መላክ ያሕዌ – ክርስቶስ በዘመነ ብሉይ የተገለጠበት መንገድ [ክፍል 5]
ከዚህ በፊት እያየን እንደመጣነው፥ ጌታ ኢየሱስ በአምሳለ መልአክ በብሉይ ኪዳን ተገልጦ ነበር። መልአክ ማለትም መልእክተኛ ማለት ብቻ እንደሆነና የመልእክተኛውን ማንነት ማወቅ የምንችለው በአውዱ እንደሆነ አይተናል። በዚህ ጽሑፍ ደግሞ በመጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ የሚገኙ መሰል ጥቅሶችን እንዳስሳለን።
“የእግዚአብሔርም መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ። እኔ ከግብፅ አውጥቻችኋለሁ፥ ለአባቶቻችሁም ወደ ማልሁላቸው ምድር አግብቻችኋለሁ፤ እኔም። ከእናንተ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ለዘላለም አላፈርስም፤ እናንተም መሠዊያቸውን አፍርሱ እንጂ በዚህች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ አልሁ። እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም።” (መሳፍንት 2፡1-2)
በዚህ ስፍራ የእግዚአብሔር መልእክተኛ (መልአክ) ከጌልገላ ወደ ቦኪም ሲወጣ እንመለከታለን። ይህ ጊዜ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር የገቡበት ዘመን ነበር። ነገር ግን ጣዖት አምላኪ ከነበሩት አሕዛብ ጋር በአንድ ላይ መኖር ጀመሩ ( መሳ 1:28-30 )። እነዚያን አሕዛብ ከመካከላቸው ስላላስወጧቸው እግዚአብሔር አዝኖባቸው ነበር። ቀጥለን እንደምንመለከተው፥ ይህ መልእክተኛ እንደ ተራ መልእክተኛ ሳይሆን ከግብጽ እንዳወጣቸው እግዚአብሔር ይናገራል። ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደምንረዳው፥ እግዚአብሔር ብቻ ነው የእስራኤልን ህዝብ ከባርነት ያዳነው፦
“እግዚአብሔር ብቻውን መራው፤ ከእርሱም ጋር ሌላ አምላክ አልነበረም።” (ዘዳግም 32፡12)
ተመልከቱ፥ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እግዚአብሔር ብቻ የእስራኤልን ሕዝብ እንዳወጣ ተናግሯል። ይህ መልእክቸኛ ግን እኔ አወጣዋችሁ ይላል። ቀጥሎም፥ አንድ በጣም የሚገርም ነገር ይናገራል። “ለአባቶቻችሁ ወደ ማልሁላቸው” ይላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሁ፥ ለእስራኤል አባቶች ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ መሃላን የማለላቸው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ሌላ ፍጡር ለአባቶች አልማለም። ይህ መልአክ ግን ለአባቶቻችሁ ወደ ማልኩት ይላል። ለዚያም ነው ያዕቆብ ልጆቹን በሚባርክበት ሰዓት እንዲህ ብሎ የባረካቸው፦
“ያዕቆብም ዮሴፍን ባረከ እንዲህም አለ። አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር፥ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፥ ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ፤ ስሜም የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅም ስም በእነርሱ ይጠራ፤ በምድርም መካከል ይብዙ።” (ዘፍጥረት 48፡15-16)
ያዕቆብ በዚህ መልእክተኛ ስም የባረካቸው ፍጹም መለኮት ስለሆነና በዘመኑ ሁሉ ስለመራው ነው። ስለዚህ ይህ መልእክተኛ፥ “ለአባቶቻችሁ ለማልኩላቸው” ሲል የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ ነኝ ማለቱ ነው። ለዚያም ነው በአዲስ ኪዳን ሐዋርያቱ፥ ጥንት የእስራኤል ልጆችን ከባርነት ነጻ ያወጣቸው ኢየሱስ ነው ያሉት
“ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ። ዳሩ ግን ሁሉን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ምንም የተማራችሁ ብትሆኑ ጌታ ከግብፅ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ። (የይሁዳ መልእክት 1፡4-5)
ይህ እውነታ በብሉይ ኪዳን በአምሳለ መልአክ ይገለጥ የነበረው ፍጹም እግዚአብሔር የሆነው አካል ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ያረጋግጣል፤ ምክንያቱም ይህ መልእክተኛ የሚናገረውን ነገር ከእግዚአብሔር በቀር የትኛውም ፍጡር ሊናገረው አይችልምና።
