ክርስቲያናዊ ዐቅብተ እምነት – CHRISTIAN APOLOGETICS

ክርስቲያናዊ ዐቅብተ እምነት – CHRISTIAN APOLOGETICS


አስተዋፅዖ

መግቢያ    

  1. የክርስቲያናዊ ዐቅብተ እምነት ትርጉምና ታሪክ

1.1.      ትርጉም      

1.2.      የክርስቲያን ዐቅብተ እምነት ታሪክ    

1.2.1.    የጥንት ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ እምነታውያን    

1.2.2.   ዐቅብተ እምነት በዚህ ዘመን    

  1. የክርስቲያን ዐቅብተ እምነት ዓላማዎች
  2. የክርስቲያን ዐቅብተ እምነት ዓይነቶች
  1. የዐቅብተ እምነት አስፈላጊነትና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ

5.1.  የዐቅብተ እምነት አስፈላጊነት    

5.2.    የዐቅብተ እምነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ    

  1. የዐቅብተ እምነት መርሆች

ዋቢ መጻሕፍት


መግቢያ

“ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።” 1ጴጥ. 3፡15

የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ያለ ተግዳሮት የኖረችበት ዘመን የለም፡፡ በየዘመናቱ የነበሩት ተግዳሮቶች አንድ መልክ ባይኖራቸውም ነገር ግን አንድ ዓላማና ግብ ያላቸው ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እርሱም ቤተ ክርስቲያንን ማዳክም ብሎም ማጥፋት ነው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ዘመናት የኖሩት ክርስቲያኖች መሠረታዊውን የክርስትና አስተምሕሮ ከውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች ተከላክሎ በማቆየቱ ረገድ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል፡፡

የምንኖረው መንፈሳዊ ውጊያ ባለበት ዓለም ውስጥ ነው፡፡ ውጊያው ደግሞ የሚደረገው በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ነው፡፡ ይህንን ውጊያ ለማሸነፍ የተዘጋጀንና የታጠቅን መሆን ያስፈልገናል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስለ ክርስቲያናዊ ዐቅብተ እምነት ታሪካዊ አመጣጥና መጽሐፍ ቅዱሳዊነት መሠረታዊ ግንዛቤን ማስጨበጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ 1ቆሮ 10፡4-6 ላይ በተናገረው መሠረት በእግዚአብሔር ሐሳብ ላይ የሚነሳውን ከፍ ያለውን የሰውን ሐሳብ በማፍረስ አዕምሮን ሁሉ ለክርስቶስ እንዴት መማረክ እንደምንችል ክርስቲያናዊውን መንገድ ያመላክታል፡፡ አንባቢያንም ስለ ክርስቲያናዊ ዐቅብተ እምነት የበለጠ ጥናት እንዲያደርጉ እንደሚያነሳሳና አቅጣጫን እንደሚጠቁም ይታመናል።

1.       የክርስቲያናዊ ዐቅብተ እምነት ትርጉምና ታሪክ

1.1. ትርጉም

“አፖሎጀቲክስ” የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል አፖሎጊያ ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጓሜውም “በመከላከል መናገር” እንደ ማለት ነው፡፡ በጥንታዊቷ ግሪክ የሕግ ስርኣት ውስጥ ሁለት ቁልፍ የሆኑ ቃላት ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር፤ የከሳሽ ወገን ንግግር “ካታጎሪያ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን የተከሳሽ ወገን ምላሽ ደግሞ “አፖሎጊያ” በመባል ይታወቃል፡፡ “አፖሎጊያ’ የሚለው ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። በሐዋርያት ሥራ 26፡2 ላይ ሐዋርው ጳውሎስ ተከሶ በፊስጦስና አግሪጳ ፊት በቀረበ ጊዜ ተጠቅሞበታል፤ እንዲሁም በፊልጵስዩስ 1፡7፣ 1፡16 እና 1ጴጥሮስ 3፡15 ላይ እናገኘዋለን፡፡

ዐቅብተ እምነት ከነገረ መለኮት የጥናት ዘርፎች መካከል አንዱ ሲሆን መረጃዎችን በተቀናበረ ሁኔታ በመጠቀም ለሃይማኖታዊ አስተምህሮ ጥብቅና መቆም ነው፡፡ የአንድ ሃይማኖት አስተምህሮ ትክክል መሆኑንና እምነቱን መምረጥ ከሰው አመክንዮአዊ አስተሳሰብ ጋር የማይጣረስ መሆኑን ለማሳየት የሚደረግ ጥረትም ነው፡፡ ስለዚህ ዐቅብተ እምነት ሰዎች አስተሳሰባቸውን እንዲለውጡ የማሳመን ሥራ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ዐቅብተ እምነት ክርስቲያናዊ ሥነ መለኮት (Christian Theology)፣ ተፈጥሯዊ ሥነ መለኮት (Natural Theology) እና ፍልስፍናን በማጣመር ክርስቲያናዊውን አስተምህሮ ከውጪያዊ ጥቃቶችና የተሳሳቱ ትርጓሜዎች ለመከላከል ይጥራል፣ እንዲሁም የሌሎች ንፅረተ ዓለማት አስተምሕሮዎችን ይመረምራል፡፡

1.2. የክርስቲያን ዐቅብተ እምነት ታሪክ

የክርስቲያን ዐቅብተ እምነት ታሪክ ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን የሚጀምር ቢሆንም እንደ አንድ የጥናት ዘርፍ የጎለበተውና ወጥ የሆነ መልክ የያዘው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ ክርስቲያናዊው ዐቅብተ እምነት በተለያዩ የዕድገት ደረጃዎች ውስጥ አልፏል፡፡

ክርስትና በተጀመረበት ዘመንና ተከትለው በነበሩት ጥቂት ክፍለ ዘመናት መካከል ክርስቲያኖች በሮማ መንግሥት ከፍተኛ ስደት ይደርስባቸው ነበር፡፡ ይህንን ስደት ለመቀስቀስና ለማጽደቅ ተቃዋሚዎች የተለያዩ የሐሰት ክሶችን ይጠቀሙ ነበር፡፡ ኔሮ የተባለው የሮም ንጉሥ ክርስቲያኖች ላይ ስደት ለማስነሳት በ64 ዓ.ም. ለስድስት ተከታታይ ቀናት በመንደድ የሮምን ከተማ አብዛኛውን ክፍል ያወደመውን የእሳት አደጋ ያቀጣጠሉት ክርስቲያኖች እንደሆኑ በሐሰት እንደወነጀላቸው ታሲተስ የተባለ ሮማዊ ጸሐፌ ታሪክ ዘግቧል፡፡ የጌታን እራት በቀጥታ በመተርጎም ክርስቲያኖች የሰው ሥጋ እንደሚበሉም ተከሰው ነበር፡፡ እንዲሁም ክርስቲያኖች “ወንድምና እህት” በማለት እርስ በርሳቸው የመጠራራት ልማድ ስለነበራቸው ይህንንም በቀጥታ በመተርጎም የዝምድና ጋብቻ (incest) እንደሚፈጽሙ ተወርቶባቸዋል፡፡ የይሁዲ ኃይማኖት፣ ኖስቲዝምና የግሪክ ፍልስፍና የክርስትናን አስተምህሮ የሚገዳደሩ አስተሳሰቦችም ነበሩ፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ውንጀላዎችንና ስም ማጥፋቶችን እንዲሁም አስተምሕሯዊ ተግዳሮቶችን ለመከላከል የጥንት የቤተ ክርስቲያን አበው የተለያዩ ጽሑፎችን መጻፍ አስፈልጓቸው ነበር፡፡

በጥቅሉ ሲታይ የአበው ጽሑፎች ሦስት ዓላማዎችን ያነገቡ ነበሩ። እነርሱም፦

  1. ክርስትናን ከሐሰት ክሶችና ውንጀላዎች መከላከል
  2. የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ፍጻሜ ላይ በመመሥረት የክርስትና አስተምህሮ እውነት መሆኑን ማስረዳት
  3. ክርስትና የግሪክ ፍልስፍና ላዕላይና ምልዓት መሆኑን ማስረዳት ናቸው፡፡

የኋለኞቹ ክርስቲያን ዐቃቤ እምነታውያን ሥራዎች የተለያዩ የክርስትና አስተምሕሮዎችን ከተቃዋሚዎች በመከላከልና ስለ እግዚአብሔር መኖር አመክንዮአዊ ማስረጃዎችን በማቅረብ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡

