የእስላማዊ ስነ-ፅንስ ተረክ በዘመናዊ ሳይንስ መነፅር [ክፍል ሁለት]

የእስላማዊ ስነ-ፅንስ ተረክ በዘመናዊ ሳይንስ መነፅር [ክፍል ሁለት]

ዶ/ር ሻሎም መኮንን


የወንዴ ዘር ከየት ይመነጫል?

አንድን ነገር አውቀናል ብለን ስለ እርሱ ማብራርያ ስንሰጥ ለምናብራራውን ነገር መንስኤ ምን እንደሆነ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ማወቅ ይኖርብናል። በተመሳሳይ ስለ ፅንስ ከማውራታችን በፊት ፅንሱን የሚያስገኘውን ነገር ምንነት ማወቅ ለስነ-ፅንስ ዕውቀት መሠረታዊ ነገር ነው። ነገር ግን ቁርአን ላይ “ፅንስ” ያስገኛል ተብሎ የሰፈረው “የወንዴ ዘር መመንጫ ቦታ” ከዘመናዊው የጥናት ግኝት በእጅጉ ያፈነገጠ ነው። እንግዲህ የቁርአን እና የስነ-ፅንስ ሳይንስ በተቃርኖ መቆም የሚጀምረው ገና ከመነሻው ነው።

የወንዴ ዘር የሚመነጭበት የሰውነት ክፍል የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ሊረዱት የሚችሉት በጣም የተወሳሰበ ሳይንስ ሳይሆን ተራ የሆነ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ሳይቀር የሚሰጥ ትምህርት ነው። የወንዴ ዘር የሚመነጨው ከቆለጥ ሲሆን በወሲባዊ መነቃቃት ወቅት ከቋተውዝፍ እና ከፍሰውሃ እጢ  የሚነሱ ፈሳሾች ጋር ይቀላቀላል።  በተጨማሪም ዩሬትራል ግላንድ እና ከቡልቦ ዩሬተር ከሚመጣ ዝልግልግ መሰል ፈሳሾች ጋር ይቀላቀላል።[1]

ነገር ግን ቁርአን እንዲህ ይለናል፦

“ሰውም ከምን እንደተፈጠረ ይመልከት ከተስፈንጣሪ ውሃ ተፈጠረ ከጀርባ እና ከእርግብግብቶች (RIBS) መካከል የሚወጣ ከሆነ ጌታችሁ እርሱ (አላህ) በመመለሱ በእርግጥ ቻይ ነው።” (ሱራ 86: 5-8)

ክፍሉ ግልፅ ቢሆንም ይህንን የቁርአን መሠረታዊ ስህተት የሙስሊም አቃቤያን ለማድበስበስ የሚሞክሩት በሁለት መንገዶች ነው። የመጀመርያው የማስተባበያ መንገድ “በዚህ የቁርአን ክፍል ላይ የቀረበው ንግግር ዘይቤያዊ ገለፃን የሚያመላክት እንጂ ትክክለኛ የወንዴ ዘር የሚወጣበትን የሰውነት ክፍል የሚጠቁም ሀተታ አይደለም” የሚል ነው። ሁለተኛው መንገድ ደግሞ ንግግሩ ግልፅ መሆኑን በመቀበል ነገር ግን ደግሞ ንግግሩን ትክክለኛ ለማድረግ ማብራርያ መስጠት ነው።

የመጀመርያው የማስተባበያ መንገድ ሌላውን ሰው ቀርቶ የክፍሉን ስህተት በሁለተኛው መንገድ ለማረም የሚታትሩ የሙስሊም መምህራንን እንኳን አያስማማም። ቦታው በቀጥተኛ ቃላት፣ እጅግ ግልፅ በሆነ መልኩ በመቀመጡ ቀጥተኛውን ንግግር ገሸሽ በማድረግ “ዘይቤያዊ አገላለፅ ነው ” ብሎ ለመደምደም የሚያስደፍር ነገር አይደለም።

