የአብደላህ ኢብን መስዑድ የቁርኣን ጥራዝ ከሌሎች ለምን ተለየ? የአቡ ሀይደር ትርጉም አልባ ትርጉም

የአብደላህ ኢብን መስዑድ የቁርኣን ጥራዝ ከሌሎች ለምን ተለየ?

የአቡ ሀይደር ትርጉም አልባ ትርጉም


የቁርኣንን አሰባሰብ ታሪክ ያጠኑ ወገኖች በመጀመርያው የሙስሊም ትውልድ ዘመን የተለያየ ርዝማኔ ያላቸው ቁርኣኖች እንደነበሩ ያውቃሉ። የአብዱላህ ኢብን መስዑድ ቁርኣን 111 ምዕራፎች፣ የኡበይ ቢን ካዕብና የኢብን አባስ ቁርኣን 116 ምዕራፎች፣ የኡሥማን ኢብኑ አፋን ቁርኣን 114 ምዕራፎች ነበሯቸው። በውስጣዊ ይዘት ረገድም ስንመለከት እርስ በርሳቸው የማይስማሙ የተለያዩ ቁርኣኖች እንደነበሩ ከእስላማዊ ምንጮ መረዳት ይቻላል። ለጽሑፍ ሳይበቁ የጠፉና ከተጻፉ በኋላ የተረሱ ብዙ አናቅፅ መኖራቸውም እንደዚያው። በዚህ ዙርያ ያዘጋጀናቸው በርካታ ጽሑፎች በገጻችን ላይ ይገኛሉ። በዚህ ጽሑፍ የአብደላህ ኢብን መስዑድ የቁርኣን ጥራዝ ከሌሎች ለምን እንደተለየ በአንድ ሙስሊም ሰባኪ የተሰጠውን ምላሽ የምንመለከት ይሆናል። ሙስሊሙ ሰባኪ ጽሑፉን ከሌላ ምንጭ “በመተርጎም” ያቀረበ ሲሆን የገዛ ራሱን ቁጣ፣ ዘለፋና ምሬት በማከል ጽፏል። በአጠቃላይ ሲታይ ለክርስቲያኖች ትክክለኛ ጥያቄ መልስ ሊሆን የማይችል ትርጉም አልባ ጽሑፍ ነው። እንዲህ ሲል ይጀምራል፦

አቡ ሀይደር

ክፍል አንድ

የክፍል አንድ መግቢያ

የክርስቲያን ሚሽነሪዎች እና  የምስራቁ አለም አጥኚዎች ሁሌም እስልምናን ለማንቋሸሽ እና  የእስልምና ዋና መመሪያ የሆነውን ቁርኣንን በተመለከተ የተለያዩ ትችቶችን ይሰነዝራሉ።  ከነዚህም ትችቶች መካከል አንደኛው “የነብዩ ባልደረባ የሆኑትና ቁርኣንን ሰዎች እንዲማሩ ከተናገሩለት አንዱ የሆኑት አብደላህ ኢብን መስዑድ ከሌሎች ባልደረቦቹ የተለየ ቁርኣን ሙስሐፍ ነበረው! በዚህ አብደላህ ያዘጋጀው ጥራዝ ላይ ያለው የምዕራፍ ብዛት 114 ሳይሆን 111 በመሆኑና አሁን በእጃችን ከሚገኘው የቁርኣን ምእራፍ አንጻር የተለየ ስለነበር ቁርኣን ‘አልተበረዘም’  እያላችሁ ሙስሊሞች የምትሞግቱት ሙግት ከራሳችሁ ማስረጃ እየጠቀስን ሙግታችሁ ውሃ የማይቋጥር መሆኑን ማስገንዘብ እንፈልጋለን!” ይላሉ።

መልስ

ሙስሊም ሰባኪያን በእስልምና ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች እስልምናን እያንቋሸሹ እንደሆኑ የሚሰማቸው ለምን ይሆን? የጥንት ሙስሊሞች በቁርኣን ይዘት ዙርያ ስምምነት ለምን እንዳልነበራቸው መጠየቅ በምን ሒሳብ ነው “ማንቋሸሽ” የሚሆነው? ለጥያቄያችን መልስ ስለሌላቸው የሙስሊም አንባቢያንን አእምሮ አስቀድሞ መመረዝ ደካማ ምላሾቻቸውን ለመደገፍ የሚጠቀሙበት እኩይ አካሄድ መሆኑ ግልፅ ነው።

አቡ ሀይደር

አሁን በሙስሊሞች እጅ ያለው ቁርኣን 114 ምእራፍ ያለው ነው ። በአብደላህ ኢብን መስዑድ ሙስሐፍ ( Codex ) ውስጥ ለክስ የቀረቡት ምእራፎች ደግሞ እንደሚከተሉት ናቸው ። ከሳሾቻችን እንደሚሉት ከሆነ እነዚህ ሶስት ምእራፎች የቁርኣን ክፍል አልነበሩም።

ምእራፍ 1 ፡- ሱረቱል አል-ፋቲሃ(የመክፍቻ ምእራፍ ) የሚባል 7 አንቀፅ ያሉት፡

ምእራፍ 113፡-ሱረቱል አል-ፈለቅ (አምስት አንቀፆች ያሉት – ቁል አኡዙ ቢረቢል ፈለቅ…..)