1.2.1. የጥንት ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ እምነታውያን

  • በዐቃቤ እምነታዊ ሥራቸው ከሚታወቁ የጥንት ቤተ ክርስቲያን አበው መካከል ዮስጦኒዮስ ሰማዕት (100-165 ዓ.ም.) ይጠቀሳል፡፡ ይህ አባት ከፕሌቶ የፍልስፍና አስተምሕሮ ወደ ክርስትና የተለወጠ ነበር፡፡ “ከአይሁዳዊው ትሪፎ ጋር የተደረገ ውይይት” በሚለው ጽሑፉ ውስጥ ኢየሱስ አይሁድ ሲጠብቁት የነበሩት መሲህ መሆኑን ለማሳየት የብሉይ ኪዳንን ትንቢቶች እንደ ማስረጃ ተጠቅሟል፡፡ “አፖሎጂስ” በሚል ርዕስ በተጻፉት ሁለት ጽሑፎቹ ውስጥ ደግሞ ክርስትና ነጻነትን ማግኘት ይችል ዘንድ የተለያዩ የሐሰት ክሶችን ውድቅ በማድረግና ከግብረ ገብነት አንጻር ክርስትና የበላይነት ያለው እውነተኛ ፍልስፍና መሆኑን በማመልከት ተከራክሯል፡፡ ዮስጦኒዮስ ሰማዕት የክርስቶስን ማንነት በተመለከተ ይከተል የነበረው አስተምሕሮ መጠነኛ ችግር የነበረበት ቢሆንም የአዲስ ኪዳን ጽሑፎች ከተጻፉ በኋላ ከተነሱት አበው መካከል ለክርስቲያናዊው ዐቅብተ እምነት መሠረት የጣለ ሰው እንደነበር መናገር ይቻላል፡፡
  • በክርስቲያን ዐቅብተ እምነት ታሪክ ውስጥ የእስክንድሪያ ክርስቲያኖች ያበረከቱት አስተዋጽዖ ከሁሉም የላቀ ነበር፡፡ የእስክንድሪያው ቀለሜንጦስ “ፕሮትሬፕቲከስ” (ልባዊ ምክር) በሚል ርዕስ የጻፈው ዐቃቤ እምነታዊ ጽሑፍ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ከተጻፉ ተመሳሳይ ጽሑፎች ሁሉ የላቀ ነበር፡፡
  • በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ከተነሱት ክርስቲያን ዐቃቤ እምነታውያን መካከል ኦሪጎን (185-254 ዓ.ም.) ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ ሴልሰስ የተባለ ሰው በክርስትና ላይ ላቀረበው ፍልስፍናዊ፣ ግብረ ገባዊና ታሪካዊ ትችት ምላሽ ለመስጠት “ኮንትራ ሴልሰስ” በሚል ርዕስ የጻፈው ረዘም ያለ ጽሑፉ እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ ጠቃሚ የመረጃ ምንጭ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ በዚህ ጽሑፉ ኦሪጎን ኢየሱስ ተዓምራቱን በአስማት እንዳላደረገና የአረማውያን የተዓምራት ታሪኮች ከኢየሱስ ታሪኮች እጅግ ያነሰ ተዓማኒነት እንዳላቸው ተሟግቷል፡፡ የኢየሱስን ትንሣኤ ታሪካዊነት “ከቁም ቅዠት” (Hallucination) መላ ምት በመከላከል ረገድም የሚደነቅ የመከላከያ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
  • የሂፖ ሬጊዩስ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ አውጉስጢኖስ (354-430 ዓ.ም.) ክርስቲያኖች በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ አዋጅ ነጻነትን ከተጎናጸፉ በኋላ ከተነሱት ክርስቲያን ዐቃቤ እምነታውያን መካከል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ ክርስትና ከአረማዊነት የላቀ መሆኑን የሚያሳዩ፣ የስህተት ትምህርቶችን የሚያጋልጡና የክርስትናን አስተምህሮዎች ቀና በሆነ መንገድ የሚያስተምሩ ብዙ ጽሑፎችን የጻፈ ታላቅ ሊቅ ነበር፡፡ የአውጉስጢኖስ ክርስቲያናዊ ፍልስፍና የበለጠ ሰፋ ባለ መልኩ ሰፍሮ የምናገኘው በምዕራቡ ዓለም ውስጥ ከተጻፉ አስር በጣም ጠቃሚ መጻሕፍት መካከል አንዱ ተደርጎ በሚቆጠረው “የእግዚአብሔር ከተማ” በሚል ርዕስ በጻፈው የመጨረሻ መጽሐፉ ውስጥ ነው፡፡ አውጉስጢኖስ ስለ ዐቅብተ እምነት ያስተማረው ትምህርት ከርሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚህ ዘመን ድረስ ለብዙ ክርስቲያን ዐቃቤ እምነታውያንና የነገረ መለኮት ምሑራን መነሳት ምክንያት ሆኗል፡፡
  • ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ታላላቅ ሊቃውንት መካከል የካንቴርበሪ ሊቀ ጳጳስ የነበረው አንሴልም (1033-1109 ዓ.ም.) ይጠቀሳል፡፡ ከርሱ በፊት ያልተነገሩ የራሱ የሆኑ አዳዲስ ሐሳቦችን በማመንጨት የሚታወቅ ሲሆን አውጉስጢኖስ ስለ እምነትና ምክንያት ያስተማራቸውን ነገሮች በማጉላትም ይታወቃል፡፡ ስለ እምነትና ስለ ምክንያት ከተናገራቸው ነገሮች መካከል የሚከተለው ይገኝበታል፦ “ለማመን መረዳት እንዲኖረኝ ጥረት አላደርግም ነገር ግን ለመረዳት እምነት እንዲኖረኝ ጥረት አደርጋለሁ፡፡” አንሴልም ፈላስፎች “Ontological Argument” በማለት ለሚጠሩት የእግዚአብሔርን መኖር ለሚያስረዳ እጅግ ጠቃሚ ሐሳብ መሠረት የጣለ ሰው ነበር፡፡ “ኩር ዴኡስ ሆሞ” (አምላክ ሰው የሆነበት ምክንያት) በሚለው መጽሐፉ ውስጥ የኢየሱስ በሰው ሥጋ መምጣት ለምን እንዳስፈለገ አመክንዮአዊ በሆነ መንገድ በማስረዳት ለክርስቲያን ዐቅብተ እምነት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል፡፡
  • በአስራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን አቬሮስ በተባለ የእስፔን አረብ አማካይነት የአርስጣጣሊስ (አርስቶትል) ፍልስፍና በመላው አውሮፓ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከመሰራጨቱ የተነሳ ክርስቲያናዊው ንፅረተ ዓለም ከፍተኛ ቀውስ ገጥሞት ነበር፡፡ ሊቃውንት ያለ ምንም ምርመራ የአርስጣጣሊስን አስተሳሰብ የተቀበሉ ሲሆኑ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም ያለ ምንም ምርመራ ከአርስጣጣሊስ ፍልስፍና ጋር የተያያዙትን ነገሮች ሁሉ ይቃወሙ ነበር፡፡ ታላቁ አልበርት የተባለ ክርስቲያን ሊቅ ለአቬሮስ ምላሽ የሚሆን ጽሑፍ የጻፈ ቢሆንም ነገር ግን ለዚህ ተግዳሮት ምላሽን በመስጠት የክርስቲያናዊውን ፍልስፍናና ዐቅብተ እምነት አቅጣጫ ማስለወጥ የቻለው የአልበርት ደቀ መዝሙር የነበረው ቶማስ አኳይነስ (1225-1274) ነበር፡፡ ለአቬሮስ ምላሽ ሊሆን የሚችል ጽሑፍ የአርስጣጣሊስን ቋንቋ በመጠቀም ከመጻፉ ሌላ ለክርስቲያን ተማሪዎች ሊሆን የሚችል የሥነ መለኮት መጽሐፍም አበርክቷል፡፡ አኳይነስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከተነሱ ታላላቅ ፈላስፎች መካከል አንዱ ነበር፡፡
  • የተሓድሶ ዘመን ታላቅ የሥነ መለኮት ሊቅ የነበረውን ጀርመናዊው ማርቲን ሉተርን (1483-1546 ዓ.ም.) እዚህ ጋር ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡ በተሓድሶ ዘመን የነበረው ክርክር በጸጋ መዳንና በሥራ መዳን በሚሉት ሐሳቦች መካከል ይደረግ የነበረ ሲሆን ማርቲን ሉተር በጸጋ መዳን የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምሕሮ በማስተማር በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ለሚሰጠው የተሓድሶ እንቅስቃሴ መፋፋም ምክንያት ሆኗል፡፡