በማስከተል ደግሞ በጌዴዎን ሕይወት እንዴት እንደተገለጠ እንመለከታለን።
“የእግዚአብሔርም መልአክ መጥቶ በዖፍራ ባለችው ለአቢዔዝራዊው ለኢዮአስ በነበረችው በአድባሩ ዛፍ በታች ተቀመጠ፤ ልጁም ጌዴዎን ከምድያማውያን ለመሸሸግ በወይን መጥመቂያው ውስጥ ስንዴ ይወቃ ነበር። የእግዚአብሔርም መልአክ ለእርሱ ተገልጦ። አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው አለው።” (መሳፍንት 6፡11-12)
ይህ ክፍል፥ እስራኤላውያን በምድያማውያን ተጨቁነው የነበሩበትን ዘመን ያስነብበናል። የአይሁድ ሕዝብ ኃጢአት በሠራ ቁጥር፥ በአሕዛብ ይጨቆናል። ንሰሃ በገባ ጊዜም እግዚአብሔር መሳፍንት አስነስቶ ነጻ ያወጣዋል። አሁንም እንዲሁ፥ እግዚአብሔር የእስራኤልን ህዝብ ነጻ ለማውጣት ወደ ጌዴዎን ሲሄድ እንመለከታለን። ከዚያም ይህ መልእክተኛ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደሆነ ለጌዴዎን ይነግረዋል። አስተውሉ! ይህ ልዑክ ራሱ መለኮት ሆኖ፥ ስለ ሌላ መለኮት ስለሆነ አካል/person ይናገራል። ይህ ደግሞ ከአዲስ ኪዳን መገለጥ ጋር ይስማማል። ከዚያም የሚለውን እንመልከት፦
“ጌዴዎንም። ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ። እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ? ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፥ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል አለው። እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ። በዚህ በጕልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን፤ እነሆ፥ ልኬሃለሁ አለው።” (መጽሐፈ መሳፍንት ምዕራፍ 6:13-14)
በዚህ ቦታ ጌዴዎን “እግዚአብሔር ከኛ ጋር እንደ ጥንቱ ቢሆን ኖሮ ይህ ለምን ይሆን ነበር? እግዚአብሔር ትቶናል” በማለት ኅዘኑን ይነግረዋል። ከዚያም ይህ መልእክተኛ፥ ጌዴዎንን በጉልበቱ እንዲሄድና እስራኤልን እንዲያድን እንደላከው ይነግረዋል። አስተውሉ! በመሳፍንት መጽሐፍ ሁሉ መሳፍንትን የሚያስነሳው እግዚአብሔር ብቻ ነው። የአይሁድ ሕዝብም በኃጢአቱ ሲጨቆን፥ መስፍንን እንዲያስነሳለት የሚለምነው እግዚአብሔርን ብቻ ነው (መሳ 2:16፣ 2:18)። ነገር ይህ መልእክተኛ ጌዴዎንን፥ እንደ መስፍን ለእስራኤል ህዝብ አዳኝ አድርጎ እንደላከው ይናገራል። ይህ ፍጹም መለኮት መሆኑን ያሳየናል።
ይህን መልእክተኛ እግዚአብሔር መሆኑን የሚያሳያን ከዚህ የበለጠ ማሳያ አለ፦
“እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ። በዚህ በጕልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን፤ እነሆ፥ ልኬሃለሁ አለው።” (መሳፍንት 6:14)
አስተውሉ! ጌዴዎን፥ “እግዚአብሔር ትቶናል፥ እንደ ጥንቱ ከኛ ጋር ቢሆን ኖሮ” እያለ ሲናገር የነበረው ለመልአኩ ነበር። ነገር ግን ለእርሱ ዘወር ብሎ መለሰለት የተባለው እግዚአብሔር ነው። በዚህ ስፍራ መልእክተኛው “እግዚአብሔር” ተብሎ ሲጠራ እንመለከታለን፤ እርሱ ነውና ለጌዴዎን ዘወር ብሎ የመለሰለት። በተጨማሪም፥ ዘወር ብሎ በማለቱ በሰው መልክ (human appearance) ነበር ማለት ነው።
ይህ መልእክተኛ (በቁ.14) የተጠራበት ስም በዕብራይስጡ “ያሕዌ/יהוה” የሚል ነው። ይህ ስም የእግዚአብሔር የተፀዋዖ ስም ሲሆን፥ ለየትኛውም ፍጡር አይሰጥም። ይህ ልዑክ በዚህ ስም መጠራቱ ፍጡር አለመሆኑን ያሳየናል።
ከዚያም ጌዴዎን እንዴት እስራኤልን ሊያድን እንደሚችል ይጠይቀዋል
“እርሱም። ጌታ ሆይ፥ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፤ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ አለው። እግዚአብሔርም በእርግጥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ምድያምንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታለህ አለው።” (መሳፍንት 6፡15-16)
ተመልከቱ፥ አሁንም ጌዴዎን የሚያዋራው አካል እግዚአብሔር/יהוה ተብሎ እየተጠራ ነው። መልእክተኛው እግዚአብሔር መሆኑን ያጸናልናል.