ምእራፍ 114፡ ሱረቱል አንናስ ( ስድስት አንቀጾች ያሉት – ቁል አኡዙ ቢረቢናስ…….)

ምእራፍ 1( ሱረቱል ፋቲሃ/የመክፍቻ ምእራፍን) በተመለከተ፡-

መልስ

ሙሐመድ ራሱ ቁርኣንን እንዲያስተምሩ ሥልጣን ከሰጣቸው አራት ሰዎች መካከል አንዱ የነበረው አብደላህ ኢብን መስዑድ እነዚህ ሱራዎች በጽሑፍ የሰፈረው ቁርኣ አካል እንደሆኑ አያምንም ነበር። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ጠያቂን ማጠልሸት ለምን አስፈለገ?

አቡ ሀይደር

ይህ ምእራፍ ማለት እያንዳንዱ ሙስሊም በቀን አምስት ግዜ የሚሰግደዉ የግዴታ ሰላት ላይ በቀን  17 ግዜ የሚደጋግመው መነባንብ ነው።  ነብዩም(ዐሰወ) ይህንን የሰላት አሰገዳድ  በተግባር አሳይተው ማንኛውም ሰው ሰላት  በሚሰግደበት ሰአት ይህንን የቁርአን ምእራፍ  ማንበብ ግዴታ እንደሆነም ጭምር አስተምረዋል። ይህንን ለተከታዮቻቸው አንዲሁም ለእኛም ጭምር በተለያዩ ሐዲሶች ደርሶን ይኸው እስከዛሬ ድረስ  በቀን 17 ግዜ  በሰላት ላይ እናነበዋለን።

አብደላህ ኢብን ቀታዳ እንደዘገበው አባቴ እንዲህ ማለቱን ዘግቧል

“ ነብዩ (ዐሰወ) ሱረቱል አል-ፋቲሃን  ከሌሎች አንቀጾች ጋር በዙሁር እና በአሱር ሰላት ወቅት ይቀሩ ነበር አንዳንዴ አንድ  ወይም ከዚያ በላይ አንቀጾችን ድምጻቸውን አውጥተው ይቀሩት ነበር።”

ሰሂህ አል-ቡኻሪ 762 እና ሰሂህ አል-ቡኻሪ 729

ከዚህ ሐዲስ የምንረዳው አብደላህ ኢብን መስዑድ እንደማንኛውም ሙስሊም  የግዴታ ሰላትን እየሰገደ ህይወቱን ያሰለፈ አማኝ መሆኑን ልብ ይበሉ።

መልስ

ሙስሊሙ ሰባኪ ለትክክለኛው ጥያቄ መልስ እየሰጠ አይደለም። የኢብን መስዑድ አመለካከት ሦስቱ ሱራዎች የቁርኣን አካል አይደሉም የሚል ሳይሆን በጽሑፍ የሰፈረው ቁርኣን አካል አይደሉም የሚል ነው፡፡ በዚህም ሳብያ ከራሱ ጥራዝ እንዲወገዱ አድርጓል፡፡ ኢብን መስዑድ ሱራዎቹ ለሙሐመድ የተገለጡለት የቁርኣን ክፍሎች መሆናቸውን ቢቀበልም ጸሎቶች ብቻ በመሆናቸው በጽሑፍ መስፈር እንደሚገባቸው አያምንም ነበር፡፡ ስለዚህ ሙስሊሙ ሰባኪ ያቀረበው የሐዲስ ማስረጃ ሦስቱ ሱራዎች በኢብን መስዑድ ጥራዝ ውስጥ ስለመካተታቸው ማስረጃ ሊሆን አይችልም፡፡ ሙሐመድ ሦስቱ ሱራዎች ከሌሎች ሱራዎች ጋር በአንድ ጥራዝ እንዲቀመጡ ትዕዛዝ መስጠቱን የሚያመለክት ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም።

አቡ ሀይደር

ሌላው  አብደላህ ኢብን መስዑድ ሰለ ቁርኣን 15፡87 ማብራሪያ ተጠይቀው፡-

وَلَقَدْ آتَيْنَاكَ سَبْعًا مِّنَ الْمَثَانِي وَالْقُرْآنَ الْعَظِيمَ

ከሚደጋገሙ የኾኑን ሰባትንና ታላቁንም ቁርኣን (በሙሉ) በእርግጥ ሰጠንህ።

ሱረቱል ሒጅር 15፡87

ይህ አንቀጽ ” ሰለ አልፋቲሃቱል ኪታብ ‘’ በማለት ሰለ አል ፋቲሃ የቁርአን ክፍል መሆኑን  አብራርተዋል።1  ይህም የሚያመለክተው አብደላህ ኢብን መስዑድ ሰለዚህ የቁርአን ክፍል ያላቸው ግንዛቤ እንደማንኛውም ሙስሊም ጥርት ያለ መሆኑን ነው።

