ֣ל ማለትምአምላክየሚለው እናአብ” אֲבִ ማለትምአባትየሚለው በዕብራይስጡ በመነሻ ቅጥያ “prefix” አጫፋሪ ስም ሆነው የመጡ ናቸው። ልክኤልጊቦር” אֵ֣ל גִּבּ֔וֹר ለሕጻኑ ስም እንደሆነ ሁሉኤልአብ” “ኤልአታህ” “ኤልናታህ” “ኤልሹአ” “ኤልያህለሰዎች ስም ሆኖ መጥቷል፥ ልክአብአድ” אֲבִיעַ֖ד ለሕጻኑ ስም እንደሆነ ሁሉአብራሃም” “አብጋኤል” “አብአሳፍ” “አብአልቦን” “አብያህለሰዎች ስም ሆኖ መጥቷል። እነዚህ ሰዎችአምላክእናአብእንዳልሆኑ ሁሉ ሕጻኑምአምላክእናአብአይደለም። ቅሉ ግንኤል” אֵ֣ל አምላካዊ ማዕረግን “theo-phoric” እንጂ አምላክ መሆንን እንደማያሳይ ሁሉአብ” אֲבִ አባታዊ ማዕረግን “Patro-phoric” እንጂ አብ መሆን በፍጹም አያሳይም።

መልስ

ከላይ የሚገኘው ሙግት ትርጉም አልባ የሚሆንባቸው ሦስት ምክንያቶች አሉ፡፡ የመጀመርያው ጸሐፊው “ኃያል አምላክ” የሚለው አምላክነትን አያሳይም የሚል ከሆነ ያሕዌ እግዚአብሔር እዚሁ ኢሳይያስ 10፡21 “ኃያል አምላክ” (ኤል-ጊቦር) ተብሎ መጠራቱ አምላክነቱን አያሳይም ይለን ይሆን? “ኃያል አምላክ” ተብሎ የሚተረጎም ንግግር አምላክነትን ካላሳየ ምንነትን ነው የሚያሳየው? ትዝብት ላይ የሚጥል ክህደት ነው፡፡

ሙግቱ ትርጉም አልባ የሚሆንበት ሁለተኛው ምክንያት ጸሐፊው “የዘላለም አባት” (አቢ-ያድ) ምን ማለት እንደሆነ አለማወቁ ነው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ መሲሁ “የዘላለም አባት” ተብሎ መጠራቱ እግዚአብሔር አብ ነው የሚል ሐሳብ የለውም፡፡ በእብራይስጥ አቢ-ያድ የሚለው ቃል መሲሁ ዘላለማዊ ብቻ ሳይሆን የዘላለማዊነት የራሱ ምንጭና አስገኚ መሆኑን ለማመልከት የመጣ ነው፡፡ ይህ አባባል ዘላለም (Eternity) ራሱ በጌታችን የተፈጠረ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ የሰው ቃል መግለፅ በሚችለው የመጨረሻው አገላለፅ አምላክነቱን ለማስረዳት የታለመ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

ሙግቱን ትርጉም አልባ የሚያደርገው ሦስተኛው ነጥብ ትንቢቱ ለመሲሁ የተነገረ መሆኑን አውዱ ማመልከቱን እንዲሁም የተጠቀሱት ቃላት የመሲሁን አምላክነት የሚያመለክቱበት መሠረታዊው ምክንያት ከተጠቀሱበት አውድ አንፃር መሆኑን ጸሐፊው አለማስተዋሉ ነው፡፡ የጥቅሱ ሙሉ አውድ እንዲህ ይነበባል፡-

