መላክ ያሕዌ – ክርስቶስ በዘመነ ብሉይ የተገለጠበት መንገድ [ክፍል 2]

መላክ ያሕዌ – ክርስቶስ በዘመነ ብሉይ የተገለጠበት መንገድ [ክፍል 2]

Isaiah 48 Apologetics


በዘፍጥረት 22 ላይ አንድ ብዙዎቻችን የምናውቀው ታሪክ አለ። ይህ ታሪክ አብርሃም በእግዚአብሔር ታዞ ልጁን ይስሃቅን ለመሠዋት የሄደበት ታሪክ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር እሱን መታዘዙን አይቶ ልጁን ከመሠዋት እንዲታቀብ አድርጎታል። በዚህ ስፍራ “የእግዚአብሔር መልአክ” በመባል የሚታወቀው አካል አብርሃምን ያነጋግረዋል። ሲያነጋግረው ግን እንደ ተራ መልእክተኛ ሳይሆን፥ አብርሃምን እንዳዘዘው አምላክ ነው፦

“የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ጠራና። አብርሃም አብርሃም አለው፤  እርሱም እነሆኝ አለ። እርሱም በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፥ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ አለ።” (ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 22፡11᎐2)

እዚህ ጋር እንደምንመለከተው ይህ መለኮታዊ ልዑክ አብርሃም ከእሱ ልጁን እንዳልከለከለበት ይናገራል። ለአብርሃም ልጅህን ሰዋልኝ ያለው እግዚአብሔር ነው። ነገር ግን ይህ መልአክ ልጅህን ከእኔ አልከለከልክም ይለዋል። ይህ መልአክ ልጅህን ከእኔ አልከለከልክም በማለቱ ፍጹም አምላክነቱን አሳይቷል።

በተጨማሪም ይህ አካል ከእራሱ ሌላ እግዚአብሔር በማለት የሚጠራው አካል (person) አለ። እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል በማለትም ይናገራል። ይህ በአምላካችን ውስጥ ያለውን የአካል ብዝኃነት ያሳያል፦

“እንዲህም አለው። እግዚአብሔር። በራሴ ማልሁ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና፥ አንድ ልጅህንም አልከለከልህምና” (ኦሪት ዘፍጥረት 22:16)

ይህ በቀጥታ ከክርስትና አስተምህሮ ጋር አንድ ነው፥ ምክንያቱም ወንጌላችን እንደሚያስተምረን አብ ከልጁ ከኢየሱስ በአካል ይለያልና።  በአካል መለየት ብቻ ሳይሆን ጌታ ኢየሱስ ከአባቱ የሰማውን እንደሚናገር አስተምሯል። እርሱ በራሱ ስልጣን ይናገራል፥ ከአባቱ የሰማውንም ይናገራል። ይህ የብሉይም የአዲስም ትምህርት ነው። ስለዚህ ከዚህ ታሪክ የምንረዳው ይህ በብሉይ ኪዳን በአምሳለ መልአክ ይገለጥ የነበረው፥ ለአብርሃምም ልጅህን ሰዋልኝ ያለው ፍጹም መለኮት የአብ አንዲያ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ነው።



መሲሁ ኢየሱስ