በዚህ የቁርአን ክፍል ላይ በግልፅ፦

  • የፈሳሹ ዓይነት ተስፈንጣሪ መሆኑ ተጠቅሷ።
  • የሚወጣበት የሰውነት ክፍል ተለይቶ በስም ተጠቅሷል።

ቦታው ከእዚህና ከእዚህ መሀል የሚወጣ ተብሎ የተቀመጠን ቀጥተኛ ንግግር እንዴትና በምን መልኩ ነው ዘይቤአዊ ንግግር ነው የምንለው? “የዘይቤያዊ ንግግርን ምንነት የማያውቅ” አልያ ” ግልፅ ቅጥፈት” ለመፈፀም ፈልጎ ካልሆነ በቀር አንድ ሰው ይህንን የቁርአን ክፍል አንብቦ ዘይቤያዊ ንግግር ነው ሊል አይችልም።

ክፍሉ ከሳይንሳዊ ግኝት ጋር የተኳረፈ መሆኑ የገባቸው ሙስሊም መምህራንን “ዘይቤያዊ ገለፃ ነው” የሚሉትን የፈጠራ ማብራርያቸውን እንዳንቀበል የሚያደርገን ከክፍሉ ግልፅነት ባሻገር ሌላ ትልቅ ምክንያት አለ። ክፍሉ ከሳይንሳዊ ግኝት ጋር እንደሚጣረስ የማያውቁ ሙስሊሞች ክፍሉን በምን መልኩ ነው ሲረዱት ነበር? ዘይቤያዊ ገለፃ ነው ሲሉ ነበር? በፍፁም። በሙሐመድ ዘንድ የቁርአን ፍቺ ተሰጠው የተባለውን ሰው ጨምሮ ታላላቅ የእስልምና ሙፈሲሮች የክፍሉን ስህተትነት የሚያጎላ ማብራርያ አክለውበታል።[2]

ለምሳሌ ኢብን ከቲር የወንዴ ዘር ከጀርባ (ሱልብ) እንደሚመነጭ አብራርቶ እርግብግቢት (ተራዒብ) ግን የሴቷን ሰውነት ለማመልከት የገባ እንደሆነ አድርጎ ያብራራዋል።

(ከጀርባና ከእርግብግብቶች መካከል የሚወጣ ከኾነ) ከወንድ የጀርባ አጥንትና ከሴት እርግብግቢት ሲሆን ፈሳሹ ቢጫና ለስላሳ ነው። ከሁለቱም (ወሲባዊ ፈሳሾች) ካልሆነ በቀር ልጅ አይወለድም።

ምንም እንኳን የቁርአን ክፍል ስለ አንድ የፈሳሽ አይነት ቢያወራም ኢብን ከቲር ሱልብ (የጀርባ አጥንት) የወንዴ ዘር መመንጫ ቦታ መሆኑን ተቀብሎ በተጨማሪም የሴቷን ፈሳሽ ለማስገባት ሲል በክፍሉ ላይ ተራዒብ (እርግብግቢት) ተብሎ የተጠቀሰው የሴቷ ፈሳሽ የሚወጣበት የሰውነት ክፍልን እንደሚወክል አድርጎ አቅርቧል።  የወንዱ ፈሳሽ ከጀርባ አጥንት የሴት ልጅ ፈሳሽ ከደረት አጥንት መንጭቶ ካልተቀላቀለ ልጅ እንደማይወለድ ይገልፃል። ማብራርያውን ይቀጥላልል-

ሱልብ” የጀርባ አጥንት ሲሆን “ተረዒብ” ደግሞ እርግብግቢት ወይም የደረት አጥንት ነው። ለሁለቱም ማለትም ለሴትም ሆነ ለወንድ ወሲባዊው ፈሳሽ ከጀርባ አጥንት እና ከእርግብግቢት መካከል ስለሚመነጭ ነው “ሰው ከጀርባ እና ከእርግብግቢት መካከል በሚወጣ ፈሳሽ ተፈጥሯል የሚባለው። የሚገናኘው። ይህ ፈሳሽ ሰው እጁና እግሩ ቢቆረጥ እንኳን መመንጨቱን አይተውም።  ስለዚህ ይህ ፈሳሽ ከሁሉም የሰውነት ክፍል ይመነጫል ብሎ ማሰበ ስህተት ነው። የፈሳሹ ዋነኛ ምንጮች መኖራቸው ቢታወቅም ግን ምንጮቹ በግንዳችን ውስጥ ናቸው። አዕምሮ በዚህ ዝርዝር አልተካተተም። ምክንያቱም የጀርባ አጥንታችን የአእምሯችን ክፍል ነውና። መላው ሰውነታችን በእርሱ አማካኝነት ነው ከአእምሯችን ጋር የሚገናኘው።

