ዘላለማዊ ዙፋን ያለው አምላክ – ዕብራውያን 1፡8ን በተመለከተ ለሙስሊም ኡስታዝ ስህተት የተሰጠ ምላሽ

ዘላለማዊ ዙፋን ያለው አምላክ

ዕብራውያን 1፡8ን በተመለከተ ለሙስሊም ኡስታዝ ስህተት የተሰጠ ምላሽ

የይሖዋ ምስክሮችንና የዩኒቴርያንን ሙግቶች በመቅዳት የሚታወቅ አንደ ሙስሊም ኡስታዝ ዕብራውያን 1፡8 የክርስቶስን አምላክነት እንደማይናገር ለማሳመን ለጻፈው ጽሑፍ ምላሽ እንድንሰጥ አንዳንድ ወገኖች ጥያቄ አቅርበውልናል፡፡ ሙስሊሙ ተሟጋች የቋንቋና የአውድ ሙግቶችን በመጠቀመ እንደሚያስረዳ ቢናገርም ብዙ ሙስሊም ዐቃቤ እምነታውያን እንደሚያደርጉት ሁሉ ለራሱ የሚመቸውን ሐሳብ ብቻ በመውሰድና ሌሎቹን በቸልታ በማለፍ፣ የምሑራንን አቋም በተሳሳተ መንገድ በማቅረብ እንዲሁም የጥቅሶችን አውድ በማዛባት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሲደርስ ታዝበናል፡፡ በዚህ ምላሻችን የኡስታዙን ስህተቶች በማረም ክርስቶስ ጌታችን ዘላለማዊ ዙፋን ያለው መለኮት መሆኑን ከበቂ በላይ በሆኑ የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎች እናረጋግጣለን፡፡ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-

አብዱል

ዕብራውያን 1፥8

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኛ በሆነው፡፡

መዝሙረ ዳዊት 45፥6 አምላክ ለዘላለም ዙፋንህ ነው፣ RSV

መግቢያ

ብዙ ክርስቲአኖች ለኢየሱስ አምላክነት ከሚጠቅሳቸው ጥቅሶች መካከል ኣንዱ ይህ ነው፣ እኔ ደግሞ በተቃራኒው ይህ ጥቅስ የኢየሱስ ኣምላክነት አያሳይም ብዬ፦ ዕብራውያን 1፥8 እና መዝሙረ ዳዊት 45፥6 የተጻፈበትን ቋንቋ፣ አውድ እና የአረፍተ-ነገር አሰካክ ይዤ እሞግታለው፦

    1. የቋንቋ ሙግት

የዕብራውያን 1፥8 ጸሐፊ ጥቅሱ የጠቀሰው ከመዝሙረ ዳዊት 45፥6 ላይ ሲሆን ጥቅሱ ቃል በቃል ሲተረጎም በዕብራይስጡ ሆነ በግሪኩ እንዲህ ይነበባል፦

መዝሙረ ዳዊት 45፥6 አምላክ ለዘላለም ዙፋንህ ነው

כִּסְאֲךָ אֱלֹהִים, עוֹלָם וָעֶד; שֵׁבֶט מִישֹׁר, שֵׁבֶט מַלְכוּתֶךָ.

“God is your throne” – AT (Dr. Goodspeed) – Mo (Dr. James Moffatt) – Byington – Dr. Barclay – Dr. Westcott – Dr. Young – RSV – NRSV – NEB – ASV .

ዕብራውያን 1፥8 አምላክ ለዘላለም ዙፋንህ ነው

Ὁ θρόνος σου ὁ θεὸς εἰς τὸν αἰῶνα τοῦ αἰῶνος,

“God is your throne” – AT (Dr. Goodspeed) – Mo (Dr. James Moffatt) – Byington – Dr. Barclay – Dr. Westcott – Dr. Young – RSV – NRSV – NEB – ASV.

