ኢየሱስ ለእስራኤል ቤት ብቻ?
ሙስሊም ሰባኪያን ክርስትናን በተመለከተ ከሚጽፏቸው መጻሕፍት ውስጥ የማይጠፋ አንድ የተለመደ ሙግት ቢኖር ኢየሱስ ነቢይነቱ ለዓለም ሳይሆን ለእስራኤል ብቻ ነው የሚል ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ሕዝባቸው ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእውነት ብርሃን ሲጎርፍ የሚያደርጉት ሲጠፋቸውና ግራ ሲገባቸው በከንቱ ይፍጨረጨራሉ፤ የማይገታውን ለመግታት የሞት ሽረት ትግል ያደርጋሉ፤ ቁርአናቸውን መመዘን በማይፈልጉበት መመዘኛ መጽሐፍ ቅዱሳችንን ይመዝናሉ፤ የነቢያቸውን ጉድ ለመሸፈን ቅዱሱን ኢየሱስንና ሐዋርያቱን ያብጠለጥላሉ፡፡ አረባዊውን እምነታቸውን በኛ ላይ ለመጫን ያመቻቸው ዘንድ የኢየሱስን ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮ ለማጣጣል የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅሶች ከአውድ ገንጥለው በማውጣት የተለየ ትርጉም ሲሰጡ ይታያሉ፡፡ በዚህ ጽሑፋችን ይህንን ሙግት በቃሉ ብርሃን እንፈትሻለን፡፡
ኢስላማዊው ሙግት መሠረቱ ቁርአን ቢሆንም ተከታዮቹን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ በእማኝነት ያቀርባል፡-
ማቴ. 10፡23 በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም።
ማቴ. 15፡ 24 እርሱም መልሶ። ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ።
ማቴ. 10፡5 “እነዚህን አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፥ አዘዛቸውም፥ እንዲህም አለ። በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፥ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ ይልቅስ የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ እንጂ።”
እንግዲህ እነዚህን ጥቅሶች እንደ ማስረጃ በማቅረብ ነው ኢየሱስ ለእስራኤል ብቻ የተላከ ነቢይ ነው ብለው የሚከራከሩት፡፡
ሙስሊም ሰባኪያን የኢየሱስን ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮ ለማጣጣል መጽሐፍ ቅዱስን መጥቀሳቸው የዕውቀት ውስንነታቸውን ወይንም ደግሞ ሆን ብለው የማሳሳት የልብ ጥመታቸውን ያሳብቃል፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ ምሉዕ መረዳትን ያገኘ ሰው ኢየሱስ ለዓለም የተላከ የዓለም አዳኝ መሆኑን ይረዳልና፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በወጉ ያነበበ ክርስቲያን ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች ቢቀርቡለት ትክክለኛ ሐሳባቸውን ያለምንም ችግር ማስረዳት ይችላል፡፡ ሙስሊሞቹ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ መልእክቱ የኢየሱስ አዳኝነት ለዓለም እንደሆነ የሚያረጋግጥ ሆኖ ሳለ ሁለትና ሦስት ጥቅሶችን ጠቅሰው ነገሩ ሁሉ በዚያ የተቋጨ ለማስመሰል ይጥራሉ፡፡ ይህንን ድምዳሜ ለማፅደቅ ተከታዮቹን አራት ስህተቶች ይፈፅማሉ፡-
- የኢየሱስን አገልግሎት ምንነትና አካሄድ መዘንጋት
- ኢየሱስ ራሱ ያስተማረውን መካድ
- ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምሕርት ያለማገናዘብ
- የኢየሱስ ደቀ-መዛሙርት ያስተማሩትንና ያደረጉትን መካድ
1. የኢየሱስን አገልግሎት ምንነትና አካሄድ መዘንጋት
እንደሚታወቀው የኢየሱስ ውልደትና ዕድገት በምድረ እስራኤል ነበር፡፡ በአገልግሎት ዘመኑም ከእስራኤል ሳይወጣ ነበር የምድር አገልግሎቱን ያገባደደው፡፡ ለዚህም ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡-
የመጀመርያው መዳን ለአይሁድ ከዚያም ለአሕዛብ ሁሉ በመሆኑ ነው፡፡
ዮሐ. 1፡11-12 “የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤”
ሮሜ. 1፡16 “በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና።”