“ነገር ግን ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም። በመጀመሪያው ዘመን የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር አቃለለ፤ በኋለኛው ዘመን ግን በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ ያለውን የአሕዛብን ገሊላ ያከብራል። በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው። ሕዝብን አብዝተሃል፥ ደስታንም ጨምረህላቸዋል፤ በመከር ደስ እንደሚላቸው፥ ሰዎችም ምርኮን ሲካፈሉ ደስ እንደሚላቸው በፊትህ ደስ ይላቸዋል። በምድያም ጊዜ እንደ ሆነ የሸክሙን ቀንበር የጫንቃውንም በትር የአስጨናቂውንም ዘንግ ሰብረሃል። የሚረግጡ የሰልፈኞች ጫማ ሁሉ፥ በደምም የተለወሰ ልብስ ለቃጠሎ ይሆናል፥ እንደ እሳት ማቃጠያም ሆኖ ይቃጠላል። ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም። የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል።” (ኢሳይያስ 9፡1-7)

ጥቅሱ ስለገሊላ በመናገር እንደሚጀምር ልብ በሉ፡፡ እግዚአብሔር በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ ያለውን ቀደም ሲል ተዋርዶ የነበረውን የአሕዛብ ገሊላ እንደሚያከብር ይናገራል፡፡ ይህ በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወቅቱ የነበሩት የአይሁድ ሊቃውንት ባልጠበቁት ሁኔታ ከተናቀው የገሊላ ግዛት ነበር የመጣው፡፡ በወቅቱ የነበሩት አይሁድ መሲሁን ከገሊላ አይጠብቁትም ነበር፡፡ በትንቢቱ መሠረት ግን እግዚአብሔር ገሊላን አከበረ፡፡ (ማቴ. 3፡13፣ 4፡15፣ 4፡25፣ 21፡11፣ ማር. 1፡9፣ ሉቃ. 4፡14፣ ዮሐ. 7፡41-52)

የጥቅሱ መዝጊያ ህፃኑ በዳዊት ዙፋን ላይ ሆኖ ለዘላለም እንደሚገዛ ይናገራል፡፡ በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀምጦ ለዘላለም የሚገዛው መሲሁ ብቻ ነው፡፡ ደግሞስ ተራ ፍጡር ዘላለማዊ መንግሥት ሊኖረውና ፍፃሜ የሌለው ሰላም ሊሰጥ የሚችለው እንዴት ነው? ይህ በክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ወቅት የምድር መከራ ሲያከትም የሚከሰት ክስተት ነው፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ፍፃሜ የሌለው ሰላም ያሰፍናል ተብሎ የሚታመን ሰብዓዊ መሪ የለም፡፡

ጸሐፊው ሙግቱን እንዲህ ሲል ይቀጥላል፡-

ሙግቱን አጥብበን ሕጻኑ ኢየሱስ ነው ብለን ብንቀበል እንኳን ኢየሱስ አምላክ እና አባት ነው ማለት አይደለም፥ ምክንያቱም ኢየሱስ የራሱ አምላክ እና አባት አለው፦

2ቆሮንቶስ 13 “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እና አባት ይባረክ።

ኢየሱስ አባትነቱ ለእኛ እንጂ የራሱ አባት አለውካላችሁ እንግዲያውስ አምላክነቱ ለእናንተ እንጂ የራሱ አምላክ አለው። ይህም አባት እና አምላክ የሁሉም አንድ አባት እና አንድ አምላክ ነው፦

ሚልኪያስ 210 ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን?

ኤፌሶን 46 ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።

ኢየሱስየእኔ አምላክ” “የእኔ አባትየሚለው ይህንን አንድ አምላክ እና አንድ አባት ነው፦

ዮሐንስ 2017 “እኔወደ አባቴ እና ወደ አባታችሁ፥ ወደ አምላኬ እና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁብለሽ ንገሪአቸው፤ አላት።