ምሁራን ይህ ጥቅስ አምላክ ለዘላለም ዙፋንህ ነው አሊያም የአንተ ዙፋን እንደ አምላክ ዙፋን ነው ተብሎ ሊተረጎም ይችላል ብለው አስቀምጠዋል፦

Gill’s Exposition of the Entire Bible 45:7 and 1:8 ይመልከቱ፣

መልስ

ዕብራውያን 1፡8 በአማርኛ ነባር ትርጉም እንዲህ ይነበባል፡- “ስለ ልጁ ግን፦ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው።”

በጥንቶቹም ሆነ በአሁኖቹ ከሞላ ጎደል ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ የሚገኘውና በሊቃውንት ተቀባይነት ያለው ትርጉም ይህ ቢሆንም አንዳንድ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች “አምላክ ለዘላለም ዙፋንህ ነው” “God is your throne forever and ever” ተብሎ ሊተረጎም እንደሚችል በግርጌ ማስታወሻዎቻቸው ማመላከታቸው እውነት ነው፡፡ “የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም” የተሰኘው የይሖዋ ምስክሮች ትርጉምም ጥቅሱን “አምላክ ለዘላለም ዙፋንህ ነው” በማለት ተርጉሞታል፡፡ ነገር ግን ይህ ትርጉም በሁለት ምክንያቶች ትክክለኛ ትርጉም ሊሆን አይችልም፡፡

የመጀመርያው ከመጽሐፍ ቅዱስ  አገላለጾች ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ ለመሆኑ እግዚአብሔር ለሌላ አካል ዙፋኑ ነው ማለት ምን ማለት ነው? ትርጉም አልባ ንግግር ነው፡፡ አንድ አካል እግዚአብሔር ዙፋኑ ነው ከተባለለት ከእግዚአብሔር በላይ ነው ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ዙፋን አለው፣ ከዘላለም እስከ ዘላለምም በዙፋኑ ላይ ነው እንጂ የማንም ዙፋን አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው ንግግር ለክርስቲያኖች ትርጉም እንደማይሰጠው ሁሉ ለሙስሊሞችም ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፡፡

ይህ ትርጓሜ ትክክል የማይሆንበት ሁለተኛው ምክንያት ከዕብራውያን ምዕራፍ 1 አውድ አኳያ የሚታይ ነው፡፡ የዕብራውያን ጸሐፊ እዚሁ ምዕራፍ ላይ ስለ ልጁ ፈጣሪነትና ዘላለማዊነት እንዲህ ሲል ይናገራል፡-

“ደግሞ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል።” (ዕብራውያን 1፡10-12)

የዕብራውያን ጸሐፊ ይህንን ጥቅስ የወሰደው ከመዝሙር 102፡24-25 ሲሆን ለያሕዌ የተነገረ ነው፡፡ ስለዚህ በዚሁ አውድ ልጁ ፅንፈ ዓለሙን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ ፈጣሪና ዘላለማዊ መሆኑ ተነግሮ ሳለ ለጥቅሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽና ከምዕራፉ አውድ ጋር የማይሄድ ትርጓሜ መስጠት ተቀባይነት የለውም፡፡

“አምላክ ለዘላለም ዙፋንህ ነው” የሚለው እንደ “ሊሆን ይችላል” ትርጉም (possible translation) በግርጌ ማስታወሻነት ቢቀመጥም ከሞላ ጎደል ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ትክክለኛው ትርጓሜ “አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል” የሚለው መሆኑን ይስማማሉ፡፡ ይህ ሙስሊም ተሟጋች በመግቢያው ላይ የጠቀሰው “God is thy throne” የሚለው የ RSV ትርጉም በዋናው ጽሑፍ ውስጥ ሳይሆን በግርጌ ማስታወሻ የተመላከተ ነው፡፡ ዋናው ንባብ ውስጥ የሚገኘው ግን “Thy throne, O God, is for ever and ever” የሚል ነው፡፡ በተጨማሪም እርሱ የጠቀሳቸው እንደ RSV፣ NRSV፣ NEB፣ ASV ያሉ ትርጉሞች “God is thy throne” የሚለውን ትርጉም በግርጌ ማስታወሻ እንጂ በዋናው ጽሑፍ ውስጥ አላስቀመጡም፡፡ ይህ ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ሙስሊሙ ተሟጋች ለአንባቢያኑ መግለፅ ነበረበት፡፡ “God is thy throne” የሚለውን ትርጓሜ እንደ “ሊሆን ይችላል” ትርጉም የጠቀሱት ተርጓሚዎች የተሻለና ትክክለኛ ትርጓሜ አድርገው አልቆጠሩትም ማለት ነው፡፡

