ማነው ወፍን የፈጠረው? ለአቡ ሀይደር ቅጥፈት የተሰጠ መልስ

ማነው ወፍን የፈጠረው?

ለአቡ ሀይደር ቅጥፈት የተሰጠ መልስ


ተከታዩ ጽሑፍ በኡስታዝ አቡ ሀይደር የተዘጋጀ ነው። በዚህ ጽሑፉ በቁርኣን መሠረት ክርስቶስ ወፍ አልፈጠረም ይለናል። ኡስታዙ እንደተለመደው በገዛ መጽሐፉ ውስጥ በግልፅ የተጻፈውን በመካድና አጣምሞ በመተርጎም እስልምናን የመታደግ ቀቢፀ ተስፋዊ ትግል አድርጓል። እኛም ደግሞ ከዚህ ቀደም ስናደርግ እንደነበረው ቅጥፈቱንና ክህደቱን ለማጋለጥ ብዕራችንን አንስተናል። እንዲህ ሲል ይጀምራል፦

አቡ ሀይደር

ሀሰት ሲደጋገም እውነት ይመስላል እንዲሉ ሆነና ከሰብአዊ ፍጡርነት እና ከነቢይነት ውጪ ምንም ድርሻ የሌለውን የመርየምን ልጅ ዒሳን (የአላህ ሰላም በሁለቱም ላይ ይሁን) አምላክ እና ፈጣሪ ለማድረግ የቅጥፈት ዘመቻዎች በየአቅጣጫው እየተደጋገሙ ነው። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ “ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ወፍን ፈጥሯል” የሚለው ተረት ተረት ነው። እንኳን ወፍን ሊፈጥር ይቅርና ፍጥረተ ዓለሙ እራሱ ቢተባበረውና ቢያግዘው ዝንብ መፍጠር እንኳ አይችልም። ይህ የጌታችን ቃል ነው እንዲህ ይላል።

እናንተ ሰዎች ሆይ! አስደናቂ ምሳሌ ተገለጸላችሁ። ለእርሱም አድምጡት። እነዚያ ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸው (ጣዖታት) ዝምብን ፈጽሞ አይፈጥሩም። እርሱን (ለመፍጠር) ቢሰበስቡም እንኳ (አይችሉም)። አንዳችንም ነገር ዝንቡ ቢነጥቃቸው ከእርሱ አያስጥሉትም። ፈላጊውም ተፈላጊውም ደከሙ (ደካሞች ናቸው)። ሱረቱል ሐጅ 22፡73

መልስ

ኡስታዙ ዒሳ ወፍ ፈጥሯል የሚለው የቁርኣን ትረካ ተረት ተረት መሆኑን በመግለጹ አልተሳሳተም። የቁርኣን ደራሲ ትረካውን የወሰደው የቶማስ ወንጌል ከተሰኘ የአፖክሪፋ መጽሐፍ ላይ ነው። ይህንን በማድረጉ የቁርኣን ደራሲ ሁለት ስህተቶችን ፈጽሟል። የመጀመርያው ስህተቱ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈ የታወቀ ተረት ከሰማይ የመጣለት መገለጥ በማስመሰል ማቅረቡ ነው። የሙስሊሞች ተወዳጅ የክርስትና ተቃዋሚ የሆነው ባርት ኤህርማን መጽሐፉ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ የተጻፈ መሆኑ ጥርጥር እንደሌለው ተናግሯል (Bart D. Ehrman. Lost Scriptures፡ Books that Did Not Make it into the New Testament. Oxford University Press, 2003, p. 20)። ሁለተኛ ደግሞ የተረቱን ዓላማና ትርጉም ሳያውቅ መውሰዱ ነው። የቶማስ ወንጌል ደራሲ የኢየሱስን አምላክነት ስለሚያምን ከጭቃ ወፎችን መፍጠሩን ለአምላክነቱ እንደ ማሳያ ነው የጠቀሰው። ትረካውን ሲጀምር “ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገው ተዓምር…” በማለት ነው። (The Second Gospel of the Infancy of Jesus Christ: Chapter 1:1-10)። በማስከተል እንደምንመለከተው የቁርኣን ደራሲ ተረቱ የክርስቶስን አምላክነት የሚያሳይና የእርሱን አስተምህሮ የሚያፈርስበት መሆኑን አልተገነዘበም። በአረብ ክርስቲያኖች ዘንድ የታወቀውን የአዋልድ መጽሐፍ ተረት እንዳለ በመውሰዱ ምክንያት የገዛ አስተምህሮውን አፍርሷል፤ ሙስሊሞችንም በቂ ማብራርያ በሌለበት ጉዳዩን የማብራራት ዕዳ እንዲሸከሙ አድርጓቸዋል።

