ኢየሱስ ቃል ነው ወይንስ በቃል የተፈጠረ? የዮሐንስ 1፡14 ትክክለኛ ትርጓሜ

ኢየሱስ ቃል ነው ወይንስ በቃል የተፈጠረ?

የዮሐንስ 1፡14 ትክክለኛ ትርጓሜ

ሙስሊም ሰባኪያን እንደ ልማዳቸው በማያውቁት ጉዳይ ገብተው በግምትና ያለ ዕውቀት ማማሰላቸውን ቀጥለውበታል። ከሁሉም የሚገርመው ግን የአዲስ ኪዳንን ግሪክ እንደሚያውቅ ሰው ከሌሎች ኑፋቄያዊ አንጃዎች የቀዱትን በስህተት የተሞላ ሰዋሰው የግላቸው ጥናት አስመስለው በኩራት የሚያቀርቡት ነገር ነው። በዚህ ተግባር ከሚታወቁት ሙስሊም ሰባኪያን መካከል አንዱ የጻፈውን ላስነብባችሁ። እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-

 ዮሐ.1:14 Καὶ Λόγος σὰρξ ἐγένετο ቃልም ሥጋ ሆነ፤

 ነጥብ አንድ

ቃል Λόγος

እዚህ ጋር የተጠቀሰው ቃል ስፐርማቲኮስ ሎጎስ ማለት የንግግር ቃል*speech* ሲሆን ፈጣሪ ሁሉን ነገር ያስገኘበት፣ ከራሱ አፍ የሚወጣ የራሱ *ሁን* የሚልበት ባህርይ ነው፦

ኢሳ.55:11 ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል፥

መዝ.33:9 እርሱ ተናግሮአልና፥ ሆኑም፤ እርሱ አዘዘ፥ ጸኑም።

መዝ.148:5 እርሱ ብሎአልና፥ ሆኑም፤ እርሱም አዝዞአልና፥ ተፈጠሩም፤

ዮሐ.1:3 ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።

ዘፍጥረት 1.3 እግዚአብሔርም፦ ብርሃን ይሁን አለ ብርሃንም ሆነ 

ምላሻችን

በመጀሪያ ደረጃ፣ ሎጎስ “ንግግር” አይደለም። በጥንታዊ ግሪክ ቋንቋ ይቀርበዋል የሚባለው ትርጉም “Reason” ነው። ሆኖም Λόγος ሎጎስ ወይም “ቃል” እኛ በ 21ኛው ምዕተ ዓመት ውስጥ ሆነን እንደምናስበው ዝም ብሎ የንግግር ቃል አይደለም። ሎጎስ ዮሐንስ ወንጌሉን ከመጻፉ ከብዙ ዘመናት በፊት በብዙ የግሪክ ፍልስፍናና እምነቶች ውስጥ ጥቅም ላይ ውሎ ነበር። ትርጉሙም ሰፊ ነው። የቃሉን ትርጉም በትክክል ለመረዳት ዮሐንስ ወንጌሉን በጻፈበት ዘመን የነበረውን ግንዛቤ ማወቅ ወሳኝ ነው፡፡

1. ሔራቅሊጦስ (Heraclitus) 535-475 ዓ.ዓ. ከሶቅራጦስ በፊት በኤፌሶን ይኖር የነበረ የግሪክ ፈላስፋ ነበር። ይህ ፈላስፋ “ሎጎስ” የሚለውን ቃል “The principle which controls the Universe”(አፅናፈ ዓለምን የሚቆጣጠር ፕሪንሲፕል ወይንም መርህ) ብሎ ያስተምር ነበር።

2. እስጦይቆች የተሰኙ የፍልስፍና ግንዶች ደግሞ ሎጎስን “Anima Mundi” ብለው ይገልፁ ነበር። ይህም ማለት “የዓለማችን ሕይወት ወይንም የሕይወት ምንጭ” (Soul of the World) ማለት ነው።

