ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ተናግሯልን?
ሙስሊም ወገኖች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል “ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እኔ አምላክ ነኝና አምልኩኝ በማለት የተናገረበትን ቦታ አሳዩን” የሚለው አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ይህ አግባብ የሆነ ጥያቄ ቢመስልም ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስን ተልዕኮ በትክክል ካለመረዳትና የመጽሐፍ ቅዱስን ቋንቋ በትክክል ካለማወቅ የመነጨ ጥያቄ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ለመሆን የግድ እኔ አምላክ ነኝና አምልኩኝ በማለት መናገር ያስፈልገዋል የሚለው እሳቤ ምክንያታዊ አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ስለመሆኑ፣ ስለስቅለቱ፣ ስለሞቱና ስለትንሳኤው የተናገረባቸው በርካታ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ ሙስሊም ወገኖች እነዚህን እውነታዎች አለመቀበላቸው ኢየሱስ “አምላክ ነኝና አምልኩኝ” ያለበትን ቦታ ብናሳያቸው ሊቀበሉ እንደማይችሉ ያሳያል፡፡ ታድያ የጥያቄቸው ትክክለኛው ነጥብ ምንድነው?
ሙስሊም ወገኖች በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ አምላክ መሆኑን የተናገረባቸውን ቦታዎችበመጥቀስ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በተመሳሳይ መንገድ መናገር ነበረበት ይሉናል፡፡ ነገር ግን የብሉይ ኪዳን እና የአዲስ ኪዳን ዘመናት ልዩነት እንዳላቸው አይገነዘቡም፡፡ እግዚአብሔር በሁሉም ዘመናት በተመሳሳይ መንገድና ሁኔታ ራሱን መግለጥ የግድ አያስፈልገውም፡፡ ጥያቄያችን ሊሆን የሚገባው ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነቱን በምን ዓይነት መንገድ ነው የገለጠው? የሚል እንጂ “እኛ በምንፈልገው መንገድ ስላልተናገረ አምላክ አይደለም” በማለት መደምደም ትክክል አይደለም፡፡
በአዲስ ኪዳን ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ገልጧል፡፡ ነገር ግን ይህ መንገድ “አምላክ ነኝና አምልኩኝ” የሚሉትን እነዚህን ቃላት በመናገር ላይሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ “እኔ ባልኩት መንገድ ካልተናገረ በስተቀር አምላክነቱን አልቀበልም” በማለት ሌሎች ማስረጃዎችን መካድ ጠያቂው መልስ ፈላጊ ሳይሆን ክርክር ፈላጊ መሆኑን ያሳያል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ይመላለስ በነበረበት ዘመን “አምላክ ነኝና አምልኩኝ” የሚሉትን እነዚህን ቃላት መናገር ያላስፈለገበትን የተወሰኑ ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህንን ስንል ግን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነቱን ክዷል፣ ሸሽጓል ወይንም ደግሞ በምንም አይነት መንገድ አልተናገረም ማለታችን አይደለም፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው አምላክነቱንና ጌትነቱን ለማወጅ አልነበረም፡፡ የኢየሱስ ተልዕኮ ራሱን በማዋረድ ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ መስጠት እንጂ መለኮታዊ ክብሩን በማወጅ ሰዎች እንዲያውቁት ባለመሆኑ በየስፍራው እየዞረ አምላክነቱን ቢያውጅ ከተልዕኮው ጋር የሚጣጣም አይሆም፡፡ ጌታችን የራሱን ክብር ፍለጋ እንዳልመጣ በተደጋጋሚ ተናግሯል (ዮሐንስ 8:50፣ ማቴዎስ 20:28)፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን ሐሳብ ልብን በሚነካ መንገድ ገልፆታል (ፊልጵስዩስ 2፡5-10)፡፡