ከዚህ በፊት እንደተነጋገርነው፥ መልአክ ማለት መልእክተኛ ማለት ብቻ ነው። አንድ አካል መልአክ ተብሎ ስለተጠራ ብቻ ፍጡር መንፈስ አይደለም። የአካሉ/person ምንነት የሚታወቀው በአውዱ ነው። ይህ ደግሞ ከአዲስ ኪዳን ትምህርት ጋር ይስማማል። አብ ልጁን ወደ አለም ልኮታልና (ሮሜ 8:3)።
ሌላው ነገር ይህ እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራው መልአክ፥ በጦርነት ከእርሱ ጋር እንደሆነ ለጌዴዎን ይነግረዋል። ይህ ቃል፤ መልአኩ ተራ ፍጡር መንፈስ ሳይሆን ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ምክንያቱም፥ በሰልፍና በውጊያ ከብሉይ ኪዳን አባቶች ጋር የሚሆነው እውነተኛው አምላክ ብቻ ነውና።
“በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ አልተውህም።” (ኢያሱ 1:5፣ ተጓዳኝ ጥቅስ መዝ 144:1)።
ይህን ልዑክ፥ በውጊያ ከጌዴዎን ጋር እሆናለሁ በማለቱ፥ እግዚአብሔር መሆኑን ያሳየናል። ቀጥሎ እንደዚህ ይላል፦
“እርሱም። ጌታ ሆይ፥ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፤ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ አለው። እግዚአብሔርም። በእርግጥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ምድያምንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታለህ አለው። እርሱም። በአንተ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ፥ የምትናገረኝም አንተ እንደ ሆንህ ምልክት አሳየኝ።” (መሳፍንት 6፡15-17)
በዚህ ክፍል ጌዴዎን ከዚህ መልአክ ጋር የሚያደርገውን ንግግር ይቀጥላል። ይህ ንግግር ከቁ.14 የቀጠለ ሲሆን፥ መልአኩ እግዚአብሔር/ያሕዌ ተብሎ ተጠርቷል። እርሱም ምድያምን እንደ አንድ ሰው እንደሚመታ ይነግረዋል። ጌዴዎንም በቁ.17 ላይ ይህ አካል በእርግጥም እርሱ መሆኑን እንዲያረጋግጥለት ምልክትን ይጠይቀዋል። በፊትህ ሞገስ ካገኘው አንተ መሆንህን አረጋግጥልኝ ሲለው ምን ማለቱ ነው?
ጌዴዎን እግዚአብሔር የጥንት አባቶቻቸውን እንዴት እንዳዳናቸው ያውቃል። ያዳናቸው ይህንን መልእክተኛ በመላክ ነበር።
በዘጸአት 3 ላይ እንደተመለከትነው፥ ለሙሴ የተገለጠለት እርሱ ነው (ዘጸ 3:2) ከግብጻዊያን ያዳናቸው እርሱ ነው (ዘጸ 3:8) ሙሴንም የላከው እርሱ ነው (ዘጸ 3:10) እግዚአብሔርም ነኝ ያለው እርሱ ነው (ዘጸ 3:16)።
ጌዴዎንም እርሱን እንደ እግዚአብሔር የሚያዋራው አካል ያ ለሙሴ የተገለጠው አምላክ መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋል። ያኔ አባቶቻቸውን ሙሴን በመላክ ከግብጻውያን እንዳዳናቸው ሁሉ እርሱን በመላክ ከምድያማውያን እንዲያድናቸው ይፈልጋልና። ከዚያም የጠየቀውን ምልክት እናነባለን፦
“ወደ አንተም እስክመለስ ድረስ፥ ቍርባኔንም አምጥቼ እስካቀርብልህ ድረስ፥ እባክህ፥ ከዚህ አትላወስ አለው። እርሱም። እስክትመለስ ድረስ እቆያለሁ አለ። ጌዴዎን ገባ የፍየሉንም ጠቦት የኢፍ መስፈሪያም ዱቄት የቂጣ እንጎቻ አዘጋጀ፤ ሥጋውን በሌማት አኖረ፥ መረቁንም በምንቸት ውስጥ አደረገ፥ ሁሉንም ይዞ በአድባሩ ዛፍ በታች አቀረበለት።” (መሳፍንት 6፡18-19)
