ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን አዋቂ መለኮት ነው!
ለሙስሊም ሰባኪ ስሁት ሙግት የተሰጠ ምላሽ
የእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ መሆኑን ያስተምራል። በተጻራሪው ግን ቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፈው ከተጠናቀቁ ከክፍለ ዘመናት በኋላ የመጣው እስልምና መለኮትነቱን በመካድ ሰው ብቻ እንደሆነ ያስተምራል። ሙስሊም ወገኖቻችን ይህ ለቅዱሳት መጻሕፍት ባዕድ የሆነው ትምህርታቸው ትክክል መሆኑን ለማሳየት ብዙ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ ለማድረግ ሲሞክሩ እንታዘባለን። ይህንንም ሲያደርጉ የክርስቶስን ሰብዓዊ ባሕርያት በሚያንጸባርቁ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች ላይ ብቻ አተኩረው አምላክነቱን የሚናገሩ ክፍሎችን በቸልታ ያልፋሉ። ለአብነት ክርስቶስ ጌታችን ከአምላክ ባሕርያት መካከል አንዱ የሆነውን የሁሉን አዋቂነት (አእማሬ ኲሉ) ባሕርይ እንዳለሁ መጽሐፍ ቅዱስ በአፅንዖት ቢያስተምርም ሙስሊም ወገኖቻችን ግማሹን እውነት ብቻ በመጥቀስ ሌላኛውን በቸልታ ሲያልፉ ወይንም ደግሞ ጥቅሶቹን በተለየ መንገድ ለመተርጎም ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ። ግማሽ እውነት ብቻ ይዞ መሮጥ የሐሰት ትምህርቶች ሁሉ ጠባይና የሰይጣን ባሕርይ ስለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስና ታሪክ ምስክር ናቸው። በዚህ ጽሑፍ በኢንተርኔት ላይ ሲዘዋወሩ ከተመለከትናቸው መሰል ይዘት ካላቸው ጽሑፎች መካከል አንዱን እንፈትሻለን። ሙስሊሙ ሰባኪ እንዲህ ሲል ይጀምራል፦
አብዱል
እውን ኢየሱስ ሁሉን አዋቂ ነውን?
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኛ በሆነው፡፡
ማርቆስ 13:32 ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም።
መንደርደሪያ
*ልጅ* የሚለው የግሪኩ ቃል ሁዎስ Υἱός ሲሆን ወልድ ማለት ነው፣ ወልድ የተባለው ኢየሱስ ከሆነ ኢየሱስ ቀንና ሰዓቱን አያውቅም ማለት ነው፣ አይ በሰውነቱ እንዳይባል እውቀት የስጋ ሳይሆን የዓይምሮ ባህርይ ነው፣ ጥቅሱ *ከአብ በቀር* በማለት ይዘጋዋል፣ *በቀር* ደግሞ ተውሳ-ከግስ ስለሆነ ያ እውቀት የአብ ብቻ መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፣ *አባት* የሚለው የግሪኩ ቃል ፓተር Πατήρ ሲሆን አብ ማለት ነው፣ ይህን ጥቅስ ለመንደርደሪያ ያክል በዚህ ከተረ3ዳን ኢየሱስ ሁሉን አዋቂ ያልሆነበትን የተለያየ ሙግት እንመለከታለን፦
መልስ