ወደየሚለው መስተዋድድእኔየሚለውን ማንነት ከአንዱ አምላክ እና ከአንዱ አባት ነጥቶ ቁጭ አርጎታል።አምላክበሚለው መድረሻ ቃል ላይየነበረውን ሳድስ ወደኃምስ ስናመጣውበሚለው ቃል ውስጥየእኔየሚል በውስጠታዋቂ አገናዛቢ ዘርፍ አለ፥አባትበሚለው መድረሻ ቃል ላይየነበረውን ሳድስ ወደኃምስ ስናመጣውበሚለው ቃል ውስጥየእኔየሚል በውስጠታዋቂ አገናዛቢ ዘርፍ አለ። ስዚህ አንዱ አምላክ እና አባት አምላክነቱ እና አባትነቱ ለኢየሱስ ሙሉእኔነትእንጂ ለስጋው፣ ለሰውነቱ፣ ለቁርበቱ የሚል ድራማና ቁማር አይሠራም።

መልስ

ይህ ሰው በያንዳንዱ አጋጣሚ የአማርኛ ሰዋሰው መምህር ለመሆን ጥረት ከማድረጉ አንፃር ጽሑፉን አንብቦ መጨረስ በራሱ ትዕግስትን ይፈታተናል፡፡ እንዲህ ያለውን ጽሑፍ ማንበብ የተበላሸ ድምፅ ያለው ነገር ግን አጉል ቅላፄ እየቀለፀ ለመዝፈን የሚሞክር የድግስ ቤት ዘፋኝ የመስማት ያህል ቀፋፊ ነው፡፡

“አቢ-ያድ” (የዘላለም አባት – Father of Eternity) የሚለው አገላለፅ ቀደም ሲል እንደተባለው መሲሁ አብ መሆኑን ለማሳየት ሳይሆን የዘላለም ምንጭና አስገኚ መሆኑን ለማመልከት የገባ ነው፡፡ የጠቀሳቸው ጥቅሶች ኢየሱስ የአብ ልጅ መሆኑን የሚያሳዩ እንጂ የዘላለም ምንጭና አስገኚ አለመሆኑን የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ሙግቱ ከጅምሩ በተሳሳተ መረዳት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክም ሰውም መሆኑን የሚያውቅ ሰው አብ አባቱና አምላኩ መሆኑ መነገሩን ጠቅሶ አምላክነቱን ለማስተባበል አይሞክርም፡፡ ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ መለኮት ነው፤ ሥጋ ለብሶ ወደ ምድር በመምጣቱ ደግሞ ሰው ነው፡- “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ…” (ፊል. 2፡6-7)፡፡ ኢየሱስ ከመለኮታዊ ባሕርዩ አንፃር “እኔ” ብሎ መናገሩና ሌላ ጊዜ ደግሞ ከሰብዓዊ ባሕርዩ አኳያ “እኔ” ብሎ መናገሩ ምንም ግራ የሚያጋባ ጉዳይ አይደለም፡፡ እንኳንስ በሰው አካል የተገለጠው መለኮት ይቅርና ሰብዓውያን ፍጡራን እንኳ በአንድ ማንነት ሁለት ሚናዎችን መጫወት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የንጉሥ ልጅ አባቱን “አባቴ እና ንጉሤ” ብሎ መግለፅ ይችላል፡፡ ከእርሱ በመወለዱ ምክንያት አባቱ ነው፤ የአገሪቱ ዜጋ በመሆኑ ምክንያት ደግሞ ንጉሡ ነው፡፡ በሰብዓዊ ፍጡራን ደረጃ በአንድ ማንነት ሁለት ሚናዎችን መጫወት ከተቻለ ሁለት ግልፅ ልዩነት ያላቸውን ባሕርያት በአንድ ማንነት የተላበሰው ኢየሱስ “እኔ” በሚል አንድ ማንነት በሁለት ባሕርያት ራሱን ሊገልፅ የማይችለው እንዴት ነው? በዚህ ግራ የሚጋባ ሰው ካለ ግራ ለመጋባት የወሰነ መሆን አለበት፡፡ እንዲህ ያለ ሰው ደግሞ ቢያስረዱትም ሊገባው አይችልም፡፡

በማስከተል እንዲህ ይላል፡-

ሲቀጥል ወንድ ልጅምተሰጥቶናልበሚለው ኃይለቃል ሕጻኑን የሰጠ ማንነት እንዳለ ያሳያል፥ ሕጻኑ ኢየሱስ ነው ከተባለ ባይብሉ አምላክ ኢየሱስን እንደሰጠ ይናገራል፦