ሙስሊሙ ተሟጋች አቋሙን እንደሚደግፍለት በማስመሰል የጠቀሰውን Gill’s Exposition of the Entire Bible የመጽሐፍ ቅዱስ ሐተታ ሄደን ስንመለከት ደግሞ የተሟጋቹን ሐሳብ እንደማይደግፍና “አምላክ ለዘላለም ዙፋንህ ነው” የሚለው ትርጉም ስህተት መሆኑን መግለጹን ማየት እንችላለን፡-

Thy throne, O God, [is] for ever and ever

This verse and (Psalms 45:7) are cited in (Hebrews 1:8 Hebrews 1:9); and applied to the Son of God, the second Person in the Trinity; and therefore are not an apostrophe to the Father, as some have said; nor will they bear to be rendered, “thy throne is the throne of God”, or “thy throne is God”; or be supplied thus, “God shall establish thy throne”. But they are spoken of the Son of God, who is truly and properly God, the true God and eternal life; as appears by the names by which he is called, as Jehovah, and the like; by his having all divine perfections in him; by the works which he has wrought, and by the worship which is given unto him; and to whom dominion is ascribed, of which the throne is an emblem, (Genesis 41:40).

ትርጉም፡-

አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ ለዘላለም ነው፤ [መዝሙር 45፡6]

“ይህ ጥቅስ እና መዝሙር 45፡7 በዕብራውያን 1፡8-9 ላይ የተጠቀሱ ሲሆን የሥለሴ ሁለተኛው አካል ለሆነው ለእግዚአብሔር ልጅ ጥቅም ላይ ውለዋል፤ ስለዚህ አንዳንዶች ወደ አብ ያመለክታሉ እንደሚሉት አይደሉም፤ “ዙፋንህ የአምላክ ዙፋን ነው” ወይም “አምላክ ዙፋንህ ነው”  ወይም ደግሞ “አምላክ ዙፋንህን ያፀናል” ተብለው ሊተረጎሙም አይችሉም፡፡ ነገር ግን በእውነትና በትክክል አምላክ ለሆነው፣ እውነተኛ አምላክና የዘላለም አምላክ ለሆነው ለእግዚአብሔር ልጅ የተነገሩ ናቸው፡፡ ይህም ያሕዌ የሚለውን በመሳሰሉ ስሞች በመጠራቱ፣ ሁሉም ባሕርያተ መለኮት ያሉት በመሆኑ፣ በሠራቸው ሥራዎች፣ እንዲሁም ለእርሱ በተሰጠው አምልኮ ይታያል፡፡ ዙፋኑ መገለጫው የሆነው ሥልጣንም (ዘፍጥረት 41፡40) የእርሱ መሆኑ ተነግሯል፡፡” ምንጭ

የጆን ጊል የመጽሐፍ ቅዱስ ሐተታ እንዲህ ባለ መንገድ አቋሙን የሚያፈርስ ሆኖ ሳለ ሙስሊሙ ተሟጋች ማስረጃ ይሆነኛል ብሎ መጥቀሱ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው ሙስሊሙ ተሟጋች ወይ እንግሊዝኛ ቋንቋን የመረዳት ችግር አለበት አለበለዚያም አንባቢያኑ ምንጩን እንደማያነቡት በመገመት እያወናበደ ነው፡፡ እንግሊዝኛ የመረዳት ችግር ካለበት በአቅሙ ልክ ቢጽፍና ቢጠቅስ ጥሩ ነው፡፡ አንባቢያኑ አያመሳክሩም በሚል ግምት እያወናበደ ከሆነ ደግሞ ንስሐ መግባትና እንዲህ ያለውን አስነዋሪ ተግባር መተው ያስፈልገዋል!

