መንፈስ ቅዱስ ሁሉን አዋቂ መለኮት ነው!
ለሙስሊም ሰባኪያን ስሁት ሙግት የተሰጠ ምላሽ
በኩረጃ የሚታወቅ አንድ ሙስሊም ኡስታዝ “የተረሳው መንፈስ ቅዱስ” በሚል ርዕስ አጠር ያለ ጽሑፍ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶ ነበር፡፡ ጽሑፉ ከዚህ ቀደም ኢብን አንዋር በተሰኘ የሱፊ እስልምና ተከታይ አፖሎጂስት የተጻፈ ሲሆን ይህ ሙስሊም ኡስታዝ እንደ ልማዱ የትርጉሙን ምንጭ ሳይጠቅስ የራሱ ጽሑፍ በማስመሰል በማቅረብ ብዙ ውዳሴዎችን ከተከታዮቹ ዘንድ አትርፎበታል፡፡ መጻሕፍትን ሳይቀር ሙሉ በሙሉ ከሌሎች ምንጮች በመቅዳት በመተርጎም ያሳተመው ይህ ወገናችን የሌሎች ደራሲያን ሥራዎችን በመቅዳት የግል ሥራው ማስመሰሉ ትክክል አለመሆኑን በመግለፅ አንዳንድ ወገኖች ቢመክሩትና ቢገስጹትም ለመታረም ፈቃደኛ አለመሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል፡፡ አንድ ጽሑፍ የትርጉም ሥራ ከሆነ ምንጩን ጠቅሶ ለዋናው ደራሲ ዕውቅና መስጠት ተገቢ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው፡፡ አንድን ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ ተርጉሞ ካቀረበ በኋላ የግል ሥራው ይመስል የራሱን ስም ከርዕሱ ስር አስፍሮ ምንጭ አለመጥቀስ በትምሕርቱ ዓለም ከስርቆት የሚቆጠር ድርጊት ነው፡፡ የእንግሊዘኛውን ጽሑፍ ከምንጩ ማንበብ ለሚፈልጉ ወገኖች በዚህ አድራሻ ይገኛል https://unveiling-christianity.net/2017/12/24/christmas-special-holy-spirit-art-thou/
ሙስሊሙ ሰባኪ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-
◾️የተረሳው መንፈስ ቅዱስ
(የሕያ ኢብኑ ኑህ)
እንደ ክርስቲያኖች እምነት መሠረት ከሥላሴ አካላት ውስጥ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ እንደ አብና ወልድ እኩል መለኮታዊ ስልጣን ያለው አምላክ ነው ብለው ያምናሉ። እንዳለመታደል ሀኖ ግን መንፈስ ቅዱስ የሚገባውን ያክል ቦታ አልተሰጠውም። አንዳንዴም እንዴውም ሌሎች አካላት ሁሉ ተጠቅሰው እሱ ሲረሳ እንታዘባለን። እንዴው መንፈስ ቅዱስ አምላክ የተባለው ሁሉ “አምላክ ሁለት ነው” እንዳይባል ተብሎ ብቻ የኃለኛው ጉባኤ የጨመረው ይመስላል። ይህንን ጥርጣሬ እስኪያረጋግጥልን ድረስ መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያኖች ልብም ሆነ በመጽሀፍ ቅዱስ ከአብና ወልድ ጋር እንኳን እኩል የማይታወስ ባይተዋር ተደርጓል።
መንፈስ ቅዱስ ከሥላሴ አካላት አንዱ የመሆኑን እውነታ የኋለኛው ጉባዔ የጨመረው ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማያሻማ መንገድ ተጠቅሶ የምናገኘው ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ባሕርያት ሁሉ እንዳሉት ተገልጿል፡፡ ለአብነት ያህል፡-
- ፈጣሪ ነው – ኢዮብ 33፡4፣ መዝሙር 33፡6፣ መዝሙር 104፡29-30፣ ኢዮብ 33፡4
- ምሉዕ በኲለሄ (በሁሉም ቦታ የሚገኝ) ነው – መዝሙር 139፡7-10፣ 1ቆሮንቶስ 2፡10-11
- አዕማሬ ኲሉ (ሁሉን አዋቂ) ነው – ኢሳይያስ 40፡13፣ ዮሐንስ 14፡16፣ 1ቆሮንቶስ 2፡10-11
- ከኃሊ ኲሉ (ሁሉን ቻይ) ነው – ሚክያ 2፡7፣ መዝሙር 104፡30፣ ማቴዎስ 12፡28፣ ሮሜ 15፡18-19