3. ማርቆስ አውራሊዮስ (Marcus Aurelius) ከ 121 -180 ዓ.ም. የኖረ ሮማዊ ባለ ሥልጣን እንዲሁም ፈላስፋ ነበር። እርሱም Spermatikos Logos (የዓፅናፈ ዓለም አስገኚ ፕሪንሲፕል ወይንም መርህ) የሚል ፅንሰ ሐሳብ ይጠቀም ነበር። ይህም “ሎጎስ” የዓለማችንን የመፍጠርና የመራባትን ሕግ የሚቆጣጠር (Generative principle of the Universe) ነው፡፡ በሌላ አባባል ወይም ፍልስፍናዊ ባልሆነ ቋንቋ ሲገለፅ “አምላክን” የሚወክል ማለት ነው።

4. አይሁድ ሊቃውንት ደግሞ በእብራይስጥና በአረማይክ ቋንቋዎች የእግዚአብሔርን ቃል “ሜምራ” (Memra) በሚል ፅንሰ ሐሳብ ገልፀውታል፡፡ ይህም በዕብራውያን መረዳት መሠረት እግዚአብሔርን የሚገልፅ ነው። ለምሳሌ በታርጉማቸው ውስጥ ስለ ኦሪት ዘዳግም 26፡17-18 ሲጽፉ “Ye have appointed The MEMRA (logos) a king over you this day, that he may be YOUR GOD” (ሜምራን (ሎጎስን) በራስህ ላይ ንጉሥ አድርገህ ሹመሃል፤ ይህም አምላክ እንዲሆንህ ነው) ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ዘፍጥረት 28፡20-21 ላይ በአረማይክ ታርጉም ያዕቆብ እግዚአብሔር አምላኩ እንደሚሆን ከመናገር ይልቅ የእግዚአብሔር ቃል (ሜምራ) አምላኩ እንደሚሆን ስዕለትን ሲሳል ይታያል፡፡ በዚሁ የአረማይክ ታርጉም ውስጥ ዘዳግም 4፡7 ሲብራራ የእግዚአብሔር ቃል (ሜምራ) በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ የሰዎችን ጸሎት እንደሚቀበል ተገልጿል፡፡

በዮሐንስ ዘመን የነበረው የሎጎስ ፅንሰ ሐሳብ ይህንን የሚመስል እንደነበረ ከተረዳን ዘንዳ ሎጎስ የሚለውን ቃል ለምን መረጠ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያስፈልገናል፡፡

ዮሐንስ ይህንን ወንጌል ሲጽፍ ኖስቲሳውያን (GNOSTICS) የሚባሉ ቡድኖች እንዲሁም ዲሲፕሊን ኦፍ ቫሌንቲነስ (Discipline of Valentinus)  የተሰኘ የኑፋቄ አስተምህሮ ተነስቶ ነበር። እነኚህ ቡድኖች “ሎጎስ” የተባለ አካል ኤዮን (Aeions) ከሚባሉ የመጀመሪያ ፍጡሮች አንዱ ሲሆን “ዞዪ” (Zoe) ከምትባል ሌላ “ኤዎን” ጋር በመሆን ሌሎች ፍጡሮችን ማስገኘት እንደጀመረ ይናገራሉ። እነኚህ ቡድኖች የመጽሐፍ ቅዱስን አስተምህሮ በማዛባትና ከነሱ በፊት የነበረውን የሎጎስ ትርጉሞች በመጠቀም የራሳቸውን ሐሰተኛ ወንጌል መስበክ በጀመሩ ጊዜ ነው ዮሐንስ መጻፍ የጀመረው። እናም ዮሐንስ “የሎጎስን” ፍልስፍና በሚያውቅ ማሕበረሰብ ውስጥ ነው ይህንን ስያሜ ለኢየሱስ የተጠቀመው። ይህንን ቃል ሲጠቀም ግን የነሱ ትርጉም ትክክል ነው ብሎ እንደወረደ አልተጠቀመም። ይልቁንስ ሎጎስ የተፈጠረ አምላክ ሳይሆን እራሱ ዘላለማዊና ፈጣሪ መሆኑን ለማሳየት ዮሐንስ 1፡1 “ኤን አርኬ” ብሎ ጀመረው። ከዛም “ቃሉም በመጀመሪያ ከእግዚያብሔር ጋር ነበር” በማለት “ተፈጠረ” የሚለውን ሐሳብ አፈረሰ። ዘላለማዊ መሆኑን ደግሞ የሚያሳየው  “ቃሉም ከእግዚያብሔር ጋር ነበር፣ ቃሉም እግዚያብሔር ነበር” ብሎ የተጠቀመበት የግሪክ ትርጉም  καὶ ὁ Λόγος ἦν πρὸς τὸν Θεόν, καὶ Θεὸς ἦν ὁ Λόγος ሲሆን  ἦν (ነበር was) የሚለው ቃል “Imperfect` ነው። ይህ ማለት ደህሞ በግሪክ መጀመሪያው የማይታወቅ ወይም ዘላለማዊነትን የሚያሳይ ነው።