ሙስሊሙ ሰባኪ ሱራ 22፡73 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የዒሳን ፈጣሪነት ለማስተባበል መጠቀሙ በቁርኣን ውስጥ የሚገኝን አንድ ለመፍታት የሚቸግር ግጭት ያስከትላል። ሱራ 21፡98 ላይ “እናንተ፣ ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸውም (ጣዖታት) የገሃነም ማገዶዎች ናችሁ፤ እናንተ ለርሷ ወራጆች ናችሁ” ተብሏል። ሰዎች የሚያምልኳቸው ነገሮች ከአምላኪዎቻቸው ጋር በገሃነም የሚቃጠሉ ከሆነ፤ ከእነዚህ ተመላኪዎች መካከል አንዱ ዒሳ ከሆነና ሙስሊሙ ሰባኪ በጠቀሰው ጥቅስ መሠረት ዒሳ ከጣዖታት መደብ ከሆነ በገሃነም ሊቃጠል ነው ማለት ነው። ይህ ደግሞ ዒሳ በአላህ ዘንድ የተመረጠ ነቢይ መሆኑን ከሚናገረው የቁርኣን አንቀጽ ጋር ይጋጫል።

አቡ ሀይደር

ታዲያ ከምን ተነስተው ነው ዒሳን ወፍ እንደፈጠረ ለማሳመን የሚኳትኑት ከተባለም ቀጣዩን ማስረጃ ይሆነናል ያሉትን ጥቅስ እናቅርበውና ምላሹን አብረን እንከታተል፡-

ወደ እሥራኤልም ልጆች መልዕክተኛ ያደርገዋል። (ይላልም) ፡-እኔ ከጌታዬ ዘንድ በተዓምር ወደ እናንተ መጣሁ። እኔ ለእናንተ ከጭቃ አንደ ወፍ ቅርጽ እፈጥራለሁ። በእርሱም እተነፍስበታለሁ። በአላህም ፈቃድ ወፍ ይሆናል። በአላህም ፈቃድ ዕውር ሆኖ የተወለደን፤ ለምጸኛንም አድናለሁ። ሙታንንም አስነሳለሁ። የምትበሉትንና በቤታችሁ የምታደልቡትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ። የምታምኑ እንደሆናችሁ ለእናንተ በዚህ ውስጥ በእርግጥ ተዓምር አለበት። ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡49

እስኪ መጠነኛ ማብራሪውን አብረን እንከታተል።

ሀ. “ወደ እሥራኤልም ልጆች መልዕክተኛ ያደርገዋል።”

ይህ የሚያስረዳን ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) መልዕክተኛ መሆኑንና የተላከውም ወደ ቤተ እስራኤል ብቻ እንደሆነ ነው። ከዚህ መልዕክተኝነት ውጪ ሌላ ሚና የለውም። በሌላም አንቀጽ ላይ እንደተነገረው የእሱ መልዕክተኝነት እንዳለፉት መልዕክተኞች የሆነ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ሲናገር እንዲህ ይላል፡-

የመርየም ልጅ አልመሲሕ ከበፊቱ መልዕክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆነ መልዕክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም። እናቱም በጣም እውነተኛ ናት። (ሁለቱም) ምግብን የሚበሉ ነበሩ። አንቀጾችን ለእነርሱ (ለከሐዲዎች) እንዴት እንደምናብራራ ተመልከት። ከዚያም (ከእውነት) እንዴት እንደሚመለሱ ተመልከት። ሱረቱል ማኢዳህ 5፡75

መልስ

በመጀመርያ ደረጃ ቁርኣን ዒሳ የተላከው ወደ እስራኤል ብቻ ነው አይልም። ዒሳ ጊዜያዊ ተልዕኮው ለእስራኤላውያን ቢሆንም ለመላው ዓለም የተላከ ምልክት መሆኑ ተነግሯል። “ያችንም ብልቷን የጠበቀቺውን በርሷም ውስጥ ከመንፈሳችን የነፋንባትን እርሷንም ልጅዋንም (እንደዚሁ) ለዓለማት ተዓምር ያደረግናትን (መርየምን አስታውስ)።” (ሱራ 21፡91)

