አወዛጋቢው የሐፍስ ቁርኣን አመራረጥ – ቁርኣን ሰው ሠራሽ መጽሐፍ መሆኑን የሚያሳይ የማይታበል ማስረጃ

አወዛጋቢው የሐፍስ ቁርኣን አመራረጥ

ቁርኣን ሰው ሠራሽ መጽሐፍ መሆኑን የሚያሳይ የማይታበል ማስረጃ

ከሙሐመድ ህልፈት በኋላ በርካታ ዓይነት ቁርአኖች እንደነበሩና እነዚህን ቁርአኖች አንድ ለማድረግ ብዙ ያልተሳኩ ጥረቶች መደረጋቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ልዩነቶቹ እንዲፈጠሩ ምክንያት የሆነው መሠረታዊው ችግር የአረብኛ ቋንቋ ፊደላት እንደ ማናቸውም ጥንታዊ የሴሜቲክ ቋንቋ ፊደላት አናባቢ ነቁጦች ያልነበሯቸው መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በመጀመርያዎቹ የእስልምና ዘመናት ቁርኣንን በብዙ መንገዶች ማንበብ የተለመደ ነበር፡፡ ንባባቸውን ልክ እንደ ሐዲስ ዘገባዎች የአስተላላፊዎችን ስሞች ወደ ኋላ በመቁጠር ከሙሐመድ ጋር በማገናኘት ከሙሐመድ የተላለፈ ትክክለኛ ንባብ መሆኑን የሚናገሩ ታዋቂ አነብናቢዎችም ነበሩ፡፡ የነዚህ አነብናቢዎች ቁርአኖች አረብኛን ከአናባቢ ነቁጦች ጋር መጻፍ ከተጀመረ በኋላ በጽሑፍ የሰፈሩ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ ቁርአኖች እስከዚህ ዘመን ድረስ በዓለም ላይ ለመሰራጨታቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ ከነዚህ ቁርአኖች መካከል በዓለም ላይ ከፍተኛ ስርጭት ያለውና በሀገራችንም ሙስሊሞች እጅ የሚገኘው በኢማም ሐፍስ ስም የተሰየመው የሐፍስ ቁርኣን ነው፡፡

ኢማም ሐፍስ በ796 ዓ.ም. (ከሙሐመድ ሞት በኋላ 144 ዓመታት) ከባግዳድ በስተ ደቡብ በምትገኝ ኩፋ በተሰኘች ከተማ ውስጥ ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን ይህ የቁርኣን ቅጂ በስሙ ተሰይሟል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት 95% የሚሆኑት ሙስሊሞች የሐፍስን ቁርኣን ይጠቀማሉ፡፡ ከእርሱ ጋር ተፎካካሪ የሆኑ የዋርሽ እና የአል-ዱሪ ቁርአኖችም ይገኛሉ፡፡ የሐፍስ ቁርኣን የኦቶማን ኢምፓየር ገናና በነበረባቸው በ16ው እና 17ው ክፍለ ዘመናት ጥቅም ላይ ውሎ ነበር፡፡

የሐፍስ ቁርኣን ዓለም አቀፋዊ ገፅታን የመላበስ ታሪክ የጀመረው በ1924 ዓ.ም ነበር፡፡ በዚያን ወቅት በግብፅ ለዚያውም የካይሮ ከተማ ኦፊሴላዊ የቁርኣን ቅጂ ሆኖ ታወጀ፡፡ ይህም የተደረገው የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ተማሪዎች የተለያዩ የቁርኣን ቅጂዎችን ይጠቀሙ ስለነበር በፈተና ወቅት የተለያዩ ምላሾችን በመስጠታቸው ነበር፡፡ ከዚያም ፕሮፌሰር ሙሐመድ ቢን ዓሊ አል-ሁሰይኒ አል-ሐዳድ የተሰኙ ሰው ለመላው ግብፅ ወጥ የሆነ ንባብ ያለው አንድ ቁርኣን እንዲያዘጋጁ ተጠየቁ፡፡ እርሳቸውም የሐፍስ ቁርኣንን በመምረጥ ውሳኔ አስተላለፉ፡፡ በወቅቱ አምስት የሚሆኑ የተለያዩ የሐፍስ ቁርኣን ቅጂዎች ነበሩ፡፡ ልብ በሉ፤ ይህ የሌሎች አስተላላፊዎችን የቁርኣን ቅጂዎች የሚያጠቃልል ሳይሆን ሐፍስ የተሰኘው አስተላላፊ አምስት ዐይነት የተለያዩ ቁርአኖች ናቸው፡፡ አል-ሐዳድ ግን ከአምስቱ የተለያዩ የሐፍስ ቅጂዎች መካከል ለምን የኦቶማኖችን የሐፍስ ቅጂ ቁርኣን እንደመረጡ ማብራርያ አልሰጡም፡፡ ከምርጫው በኋላ ከዚህኛው ቅጂ ጋር የማይስማሙትን ሌሎች የቁርኣን ቅጂዎችን በመሰብሰብ በጀልባ ጭነው በአባይ ወንዝ ውስጥ አሰጠሟቸው፡፡ (Gabriel Said Reynolds (Ed.), The Qur’an in its historical context, (London & New York: Routledge, 2008) pgs. Introduction, and pages 2-3;  Angelika Neuwirth, & Nicholas Sinai, (Eds.), The Qur’an in Context: Historical and Literary Investigations into the Qurʾānic Milieu, Leiden/Boston: Brill, 2010, p. 1 

