የይሖዋ ምስክሮችና ዮሐንስ 1÷1
“ቃልም እግዚአብሔር ነበረ”
ዋች ታወር የተሰኘው የሐሳውያን ማሕበር ዮሐንስ 1÷1 ላይ “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” የሚለውን “እግዚአብሔር” በግሪክ “ቴዎስ” ፊት “ሆ” የሚል መስተኣምር አለመኖሩ ኢየሱስ ትንሽ አምላክ መሆኑን ያመለክታል የሚል ሙግት አለው፡፡ የድርጅቱ ሙግት ጠቅለል ባለ ሁኔታ የሚከተለውን ይመስላል፡-
እግዚአብሔር ከሚለው የግሪክ ቃል ፊት የተወሰነ መስተኣምር (the) ካለ፣ ቃሉ በአብዛኛው መተርጐም ያለበት እግዚአብሔር (God) ተብሎ ነው፡፡ ነገር ግን ቃሉ አብዛኛውን ጊዜ እንደሚገኝበት ዐውድ ስለሚወሰን የቃሉን ፍቺ የሚወስኑት ተርጓሚዎቹ ናቸው፡፡ በዚህ ክፍል ግን “ቃል” የተባለው ክርስቶስ “በእግዚአብሔር ዘንድ” ስለነበር እርሱ ራሱ እግዚአብሔር (God) ሊሆን አይችልም፡፡ ይህንን ዐውዱ ራሱ ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም ማንም ከራሱ ጋር (“ዘንድ”) አብሮ ሊሆን አይችልምና፡፡ ስለዚህ የዮሐንስ 1÷1 ትክክለኛ ትርጉም (a god) የሚለው ነው፡፡
ዮሐንስ 1÷1 “ቴዎስ” (“θεὸς” እግዚአብሔር) የሚለው የግሪክ ቃል፣ አብዛኛውን ጊዜ የሚተረጐመው፣ እግዚአብሔር ወይም አምላክ (God) ተብሎ ነው፡፡ ቃሉ በዚህ መልኩ የሚተረጐመው ከቃሉ ፊት የተወሰነ መስተኣምር ሲኖር እንዲሁም ሳይኖር ነው፡፡ በግሪክ ሰዋስው (እንዲሁም በእንግሊዝኛ) በስም (noun) ፊት የተወሰነ መስተኣምር (the) መኖርም ሆነ ያለመኖር አንዳችም የትርጒም ልዩነት አያመጣም፡፡ በተለይ “ቴዎስ” (“θεὸς”) የሚለውን የግሪክ ቃል አስመልክቶ የውስን መስተኣምር መኖርም ሆነ ያለመኖር አንዳችም የትርጒም ለውጥ አያስከትልም፡፡ ለምሳሌ:— ሰይጣን “የዚህ ዓለም አምላክ” (2ቆሮ. 4÷4) ተብሎአል፡፡ ነገር ግን ቴዎስ (“θεὸς” አምላክ) ከሚለው ቃል ፊት የተወሰነ መስተኣምር መኖሩ ሰይጣንን እውነተኛ አምላክ አያደርገውም፡፡
በአጠቃላይ “ቴዎስ” (“θεὸς”) ከሚለው ነጠላ ቃል ፊት የተወሰነ መስተኣምር ቢኖርም ባይኖርም ቃሉ እግዚአብሔር ወይም አምላክ (God) ተብሎ መተርጐም ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ዐውዱ እውነተኛውን አምላክ የማያመለክት ከሆነ፣ በእንግሊዝኛው “god” ተብሎ ይተረጐማል፡፡
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ ላይ ብቻ እንኳ፣ “ቴዎስ” (“θεὸς”) የሚለው ቃል፣ የተወሰነ መስተኣምር ሳይኖረው፣ እግዚአብሔር (God) ተብሎ ነው የተተረጐመው (ዮሐ. 1÷1:12:13:18)፡፡ በዮሐንስ 1÷1 ላይ “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር” እግዚአብሔር (ቴዎስ) ከሚለው ቃል ፊት የተወሰነ መስተኣምር አለ፡፡ የትርጒም ይዘቱን ሳይቀይር ቴዎስ የሚለው ቃል ተጠቅሶአል “ቃልም እግዚአብሔር ነበር”፡፡ የተወሰነ መስተኣምር አለ፡፡ የትርጒም ይዘቱን ሳይቀይር “ቴዎስ” (“θεὸς”) የሚለው ቃል የተወሰነ መስተኣምር ሳይኖረው በሚቀጥለው ሐረግ ውስጥ ተጠቅሶአል፣ “ቃልም እግዚአብሔር ነበር” [Ἐν ἀρχῇ ἦν ὁ λόγος, καὶ ὁ λόγος ἦν πρὸς τὸν θεόν, καὶ θεὸς ἦν ὁ λόγος.]