ይህ የቁርኣን ጥቅሰ ማርያምና ልጇ ለዓለማት ተዓምር መሆናቸውን ይናገራል። ዓለም አቀፋዊ አስፈላጊነት የሌለው አካል ለመላው ዓለም ምልክት ሊሆን እንዴት ይችላል? እስላማዊ መጻሕፍት ይህንን ሐቅ በማጠናከር ክርስቶስ ሐዋርያቱን ወደ መላው ዓለም መላኩን ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል ቀዳሚውን የሙሐመድ ግለ ታሪክ የመዘገበው ኢብን ኢስሐቅ የክርስቶስ ሐዋርያት የተላኩባቸውን ሕዝቦች ቋንቋዎች ሁሉ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ እየተናገሩ ማስተማራቸውን፣ ጳውሎስና ጴጥሮስን በስም በመጥቀስ ወደ ሮም እንደተላኩ እንዲሁም በርቶሎሜዎስ ወደ አረብያ እንደተላከ ጽፏል (The Life of Muhammad: A Translation of Ibn Ishaq’s Sirat Rasul Allah, by Alfred Guillaume, p. 653)። አል-ጃለላይን እና ኢብን አባስ በተፍሲራቸው ወደ አንፆኪያ ስለተላኩ ሦስት የክርስቶስ መልእክተኞች ጽፈዋል https://quranx.com/Tafsirs/36.13 ። ኢብን ከሢር ደግሞ ሦስቱ መልእክተኞች ስምዖን፣ ዮሐንስና ጳውሎስ መሆናቸውን ጠቅሷል (Tafsir Ibn Kathir (Abridged), Volume 8, Surat Yasin (36) Verse 14 to 15)። አጥ-ጠበሪም በተመሳሳይ ጳውሎስና ጴጥሮስ ወደ ሮም፣ ቶማስ ወደ ባቢሎን፣ ዮሐንስ ወደ ኤፌሶን፣ በርቶሎሜዎስ ወደ ሂጃዝ፣ ስምዖን ወደ ሰሜን አፍሪካ እንደተላኩ ጽፏል (Tabari, History, Volume IV, p. 123)። እነዚህ ዘገባዎች ከመጽሐፍ ቅዱስና ከክርስትና ታሪኮች ጋር ይስማማሉ ስለዚህ ሐዋርያት ዓለም አቀፋዊ ድንበሮችን ተሻግረው ወደ ሌሎች ሕዝቦች እንደተላኩ እስላማዊ ምንጮች እስከተናገሩ ድረስ ሙስሊሞች የክርስቶስን ተልዕኮ በአንድ ሕዝብ መወሰን አይችሉም። ቁርኣንና ሐዲስን ስንመለከት ሙሐመድ ከአሕዛብ ወገን የሆኑና ክርስቲያኖች የሆኑ ሕዝቦችን “የኢንጂል ሰዎች” “የመጽሐፉ ሰዎች” በማለት የክርስቶስ ተከታዮች መሆናቸውን ዕውቅና በመስጠት ይጠቅሳቸዋል። ክርስቶስ ለአይሁድ ብቻ ቢሆን ኖሮ አላህ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑት ተከታዮቹ ዕውቅናን ባልሰጠ ነበር።

ሌላው እኛ ክርስቲያኖች የዒሳ ወፍን መፍጠር ለአምላክነቱ ማስረጃ ነው የምንለው ታሪኩ ራሱን በቻለ ሁኔታ አምላክነቱን ያሳያል ከሚል አቋም አኳያ እንጂ ቁርኣን የዒሳን አምላክነት አይክድም ከሚል አቋም አኳያ አይደለም። የኛ አቋም ቁርኣን የዒሳን አምላክነት የሚክድ ሆኖ ሳለ የአምላክነቱ ማስረጃ ሊሆን የሚችል የተኮረጀ ትረካ በውስጡ ይዞ ተገኝቷል የሚል ነው። ይህም በሁለት መንገድ የሙሐመድን ሐሰተኛነት ይገልጣል። አንደኛ የተኮረጀ ትረካ ከሰማይ መጣልኝ በማለቱ እና ሁለተኛ እርስ በርሱ የሚጋጭ ትምህርት በማስተማሩ። የክርስቶስን አምላክነት የሚክዱት ሙስሊም ወገኖቻችን የገዛ መጽሐፋቸው የክርስቶስን አምላክነት ስለሚመሰክር አቋማቸውን መመርመር ግድ ይላቸዋል።

አቡ ሀይደር

ለ. “እኔ ከጌታዬ ዘንድ በተዓምር ወደ እናንተ መጣሁ።”

በማለት አላህ የዒሳ ጌታው እና አምላኩ የላከው እንደሆነ መስክሯል። ተዓምርንም ያመጣው ከእሱ ዘንድ እንጂ ከራሱ እንዳልሆነም አብሮ ገልጿል። በአምስት የቁርኣን አንቀጾች ላይ አላህ የእሱም የህዝቦቹም ጌታ እንደሆነና እሱ ብቻ መመለክ እንዳለበት አስተምሯል፡-

እነዚያ “አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው” ያሉ በእርግጥ ካዱ። አልመሲሕም አለ “የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ።” እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በእርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ። መኖሪያውም እሳት ናት። ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም። ሱረቱል ማኢዳህ 5፡72