ከክፍለ ዘመናት በፊት ኸሊፋ ኡሥማንም የተለያዩ ቁርአኖችን ለማስወገድ ሰብስቦ አቃጥሏቸው እንደነበር እስላማዊ ምንጮች ይናገራሉ፡፡

ፕሮፌሰር ገብርኤል ሰይድ ሬይኖልድስ የተሰኙ ሊቅ በጻፉት መሠረት በ1926 እና በ1934 መካከል ስድስት የሚሆኑ ልዩነትን የሚያሳዩ የተለያዩ የቁርኣን ቅጂዎች በምድረ ግብፅ ነበሩ፡፡ ነገር ግን በ1936 የሐፍስ ቅጂ ግብፅ-አቀፍ ብቸኛ የቁርኣን ቅጂ እንዲሆን የግብፅ መንግሥት ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ወቅቱንጉሥ ፋሩቅ ወደ ሥልጣን የወጣበት ወቅት ስለነበር ይህ ቅጂ “የንጉሥ ፋሩቅ ሕትመት” የሚል ስያሜ ተሰጠው፡፡ ከዚያም ይኸው ቅጂ ለካይሮ ብቻ ሳይሆን በመላው ግብፅ ለሚገኙት የሃይስኩል ተማሪዎች ብቸኛ መደበኛ ጽሑፍ እንዲሆን ተወሰነ፡፡ የሐፍስ ቁርኣን ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን የተደረገው በ1985 ዓ.ም. በሳዑዲው ንጉሥ በፈሃድ አማካይነት ነበር፡፡ (Ibid.)

ይህ የቁርኣን ቅጂ የተመረጠበትና ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን የተደረገበት ሒደት ድንገተኛና ያልተጠና ከመሆንም አልፎ በአንድ ግለሰብ ውሳኔ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ለሙስሊሙ ዓለም የራስ ምታት ነው፡፡ ቀደምት ሙስሊሞች የአናባቢ ነቁጦችና የተነባቢ ፊደላትን ልዩነቶች የሚያሳዩ የቁርኣን የእጅ ጽሑፎችን ከሐፍስ ቅጂ ጋር ለማስማማት እንደገና የመሰረዝና የመደለዝ ሥራ መሥራታቸውና ይህም ተግባር ለዓለም ሕዝብ ይፋ መሆኑ ለዘመናችን ሙስሊሞች ሌላው የራስ ምታት ነው፡፡ ይህንን ሸፍጥ ይፋ በማድረግ ረገድ በተለይም ዶ/ር ዳን ብሩቤከር የተሰኙ ሊቅ በቅርቡ ያሳተሙት መጽሐፍ ተጠቃሽ ነው፡፡ (Daniel Alan Brubaker; Corrections in Early Qurʾān Manuscripts: Twenty Examples, 2019)

ኢማም ሐፍስ ሐሰተኛ ስለመሆኑ የሙስሊም ሊቃውንት ምስክርነት

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ከተገለፁት ችግሮች በላይ ሙስሊሙን ማሕበረሰብ ሊያሳስብ የሚገባው አንድ ትልቅ ችግር አለ፤ እርሱም ኢማም ሐፍስ ሐሰተኛ ሐዲሶችን በመዘገብና የሌሎች ሰዎችን መጻሕፍት በመስረቅ የሚታወቅ ሰው መሆኑ ነው፡፡ ኢማም አል-ቡኻሪ፣ “ታሪኽ አል-ሰግሂር” በሚለው መጽሐፉ ቅፅ 2፣ ቁጥር 233 ላይ እንደተናገረው ሐፍስ ሐሰተኛ ሐዲሶችን በመዘገብ የሚታወቅ ሰው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የሐዲስ ጸሐፊዎች የእርሱን ሐዲሶች ጥለዋቸዋል፡፡ ኢማም አል ቡኻሪ “አል-ዱዋፋ አል-ሰግሂር” በሚል ሌላ መጽሐፉ ገፅ 35 ላይ ሐፍስ የሰዎችን መጽሐፍ እየወሰደ እንደሚቀዳና የወሰደውን በታማኝነት እንደማይመልስ ጽፏል፡፡ የሐዲስ ሊቅ የሆኑት አል-ባኒ በሱናን አት-ትርሚዚ ውስጥ የሚገኝ ሐዲስ ሲመረምሩ ሐዲሱ ያልተለመደ መሆኑንና የሐፍስ ስም በውስጡ መገኘቱ በራሱ ደኢፍ (ደካማ) ሐዲስ እንደሚያደርገው ተናግረዋል (Al-Albani, The Daif in Sunan-Al-Tirmidhi, p. 348)፡፡ ታድያ ኢማም ሐፍስ በሐዲስ ዘገባ እንኳ የማይታመን የፈጠራ ሐዲሶች አስተላላፊ ከነበረ፣ ስሙ በሐዲስ ኢስናድ ዝርዝር ውስጥ መጠቀሱ ብቻ አንድን ሐዲስ ደካማ የሚያደርገው ከሆነ፣ በግል ሕይወቱም ታማኝነትን የሚያጎድል ሰው ከነበረ እርሱ ያስተላለፈው የቁርኣን ቅጂ በምን መስፈርት ነው ተዓማኒ ሊባል የሚችለው?  

 

ቅዱስ ቁርኣን