- ዘላለማዊ ነው – ኢሳይያስ 48፡16፣ ዮሐንስ 14፡16፣ ዕብራውያን 9፡14
መንፈስ ቅዱስ ማንነት ያለው (እኔ ማለት የሚችል) አካል መሆኑንና አንዳንዶች እንደሚሉት ኃይል ብቻ አለመሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ለአብነት ያህል፡-
- ይናገራል:- 2 ሳሙኤል 23:2፣ የሐዋርያት ሥራ 8:29፣ የዮሐንስ ራዕይ 2፡7
- ይመራል:- ሮሜ 8 14፣ ዮሐንስ 16:13
- ይጠራል፣ ተልእኮዎችንም ይሰጣል፡- ሐዋርያት ሥራ 13፡2፣ 20:28
- ያዛል፡- የሐዋርያት ሥራ 8፡29
- በአማኞች ውስጥ ይኖራል፡- ዮሐንስ 14 17፣ 1 ቆሮንቶስ 6:19
- ያስተምራል፡- ዮሐንስ 14 26; 1 ዮሐንስ 2:27
- ይልካል፡- የሐዋርያት ሥራ 13:4
- ኃይልን ይሰጣል፡- የሐዋርያት ሥራ 1:8፣ 2ጴጥሮስ 1:21
- ይመሰክራል፡- ዮሐንስ 15፡26፣ 27፣ 16: 13,14
- ሊመረር ይችላል፡- ኢሳይያስ 63:10
- ያዝናል፡- ኤፌሶን 4፡30
- ሰዎች ሊዋሹት ይችላሉ፡- የሐዋርያት ሥራ 5 3
- ሰዎች ሊሰድቡት ይችላሉ፡- ማቴዎስ 12፡31
- ይከበራል፡- መዝሙር 51፡11
- ስጦታን ይሰጣል፡- 1ቆሮንቶስ 12፡27-28
- ያፅናናል፡- ዮሐንስ 16፡7
- ይወቅሳል፡- ዮሐንስ 16፡8-11
ማንነት አልባ ኃይል ከላይ የተጠቀሱት ባሕርያት ሊኖሩት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም በዝርዝሩ ውስጥ እንደሚታየው መንፈስ ቅዱስ የማንነት መገለጫ የሆኑትን ሦስቱን ባሕርያት፤ ማለትም ዕውቀት፣ ፈቃድና ስሜት ስላለው ማንነት አለው፡፡
በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ ከሠላሳ በሚልቁ መጠርያዎች በመቶዎች በሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት የሠራቸውን ታላላቅ ሥራዎች የሚተርክ ሲሆን እኔ ባደረኩት ቆጠራ በመጽሐፉ ውስጥ ብቻ ለ 56 ያህል ጊዜያት ተጠቅሷል፡፡ በአማኞችም ከሥላሴ አካላት እንደ አንዱ ተገቢው ክብር ይሰጠዋል፡፡ በቤተክርስቲያን የአምልኮ ስርዓት ወቅትም መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር ሊጠቀስ የማይችልበትን አጋጣሚ ማሰብ ያዳግታል፡፡ ስለዚህ ይህ ጸሐፊ “መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያኖች ልብም ሆነ በመጽሀፍ ቅዱስ ከአብና ወልድ ጋር እንኳን እኩል የማይታወስ ባይተዋር ተደርጓል” ብሎ ማለቱ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ይህ ክርስትናንና መጽሐፍ ቅዱስን ከማያውቅ አንድ ሙስሊም የሚጠበቅ የተሳሳተ መረዳት ነው፡፡ በሌላ ጽሑፋችን እንዳሳየነው የቁርኣን ጸሐፊ የሥላሴን አስተምሕሮ በትክክል ያቀረበበት አንድም ጥቅስ የለም፡፡ ሦስቱን የሥላሴ አካላት፣ ማለትም አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስን በጋራ አንድም ጊዜ አልጠቀሰም፡፡ ከዚህ በተፃራሪ ተከታዩን ጥቅስ በመጻፍ ሙስሊሞችን ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ የመራ መልዕክት አስተላልፏል፡-