መልስ

በመጀመርያ ደረጃ እየተመለከትነው ባለነው ሱራ 3፡49 ላይ ዒሳ “ጌታዬ” የሚል ቃል አልተናገረም። ይህ የአማርኛ ተርጓሚዎች የተጭበረበረ ትርጉም ነው። በዚህ ቦታ የተጠቀሰው رَبِّكُمْ “ረቢኩም” የሚል የአረብኛ ቃል ሲሆን ትርጉሙም “ጌታችሁ” ማለት ነው። በአረብኛ “ጌታዬ” ለማለት رَبِّي “ረቢ” እንላለን እንጂ “ረቢኩም” አንልም። ለምሳሌ ያህል ሱራ 5፡72 ላይ የቁርኣን ደራሲ የዒሳን አምላክነት ለመካድ ሲፈልግ ዒሳ አላህን “ረቢ” ብሎ እንደጠራው ተናግሯል። አቡ ሀይደር አረብኛ እችላለሁ እያለ በተሳሳተ ትርጉም ላይ ሙግቱን መመሥረት አልነበረበትም። ይሁን እንኳ ብንል አላህ በቁርኣን ውስጥ አምላክነቱን ከማንም ጋር እንደማይጋራ ከተናገረ በኋላ ለዒሳ የአምላክ የብቻው ሥልጣን የሆነውን ሕይወትን የመፍጠር ችሎታን እንዴት እንዳጋራው ማብራራት እንጂ የዒሳን አምላክነት የሚክዱ ነጥቦችን መጥቀስ ቁርኣን እርስ በርሱ እንደሚጋጭ ከማሳየት የዘለለ ፋይዳ የለውም። ክርስቶስ በሥጋው አብን “አምላኬ” ያለባቸው ክፍሎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከመገኘታቸው አንጻር ዒሳ አላህን ጌታዬ ብሎ መጥራቱ ከክርስትና አስተምህሮ ጋር ግጭት እንደማይፈጥር ሊታወቅ ይገባል። የቁራኑን ታሪክ በጥንቃቄ ስንመረምር ዒሳ ተዓምር ከመሥራት ያለፈ ተግባር ነው የፈጸመው። አምላክ ከማንም ጋር የማይጋራውን ሕይወትን የመፍጠር አምላካዊ ሥራ ሲሠራ ነው የምንመለከተው።

አቡ ሀይደር

ሐ. “እኔ ለእናንተ ከጭቃ አንደ ወፍ ቅርጽ እፈጥራለሁ።”

ቁም ነገሩ እዚህ ጋር ነው ያለው። አማርኛ ማንበብን ለቻለ ሰው አንቀጹ የሚናገረው ስለ ወፍ ቅርጽ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ለመረዳት አያዳግተውም። ዒሳ ከጭቃ “እንደ ወፍ ቅርጽ” እፈጥራለሁ አለ እንጂ፤ መች ወፍ እፈጥራለሁ አለ? ጭቃ አምጥቶ የወፍ ቅርጽ መፍጠር ማንም ሰው ሊያደርገው የሚችል ቀላል ተግባር ነው። ቁም ነገሩ በወፍ ቅርጽ በተሰራው ጭቃ ላይ ህይወትን ዘርቶ የእውነት ወፍ እንዲሆን በማድረግ እንዲበር ማስቻሉ ነው። ታዲያ ዒሳ ይህን አላደረገም ወይ? ከተባለም አንቀጹ ይቀጥልና፡-

መልስ

በቁርኣን መሠረት ይህ የአፈጣጠር መንገድ አላህ አዳምን ከአፈር አበጅቶት የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ካለበት ጋር ተመሳሳይ ነው፡-

“ጌታህ «ለመላእክት እኔ ሰውን ከጭቃ ፈጣሪ ነኝ ባለ ጊዜ» (አስታውስ)።«ፍጥረቱንም ባስተካከልኩና ከመንፈሴ በነፋሁበት ጊዜ ለእርሱ ሰጋጆች ኾናችሁ ውደቁ» (አልኩ)።” (ሱራ 38፡71-75)