ከዚህ በኋላ ነው ዮሐንስ 1፡14 ላይ “ቃልም ሥጋ ሆነ” ብሎ የደመደመው። ይህ ማለት አንድ አስቀድሞ የነበረ አካል በማንነቱ ላይ ሥጋን ጨመረ ማለት ነው። ምክንያቱም ቃሉ መጀመሪያውኑ የነበረና ኋላ ላይ ግን ሥጋ የሆነ እንጂ ሥጋ በሆነበት ሰዓት ወደ መኖር የመጣ አይደለምና። ከዚህ ውጪ ቃሉ ንግግርና ተፈጣሪ ነው የሚል አዝማሚያ በዮሐንስ ምዕራፍ 1 ላይ ፈፅሞ አይገኝም። 

References

  1. Barnes note on John 1:1
  2. Iraneus Against Heresies Bk 1, Ch 1.
  3. Michael L. Brown, Answering Jewish Objections to Jesus – Volume 2: Theological Objections, 2000, pp. 18-22

ይህ አብዱል ቀጥሎ የጻፈውን እንመልከት (ጥቅሶቹ ለሙግቱ ብዙም ጠቃሚ ስላልሆኑ አንዳንዱን ዘልያለሁ)፡-

ነጥብ ሁለት

ሥጋ σὰρξ

በቅድሚያ ሥጋ ሰው ለማለት እንደተፈለገ ሊሰመርበት ይገባል

ዘፍጥረት 613 እግዚአብሔርም ኖኅን አለው፦ የሥጋ σὰρξ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል፥…..

ኤርምያስ 3227 እነሆ፥ እኔ የሥጋ σὰρξ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፥

ይህ ሥጋ  በድንግል ማርያም ማህጸን የተዘጋጀ ፍጡር ነው፦

ዕብ.10:5 ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ። መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን *አዘጋጀህልኝ*

ሐዋ.17:31 ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን *ባዘጋጀው* ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤

ተዘጋጀ ማለት ተፈጠረ ማለት ነው አምላክ ፀሓዩንና ጨረቃ፣ ደመናትን፣ ዓለሞችን አዘጋጀ ማለት ፈጠረ ማለት እንደሆነ ሁሉ፦

መዝ.74:16 ቀኑ የአንተ ነው ሌሊቱም የአንተ ነው፤ አንተ ፀሓዩንና ጨረቃውን *አዘጋጀህ*

ምሳ.8:28 ደመናትን በላይ *ባዘጋጀ* ጊዜ፥ የቀላይን ምንጮች ባጸና ጊዜ፥

ዕብ.11:3 ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ *ተዘጋጁ* ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን።

ይህም ሥጋ  የተገኘው ከማርያም ዘረመል ነው፦

ማቴ 1:20 *ከእርስዋ* የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።

ከእርስዋ የሚለው ይሰመርበት * * የሚል መስተዋድድ እንደገባ አስተውል፥…..”