ለዚህ ጥያቄ ከዚህ ቀደም በቂ መልስ የሰጠን ቢሆንም ከተጨማሪ ማብራርያ ጋር ሌላ አንድ ነጥብ በማከል እንመለከታለን፡፡ ጌታችን በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚፈረድበት ቀንና ሰዓት አለማወቁ የተነገረው በሥጋዊ ባሕርዩ ነው፡፡ ይህንን ምላሽ ሙስሊሙ ጸሐፊ “ዕውቀት የሥጋ ሳይሆን የአእምሮ ባሕርይ ነው” በማለት ለማስተባበል ሞክሯል ነገር ግን ሥጋ ሲባል የአንድ ሰው ሰብዓዊ ሁለንተናውን ለማመልከት የሚነገር ነው፤ ስለዚህ ጌታችን እንደ ማንኛውም ሰው በጥበብና በዕውቀት ማደግ የተገባው ሰብዓዊ አእምሮው መለኮታዊ ዕውቀቱን ሁሉ ከማወቅ የተገደበ ነበር፡፡ ይህንን ደግሞ ከሰማይ ሲወርድ ወዶና ፈቅዶ ያደረገው መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል (ፊልጵስዩስ 2፡5-11)፡፡ “ከአብ በቀር” የሚለው አባባል ኢየሱስ በመለኮቱ እንደማያውቅ አያሳይም ምክንያቱም ጥቅሱ ሰዎች፣ መላእክትና ሥጋ የለበሰው ክርስቶስ የሚገኙበትን መደብ እንጂ በመለኮት ዓለም ውስጥ ገደብን የሚያስቀምጥ አይደለምና፡፡ አብ ብቻ የሚያውቅ ከሆነ የእርሱ ጥበብና ቃል የሆነው ወልድ እና የእርሱ ኃይል የሆነው መንፈስ ቅዱስ ማወቅ የማይችሉበት መንገድ የለም፡፡ ይህንን ለመረዳት አዲስ ኪዳን “ብቻ/በቀር” (በግሪክ “ኤይ ሜ”) የሚለውን ቃል እንዴት እንደሚጠቀምበት መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡ ለናሙና ያክል አንድ ጥቅስ እንመልከት፡-
“ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፥ እነሆም አምባላይ ፈረስ፥ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፥ በጽድቅም ይፈርዳል ይዋጋልም። ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፥ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፤ በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል።” (ራዕይ 19፡11-13)
በዚህ ጥቅስ ውስጥ “ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው” ለሚለው የመጣው “ኤይ ሜ” የሚል ተመሳሳይ የግሪክ ቃል ሲሆን የክርስቶስን አምላክነት የማይቀበሉ ወገኖች ስለ ምፅዓቱ ቀን እንደማያውቅ የተናገረውን በሚረዱበት መንገድ እንረዳ ከተባለ ክርስቶስ ብቻ የሚያውቀው አብና መንፈስ ቅዱስ የማያውቁት ነገር አለ ልንል ነው፡፡ ይህ ግን እውነት ሊሆን እንደማይችል ግልፅ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ከኢየሱስ በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው” ብሎ ሲል አብና መንፈስ ቅዱስን ለማግለል የታለመ አለመሆኑ ካግባባን “ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም” ብሎ ሲል መለኮታዊውን የወልድ ባሕርይ እና የአብ መንፈስ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ለማግለል የታለመ አለመሆኑም ሊያግባባን ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ ለሁለቱ ጥቅሶች የተለያዩ ትርጓሜዎችን ለመጠቀም የሚያስችል በቂ ሰበብ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ መሆንን የሚያመለክቱ ቃላትን (Exclusive Words) ሲጠቀም የሥላሴ አካላትን ለመነጣጠል አለመሆኑን ሊያሳዩ የሚችሉ በርካታ ጥቅሶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንዲህ ያሉ ጥቅሶች ሚዛኑን በጠበቀ የአፈታት ሥርዓት ሊተረጎሙ ሲገባቸው አንዳንድ ወገኖች የክርስቶስንና የመንፈስ ቅዱስን መለኮትነት ከሚክድ ቅድመ ግንዛቤያቸው በመነሳት በተሳሳተ መንገድ ሲተረጉሟቸው እንታዘባለን፡፡