፡፡ ከቴዎስ ፊት የተወሰነ መስተኣምር መኖርም ሆነ ያለመኖር አንዳችም የትርጒም ለውጥ እንደማያመጣ የሚከተሉትን ጥቅሶች በአዲሱ ዓለም ትርጒም እንኳ መመልከት ይቻላል (ዮሐ. 3÷2፤ 13÷3፤ ሮሜ 1÷21፤ 1ተሰ. 1÷9፤ ዕብ. 9÷14፤ 1ጴጥ. 4÷11-12) [ለበለጠ መረጃ Robert M. Bowman, Jr., Jesus Christ, and the Gospel of John. (Grand Rapids: Baker, 1989) እንዲሁም Murray J. Harris, Jesus as God: The New Testament Use of Theos in reference to Jesus, (Grand Rapids: Baker, 1992) ይመለከቷል፡፡]፡፡
“ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር” የሚለው ዐረፍተ ነገር የሚያሳየን፣ ቃል የተባለው ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር አብሮ እንዳለና (“ዘንድ”) ቃልም ከእግዚአብሔር አብ የተለየ ህልውና (personality) እንዳለው የሚያስተምረን ነው፡፡ በዚህ ትምህርት፣ “የይሖዋ ምስክሮች” ራሳቸው ይስማማሉ [የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን” አስተማሪዎች፣ አብም ወልድም አንድ ህላዌ አላቸው ከሚለው ትምህርታቸው ጋር ይህን ጥቅስ እንዴት ያስታርቁት ይሆን?]፡፡ ቀጣዩ ዐረፍተ ነገር “ቃልም እግዚአብሔር ነበር” ሲል ቃል የእግዚአብሔር ባሕርይ (Nature) እንዳለው የሚያሳይ ነው እንጂ፣ “የይሖዋ ምስክሮች” እንደሚሉት፣ እግዚአብሔር የሚለው ቃል ከሁሉን ቻዩ እግዚአብሔር ወደ ኀያሉ እግዚአብሔር መለወጡን ለማሳየት ተፈልጎ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ በዮሐንስ 1÷1 ላይ ለማለት የተፈለገው፣ ቃል በእግዚአብሔር አብ ዘንድ እንደ ነበረ፣ እንዲሁም ቃል ራሱ የእግዚአብሔር ባሕርይ (natural) እንዳለው ነው፡፡ ዮሐንስ እግዚአብሔር (ቴዎስ) ከሚለው ቃል ፊት የተወሰነ መስተኣምር (“ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር”) በማድረግ፣ እግዚአብሔር አብን ለማመልከት እንደ ፈለገ ሁሉ ለወልድም “ቃልም እግዚአብሔር ነበር” የተወሰነ መስተኣምር ቢጠቀም ኖሮ “ቃል” የተባለው ክርስቶስ ራሱ እግዚአብሔር አብ ነው የሚል የትርጒም እንድምታ ውስጥ ይከት ነበር፡፡ ዮሐንስ የክርስቶስ ፍጹም አምላክነትና ክርስቶስ ከአብ የተለየ ህላዌ እንዳለው ያሳየው፣ በቴዎስ (“θεὸς”) ፊት ውስን መስተኣምር በማኖርና ባለማኖር ነው፡፡
ምንጭ በተስፋ ዐቃቤያነ እምነት ማሕበር የተዘጋጀ ጽሑፍ ከመጠነኛ ማሻሻያ ጋር፡፡