ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው

ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው

ሰሞኑን ሙስሊም ኡስታዞች ተከታዩን ሙግት “የሞኝ ዘፈን” ስላደረጉት መልስ ልንሰጣቸው ወደድን፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው መሆኑን በተመለከተ ያለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምሕሮ ለማጣጣል “ሎጂክ” የሚመስል ሙግት አቅርበዋል፡፡ በኢታሊክስ የተጻፈው የእነርሱ ሙግት ነው፡፡ እንዲህ በማለት ይጀምራሉ፡-

1. በመጀመር ነገር ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትም ቦታ አይገኝም! የተለመደ የሥላሴ አማኞች የቃላት ውሕደት ውጤት ነው፡፡

በሃይማኖታዊ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ፅንሰ ሐሳቦችን ለመግለፅ ቃላትን ማዋሓድ እስልምናን ጨምሮ በየትኛውም ሃይማኖት የተለመደ በመሆኑ ይህንን እንደ ትችት ማንሳት አስቂኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሦስቱ የተውሒድ አስተምሕሮ መሠረታውያን የሚባሉትን (ተውሒድ አር-ሩቡቢያ፣ ተውሒድ አል-ኡሉሒያ፣ ተውሒድ አስማ ወስሲፋት የሚሉ ቃላትን) ከቁርኣን ውስጥ ልታሳዩን አትችሉም፡፡ ይህ ማለት ግን ፅንሰ ሐሳቦቹ በቁርኣን ውስጥ የሉም ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ ጥያቄው መሆን ያለበት ቃላቱ የሚወክሉት ፅንሰ ሐሳብ በመጽሐፉ ውስጥ አለ ወይንስ የለም? የሚል እንጂ ቃሉ አለ ወይንስ የለም? የሚል አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሙግት የማሰብ ደረጃችሁን ስለሚያስገመግም ባትደጋግሙት ጥሩ ነው፡፡

2. አንድ ነገር በጭራሽ ሁለት ተቃራኒ “ፍፁሞች” ሊሆን አይችልም! አስቡት አንድን አካል “ፍፁም ነጭ ፍፁም ጥቁር” ነው ስትሉት! ከአመክንዬ አንፃርም እጅግ የተፋለሠ ገለፃ ነው፡፡

ለመፈላሰፍ ብትሞክሩም ፍልስፍናውን አልቻላችሁበትም፡፡ አንድ ነገር በአንድ ጊዜ ፍፁም ነጭና ፍፁም ጥቁር የማይሆንበት ምክንያት ንጣትና ጥቁረት ከአንድ መደብ፣ ማለትም ከቀለም መደብ ስለሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር በአንድ ጊዜ ፍፁም ነጭ እና ፍፁም ክበብ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ንጣትና ክብነት ከሁለት የተለያዩ መደባት፣ ማለትም ከቀለምና ከቅርፅ መደባት ናቸውና፡፡ ሰውነትና አምላክነት ሁለት መደባት በመሆናቸው ኢየሱስ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው እንዳይሆን የሚከለክለው “የአመክንዮ ሕግ” የለም፡፡ በሌላ ወገን ካየነው ደግሞ ንጣት የሁሉም መሠረታዊ ቀለማት ውሕድ ሲሆን ጥቁረት ደግሞ ከመሠረታዊ ቀለማት የተገኙ የሁለተኛ ደረጃ መሠረታዊ ቀለማት ውሕድ ነው፡፡ ስለዚህ ጥቁረት በንጣት ውስጥ ይገኛል፡፡ በዚህ ደረጃ ካየነው ንጣትና ጥቁረት ተቃራኒ መስለው የታዩን እኛ በዚያ መንገድ ስለተመለከትናቸው እንጂ ሁለቱም ቀለማት ተወራራሽ ናቸው፡፡ እናም በሁለቱ ቀለማት መካከል ያለውን ጥልቅ ትስስር እንዳልተረዳችሁት ሁሉ ስለ መለኮትና ስለ ሰው ያልተረዳችሁት ጉዳይ ሊኖር ስለሚችል ተረጋግቶ ማሰቡ አይከፋም፡፡