አንዳንድ ወገኖች የዕብራውያን ጸሐፊ የጠቀሰውን መዝሙር 45፡6 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ “Your divine throne” (መለኮታዊ ዙፋንህ) በማለት የተረጎሙ ቢሆንም ከእብራይስጡ አንጻር ለምን እንደማያስኬድ የሥልታዊ ነገረ መለኮት ሊቅ የሆኑት ዌይን ግሩደም እንዲህ በማለት አስረድተዋል፡-

“…this is a highly unlikely translation because it requires understanding the Hebrew noun for “throne” in construct state, something extremely unusual when a noun has a pronominal suffix, as this one does . . . The KJV, NIV, and NASB all take the verse in its plain, straightforward sense, as do the ancient translations . . . ” (Wayne Grudem, Systematic Theology, 1994, p. 227.)

ትርጉም፡-

“ይህ በጣም የማይመስል ትርጓሜ ነው ምክንያቱም “ዙፋን” የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል መሥራች ቃል አድርጎ መረዳትን ይጠይቃልና፤ ይህ ደግሞ ልክ እንደዚህኛው ቃል ሁሉ አንድ ስም የሆነ ቃል ባለቤት አመላካች ድህረ ቅጥያ ካለው እጅግ በጣም ያልተለመደ ነው … KJV NIV እና NASB ትርጉሞች ልክ እንደ ጥንታውያን ትርጓሜዎች ሁሉ ጥቅሱን ግልጽና ቀጥተኛ በሆነ ትርጉሙ ወስደውታል…”

ስለዚህ የጥቅሱ ግልፅና ቀጥተኛ ትርጉም በነዚህ ትርጉሞች ውስጥ የሚገኘው “አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል” የሚለው ነው፡፡ ሌሎች ትርጉሞች ከመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽም ሆነ ከዕብራውያን አውድ አንፃር የማያስኬዱ፣ ከሞላ ጎደል በሁሉም ሊቃውንት ከትክክለኛ ትርጉሞች የማይቆጠሩ መሆናቸውን ተመልክተናል፡፡

አብዱል

የመዝሙረ ዳዊት 45፥6 ተናጋሪ ዳዊት ሲሆን እየተናገረ ያለው ስለ ልጁ ስለ ሰለሞን ነው፣ ይህን ምሁራን ይስማማሉ አዲሱ መደበኛ ትርጉምም በግርጌ ህዳጉ ላይ አስፍሮታል፣ የዕብራውያን 1፥8 ጸሐፊ ደግሞ በድርብነት ለኢየሱስ ይጠቀማል፣ ጥቅሱን ከቋንቋ ሙግት አንጻር ካየነው ስለ ሰለሞን ሆነ ስለ ድርብ ፍጻሜ አምላክነት አያወራም፣ ባይሆን የሰለሞንና የመሲሁ ዙፋን የአምላክ ዙፋን አሊያም አምላክ የሰለሞንና የመሲሁ ዙፋን ምንጭ መሆኑን ቢያሳይ እንጂ፦

1ዜና 28:5 በእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀምጦ በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ ልጄን ሰሎሞንን መርጦታል።

1ዜና.29:23ሰሎሞንም በአባቱ በዳዊት በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ተቀመጠ፥ NIV

2ሳሙ.7:12-13 ዕድሜህም በተፈጸመ ጊዜ ከአባቶችህም ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ፥ ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፥ መንግሥቱንም አጸናለሁ። እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፤ የመንግሥቱንም ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ።

