ኢየሱስ በለሲቱን ለምን ረገማት? ፍሬ እንደሌላትስ አስቀድሞ እንዴት አላወቀም?

ኢየሱስ በለሲቱን ለምን ረገማት? ፍሬ እንደሌላትስ አስቀድሞ እንዴት አላወቀም?

በማርቆስ 11፡12-14 ላይ “በማግስቱ ከቢታንያ ሲወጣ ተራበ ቅጠል ያለበት በለስ በሩቁ አይቶ ምናልባት አንዳች አገኝባት እንደሆነ ብሎ ወደርሷ መጣ፤ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም፡፡ ከዚያም ዛፏን ከአሁን ጀምሮ ለዘለዓለም ማንም ፍሬ ከአንቺ አይብላ አላት፡፡ ደቀመዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙት” ይላል፡፡ “አምላክ ነው” የሚበላው ኢየሱስ እርሱ እንኳን ባለበት ኾኖ ፍሬ ይኑራት አልያም አይኑራት የሚለውን ማወቅ ተስኖት ለማረጋገጥ ቀርቦ ቢያጣባት ለምን ይረግማታል? እርሷ ምን ታድርግ? የበለስ ወቅት አልነበረም፡፡ ኢየሱስ አምላክ ቢሆን ኖሮ እንዴት ከፊቱ ራቅ ብላ ያለች በለስ ፍሬ ይኑራት አይኑራት ማወቅ ይሳነዋል? በለሷንስ አምላክ አይደል ፍሬ እንድታፈራ የሚያደርጋት? አምላክስ ከበለስ ምን ጉዳይ ኖሮት ሲያጣባት ይረግማታል?

መጽሐፍ ቅዱስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአት ያልነካው ፍጹም ሰው እንደሆነ ይናገራል፡፡ ነገር ግን ከሰማይ የወረደ የእግዚአብሔር ልጅ በመኾኑ ኹሉን የሚያውቅ መለኮት ነው (ስለ ኢየሱስ መለኮታዊ ዕውቀት የተሟላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ለማግኘት እዚህ ጋ ይንኩ)፡፡ ስለዚህ የዕውቀት ውሱንነት ቢታይበት ወይም ቢራብ በሰብዓዊ ባሕርዩ እንጂ መለኮታዊ ባሕርዩን የሚነካ ባለመሆኑ በጥያቄው ላይ ጊዜ ማጥፋት አያሻንም፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ የበለስ ወራት እንዳልሆነ እያወቀ ስለምን ሄደ? ለምንስ ረገማት? ጉዳዩ ወዲህ ነው፡፡ በለስ የፍሬ ወራትዋ ሲቀርብ ቅጠሏ ይለመልማል፡፡ በዚህ ጊዜ በጫፎቿ ላይ ለምግብነት የሚውሉ በአረብኛ ታቅሽ የተሰኙ እንቡጦች ይኖሯታል፡፡ እነዚህ እንቡጦች ካልታዩ በለሲቱ በዚያን ዓመት ፍሬ የማፍራት ተስፋ የላትም፡፡ ስለዚህ የበለስ ወራት ባይኾንም ቢያንስ ታቅሽ ሊኖራት ስለሚችል ኢየሱስ ከበለሲቱ አንዳች የሚበላ ነገር ፈልጎ መኼዱ ስህተት አልነበረም፡፡ (F.F. Bruce, Are the New Testament Documments Reliable?: Intervarsity Press; Downers Grove, III, 5th Revised Edition, 1992, pp. 73-74.)

ኢየሱስ በለሲቱን በመርገም እንድትደርቅ በማድረግ በፍጥረት ላይ ሥልጣን ያለው ጌታ መኾኑን ከማሳየቱም ባለፈ ሁለት መንፈሳዊ ትምሕርቶችን አስተላልፎበታል፡፡ የመጀመርያው ለደቀ መዛሙርቱ እምነትን ማስተማር ሲሆን (ማርቆስ 11፡21,24) ሁለተኛው ደግሞ ለእስራኤል በተግባራዊ ምሳሌ የተደገፈ መልዕክትን ማስተላለፍ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅደስ መሠረት በለስ የእስራኤል ምሳሌ ስትሆን ፍሬ ካላፈራች ወይም ፍሬዋ መልካም ካልሆነ እግዚአብሔር እንደሚያደርቃት በነቢያቱ በኩል በተደጋጋሚ ተናግሯል (ሆሴዕ 9፡10-16፣ ሚክያስ 7፡1-4፣ ናሆም 3፡12፣ ኤርምያስ 29፡15-19)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የእስራኤልን እንደ ፍሬ አልባ በለስ መድረቅ አስቀድሞ ተናግሯል (ሉቃ. 12፡5-9)፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ መካኒቱ በለስ ፍሬ አልባ የሆነችው እስራኤል እንደምትደርቅ ተግባራዊ ምሳሌ እየሰጠ መኾኑ ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ታላቅ መንፈሳዊ መልዕክት ያዘለ ታሪክ ጠምዝዞ የኢየሱስን አምላክነት ለመቃወም መጠቀም አግባብ አይደለም፡፡

 

መሲሁ ኢየሱስ

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