“አላህም፡- የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ አንተ ለሰዎቹ፡- እኔንና እናቴን ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለሃልን? በሚለው ጊዜ (አስታውስ)፤ ጥራት ይገባህ፤ ለኔ ተገቢዬ ያልሆነን ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም፤ ብዬው እንደሆነም በእርግጥ አውቀኸዋል፤ በነፍሴ ውስጥ ያለውን ኹሉ ታውቃለህ፤ ግን አንተ ዘንድ ያለውን አላውቅም፤ አንተ ሩቆችን ኹሉ በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህና ይላል” (ሱራ 5፡116)፡፡
ይህ ምናባዊ ምልልስ በዕለተ ቂያማ (በፍርድ ቀን) በአላህና በዒሳ መካከል የሚደረግ እንደሚሆን ሙስሊሞች ያምናሉ፡፡ የቁርኣን ጸሐፊ መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ አካል መሆኑ በክርስቲያኖች መታመኑን የጠቀሰበት ቦታ ባለመኖሩ ብዙ ሙስሊሞች ከዚህ ጥቅስ በመነሳት ሥላሴ ማለት አላህ፣ ማርያምና ኢየሱስ እንደሆኑ ያስባሉ፡፡ በዚህ ዘመን የሚገኙት አንዳንድ ሙስሊም ምሑራን አሸማቃቂ የሆነውን ይህንን የቁርኣን ስሁት መረዳት አለባብሶ ለማለፍ የተለያዩ ትርጉሞችን ለመስጠት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ጥንታዊያን ሙስሊም ሊቃውንት ይህ ጥቅስ ስለ ሥላሴ የሚናገር መኾኑን በጽሑፎቻቸው አስፍረዋል፤ በዚህ ዘመን የሚገኙት ብዙ ሙስሊሞችም ተመሳሳይ አመለካከት ያንፀባርቃሉ፡፡ (ቀዳሚውን የሙሐመድ ግለታሪክ የከተቡት ኢብን ኢስሐቅና ከነባርሐታቾች (Classical Commentators) መካከል አንዱ የሆኑት አል–ዘመቅሻሪ ይጠቀሳሉ፡፡ Ibn Ishaq, Sirat Rasul Allah, Translated by Alfred Guillaume, Oxford University Press, 1995, pp. 271-272; Helmut Gätje, The Quran and its Exegesis, One Word Publications, 1996, pp. 126-127)፡፡ ለክርስቲያናዊ አስተምሕሮ መሠረታዊ እውቀት የጎደለው ሰው ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም ክርስቲያን ሥላሴ ማለት አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ መኾኑን ያውቃል፡፡ ክርስቲያኖች ኢየሱስና ማርያም ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች እንደሆኑ አያምኑም፡፡ ነገር ግን አንዱና ብቸኛው አምላክ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ የተሰኙ ሦስት አካላት እንዳሉት ያምናሉ፡፡ የቁርኣን ደራሲ ይህንን ሃቅ ባላወቀበት ሁኔታ ከዚህ የተሻለ ዕውቀት ከሙስለሊም ሰባኪያን መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ በማስከተል እንዲህ ሲል የቅጥፈት ዲስኩሩን ይቀጥላል፡-
ማቴዎስ በወንጌሉ እንዲህ ማለቱ ተፅፏል፦
“ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም።” — ማቴዎስ 11፥27
በዚህ ምስል ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ተቆርጦ ቀርቷል። በአንቀፁ ላይ ተቆርጦ መቅረቱ ብቻ ሳይሆን የመለኮታዊነቱ ፅንሰሀሳብም ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ምክንያቱም በዚህ አንቀፅ መሠረት ስለ አብ የሚያውቀው ወልድ ብቻ ሲሆን ስለወልድም የሚያውቀው አብ ብቻ ነው። ማርክ ግሪሰርና ባልደረቦቹ በህብረት ባዘጋጁት “Reconsidering the Cornerstone of the Christian Faith” በተሰኘው መጽሀፍ ገፅ 584 ላይ ይህንን አስመልክቶ እንዲህ ይላሉ፦