ዮሐንስ 316 “አምላክ” Θεὸς አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና

አምላክ አምላክን ከሰጠ ሁለት አምላክ ይሆናል፥ ቅሉ ግን አምላክ የሰጠው እራሱ ወይም ሌላ አምላክን ሳይሆን ልጁን ነው።

መልስ

ይህ ጸሐፊ ስለ ትምሕርተ ሥላሴ ሰምቶ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ እግዚአብሔር በሦስት አካላት የሚኖር አንድ መለኮት ነው፡፡ አብ ልጁን ኢየሱስን መስጠቱ ልጁ አምላክ እንዳይሆን አያደርገውም፡፡ እግዚአብሔርንና መለኮት የሆነውን ዘላለማዊ ቃሉንም በመነጣጠል ሁለት አምላኮች ልናደርጋቸው አንችልም፡፡ በማንነት ቢለያዩም በምንነት አንድ ናቸውና፡፡ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ…” (ዮሐ. 1፡1)

ቀጥሎ እንዲህ ይላል፡-

ሢሠልስ አምላክ አሊያም አብ ተጠቅልሎ ይተኛልን? ሕጻኑ ግን ተኝቷል፦

ሉቃስ 212 ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምምተኝቶታገኛላችሁ።

ሉቃስ 216 ፈጥነውም መጡ ማርያምን እና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግምተኝቶአገኙ።

አንድ አምላክ አይተኛም፥ አያንቀላፋም። አምላክ አሊያም አብ ያድጋልን? ሕጻኑ ግን አድጓል፦ የአምላክም ጸጋ በላዩ ላይ ነበረ፦

ሉቃ2:40 “ሕፃኑም አደገ ጥበብም ሞልቶበት በመንፈስ ጠነከረ፤ የአምላክም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ።

ሉቃስ 252 ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በአምላክ እና በሰው ፊትያድግነበር።

የአምላክም ጸጋ በአምላክ ላይ ነበረ፥ አምላክ በአምላክ ፊት ያድግ ነበርትርጉም አይሰጥም። አምላክ አሊያም አብ እናት አለውን? ሕጻኑ ግን እናት አለው፦

ማቴዎስ 213 ሕፃኑን እና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ።

ማቴዎስ 220 ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ አለ።

መልስ

ከላይ የሚገኘው ዓይነት ሙግት ለመጽሐፍ ቅዱስና ለክርስቲያናዊ አስተምሕሮ ባይተዋል ለሆነ ሰው ካልሆነ በስተቀር ለሌለው ሚዛን የሚያነሳ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን አውቃለው እያለ ጥቅሶችን ከሚደራርት ሰውም እንዲህ ያለ ሙግት አይጠበቅም፡፡ ሲጀመር በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት እግዚአብሔር ሥላሴ ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ አምላክ ለመሆን የግድ አብ መሆን አለበት የሚለው ምልከታ Strawman Fallacy ነው፡፡ መለኮት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ተወልዶ እንደ ሰው አደገ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ዕብራውያን 4፡15 ላይ “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም” በማለት ይናገራል፡፡ ነገር ግን ከሰማይ የወረደ ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረ አምላክ ነው፡- “ስለ ልጁ ግን፦ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው… ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው…” (ዕብራውያን 1፡8)፡፡ ስለዚህ ስለ ሰውነቱ የሚናገሩትን ጥቅሶች በመጥቀስ አምላክነቱን መካድ የመጽሐፍ ቅዱስን አስተምሕሮ አለማወቅ ነው፡፡

በማስከተል እንዲህ ሲል ይሟገታል፡-

ሲያረብብ ሕጻኑኤልጊቦር” אֵ֣ל גִּבּ֔וֹר ማለትምኃያል አምላክቢባል እንኳንኤልሻዳይ” אֵ֣ל שַׁדַּ֔י ማለትምሁሉን የሚችል አምላክነው ማለት አይደለም። ምክንያቱም ነገሥታት “”ኤልጊቦርተብለዋልና፦

