ኢየሱስ “ጌታ አትበሉኝ” ብሏልን?

ኢየሱስ “ጌታ አትበሉኝ” ብሏልን?

አሕመዲን ጀበል የተሰኙ ሙስሊም ጸሐፊ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-

ኢየሱስን «ጌታ» ይሉታልን? ይህ ከሆነ መንግሥተ ሰማያት መግባት አይፈልጉም ማለት ነው፡፡ ለምን ቢሉ በማቴዎስ ወንጌል 7፡20-23 ላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፡፡ «በሰማያት ያለውን የአባቱን ፍቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! የሚለኝ ኹሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ በዚያን ቀን ብዙዎቹ፡- ጌታ ሆይ!ጌታ ሆይ! በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህ ብዙ ተአምራት – አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ በዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ ብዬ አመሠክርባቸዋለሁ» ይላል፡፡ ኢየሱስን «ጌታ» የሚለው ማነው? ሙስሊሞች ወይስ ክርስቲያኖች? «አላውቅኋችሁም፣ እመሰክርባቸኋለሁ» ያለውስ ማንን ነው? ክርስቲያኖችን የትኞቹን ክርስቲያኖች? የሚል ጥያቄ ከተነሳ ደግሞ «ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ የሚለኝ ኹሉ» ብሎ ኢየሱስ ገልጾታል፤ እና መንግሥተ ሰማያት መግባት አይፈልጉም? ለምን ሌላ ትርጉም በመስጠት ራስዎን ያታልላሉ? ኢየሱስን ጌታ ከማለት ውጭ የአምላክን ተእዛዛት መጠበቅና የአምላክን ፈቃድ መተግበር ትተዋል፡፡ ታዲያ እንዴት ተዘናጉ?

ይህ ጥያቄ የአሕመዲን መጽሐፍ ቅዱስን እንደልባቸው የመተርጎም ድፍረት ጣርያ ነው፡፡ በመሠረቱ ጌታ መኾኑን የተናገረው ራሱ ኢየሱስ ነው፡-

“እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ፡፡ እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል” (ዮሐ. 13፡13-14)፡፡

“እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው አላቸው” (ማርቆስ 2፡28)፡፡ እግዚአብሔር ለራሱ ክብር እና አምልኮ በፈጠራት ቀን ላይ ጌታ  መኾን የሚችል ከእርሱ በስተቀር ማነው?

የኢየሱስ ጌትነት መታወጅ የጀመረው በብሉይ ኪዳን ነው፡፡

  • ዳዊት “ጌታ” ብሎ ጠርቶታል (ማቴዎስ 22፡41-46 ከመዝሙር 110፡1 ጋር ያነፃፅሩ)፡፡ ኢየሱስ የዳዊት ጌታ ከሆነ የኔና የናንተ ጌታ የማይሆንበት ምክንያት ምንድነው?
  • ነቢዩ ሚልክያስ ጌታ ብሎታል (ሚልክያስ 3፡1)፡፡
  • ገና በማህፀን ሳለ ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ “ጌታዬ” ብላዋለች (ሉቃ. 1፡43)፡፡
  • መላእክት ጌትነቱን መስክረዋል (ሉቃ. 2፡11)፡፡
  • እግዚአብሔር አብ ራሱ ጌታ መኾኑን መስክሯል (ዕብ. 1፡10)፡፡

እኔ ባደረኩት ቆጠራ መሠረት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከ250 ጊዜያት በላይ “ጌታ” ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ሰዎች ጌታ ሲሉት አንድም ቀን ተቃውሞ አሰምቶ አያውቅም፡፡ ነገር ግን አሕመዲን የቋንቋ ችግር ያለባቸው ይመስል ኢየሱስ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፍቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ኹሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” በማለት የተናገረውን አጣምመው በመተርጎም ኢየሱስ “ጌታ አትበሉኝ” ያለ ለማስመሰል ሞክረዋል፡፡ ኢየሱስ እያለ ያለው በተግባር አማኝ ሆናችሁ ካልተገኛችሁ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ስላላችሁ ብቻ አትገቡም ነው፡፡ ጠያቂው የአገራቸው ቋንቋ ካልገባቸው በእንግሊዘኛ እንዲያነቡት ከታች አስቀምጠናል፡፡[1]

በኢየሱስ ስም ትንቢት መናገርም ሆነ ተዓምራትን ማድረግ ለመንግሥተ ሰማያት አያበቃም፡፡ በኢየሱስ ስም ተዓምር ማድረግ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ዋስትና ከሆነ ጌታውን የሸጠው ይሁዳም ሊገባ ነው፡፡ ለመንግሥተ ሰማያት የሚያበቃው የአብን ፈቃድ በመፈፀም እስከ መጨረሻው ድረስ እውነተኛ አማኝ ኾኖ መገኘት ነው፡፡ መፈፀም ያለበት ቀዳሚው የአብ ፈቃድ ደግሞ እርሱ በላከው በአንድ ልጁ ማመን ነው(ዮሐ. 6፡40)፡፡

አሕመዲን ህሊናቸውን በመጨቆን የእግዚአብሔርን ክቡር ቃል ለማጣመም እስከዚህ ጥግ ድረስ መሄዳቸው በእውነቱ ከሆነ እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች አንድ ሰው በእንዲህ ዓይነት ኹኔታ የሙስሊሞችን መጽሐፍ ሲያጣምም ቢመለከቱ ከመገሰፅ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ተመሳሳይ ነገር በክርስቲያኖች መጽሐፍ ላይ ሲፈፀም ህሊና ያላቸው ሙስሊሞች ኹሉ ሊቃወሙ ይገባል፡፡ ወዳጆች ሆይ ስለ ነፍስ ጉዳይ ነው እያወራን ያለነው፡፡ አንዳችን የሌላችንን ቅዱስ መጽሐፍ እያጣመምን እንዴት ነው ልንተማመንና አንዳችን ሌላችንን የእውነት አምላክ ወደሆነው ፈጣሪያችን ልንመራ የምንችለው? ፈጣሪ በሐሰት እና በማጭበርበር ደስ ይሰኛልን?


[1] “Not every one that saith unto me, Lord, Lord, shall enter into the kingdom of heaven; but he that doeth the will of my Father which is in heaven.” (KJV) John 7:21

 

መሲሁ ኢየሱስ

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