ጌዴዎን የጠየቀው ምልክት፥ ለዚህ አካል መስዋዕትን ማቅረብ ነበር። መስዋዕቱን ከተቀበለው፥ በእርግጥም ለሙሴ የተገለጠለት መልእክተኛ መሆኑን ያረጋግጣል። አስተውሉ! ጌዴዎን ይህ አካል ለሙሴ የተገለጠው መሆኑን ለማረጋገጥ መስዋዕት መሰዋቱ፥ በእርግጥም ይህ ልዑክ ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ያሳያል፤ ምክንያቱም በኦሪት ሕግ መሠረት ለየትኛውም ፍጡር መስዋዕት ማቅረብ የተከለከለ ነው (ዘጸ 23:24)። የትኛውም የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ፍጡር መስዋዕት ተቀብሎ አያውቅም። ነገር ግን ለዚህ መልአክ መስዋእቱን ማቅረቡ ይህ አካል መለኮት መሆኑን ያሳየናል። በተጨማሪም “አትላወስ” በማለቱ በሰው አምሳል ተገልጦ እንደነበር እንረዳለን።
“የእግዚአብሔርም መልአክ። ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ ወስደህ በዚህ ድንጋይ ላይ አኑር፥ መረቁንም አፍስስ አለው። እንዲሁም አደረገ። የእግዚአብሔርም መልአክ በእጁ ያለውን የበትሩን ጫፍ ዘርግቶ ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ አስነካ፤ እሳትም ከድንጋዩ ውስጥ ወጥቶ ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ በላ። የእግዚአብሔርም መልአክ ከዓይኑ ተሰወረ።” (መሳፍንት 6፡20-21)
እጅግ አስገራሚ ነው! ከላይ “መስዋዕት ተቀበለ፥ አትላወስ ተባለ” የተባለለት አካል እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ ቁ.21 ላይ ይህንን አደረገ የተባለው የእግዚአብሔር መልአክ ሆኖ እናገኘዋለን። ከዚያም በበትሩ ጫፍ፥ የቀረበውን የእህል መስዋዕት ተቀበለ። ይህ እርሱ መስዋዕት ተቀባይ መለኮት መሆኑን ከምንም በላይ ያሳየናል።
ጌዴዎን ሕግ ከተሰጠ በኋላ የኖረ ሰው ቢሆንም፥ ለዚህ አካል መስዋዕት አቀረበ። መለኮት መሆኑን ያውቃልና።
“ጌዴዎንም የእግዚአብሔር መልአክ እንደ ሆነ አየ፤ ጌዴዎንም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወዮልኝ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና አለ።” (መሳፍንት 6:22)
ይህ ከሆነ በኋላ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ይሰወራል። በዚህም ምክንያት ጌዴዎን እርሱን ስላየው እንዳይሞት ፈራ። ጌዴዎን የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ካወቀ በኋላ፥ እርሱን ስላየሁ እሞታለሁ ብሎ ለምን ፈራ? ይህ የሆነው፥ በኦሪት ሕግ መሠረት ማንም እግዚአብሔርን አይቶ መትረፍ እንደማይችል ስለተጻፈ ነው (ዘጽ 33:20)። ጌዴዎን ያየው አካል/person መልእክተኛ መሆኑን ቢያውቅም፥ መለኮት መሆኑን ስላወቀ እሱን በማየቱ ለህይወቱ ፈራ።
እናስታውስ! ማንም አብን አይቶት አያውቅም፥ ነገር ግን አንድ ልጁ ተረከው (ዮሐ 1:18)፤ ስለዚህ በዚህ ስፍራ በአምሳለ መልአክ የተገለጠለት አምላክ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድመ ሥጋዌው መሆኑን እንረዳለን።
- መላክ ያሕዌ – ክርስቶስ በዘመነ ብሉይ የተገለጠበት መንገድ [ክፍል 1]
- መላክ ያሕዌ – ክርስቶስ በዘመነ ብሉይ የተገለጠበት መንገድ [ክፍል 2]
- መላክ ያሕዌ – ክርስቶስ በዘመነ ብሉይ የተገለጠበት መንገድ [ክፍል 3]
- መላክ ያሕዌ – ክርስቶስ በዘመነ ብሉይ የተገለጠበት መንገድ [ክፍል 4]
- መላክ ያሕዌ – ክርስቶስ በዘመነ ብሉይ የተገለጠበት መንገድ [ክለሳ]