3. አምላክና ሰው በባህሪያቸው የተለያዩ አካላት ናቸው! የሰው ልጅ ደካማ ሲሆን አምላክ ሁሉን ቻይ ነው፣ የሰው ልጅ እውቀቱ የተገደበ ሲሆን አምላክ ሁሉን አዋቂ ነው፡፡ ሁለት በባህሪይ ፍፁም የተለያዩ አካላት በፍፁም አንድ የሚሆኑበት መንገድ የለም፡፡

ይህ ሙግት ሁለት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡- የመጀመርያው ሰብዓዊነትና አምላክነትን በፍፁም አንድ ላይ ሊኖሩ የማይችሉ ተቃራኒ ባሕርያት አድርጎ ማቅረቡ ነው፡፡ ይህም የክርስትናን ትምሕርተ-ሰብዕ (አንትሮፖሎጂ) ካለመረዳት የመነጨ ስህተት ነው፡፡ ሰው መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ለሚለው ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ “በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ መፈጠር ማለት ነው” የሚል ምላሽ ይሰጠናል፡፡

“እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” (ዘፍ. 1፡26-27)

“አምሳለ እግዚአብሔር” ሲባል ብዙ ገፅታዎች አሉት፡፡ በመጀመርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን አገዛዝ በምድር ላይ ይወክላሉ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰዎች የእርሱን አገዛዝ በመወከል በምድር ላይ እንዲገዙ ሥልጣንን ሰጥቷቸዋል (ዘፍ. 1፡26)፡፡ ሁለተኛ የእግዚአብሔርን ባሕርይ እናሳያለን ማለት ነው፡፡ የሰው ልጆች እንደ ቅድስና፣ ፍቅር፣ ቸርነት የመሳሰሉትን መልካም የሆኑትን የእግዚአብሔር ባሕርያት ማንፀባረቅ ይችላሉ፡፡ ሰዎች የእግዚአብሔርን ባሕርይ ማሳየትና በዚያም ምክንያት የእግዚአብሔርን ክብር መግለጥ እንደሚችሉ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል (ዘሌ. 19፡2፣ ኤፌ. 5፡1፣ 1ጴጥ. 1፡16፣ 1ዮሐ. 4፡8)፡፡ ሰውን ዝቅ አድርጎ መመልከት ከእስልምና ስህተቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ሦስተኛ በአምሳለ እግዚአብሔር መፈጠር ማለት በእርሱ ክብርና ሕይወት ውስጥ ተካፋዮች እንሆናለን ማለት ነው (ኢሳ. 60፡1-2፣ ሕዝ. 10፡19፣ ዮሐ. 12፡22፣ ሮሜ 5፡2፣ 1ጴጥ. 4፡14፣ 2ጴጥ. 1፡3-4፣ 2ቆሮ. 3፡19)፡፡ የሰው ልጆች የክብሩ ተካፋዮች ይሆኑ ዘንድ የእግዚአብሔር ዕቅድ ነው፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሔር በአምሳሉ ሲፈጥረን በእርሱና በኛ መካከል ልዩ ግንኙነት እንዲኖር አድርጎ ነው ማለት ነው፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሰው የእግዚአብሔርን አገዛዝ ሊወክል ይችላል፣ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ማንፀባረቅ ይችላል፣ የክብሩም ተካፋይ መሆን ይችላል፡፡ ኃጢአት እነዚህን ነገሮች ከማድረግ ቢያግደንም ኃጢአት አልባ የሆነ ሰው የነዚህ ሁሉ ትሩፋት ተቋዳሽ ነው፡፡ በእስልምናም ሆነ በክርስትና አስተምሕሮ መሠረት በሰው ልጆች ታሪክ ኃጢአት ያልነካው አንድ ሰው ቢኖር ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህ መለኮታዊ ባሕርይን መግለጥ ይችላል፡፡ አባታችን አዳም ንፁህ ሆኖ የተፈጠረ ቢሆንም በኃጢአት በመውደቁ ምክንያት ከገነት ተባረረ፡፡ “ሁለተኛው አዳም” ተብሎ የተጠራው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ክብር የጎደሉትን የሰው ልጆች ወደ ስፍራቸው ለመመለስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር መጣ (1ቆሮንቶስ 15:45)፡፡