ኢየሱስ በእርሱና በአብ መካከል ያለውን የአካል ልዩነት ግልፅ ሳያደርግ ‹አምላክ ነኝና አምልኩኝ› የሚሉትን ቃላት ቢናገር አይሁዶች ግራ ይጋቡ ነበር፡፡ አይሁዶች ስለ እግዚአብሔር ሦስቱ አካላት፣ ማለትም ስለ ሥላሴ ግንዛቤ ስላልነበራቸው ኢየሱስ ‹አምላክ ነኝና አምልኩኝ› የሚሉትን ቃላት ቢናገር ‹አብ ነኝ› የሚል ስለሚመስላቸው እንዲህ ብሎ መናገሩ ግርታን ከመፍጠርና በእርሱ ላይም ተቃውሞን ከማስነሳት የዘለለ ጠቀሜታ ሊኖረው አይችልም ነበር፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ አምላክነቱን የሚያሳዩ ስራዎችን እየሰራ እና በትምህርቶቹም ውስጥ ጥበብን በተሞላ መንገድ እየነገራቸው ሰዎች አምላክ መሆኑን ወደማወቅ ደረጃ እንዲመጡ መርቷቸዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ሲያደርግ ሁል ጊዜ ከአብ ጋር ያለውን የአካል ልዩነት ግልፅ በማድረግ ነበር፡፡
ኢየሱስ በምድር ላይ ይመላለስ በነበረበት ዘመን ከሌሎች ሰዎች የተለየ መልክ አልነበረውም፡፡ ዛሬ አንድ ሰው ወደ እኛ መጥቶ ‹አምላክ ነኝና አምልኩኝ› ቢለን እንደማንቀበለው ሁሉ ኢየሱስም በዘመኑ ይህንን ቢል ኖሮ ተቃውሞን ከማትረፍ ውጪ ምንም ጠቀሜታ አይኖረውም ነበር፡፡ ‹አምላክ ነኝና አምልኩኝ› ከሚለው መንገድ ይልቅ በተግባር አምላክ መሆኑን መግለጥ የተሻለ በመሆኑ ይህንኑ አድርጓል፡፡ ሰዎች ደግሞ ሥራውን በማየት አምላክነቱን ወደ ማወቅ ሲመጡና ለአምላክ የሚገባውን ክብር ሲሰጡት በመስማማት ሲያረጋግጥላቸው እንጂ አንድም ጊዜ ሲቃወማቸው አልታየም (ዮሐንስ 20:24-29)፡፡
ኢየሱስ አምላክ መሆኑን የገለጠባቸው መንገዶችና ንግግሮች
መሲህ መሆኑን (ክርስቶስ መሆኑን) በመናገር፡-
ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ትንቢት የተነገረለት መሲህ መሆኑን በተደጋጋሚ ተናግሯል (ማቴዎስ 16፡13-17፣ ዮሐንስ 4፡25-26፣ 26፡1-3 ማርቆስ 14:1-2፣ 12:35-37፣ 13፡26-27 ሉቃስ 24፡13-15፣ 24፡25-27፣ 24፡44-49 ይመልከቱ)፡፡
የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች መሲሁ አምላክ መሆኑን ይናገራሉ:-
“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም፡፡ የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል፡፡” ትንቢተ ኢሳይያስ 9፡6-7
“የጭፍሮች ሴት ልጅ ሆይ፥ ጭፍሮችሽን አሁን ሰብስቢ ከብቦ አስጨንቆናል የእስራኤልን ፈራጅ ጕንጩን በበትር ይመታሉ፡፡ አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል፡፡” ትንቢተ ሚክያስ 5፡1-2
“እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል የምትወዱትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፦ ነገር ግን እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና የሚመጣበትን ቀን መታገሥ የሚችል ማን ነው? እርሱስ በተገለጠ ጊዜ የሚቆም ማን ነው? እርሱም ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፥ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፥ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቍርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ፡፡” ትንቢተ ሚልክያስ 3፡1-3
“አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ ለዘለዓለም ነው የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው፡፡ ጽድቅን ወደድህ ዓመፃንም ጠላህ ስለዚህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ እግዚአብሔር አምላክህ የደስታ ዘይትን ቀባህ፡፡” መዝሙረ ዳዊት 45
ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ነጥቦች አመክንዮአዊ በሆነ መንገድ ስናስቀምጣቸው እንደሚከተለው ይሆናል:-
- ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ትንቢት የተነገረለት መሲህ መሆኑን ተናግሯል
- በብሉይ ኪዳን ትንቢቶች መሠረት መሲሁ አምላክ ነው