የኢብን ከቲር ማብራርያን ጨምሮ ሌሎች እስላማዊ መዛግብትን ብናገላብጥ በምናገኘው መረጃ መሠረት የምንገነዘበው የቁርአኑ ክፍል ትክክለኛው እስላማዊ መረዳት “ዘይቤያዊ አገላለፅ” እንደሆነ ሳይሆን “ቀጥተኛ ንግግር እንደሆነ” ነው።

በጥቅሱ መሠረት ቦታዎቹን ለመግለፅ የተቀመጡት የአረብኛ ቃላት “ሱልብ” እና “ተረዒብ” ናቸው። ሱልብ ማለት ጀርባ፣ የጀርባ አጥንት የሚል ትርጉም ሲኖረው ነጠላ መደብ ቃል ነው። “ተረዒብ” ደግሞ የጎድን አጥንት ሲሆን የብዜት መደብ ያለው ቃል ነው። በሁለቱ መካከል እንደሚወጣ የሚያመለክተው የአረብኛው ግልፅ ቃል “ሚን በይኒ” የሚል ነው። ፈሳሹ እንደሚፈነጠር የሚገልፀው ቃል “ዳፊቅ” ሲሆን  የአረቢኛ ቃል ትንታኔ ውስጥ እንግባ ቢባል እንኳን ቃላቶቹ ቀጥተኛ ና ለጥልቅ ማብራርያ የዋሉ ናቸው።

ፈልያንዙሪል ኢንሳኑ ሚማ ኹሊቅ فَلْيَنْظُرِ الْإِنْسَانُ مِمَّ خُلِقَ

ኹሊቃ ሚን ማኢን ዳፊቅ خُلِقَ مِنْ مَاءٍ دَافِقٍ

ያኹሩጁ ሚን በይኒ አስሱልቢ ወትተረዒብ يَخْرُجُ مِنْ بَيْنِ الصُّلْبِ وَالتَّرَائِبِ

ሁለተኞቹ ለእዚህ ክፍል ምላሽ እንሰጣለን የሚሉ ሙስሊም ሰባኪያን የቁርአን ገለፃ ቀጥተኛና ግልፅ በመሆኑ እንዲሁ በቀላሉ “ይሄ ዘይቤአዊ አነጋገር ነው” ተብሎ ብቻ እንደማይታለፍ የተረዱ ናቸው። ምናልባት የእነዚህኞቹ ማስተባበያ በቁርአን ክፍል ላይ የተጠቀሱትን የሰውነት ክፍሎች መገኛ ቦታን እና የወንዴ ዘር የሚመነጭበትን ቦታ የት እንደሆነ የማያውቁ ሰዎችን ያደናብር ካልሆነ በቀር ፍፃሜው እንደመጀመርያዎቹ ሁሉ ሩቅ መንገድ አይሄድም።

ሁለተኛውን ዓይነት ማስተባበያ ከሚጠቀሙት ምድብ ውስጥ ያሉ የሙስሊም መምህራን የሚያነሱት ነጥብ የጀርባ አጥንት እስከ መቀመጫ (coccyx) ስለሚደርስ የቁርአን ገለፃ የወንዴ ዘር የሚመነጭበትንም የሰውነት ክፍል ያጠቃልላል የሚል ነው። የእነዚኞቹን ሙስሊም መምህራን ማብራርያ የሚገልፅ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ:-

አንድ ሰው  “አበበ እና በለጠ መካከል የቆመችው ልጅ ስሟ ሮዛ ነው” ካለን ንግግሩን ትክክል ነው የምንለው “ሮዛ” የተባለች ሰው “አበበ” እና “በለጠ” መካከል ባለው ስፍራ ከቆመች ብቻ ነው። መካከላቸው ቆማ ያየናት ሌላ ሰው ከሆነች ወይንም መካከላቸው ባለው ስፍራ ውስጥ ሮዛ ከሌለች የጠቆመን ሰው ተሳስቷል ማለት ነው።