ሕዝቅኤል 3221ኃያላን አምላክበሲኦል ውስጥ ሆነው ከረዳቶቹ ጋር ይናገሩታል፤ በሰይፍም የተገደሉት ያልተገረዙ ወርደው ተኝተዋል።

በእንግሊዝኛው Young’s Literal Translation የሚባለው ትርጉም ይመልከቱ። ዐማርኛው ላይ እና አንዳንድ እንግሊዝኛ ላይ በትክክል ለማስቀመጥ ቢዳዳቸውም ዕብራይስጡ ግንኤልጊቦሪም” אֵלֵ֧י גִבּוֹרִ֛ים በማለት ሳቅማማ አስቀምጦታል፥ጊቦሪም” גִבּוֹרִ֛ים የጊቦር ብዙ ቁጥር ሲሆንኃያላንማለት ነው።

መልስ

ጥቅሱ የሚናገረው ስለ ግብፃውያን ነገሥታት ነው፡፡ የግብፅ ፈርዖኖች ራሳቸውን አማልክት አድርገው ይቆጥሩ ስለነበር እነዚህ አማልክት የተባሉት ነገሥታት ሲዖል ውስጥ መሆናቸውን እየተናገረ ነው፡፡ እነዚህ ራሳቸውን አማልክት አድርገው ሲመለኩ የኖሩት ኃያላን ሲዖል ውስጥ መሆናቸውን በምፀት የሚናገር ጥቅስ “ኤል-ጊቦር” መለኮታዊ ማዕርግ መሆኑን ለማስተባበል ሊውል አይችልም፡፡ ስለዚህ ሙግቱ ገለባ ነው፡፡  ሲጀመር “ኤል” ወይም “ኤሎሂም” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እውነተኛውን አምላክ ወይንም ሰዎች እንደ አምላክ የሚያመልኳቸውን ጣዖታትና ፍጡራን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ “ኤል” ስለተባሉ ብቻ እውነተኛ አማልክት ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ወሳኙ ነጥብ “ኤል” የተባለው አካል እውነተኛውን አምላክ በሚያመለክት መንገድ መጠቀስ አለመጠቀሱ ነው፡፡ ህፃኑ “ኤል-ጊቦር” የተባለው ሰዎች ስላሉት ወይንም ሐሰተኛ አማልክትን በሚያሳይ መንገድ ሳይሆን ያሕዌ እግዚአብሔር ራሱ ነው “ኤል-ጊቦር” ብሎ ለሰዎች ያስተዋወቀው፡፡ “ኤል ሻዳይ” እግዚአብሔርን ለመግለፅ እንደገባው ሁሉ “ኤል ጊቦርም” በተመሳሳይ እግዚአብሔርን ለመግለፅ ጥቅም ላይ ስለዋለ መለኮታዊ ባሕርይን ይገልፃል፡፡

ቀጥሎ እንዲህ ይላል ጸሐፊው፡-

ይህ የተለመደ አገላለጽ ነው፥ኤል” אֵ֣ל የሚለው አጫፋሪ ስም ለቦታ ስም ሆኖ መጥቷል፦

ዘፍጥረት 357 “የዚያንም ቦታ ስምኤልቤቴልብሎ ጠራው

ኤልቤቴል” אֵ֖ל בֵּֽית אֵ֖ל ማለትየቤቴል አምላክማለት ነው። ቦታ አምላክ ነውን? “አይ የቦታው ስም እንጂ ምንነቱ አምላክ አይደለምካላችሁ እንግዲያውስ የሕጻኑ ስም እንጂ ምንነቱ አምላክ አይደለም። ኢሳይያስ 96 “ስሙምስለሚልኃያል አምላክልክ እንደኤልቤቴልየሕጻኑ ስም እንጂ እንደ ያህዌህ በቀጥታኃያል አምላክአልተባለም፦