በማስከተል የማቀርበው ሙግት ከላይ ከተጠቀሰው ጋር ተያያዥ ቢሆንም ሁሉንም ክርስቲያን ምሑራን ላያስማማ ይችላል፡፡ ይህ መሆኑ አሳሳቢ ሊሆን አይገባውም ምክንያቱም በነገረ መለኮት ዘርፍ ይብዛም ይነስም ተቃዋሚ የሌለው ሐሳብ የለምና፡፡ ሙግቱ የቅዱሳት መጻሕፍት ድጋፍ ያለውና በአመክንዮ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ልዩነት ካለን በፍቅር ይሁን እያልኩ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
ይህ ጥቅስ መለኮታዊ ችሎታ ሲባል ምን ማለታችን ነው የሚል ጥያቄ የሚያስነሳና በዚያም መነፅር ሲታይ ቀላል መፍትሄ ያለው ነው፡፡ በርግጥ እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነው ስንል ማድረግ የወደደውን ሁሉ የማድረግ ኃይልና ጥበብ አለው ማለታችን እንጂ ሁሉን ያደርጋል ማለታችን አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል በዓለም ላይ የሚፈፀሙ ብዙ አሳዛኝና አስደንጋጭ ክስተቶች ቢኖሩም እግዚአብሔር በሁሉን ቻይነቱ ጣልቃ ሲገባና ሲያስቆማቸው አንመለከትም፡፡ ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ አይደለም ማለት አይደለም፡፡ የሁሉን ቻይነት እምቅ ኃይሉን በወደደው ጊዜ፣ ስፍራና በወደደው መጠን ይጠቀማል፡፡ ለምሳሌ ያህል ጌታችን ኢየሱስ በዲያብሎስ በተፈተነ ጊዜ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል” የሚል ተግዳሮት ከዲያብሎስ ዘንድ ቢቀርብበትም ሁሉን ቻይነቱን ተጠቅሞ ድንጋዮቹን ወደ ምግብነት የመቀየር ተግባር አልፈፀመም (ማቴ. 4፡3)፡፡ የሁሉን ቻይነት መለኮታዊ ኃይሉን አልተጠቀመም ማለት ግን ሁሉን ቻይ አይደለም ወደሚል ድምዳሜ አይመራም፡፡ ልክ እንደዚሁ ጌታችን ኢየሱስ ሁሉን አዋቂ መለኮት ቢሆንም ለዓላማውና ለሐሳቡ ሲል ሁሉን አዋቂነቱን በመገደብ አለማወቅ ይችላል፡፡ ይህ መሆኑ በሁሉን አዋቂነቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ሳይሆን በወደደው ጊዜና መጠን ዕውቀቱን መጠቀም እንደሚችል የሚያሳይ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ዕውቀት ያለው ወልደ እግዚአብሔር ቢሆንም የሰው ልጆችን የማዳን ዓላማውን ለመፈፀም ሲል ራሱን በመመጠን በሰው አካል ተገልጧል፡፡ በዚህ ጊዜ ለሰው ልጆች መዳንና ለምድር አገልግሎቱ አስፈላጊ የሆነውን ዕውቀቱን ብቻ ተጠቅሟል፡፡ የምፅዓቱን ቀን ማሳወቅ የሰው ልጆችን በማዘናጋት ለብዙ ጥፋት ስለሚዳርግ ከማወቅም ሆነ ከማሳወቅ ራሱን በማቀብ ምልክቶቹን ብቻ ተናግሯል፡፡ ሁሉን ማድረግ እየቻለ ሁሉን የማድረግ መለኮታዊ ኃይሉን አለመጠቀሙ ሁሉን ቻይ አይደለም እንደማያሰኘው ሁሉ ሁሉን ማወቅ እየቻለ ሁሉን የማወቅ መለኮታዊ ዕውቀቱን ለጊዜው አለመጠቀሙ ሁሉን አዋቂ አይደለም አያሰኘውም፡፡
አብዱል
ሙግት አንድ
ኢየሱስ ሁሉን አዋቂ ቢሆን ኖሮ ከሌላ ህላዌ እውቀት ይማራልን?