ምላሻችን

ይሄ ጸሐፊ አንደኛ ሎጂክ አያውቅም፣ ሁለተኛ የክርስትና መሠረታዊ ትምህርቶች አልገቡትም፣ ሦስተኛ መጽሐፍ ቅዱስን በአውድ ማንበብ አይችልም።

1. የሎጂክ ችግር- ከላይ እንዳየነው ስለ ሥጋ ሲጽፍ እብራውያን 10፡5 ላይ “ሥጋን አዘጋጀህልኝ” የሚለውን ሌሎች ክፍሎች ላይ አዘጋጀህ ከሚል ቃል ጋር በማመሳከር በትርጉም አንድ እንደሆኑ እያስነበበን ነው። ይህ ሙግት false analogy የሚባል የሥነ አመክንዮ ተፋልሶ ነው፤ በሌላ አባባል ምስስሎሽ ሐሰተኛ በመሆኑ ሙግቱ ከመሠረቱ ሐሰት ነው ማለት ነው። የዚህ ምክንያቱ “አዘጋጀህልኝ” እያለ ያለው ከመጀመሪያውኑ የነበረው አካል መሆኑ ነው። አንድ ነገር “ተዘጋጀለት” የሚባለው የሚዘጋጅለት አካል መጀመሪያውኑ ሲኖር ነው። ለምሳሌ እኔ አባቴን “ቤት አዘጋጀህልኝ” ካልኩት እኔ ቤቱ እንዳልሆንኩ ይታወቃል፤ ነገር ግን እኔ ከሌላ ቦታ እየመጣው ሳለሁ አባቴ የማርፍበትን ቤት አዘጋጀልኝ ማለት ነው። ይህ ግን ሊሆን የሚችለው ከመጀመሪያው እኔ ስኖር ነው። የኢየሱስም ሕልውና ከመጀመሪያው የነበረ ሲሆን የፍጥረት አካል ለመሆን የአምላክነት ባሕርዩ ላይ ሥጋን አክሏል። ኢየሱስ የወሰደው ሥጋ ፍጥረት ነው። ያ ማለት ግን ወልድ ከሱ በፊት አልነበረም ማለት አይደለም። እንደዛ ካልንማ false dichotomy የሚባለውን የሥነ አመክንዮ ተፋልሶ ፈፅመናል ማለት ነው። “አዘጋጀ” (ለምሳሌ፣ አንተ ምድርን አዘጋጀህ) የሚለው ግን ከዕብራውያን 10 ጋር ፍፁም የተለያዩና የማይገናኙ ናቸው። ምክንያቱም እዚህ ላይ “ምድር” ተደራጊና ከመዘጋጀቱ በፊት መኖሩን የሚያሳይ ምንም ስለሌለ። ነገር ግን ብራውያን 10 ላይ “አዘጋጀህልኝ” እያለ ያለው ኢየሱስ ሲሆን ሥጋውንና አስቀድሞ የነበረውን ማንነቱን ለይቶ በተናጠል እየተናገረ ነው። ስለ ምድር መፈጠር ግን እየተናገረ ያለው እራሱ ፈጣሪው ሲሆን ምድር ከመፈጠሯ በፊት በሌላ ማንነት ስለመኖሯ ምንም ማስረጃ የለም፤ ለዚህ ነው ሁለቱን ጥቅሶች ማመሳሰል false analogy ወይንም ሐሰተኛ ምስስሎሽ ነው ያልነው፡፡

2. የክርስትናን ሥነ መለኮት አለማወቅ- እኛ የክርስቶስ በሥጋ መገለጥ የፍጥረት አካል እንዳረገው የምናምን ክርስቲያኖች ሆነን ሳለን ጸሐፊው ለምን ደጋግሞ ሥጋ ሥጋ እንደሚል አልገባኝም። ኢየሱስ ሥጋን ጨመረ ማለት የነበረውን የመለኮታዊ ማንነት ቀየረ ማለት አይደለም። ነገር ግን የኃጢአት ዕዳችንን ለመክፈል መሞት የሚችለው ሥጋ ብቻ ስለሆነ እሱን ጨምሮ መጣ፤ ስለዚህም ፍፁም አምላክ ፍፁምም ሰው ሆነ ማለት ነው። ጸሐፊው ለማለት የፈለገው ኢየሱስ ሥጋ ስለወሰደ፣ አምላክ አይደለም ነው። ይሄ ሙግት ደግሞ አመክንዮአዊ ተፋልሶ መሆኑን ደጋግመን አሳይተናል።