ኢሳይያስ 1021 “የያዕቆብም ቅሬታ ወደ ኃያል አምላክ ይመለሳሉ

መልስ

“ኤል” ከሰዎችም፣ ከቦታም ስሞች ጋር የመጣባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ነገር ግን የሚሰጠን ምልከታ ሰዎቹን ወይንም ቦታውን አምላክ ለማድረግ የዋለ አለመሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡ ለምሳሌ ያህል “ኤል-ቤቴል” ማለት የቤቴል አምላክ ማለት ነው፡፡ የምን አምላክ? የቤቴል፡፡ ስለዚህ ቤቴል (የአምላክ ቤት) ቦታ እንጂ አምላክ አይደለም፡፡ “ኤል-ጊቦር” ግን “ኃያል አምላክ” ማለት ነው፡፡ ያ አምላክ ምን ዓይነት ነው? ኃያል አምላክ ነው፡፡ አጠራሩ የተጠቀሰው አካል ኃያል አምላክ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ስለዚህ ይለያል፡፡

ኢሳይያስ 10፡21 ላይ “የያዕቆብም ቅሬታ ወደ ኃያል አምላክ ይመለሳሉ” በሚለው ውስጥ “ኃያል አምላክ” ያሕዌ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ በሌሎች ቦታዎችም ላይ ያሕዌ “ኤል-ጊቦር” ተብሎ ተጠርቷል፡- “ለብዙ ሺህ ምሕረት ታደርጋለህ፥ የአባቶችንም በደል ከእነርሱ በኋላ በልጆቻቸው ብብት ትመልሳለህ፤ ስምህ ታላቅና ኃያል አምላክ (ኤል-ጊቦር) የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።” (ኤር. 32፡18)፡፡ በተጨማሪም ሶፎኒያስ 3፡17 ላይ ያሕዌ “ጊቦር” ተብሏል፡፡ መሲሁ በዚሁ ቃል በቀጥታ ተጠርቷል፡፡ ይህ ስም እንደ ሌሎች ስሞች ወደ ሌላ አካል ጠቋሚ ሳይሆን ወደ ራሱ ወደ ተጠሪው ጠቋሚ በመሆኑ የመሲሁን መለኮታዊነት መካድ አይቻልም፡፡ ያሕዌ ራሱ በዚህ ስም ለሰው ልጆች ያስተዋወቀው ሌላ አካል የለም፡፡

ጸሐፊው እንዲህ ሲል ይቋጫል፡-

መቼም በኢሳይያስ ዘመን የተወለደው የነቢይቱ ልጅ ሕጻኑን ስሙ እንጂኃያል አምላክነው እንደማትሉ ሁሉ ኢሳይያስ 96 ላይ ለኢየሱስ ድርብ ትንቢት ነው ካላችሁ እንግዲያውስ ሕጻኑ ኢየሱስ ስሙ እንጂ ምንነቱኃያል አምላክአይደለም። ስለዚህ ብዙ ዐበይት ክርስትና፦አምላክ ተወልዷልየሚለው ድምዳሜአችሁ ሥረመሠረት የሌለው የእምቧይ ካብ ነው።

መልስ

ኢሳይያስ 9፡6 ስለ ነቢይቱ ልጅ ሳይሆን ወደ ፊት ከገሊላ ስለሚመጣው፣ ዘላለማዊ ንግሥና ስላለው ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባትና የሰላም አለቃ ስለሆነው ስለ መሲሁ የሚናገር ነው፡፡ ትንቢቱ ድርብ ነው የሚያስብል ምንም ነገር በቦታው ላይ የለም፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ፍፃሜን ያገኘ አስደናቂ መሲሃዊ ትንቢት ነው፡፡ ይህንን ሃቅ ላለማየት ዓይኖቹን የሚጨፍን ሰው ምንኛ ምስኪን ነው!


 

ድንግል ወይንስ ወጣት ሴት? “የዐልማህ” ትክክለኛ ትርጉም

መሲሁ ኢየሱስ