ዮሐ 8:28 አባቴም *እንዳስተማረኝ* እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ።
ዮሐ.7:15-16 አይሁድም። ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል? ብለው ይደነቁ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። *ትምህርቴስ* ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤
ዕብራውያን 5:8 ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን *ተማረ*፤
ተከታዩም ሙግት ተያይዞ ምላሽ የሚሰጥበት ነው፡-
ሙግት ሁለት
ኢየሱስ ሁሉን አዋቂ ቢሆን ኖሮ በጥበብ ያድግ ነበርን? የጥበብና የማስተዋል፥ የእውቀት መንፈስ ያርፍበታልን?
ሉቃስ 2:52 ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።
ኢሳይያስ 11:2 የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።
መልስ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ክብሩንና ሥልጣኑን በመተው ከሰማይ ወርዶ ሰው ሆኖ በምድር ላይ በመኖሩ ምክንያት ፍፁም ሰው ነው፡፡ ፍፁም ሰው ሆኖ መምጣቱ የኛ ምትክ በመሆን የኃጢአታችንን ዕዳ ለመክፈል አስፈላጊ በመሆኑ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ሰብዓዊ ባሕርያትን ተላብሶ ተመላልሷል፡፡ ኢየሱስ ፍጹም ሰው ስለነበረ የሰው አካልና የሰው አእምሮ ነበረው፡፡ ስለዚህ በቁመት ማደግ እንዳስፈለገው ሁሉ በጥበብም ማደግ አስፈልጎታል፡፡ በመለኮቱ ግን እርሱ ራሱ የእግዚአብሔር ሎጎስ (ቃል፣ ዕውቀት፣ ፍጥረትን የሚያስተናብርበት መርህ፣, ወዘተ.) እንዲሁም የእግዚአብሔር ጥበብ ነው (ዮሐንስ 1፡1፣ 1ቆሮ. 1፡24)፡፡ ስለ ክርስቶስ የሚናገሩ ጥቅሶችን ስናነብ ስለየትኛው የክርስቶስ ባሕርይ እንደተነገረ በማስተዋል መሆን ያስፈልገዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን ከርስቶስን ሁሉን አዋቂ መለኮት አድርጎ ገልፆት ሳለ ስለ ሰብዓዊ ባሕርያቱ የተነገሩትን ጥቅሶች በመጥቀስ ሁሉን አዋቂ አይደለም ማለት አላዋቂነት ነው፡፡
አብዱል
ሙግት ሶስት
ኢየሱስ ሁሉን አዋቂ ቢሆን ኖሮ ምናልባት ብሎ ይናገር ነበርን?
ማርቆስ 11:13 ቅጠልም ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ምናልባት አንዳች ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ መጣ፥ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና መጥቶ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም።
መልስ
አሁንም ጥቅሱ የክርስቶስን ሰብዓዊ ባሕርይ የሚጠቅስ እንጂ መለኮታዊ ባሕርዩን የተመለከተ አይደለም፡፡ በዚህ ጥቅስ ዙርያ የሰጠነውን ማብራርያ እዚህ ጋ ጠቅ በማድረግ ማንበብ ይቻላል፡፡
አብዱል
ይህን የስነ-አመክንዮ ሙግት ታሳቢና ዋቢ ባደረገ መልኩ ከተረዳን ወዲህ ከተቆላበት ወደ ተጋፈበት ጉዳይ እንገባለን፣ ኢየሱስ ሁሉን አዋቂ ነው ብለው የተነሱባቸውን ጥቅሶች እንመልከት፦
መልስ
ጥቅሶቹን ከመዘርዘር የዘለለ ክርስቲያናዊውን ምላሽ በማገናዘብ ያቀረብከው ማብራርያ በሌለበት ስለ ምን አመክንዮ ነው የምታወራው?