“መንፈስ ቅዱስ በትክክል ራሱን የቻለ አካል ከነበረና ከሶስቱ አካላት የተለየ አምላክ ከነበረ (በዚህ ንግግሩ መሠረት) ወይ ኢየሱስ ያንን አያውቅም ነበር ማለት ነው፤ አልያም ለመንፈስ ቅዱስ በሚሰጠው ክብር ዙሪያ ቋሚ መርህ አልነበረውም ማለት ነው” [1] Graeser, M. H., Lynn, J. A. & Schoen (2010). One God & One Lord: Reconsidering the Cornerstone of the Christian Faith. Indiana: Spirit & Truth Fellowship international. p. 584
ሙስሊሙ ሰባኪ የጠቀሳቸው የሥላሴ ተቃዋሚዎች የሆኑት የኑፋቄ መምህራን ከተናገሩት በተጻራሪ መንፈስ ቅዱስ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ውስጥ አለመጠቀሱ ተቆርጦ ቀርቷል አያስብልም፡፡ አብና መንፈስ ቅዱስ ተጠቅሰው ወልድ ያልተጠቀሰባቸው ወይንም ወልድና መንፈስ ቅዱስ ተጠቅሰው አብ ያልተጠቀሰባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መኖራቸውን ማስታወስ ያሻል፡፡ ነገር ግን የማቴዎስ ወንጌል 11፡27 ተጓዳኝ ንባብ የሆነውን በሉቃስ ወንገል ውስጥ የሚገኘውን ክፍል ስንመለከት መንፈስ ቅዱስም በምስሉ ውስጥ መካተቱን እንመለከታለን፡-
“በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አደረገና፦ የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግናለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፥ ወልድንም ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፥ አብንም ማን እንደ ሆነ ከወልድ በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር የሚያውቅ የለም አለ።” (ሉቃስ 10፡21-22)
በዚህ ቦታ ሦስቱም የሥላሴ አካላት ተጠቅሰው ሳሉ ጌታችን ኢየሱስም ይህንን ንግግር በመንፈስ ቅዱስ ሆኖ እንደተናገረ በግልፅ ተነግሮ ሳለ በቁንፅል ንባብ ተነስቶ መንፈስ ቅዱስ ተቆርጦ እንደቀረ መናገር ለትዝብት ይዳርጋል፡፡
የመንፈስ ቅዱስን ማንነትና በሥላሴ አካላት ውስጥ ያለውን ሚና የተረዳ ሰው በዚህ ንግግር ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመንፈስ ቅዱስን ዕውቀት አለመጥቀሱ ጥያቄ ሊፈጥርበት አይችልም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሌላ ቦታ ላይ መንፈስ ቅዱስ ከአብ የሚሰርፅ መሆኑን ስላስተማረ የአብ ቃልና ጥበብ የሆነው ኢየሱስ ከአብ ተነጥሎ እንደማይታየው ሁሉ የአብ መንፈስ የሆነው መንፈስ ቅዱስም ከአብ ተነጥሎ አይታይም (ዮሐንስ 15፡:26)፡፡ ለዚህ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል የተናገረው፡-
“መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም።” (1ቆሮንቶስ 2፡10-11)