1.2.2. ዐቅብተ እምነት በዚህ ዘመን

ከተሓድሶ ዘመን ጀምሮ እስከ አስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ አብዛኞቹ ክርክሮች ሲደረጉ የነበሩት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረ ሲሆን ከዚያ ወዲህ ግን ከዘመነ አብርሆት (Enlightenment) እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የክርስትናን መሠረታዊ አስተምህሮዎች እውነተኛነት ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገቡ ክርክሮች ተነስተዋል፡፡ እነዚህ የጥርጣሬ አመለካከቶች አዲስ ለሆነ ክርስቲያናዊ ዐቅብተ እምነት መነሳት ምክንያት ሆነዋል፡፡ ይህ አዲስ የሆነ ክርስቲያናዊ ዐቅብተ እምነት ሁለት መልኮች ነበሩት፡፡ አንደኛው ወገን በሰው ልጆች አመክንዮአዊ አስተሳሰብ ላይ መደገፍ እንደማይቻልና ነገሮችን በእምነት መቀበል የተሻለ እንደሆነ የሚሟገት ሲሆን ሁለተኛው ወገን ደግሞ ክርስትና የዘመናዊውን ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ያህል አመክንዮአዊ የሆነ ነው የሚል ነው፡፡

ከአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተነሱት ክርስቲያን ዐቃቤ እምነታውያን ክርስትና አመክንዮአዊና ከዘመናዊው ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ጋር የማይጣረስ እንደሆነ የሚያምኑ ሲሆኑ ከከሃዲነት (Atheism)፣ ከስህተት ትምህርቶች (Cults) እና ከሌሎች ኃይማኖቶች (በተለይም ከእስልምና) የሚመጡ ጥያቄዎችን በመመለስ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ በጣም ታዋቂ ከሆኑት የቅርብ ዘመንና የዘመናችን ክርስቲያን ዐቃቤ እምነታውያን መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-

  • ዊልያም ኤፍ. አልብራይት (1891 – 1971) – “ፓሊስቲኖሎጂ” ለተሰኘ የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ቁፋሮ ጥናት ዘርፍ መሠረት የጣሉና ለዕድገቱም ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ታላቅ ዐቃቤ እምነት የነበሩ ሲሆኑ ብዙ የለዘብተኛ ሥነ መለኮት ምሑራንን አመለካከቶች ውድቅ ያደረጉ የሥነ ቁፋሮ ምርምር ውጤቶችን አግኝተዋል፤ እንዲሁም በርካታ መጽሐፍቶችን ጽፈዋል፡፡
  • ፍሬዴሪክ ኬንዮን (1863 – 1952) – የብሪቲሽ ቤተ መዛግብት ዋና ተጠሪና የብሪቲሽ አካዳሚ ፕሬዝዳንት የነበሩ ሲሆኑ “ፓሌኦግራፊ” በተሰኘ የጥናት ዘርፍ እጅግ እውቅ ሰው ነበሩ፡፡ እኚህ ሰው በጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች ላይ ሥልጣናዊ ንግግር በማድረግ ረገድ በእውቀት የሚስተካከላቸው ሰው እንዳልነበረ ተነግሮላቸዋል፡፡ አዲስ ኪዳንን በተመለከተ ከተናገሯቸው ነገሮች መካከል የሚከተለው ይገኝበታል፡- “የመጀመርያው ጽሑፍ በተጻፈበት ጊዜና በቀዳሚው ጽሑፍ መካከል ያለው የጊዜ ልዩነት ምንም የለም እስኪያስብል ድረስ በጣም አናሳ ሆኗል፤ እናም ቅዱሳት መጻሕፍት ልክ መጀመርያ በተጻፉበት ይዘት እኛ ዘንድ በመድረሳቸው ላይ የነበረው የመጨረሻው የጥርጣሬ መሠረት ተወግዷል፡፡ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ተዓማኒነትና አጠቃላይ ተግባቦት በመጨረሻ እንደተረጋገጠ ሊቆጠር ይችላል፡፡”
  • ሲ. ኤስ. ሌዊስ (1898 – 1963) – በ20ው ክፍለ ዘመን ከኖሩ ታላላቅ የሥነ ጽሑፍ ምሑራን መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ሲ. ኤስ. ሌዊስ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ከከሐዲነት ወደ ክርስትና የመጡ ሰው ነበሩ፡፡ በካምባሪጅ ዩኒቨርቲ የመካከለኛው ዘመንና የዘመነ ሕዳሴ (ሬኔሳንስ) ጽሑፎች ምርምር ዋና ተጠሪ የነበሩ ሲሆኑ የበርካታ ዐቃቤ እምነታዊ መጻሕፍት ደራሲም ነበሩ፡፡
  • ዋልተር ማርቲን (1928 – 1989) – በስህተት ትምህርቶች ላይ ጥልቅ ጥናቶችን ያደረጉ ሲሆኑ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመዘዋወር ክርስቲያን አገልጋዮችን በማሰልጠንና የስህተት ትምህርቶችን የሚያጋልጡ መጽሐፍቶችን በመጻፍ ይታወቃሉ፡፡
  • ጆሽ ማክዶዌል (ከ1939 እስካሁን) – ጀስሊን (ጆሽ) ማክዶዌል ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ጌታና አዳኛቸው ወደ ማወቅ የመጡት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እያሉ ክርስትናን የሚቃወም መጽሐፍ ለመጻፍ ጥናት ያደርጉ በነበረበት ወቅት ባገኟቸው መረጃዎች ምክንያት እንደነበር ይናገራሉ። በክርስቲያኑ ዓለም ውስጥ ዕውቅናን ያተረፈላቸውን Evidence that Demands a Verdict (ፍርድ የሚሻ ማስረጃ) በሚል ርዕስ የጻፉትን ቀደምት መጽሐፋቸውን ጨምሮ ወደ 115 የሚሆኑ መጻሕፍትን በግላቸውና ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን ጽፈዋል።
  • ኖርማን ጌይዝለር (ከ1932 እስካሁን) – ዓለም አቀፍ አስተማሪና የበርካታ መጽሐፍቶች ደራሲ ሲሆኑ በክርስትና ላይ ለሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሾችን የሚሰጡ መጽሐፍቶችንና ጽሑፎችን በመጻፍ ይታወቃሉ፡፡
  • አልቪን ፕላንቲንጋ (ከ1932 እስካሁን) – በኖተርዳም ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ፕሮፌሰር ሲሆኑ በትምህርቱ ዓለም እጅግ የታወቁ (ምናልባትም በሕይወት ካሉ ፈላስፎች ሁሉ የላቀ እውቅና ያላቸው) ምሑርና ክርስቲያን ዐቃቤ እምነት ናቸው፡፡
  • ዊልያም ሌን ክሬግ (ከ1949 እስካሁን) – በካሊፎርኒያ ውስጥ በሚገኝ ታልቦት የሥነ መለኮት ትምህርት ቤት ውስጥ የሪሰርች ፕሮፌሰር ሲሆኑ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ምሑራንና ሳይንቲስቶች ጋር ስለ እግዚአብሔር መኖርና ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ታሪካዊነት በመከራከርና በመወያየት የታወቁ የዘመናችን ታላቅ ዐቃቤ እምነት ናቸው፡፡
  • ጌሪ ሀበርማስ (ከ1950 እስካሁን) – የኢየሱስን ትንሣኤ በተመለከተ በርካታ ጥናቶችን ያደረጉና በርካታ መጽሐፍቶችን የጻፉ በዚህ የክርስቲያን ዐቅብተ እምነት ዘርፍ ግንባር ቀደም ከሚባሉ ምሑራን መካከል አንዱ ናቸው፡፡