የእነዚኞቹ ሙስሊም መምህራን ድምዳሜ “በለጠ” እና “አበበ” መካከል “ሮዛ” ባትኖርም  “በለጠ” የቆመበት አካባቢ “ሮዛ” ስላለች ንግግሩ ትክክል ነው ዓይነት ነው።

ከታች የቀረቡትን ምስሎች በጥንቃቄ ይመልከቱ።

የጀርባ አጥንት እና የጎድን አጥንት መገኛ ቦታ

የጀርባ አጥንት እና የደረት አጥንት መሀከል ከተባለ ሊያመላክት የሚችለው ቦታ

እነዚኞቹ የሙስሊም ሰባኪያን እንደሚሉት የጀርባ አጥንት በእርግጥ እስከመቀመጫ ድረስ ይወርዳል። ቢሆንም ግን የጎድን አጥንት(ribs) ሆድ ላይ እንኳን አይደርስም። ስለዚህ የሁለቱ መሀከል ከተባለ የሚያመለክተው ቦታ አሻሚ አይደለም። በተጨማሪም “ተረዒብ” የብዛት መደብ ስለሆነ “የደረት አጥንቶች እና የጀርባ አጥንት መካከል” ከተባለ የቱ ጋር ለማለት እንደተፈለገ በጣም ግልፅ ነው። ይህ ማስተባበያ እንደማይሠራ ለመገንዘብ ምሁር መሆን ሳያስፈልግ የደረት አጥንቶቹን እና የጀርባ አጥንቱን በመዳበስ ማንኛውም ሰው ማረጋገጥ ይችላል።

ከላይ በምስሎቹ ለማየት እንደሞከርነው በቁርአን “የጀርባ አጥንትና የጎድን አጥንት መካከል” ተብሎ የተገለፀበት ቦታ የሚያከራክር አይደለም። የሙስሊም መምህራን እንደሚሉን ይሁን ብንል እንኳን መቀመጫ ድረስ የሚደርሰው የጀርባ አጥንትን (coccyx) በመያዝ የጎድን አጥንትን የሚያዋስን ቦታ ላይ የፈለገውን ያህል ብናስስ እኛ የማናውቀው ከሰው የተለየ ፍጥረት ተፈጥሮ ካልሆነ በስተቀር በየትኛውም አቅጣጫ በኩል የወንዴ ዘር አይመነጭም። (ከላይ ያለውን ምስል ይመለከቷል።)

የእነዚህኞቹ ሰባኪያን የማስታረቅ ሙከራ እንደሌሎቹ ሁሉ ቢከሽፍም  እንደሚሉት ቋተውዝፍ እና ፍሰውሀ ከጎድን አጥንቶች እና ከጀርባ አጥንት ጫፍ (coccyx ) መካከል ይገኛል እንበል (ባይገኝም)። ነገር ግን ከሴቴ እንቁላል ጋር ተዋህዶ ፅንሱን የሚያስጀምረው ከቆለጥ የሚመነጨው የወንዴ ዘር (sperm) እንጂ ሌሎች አብረውት የተቀላቀሉ ፈሳሾች (semen) አይደሉም። ከወንዴ ዘር ጋር የሚቀላቀሉት ፈሳሾች እና የወንዴ ዘር አንድ ዓይነት አይደሉም ። በሚያሳዝን መልኩ አጥንቶቹ ለእነሱ ስብከት ብለው ቢጠጋጉ እንኳ አንዱን አለፍን ቢሉ ሌላ ወጥመድ እጁን ዘርግቶ ይቀበላቸዋል። አላህ ከየት የሚመጣው የፈሳሹ ክፍል ፅንስ እንደሚፈጥር አያውቅምን? “ሰው ከምን እንደተፈጠረ ይመልከት” ብሎ ፅንስ የማይፈጥሩ ፈሳሾችን መመንጫ ቦታ እንዴት ይጠራል? የሚሉ ጥያቄዎች ይከተላሉ።