በአረብኛ ስናነበው አላህ አዳምን ሲፈጥር የፈጸመው ተግባርና ዒሳ ወፍ ሲፈጥር የፈጸመው ተግባር በእጅጉ ይመሳሰላል። አላህ አዳምን መፍጠሩን ለማሳየት “ኢንኒ ኻሊቁን በሸረን ሚን ጢኒን” (እኔ … ከጭቃ ፈጣሪ ነኝ) በማለት ነው የተናገረው (ሱራ 38፡71-72)። በተመሳሳይ ዒሳ ወፍ መፍጠሩን ለማሳየት “አንኒ አኽሉቁ ለኩም ሚነ አል-ጢኒ” (እኔ ለናንተ ከጭቃ … እፈጥራለሁ) ብሏል (ሱራ 3፡49)። በማስከተል ደግሞ ልክ አላህ ከጭቃ በሠራው የሰው ቅርፅ ላይ በመተንፈስ ሕያው እንዳደረገው ሁሉ ዒሳም በሠራው የወፍ ቅርፅ ላይ በመተንፈስ ሕያው አድርጓል። ዒሳ በፈጠረው የወፍ ቅርጽ ላይ እፍ በማለት ሕያው ማድረጉ ፈጣሪነት አይደለም ከተባለ አላህም በፈጠረው የሰው ቅርጽ ላይ እፍ በማለት ሕያው ማድረጉ ፈጣሪነት አይደለም ሊባል ነው?

አቡ ሀይደር

መ. “በእርሱም እተነፍስበታለሁ፤ በአላህም ፈቃድ ወፍ ይሆናል።”

በማለት ወፍ አድራጊው የጌታ አላህ ፈቃድና ኃይል እንጂ የዒሳ ችሎታ እንዳልነበር ያሳያል። የታለ ታዲያ ዒሳ ወፍ ፈጠረ የሚለው? የአላህ ፈቃድ ባይኖር ኖሮ ጭቃው ጭቃ እንደሆነ ይቀር ነበር እንጂ መች ወፍ ሆኖ ይበር ነበር? ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ጭቃውን አምጥቶ የወፍ ቅርጽ የሰራው እንኳ በራሱ ፍላጎት ሳይሆን በጌታው አላህ ፈቃድ እንደሆነ ቅዱስ ቁርኣን በሱረቱል ማኢዳህ ቁጥር 110 ላይ ይናገራል።

መልስ

“ኃይል” የሚል ቃል በዚህ ጥቅስ ውስጥ የት አል? ወፊቷን ሕይወት የዘራባት ኃይል የወጣው ከዒሳ እንጂ ከአላህ አይደለም። ዒሳ ራሱ ነው ተንፍሶባት ሕይወትን የዘራባት። ዒሳ የወፍ ቅርፅ ከጭቃ ሠርቶ እፍ በማለት ሕያው እንዲሆን እንዳደረገ እያነበበ ሙስሊሙ ሰባኪ “የታለ ታዲያ ዒሳ ወፍ ፈጠረ የሚለው?” በማለት መጠየቁ አስቂኝ ነው። ዒሳ በአላህ ፈቃድ ይህንን አደረገ መባሉ የመፍጠር ኃይል አለው ከሚለው ሐሳብ ጋር የሚጋጭ አይደለም። ከዚህ ቀደም ለሌላ ሙስሊም ሰባኪ በሰጠነው ምላሽ እንደገለፅነው ቁርኣን ውስጥ ዒሳ በአላህ ፈቃድ መሠረት ይህንን እንደፈፀመ ቢነገርም ዳሩ ግን መፍጠር ፈጣሪ ከማንም ጋር የማይጋራው መለያው በመሆኑ ምክንያት ይህ የዒሳን አምላክነት ውድቅ አያደርግም። ፈጣሪ ይህንን ችሎታ ለዒሳ ካጋራው ዒሳ የፈጣሪን ልዩ ችሎታ ተጋርቷል ማለት ነው። ፈጣሪ ይህንን ችሎታ ለሌሎች የሚያጋራ ከሆነ ደግሞ ልዩ መሆኑ ይቀራል። ስለዚህ “በአላህ ፈቃድ” የሚለው ሐረግ የቁርኣን ደራሲ እንደ ተምታታበት ከማሳየት በዘለለ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም።  በጥቅሱ መሠረት ዒሳ ፈጣሪ ነው። ሌላው ክርስቲያኖች የኢየሱስን አምላክነት ቢያምኑም የሥላሴ አካላት ተነጣጥለው ሳይሆን ፍፁማዊ በሆነ አንድነት እንደሚሠሩ ስለሚያምኑ ኢየሱስ በአብ ፈቃድ እንደሚሠራ መነገሩ ከእምነታቸው ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። ኢየሱስ የመፍጠር መለኮታዊ ሥልጣን አለው ነገር ግን የሚፈጥረው በአባቱ ፈቃድ መሠረት ነው። ይህ ክርስቲያናዊ አስተምህሮን የሚደግፍ እንጂ የሚቃወም አይደለም። ሙስሊሞች ሊያስቡበት የሚገባው ጉዳይ ፈጣሪ ሕይወትን የመፍጠር ልዩ ችሎታውን ለፍጡራን ያጋራል ወይ? የሚል ነው።

አቡ ሀይደር

ሠ. “በአላህም ፈቃድ ዕዉር ሆኖ የተወለደን፤ ለምጸኛንም፤ አድናለሁ። ሙታንንም አስነሳለሁ።”