አብዱል
ጥቅስ አንድ
ዮሐ 21:17 ጴጥሮስ አዘነና። ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤
ይህ ጥቅስ የተጻፈበት ሙሉውን ምዕራፍ የዮሐንስ ወንጌል ክፍል እንዳልሆነ የአዲስ ኪዳን ምሁራን ይስማማሉ፣ ዮሐንስ ወንጌሉ የሚጠናቀቀው ዮሐ 20:31 ላይ ነው የሚል መረጃ አላቸው፣ ነገር ግን ይህ ሙግት በጥራዝ ጠለቅ ጥናት ካልታየ በስተቀር በጥራዝ ነጠቅ ጥናት ከባድ ስለሆነ የመጣው ጥቅስ ባሉበት ደረጃ መመለሱ ብልህነት ነው፡፡
መልስ
የወንጌሉ የመረጨረሻው ምዕራፍ የኋላ ዘመን የአርትዖት ጭማሬ እንደሆነ የሚናገሩ አንዳንድ ምሑራን ቢኖሩም የሚሰጡት ምክንያት ውኀ የሚያነሳ አይደለም፡፡ ጭማሬ ስለመሆኑ ማስረጃ ሊሆን የሚችል የእጅ ጽሐፍ ማስረጃም ሆነ የአጻጻፍ ልዩነት የለም፡፡ በነዚህ ሁለቱ ምክንያቶች ይህ አመለካከት በብዙኀኑ ሊቃውንት ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የሆነው ሆኖ የሙስሊሙ ሰባኪ ዓላማ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የክርስቶስን ሁሉን አዋቂነት መሞገት ወይስ የንባብ ሕየሳ? ርዕስ ማደበላለቅ ደካማ ሙግቶችን የመደገፍያ ደካማ ስልት ነው፡፡
አብዱል
ሁሉን ታውቃለህ ማለት አጠቃላይ ታውቃለህ ማለት ነውን? መልሱ አዎ ከሆነ አማንያንም ሁሉን አዋቂዎች ናቸው፦
1ዮሐ.2:20 እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ *ሁሉንም ታውቃላችሁ*።
*ሁሉ* የሚለው ቃል በአንጻራዊ ደረጃ ለአማንያን እንደተጠቀመበት ሁሉ ለኢየሱስም በዚህ ሂሳብ ነው የሚታየው፣ ምክንያቱም ኢየሱስ የማያውቀው ነገር ስላለ።
መልስ
ቃላት የሚተረጎሙት በአውድ እንጂ በዘፈቀደ አይደለም፡፡ ዮሐንስ 21፡17 ላይ ጌታችን ሁሉን አዋቂ የተባለው የሰዎችን ልብ ከማወቅ አንጻር ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን አዋቂ መለኮት በመሆኑ ምክንያት የሰዎችን ሁሉ ልብ ያውቃል፡-
“ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና።” (ዮሐንስ 2፡24-25)
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍጡር የማይቻለውን የሰዎችን ሁሉ ልብ የማወቅ መለኮታዊ ኃይል አለው፡፡ እግዚአብሔር ለአገልጋዮቹ የሰዎችን የልብ ሐሳብ የገለጸባቸው አጋጣሚዎች ስለመኖራቸው በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ቢነገርም የሰዎችን ሁሉ ልብ የማወቅ ኃይል እንዳለው የተነገረለት ፍጡር የለም፡፡ ይህ ችሎታ ከመለኮት ውጪ ለማንም የሚነገር አይደለም፡፡
የጌታችን ሁሉን አዋቂነት የሰዎችን ሁሉ ልብ ከማወቅ አንጻር የተነገረ ከሆነ 1ዮሐንስ 2፡20 ላይ “ሁሉን “ እንደሚያውቁ የተነገረላቸው አማኞችስ? የጥቅሱን አውድ ስንመለከት አማኞች “ሁሉን” አዋቂነት ሐሰተኛ መምህራንን ለይተው ከማወቃቸው አንጻር የተነገረ እንጂ ስለ ሁሉም ጉዳዮች የተነገረ አለመሆኑን እንመለከታለን፡-
“ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ። እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ።”
በጥቅሱ ውስጥ “ሁሉንም” የሚለው ከአማኞች ተለይተው የወጡ “ሁሉንም” ሐሰተኞች ለማለት እንጂ እንደ መለኮት ያለ ሁሉን አዋቂነትን የሚያሳይ አይደለም፡፡ ሁለቱ ጥቅሶች በምንም የሚገናኙ አይደለም፡፡ ሙግቱ ገለባ ነው፡፡
አብዱል
ጥቅስ ሁለት
ማቴዎስ 9:4 ኢየሱስም አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ፦ ስለ ምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ?