ሉቃ1:32 እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤

መልስ

ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ጆን ጊልን የመሳሰሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ሕታቴ ሊቃውንት በዚህ የማይስማሙ ቢሆንም መዝሙሩ አስቀድሞ ለዳዊት ልጅ ለሰለሞን የተነገረ ሊሆን እንደሚችል ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ሙስሊም ተሟጋች እንዳደረገው “አምላክ ሆይ” መባሉን በመካድ አይደለም፡፡ አዲሱ መደበኛ ትርጉም መዝሙር 45፡6 ላይ የሚገኘውን ቃል “አምላክ ሆይ ዙፋንህ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይኖራል” በማለት ተርጉሞታል፡፡ በግርጌው ላይ የሚገኘውን ሐተታ ስንመለከትም ትርጉሙ እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ከዳዊት ስረወ መንግሥት የመጣው ንጉሥ ከፍ ባለ የማዕረግ ስም “አምላክ” ተብሎ መጠራቱ ተገልጿል፡፡ በአዲሱ መደበኛ ትርጉም ተርጓሚዎች መሠረት በጥቅሱ ውስጥ ንጉሡ “አምላክ” ተብሎ ተጠርቷል ነገር ግን ሰብዓውያን ባለ ሥልጣናት በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች “ኤሎሂም” (አማልክት) ተብለው በተጠሩበት ሁኔታ ነው፡፡ ስለዚህ ጥቅሱ የክርስቶስን አምላክነት እንዲያመለክት ያደረገው የዕብራውያን ጸሐፊ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የጠቀሰበት አጠቃቀስ እንጂ መዝሙሩ ሲጻፍ የነበረውን የቀደመ እሳቤ ብዙ ሊቃውንት የሚቀበሉት ነው፡፡ የዳዊት ዙፋን ወራሽ የሆነው ንጉሥ ከፍ ባለ ማዕረግ “አምላክ” ተብሎ ቢጠራም የሰማይና የምድር ፈጣሪ አምላክ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ለዳዊት በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት በዙፋኑ ላይ ለዘላለም የሚቀመጠው መሲሁ ግን የሰማይና የምድር ፈጣሪ አምላክ ነው፡፡ የዕብራውያን ጸሐፊ እየነገረን ያለው እውነተኛ የዙፋኑ ባለቤት የሆነውን ዘላለማዊውና አማናዊውን አምላክ ክርስቶስን ሰለሞን አስቀድሞ በጥላነት እንዳሳየን ነው፡- “ደግሞ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል።” (ዕብራውያን 1፡10-12)

አብዱል

    1. የአውድ ሙግት

ዳዊት 45፥7 ጽድቅን ወደድህ ዓመፃንም ጠላህ ስለዚህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ እግዚአብሔር አምላክ የደስታ ዘይትን ቀባህ።

ዕብ.1:9 ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ

ከአውዱ አንጻር ስንመለከተው ሰለሞን ሆነ ኢየሱስ ባለንጀሮች ማለትም ጓደኞች እንዳሉት ተገልጿል፣ አምላክ ባለንጀራ አልውን? በደስታ ዘይት ማለትም በመንፈስ ቅዱስ እንደተቀባ ተነገሯል፣ አምላክ አምላክን ይቀባልን? እግዚአብሔር የሰለሞን አሊያም የመሲሁ አምላክ እንደሆነ ተገልጿል፣ እንደ ሦላሴ አማንያን እንተርጉመውና አምላክ ሆይ ይባል፣ ለአምላክ አምላክ አለውን? እግዚአብሔር አምላኩስ ከሆነ የመሲሁ ሆነ የሰለሞን አምላክነት የጸጋ እንጂ የባህርይ አይደለም፣ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን ነቢያት ሁሉ አምላክ ተብለዋልና፦

ዮሐ.10:34 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። እኔ። አማልክት θεοὺς ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን? መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አምላክ θεός ካላቸው፥

የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸው አብራሀም ፣ ሙሴ፣ ሰለሞን፣ ኤልያስ፣ ኢሳያስ፣ ኤርሚያስ የመሳሰሉት ናቸው ፦

ዘፍ.15:4፤ እነሆም፥ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት።

ነገሥት ቀዳማዊ 6፥11 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ሰሎሞን መጣ እንዲህ ሲል፦

1ነገ 17:2 የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ለእርሱ መጣለት።

1ነገ 17:9 እነሆም፥ ትመግብህ ዘንድ አንዲት ባልቴት አዝዣለሁ የሚል የእግዚአብሔር ቃል መጣለት።

2ነገ 20:4 ኢሳይያስም ወደ መካከለኛው ከተማ አደባባይ ሳይደርስ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት።