እነዚህም ተአምራት የተከናወኑት አሁንም በአላህ ፈቃድ እንጂ በዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ችሎታ አይደለም።

መልስ

ቀደም ሲል ከተነሳው ሐሳብ ጋር ተመሳሳይ ነው። ዒሳ በአላህ ፈቃድ እነዚህን ነገሮች ማድረጉ እነዚህን ነገሮች የማድረግ ኃይል እንደሌለው አያሳይም። በቁርኣን መሠረት ዒሳ ራሱ የአላህ ቃልና መንፈስ በመሆኑ ምክንያት የአላህ ኃይል ሁሉ የእርሱም ነው። የአላህ ቃልና መንፈስ አላህ እንደፈቀደው ይሠራል እንጂ በየጊዜው ከአላህ ኃይል መቀበል አያስፈልገውም። ራሱ የአላህ ኃይል ነውና! ለበለጠ መረጃ ተከታዮቹን  ጽሑፎች ያንብቡ

አቡ ሀይደር

ረ. “የምትበሉትንና በቤታችሁ የምታደልቡትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ።”

አንዳንድ ወገኖች ይህን ሀሳብ ይዘው ‘ዒሳ ሁሉን እንደሚያውቅ ቁርኣን መሰከረ’ ይሉናል። ሰዎቹ የሚበሉትንና በቤታቸው ያከማቹትን መናገር ሁሉን ማወቅ ሆነ በቃ? ይህ ዕውቀት በጊዜም፣ በቦታም፣ በአይነትም የተገደበ ዕውቀት እንጂ ሁሉን የማወቅ ስልጣን አይደለም። እንዴት የሚሉ ከሆነም፡-

ከጊዜ አንጻር፡- ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) እየተናገረ ያለው በእርሱ ዘመን ስለነበሩት ህዝቦቹ እንጂ ከእሱ በፊት ስላለፉት ወይም ወደፊት ስለሚመጡት ትውልዶች አይደለም። በወቅቱ የነበረውን ብቻ የሚመለከት ነው።

ከቦታ አንጻር፡- ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) እየተናገረ ያለው ነቢይ ሆኖ በተላከበት አካባቢ ለነበሩት እስራኤላውያን እንጂ በሌላ አካባቢ ስላሉት ህዝቦች አይደለም። አሁንም ዕውቀቱ ከቦታ አንጻር ግድብ ነው።

ከአይነት አንጻር፡- ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) እነግራችኋለሁ በማለት እየተናገረ ያለው ስለ መብላቸው ብቻ ነው። ከዛ ውጪ ስለሌላ ነገር አልተናገረም። ታዲያ በምን መልኩ ነው ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ሁሉን ያውቃል ብለን ድምዳሜ የምንሰጠው?

መልስ

በርግጥ ሰዎች የሚበሉትንና በቤታቸው የሚያከማቹትን ኃብት ማወቅ ነቢይ ለተባለ ሰው ቀላሉ ጉዳይ በመሆኑ ይህንን ለዒሳ ሁሉን አዋቂነት እንደ ማስረጃ መጥቀስ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። ነገር ግን ለዒሳ ሁሉን አዋቂነት ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል በቁርኣን ውስጥ የሚገኝ ሐሳብ ዒሳ የአላህ ቃልና መንፈስ እንደሆነ መነገሩ ነው። ለዚህ ደግሞ ማስተባበያ ያለው ሙስሊም የለም!

አቡ ሀይደር

ሰ. “የምታምኑ እንደሆናችሁ ለእናንተ በዚህ ዉስጥ በእርግጥ ታምር አለበት።”

በማለት አንቀጹ ይጠናቀቃል። እኛም ምላሻችን፡- አዎ አምነናል! የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! አንተ ከአላህ ዘንድ በተአምራት የተላክህ የእሱ መልዕክተኛ እንደሆንክ አምነን ተቀብለናል፤ ደግሞም መስክረናል። አምላክ ግን አልነበርክም፣ አይደለህምም፤ ወደፊትም አትሆንም።

መልስ

ዒሳ በጊዜም በቦታም የተገደበ መሆኑን ኡስታዙ ካመነ ስለምን ዒሳ በሌለበት ይናገረዋል? ይህ ዒሳን በሁሉ ቦታ ተገኝቶ ንግግሩን መስማት የሚችል መንፈስ  አያደርገውምን? ሙሐመድም የተምታታበት ልክ እንደዚሁ ነበር። የዒሳን አምላክነት ክዶ ሳለ ነገር ግን የአምላክ የብቻው የሆነው ሕይወትን የመፍጠር ችሎታ እንዳለው መስክሮ አረፈው!