ኢየሱስ ሁሉ አዋቂ ካልሆነ በልባቸው ክፉ ማሰባቸውን በምን አወቀ? ይህ ቆንጆ ጥያቄ ነው፣ ኢየሱስ በልባቸው ያለውን ያወቀው የእውቀት መንፈስ ስላረፈበት ያወቀው በመንፈስ ቅዱስ ነው፦
ማርቆስ 2:8 ወዲያውም ኢየሱስ በልባቸው እንዲህ እንዳሰቡ *በመንፈስ* አውቆ እንዲህ አላቸው፦ በልባችሁ ይህን ስለ ምን ታስባላችሁ?
ሉቃስ 4:1 ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥ አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ።
ኢሳይያስ 11:2 የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።
ምን ኢየሱስ ብቻ ጴጥሮስም ሐናንያና ሰጲራ የደበቁትን ነገር አውቆ ነበር፦ ሃዋርያት ስራ 5:1-10 ጴጥሮስ ያወቀው በመንፈስ ነው ከተባለ ጴጥሮስ ላይ ያረፈው መንፈስ አይደል እንዴ ኢየሱስ ላይ ያረፈው?
መልስ
የጸሐፊው ሙግት የኢየሱስን መሲሃዊ አገልግሎትና ከሰማይ እንደመጣ የእግዚአብሔር ሎጎስ ያለውን መለኮታዊ ኃይል ከማምታታት የመነጨ ነው፡፡ መሲሃዊ አገልግሎት በመንፈስ ቅዱስ መቀባትንና ከሰው ልጆች መካከል እንደሚመረጥ ነቢይና ካህን ማገልገልን የሚጠይቅ በመሆኑ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር መምጣትና በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ (መሲህ ወይም ክርስቶስ ሆኖ) ማገልገል አስፈልጎታል፡፡ እርሱ ራሱ ግን ዘላለማዊ የአብ ቃልና ጥበብ በመሆኑ የአብና የመንፈስ ቅዱስን መለኮታዊ ዕውቀት የሚጋራ መለኮት ነው፡፡ እንደ ነቢይና እንደ ካህን በመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ኃይል ቢያገለግልም እንደ እግዚአብሔር ሎጎስ ግን ያልተገደበ መለኮታዊ ችሎታ አለው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ያልተገደበ መለኮታዊ ዕውቀት ስለማይሰጥ የጌታችን ሁሉን አዋቂነት በተጠቀሰባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ከመለኮታዊ ባሕርዩ አንጻር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
በርግጥ ሙስሊሙ ሰባኪ ማርቆስ 2፡8 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ በተሳሳተ መንገድ ነው የተረዳው። “ወዲያውም ኢየሱስ በልባቸው እንዲህ እንዳሰቡ በመንፈስ አውቆ” የሚለው ኢየሱስ በራሱ እንዳወቀ የሚያሳይ መሆኑን ከግሪኩ ንባብ መረዳት ይቻላል። τῶ πνεύματι αὐτοῦ (ቶ ፕኔውማቲ አውቶው) ማለት “በራሱ መንፈስ አውቆ” የሚል ትርጉም አለው። ለዚህ ነው አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ኢየሱስም ወዲያው በልባቸው የሚያስቡትን በመንፈሱ ተረድቶ” በማለት ያስቀመጠው።
ማጠቃለያ
መጽሐፍ ቅዱሳችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን አዋቂ መሆኑን በግልፅና በማያሻማ መንገድ ይናገራል፡፡
1. በመጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ልብ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው (1ነገሥት 8፡39)፡፡ የሰዎችን ልብና ኩላሊት በመመርመር እንደየሥራቸው መስጠት የእግዚአብሔር ሥልጣን መኾኑን ያስገነዝባል፡- “እኔ እግዚአብሔር ለሰው ኹሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ፡፡” (ኤር. 17፡10)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ መለኮታዊ ኃይል እንዳለው ተናግሯል፡- “አብያተ ክርስቲያናትም ኹሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ፡፡” ራዕይ 2፡23፡፡ (በተጨማሪም ማቴዎስ 9፡3-4፣ ሉቃስ 9፡46-47፣ ዮሐንስ 6፡60-66፣ 1ቆሮንቶስ 4፡5፣ ማርቆስ 2፡5-12)፡፡
በብሉይ ኪዳን የሰዎችን ልብና ኩላሊት በመመርመር የውስጣውን ሐሳብ እንደሚያውቅ የተናገረው እግዚአብሔር አምላክ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ በአዲስ ኪዳን ግልፅ ሆኗል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን አዋቂ ተብሏል፡- “ሁሉን እንድታውቅ ማንምም ሊጠይቅህ እንዳትፈልግ አሁን እናውቃለን፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን አሉት፡፡ ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ አሁን ታምናላችሁን?” ዮሐንስ 16፡30-31
“ሦስተኛ፦ ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው፡፡ ኢየሱስም፦ በጎቼን አሰማራ፡፡” ዮሐንስ 21፡17
2. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን አዋቂ ብቻ ሳይሆን ማንም መርምሮ ሊያውቀው የማይችል ከመታወቅ ያለፈ አምላክ መሆኑን፤ እንዲሁም ማንም ሊያውቀው የማይችለውን አብን ማወቅ የሚቻለው በእርሱ ፈቃድ ብቻ መሆኑን ተናግሯል፡-
“ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ ለም።” (ማቴዎስ 11፡27)፡፡
ጌታችን በዚህ ጥቅስ ውስጥ በፍጥረት ከመታወቅ ያለፈ መሆኑንና እርሱን የሚያውቀው አብ ብቻ መሆኑን እንዲሁም በፍጥረት ከመታወቅ ያለፈውንና ኢ-ውሱን የሆነውን አብን የሚያውቀው እርሱ ብቻ መሆኑን መናገሩ ሁሉን አዋቂ መለኮት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
3. መጽሐፍ ቅዱሳችን ኢየሱስ ሁሉን አዋቂ መሆኑን ብቻ ሳይሆን እርሱ ራሱ የእግዚአብሔር ሎጎስ (ቃል፣ ዕውቀት፣ ፍጥረትን የሚያስተናብርበት መርህ፣ ወዘተ.) እንዲሁም የእግዚአብሔር ጥበብ መሆኑን ይነግረናል (ዮሐንስ 1፡1፣ 1ቆሮ. 1፡24)፡፡ ኢየሱስ ሁሉን አዋቂ አይደለም ብሎ መናገር የእግዚአብሔር ዕውቀትና ጥበብ የተገደበ ነው የሚል ክህደት ነው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ክብሩንና ሥልጣኑን በመተው ከሰማይ ወርዶ ሰው ሁኖ በምድር ላይ በመኖሩ ምክንያት ፍፁም ሰው ነው፡፡ ፍፁም ሰው ሆኖ መምጣቱ የኛ ምትክ በመሆን የኃጢአታችንን ዕዳ ለመክፈል አስፈላጊ በመሆኑ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ሰብዓዊ ባሕርያትን ተላብሶ ተመላልሷል፡፡ ኢየሱስ ፍጹም ሰው ስለነበረ የሰው አካልና የሰው አእምሮ ነበረው፡፡ ስለዚህ በቁመት ማደግ እንዳስፈለገው ሁሉ በጥበብም ማደግ አስፈልጎታል፡፡ በመለኮቱ ግን ሁሉን አዋቂ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል፤ ስለዚህ ስለ ሰብዓዊ ባሕርዩ የሚናገሩትን ጥቅሶች በመጥቀስ ሁሉን አዋቂ አይደለም ብሎ መደምደም መጽሐፍ ቅዱስን ካለማወቅ የሚመነጭ ስህተት ነው፡፡