- ስለዚህ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ይህ ቀላል ሲሎጂዝም (የአመክንዮአዊ አረፍተ ነገሮች ድርደራ) ኢየሱስ አምላክ መሆኑን እንደተናገረ በግልፅ ያሳያል፡፡
በሰማይ ደመና የሚመጣው “የሰው ልጅ” መሆኑን በመናገር:-
ኢየሱስ ክርስቶስ በተደጋጋሚ “የሰው ልጅ” የሚለውን ማዕርግ ሲጠቀም እናያለን (ማርቆስ 13፡23-27፣ 14፡60-64)፡፡
“የሰው ልጅ” የሚለውን ስያሜ ሚስጥር የምናገኘው በትንቢተ ዳንኤል 7፡13-14 ላይ ነው:-
“በሌሊት ራእይ አየሁ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ ወደ ፊቱም አቀረቡት፡፡ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው ግዛቱም የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፡፡”
በዚህ ጥቅስ መሠረት ይህ የሰው ልጅ የተባለው አካል ህዝቦችን ሁሉ የሚገዛ፤ የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት ያለው እና የማይጠፋ መንግሥት ያለው ነው፡፡ ከአምላክ በስተቀር ህዝቦች ሁሉ ሊገዙት የሚገባ እና ዘለዓለማዊ ግዛትና መንግሥት ሊኖረው የሚችል ማነው? ኢየሱስ “የሰው ልጅ” የሚለውን ማዕርግ መጠቀሙ ስጋ ለብሶ የመጣ አምላክ መሆኑን ለማሳየት እንደነበር ከዚህ ትንቢት እንረዳለን፡፡
አምላክ ብቻ ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን ነገሮች በማድረግ:-
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ኢየሱስ ኃጢዓትን ይቅር የማለት ችሎታ እንዳለው ማሳየቱ ነው (ማርቆስ 2፡1-12)፡፡
ከአምላክ በስተቀር ኃጢዓትን ይቅር ሊል የሚችል ማነው?
ለአብ የሚገባው ክብር ሁሉ ለእርሱም እንደሚገባ በመናገር:-
“ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም፡፡ ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም፡፡” (ዮሐንስ 5፡22-23)
አብን የምናከብረው እርሱን በማምለክ ነው፡፡ ኢየሱስንም አብን እንደምናከብረው ማክበር የምንችለው ለአብ የምንሰጠውን ክብር ሁሉ ስንሰጠው ነው፡፡
ወደ እርሱ እንድንጸልይ እና እርሱም ደግሞ የምንለምነውን በሙሉ እንደሚያደርግልን በመናገር:-
“እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ፡፡ ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ፡፡” (ዮሐንስ 14)፡፡
ኢየሱስ የሁሉን ሰው ጸሎት ለመስማት በሁሉም ስፍራ መገኘት እና ሁሉን ማወቅ መቻል አለበት፤ የምንለምነውን ሁሉ ለማድረግ ደግሞ ሁሉን ቻይ መሆን አለበት፡፡ ከአንዱ አምላክ በስተቀር ፀሎታችንን ሰምቶ የምንለምነውን ሁሉ ማድረግ የሚችል ማነው? ኢየሱስ ግን ይህንን ማድረግ እንደሚችል ነግሮናል ስለዚህ አምላክ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በሁሉም ስፍራ መገኘት እንደሚችል በመናገር:-
“ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል፡፡ ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና፡፡” (ማቴዎስ 18፡19-20)፡፡
“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡” (ማቴዎስ 28፡19-20)፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምንሰበሰብበት ስፍራ ሁሉ በመካከላችን መገኘት የሚችለው እና እስካለም ፍፃሜ ድረስ ከእኛ ጋር መሆን የሚችለው በሁሉም ስፍራ የመገኘት ችሎታ ካለው ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ይህን ማድረግ እንደሚችል መናገሩ በሌላ ቋንቋ አምላክ መሆኑን መናገሩ ነው፡፡
ሰዎች በስሙ የኃጢዓት ይቅርታን እንደሚያገኙ በመናገር:-
“በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል፡፡ እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ፡፡” የሉቃስ ወንጌል 24፡45-48
ከአምላክ ስም በስተቀር የኃጢዓትን ይቅርታ የሚያስገኝ ስም የማን ስም ነው?