በሌላ ሐዲስ አል- ፋቲሃ ( የመጽሀፉ እናት) ያልተቀራበት ሰላት ጎዶሎ ነው ብለዋል፡፡  አዒሻ ረዓ እንደዘገበችው  የአላህ  መልእክተኛ  ዐሰወ “ ማንኛውም ኡሙል ኪታብ ያልተቀራበት ሰላት ጎዶሎ ነው “ ብለዋል። 2

መልስ

አሁንም የኢብን መስዑድ አመለካከት አልፋቲሃም ሆነ ሌሎቹ ሱራዎች በጽሑፍ የሰፈረው ቁርኣን አካል አይደሉም የሚል እንጂ በቃል የሚነበነበው ቁርኣን አካል አይደሉም የሚል ባለመሆኑ ትክክለኛው ጥያቄ መልስ እያገኘ አይደለም። ሱረቱል ሒጅር 15፡87 በግልጽ እንደሚነበበው አል-ፋቲሃ ከሌላው የቁርኣን ክፍል የተለየ ነው። ከዚህ ቀደም በሌላ ጽሑፍ እንደገለፅነው “ከሚደጋገሙ የኾኑን ሰባትን እና ታላቁንም ቁርኣን በእርግጥ ሰጠንህ” ብሎ ሲል የሚደጋገሙ ሰባት የተባሉት የአል-ፋቲሃ ሰባቱ አንቀፆችና ታላቁ ቁርኣን የተባለው መጽሐፍ ሁለት ነገሮች መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡ የአል-ቡኻሪ ሐዲስም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡-

“…Shall I not teach you the most superior Surah in the Qur’an?” He said, ‘(It is), ‘Praise be to Allah, the Lord of the worlds. ‘ (i.e., Surat Al-Fatiha) which consists of seven repeatedly recited Verses and the Magnificent Qur’an which was given to me.”

“…በቁርአን ውስጥ ታላቂቱን ሱራ ላስተምርህ አይገባኝምን? እንዲህም አለ፡- ምስጋና ለአላህ ይሁን የዓለማቱ ጌታ ለሆነው (ማለትም ሱረቱ አል-ፋቲሃ) በተደጋጋሚ የሚነበነቡ ሰባት አንቀፆችን የያዘችውን እና ለኔ የተሰጠኝ ታላቁ ቁርአን፡፡” (Sahih al-Bukhari፡ Book 66, Hadith 28)

በአል-ቡኻሪ ሐዲስ መሠረት አል-ፋቲሃ የቁርኣን አካል ነው ደግሞም ከቁርአን ተለይቶ ታይቷል፡፡ ይህም ለሙሐመድ የወረደለት ቁርኣን አካል ቢሆንም በጽሐፍ የሰፈረው ቁርኣን አካል አይደለም የሚለውን የኢብን መስዑድን አቋም የሚደግፍ ነው፡፡

አቡ ሀይደር

ከላይ ባየናቸው ማስረጃዎች አብደላህ ኢብን መስዑድ አል- ፋቲሃ የቁርአን አካል አይደለም ብሎ ሊያስብበት የሚችል ቅፅበት እንኩዋን የለም፡ ስለዚህ ኸሊፋው ኡስማን ረዐ እንዲሰባሰብ ባደረጉት የቁርአን ሙስሐፍ ላይ ይህ መኖሩ እሱ እንደጨመረው አድርጎ ማሰቡ ቅጥፈት ነዉ፡፡የቀረቡት መረጃዎች/ክሶች የሚሉት ኢብን መስኡድ አል-አልፋቲሃ የቁርአን ክፍል አይደለም ብሎ ያምናል ሳይሆን የሚሉት እሱ ዘንድ በነበረዉ ኮዴክስ (ሙስሀፍ) አልተፃፈም ነዉ የሚሉት። እሱ አልፃፈዉም ማለት ግን የቁርአን አካል አይደለም  ብሎ ያምናል ማለትን አያመላክትም!!

Abu hurairah said:The Messenger of Allah (ﷺ) commanded me to announce that prayer is not valid but with the recitation of Fatihat al-kitab and something more