3. የመጽሐፍ ቅዱስን አውድ አለማወቅ- “ቃልም ሥጋ ሆነ” የሚለውን ነጥሎ በማውጣት ዮሐንስ 1፡1-13 የሚገኘውን ሐሳብ በሙሉ ዘሎ የራስ ትርጉም መስጠት የሚገርም ስህተት ነው። የዮሐንስ 1፡1 ማብራርያችንን ለማንበብ እዚህ ጋ ጠቅ ያድርጉ፡፡

መሳሳት የማይሰለቸው ጸሐፊ በማስከተል እንዲህ ሲል ጽፏል፡-

“…ስለዚህ ቃል ሥጋ  ሆነ ማለት ቃል ለሥጋው መገኘት መንስኤ እንጂ ውጤት አይደለም። ሆነ የሚለው የግሪኩ ቃል ኤግኔቶ ἐγένετο ሲሆን ተደራጊ ግስ passive verb ሆኖ ነው የመጣው፥ ቃል ደግሞ አድራጊ ግስ active verb ተላኮ ነው የመጣው፦

ዮሐ.1:3 πάντα δι αὐτοῦ ἐγένετο καὶ χωρὶς αὐτοῦ ἐγένετο οὐδὲ ἕν γέγονεν ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም፥

ኢየሱስ ሰው ከሆነ የሚሆን ነገር ሁሉ ያለ ቃል ካልሆነ ኢየሱስ ሥጋ  ከማርያም ሲሆን በምን ሆነ? መልሱ በቃል ነው፣ አንድ ናሙና ብናይ፦

ዘፍጥረት 1.3 እግዚአብሔርም፦ ብርሃን ይሁን አለ ብርሃንም *ሆነ* ἐγένετο

*ብርሃንም ሆነ* ማለት ብርሃኑ ብርሃን ከመሆኑ በፊት ቃል ነበረ ማለት ሳይሆን ብርሃን በቃሉ ተገኘ ማለት ነው…”

ምላሻችን

ዮሐንስ 1፡14 “Καὶ ὁ Λόγος σὰρξ ἐγένετο” (ካይ ሆ ሎጎስ ሳርክስ ኤጌኔቶ) የሚለው በቀጥታ ሲተረጎም “The word was made flesh” (ቃልም ሥጋ ተደረገ) ይሆናል። ኤጌኔቶ Aorist middle voice ሲሆን “was made” ተብሎ ይተረጎማል። ይህ ግልፅ ከሆነ ስህተቶችህን ላሳይህ፡-

1. በመጀመሪያ ደረጃ “ቃል” “ሆ ሎጎስ” የሚለው active verb አይደለም። “ሆ ሎጎስ” ስም (Noun Masculine Singular) ነው። ስለዚህ አድራጊ ግሥ አይደለም። እራሱ የዓረፍተ ነገሩ ባለቤት (subject) ነው። ስለዚህ ሳታውቅ አዋቂ ለመምሰል መሞከር ዋጋ ያስከፍላል፡፡

2. ስለዚህ “ኤጌኔቶ” (was made)” የሚለው ቃል እራሱ “ሎጎስ” (ቃል) ላይ አንድ የተደረገ ነገር እንዳለ ነው የሚያመለክተው። ይህም “ሥጋ መሆኑን” ነው። ቃሉ እዚህ ጋር ተደራጊ ሆኖ ነው የመጣው። ምክንያቱም ይህ ዓረፍተ ነገር passive sentence ነው። “ቃል”  ደግሞ የዓረፍተ ነገሩ ባለቤት (subject) ነው። ለምሳሌ በእንግሊዘኛ “she was made beautiful”  በሚለው ዓረፍተ ነገር ውስጥ “she” ተደራጊ እንጂ አድራጊ አደለችም። ምክንያቱም ዓረፍተ ነገሩ ራሱ passive ስለሆነ። ሎጎስም እዚህ ክፍል ላይ እራሱ subject ሆኖ ተደራጊ እንጂ ንግግርና አድራጊ አይደለም። በሌላ ቋንቋ ቃሉ እራሱ ሥጋ ሆነ እንጂ ያ ቃል ከሌላ አካል የወጣ ንግግርና የኢየሱስ ፈጣሪ አይደለም። ቃሉ እራሱ ኢየሱስ ነው።

