ጌታችን ኢየሱስ ሥልጣንን ከአብ መቀበሉ አምላክ አለመሆኑን ያሳያልን?
ጥያቄ፡-
“ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28፡18-20)፡፡
ሥልጣን የራሱ ቢሆን ኖሮ ግን “ሥልጣን ተሰጠኝ” ሳይኾን “ሥልጣን አለኝ ” ነበር የሚለው ስለዚህ ለኢየሱስ ሥልጣን የሰጠው አምላክ መኾኑን እንረዳለን፡፡
መልስ፡-
ይህንን ጥያቄ የሚጠይቁ ሰዎች እግዚአብሔር አንድ አካል ብቻ እንዳለው ቅድመ ግንዛቤ የያዙ ናቸው፡፡ የሥሉስ ቅዱስ አካላት አንዳቸው ከሌላቸው የመቀበላቸውና አንዳቸው ለሌላቸው የመታዘዛቸው እውነታ መታየት ያለበት አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ የአንዱ ግፃዌ መለኮት አካላት መሆናቸውን በሚናገረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምሕሮ መሠረት እንጂ በነጠላ አሓዳዊነት መሠረት መኾን የለበትም፡፡ ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል ግን ከሞላ ጎደል በእያንዳንዱ ጥያቄያቸው ውስጥ ይህንን መሠረታዊ ሃቅ በመዘንጋት የራሳቸውን ቁርአናዊ እምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለመጫን ሲሞክሩ ይስተዋላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ከአብ እንደሚቀበል ብቻ ሳይኾን ለአብ እንደሚሰጥም ጭምር ይናገራል፡- “በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ኹሉና ሥልጣንን ኹሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል” (1ቆሮ. 15፡24)፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በመለኮት አንድ ቢሆንም በአካል ግን ሦስት በመኾኑ አንዱ የሥላሴ አካል ከሌላው መቀበሉ ከአንዱ ግፃዌ መለኮት ውጪ ከሚገኝ ሌላ አካል እስካልተቀበለ ድረስ አምላክነቱን ሊያጠራጥር አይችልም፡፡ ሌላው መረሳት የሌለበት ነጥብ በባሕርዩ ፍጹም አምላክ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብሩን ጥሎ የባርያን መልክ በመያዝ ወደ ምድር መምጣቱ ነው (ዮሐ. 6፡38፣ ማቴዎስ 20፡24-28፣ ፊልጵሲዩስ 2፡5-8)፡፡ ስለዚህ ተልዕኮውን ከፈፀመ በኋላ አብ አክብሮታል፡-
“በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ኹሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ኹሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ኹሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው” (ፊልጵሲዩስ 2፡9-11)፡፡
በማቴዎስ 28፡18 ላይ የሚገኘውን ቃል በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ከተመለከትን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን ለአባቱ ታዝዞ በገዛ ፈቃዱ ትቶት የመጣውንና መለኮታዊ መብቱ የሆነውን ሥልጣን መልሶ ተቀበለ እንጂ የእርሱ ያልሆነውን ስላልተቀበለ ይህ አባባል አምላክነቱን አጠራጣሪ ለማድረግ ምክንያት አይኾንም፡፡
ሌላው መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር ከተሠግዎ በፊት ጌታችን ፍጹም አምላክ እንደነበረና ከተሠግዎ በኋላ ግን አምላካዊ ባሕርዩ ሳይለወጥ ፍጹም ሰው መኾኑ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ክብሩ የተመለሰው ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ኾኖ ነው፡፡ የአባቱን ፈቃድ ያለ ምንም እንከን ከዳር በማድረሱ ምክንያት መለኮታዊ ባሕርዩ ብቻ ሳይኾን ሰብዓዊ ባሕርዩም ጭምር ክብርን ተቀዳጅቷል፡፡ ይህ ደግሞ በስሙ የሚያምኑት ቅዱሳን የርስቱ ወራሽና የግዛቱ ተካፋይ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው (ሉቃ 22፡29-30፣ ዮሐ 17፡24፣ ሮሜ 8፡17፣ ራዕ 2፡26-27፣ ራዕ 3፡21)፡፡
ጠያቂው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣንን ከአብ መቀበሉን የሚናገረውን ቃል ብቻ ነጥለው ጠቀሱ እንጂ ሙሉ አውዱን ቢያነቡት ኖሮ የኢየሱስን አምላክነት አሻሚ ባልሆነ ኹኔታ በተመለከቱ ነበር፡፡ እስኪ በክፍሉ አውድ ውስጥ የሚገኙትን ደምቀው የተጸፉትን ቃላት ልብ ብለን እንመልከት፡-
“አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፥ ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ የተጠራጠሩ ግን ነበሩ፡፡ ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ሥልጣን ኹሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ፡፡ እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ኹሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ኹሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ 28፡16-20)፡፡
በዚህ ቦታ ላይ ሐዋርያት ለኢየሱስ ሰግደዋል፡፡ የጠያቂው ሃይማኖት አጥብቆ እንደሚያስተምረው ኢየሱስ ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ሌሎች ቅዱሳን ሰዎችና መላዕክት እንዳደረጉት ሐዋርያቱ እንዳይሰግዱለት በነገራቸው ነበር (ሐዋ. 10፡25-26፣ ራዕ 22፡8-9)፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ አንድም ጊዜ ያንን አድርጎ አያውቅም፡፡ ኢየሱስ በሰማይና በምድር ሥልጣን ኹሉ እንደተሰጠው ተናግሯል፡፡ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅና ወራሽ ባይኾን ኖሮ አብ እንዴት በሰማይና በምድር ሥልጣንን ኹሉ ይሰጠው ነበር? የጥምቀቱ ደግሞ ከኹሉም በላቀ ኹኔታ አምላክነቱን ይገልጣል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የእግዚአብሔር ስም ባሕርዩን ይወክላል (ዘጸ 33፡17-23፣ 34፡5-7)፡፡ የእግዚአብሔርን ስም ማመስገን ማለት እግዚአብሔርን ማመስገን ማለት ነው (መዝ 7፡17)፡፡ የእግዚአብሔር ስም ረዳታችን እንደሆነ መናገር እግዚአብሔር ረዳታችን እንደሆነ መናገር ነው (መዝ. 124፡8፣ 121፡2)፡፡ በእግዚአብሔር ስም መምጣት ማለት በእግዚአብሔር ኃይል መምጣት ማለት ነው (1ሳሙኤል 17፡45፣ ዮሐንስ 5፡43)፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርና ስሙ አይነጣጠሉም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀት የገዛ ስሙ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ እኩል እንዲጠቀስ በማዘዝ አንድ ስም እንዳላቸው ግልፅ አድርጓል፡፡ ይህም ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በባሕርይም ሆነ በአገዛዝ አንድ መኾኑን ያሳያል፡፡ ማንም ፍጡር እንዲህ ዓይነት ነገር ቢናገር በእውነተኛው አምላክ ላይ ክህደትን መፈፀም በመኾኑ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ አሁንም በዚሁ ስፍራ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደሚሆን በመናገር በኹሉም ቦታ መገኘቱን አስታውቋል፡፡ በእርግጥ በኹሉ ቦታ መገኘት መቻሉን ሲናገር ይህ ለመጀመርያ ጊዜ አይደለም (ማቴ 18፡20 ይመልከቱ)፡፡ ማንም ሰው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥልጣን ከአብ መቀበል በዚህ አውድ ውስጥ በማንበብ መረዳት ያስፈልገዋል እንጂ ከአውዱ ገንጥሎ በማውጣት የተለየ ትርጉም መስጠት የለበትም፡፡