Sunan Abi Dawud 820 Book 2, Hadith 430 Book 2, Hadith 819

ይህ ወሳኝ ነጥብ ነዉ።

መልስ

የኢብን መስዑድ አቋም ሦስቱ ሱራዎች በቃል የሚነበነቡ ጸሎቶች እንጂ በጽሑፍ የሰፈረው ቁርኣን አካል አይደሉም የሚል መሆኑ ያስማማናል። ኢብን መስዑድ ቁርኣንን በቀጥታ ከሙሐመድ የተማረና እንዲያስተምር ሥልጣን የተቀበለ በመሆኑ የትኛው ሱራ በጥራዝ መስፈር እንዳለበትና እንደሌለበት ያውቃል፤ ስለዚህ ሦስቱ ሱራዎች በጥራዝ እንዲሰፍሩ በማድረጋቸው ምክንያት ኡሥማንና ተባባሪዎቹ ተሳስተዋል። ከሙሐመድ ቁርኣንን በቀጥታ የተማረው ኢብን መስዑድ አል-ፋቲሃ እና የተቀሩት ሁለት ሱራዎች በጽሑፍ የሰፈረው ቁርኣን አካል እንዳልሆኑ ያምን የነበረ ሆኖ ሳለ ኡሥማንና ተባባሪዎቹ ስለምን በዋናው ጥራዝ ውስጥ በማካተት በጽሑፍ አሰፈሯቸው? ትክክለኛው የክርስቲያኖች ጥያቄ ይህ ሆኖ ሳለ ሙስሊሙ ሰባኪ ያልተጠየቀውን ሲመልስ መቆየቱ አስገራሚ ነው።

አቡ ሀይደር

ታዲያ ለምንድ ነው  አብደላህ ኢብን መስዑድ አል-ፋቲሃን ያልጻፈው ?

አቡበከር አል አንባሪ( የሞቱት 304 ሒጀሪያ)፡- አብደላህ ኢብኑ መስዑድ ለምን አል-ፋቲሃን በሱ ጥራዝ ላይ እንዳልጻፈ ተጠይቆ ሲመልስ “ ብጽፈው ኖሮ  ከእያንዳንዱ አንቀጽ በፊት እጽፈው ነበር “  ማለቱን ተዘግቧል። ይህንን አንባሪ ሲያብራሩት ‘ በሰላት ላይ ማንኛውም ረከዓ በፋቲሃ ይጀምራል ከዚያም ሌላ አንቀጽ ይቀራል፡ ኢብን መስዑድ ለማለት የፈለገው ያልጻፈበት ምክንያት ለማሳጠር እና  አንቀጹ በሙስሊሞች ዘንዳ ይዘነጋል ብዬ ስለማላስብ ነው ‘  ብለው አብራርተዉታል።

قيل لعبد الله بن مسعود: لم لم تكتب فاتحة الكتاب في مصحفك؟ قال: لو كتبتها لكتبتها مع كل سورة. قال أبو بكر يعني أن كل ركعة سبيلها أن تفتتح بأم القرآن قبل السورة المتلوة بعدها، فقال: اختصرت بإسقاطها، ووثقت بحفظ المسلمين لها

Abdullah bin Mas’ood was asked as to why he did not write al-Fatihah in his mushaf. He replied, “If I were to write I would write it before every surah.” Abu Bakr al-Anbari explains this saying every raka‟ah (in prayers) starts with al-Fatihah and then another surah is recited. It is as if Ibn Mas’ood said, “I have dropped it for the sake of brevity and I have trusted its preservation by Muslims (collectively).”

Al-Qurtubi, al-Jami’ li-Ahkam al-Qur’an,Vol.1, 115

መልስ

ከሌላ ዘገባ እንደምንመለከተው ኢብን መስዑድ ይህንን ሱራ ያስወገደበት ምክንያት ሙሐመድ በጽሑፍ እንዲሰፍር ስላላዘዘ መሆኑ ተነግሯል፦

“ኢማም ፈኽሩዲን እንደተናገሩት በአንዳንድ ጥንታውያን መጻሕፍት ውስጥ ኢብን መስዑድ ሱረቱል ፋቲሃ እና ሙዐዊዘተይን (ሱራ 113 እና 114) የቁርአን አካል መሆናቸውን ክዷል የሚሉት ዘገባዎች አሸማቃቂ ምልከታ አላቸው … ነገር ግን ቃዲ አቡ በከር እንዲህ ብለዋል፡- “የቁርአን አካል አይደሉም የሚል ተዓማኒ ዘገባ ከእርሱ አልተላለፈም፤ እንዲህ ብሎም መናገሩ አልተጻፈም፡፡ ከራሱ የእጅ ጽሑፍ ያስወገደበት ምክንያት በጽሑፍ መስፈር እንዳለባቸው ስላላመነ ነው፡፡ ይህ ማለት የቁርአን አካል መሆናቸውን ክዷል ማለት አይደለም፡፡ በእርሱ አመለካከት መሠረት ሱና ነቢዩ ያላዘዙት የትኛውም ነገር በጽሑፍ (ሙሳሒፍ) መስፈር የለበትም የሚል ነበር … እንደዚያ ዓይነት ትዕዛዝ መሰጠቱን ደግሞ አልሰማም፡፡” (አል-ኢትቃን፣ ገፅ 186)

