መላክ ያሕዌ – ክርስቶስ በዘመነ ብሉይ የተገለጠበት መንገድ [ክፍል 3]

መላክ ያሕዌ – ክርስቶስ በዘመነ ብሉይ የተገለጠበት መንገድ [ክፍል 3]

የእግዚአብሔር መልአክ በያዕቆብ ሕይወት

Isaiah 48 Apologetics


ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ መልአክ ለያዕቆብ የተገለጠለት በላባ ቤት በነበረበት ወቅት ነበር። በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ከላባ ጋር ተጋጭተው እንደ በፊቱ ያልሆኑበት ጊዜ ነበር። ይህም መልአክ ምን እንደሚል እንመልከት፦

የእግዚአብሔርም መልአክ በሕልም። ያዕቆብ ሆይ አለኝ፤ እኔም። እነሆኝ አልሁት። እንዲህም አለኝ። ዓይንህን አቅንተህ እይ፤ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ናቸው፤ ላባ በአንተ ላይ የሚያደርገውን ሁሉ አይቼአለሁና። ሐውልት የቀባህበት በዚያም ለእኔ ስእለት የተሳልህበት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ፤ አሁንም ተነሥተህ ከዚህ አገር ውጣ፥ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመለስ።” (ዘፍጥረት 31፡11-13)

እዚህ ጋር እንደምናስተውለው፥ ይህ መልአክ ላባ የሚያደርግበትን እንደተመለከተ ይነግረዋል። የሰውን መገፋት ተመልክቻለሁ ማለት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

“እግዚአብሔርም አለ። በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፥ ከአስገባሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ”
(ኦሪት ዘጸአት 3:7)

ይህ መልአክ “የሚደርስብህን አይቻለሁ” በማለቱ እንደ ማንኛውም መልእክተኛ አለመሆኑን እንረዳለን። “የሚደርስብህን አይቻለሁ” ሲል አምላክነቱን ነው የሚያሳየው። አስተውሉ! ይህ መልአክ ሲናገር እግዚአብሔር እንዲህ ይላል አላለም። እንደ ባለስልጣን ነው የሚናገረው። ቀጥሎም በጣም አስገራሚ ነገርን ይናገራል። ያዕቆብ በቤቴል ሐውልትን በመቀባት የተሳለበት አምላክ እሱ መሆኑን ይናገራል። ይህንን ታሪክ እንመልከት፦

ያዕቆብም ማልዶ ተነሣ፥ ተንተርሶት የነበረውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፥ በላዩም ዘይትን አፈሰሰበት። ያዕቆብም ያንን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው፤ አስቀድሞ ግን የዚያች ከተማ ስም ሎዛ ነበረ። ያዕቆብም እንዲህ ብሎ ስእለት ተሳለ። እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን፥ በምሄድባትም በዚች መንገድ ቢጠብቀኝ፥ የምበላውንም እንጀራ የምለብሰውንም ልብስ ቢሰጠኝ፥ ወደ አባቴ ቤትም በጤና ብመለስ፥ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል፤ ለሐውልት የተከልሁት ይህም ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል፤ ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከአሥር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ።” (ዘፍጥረት 28፡18-22)

እዚህ ጋር በግልጽ እንደምንመለከተው፥ ያዕቆብ የእግዚአብሔርን ስም በመጥራት ለእግዚአብሔር ስዕለትን ያቀርባል። ሲሳልም ሐውልትን በመቀባት ነው። ይህ መልአክ ያዕቆብ የተሳለለት አምላክ እሱ መሆኑን ለያዕቆብ ይነግረዋል። ልብ በሉ! ይህ መልአክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በማለት አይደለም የተናገረው። እሱ ራሱ ነው፥ “እኔ ነኝ” ያለው። ይህ የእሱን ማንነት በግልጽ ያሳየናል። እግዚአብሔር መሆኑን ተናግሯልና። ከዚህ ምዕራፍ የምንረዳው፥ ይህ መለኮታዊ ልዑክ፥ ራሱን በአካል (person) ከላኪው ከእግዚአብሔር ቢለይም ፍጹም አምላክ መሆኑን እንረዳለን። ይህ ደግሞ ከወንጌል አስተምህሮ ጋር አንድ ነው። አብ እና ልጁ ኢየሱስ በአካል ሁለት ናቸው፤ ስለዚህ የያዕቆብን መከራ ያየው መልአክ፥ በቤቴል ያዕቆብ የተሳለለት እግዚአብሔር በአምሳለ መልአክ የተገለጠው ጌታ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ይህንን የሚያጠናክር ሌላ ጥቅስ እንመልከት፦

ያዕቆብ ግን ለብቻው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስከ ንጋት ድረስ ይታገለው ነበር። … እንዲህም አለው። ሊነጋ አቀላልቶአልና ልቀቀኝ። እርሱም። ካልባረክኸኝ አልለቅቅህም አለው። … አለውም። ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ያዕቆብ አይባል፤ ከእግዚአብሔር ከሰውም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና። ያዕቆብም። ስምህን ንገረኝ ብሎ ጠየቀው። እርሱም። ስሜን ለምን ትጠይቃለህ? አለው። በዚያም ስፍራ ባረከው።” (ዘፍጥረት 32፡24-29)