ሰውና መንፈሱ እንደማይነጣጠሉ ሁሉ እግዚአብሔርና መንፈሱም ስለማይነጣጠሉ እግዚአብሔር የሚያውቀውን ሁሉ መንፈሱም ያውቃል፡፡ አንድን ጉዳይ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን በተናገርንበት ቅፅበት መንፈሱም እንደሚያውቅ ተናግረናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ መረዳት አኳያ ተከታዮቹ ሙግቶች ትርጉም አልባ ይሆናሉ፡-
የማቴዎስ 11፥27ን መልዕክት አስመልክቶ ክርስቲያኖች የሚከተሉት ሁለት ምርጫዎች ይኖሯቸዋል፦
1- ሥላሴ እውነት ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ከሥላሴ አካላት ውስጥ አንዱ የሆነ አምላክ ነው። ነገር ግን ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን አስመልክቶ በሚናገራቸው ንግግሮች ውስጥ ቋሚነት/Consistency/ የለም። እሱን በተመለከተ የሚያውቀው አብ ብቻ እንደሆነ ሲናገርም አማኙን አታሏል ማለት ነው።
በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ እንደተጻፈው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመንፈስ ቅዱስ የሰጠው ክብር ለመለኮት ብቻ ተገቢ የሆነ ነው፡-
“ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፥ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም። በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም።” (ማቴዎስ 12፡31-32)
መንፈስ ቅዱስን መሳደብ ከሌሎች ስድቦች ሁሉ ተለይቶ ስርየት የሌለው ኃጢአት የሆነበት ምክንያት መንፈስ ቅዱስ መለኮት በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህ ነው ይህንን ሙስሊም ጸሐፊ የመሳሰሉት አጉል ሐያሲያን ዛሬ በግድየለሽነት በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚናገሩት ቃል በፍርዱ ቀን ነፍሳቸውን እንዳያስከፍላቸው መጠንቀቅ የሚገባቸው፡፡
በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ ከአብ የሚሰርፅ መሆኑን አስተምሮናል፡- “ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፡፡” (ዮሐንስ 15፡26)
መንፈስ ቅዱስ የአብ መንፈስ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱና በአብ መካከል ያለውን ትውውቅ በልዩ ሁኔታ መግለፁ ፍጡራንን ታሳቢ ያደረገ እንጂ መንፈስ ቅዱስን ታሳቢ ያደረገ አይደለም፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ዕውቀት አለመጥቀሱ ከአብ ጋር አንድ መሆኑን ከማወቅ የመነጨ በመሆኑ የጸሐፊው የተሳሳተ መረዳት በቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ ውስጥ ቦታ ያለው አይደለም፡፡ በማስከተል እንዲህ በማለት በተሳሳተ ቅድመ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ “አመክንዮ” ያቀርባል፡-
2. ኢየሱስ በማቴዎስ ወንጌል ንግግሩ ቋሚ መርህን ካንፀባረቀና አታላይም ካልነበር መንፈስ ቅዱስ አምላክ አልነበረም፤ ሥላሴም ፈጠራ ነው ማለት ነው።
ሀሳቡን ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ በሚከተለው መንእሳዊ አመክንዮት ተነስተን በአጭር ሲሎጂዝም እናስቀምጠው፦