በዚህ መሠረት ኢብን መስዑድ ሦስቱ ሱራዎች ለሙሐመደ የወረዱለት እንደሆኑ ቢያምንም በጽሑፍ መስፈር እንዳለባቸው አላመነም፤ ከሙሐመድም እንደዚያ የሚል ትዕዛዝ አልደረሰውም፤ እናም በራሱ ጥራዝ ውስጥ አላካተተም። በራሱ ጥራዝ ውስጥ ላለማካተቱ መሠረታዊው ምክንያት ይህ ቢሆንም ሌሎች ሰበቦችም ሊኖሩት ይችላሉ። ስለዚህ ለጠያቂዎቹ የተለያዩ ምላሾችን ቢሰጥም ቅሉ መሠረታዊው ምክንያት ምን እንደሆነ ተነግሮናል። ሙስሊሙ ሰባኪ ይህንን ወሳኝ ነጥብ ወደ ጎን በማድረግ ኢብን መስዑድ አል-ፋቲሃ የተጻፈው ቁርኣን ጥራዝ አካል እንደሆነ ያምን እንደነበር ለማስመሰል ሲሞክር ይታያል። ይህ ስሁት አካሄድ ነው።

አቡ ሀይደር

የክፍል አንድ ማጠቃለያ፡-

አብደላህ ኢብን መስዑድ አልፋቲሃ የቁርአን ክፍል አይደለም ብሎ እንደማያምን በሰላት ውስጥ ከቁርአን ውጪ ሌላ እንደማይቀራ፡ ነብዩ አሰወ ያለ ፋቲሃ ሰላት ሙሉ እንደማይሆን የተናገሩበት ሀዲስ እንዲሁም እራሳቸው በቀን ሰላቶች ላይ ማለትም ዙሁር እና አስር ስላት ላይ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ( ምንም እንኳ በነዚህ የሰላት ወቅቶች ድምጽ ከፍ ተደርጎ ባይነበብም)  ሰላት ማሰገዳቸውን  ይኽም ሰዎችን በተግባር እያስተማሩ እንደነበረ የሚያሳያ በቂ አሳማኝ ማስረጃዎች ናቸው።

መልስ

ሙስሊሙ ሰባኪ ከተናገረው በተጻራሪ ኢብን መስዑድ አል-ፋቲሃ በጽሑፍ የሰፈረው ቁርኣን አካል እንደሆነ እንደማያምን፣ ቁርኣንና የአል-ቡኻሪ ሐዲስ ውስጥ በተጻፈው መሠረት አል-ፋቲሃ ከተቀረው ቁርኣን ተለይቶ እንደተጠቀሰ፣ ሙሐመድ አል-ፋቲሃ በጽሑፍ እንዲሰፍር የተናገረበት ወይም እንዲጻፍ ያደረገበት አጋጣሚ ስለመኖሩ ማስረጃ አለመኖሩንና ኢብን መስዑድም በዚህ ምክንያት ከገዛ ጥራዙ እንዳስወገደው ተመልክተናል። እውነታው ይህ ከሆነ ኡሥማንና ተባባሪዎቹ በምን ማስረጃ ነው የቁርኣን ጥራዝ አካል እንዲሆን ያደረጉት? ጥያቄው መልስ አላገኘም።

አቡ ሀይደር

ክፍል  ሁለት

የክፍል ሁለት መግቢያ

በክፍል አንድ ለምን አብደላህ ኢብን መስዑድ አል ፋቲሃን እንዳልጻፈው ነገር ግን የተለያዩ ሐዲሶችን እና ነቢያዊ ትግበራዎችና ትእዛዞችን በማየት አልፋቲሃ የቁርአን አካል መሆኑን እራሱ እንደሚያምን አይተናል በዚህ ክፍል ደግሞ ምእራፍ 113 እና ምእራፍ 114 በተመለከተ ለሚቀርቡ ክሶችን እንዳስሳለን።

እንደተለመደው ወገኖቻችን  አብደላህ ኢብን መስዑድ ምእራፍ 113 እና ምእራፍ 114 ቁርኣን አይደሉም ብሎ ያምናል ስለዚህ እናንተ ከ 1400 አመት በዃላ ቁርአን 114 ምእራፍ አለው ብላአችሁ ትከራከራላችሁ ይሉናል።

መልስ

ቀደም ሲል እንዳልነው ኢብን መስዑድ ሦስቱ ሱራዎች የተጻፈው ቁርኣን አካል እንዳልሆኑ ያምን ነበር፤ ስለዚህ በገዛ ቁርኣኑ ውስጥ ስላላካተታቸው የእርሱ ቁርኣን 111 ሱራዎች ብቻ ነበሩት። ሙስሊሙ ሰባኪ ይህንን ማስተባበል አልቻለም።

አቡ ሀይደር

1-ከነብዩ (ዐሰወ) የተዘገቡ ሐዲሶች ሁለቱ ምእራፎች የቁርኣን ክፍሎች መሆናቸውን ያመለክታሉ።

እነዚህ ሁለት ሱራዎች የቁርአን ክፍል መሆናቸውን አሁንም የነብዩ ሀዲስ አለ ሀዲሱ እንዲህ ይነበባል።

በአዒሻ ኡሙል ሙእሚኒን (ረአ) እንደተዘገበው፡አብዱልአዚዝ ኢብኑ ጁራይጅ እንዲህ አለ”የምእመናን እናት አዒሻን የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) በየትኛው (ሱራ) የዊትር ስላትን ይፈጽማሉ ? ብዬ ጠየቅኩኝ በሦስተኛው ረከዓ “በል «እርሱ አላህ አንድ ነው።” (ሱራ 112) እና “በል «በተፈልቃቂው ጎህ ጌታ እጠበቃለሁ።” (ሱራ 113) ፣ እና “በል «በሰዎች ፈጣሪ እጠበቃለሁ።”  (ሱራ 114)።