የሙግቱ ሁለተኛው ስህተት መለኮታዊ ሉኣላዊነትን ከስሌቱ ውጪ ማድረጉ ነው፡፡ ሰው አምላክ የመሆን ችሎታ የለውም ነገር ግን እግዚአብሔር በሰው አምሳል ተገልጦ ከሰዎች ጋር መኖር ከፈቀደ ከልካይ የሌለው ሁሉን ቻይ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ ሁኔታ ከመጀመርያውኑ በራሱ አምሳል በመፍጠር ለባሕርዩ ተስማሚ ስላደረገው ሰው ሆኖ ወደ ምድር ቢመጣ ከባሕርዩ ጋር የሚጋጭ ምንም ነገር የለውም፡፡ የኛ ድርሻ “እውን አምላክ ሰው ሆኖ ወደ ምድር መጥቷል ወይ?” ብሎ ማስረጃዎችን ማጤን እንጂ “በፍፁም ሊሆን አይችልም” ብሎ መከራከር ሉኣላዊ ሥልጣኑን የመቃወም አጉል ድፍረት ነው፡፡

4. መጽሐፍ ቅዱስ ቅዱስ በግልፅ ቋንቋ አምላክ ሰው እንዳልሆነ ይገልፃል ፦ “እኔ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁምና፥ በመካከልህም ቅዱሱ ነኝና የቁጣዬን መቅሠፍት አላደርግም፥ ኤፍሬምንም አጠፋ ዘንድ አልመለስም፤ በመዓትም አልመጣም። ” (ትንቢተ ሆሴዕ 11:9)

መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ሰው አለመሆኑን ሲናገር ሰው ሆኖ ወደ ምድር መምጣት አለመቻሉን ሳይሆን እንደ ሰው ኃጢአተኛ ባሕርይ እንደሌለበትና ኢ-ፍትሃዊ አለመሆኑን ለመግለፅ ነው፡፡ በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር በሰው አምሳል የተገለጠባቸው ጊዜያት ነበሩ (ዘፍጥረት 18፡1-33፣ 32፡24-32)፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በእነዚህ የሰው ልጆች መጥፎ ባሕርያት ባልተበከለ ሁኔታ ወደ ሰው ልጆች ምሕዳር መግባት ይችላል፡፡ ሌላው መታወቅ ያለበት ጉዳይ እኛ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው እንደሆነ እንጂ ግማሽ ሰው ግማሽ አምላክ ወይንም ወደ ሰው የተለወጠ አምላክ እንደሆነ አለማመናችን ነው፡፡ ክርስቲያኖች “አምላክ ሰው ነው” አይሉም፡፡ ነገር ግን “ኢየሱስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው” በማለት ያምናሉ፡፡ ሰው የሆነው የኢየሱስ ባሕርይ አምላክ አይደለም፡፡ አምላክ የሆነውም የኢየሱስ ባሕርይ ሰው አይደለም፡፡ ስለዚህ በብሉይ ኪዳን ዘመን አምላክ ሰው አለመኾኑ መነገሩ በአዲስ ኪዳን ዘመን አምላክ በሥጋ የመገለጡን እውነታ አይፃረርም፡፡

5. የኢየሱስን ታሪክ ስንመለከት ደግሞ በምድር ላይ ሲኖር የፍፁምነት ባህሪ አልነበረውም፤ የረገማትን የበለስ ፍሬ ወራቷን ካለማወቅ ጀምሮ ብዙ አይነት የሰው ልጅ ደካማ ባህሪያትን አስተናግዷል፡፡ እናም ምዕመናን ቃሉ ብዙም አያስኬድምና ከሰበካ ውጭ ለውይይት አትጠቀሙበት!

የተጠቀሰው ምሳሌ የኢየሱስን ፍፁምነት የሚያሳይ ነው፤ ፍፁም ሰውነቱን! ጸሐፊው “ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው” ብሎ በመጀመር “ፍፁም ሰው” መሆኑን የሚያሳይ ምሳሌ ከጠቀሰ በኋላ “የፍፁምነት ባሕርይ አልነበረውም” ብሎ ማለቱ ከቀልቡ ሆኖ እየጻፈ እንዳልሆነ ያሳያል፡፡

እናም ኡስታዞች ሙግታችሁ በጭራሽ አያስኬድምና በስውር ግሩፖች ውስጥ ምዕመናንን “ጀዘክ” ለማስባል ካልሆነ በስተቀር አደባባይ ላይ አትጠቀሙት፡፡

 

መሲሁ ኢየሱስ