አቡ ሀይደር

ሸ. ወገኖች ሆይ! ኢየሱስ ተአምራትን በራሱ ኃይል ማድረግ እንደማይችል የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የት አድርጋችሁት ነው በእኛ ቅዱስ ቁርኣን ላይ የምትከራከሩን?

ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። የማቴዎስ ወንጌል 28፡18

ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ከሆነ በሰማይና በምድር ያሉ ስልጣኖችን ከማን ነው የተቀበለው? አምላክ ይሰጣል ወይንስ ይቀበላል?

መልስ

ይህ ጥያቄ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ምላሽ የሰጠንበት ነው። አሕመዲን ጀበል ለተባለ ሌላ ሙስሊም ሰባኪ ምላሽ እንደሰጠነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን ለአባቱ ታዝዞ በገዛ ፈቃዱ ትቶት የመጣውንና መለኮታዊ መብቱ የሆነውን ሥልጣን መልሶ ተቀበለ እንጂ የእርሱ ያልሆነውን ስላልተቀበለ ይህ አባባል አምላክነቱን አጠራጣሪ ለማድረግ ምክንያት አይኾንም።

ጠያቂው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣንን ከአብ መቀበሉን የሚናገረውን ቃል ብቻ ነጥሎ ጠቀሰ እንጂ ሙሉ አውዱን ቢያነብ ኖሮ የኢየሱስን አምላክነት አሻሚ ባልሆነ ሁኔታ በተመለከተ ነበር። እስኪ በክፍሉ አውድ ውስጥ የሚገኙትን ደምቀው የተጸፉትን ቃላት ልብ ብለን እንመልከት፡-

“አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፥ ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ የተጠራጠሩ ግን ነበሩ። ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ሥልጣን በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ኹሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ኹሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ 28፡16-20)።

በዚህ ቦታ ላይ ሐዋርያት ለኢየሱስ ሰግደዋል። የጠያቂው ሃይማኖት አጥብቆ እንደሚያስተምረው ኢየሱስ ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ሌሎች ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት እንዳደረጉት ሐዋርያቱ እንዳይሰግዱለት በነገራቸው ነበር (ሐዋ. 10፡25-26፣ ራዕ 22፡8-9)። ነገር ግን ኢየሱስ አንድም ጊዜ ያንን አድርጎ አያውቅም። ኢየሱስ በሰማይና በምድር ሥልጣን እንደተሰጠው ተናግሯል። የእግዚአብሔር አንድያ ልጅና ወራሽ ባይኾን ኖሮ አብ እንዴት በሰማይና በምድር ሥልጣንን ይሰጠው ነበር? የጥምቀቱ ደግሞ ከሁሉም በላቀ ሁኔታ አምላክነቱን ይገልጣል። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የእግዚአብሔር ስም ባሕርዩን ይወክላል (ዘጸ 33፡17-23፣ 34፡5-7)። የእግዚአብሔርን ስም ማመስገን ማለት እግዚአብሔርን ማመስገን ማለት ነው (መዝ 7፡17)። የእግዚአብሔር ስም ረዳታችን እንደሆነ መናገር እግዚአብሔር ረዳታችን እንደሆነ መናገር ነው (መዝ. 124፡8፣ 121፡2)። በእግዚአብሔር ስም መምጣት ማለት በእግዚአብሔር ኃይል መምጣት ማለት ነው (1ሳሙኤል 17፡45፣ ዮሐንስ 5፡43)። ስለዚህ እግዚአብሔርና ስሙ አይነጣጠሉም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀት የገዛ ስሙ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ እኩል እንዲጠቀስ በማዘዝ አንድ ስም እንዳላቸው ግልፅ አድርጓል። ይህም ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በባሕርይም ሆነ በአገዛዝ አንድ መሆኑን ያሳያል። ማንም ፍጡር እንዲህ ዓይነት ነገር ቢናገር በእውነተኛው አምላክ ላይ ክህደትን መፈፀም በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም። አሁንም በዚሁ ስፍራ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደሚሆን በመናገር በሁሉም ቦታ መገኘቱን አስታውቋል። በእርግጥ በሁሉ ቦታ መገኘት መቻሉን ሲናገር ይህ ለመጀመርያ ጊዜ አይደለም (ማቴ 18፡20 ይመልከቱ)። ማንም ሰው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥልጣን ከአብ መቀበል በዚህ አውድ ውስጥ በማንበብ መረዳት ያስፈልገዋል እንጂ ከአውዱ ገንጥሎ በማውጣት የተለየ ትርጉም መስጠት የለበትም።