ኤር.1:2 በይሁዳ ንጉሥ በአሞጽ ልጅ በኢዮስያስ ዘመን በመንግሥቱ በአሥራ ሦስተኛው ዓመት የእግዚአብሔር ቃል መጣለት።

እግዚአብሔር በነቢያት ማህበር ቆሞ ሁሉንም ነቢያት አምላኮች ናችሁ ብሏቸዋል፦

መዝ.82:1 እግዚአብሔር በአማልክት ማኅበር ቆመ፥

መዝ.82:6 እኔ ግን። አማልክት ናችሁ፥ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፤

ታዲያ የነቢያት አምላክነት በጸጋና በስጦታ የተገኘ ከሆነ የእግዚአብሔር አምላክነት ደግሞ የባህርይ ሲሆን እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ ነው፦

መዝ 50:1 የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ተናገረ፥

ኢየሱስ አንድም ቦታ አንድ አምላክ አሊያም የአማልክት አምላክ አልተባለም፣ ከዛ ይልቅ ነብይ ስለሆነ አምላክ አለው ከዛም ባሻገር የእግዚአብሔር ቃል መጥቶለታልና ኢየሱስ አምላክ ተባለ ከተባለ እንኳን ነቢያት በተባሉበት ሂሳብ የጸጋ ነው የሚሆነው፦

ዮሐንስ 12:49 እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ።

ዮሐንስ 14:24 የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም።

ዮሐንስ 17:8 የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፥

2ኛ ቆሮንቶስ 1፥3 የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።

ኤፌሶን 1፥3 የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።

1ኛ ጴጥሮስ 1፥5 የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።

መልስ

ከላይ ባለው ሐተታ ውስጥ ይህ ሙስሊም ተሟጋች ሦስት ጉዳዮችን አንስቷል፡፡ የመጀመርያው ኢየሱስ ባልንጀሮች እንዳሉትና ከባልንጀሮቹ በተለየ ሁኔታ መመረጡና መቀባቱ ተነግሯል ስለዚህ አምላክ ሊሆን አይችልም የሚል ነው፡፡ ሁለተኛ ሰዎችም አማልክት ተብለዋል ስለዚህ ኢየሱስም አምላክ መባሉ ከዚያ የተለየ አይደለም የሚል ነው፡፡ ሦስተኛው አብ የኢየሱስ አምላክ ስለተባለ ኢየሱስ አምላክ ሊሆን አይችልም የሚል ነው፡፡

አንደኛውና ሦስተኛው ነጥቦች ኢየሱስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ መሆኑን ከመዘንጋት የመነጩ ስህተቶች ናቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መሠረት መሲሁ ኢየሱስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ ነው፤ ስለዚህ በሰብዓዊነቱ ከሰው ልጆች ጋር ስለተቆጠረ ባልንጀሮች አሉት ደግሞም አብ አምላኩ ተብሏል፤ ስለዚህ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስናነብ ለክርስቶስ ሰብዓዊና መለከታዊ ባሕርያት የተነገሩትን በማስተዋል መሆን ይኖርበታል፡፡ ሁለተኛው ነጥብ ሙስሊሙ ተሟጋች ክርስቶስ አምላክ የተባለበትን አውድ እንዳልተገነዘበ ያሳያል፡፡ እነዚህ ሰዎችና መላእክት መለኮታዊ ባሕርይ ያላቸው አማልክት መሆን የማይችሉበት ምክንያት አውዱ ክቡራን ፍጥረታት እንጂ ፈጣሪ መሆናቸውን ስለማያሳይ ነው፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ክርስቶስ ጌታችን የፍጥረተ ዓለሙ ሁሉ ፈጣሪና ገዢ ነው፡-

“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።” (ዮሐንስ 1፡1-3)

“እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል።” (ቆላስይስ 1፡15-17)

የዕብራውያን ጸሐፊ ራሱ በዚያው ምዕራፍ ከአንድም ሁለቴ ኢየሱስ ፅንፈ ዓለሙን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪና የፈጠረውንም ፅንፈ ዓለም ማጥፋት የሚችል ኃይል ያለው መለኮት መሆኑን ተናግሯል፡-

ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ኹሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ኾኖ፥ ኹሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” (ዕብራውያን 1፡1-3)