ሮሜ. 2፡9-11 “ክፉውን በሚያደርግ ሰው ነፍስ ሁሉ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፥ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ደግሞም በግሪክ ሰው፤ ነገር ግን በጎ ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሆንላቸዋል፥ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው። እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና።”
ከላይ ባየናቸው ክፍሎች አይሁዳውያን ቀድመው የተመረጡና ቅዱሳት መጻሕፍ የተሰጣቸው ሕዝቦች እንደመሆናቸውና መሲሁ በሥጋ ከእነርሱ እንደመምጣቱ ወንጌሉን ለመስማት ቀዳሚ ሆነዋል፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለአይሁድ ስላደላ ሳይሆን መሲሁ የተለደው ከአይሁድ ስለሆነ መስበክ መጀመር የነበረበትም ከገዛ ወገኖቹ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ሙስሊሞችም ነቢያቸውን በተመለከተ የሚጋሩት አመለካከት ነው፡፡ ሙሐመድ በመካ ተወልዶ አድጎ መዲና ሄዶ ከዚያም ተመልሶ ወደ መካ ወርዶ እንደገና ወደ መዲና ተመልሶ በዚያ ቢሞትም ለዓለም የተላከ ነቢይ ነው እንደሚሉት ሁሉ ኢየሱስም በአካል ከእስራኤል ባይወጣም ዓለምን ሊያድን የተላከ መሲህ ነው፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ኢየሱስ የዓለም አዳኝ የሆነው በመስቀል ላይ ሞቶ በሠራው የቤዝዎት ሥራ እንጂ በአካል እየዞረ በዓለም ላይ በማስተማር ባለመሆኑ ነው፡፡ ሙስሊሞች የሳቱት መሠረታዊና ወሳኝ እውነታ ይህ ነው፡፡ ኢየሱስ ለዓለም የተላከ ነቢይ መሆኑን ለማረጋገጥ በዓለም ላይ እየዞረ ማስተማር አይጠበቅበትም፡፡ ዓለም ሊድን የሚችለው እርሱ በመስቀል ላይ በሠራው ሥራ በመሆኑ ጌታ ዓላማውን (የመስቀል ላይ ሥራውን) እስኪፈጽም ድረስ ከምድረ እስራኤል አልወጣም፡፡ የተላከበት ዋና ዓላማ ሰዓቱ ደርሶ ግብ እስኪመታ ድረስ ከእስራኤል ለጠፉት በጎች እየዞረ አስተምሯል፡፡ ይህን ሰዓት በልዩ ትኩረት ደቀ-መዛሙርቱ ጽፈውልናል፡፡
ዮሐ. 8፡20 “ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር በግምጃ ቤት አጠገብ ይህን ነገር ተናገረ፤ ጊዜው ገና አልደረሰምና ማንም አልያዘውም።”
ዮሐ. 12፡23 “ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል። የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች።”
ዮሐ. 13፡1 “ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው።”
ዮሐ. 17፡1 “ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ ዓይኖቹን አነሣና እንዲህ አለ። አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፥ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፥ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው።”
እንግዲህ ኢየሱስ በምድረ እስራኤል እየዞረ ካስተማረ በኋላ ወደ አባቱ የመሄጃ ሰዓቱ እንደደረሰ ተናግሯል፡፡ ይህም ሰዓት ኢየሱስ የሚሞትበትና ተመልሶ የሚከብርበት (ከሞት የሚነሳበት) ሰዓት ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው ኢየሱስ አካላዊ አገልግሎቱ ለአይሁድ ብቻ መሆኑን ነው፡፡
ኢየሱስ ከስቅለቱና ከትንሣኤው በኋላ እንዲህ አለ፡-
ማቴ. 28፡18-20 “ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”
በዚህ ጥቅስ ውስጥ “ሥልጣን ሁሉ” እና “እንግዲህ” የሚሉ ሁለት ቃላትን እናገኛለን፡፡ እነዚህንም ቃላት ካለፈው የኢየሱስ የአገልግሎት ታሪክ ጋር አዛምደን ስንመረምር አንድ መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን፡፡ እርሱም፡-
“ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” ብሎ የተናገረው ከትንሣኤው በኋላ በመሆኑ ኢየሱስ የተላከበትን ዓላማ ከግብ በማድረሱ ቀደም ሲል ትቶት የመጣውን መለኮታዊ ሥልጣኑን በመቀዳጀት የሰማይና የምድር ባለሥልጣን እንደሆነ ያሳውቀናል፡፡ ይህም ሥልጣን በአይሁድ ብቻ ተገድቦ የነበረውን አካላዊ አገልግሎት ዓለም አቀፋዊ ይዘት እዲኖረው ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ የሰማይና የምድር ሁሉ የበላይ ባለሥልጣን ነውና! እርሱ ለዘላለም የሚመለክ ጌታ ነው!