2. የክርስቲያን ዐቅብተ እምነት ዓላማዎች

ዐቅብተ እምነት በአጠቃላይ ሦስት ዓላማዎች አሉት፡-

  1. ክርስትና እውነት መሆኑን ማስረጃ ማቅረብ (አዎንታዊ ዐቅብተ እምነት) – ዓላማው ፍልስፍናዊ፣ ሳይንሳዊ፣ ታሪካዊና ሥነ ቁፋሯዊ ማስረጃዎችን በማቅረብ የክርስትና እምነት አመክንዮአዊና እውነት መሆኑን እንዲሁም አማራጭ ከሆኑ ንፅረተ ዓለማት ይልቅ ኃይል ያለውና አዋጭ መሆኑን ማሳመን ነው፡፡ (ፊልጵ 1፡7፣ 16)
  2. በክርስትና ላይ የሚነሱ የተቃውሞ አስተሳሰቦችን መመከት (አሉታዊ ዐቅብተ እምነት) – ዓላማው በክርስትና ላይ የሚነሱ የተቃውሞ ሐሳቦችንና የተሳሳቱ ትርጓሜዎችን በማስወገድ ክርስትና ኢ-ምክንታዊ አለመሆኑን ማሳየት ነው፡፡ (1ጴጥ 3፡15)

ተቃዋሚዎች የሚያተኩሩባቸው የክርስትና መሠረተውያን የሚከተሉት ናቸው

  • ሥላሴ
  • የኢየሱስ አምላክነት
  • የኢየሱስ ትንሣኤ
  • ደህንነት
  • መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑ
  1. ተጻራሪ ንፅረተ ዓለማትን መቃወም (ቅዋሜያዊ ዐቅብተ እምነት) – ይህ ዐቅብተ እምነት በእንግሊዘኛ “polemics” በመባል የሚታወቅ ሲሆን ዓላማው ከክርስትና ውጪ ያሉ ሃይማኖቶችና ፍልስፍናዎች ኢ-አመክንዮአዊ መሆናቸውንና እውነት አለመሆናቸውን ማስረዳት ነው፡፡ (2ቆሮ 10፡4-5)

4. የክርስቲያን አቅብተ እምነት ዓይነቶች

·             ነባር ዐቅብተ እምነት (Classical Apologetics)

ነባር ዐቅብተ እምነት ስለ እግዚአብሔር መኖር እንዲሁም ክርስትና እውነት መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በማቅረበ ላይ ያተኩራል፡፡ ይህ የዐቅብተ እምነት ዓይነት መጀመርያ ልዩ መገለጥን እንደ ማስረጃ ሳይጠቅስ እግዚአብሔር መኖሩን የተለያዩ ተፈጥሯዊ ምክንቶችን በማቅረብ ያስረዳል፡፡ ከዚያም በነዚህ ምክንያቶች መሠረት የእግዚአብሔር መኖር እውነት ከሆነ ተዓምራትም ሊደረጉ ይችላሉ የሚል ሐሳብ በማስከተል፤ ለአዲስ ኪዳን ታሪካዊ ተዓማኒነት ማስረጃ ከሰጠ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ራሱ የተናገራቸው ነገሮች፣ ያደረጋቸው ተዓምራትና ትንሣኤው እውነት መሆናቸውን በማሳመን ይደመድማል፡፡

የነባር ዐቅብተ እምነት አራማጅ ከሆኑ ክርስቲያን ምሑራን መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡- ከጥንታውያኑ መካከል አውጉስጢኖስ፣ አንሴልም እና ቶማስ አኳይነስ ሲሆኑ ከዘመናዊዎቹ መካከል ደግሞ ዊንፍሬድ ኮርዱዋን፣ ዊልያም ሌን ክሬግ፣ ኖርማን ጌይዝለር፣ ጆን ጌርስትነር፣ ስቱዋርት ሀኬት፣ ፒተር ክሪፍት፣ ሲ. ኤስ. ሌዊስ፣ ጄ. ፒ. ሞርላንድ፣ ጆን ሎክ፣ አር. ሲ. ስፕሮል እና ቢ. ቢ. ዋርፊልድ ናቸው፡፡

·             ማስረጃዊ ዐቅብተ እምነት (Evidential Apologetics)

ማስረጃዊ ዐቅብተ እምነት ለክርስትና እውነተኛነት ማስረጃዎችን በማቅረብ ላይ ያተኩራል፡፡ ማስረጃዎቹ አመክንዮአዊ፣ ታሪካዊ፣ ሥነ-ቁፋሯዊ ወይንም ደግሞ ልምምዳዊ (experiential) ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ማስረጃዊ ዐቅብተ እምነት በጣም ሰፊ አውድ ያለው ከመሆኑ የተነሳ ከሌሎች የዐቅብተ እምነት ዓይነቶች ጋር የሚነካኩ ብዙ ነገሮች አሉት፡፡ ለምሳሌ ያህል ስለ እግዚአብሔር መኖር የሚቀርቡትን ማናቸውንም የሐሳብ ሙግቶች ወይንም ደግሞ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ የሚቀርቡትን ታሪካዊ ማስረጃዎች ሊጠቀም ይችላል፤ ነገር ግን እነዚህ ሐሳቦች ለማስረጃዊ ዐቃቤ እምነታውያን ከብዙ የማስረጃ ግብኣቶች መካከል የተወሰኑት እንጂ በዋናነት የሚያነጣጥሩባቸው ብቸኛ ሐሳቦች አይደሉም፡፡ ስለዚህ ማስረጃዊ ዐቅብተ እምነትን የሚጠቀሙ ምሑራን ብዙ የሙግት ሐሳቦችን አንድ ላይ በማሰለፍ ለክርስትና እውነተኛነት ጠንካራ የመከራከርያ ሐሳብ ለመስጠት ይሞክራሉ፡፡

የማስረጃዊ ዐቅብተ እምነት አራማጆች ከሆኑ ምሑራን መካከል ዊልያም ፔሌይ፣ በርናርድ ራም እና ጆሽ ማክዱዌል ይገኙበታል፡፡

·             ልምምዳዊ ዐቅብተ እምነት (Experiential Apologetics)

ልምምዳዊ ዐቅብተ እምነት የግለ ሰቦችን ግላዊ ልምምድ እንደ ማስረጃ በመጥቀስ የእግዚአብሔርን መኖርና የክርስትናን ትክክለኛነት ለማስረዳት ይሞክራል፡፡ በዚህም መሠረት ህልሞችን፣ ራዕዮችን፣ የወዲያኛውን ዓለም አይቶ መመለስን (Near Death Experience) እና ሌሎች በግለሰቦች ልምምዶች ላይ የተመሠረቱ ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችን እንደ ማስረጃ ያቀርባል፡፡ ልምምዳዊ ዐቃቤ እምነታውያን የተለመዱትን የክርስቲያናዊ ዐቅብተ እምነት አቀራረቦችን ያጣጥላሉ፡፡ ከአመክንዮኣዊ የሙግት ሐሳቦች ወይንም ደግሞ ከተጨባጭ ማስረጃዎች ይልቅ በግል እውቀት ላይ ለተመሠረቱ ልምምዶች ስፍራ ይሰጣሉ፡፡

የልምምዳዊ ዐቅብተ እምነት አራማጅ ከሆኑ ምሑራን መካከል ሜይስተር ኤካርት፣ ሶረን ኪየርከጋርድ፣ ሩዶልፍ ቡልትማን፣ ካርል ባርስ፣ ፍሬድሪክ ሽሌይማርከር እና ፖል ቲሊክ ይገኙበታል፡፡

·             ታሪካዊ ዐቅብተ እምነት (Historical Apologetics)

ታሪካዊ ዐቅብተ እምነት የክርስትናን እውነተኛነት ለማስረዳት ታሪካዊ ማስረጃዎችን በማቅረብ ላይ ያተኩራል፡፡ እነዚህ ምሑራን የእግዚአብሔርን መኖር ጨምሮ የክርስትና እውነታዎች ታሪካዊ ማስረጃዎችን ብቻ በማጥናት ሊረጋገጡ እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡ በአንድ ወገን ታሪካዊ ዐቅብተ እምነት በማስረጃዊ ዐቅብተ እምነት ሰፊ አውድ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ነገር ግን የክርስትናን እውነተኛነት ለማረጋገጥ ከታሪካዊ መዛግብት ጥናት የመጀመር አስፈላጊነት ላይ ስለሚያተኩር ከማስረጃዊ ዐቅብተ እምነት የተለየ ነው፡፡