“ደግሞ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ኹሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል፡፡” (ዕብራውያን 1፡10-12)

ኢየሱስ አምላክ የተባለው የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ በሚል ግንዛቤ እንጂ ሰብዓውያን ፍጥረታት “ኤሎሂም” በተባሉበት መንገድ እንዳልሆነ ከላይ የሚገኙት ጥቅሶች ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ ይህንን ሙግት ያቀረበው ሰው ከስህተቱ መታረም ያስፈልገዋል፡፡

ሌላው ኢየሱስ የአማልክት አምላክ ወይም አንድ አምላክ አልተባለም የሚለው የሙስሊሙ ተሟጋች ሙግት ትርጉም አልባ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በእርሱ አመክንዮ መሠረት እንኳ ከሄድን አማልክት የተባሉት ሰብዓውያን ፍጥረታት ከሆኑና ኢየሱስ ደግሞ የእነርሱ ፈጣሪና ጌታ ከሆነ (ዮሐ. 1፡1-3፣ ሐዋ. 10፡36፣ ቆላ. 1፡15-17) ኢየሱስ የአማልክት አምላክ ነው ማለት ነው፡፡ ሌላው እንዲህ ያሉ ሙግቶችን የሚያቀርቡ ወገኖች ማስታወስ ያለባቸው አንድ እውነት ቢኖር ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ ቃል በመሆኑ ምክንያት የአብ መለኮታዊ ባሕርያት ሁሉ ተካፋይ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ “አብ እንዲህ ተብሏል ኢየሱስ ግን አልተባለም” የሚለው ሙግት የሚያስኬድ አይደለም፡፡ አብና ኢየሱስ ስለማይነጣጠሉ አብ አንድ አምላክ እንዲሁም የአማልክት አምላክ እንደሆነ በተናገርንበት ቅፅበት ኢየሱስም አንድ አምላክና የአማልክት አምላክ መሆኑን ዕውቅና ሰጥተናል ማለት ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔርና ቃሉ ሊነጣጠሉ አይችሉምና!

ይህንን ጽሑፍ የምናጠቃልለው የዕብራውያን ጸሐፊ ለክርስቶስ ስለሚገባው ክብር እንዲህ በማለት የተናገረውን በመጥቀስ ነው፡-

“ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ፦ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል።”

የሚገርመው ነገር የዕብራውያን ጸሐፊ ይህንን ጥቅስ የወሰደው ከመዝሙር 97፡7 የሰብቱጀንት የግሪክ ትርጉም ላይ ሲሆን አውዱን ስንመለከት ለያሕዌ የተነገረ ነው፡-

“ተራሮችም ከእግዚአብሔር ፊት፥ ከምድር ሁሉ ጌታ ፊት እንደ ሰም ቀለጡ። ሰማያት የእርሱን ጽድቅ አወሩ፥ አሕዛብም ሁሉ ክብሩን አዩ። ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ፥ በጣዖቶቻቸውም የሚመኩ ይፈሩ፤ መላእክቱ ሁሉ፥ ስገዱለት።” (መዝሙር 97፡:5-7)

መላእክት ሁሉ ሊሰግዱለት የተገባው ከያሕዌ ኤሎሂም በስተቀር ማን ነው!? ኢየሱስ በሥሉስ አሓዳዊነቱ የሚኖረው የያሕዌ ኤሎሂም አካል ካልሆነ አብ እንዴት መላእክት ሁሉ ይስገዱለት ይላል!? መጽሐፍ ቅዱስ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መላእክት ሁሉ ሊሰግዱለት የተገባው ያሕዌ አምላካችን መሆኑን በግልፅና በማያሻማ መንገድ ይነግረናል፡፡ እኛም ከመላእክት ጋር ለመለኮታዊ ክብሩ ተገቢ የሆነውን ስግደት እንሰጠዋለን፡፡ ክብርና ስግደት ሁሉ መለኮት ለሆነው፣ በመስቀሉ ቤዛነት ላዳነን፣ የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪና አምላክ ለሆነው ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ይሁን!

 

መሲሁ ኢየሱስ