በስሙ በሽተኞች እንደሚፈወሱና አጋንንት እንደሚወጡ በመናገርና አማኞች ይህንን ማድረግ እንዲችሉ ስልጣን በመስጠት:-
“ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ፥ የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም፤ እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ፡፡ ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ፡፡ እነርሱም ወጥተው በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፥ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፥ በሚከተሉትም ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር፡፡” የማርቆስ ወንጌል 16፡17-20
“ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት፡፡ እንዲህም አላቸው ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ፡፡ እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም፡፡ ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ፡፡” የሉቃስ ወንጌል 10፡17-20
አጋንንትን ማስወጣት የሚችልና በሽተኞችን መፈወስ የሚችል ከአምላክ ስም በስተቀር የማን ስም ሊሆን ይችላል? ሰዎች ይህንን ማድረግ እንዲችሉ ስልጣን መስጠት የሚችል ከአምላክ በስተቀር ማነው?
መላእክትን ማዘዝ እንደሚችል እና የእርሱ እንደሆኑ በመናገር:-
“ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ፡፡ በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ፡፡” (ማቴዎስ 24፡29-30)፡፡
ከአምላክ በስተቀር ቅዱሳን መላዕክትን እንደራሱ አገልጋዮች ማዘዝና መላክ የሚችል ማነው?
በመጨረሻው ቀን ሙታንን የሚያስነሳው እርሱ እንደሆነ በመናገር:-
“ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና፡፡ ከሰጠኝም ሁሉ አንድንስንኳ እንዳላጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው እንጂ የላከኝ የአብ ፈቃድ ይህ ነው፡፡ ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፡፡” (ዮሐንስ 6፡38-40)፡፡
ከአምላክ በስተቀር በፍርድ ቀን ሙታንን ማስነሳት የሚችል ማነው?
በመጨረሻው ቀን በሁሉም ላይ የመፍረድ ስልጣን ያለው እርሱ መሆኑን በመናገር:-
“የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፥ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል፡፡ ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፡፡ እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ፡፡ ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና፡፡ ጻድቃንም መልሰው ይሉታል፡፡ ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተንመቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን? ንጉሡም መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል፡፡ በዚያንጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል፡፡ እናንተርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘለዓለም እሳት ከእኔ ሂዱ፡፡ ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና …” (ማቴዎስ 25፡31-43)፡፡
“ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም፡፡ ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም፡፡” የዮሐንስ ወንጌል 5፡22-23
ከአምላክ በስተቀር በመጨረሻም ቀን በህያዋንና በሙታን የመፍረድ ሥልጣን ያለው ማነው?
የዘለዓለምን ሕይወት መስጠት እንደሚችል በመናገር:-
“በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘለዓለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም፡፡ የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም፡፡ እኔና አብ አንድ ነን፡፡ አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ፡፡” (ዮሐንስ 10፡27-31)፡፡
ከአምላክ በስተቀር የዘለዓለምን ሕይወት መስጠት የሚችል የለም!
ለአምላክ ብቻ የሚገባውን ስግደትና አምልኮን በመቀበል:-
“እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ፡፡ ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፥ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ፡፡ ኢየሱስም መልሶ፦ አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ፡፡ እርሱንም ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው፡፡” (ሉቃስ 17፡15-19)፡፡
“ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቁጥተው እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት፡፡ ኢየሱስም፦ እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው፡፡” (ማቴዎስ 21፡15-16)፡፡
እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ ውስጥ ክብሩን ለማንም እንደማይሰጥ በተደጋጋሚ ተናግሯል (ዘዳግም 5፡6-10፣ ኢሳይያስ 42፡8)፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሰዎችን ስግደትና ምስጋና ተቀብሏል፡፡ ለአምላክ ብቻ የሚገባውን ክብር በመውሰድ አምላክ መሆኑን አሳይቷል፡፡
ጌታ መሆኑን በመናገር:-
የሰዎች ጌታ መሆኑን:-
“እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ፡፡ እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል፡፡ እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና፡፡” (ዮሐንስ 13፡13-15)፡፡
የሰንበት ጌታ መሆኑን:-
“እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው አላቸው፡፡” የማርቆስ ወንጌል 2፡28
ብዙ ሙስሊሞች ኢየሱስ ጌትነቱን በግልፅ መናገሩን ስለማያውቁ “ጌታ ነኝ ያለበትን ቦታ አሳዩን” በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ነገር ግን ዮሐንስ 13፡13-15 ላይ የሚገኘውን ስናሳያቸው ትንሽ ደንገጥ በማለት ይቆዩና ሌላ ዘዴ ይፈጥራሉ፡፡ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰዎችም ጌታ ተብለዋል” ይላሉ፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ጌትነቱ ልክ ሐዋርያቱ የሚሉት ዓይነት ጌትነት መሆኑን ስለተናገረ ሐዋርያት በሚሉት ዓይነት መንገድ እንጂ በራሳችን መንገድ ልንተረጉመው አንችልም፡፡ በዚህ ርዕስ ስር በቀጣይነት እንደምንመለከተው ሐዋርያት የኢየሱስን አምላክነት ያምኑ ስለነበር “ጌታ” ሲሉት አምላክነቱን ለማመልከት እንጂ ከፍ ያለ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ጌታ በሚባሉበት መንገድ እየጠሩት አይደለም፡፡ ኢየሱስ ጌታ መሆኑን የተናገረበት ሌላው አጋጣሚ የሰንበት ጌታ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በማያሻማ ሁኔታ አምላክነቱን ያሳያል፤ ምክንያቱም ሰንበት ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ቀን መሆኑ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ተነግሯልና (ዘጸአት 31:12-17)፡፡ እግዚአብሔር ለራሱ በቀደሰው ቀን ላይ ጌታ መሆን የሚችል ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
በዮሐንስ ራዕይ ውስጥ የሚገኙ ማስረጃዎች
በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የሚገኙት የኢየሱስ ንግግሮች ወደሰማይ ካረገ በኋላ የተናገራቸው ናቸው
(1) ፊተኛውና ኋለኛው
“አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ፡፡” የዮሐንስ ራእይ 22፡13
“ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩበታች ወደቅሁ፡፡ ቀኝ እጁንም ጫነብኝ እንዲህም አለኝ፦ አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ፡፡” (ራእይ 1፡17-18)፡፡
የሚከተለው የብሉይ ኪዳን ጥቅስ ይህንን ንግግር መናገር የሚችለው አምላክ ብቻ መሆኑን ያሳያል:-
“የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም፡፡ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ይነሣና ይጥራ ይናገርም፤ ከጥንት የፈጠርሁትን ሕዝብ ያዘጋጅልኝ፥ የሚመጣውም ነገር ሳይደርስ ይንገሩኝ፡፡” (ኢሳይያስ 44፡6-7)፡፡
(2) ኵላሊትንና ልብን የሚመረምር
“አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ” (ራእይ 2፡23)፡፡
የሰዎችን የተሰወረ የውስጥ ሐሳብ መርምሮ ማወቅ የሚችለው ከአምላክ በስተቀር ማን ሊሆን ይችላል? የሚከተለው የብሉይ ኪዳን ጥቅስ ይህንን ንግግር መናገር የሚችለው አምላክ ብቻ መሆኑን ያሳያል:-
“እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ፡፡” (ኤርምያስ 17፡10)፡፡
(3) ለሁሉም እንደየስራው የሚከፍል
“እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ፡፡” (ራእይ 22፡12)፡፡
“ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ፡፡” (ራእይ 2፡23)፡፡
በመጨረሻው የፍርድ ቀን ለሁሉም ሰው እንደየስራው መክፈል የሚችል ከአምላክ በስተቀር ማን ሊሆን ይችላል?
(4) አምላክ ነኝ ብሏል
“በዙፋንም የተቀመጠው፡፡ እነሆ፥ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ፡፡ ለእኔም፤ እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ፡፡ አለኝም ተፈጽሞአል፡፡ አልፋና ዖሜጋ፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ፡፡ ለተጠማ ከሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ፡፡ ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፡፡” (ራእይ 21፡5-7)፡፡
በዚህ ጥቅስ መሠረት አልፋና ኦሜጋ ፊተኛውና መጨረሻ የሆነው እርሱ አምላክ መሆኑን ይናገራል፡፡ በራዕይ 22:12-13 ላይ ይህ አልፋና ኦሜጋ መጀመርያና መጨረሻ የሆነው በቶሎ እንደሚመጣ ይናገራል፡፡ ምዕራፍ 22፡20 ላይ ይህ በቶሎ የሚመጣው ራሱ ኢየሱስ እንደሆነ ተነግሮናል፡፡ ስለዚህ አልፋና ኦሜጋ የሆነው በቶሎ እንደሚመጣ የተናገረው በምዕራፍ 21:7-8 ላይ አምላክ መሆኑን የተናገረው ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
እግዚአብሔር አብ ስለ እርሱ ምን አለ?