በዚህ ስፍራ ያዕቆብ መሄጃ አጥቶ፥ ከወንድሙ ከዔሳው ማምለጫ አጥቶ እንመለከተዋለን። መላውን ቤተሰቡን እና ንብረቱን ወደ ፊት ልኮ፥ እሱ ብቻውን በያቦቅ ወንዝ ማዶ ቀረ። በዚህም ሰዓት አንድ ሰው መጥቶ ሌሊቱን በሙሉ ታገለው። ከዚያም ሊነጋ ሲያቅላላ ይህ ሰው ያዕቆብን ባርኮት፥ ስሙን ይለውጥለታል። ከዚያም ከእግዚአብሔር እና ከሰው ጋር ታግለህ አሸንፈሃል በማለቱ፥ አምላክነቱን አሳየው። ያዕቆብ ከአምላክ ጋር ታግሏልና። ይህ እንዴት ጌታ በአምሳለ መልአክ ተገለጠ ከሚባለው ትምህርት ጋር ይሄዳል? ይህ የሆነበት ምክንያት፥ በኋላ የመጡት ነቢያት ያንን መለኮታዊ አካል የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን በማስተማራቸው ምክንያት ነው፦

በማኅፀን ውስጥ ወንድሙን በተረከዙ ያዘው፥ በጕልማስነቱም ጊዜ ከአምላክ ጋር ታገለ፤ ከመልአኩም ጋር ታግሎ አሸነፈ፤ አልቅሶም ለመነው። በቤቴልም አገኘው፥ በዚያም ከእኛ ጋር ተነጋገረ።” (ሆሴዕ 12፡4-5)

ልብ በሉ! እግዚአብሔር በነብዩ ሆሴዕ በኩል፥ ያዕቆብ የታገለው አምላክን፥ ታግሎ ያሸነፈውም መልአኩን መሆኑን ይናገራል። ያዕቆብ አንዴ አምላክን አንዴ መልአክን አልታገለም፥ አንድ አካልን አንዴ ነው የታገለው። በዚህ ስፍራ ያዕቆብ የታገለውን መልአክ እግዚአብሔር፥ አምላክ በማለት ይጠራዋል። ይህ እግዚአብሔር ወልድ በአምሳለ መልአክ ይገለጥ እንደነበር ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው።

መጽሐፍ ቅዱሳችን እንደሚናገርው አብ ተገልጦ አይታይም (ዮሐ 1:18) ነገር ግን አንድ ልጁ ይተርከዋል። ስለዚህ ለያዕቆብ በአምሳለ መልአክ በመገለጥ፤ ስሙን በመለወጥ፥ የባረከው አምላክ ጌታ ኢየሱስ የአብ አንዲያ ልጅ ነው። አንድ ተጨማሪ ጥቅስ እንመልከትና ይህንን ክፍል እንቋጫለን፦

ያዕቆብም ዮሴፍን ባረከ እንዲህም አለ። አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር፥ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፥ ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ፤ ስሜም የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅም ስም በእነርሱ ይጠራ፤ በምድርም መካከል ይብዙ።” (ዘፍጥረት 48፡15-16)

እዚህ ጋር ያዕቆብ በሕይወቱ የመጨረሻ ወራት ላይ ይገኛል። ልጁ ዮሴፍ የራሱን ልጆች ምናሴን እና ኤፍሬምን ይባርካቸው ዘንድ ወደ ያዕቆብ ያመጣቸዋል። ያዕቆብም በእግዚአብሔር ስም ይባርካቸዋል። ሲባርካቸው ግን እርሱን ከክፉ ነገር ባዳነው መልአክ ስም ይባርካቸዋል። ይህ መልአክ ከወንድሙ ከዔሳው ያዳነው፥ “ከእግዚአብሔር ጋር ታግለሃልና” በማለት አምላክነቱን የገለጠው አካል ነው (ሆሴዕ 12:3-4)። እዚህ ጋር ደግሞ ያዕቆብ በእሱ ስም በረከትን ያስተላልፋል። በየትኛውም የእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በረከት በፍጡር ስም አይሰጥም፤ ማንምም በፍጡር ስም አይባርክም። በእግዚአብሔር ስም ብቻ ነው በረከት የሚሰጠው። ያዕቆብ በዚህ መልአክ ስም በረከትን መባረኩ፥ ይህ መልአክ ተራ ፍጡር አለመሆኑን ያስረዳል። ከዚህም በላይ ያዕቆብ ይህንን መልአክ የሚገልጥበት አገላለጽ አለ። “ከክፋ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ” በማለት ይገልጠዋል። መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስናጠና፥ ከእግዚአብሔር ውጪ አዳኝ እንደሌለ እንረዳለን፦

” እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም።” (ኢሳይያስ 43፡11)

ይህ መልአክ የያዕቆብ አዳኝ ነው። በእግዚአብሔር አሠራር ውስጥ ደግሞ ከእግዚአብሔር ውጪ አዳኝ የለም። ያዕቆብ ይህንን መልአክ አዳኝ በማለቱ ፍጹም አምላክነቱን ገልጾልናል። ከእግዚአብሔር በቀር የሚያድን የለምና! ስለዚህ ይህንን እና ሌሎች ተጓዳኝ የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍሎች በማገናዘብ ያዕቆብን ያዳነው አዳኝ በአምሳለ መልአክ የተገለጠለት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ መሆኑን እንረዳለን።



መሲሁ ኢየሱስ