ከታሪካዊ ዐቅብተ እምነት አቀንቃኞች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡- ከጥንቶቹ መካከል ጠርጡሊያኖስ፣ ዮስጦስ ሰማዕት፣ የእስክንድሪያው ቀለሜንጦስና ኦሪጎን ሲሆኑ ከዘመናዊዎቹ መካከል ደግሞ ጆን ዋርዊክ ሞንትጎመሪና ጌሪ ሀበርማስ ናቸው፡፡

·             ቅድመ ግንዛቤያዊ ዐቅብተ እምነት (Presuppositional Apologetics)

የቅድመ ግንዛቤያዊ ዐቅብተ እምነት አመለካከት አራማጆች የክርስትና መሠረታዊ አስተምህሮዎች እውነት መሆናቸውን እንደ ቅድመ ግንዛቤ በመያዝ ክርስትና ብቻ እውነተኛ ሃይማኖት መሆኑን ለማስረዳት ይጥራሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል “መገለጣዊ ቅድመ ግንዛቤያዊነት” (revelational presuppositionalism) የተሰኘውን የቅድመ ግንዛቤያዊ ዐቅብተ እምነት ዘርፍ አመለካከት የሚያራምዱ ወገኖች በፍጥረተ ዓለም ወይንም ደግሞ በታሪክ ውስጥ የሚታዩ ነገሮች ትርጉም ሊሰጡን የሚችሉት ሥላሴ የሆነው እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ራሱን እንደገለጠ ማመን ስንችል ብቻ ነው ይላሉ፡፡ “ምክንያታዊ ቅድመ ግንዛቤያዊነት” (rational presuppositionalism) የተሰኘውን የቅድመ ግንዛቤያዊ ዐቅብተ እምነት አመለካከት የሚያቀነቅኑ ወገኖች ደግሞ በዓለም ላይ ከሚገኙ ንፅረተ ዓለማት ሁሉ ክርስትና ብቻ እርስ በርሱ የተስማማ አስተምሕሮ ስላለው እርሱ ብቻ እውነተኛ ሃይማኖች ነው በማለት ይሟገታሉ፡፡

የቅድመ ግንዛቤያዊ ዐቅብተ እምነት አቀንቃኞች ከሆኑ ምሑራን መካከል ኮርኔሊየስ ቫን ቲል፣ ግረግ ባህንሰን፣ ጆን ፍሬም፣ ጎርደን ክላርክ፣ ጎርደን ሄንሪ፣ ኤድዋርድ ጆን ካርኔል፣ ካርል ኤፍ. ኤች. ሄንሪ እና ፍራንሲስ ሼፈር ይገኙበታል፡፡

5. የዐቅብተ እምነት አስፈላጊነትና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ

የዐቅብተ እምነት አገልግሎት አስፈላጊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን የማይቀበሉ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ በነዚህ ሰዎች አስተሳሰብ መሠረት ክርቲያኖች በተለሳለሰና ተለማጭ (flexible) በሆነ መንገድ ወንጌልን መስበክ እንጂ ፊት ለፊት በመጋፈጥ መናገርም ሆነ ለሚነሱት ተቃውሞዎች ጠንካራ ምላሾችን መስጠት የለባቸውም፡፡ ነገር ግን ይህ ዓይነቱ እሳቤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነውን? ለተቃዋሚዎችና ለሐሰት አስተማሪዎች ክርስቲያኖች ሊሰጡት የሚገባቸው ምላሽ ምን መምሰል አለበት? ክርስቲያኖች ስለ እምነታቸው መሟገት ያስፈልጋቸዋልን? በማስከተል ለነዚህ ጥያቄዎች ምላሾችን እንሰጣለን፡፡

5.1. የዐቅብተ እምነት አስፈላጊነት

ይህ አገልግሎት በሚከተሉት ምክንያቶች አስፈላጊ ነው፡

  1. የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ስለሆነ፡

ዐቅብተ እምነት አስፈላጊ የሚሆንበት የመጀመርያውና ትልቁ ምክንያት ክርስቲያኖች ስለ እምነታቸው ለተቃዋሚዎችና ለጠያቂዎች ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጁ እንዲሆኑ በእግዚአብሔር ቃል መታዘዛቸው ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዐቅብተ እምነት የሚናገራቸውን ሐሳቦች ከአፍታ በኋላ እናያለን።

  1. አመክንዮአዊነት የሰው ተፈጥሮ ስለሆነ፡

እግዚአብሔር ሰውን አመክንዮአዊ የሆነ አስተሳሰብ እንዲኖረው አድርጎ በራሱ አምሳል ፈጥሮታል (ዘፍ. 1፡27፣ ቆላ. 3፡10)፡፡ በእርግጥ ሰው ከእንስሳት የሚለየው አመክንዮአዊ አስተሳሰብ ያለው በመሆኑ ነው (ይሁዳ 10)፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡ ትክክል የሆነውን ትክክል ካልሆነው እንዲለይ (ዕብ. 5፡14) እንዲሁም እውነትን ከሐሰት እንዲለይ (1ዮሃ 4፡6) አመክንዮአዊ የሆነውን አስተሳሰቡን እንዲጠቀም ጥሪ ሲያደርግለት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንመለከታለን (ኢሳ 1፡18)፡፡ እግዚአብሔር በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችንና በፍጹም ሐሳበችን እንድንወደው ይፈልጋል (ማቴ 22፡36-37)፡፡ ልብ ዕውቀትን የሚያመለክት በመሆኑ እግዚአብሔር ፍቅራችን በእውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ይፈልጋል ማለት ነው፡፡

  1. ክርስቲያኖች እምነታቸውን እንዲያውቁ ይረዳል፡

ብዙ ክርስቲያኖች መሠረታዊውን የክርስትና አስተምህሮ እንኳ አያውቁም፡፡ በተቃዋሚዎችና በሐሰት አስተማሪዎች እምነታቸው ተግዳሮት ሲገጥመው መልስ ለመስጠት ሲሉ የበለጠ ለማጥናትና ለማወቅ ይበረታታሉ፡፡

  1. በክርስትና ላይ የሚነሱትን አስተምህሯዊ ተግዳሮቶችና የሐሰት ውንጀላዎችን ለመከላከል ይረዳል፡

በዓለም ላይ ከሚገኝ ከየትኛውም ሃይማኖት ይልቅ ክርስትና ብዙ ተቃውሞዎችን ከብዙ አቅጣጫዎች ያስተናገደና እያስተናገደም የሚገኝ ሃይማኖት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለነዚህ ተቃውሞዎችና የሐሰት ክሶች የክርስቲያኖች ምላሽ ዝምታ ወይንም ደግሞ ግዴለሽነት መሆን የለበትም፡፡ እውነትን ያለ ፍርሃትና ያለምንም መሸፋፈን እንድንገልጥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ኃላፊነት ተጥሎብናል፡፡ ቅዱስ አውጉስጢኖስ “ጠቃሚ የሆነውን እውነት የሚሸሽግ ሰው ጎጂ የሆነውን ሐሰት ከሚነዛ ሰው እኩል ጥፋተኛ ነው” በማለት ተናግሮ ነበር፡፡ የሐሰት ትምህርቶች፣ ሰው ሰራሽ የሆኑ ሃይማኖቶችና ሰዋዊ ፍልስፍናዎች ክርስትናን ለማዳከምና ብሎም ለማጥፋት ታጥቀው በተነሱበት በዚህ ዘመን የጌታ ሐዋርያትና ቅዱሳን አባቶች እንዳደረጉት ያለ ምንም ማመቻመች ለክርስቶስ ወንጌል የማንቆም ከሆነ እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ የሰጠንን ኃላፊነት ባለመወጣታችን ተጠያቂዎች እንሆናለን፡፡

  1. በተለያዩ የስም ክርስቲያኖች በሆኑ ግለሰቦችና ማሕበረ ሰቦች ምክንያት የተዛባውን የክርስትናን ምስል ለማስተካከል ይረዳል፡

ብዙ ሰዎች ክርስትና የምዕራባውያን ሃይማኖች ብቻ እንደሆነ ይሰማቸዋል፡፡ ከዚህ የተነሳ በምዕራቡ ዓለም ውስጥ የሚታየውን የሞራል ዝቅጠት ከክርስትና ጋር ስለሚያያይዙ ለክርስትና ያላቸው አመለካከት የተዛባ ሆኗል፡፡ እውነቱ ይህ እንዳልሆነና የክርስትና መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን እንዲሁም የክርስቲያኖች ሞዴል ክርስቶስ ራሱ መሆኑን በማሳየት ይህንን የተዛባ አመለካከት ማስተካከል የኛ ኃላፊነት ነው፡፡