ሱነን አቢ ዳውድ 1424 መጽሐፍ 8 ፣ ሐዲስ 9 እንዲሁም መጽሐፍ 8 ፣ ሀዲስ 1419

ከዚህ ሐዲስ ምንረዳው ሰላተል ዊተር ላይ ከሚቀራው ቁርኣን ውስጥ ሁለቱ የመጨረሻዎቹ ምእራፎች መኖራቸውን አንባቢ ልበ ይበል።

በሌላ ዘገባ እንዲሁም አዒሻ ረአ እንደዘገበችው “ የአላህ መልእክተኛ በታመሙ ግዜ  ሙኣዉዘተይን ( ሱራ አል ፈለቅ እና ሱራ አል ናስ ) ይቀሩ ነበር ከዚያ ትንፋሻቸውን ሰውነታቸው ላይ ኡፍ ይሉ ነበር፡ በጠና የታመሙ ግዜ (እነዚህን ሁለት ሱራዎች) እቀራና  ሰውነታቸውንና እጆቻቸውን በረከቱን  ተስፋ በማደረግ አሻሻቸው ነበር። 1

መልስ

በቃል የሚነበነበው ቁርኣን አካል እንጂ የተጻፈው ቁርኣን አካል ስለመሆናቸው ማስረጃ የለም። ስለተነበነቡ ብቻ የዋናው ቁርኣን ጥራዝ አካል ናቸው ከተባለ እንደ ሱረቱ አልኸልዕ እና ሱረቱ አልሐፍድ ያሉ በቃል የሚነበነቡ በዋናው ጥራዝ ውስጥ በጽሑፍ ያልሰፈሩ የቁርኣን ክፍሎች አሉ። እነርሱም የዋናው ቁርኣን አካል ተደርገው መጻፍ ነበረባቸው ማለት ነው። ኢብን መስዑድ እነዚህ ሱራዎች የቁርኣን ጥራዝ አካል አይደሉም ብሏል፤ ስለዚህ ሙስሊሙ ሰባኪ እነዚህ ሱራዎች የቁርኣን ጥራዝ አካል ስለመሆናቸው ማስረጃ ማምጣት ይጠበቅበታል።

አቡ ሀይደር

2- ከሌሎች የቁርኣነን አንቀጾች ጋር ሲነጻጸር

ቁርኣን በነብዩ (ዐሰወ) ላይ እንደመውረዱ በቁርአን ውስጥ ያሉ አንቀጾች የሚያመሳስላቸው ብዙ ነገሮች አሉ ለምሳሌ “ቁል“ በል የሚለው ትእዛዛዊ ንግግር በቀጥታ የሚመለከተው ነብዩን (ዐሰወ) ነው በዚህም የአንቀጾቹን ተመሳሳይ መልእክት ማየት ይቻላል። ለምሳሌ ቁርኣን 6፡161  እና 6፡162 ማየት ይቻላል።

መልስ

መስፈርቱ ይህ ከሆነ አል-ፋቲሃ “ቁል” ወይም “በል” የሚል ቃል የለውም ስለዚህ ምን ልትለው ነው? ከቁርኣን ውስጥ የተወገዱ አላህ እንዳወረዳቸው የተነገረላቸው ሌሎች ሱራዎችንስ ምን ልታደርጋቸው ነው? ከሌሎች ሱራዎች ጋር የሚያመሳስሏቸው ይዘቶች አሉ። “ቁል” የሚለው ቃል መኖርም ሆነ ከሌሎች ሱራዎች ጋር መመሳሰል በቁርኣን ውስጥ ለመካተት መስፈርቶች አይደሉም። “ቁል” የሚለው ቃል ሳይኖረው በቁርኣን ውስጥ የተካተተ ሱራ አለ፤ ከሌሎች ሱራዎች ጋር በብዙ መልኩ የሚመሳሰሉ ሆነው ሳሉ ከቁርኣን ውስጥ የተወገዱ ሱራዎች አሉ። ሙግቱ ደካማ ነው።