ቁርአን በግልፅ ያስቀመጠውን ንግግር “ዘይቤያዊ ገለፃ ነው” ብሎ ለመደምደም ካልደፈሩት የሙስሊም ሰባክያን  መካከል ገሚሱ ክፍሉ በግልፅ “ተስፈንጣሪ ውሃ” ብሎ ያስቀመጠውን ቃል በማጣመም ወደ መራብያ ክፍል የሚሄደውን ደም ለማመልከት ነው ብለው ለማስተባበል ይሞክራሉ። በክፍሉ ላይ  በማያሻማ ቃል፤ ማንም በሚረዳው መልኩ “የሰው ልጅ የተፈጠረበት ተስፈንጣሪ ውሃ” እያለ አይ! አይ! ደም ለማለት ነው” ማለት ከእኛም፣ ከሙስሊም ተሰባኪዎቻቸውም በላይ ቁርአኑ ላይ እንደመሳለቅ ይቆጠራል። በክፍሉ እነዚህኞቹ የሚሉትን “ደም” የሚል ፍቺ አስገብተን እንመልከት፦

 “ሰው ከምን እንደተፈጠረ ይመልከት”

(ክፍሉ ስለሚረጭ ደም የሚያወራ ከሆነ እንዴት ሰው ከውስጡ የሚረጭ ደምን ይመልከት ይባላል? እዴትስ ሊመለከተው ይችላል?)

“ከተስፈንጣሪ ውሃ ተፈጠረ”

(ክፍሉ ስለሚረጭ ደም የሚያወራ ቢሆን ኖሮ ከተስፈንጣሪ ደም እንዴት ተፈጠረ ይባላል? ደሙ ሄዶ ልጅ ይፈጥራል ወይንስ ደሙ ወደ እነዚያ አካላት ሄዶ ልጅ ወደሚፈጥር ፈሳሽነት ይለወጣል?)

“ከጀርባ እና ከእርግብግቢቶች መካከል የሚወጣ ከሆነ”

(የቁርአኑ ክፍል የጠቀሰው አካል ላይ ልጅ የሚፈጥር ተስፈንጣሪ ውሃ ሳይሆን የሚመጣው ደም ነው። እነዚህኞቹ መምህራን ቁርአን ከጠቆመው የሰውነት ክፍል ደም ካልሆነ የወንድ ዘር እንደማይመጣ መቀበላቸውን ያሳያል። )

በዚህ ክፍል ላይ የቁርአን ደራሲ “ደም” ማለት ፈልጎ ቢሆን ደምን የሚወክል የአረብኛ አቻ ቃል እያለ ሌሎች ክፍሎች ላይ የወንዴ ዘር ፈሳሽን ለማመልከት የተጠቀመበትን ቃል ይጠቀማል ብሎ መፍታት የቁርአን ደራሲ የቋንቋ ችግር አለበት ብሎ እንደመክሰስ ይቆጠራል። በክፍሉ ላይ ውሃ ተብሎ የተተረጎመው የአረብኛ ቃል “ማዕ” ሲሆን ሌላ የቁርአን ክፍሎች ላይም የወንዴ ዘርን ለማመልከት የቁርአን ጸሐፊ ተጠቅሞበታል (ሱራ77:20 ሱራ 32:8)። እነዚህኞቹ ሙስሊም ሰባክያን ቁርአን እየጠቀሰው ያለው ቦታ ግልፅ በመሆኑ ከእኛ ጋር ተስማምተው  ነገር ግን የፈሳሹን ዓይነት በግድ ደም ነው ብለው ለመጠምዘዝ ይሞክራሉ ።