  1. መጽሐፍ ቅዱስ አጥብቆ የሚቃወማቸው ግብረ ሰዶማዊነትን የመሳሰሉ ችግሮች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሰርገው እየገቡ ስለሆነ ለመከላከል ይረዳል፡

በምዕራብ አገራት ውስጥ የሚገኙ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ዛሬ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን በመፍቀድ ላይ ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶችም በዚህ ልምምድ ውስጥ የሚገኙትን ግለሰቦች የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች አድርገው ለመሾም እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወሰድ በአገራችን በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ተጽዕኖ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህንንና መሰል ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ ድርጊቶችን ክርስቲያኖች አጥብቀው ሊቃወሙና የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ከዓለማዊ ብክለት ሊጠብቁ ይገባቸዋል፡፡

  1. ሰዎችን ወደ ክርስቶስ መንግሥት ለማምጣት ይረዳል፡

ሰው በተፈጥሮው ምክንያታዊ (reasonable) ስለሆነ የሐሳብ ሙግቶችን ተከራክሮ በመርታት ያምናል፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ ሰዎች የክርስቶስን ወንጌል እንዳይቀበሉ መጽሐፍ ቅዱስንና ክርስትናን የሚያጣጥሉ በምሑራዊ ቋንቋዎች እየተጻፉ የሚወጡ የሕትመት ውጤቶች ኁልቁ መሣፍርት የላቸውም፡፡ እነዚህን ተግዳሮቶች በማለፍ የክርስቶስን ወንጌል ተስማሚ በሆነ መንገድ በማቅረብ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ማምጣት ይችሉ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች አመክንዮአዊ ንግግሮችን ማድረግና መጽሐፍ ቅዱሳዊውን አስተምሕሮ ምሑራዊ በሆነ ንግግር የማስረዳት ችሎታቸውን ሊያዳብሩ ይገባቸዋል፡፡

5.2. የዐቅብተ እምነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ

“የዐቅብተ እምነት አስፈላጊነት” በሚለው ርዕስ ስር ከተዘረዘሩ 7 ምክንያቶች መካከል ቀዳሚው “የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ስለሆነ” የሚል ነው፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ዐቃቤ እምነታውያን እንድንሆን እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ ይናገረናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመኑ ከነበሩት የሃይማኖት መሪዎችና የሕግ አዋቂዎች ጋር ፊት ለፊት በመነጋገር መልስ ሲሰጣቸውና ጥያቄዎችንም ሲጠይቃቸው እንመለከታለን፡፡ ጌታችን ያንን በማድረግ ምሳሌ ከሆነን እንደ ክርስቲያኖች የርሱን ፈለግ መከተል ያስፈልገናል ማለት ነው፡፡

ስለ ዐቅብተ እምነት ከሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-

  • 1ጴጥ. 3፡15 “ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።”

በዚህ ጥቅስ መሠረት ስለ ተስፋችን አመክንዮአዊ በሆነ መንገድ እንድናስረዳቸው ለሚጠይቁን ሰዎች መልስ ለመስጠት ዝግጁዎች መሆን እንደሚገባን ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ይነግረናል፡፡ ዝግጅት ሲባል ትክክለኛ መልስ ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ለምንጠየቀው ጥያቄ መልስ የመስጠትና እምነታችንን የማስረዳት ውስጣዊ ፍላጎትና ሥነ ልቦናዊ ዝግጅትንም ያጠቃልላል፡፡ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ውስጥ “መልስ ለመስጠት” ተብሎ የተተረጎመው በግሪክ “አፖሎጊያ” የሚለው “አፖሎጀቲክስ” ለሚለው ስያሜ መገኛ የሆነው ቃል መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

  • 1ቆሮ 10፡4-6 “በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥ መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል።”

በዚህ ጥቅስ መሠረት የሰው አስተሳሰብ ምሽግ ተብሏል፡፡ ይህ ምሽግ በአመጽና በክፉ ሐሳቦች የተገነባ ነው፡፡ ይህንን ምሽግ መስበር፤ ማለትም በእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ የሚነሳውን የሰውን ሐሳብ ማፍረስ ሥራችን እንደሆነ ይህ የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል፡፡ በተለያዩ ምድራዊ ፍልስፍናዎች የተሞላውን የሰውን አዕምሮ ለክርስቶስ ይታዘዝ ዘንድ መማረክ የምንችለው ከሰው ፍልስፍና በላቀው መለኮታዊ እውቀት ስንታጠቅ ነው፡፡ ይህ መለኮታዊ እውቀት (የእግዚአብሔር ቃል) ለሰዎች ሊገባቸው የሚችለው ጌታ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ያደርጉ እንደነበሩት በመንፈስ ቅዱስ ጥበብ ተሞልተን አመክንዮአዊ በሆነ ንግግር ስናቀርብ ነው፡፡

  • ፊልጵ. 1፡7 “በልቤ ስላላችሁ እንዲህ ማሰቤ ተገቢ ነው፡፡ በእስራቴም ሆነ ወንጌልን ስመክት እና ሳጸናው ሁለችሁም ከእኔ ጋር የእግዚአብሔር ጸጋ ተካፋዮች ናችሁና፡፡” (አ.መ.ት.)

በዚህ ስፍራ ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለወንጌል እንደሚመክትና እንደሚያጸናው ይናገራል፡፡ እንዲሁም በቁጥር 16 ላይ “እነዚህ እኔ ለወንጌል ለመሟገት እዚህ እንዳለሁ ስለሚያውቁ በፍቅር ይህንን ያደርጋሉ” በማለት ይናገራል፡፡ በነዚህ ቦታዎች ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አፖሎጊያ” የሚለውን የግሪክ ቃል ይጠቀማል፡፡ ይህ የሚያሳየን የቃሉ አገልጋዮች ወንጌልን ከተጻራሪ አመለካከቶች መመከት እንደሚገባቸውና ስለ ወንጌል መሟገት እንደሚገባቸው ነው፡፡ የዐቅብተ እምነት (አፖሎጀቲክስ) ትርጉምና ዓላማም ይኸው ነው፡፡

  • ይሁዳ 3 “ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ። ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ።”

ይህ ቃል የሚናገረው ክርስቲያኖች ስለ እምነታቸው በጽናት መጋደል እንደሚገባቸው ነው፡፡ ይህ መጋደል በሰይፍ ሳይሆን በወንጌል ላይ የሚነሱትን የሰው ፍልስፍናዎችንና የስህተት ትምህርቶችን ለማፍረስ በሚደረግ አመክንዮአዊ የሆነ ንግግር እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

  • ቲቶ 1፡9 ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ሊኖረው ስለሚገባው ባሕርይ ሲናገር እንዲህ ይላል፡- “ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና።”

በዚህ ቃል መሠረት አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ክርስቲያኖችን መምከር የሚችል ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚዎችንም መውቀስ የሚችል መሆን አለበት፡፡ “ሊወቅስ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል “ኤሌግኮ” የሚል ሲሆን መውቀስ፣ ማስተባበል፣ ማስጠንቀቅ፣ መገሰጽ፣ ማሳመን፣ ስህተትን ማጋለጥ የሚሉ ትርጉሞች አሉት፡፡

  • 2ጢሞ 2፡24-25 “የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም። ደግሞም፦ ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሐን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው፥ ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ።”

የማያምኑ ሰዎች የሚጠይቋቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚሞክሩ ክርስቲያኖች ትዕግስት በማጣት ሊፈተኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ግባችን ስለ እነርሱ የሞተውን ኢየሱስን በማወቅ የዘላለምን ሕይወት እንዲያገኙ መንገድ መምራት ስለሆነ ይህንን ታላቅ ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ እንችል ዘንድ በዚህ ቃል ውስጥ የተቀመጠውን ትዕዛዝ በልባችን ልንጠብቅ ይገባናል፡፡ (“ይቅጣ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል “ፓኢድዮኦ” የሚል ሲሆን ማስተማር ወይንም ደግሞ ማሰልጠን ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡)