ሙስሊም ወገኖች በቁርኣን ውስጥ የሚገኙትን የአላህ ንግግሮች እንደሆኑ የሚያምኗቸውን ቃላት ያለምንም ቅድመሁኔታ ይቀበላሉ፡፡ ለምሳሌ ዒሳ ከድንግል ነው የተወለደው የሚለውን ትልቅ እምነት የሚጠይቀውን ንግግር የተቀበሉት ዒሳ በቁርኣን ውስጥ “እኔ ከድንግል ነው የተወለድኩ” በማለት ስለተናገረ ሳይሆን አላህ ራሱ ዒሳ ከድንግል እንደተወለደ ስለተናገረ ነው፡፡ ዒሳ ከድንግል መወለዱን ለማመን ለእነርሱ በቁርኣን ውስጥ የተጻፈው የአላህ ንግግር ብቻ በቂ ከሆነ ለኛም ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ለመቀበል የእግዚአብሔር አብ ንግግር ብቻ በቂ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አብ ስለልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ምን ብሎ እንደተናገረ የዕብራውያን መልዕክት ጸሐፊ መዝሙረ ዳዊት ውስጥ የተጻፈውን ትንቢት በመጥቀስ የተናገረውን እንመልከት፡፡
“ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል፡፡ ከመላእክትስ፡፡ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥ ደግሞም፦ እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ፡፡ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል፡፡ ስለ መላእክትም፡፡ መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ ይላል፤ ስለ ልጁ ግን፡፡ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘለዓለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው፡፡ ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ ይላል፡፡ ደግሞ ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል፡፡ ነገር ግን ከመላእክት ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ከቶ ለማን ብሎአል? ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?” (ዕብራውያን 1፡4-14)፡፡
በዚህ ጥቅስ መሠረት እግዚአብሔር አብ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን መላእክት የሚሰግዱለት፣ ጌታ፣ አምላክ፣ ዘለዓለማዊ ዙፋን ያለው፣ የሰማያት ፈጣሪ፣ ወዘተ. በማለት ይጠራዋል፡፡ ይህ ለክርስቲያኖች ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ለመቀበል ብቻውን በቂ ማስረጃ ነው፡፡
ሐዋርያት ምን አሉ?
የኢየሱስ ሐዋርያት ከእርሱ ጋር አብረው ስለነበሩ ስለማንነቱ ከማንም በላይ ያውቃሉ ስለዚህ የእነርሱ ምስክርነት ለኢየሱስ አምላክነት ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡ ቀጥሎ እነዚህ ቅዱሳን ሰዎች ስለ እርሱ አምላክነት የተናገሯቸውን እንመለከታለን፡፡
ስምዖን ጴጥሮስ
“የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ የሆነ ስምዖን ጴጥሮስ፥ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ፤ የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ፡፡” (2ኛ ጴጥሮስ 1፡1-3)፡፡
የዘብዴዎስ ልጅ ዮሐንስ
“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፡፡ ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፡፡ ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም፡፡” (ዮሐንስ 1፡1-3)፡፡
“የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም ሕይወትነው፡፡” (1ኛ ዮሐንስ 5፡20)፡፡
ቶማስ
“ቶማስም ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት፡፡ ኢየሱስም፦ ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው፡፡” (ዮሐንስ 20፡28-29)፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ
ጌታ ኢየሱስን ፊትለፊት በማየቱ ምክንያትና ከሐዋርያት ጋር እንደማገልገሉ መጠን የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ምስክርነት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ እርሱስ ስለ ኢየሱስ አምላክነት ምን አለ?
“አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘለዓለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን፡፡” (ሮሜ 9፡5)፡፡
“ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፡፡” (ቲቶ ፡11-13)፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትን ማስረጃዎች ካጤነ በኋላ ኢየሱስ ስለ አምላክነቱ መናገሩንና መጽሐፍ ቅዱስ አምላክነቱን ማረጋገጡን የሚክድ ለህሊናው ያደረ ሰው ይኖራል የሚል ግምት የለንም፡፡