3. ከብርሃን ጋር የቀረበው ሙግት ከ false analogy (ሐሰተኛ ምስስሎሽ) ያልዘለለ ጉንጭ አልፋ ሙግት ነው። እግዚአብሔር ብርሃንን “ሁን” ብሎ ፈጠረ። ሎጎስ ግን ከመጀመሪያው ከእግዚአብሔር ጋር ነበር እንጂ ሁን አልተባለም (ዮሐ. 1፡1)፡፡ እራሱ subject የሆነው ይህ ሎጎስ (ቃል) ደግሞ ሥጋ ሆነ እንጂ እንደ አዲስ አልተፈጠረም። ይህ ማለት መለኮታዊ ባሕርዩ ጠፍቶ ወደ ሥጋነት ተለውጧል ማለት አይደለም፡፡ ሥጋው መለኮት ሆኗል ማለትም አይደለም፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ እንደተናገረው “አምላክ ሰው ሆነ” ወይም “ቃል ሥጋ ሆነ” ማለት የሰውን ሕላዌ ወሰደ፣ ተቀበለ፣ ተገነዘበ፣ የራሱ አደረገ ማለት ነው፡፡ (መሠረት ስብሐት ለአብ፣ ስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ፣ በጥንታውያን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መምህራን ፍለጋ፣ አርቲስቲክ ማተምያ ቤት፣ 1991 .. ገፅ፣ 77)

ቀጥሎም እንዲህ ይላል ጸሐፊው፡-

ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል

ራእ.19:13 በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል።

ኢየሱስ ያለ ኣባት በእግዚአብሔር ቃል ስለተፈጠረ ስሙ የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል፤ ማለት ስሙ እንጂ እርሱ ቃል ነው የሚል ፍቺ የለውም ምክንያቱም ስም ሁልጊዜ ማንነት ይሆናል ማለት ኣይደለም፦

ምላሻችን

በመጀመሪያ ደረጃ “ኢየሱስ ያለ አባት በእግዚያብሔር ቃል ስለ ተፈጠረ”  የምትለው ዓረፍተ ነገር Straw man fallacy ናት። ምክንያቱም ይህ አብዱል የራሱን የተጣመመ ሙግት ፈጥሮ እርሱን መልሶ እያጠቃው ነውና።  ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቃል የተፈጠረ ሳይሆን እራሱ ቃሉ ነው።

ሲቀጥል፣ ለሰው ልጅ ስም ሁሉ የማንንት መግለጫ ላይሆን ቢችልም ለኢየሱስ ግን ስሙ ማንነቱ ነው። ምክንያቱም ዮሐንስ 1፡1 “ቃል ከእግዚአብሔር ጋር ነበር ቃልም እግዚያብሔር ነበር… ሁሉም በዚሁ ቃል ሆነ… ይህ ቃል እራሱ ሥጋ  ሆነ” ብሎ በግልፅ አስቀምጧልና።  ይህም ቃል ደግሞ ኢየሱስ እንደሆነ በዚህ ጽሑፍ አሳይተናል። 

መደምደሚያ

ኢየሱስ ሎጎስና እራሱም እግዚአብሔር መሆኑን በዚህ ምላሻችን አረጋግጠናል። ይህ ሙስሊም ጸሐፊ የግሪክ ቋንቋን የማያውቅ፣ የሎጎስን ታሪካዊ ዳራ የማያውቅ፣ መጽሐፍ ቅዱስን በአውድ ማንበብ ያልተማረና መሠረታዊ የአመክንዮ ሕግጋትን ያልተረዳ ሰው ነው፡፡ ነገር ግን በአጉል አውቃለሁ ባይነት በማያውቀው ገብቶ ለራሱ ተሳስቶ ሌሎችን እያሳሳተ ነው፡፡ ከእንዲህ ያሉ አሳቾች ተጠበቁ፡፡