አቡ ሀይደር

3-የሙተዋቲርና አሐድ የዘገባ ሰንሰለት

ቁርአን  ነብዩ ሙሐመድ (ዐሰወ) ላይ ከወረደ በዃላ ወደ እኛ የደረሰው በአዕምሮ በመሸምደድና በጹሁፍ ዘገባ ሰንሰለት ነው። በዚህ  የዘገባ ሂደት ውስጥ የተለያዩ ሰዎች ይህ የቁርአን አንቀጽ ቀጥታ ከነብዩ (ዐሰወ) እንደተገኘ ከተለያየ አቅጣጫ እና ከተለያየ ሰው ሲረጋገጥ የዘገባው ሒደት ሙተዋቲር ይባላል። በተቀራኒው ደግሞ የዘገባው ሰንሰለት በሌላ መንገድ ሳናረጋግጠው በአንድ ሰው በኩል ብቻ ሲረጋገጥ ይህ የዘገባ ሂደት አሐድ ይባላል። በዚህ መለኪያ መሰረት ከኢብን መስዑድ ይዘው የዘገባ ሰንሰለቱን ወደ እኛ ያደረሱን አራት አይነት የቁርኣን አነባብ ዘዴዎች አሉ።  ሁሉም  የአቀራር አይነቶች እነዚህን የቁርኣን ክፍሎች መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። ስለዚህ  ምእራፍ 113 እና ምእራፍ 114 የቁርአን ክፍሎች ለመሆናቸው በቂ ማስረጃዎች ናቸው።

መልስ

በኢብን መስዑድ መሠረት በቃል የሚነበነቡ እንጂ በጽሑፍ የሰፈረው የቁርኣን ጥራዝ አካል አይደሉም። ኢብን መስዑድ እነዚህን ሱራዎች ለተማሪዎቹ በጽሑፍ ማስተላለፉን የሚያሳይ ማስረጃ የለም። ይልቅ እነዚህ ሱራዎች በእርሱ ጥራዝ ውስጥ በጽሑፍ እንዳልሰፈሩ ማስረጃዎች አሉ፦

“Ibn Mas‘ood did not write al-mu’awwizatayn in his mushaf.” (Musnad Ahmad bin Hanbal, (Beirut: ar-Resalah Publications, 2001) Hadith 21186

“ኢብን መስዑድ አል-ሙዐዊዘተይንን (አል-ፈለቅ እና አን-ናስን) በሙሳሂፉ ውስጥ አልጻፈም፡፡”

እዚያው ሙስናድ አሕመድ ቢን ሐንበል ሐደስ ቁጥር 21186 ላይ እንዲህ ተብሏል፡-

“I told Ubayy, ‘your brother Ibn Mas‘ood erases them (surah 113 & 114) from his mushaf,’ and he did not object.”

“ኡበይን እንዲህ አልኩት “ያንተ ወንድም ሱራ 113 እና 114ን ከሙሳሂፉ ውስጥ ሰርዟቸዋል”፤ እርሱም ተቃውሞ አላቀረበም።”

ስለዚህ የሙስሊሙ ሰባኪ “ማስረጃ” መስመር የሳተ ነው።

አቡ ሀይደር

4-የአብደላህ ኢብን መስዑድ የራሱ ማስረጃ

አብደላህ ኢብን መስዑድ እንደዘገቡት “አብዝተህ እነዚህን ሁለት ሱራዎች አንብብ ፡በእነሱ ምክንያት በትንሳኤ ቀን አላህ ከፍ ያለ ደረጃ ይሰጣችዃል እነሱም አል -ሙአዉዘይተይን ናቸው “ ብለዋል። 2 ይህም የሚያሳየው  እነዚህ ሁለት ምእራፎች አሁንም በኢብን መስዑድ ዘንድ የቁርአን ክፍል  ወይንም  እንደ ቁርኣን እንደሚታዩ በቂ ማስረጃ ነው። በሌላ ዘገባ አብደላህ ኢብን መስዑድ እንዲህ ብለዋል፡-

‘አንድን የቁርኣን  ፊደል  ያልተቀበለ ሙሉውን ቁርአን እንዳስተባበለ ነው ‘

عن ابن مسعود قال: من كفر بحرف من القرآن فقد كفر به كله

“One who rejected a single letter of the Qur’an, he (is like the one who) rejected the whole of it.”

Abdur-Razzaq, al-Musannaf, Hadith 15946

በተጨማሪም አሁንም በሌላ ዘገባ

ስለ የሆነ ምእራፍ ላይ ተወዛገብን – 35 አንቀጽ ነዉ ያለዉ ወይስ 36 እያልን – ከዚያም ወደ ነብዩ  ዐሰወ ጋር ሄደን ጠየቅን ….

Ahmad bin Hanbal, al-Musnad, Hadith 832

ስለዚህ እንዲህ አይነት ለአንድ አንቀጽ ጠንቃቃ የሆኑ ግለሰብ ሶስት ምእራፎችን  የቁርአን አካል አይደሉም የሚሉበት ምክንያት የለም።

تمارينا في سورة من القرآن، فقلنا: خمس وثلاثون آية، ست وثلاث آية، قال: فانطلقنا إلى رسول الله صلى الله عليه وسلم

“We differed about a surah. We said [and differed if] it has thirty-five verses or thirty six verses. So we went to the Messenger of Allah –may the peace and blessings of Allah be upon him [to clarify the matter]…”