አቡ ሀይደር

እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና። ዮሀንስ ወንጌል 5፡30

አንዳችንም ነገር ከራሱ ማድረግ የማይችል አካል እንዴት ብዬ ነው አምላክ አድርጌ የምይዘው? ደግሞስ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻም እያለ እንዴት ብዬ ነው መልዕክተኛ ነህ የማልለው? አዎ! እሱ መልዕክተኛ ብቻ ነው። ወገኖች ሆይ! ለነገው ዓለም የሚያዋጣችሁ አንዱንና እውነተኛውን አምላክ አላህን በማምለክ፤ ለእናንተም ጭምር ነቢይና መልዕክተኛ አድርጎ በላካቸው ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ስታምኑ ብቻ ነው። መልካም ይሆንላችሁ ዘንድ ካሰባችሁ። እሱም እንዲህ ይላል፡-

…የመጽሐፉም ሰዎች ባመኑ ኖሮ ለእነርሱ የተሻለ በሆነ ነበር። ከእነርሱ አማኞች አሉ። አብዛኞቻቸዉ ግን አመጸኞች ናቸው። ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡110

መልስ

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አምላክ መሆኑን ባያቆምም ነገር ግን አምላካዊ ሥልጣኑን በመገደብ እንደ አገልጋይ ተመላልሷል፦

እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።(ፊልጵስዩስ 2፡68)።

ስለዚህ ጌታችን ከራሱ አንዳች ማድረግ እንደማይቻለው መናገሩ በገዛ ፈቃዱ መለኮታዊ ሥልጣኑን በመተው የተመላለሰበትን ሰብዓዊ ባሕርዩን የተመለከተ ነው።

አቡ ሀይደር

በአላህ አምላክነት፤ በቅዱስ ቁርኣን የአምላክ ቃልነት፤ በነቢዩ ሙሐመድ ነቢይነት የካደና በዛው ክህደቱ የሞተ ሰው ጀነት ለእሱ እርም ናት።

እነዚያ አንቀጾቻችንን ያስተባበሉ ከእርሷም የኮሩ ለእነርሱ የሰማይ ደጃፎች አይከፈቱላቸውም፤ ግመል በመርፌ ቀዳዳ እስከሚገባ ድረስ ገነትን አይገቡም። እንደዚሁም አጋሪዎችን እንቀጣለን። ሱረቱል አዕራፍ 7፡40

መልስ

ሙሐመድ ለነቢይነት የሚያበቃ አንዳች ነገር የሌለው ሐሰተኛ ነቢይ እንጂ እውነተኛ የእግዚአብሔር መልእክተኛ አይደለም። በሚስቱ በኸዲጃና ወረቃ በተባለው አጎቷ ገፋፊነት ነቢይ መሆኑን ተቀበለ እንጂ በዋሻው ውስጥ የተገለጠለት አፍኖ ያስጨነቀው አካል መልአክ መሆኑን እንኳ እርግጠኛ አልነበረም። ሥነምግባሩንም ስንመለከት ለነቢይነት የሚያበቃ አንዳች ነገር አልነበረውም። የስድስት ዓመት ህፃን አጭቶ በዘጠኝ አመቷ አብሯት ተኝቷል። የማደጎ ልጁን ሚስት ቀምቶ አግብቷል። ብዙ ንፁሃን ሰዎችን አሳቃቂ በሆነ ሁኔታ ሲገድል ነበር። ዘራፊ ነበር። የገዛ ወታደሮቹ ምርኮኛ ሴቶችን ባሎቻቸው በሕይወት እያሉ ጭምር እንዲደፍሩ ፈቃድ ሲሰጥ ነበር። የሰዎችን እጅና እግር በመቁረጥ፣ ዓይናቸውን በጋለ ብረት በማጥፋት፣ እንዲሁም እሳት ደረታቸው ላይ በማስቀመጥ ያሰቃይ ነበር። ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል። ሙሐመድ እውነተኛ ነቢይ ነው ብሎ ማለት በእውነተኛው አምላክ ላይ መሣለቅ ነው። ማስረጃዎቹን በተከታዮቹ ሊንኮች ውስጥ ታገኛላችሁ።

ለሙስሊም ወገኖቻችን የምናቀርብላቸው ጥሪ ቅዱስ በሆነው የእግዚአብሔር ልጅ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ነው። እርሱ ኃጢአት የሌለበት ፍጹም ጻድቅ ነው። እስልምና እንኳ ይህንን ይመሰክራል። መጽሐፍ ቅዱሳችን እንዲህ ይላል፦

“መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” (የሐዋርያት ሥራ 4፡12)

“ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” (ዮሐንስ 14፡6)

እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲሉ ይመሰክራሉ፦

“እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን።” (1 ዮሐንስ 4፡14)


የቁርኣን ግጭት፡ ዒሳ ፈጣሪ ነው ወይስ አይደለም?

መሲሁ ኢየሱስ