“እንግዲህ” የሚለው ቃል ደግሞ ከላይ ካለ ሐሳብ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ ኢየሱስ “እንግዲህ (therefore)” ሲል “ስለዚህ” የሚል ስሜት የያዘ አነጋገር ነው፡፡ ኢየሱስ ከሦስት ዓመት የአገልግሎት ዘመን በኋላ እንግዲህ ሂዱ ሲላቸው “አሁን ዓላማዬን ጨርሻለሁ ሥልጣን በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛልና” ማለቱ ነበር፡፡
ይህንን ሐሳብ ስናጠቃልለው የኢየሱስና የደቀ-መዛሙርቱ ቅድመ-ስቅለተ አገልግሎት በእስራኤል የተገደበ ነበር፡፡ ከስቅለትና ትንሣኤው በኋላ ግን ዓለም ሁሉ የሚድንበት የመስቀል ላይ ሥራ ተሠርቷልና ደቀ-መዛሙርቱ ወደ ዓለም ሁሉ እንዲሄዱና የመዳንን ወንጌል እንዲሰብኩ ታዝዘዋል፡፡
የሙስሊሞች መሠረታዊው ችግር እነዚህን ሁለት ዘመናት ያለመለየት ነው፡፡
2. የኢየሱስን ትምሕርት መካድ
ሙስሊሞች እንደሚሉት ኢየሱስ ለአይሁድ ብቻ የተላከ ነቢይ ከነበረና እርሱ ራሱም እንደዚያ ያምን ከነበረ ታድያ ለዓለም የተላክሁ ነኝ ብሎ ስለ ምን አስተማረ?
ዮሐ. 3፡16-18 “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።”
ዮሐ. 1፡11-12 “የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤”
ዮሐ. 12፡46-47 “በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም።”
ዮሐ. 4፡7-9 “ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም ውኃ አጠጪኝ አላት፤ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና። ስለዚህ ሳምራዊቲቱ። አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና።”
ኢየሱስ ለአይሁዳዊያን ብቻ የተላከ ነቢይ ቢሆን ኖሮ ለዚህች ሳምራዊት ሴት ወንጌሉን አይነግራትም ነበር፡፡ በዘመኑ አይሁድ ከሳምራዊያን ጋር አይተባበሩምና “ሴቲቱም አንተ አይሁዳዊ ሆነህ እንዴት ከኔ ውኃ ትጠይቃለህ” አለችው፡፡ ከብዙ ንግግር በኋላም “መሲህ እንደሚመጣና ወደ እውነቱ እንደሚመራን እናውቃለን” ብላ አለችው፡፡ ጌታ ኢየሱስም “እኔ እርሱ ነኝ” እንዳላት ከታሪኩ እንረዳለን፡፡ ይህ ታሪክ የኢየሱስ መሲሃዊ አገልግሎት ለአይሁድ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም እንደሆነ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
3. ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምሕርት ያለማገናዘብ
መጽሐፍ ቅዱስን ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ ድረስ ስናጠናው የሰው ልጅ ባለመታዘዙ ምክንያት እንደወደቀና ለዚህም ድነት ይሆነው ዘንድ በመሲሁ ሞት መዋጀት እንደሚገባው ግልጽ በሆነ ሁኔታ ተቀምጧል፡፡ ይህ ትምሕርት ሙሉ በሙሉ በጽሐፍ ቅዱሳዊ በመሆኑ የትኛውም የክርስትና ክፍል በዚህ ትምሕርት ላይ ልዩነት የለውም፡፡ ይህም የኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞት ምን ያህን እውነት እንደሆነና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡
4. የኢየሱስ ደቀ-መዛሙርት ያስተማሩትንና ያደረጉትን መካድ
ምንም እንኳን ኢስላማዊ መዛግብት የኢየሱስ ደቀ-መዛሙርት እውነተኛ እንደነበሩና ያስተማሩትን ትምሕርት ከመሲሁ ሰምተው እንዳስተማሩ ቢነግሩንም ዘመንኛ ሙስሊሞች ግን የገዛ መጽሐፋቸውን መካድ ጀምረዋል፡፡ የጌታ ደቀ-መዛሙርት በአገልግሎት ዘመናቸው አጅግ ከባድ ስደት ቢደርስባቸውም መንፈስ ቅዱስ ባነሳሳቸው መጠን ወንጌሉን በመልእክታት አማካይነት ጽፈውልናል፡-
ዮሐ. 1፡29 “ በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ። እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።”
ቲቶ. 2፡11-13 “ ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤”
1ኛ ዮሐ. 2፡2 “እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።”
እነዚህ የደቀ-መዛሙርቱ ትምህርቶች ኢየሱስ ለዓለም ሁሉ የተላከ መሆኑን ረጋግጣሉ፡፡ ሙስሊሞች ኢየሱስ ለእስራኤል ብቻ ነው የተላከው ብለው ሲናገሩ ከኢየሱስ እርገት በኋላ ደቀ-መዛሙርቱ ቢያንስ አንድ ጊዜ እንኳን ኢየሱስ ለአይሁድ ብቻ የመጣ ነው ብለው ያስተማሩበትን ማስረጃ እንዲሰጡን እንጠይቃለን፡፡ አንድም ቦታ አላስተማሩም! በተጻራሪው ግን የዓለም መድኃኒት መሆኑን፣ ዓለም በመስቀሉ ሥራ ካላመነ እንደማይድን አስተምረዋል፡፡ ታድያ ከላይ ከእስራኤል ውጪ የትም አትሂዱ የተባሉቱ ደቀ-መዛሙርቱ ምን ነክቷቸው ነው ዓለምን የዞሩት? የኢየሱስን ትምሕርት አልተረዱትም ነበር? በፍፁም! ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ በሰዓቱ ከእርስራኤል አትውጡ ሲላቸው ለምን እንደዚያ እንዳላቸው ስለገባቸው ነው፡፡ ከእስራኤል ወጥተው ማገልገል የሚችሉበት ጊዜ ሲመጣ ወደ ዓለም ሁሉ እንዲሄዱ ኢየሱስ ነግሯቸዋል፤ እነርሱም ያንኑ ተግብረዋል፡፡
ሐዋ. 1፡8 “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።”
ከዚህም በኋላ ደቀ-መዛሙርት በዓለ ሃምሳ በተባለው ቀን መንፈስ ቅዱስን ተሞልተው አስቀድሞ እንደተነገራቸው ወደ ዓለም ሁሉ የምሥራቹን ይዘው ወጥተዋል፡፡
ይህንን ግልጽና ቀላል እውነታ ባለማወቅ ወይንም ደግሞ ክርስትናን ለማጣጣል በማሰብ በከንቱ እየደከሙ የሚገኙት ሙስሊም ሰባኪያን እንዲህ ካለው የሚያስተዛዝብ ተግባር ይቆጠቡ ዘንድ እንመክራቸዋለን፡፡ የተወደዱት ሙስሊም ወገኖቻችንም እነርሱን ጨምሮ ለመላው ዓለም የተላከውን መሲሁን በማወቅና በማመን የዘለዓለምን ሕይወት ያገኙ ዘንድ ጸሎታችን ነው፡፡
ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