Ahmad bin Hanbal, al-Musnad, Hadith 832

መልስ

አሁንም ሙስሊሙ ሰባኪ በኢብን መስዑድ መሠረት እነዚህ ሱራዎች የተጻፈው ቁርኣን ጥራዝ አካል ስለመሆናቸው ማስረጃ አላቀረበም። ኢብን መስዑድ እነዚህ ሱራዎች ለሙሐመድ እንደወረዱለትና የቁርኣን አካል እንደሆኑ ቢያምንም የተጻፈው ቁርኣን ጥራዝ አካል ናቸው ብሎ አያምንም ነበር። ለዚህም ከገዛ ቁርኣኑ አስወግዷቸዋል።

አቡ ሀይደር

የክፍል ሁለት ማጠቃለያ፡-

አብደላህ ኢብን መስዑድ ከተላላቅ  የነብዩ ባልደረቦች መካከል  ሲሆኑ፡ ታላቅ የቁርኣን ተንታኝ  እንዲሁም ነብዩ (ዐሰወ ) ሰዎች ቁርኣን መማር ከፈለጉ ሄደው እንዲማሩ ከተናገሩላቸው ድንቅ ሰሃባዎች አንዱ ናቸው። ከላይ በክፍል አንድ እንዳየንው በራሳቸው ሙስሐፍ አለመጻፉ ቁርአን አይደለም ብለው ያምናሉ ማለትን አያመለክትም።

መልስ

ኢብን መስዑድ ሦስቱ ሱራዎች የቁርኣን ክፍል አይደሉም ብሏል በማለት የተናገረ ክርስቲያን አላጋጠመኝም፤ እኛም በጽሑፎቻችን ውስጥ እንደዚያ ብለን አናውቅም። ነገር ግን የተጻፈው ቁርኣን ጥራዝ አካል ነው ብሎ አልተቀበላቸውም። የዋናው ቁርኣን ጥራዝ አካል ያልሆኑ በርካታ አናቅፅ በሐዲሳት ውስጥ ከመገኘታቸው አንጻር ኡሥማንና ተባባሪዎቹ እነዚህን ሱራዎች በምን ማስረጃ የቁርኣን ጥራዝ አካል እንዳደረጓቸው ሊነገረን ይገባል። ኢብን መስዑድ ከአራቱ አነብናቢዎች መካከል አንዱ የነበረ ሲሆን ሙሐመድ በአንደኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠው ሰው ነበር፤ ስለዚህ የእርሱ ቃል ከኡሥማንም ሆነ ከዘይድ በላይ ተቀባይነት አለው። ነገር ግን የእነርሱን ቁርኣን በግልፅ ተቃውሟል፦

“አዝ-ዙህሪ እንዳስተላለፈው፤ ኡበይ ቢን አብዱላህ ቢን ኡጥባህ እንደነገረኝ አብደላህ ቢን መስዑድ ዘይድ ቢን ሣቢት ሙሳሒፉን በመጻፉ ደስተኛ ስላልነበረ እንዲህ ብሎ ነበር፡- ‹እናንተ የሙስሊም ሕዝቦች ሆይ! የዚህን ሰው ሙሳሒፍ እና የእርሱን ንባብ ከናንተ አስወግዱ፡፡ በአላህ እምላለሁ! እኔ እስልምናን ስቀበል በከሃዲ ሰው እርግብግቢት ውስጥ ነበር፡፡› አብደላህ ኢብን መስዑድ አክሎም እንዲህ አለ፡- ‹እናንተ የኢራቅ ሕዝቦች ሆይ! ከናንተ ጋር ያሉትን ሙሳሒፎች ያዟቸው፤ ደግሞም ደብቋቸው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏልና ‘የሆነ ነገር የሚሰውር ሰው በዕለተ ትንሣኤ የሰወረውን ነገር ይዞ አላህን ይገናኘዋል፡፡’ ስለዚህ አላህን ሙሳሒፉን ይዛችሁ ተገናኙት፡፡› አዝ-ዙህሪ እንደተናገረው ‹ከተከበሩ የአላህ መልእክተኛ ባልደረቦች መካከል አንዳንዶቹ ይህንን የኢብን መስዑድ አመለካከት አልወደዱትም ነበር፡፡›” (English Translation of Jami‘ At-Tirmidhi. Compiled by Imam Hafiz Abu ‘Eisa Mohammad Ibn ‘Eisa At-Tirmidhi; translated by Abu Khaliyl; Darussalam Publishers & Distributors, First Edition, 2007, Vol. 5, pp. 414)

አቡ ሀይደር

ማስታወሻ፡ ይህ ጽሁፍ ከ Journal of Islamic Sciences vol.1 issue.1 June 3, 2013 By Waqar Akbar Cheema ላይ ወደ አማርኛ የተመለሰ ነው።

መልስ

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ለጥያቄያችን መልስ የሚሆን ምንም ነገር አላገኘንም። ሌላ የተሻለ ጽሑፍ ፈልገህ ብትተረጉምልን መልካም ነው። ይኸኛው ትርጉም፣ ትርጉም አልባ ነው።


ቁርኣን