ምንስኤ 1፦ ሥላሴ ሶስት አካላት ሲሆኑ እያንዳንዱ አካል በራሱ ምሉዕ የሆነ እውቀት ያለውና አንድኛው ስለ አንድኛው እርስበርስ የሚተዋወቅ ነው።
ምንስኤ 2፦ ሦስተኛው አካል ማለትም መንፈስ ቅዱስ እንደ ማቴዎስ 11፥27 ገለፃ መሠረት ስለ አብና ወልድ የሚያውቀው ነገር የሌለ ሲሆን ተነጥሎ ባይተዋር ተደርጓል።
መደምደሚያ፦ መንፈስ ቅዱስ አምላክ አይደለም፤ ሥላሴም መሠረተ ቢስ አስተምህሮ ነው።
ቀደም ሲል እንደገለፅነው መንፈስ ቅዱስ የአብ መንፈስ በመሆኑ አብ ብቻ የሚያውቀውን ሁሉ መንፈስ ቅዱስም ያውቃል፡፡ የሥላሴ አካላት ልዩ (Distinct) እንጂ የተነጣጠሉ (Separated) አይደሉም፡፡ አንድን ጉዳይ እግዚአብሔር ብቻ ነው የሚያውቀው ማለት የእግዚአብሔር መንፈስ አያውቅም ማለት አይደለም፡፡ ሙስሊሙ ሰባኪ በማጠቃለያው ክርስቲያን ጸሐፊያንን በመጥቀስ እንዲህ ይለናል፡፡
ስኮት ሐንና ኩርቲስ ሚች አዲስ ኪዳንን ባብራሩበት ስራቸው የማቴዎስ 11:27ን አንቀፅ ሲያብራሩ፦
“አብና ወልድ የተገለፁበት እውቀት በሥላሴ አማካኝነት አንድ የሆኑበት እውቀት ነው። ይህም ማለት የተጋሩት መለኮታዊ እውቀት የተጋሩትን መለኮታዊ ባህሪን ይጠቁማል” [2] Hahn, S. & Mitch, C. (2010). Ignatius Catholic Study Bible: New Testament. San Francisco: Ignatius Press. p. 26
በዚህ ገለፃ መሠረት መንፈስ ቅዱስ ከዚህ ክብር ገሸሽ ተደርጓል። በትክክልም መልዕክቱ ስለመለኮታዊ አንድነት ከሆነ “በብቻ” ሳይታጠር ሶስተኛው አካል መንፈስ ቅዱስም አብሮ መጠቀስ ነበረበት። ይህ አንቀፅ የመንፈስ ቅዱስን የተረሳ ማንነት ከማጋለጡም በላይ አስተምህሮ– ሥላሴን ቅርቃር ውስጥ የከተተ የኢየሱስ ንግግር እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል።
ይህ የጸሐፊውን የተሳሳተ መረዳት ከማሳየት የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ አብ ብቻ የሚያውቀውን መንፈሱም ያውቃል፡፡ ምክንያቱም መንፈሱ የራሱ የአብ ነውና፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ደግመን እናስታውስ፡- “መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም።” (1ቆሮንቶስ 2፡10-11)
የሥላሴን አካላት አንድነት የተረዳ ሰው እንዲህ ያሉ ጥቅሶች ጥያቄ አይፈጥሩበትም፡፡ ለአብ የተነገሩ ባሕርያተ መለኮት ሁሉ የወልድም የመንፈስ ቅዱስም ናቸው፡፡ የአብና የወልድ ዕውቀት የመንፈስ ቅዱስም ነው፡፡ ሰውና መንፈሱ አንድ እንደሆኑ ሁሉ እግዚአብሔርና መንፈሱም አንድ ናቸውና፡፡
ጸሐፊው የጠቀሰው መጽሐፍ ጌታችን ማቴዎስ 11፡27 ላይ የተናገረው ንግግር መለኮት መሆኑን እንደሚያረጋግጥ የሚገልፅ መሆኑን ልብ ያለ አይመስልም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጥረት ከመታወቅ ያለፈ መሆኑንና እርሱን የሚያውቀው አብ ብቻ መሆኑን እንዲሁም በፍጥረት ከመታወቅ ያለፈውንና ኢ-ውሱን የሆነውን አብን የሚያውቀው እርሱ ብቻ መሆኑን መናገሩ መለኮት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ይህም የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የሚክደው የሙሐመድ አስተምህሮ ሐሰት መሆኑን አረጋጋጭ ነው፡፡