የተቀሩት ሙስሊም መምህራን ደግሞ ክፍሉ የሚያወራው ስለ “አባትየው” ሳይሆን ስለ “ፅንሱ” ነው፤ ስለዚህ “ሰው ከእርግብግቢትና ከጀርባ አጥንት መካከል በሚወጣ ተስፈንጣሪ ውሃ ተፈጠረ” የሚለው ንግግር የፅንሱን አስተዳደግ የሚያብራራ ነው” የሚል ለምላሽ እንኳ የማይበቃ ስላቅ የሚመስል ማብራርያ የሚሰጡም አሉ። በእነዚህኞቹ አባባል መሠረት ከሄድን “የሰው ልጅ እንባ የሚመነጨው ከእግሩ ጣቶች መካከል ከሚገኝ ቦታ ነው” የሚልን ንግግር ስህተት ነው ከማለት ይልቅ “በፅንስ ወቅት የእግሮቹ ጣቶችና ዓይኑ አንድ ነበሩ” የሚል ማስተባበያ እንደመስጠት ነው። ይሁን ቢባል እንኳ የቁርአኑ ክፍል የሚገልፀው ከእርሱ (ቦታው) ወጥቶ ልጅ ስለሚፈጥር ተስፈንጣሪ ውሃ ነው። በሳምንታት እድሜ ያለ ፅንስ “ፅንስን ሊፈጥር የሚችል” የወንዴ ዘርን አያመነጭም። ሙሉ አውዱን ካየን ደግሞ “ከምን እንደተፈጠረ ይመልከት” ብሎ በፅንስ ደረጃ ስላለ ሊታይ ስለማይችል ነገር አያወራም። ካወራም በሌላ ቋንቋ “ቁርአን የአገላለፅና የቋንቋ ችግር አለበት” ማለት ይሆናል። ይሄ ደግሞ ቁርአን የአምላክ ቃል ነው የሚለውን እምነት ከአፈር የሚደባልቅ ብሂል ነው።

እንግዲህ ከሁሉም የሙስሊም መምህራን ማብራርያ በግልፅ መረዳት የምንችለው ቁርአን ትልቅ ስህተት ውስጥ እንደወደቀ ነው። ለዘመናት ሙስሊሞች የተረዱትን፤ ሙሐመድም ያስረዳውን በቁርአን ላይ በግልፅ የተቀመጠውን መረዳት ዛሬ ላይ ሳይንሳዊ ግኝቶች ሐሰት መሆኑን ሲረጋግጡ የተለየ ፍቺ በመፈለግ ከሳይንስ ለማጋጠም ሁሉም የሙስሊም መምህራን በየፊናቸው ተሰማርተዋል። ይህም በቁርአን ላይ ያላቸውን እምነት ጥያቄ ውስጥ እንድናስገባ ያደርገናል። እውነተኛ የቁርአን አማኝ ከሆኑ ሳይንሳዊ መሠረት ላይ ቆመው “ለቁርአን ገለፃዎች አክብሮት ሳይኖራቸው” ከአውድ የተፋታ የተለጠጠ ፍቺ በመስጠት ወደ ሳይንስ መጎተት ባልሻቱ ነበር። አንዱ የገነባውን ሌላው ያፈርሳል፤ አንዱ ያፈረሰውን ሌላው ይገነባል። በዚህም ተባለ በዚያ በቁርአን ላይ የሰፈረው ንግግር የተለየ ትርጉም ተሰጥቶት ካልሆነ በስተቀር ቀጥተኛ ትርጉሙ ትክክል እንዳልሆነ የሙስሊም መምህራንን ያስማማል።

በቁርአን የቀረበው ገለፃ ይበልጥ ተዛማጅ ሆኖ የምናገኘው ከዘመናዊ የስነ-ፅንስ ግኝት ጋር ሳይሆን በወቅቱ ከነበሩት ኢ-ሳይንሳዊ ፍልስፍናዎች ጋር ነው። ለምሳሌ ያህል ፍላጦን (428-348 ዓ.ዓ.) እና ዲዮክለስ (240-180 ዓ.ዓ) የወንዴ ዘር ከህብለ ሰረሰር (spinal cord) እና ከአንጎል(brain) እንደሚመነጭ አስተምረዋል።[3] በመጨረሻው የጽሑፉ ክፍል ላይ ሙሐመድ እንዴት እነዚህን ፍልስፍናዎች ሊቀዳ እንደቻለ የምናይ ይሆናል።


ማጣቀሻዎች

[1] https://www.britannica.com/science/semen

[2] https://quranx.com/tafsirs/86.7

[3] Musitelli S, Bossi I (2016) A Brief Historical Survey of Generation (From Hippocrates (469-399 B.C.) to the Controversy between “Sperma-tists” and “Ooists”). Ann Reprod Med Treat 1(1): 1002. p 2.


ቁርኣን