መጽሐፍ ቅዱስ ከጅማሬው እስከ ፍጻሜው ድረስ ለዐቅብተ እምነት እንደ ምሳሌ ሊጠቀሱ በሚችሉ ሐሳቦች የተሞላ ነው፡፡ የመጀመርያው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የመጀመርያው ምዕራፍ በራሱ ዐቃቤ እምነታዊ ነው፡፡ የፍጥረትን ጅማሬ የሚተርከውን ክፍል በጥልቀት ብንመረምር በሙሴ ዘመን የነበረውን የአረማውያን የፍጥረት አጀማመር ትረካዎች የሚፃረር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ተዓምር በመስራት እውነተኛው አምላክ በኣል ሳይሆን ያሕዌ መሆኑን ማረጋገጡ ዐቃቤ እምነታዊ ነው (1ነገ 18)፡፡ ኢየሱስ በእርሱ ዘመን የነበሩትን የሃይማኖት ምሑራን ፊት ለፊት በመጋፈጥና እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚያረጋግጡ ተዓምራቶችን በማድረግ ዐቃቤ እምነታዊ ሥራዎችን ሠርቷል (ዮሃ 3፡2፣ ሐዋ 2፡22)፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በደማስቆ ከተማ በነበረ ጊዜ ከአይሁድ ጋር በመከራከር ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑንና የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በማሳመን መልስ ያሳጣቸው ነበር (ሐዋ 9፡22)፡፡ እንዲሁም በልስጥራ ከተማ ተፈጥሮን ዋቢ በማድረግ ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ መኖሩንና የጣዖት አምልኮ ከንቱ መሆኑን አስረድቷል (ሐዋ 14፡6-20)፡፡

በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኝ ለዐቃቤ እምነት አገልግሎት ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ታሪክ በሐዋ 17 ላይ ይገኛል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዘመኑ የታላላቅ ምሑራን መነሃርያ በነበረችው የአቴና ከተማ ውስጥ ከፈላስፎች ጋር ሲነጋገር እንመለከታለን፡፡ አርዮስፋጎስ ወይንም ደግሞ “የማርስ ኮረብታ” በመባል በሚታወቀው ቦታ ላይ ኢስጦኢኮችና ኤፊቆሮሶች በመባል ከሚታወቁ ፈላስፎች ጋር በመነጋገር አያሌዎችን ወደ ጌታ እንዳመጣ በክፍሉ ላይ ተጽፏል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር መኖር ማስረጃ መጥቀስ ብቻ ሳይሆን ታሪክንም ጭምር በመጥቀስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ንግግሩም ደረጃውን በጠበቀ የሥነ-አመክንዮ ንግግር የተዋቀረ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአይሁድ ወይንም ደግሞ የክርስትና አስተምሕሮዎች ከክህደት ጋር በሚጋፈጡባቸው ጊዜያት ሁሉ የዐቅብተ እምነት ሥራ መሥራቱን ማየት እንችላለን፡፡ ስለዚህ ዐቃቤ እምነት አስፈላጊ የሆነ የአገልግሎት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍም ያለው ነው፡፡

6. የዐቅብተ እምነት መርሆች

በዚህ ክፍል በሐዋ. 17፡16-34 ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአርዮስ ፋጎስ የመሰብሰብያ ቦታ ካደረገው ንግግር ውስጥ 9 ቁልፍ የሆኑ የክርስቲያን ዐቅብተ እምነት መርሆችን አውጥተን እንመለከታለን፡፡

  1. እርግጠኛነት (Certainty)

 በዐቅብተ እምነት አገልግሎት ላይ የተሰማራ ሰው ስለ እግዚእብሔር ማንነትና የክርስቶስን ትንሣኤ ስለመሳሰሉ መሠረታዊ እውነቶች እርግጠኛ መሆን ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ስፍራ ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር ማንነት እርግጠኛነት በተሞላበት ሁኔታ ሲናገር እናያለን፡፡ በንግግሩ ውስጥ ጥርጣሬንና እርግጠኛነት ማጣትን የሚያሳዩ ምንም ዓይነት ቃላት የሉም፡፡ ንግግሩን ያደርግ የነበረው በእግዚአብሔር ሥልጣን ነበር፡፡ በንግግሩ መግቢያ ቁጥር 22 እና 23 ላይ እንዲህ በማለት ይናገራል፡- “እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ።” ጳውሎስ እነርሱ የማያውቁትን ነገር እርሱ እንደሚያውቅ ከነገራቸው በኋላ ሊያውቁት የሚገባው እውነተኛው አምላክ ማን እንደሆነ አብራራላቸው፡፡ እንዲሁም ቁጥር 31 ላይ የክርስቶስ ትንሣኤ የተረጋገጠ እውነታ እንደሆነና ለሚመጣውም ፍርድ ማረጋገጫ እንደሆነ በምን ዓይነት እርግጠኛነት እንደነገራቸው ልብ እንበል፡- “ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።”

  1. ሕታቴያዊ ገለጻ (Commentary)

በዐቅብተ እምነት አገልግሎት ላይ የተሰማራ ሰው መሠረታዊ የሆኑ እውነቶችን የሚያውቅና መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ መንገድ የማብራራት ብቃት ያለው መሆን አለበት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ ለተሰበሰቡ ሰዎች ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮችን አብራራላቸው፡-

  • እግዚአብሔር ማን እንደሆነና ምን ዓይነት ባሕርይ እንዳለው – በቁጥር 24 ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እግዚአብሔር የሁሉ ፈጣሪና የሁሉ ጌታ መሆኑን እንዲህ በማለት ይናገራል፡- “ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም።” ከዚያም በቁጥር 25 ላይ እግዚአብሔር የሕይወት ምንጭና በሰው ላይ የማይደገፍ መሆኑን እንዲህ በማለት ይናገራል፡- “እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም።” እግዚአብሔር ሰዎችን የፈጠረበት ዓላማ ደግሞ እርሱን እንዲያውቁና ከእርሱ ጋር ሕብረት እንዲኖራቸው እንደሆነ ቁጥር 26 እና 27 ላይ እንዲህ በማለት ይናገራል፡- “ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።” ስለዚህ ከቁጥር 24-28 ሐዋርያው ጳውሎስ መጽሐፍ ቅዱሳዊው እግዚአብሔር ማን እንደሆነና ምን እንደሚመስል፣ ማለትም እርሱ ፈጣሪ፣ ጌታ፣ ራሱን ቻይ፣ ሁሉንም የሚያኖር፣ ገዥ እና የቅርብ አምላክ መሆኑን ያብራራላቸዋል፡፡
  • እውነታዎችን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉማቸው ጋር ማቅረብ – ሐዋርው ቅዱስ ጳውሎስ የጌታ ኢየሱስን ትንሣኤ ታሪካዊነትና ይህ ታሪካዊ እውነታ ያለውን አንድምታ በቁጥር 30 እና 31 ላይ ይናገራል፡፡ “እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤ ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።” የጌታ ኢየሱስ ትንሣኤ የክርስትና መሠረትና ለክርስትና እውነተኛነት ታላቅ ማስረጃ ነው፡፡
  1. ንጽጽር (Contrasting)

የክርስትናን ንጽረተ ዓለም አድማጮቻችን ካሉበት ንጽረተ ዓለም ጋር በማነጻጸር የኛ ዓለት ከእነርሱ ዓለት የጸና መሆኑን ማሳየት አስፈላጊ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ንግግር ሲያደርግ ያደምጡ ከነበሩት ሰዎች መካከል ኤፊቆሮሶች (Epicureans) እና ኢስጦኢኮች (Stoics) ነበሩ (ቁ. 18-21)፡፡ የንግግሩ አብዛኛው ክፍል የእነርሱን ፍልስፍና ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው እግዚአብሔር ጋር በማነጻጸር ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር

ኤፊቆሮስ (ከሃዲነት)

ኢስጦኢክ (መድብለ አማልክት)

ፈጣሪ ነው ዓለም በአጋጣሚ ነው የተፈጠረችው እግዚአብሔር የፍጥረተ ዓለም ሥርዓት አካል ነው
ጌታ ነው ጌታ የሚባል ነገር የለም እግዚአብሔር ከሰዎች ሁሉ ጋር በእኩል ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው
ራሱን ቻይ ነው (በፍጥረት ላይ የተደገፈ አይደለም) እግዚአብሔር የለም እግዚአብሔር የፍጥረተ ዓለም አካል ነው – ሁሉም እግዚአብሔር ነው፣ እግዚአብሔርም ሁሉ ነው
ፍጥረትን የሚያኖር እግዚአብሔር ምንም ተሳትፎ የለውም እግዚአብሔር ኃይል ብቻ ነው
ገዥ ነው አጋጣሚ ነው የሚገዛው እድል ነው የሚገዛው
የቅርብ ነው እግዚአብሔር የለም እግዚአብሔር ማንነት የለውም
  1. የጋራ ነጥቦችን መጠቀም (Commonality)

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት እግዚአብሔር በአጠቃላይ መገለጥ የራሱን ማንነት ለሰው ልጆች ሁሉ ግልጽ አድርጓል (ሮሜ 1፡18-20)፡፡ ስለዚህ የማያምኑ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ማንነትና ባሕርይ የተወሰነ ነገር ያውቃሉ ነገር ግን እውነትን ከሐሰት ጋር ደባልቀዋል፡፡ ሐዋርው ጳውሎስ አቴናውያን የሚያውቁትን እውነታ በመጥቀስ እንደ ማስረጃ ሲጠቀም እንመለከታለን፡- “ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ። እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን። እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም።” በእርግጥ ሐዋርያው የጠቀሰው ቅኔ “በሁሉም ነገር ከዜውስ ጋር የተቆራኘን ነን፣ በእርግጥ እኛ ዘመዶቹ ነንና” የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ይህ አባባል ዜውስ ከተባለው የግሪኮች ጣዖት ጋር የሚገጥም አይደለም፡፡ ስለዚህ ሐዋርው ጳውሎስ እነርሱ ያጣመሙትን የጋራ እውነት በመውሰድ በትክክለኛ አውዱ ውስጥ በማስገባት እውነተኛውን እግዚአብሔርን ሲገልጥበት እንመለከታለን፡፡ እኛም ዛሬ በተመሳሳይ መንገድ በመጠቀም ኢ-አማንያን ሊገባቸው በሚችል ቋንቋ እውነተኛውን እግዚአብሔርን ልናሳያቸው እንችላለን፡፡

  1. ጥሪ ማድረግ (Calling)

ሐዋርያው ጳውሎስ የጣዖት አምልኮ ኃጢኣታቸውን፣ አለማወቃቸውንና በራሳቸው ጥበብ መመካታቸውን ካጋለጠ በኋላ ንስሐ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ እንዲህ በማለት ይነግራቸዋል፡- “እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል” (ቁ. 30)፡፡ ሰዎች እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ እንዲመጡ ጥሪ ሳያደርግ የሚጠናቀቅ የዐቅብተ እምነት ሥራ ግቡን መቷል ለማለት አይቻልም፤ ስለዚህ ከዚህ አላማ እናዳናፈነግጥ መጠንቀቅ ስፈልገናል፡፡

  1. በእግዚአብሔር ቃል ላይ መመሥረት (Being Scriptural)

ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገራቸው ነገሮች ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ እነርሱን ለማሳመን በማለም ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የሚጣረስ ምንም ነገር አልተናገረም፡፡ በሌላ አባባል እውነትን በመሸፋፈን ሊያሳምናቸው ሲሞክር አናየውም፡፡ ከእነርሱ ጽሑፍ ውስጥ የጠቀሰው ክፍል እንኳ እውነት የሆነና ከብሉይ ኪዳን ጋር የሚስማማ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የሙታን ትንሣኤ ለኤፊቆሮሶችና ለኢስጦኢኮች የማይዋጥላቸው ቢሆንም እንኳ የክርስትና ዋና መሠረት በመሆኑ የክርስቶስን ትንሣኤ ከመጥቀስ አልተቆጠበም፡፡ ዛሬ አንዳንድ ወገኖች ለሙስሊሞች ወንጌልን እናደርሳ በሚል ሰበብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምሕሮዎችን ሲያመቻምቹ መታየታቸው ከዚህ አኳያ ሲታይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆኑን እንገነዘባለን።

  1. አውዳዊነት (Contextuality)

ሐዋርው ጳውሎስ ለአቴናውያን በራሳቸው የሕይወት አውድ ሲናገራቸው እንመለከታለን፡፡ አማልክትን ማክበራቸውን ጠቅሶ በመጀመር እውነተኛውን እግዚአብሔርን በማሳየት ወደ እርሱ እንዲመለሱ ጥሪን በማቅረብ ሲያጠናቅቅ እናያለን፡፡ የኤፊቆሮሶችን ከሃዲነትና የኢስጦኢኮችን መድብለ አማልክትነት የእግዚአብሔርን እውነተኛ ማንነት በመግለጥ ሲገዳደር እንመለከታለን፡፡ ጳውሎስ ይናገር የነበረው ቅዱሳት መጻሕፍትን ለሚያውቁ አይሁድ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ከአይሁድ ጋር ሲነጋገር እንደሚያደርገው ቅዱሳት መጻሕፍትን ቢጠቅስ (ሐዋ 13፡32-41) ለነዚህ ሰዎች ሊገባቸው አይችልም ነበር፡፡ ስለዚህ እነርሱ የሚያውቁትን አጠቃላይ መገለጥና የባለ ቅኔያቸውን ጽሑፍ በመጥቀስ ከቅዱሳት መጻሕፍት መገለጥ ጋር አያይዞ ሲናገራቸው እንመለከታለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም የእግዚአብሔርን እውነት በማያምኑ ሰዎች አውድ መሠረት ማቅረብ መቻል አለብን፡፡

  1. አመክንዮን መጠቀም (Being Logical)

በዚህ ስፍራ ላይ የሐዋርያው ጳውሎስ ንግግር በአመክንዮኣዊ ንግግር የተዋቀረ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እግዚአብሔር ጣዖት እንዳልሆነ ለማስረዳት ሐዋርየው ጳውሎስ የተጠቀመውን ንግግር በአመክንዮ ስርኣት ስናስቀምጠው የሚከተለውን ይመስላል፡-

  • እኛ ዘመዶቹ ነን
  • እኛ ዘመዶቹ ከሆንን እርሱ እንደኛው ማንነት ያለው ነው
  • ስለዚህ እርሱ ማንነት የሌላቸውን ነገሮች (ብር፣ ወርቅና ድንጋይ) አይመስልም፡፡

በዐቅብተ እምነት አገልግሎት ላይ የተሰማራ ሰው የሥነ አመክንዮ ሕግጋትን ጠንቅቆ ሊያውቅና ንግግሮቹንም በዚያ መሠረት ሊቃኝ ይገባዋል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ያንን በማድረግ ጥሩ ምሳሌ ሆኖናል፡፡

  1. ክርስቲያናዊነት (Christianly)

ሐዋርያው ጳውሎስ በአቀራረቡ ትሑት ነበር፡፡ አማልክትን መፍራታቸውን ከማድነቅ በመጀመር እምነታቸውን ሳያጸድቅ ትህትናና ፍቅርን በተሞላ ንግግር ስህተታቸውን ሲያሳያቸው እንመለከታለን፡፡ በዐቃቤ እምነት አገልግሎት ውስጥ ሁለቱ ክርስቲያናዊ ባሕርያት፣ ማለትም ትህትናና ፍቅር በጣም ወሳኝ ናቸው፡፡

 


ዋቢ መጻሕፍት

Bruce, FF. The New Testament Documents, Are They Reliable?, 1959

Geisler, Norman L. Baker Ensyclopedia of Christian Apologetics, Grand Rapids, 1999

Geisler, Norman and Thomas Howe. When Critics Ask, a Popular Handbook on Bible Difficulties, Victor Books, a Division of Scripture Press Publications Inc. USA

McDowell, Josh. Evidence That Demands a Verdict, Vol. 1 Rev. ed. San Bernadino, Calif.: Here’s Life, 1979

Smith, Jay. The Bible in the British Museum and the British Library, a Tour of the British Museum and the Brtish Library

Strong, James. Greek Dictionary of the New Testament, S.T.D., LL.D, AGES Software, Version 1.0, 1997

ለክርስቲያኖች