መላክ ያሕዌ – ክርስቶስ በዘመነ ብሉይ የተገለጠበት መንገድ [ክለሳ]

መላክ ያሕዌ – ክርስቶስ በዘመነ ብሉይ የተገለጠበት መንገድ [ክለሳ]

ሁሉን ተመልካቹ የእግዚአብሔር መልአክ

Isaiah 48 Apologetics


ባለፉት ተከታታይ ክፍሎች እንዴት የእግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር መልአክ ተብሎ ይጠራ እንደነበር በስፋት ለማየት ሞክረን ነበር።

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለማሳየት እንደሞከርነው፤ መልአክ ማለት መልእክተኛ ማለት ነው። አሠራርን እንጂ ባሕርይን የሚያሳይ ቃል አይደለም። የተላከ ማንኛውም አካል መልአክ ተብሎ ይጠራል። ይህ ቃል ለመለኮት (ዘፍ 48:15-16 ዘፍ 21:17-18) ለፍጡራን መናፍስት (ዘፍ 32:1 መዝ 148:2) እና ለሰዎች (2 ሳሙ 3:12 ሐጌ 1:13) ጥቅም ላይ ውሏል። የመልአኩ ባሕርይ ምን እንደሆነ የሚለየው በዙሪያው ባለው አውድ ነው።

ይህ የእግዚአብሔር መልአክ ግን በባሕርዩ መለኮት ነው (ዘጽ 23:21) አምላክ ነው (ዘጽ 3:6) ያሕዌ ነው (ዘካ 3:2) ተመልኳል (መሳ 6:18 ኢያ 5:15) እግዚአብሔር ራሱም ያሕዌ በማለት ጠርቶታል (ዘጽ 24:1 ዘጽ 23:25) አምላክ ብሎታል (ሆሴ 12:6) አስመልኮታል (ዘፍ 35:1) መልአክ ተብሎ የተጠራው የአባቱ መልእክተኛ ስለሆነ እንጂ ፍጡር ስለሆነ አይደለም።

 ዛሬም ከእነዚህ ክስተቶች መካከል አንዱን ለመመልከት እንሞክራለን።

 “እርስዋም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ኤልሮኢ ብላ ጠራች፤ የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን? ብላለችና።” (ኦሪት ዘፍጥረት 16:13)

 በዚህ ስፍራ አጋር ከእመቤትዋ ከሦራ ስትሸሽ የተከሰተውን ታሪክ እናነባለን። እርሷ ከአብርሃም ልጅን ከጸነሰች በኋላ መካን የነበረችውን እመቤቷን ማቃለል ጀመረች። በዚህም ግዜ ሦራ እርሷን ማሰቃየት ስትጀምር ወደ ምድረ በዳ ኮበለለች

ከዚያም ወደ ውኃው ምንጭ አጠገብ ስትደርስ፥ አንድ ያልጠበቀችው እንግዳ ተገናኛት፦

የእግዚአብሔር መልአክም በውኃ ምንጭ አጠገብ በበረሀ አገኛት፤ ምንጩም ወደ ሱር በምትወስደው መንገድ አጠገብ ነው።” (ኦሪት ዘፍጥረት 16:7)

ያ እንግዳ የእግዚአብሔር መልአክ ነበር። በውኃው ምንጭ አጠገብ የተገናኛት እርሱ ነው። ወደ እመቤትዋ እንድትመለስ፥ ከእጅዋ በታችም እንድትገዛ ከነገራት በኋላ፤ ዘሯን እጅግ እንደሚያበዛው፥ ከብዛቱም የተነሳ የማይቆጠር እንደሚሆን ቃል ይገባላታል (ዘፍ 16:10)።

የአንድን ሰው ዘር ማብዛት የሚችለው መለኮት ነው (ዘፍ 13:16 ዘፍ 22:17 ዘፍ 26:4) የትኛውም ፍጡር እንዲህ ብሎ አያውቅም። ስለዚህ አጋርን እያነጋገራት ያለው ፍጡር አይደለም ማለት ነው። ይህንንም የተረዳችው አጋር፥ የሚያነጋግራትን አካል በቁ.13 ላይ እንዲህ ብላ ትሰይመዋለች።

እርስዋም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ኤልሮኢ ብላ ጠራች፤ የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን? ብላለችና።” (ኦሪት ዘፍጥረት 16:13)

አንኳር ሀሳቦቹን ነጥብ በነጥብ ለመመልከት እንሞክር

  1. አጋርን የሚያነጋግራት አካል “እግዚአብሔር/ያህዌ” ተብሎ ተጠርቷል

በቁ.13 ላይ “እርሷም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም..” ይላል። የመጽሐፉ ተራኪ አጋርን ሲያናግራት የነበረው እግዚአብሔር ነው እያለ ነው። እርሱን ኤልሮኢ ብላ እንደሰየመችው የነገረን ተራኪው ነውና። ይህ በግልጽ እንደሚያሳየው የመጽሐፉ ተራኪም ልክ እንደ አጋር እርሷን ያነጋገራት እግዚአብሔር መሆኑን ያምን እንደነበር ነው። ተገለጠ የተባለው ግን መልአኩ ነው (ቁ.7) ሲያናግራት የነበረውም እርሱ ነው። እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራው እርሱ ነው ማለት ነው

ሲቀጥል፥ ተራኪው ለመልአኩ ያዋለው ስም “ያሕዌ” መሆኑ ነው። ያሕዌ ለመለኮት ብቻ የሚሰጥ የእግዚአብሔር ስም ነው (ዘጽ 3:16) ይህ መልአኩ ፍጡር አለመሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው

“And she called the name of the LORD that spake unto her, Thou God seest me: for she said, Have I also here looked after him that seeth me?” (Genesis 16:13)

ותקרא שם יהוה הדבר אליה אתה אל ראי כי אמרה הגם הלם ראיתי אחרי ראי

  1. አጋር ይናገራት የነበረውን ኤልሮኢ በማለት ጠርታዋለች

አጋር ይናገራት የነበረውን ያህዌ “ኤልሮኢ” በማለት ጠርታዋለች። ኤልሮኢ የሚለው ቃል ከሁለት የዕብራይስጥ ቃላት “ኤል/אל” እና “ራይ/ראי” የተዋቀረ ቃል ሲሆን “የሚያየው አምላክ” ወይንም “The God who sees” ማለት ነው። አጋር ይናገራት የነበረውን እግዚአብሔር “የሚያየው አምላክ” በማለት ጠርታዋለች።

ለእርሷ የተገለጠው ግን መልአኩ ነበር (ቁ.7) ሲያነጋግራት የነበረውም እርሱ ነበር (ቁ.8-12) ይህ ማለት “ኤልሮኢ” ተብሎ የተጠራው እርሱ ነው ማለት ነው። የሚያየው አምላክ መልእክተኛው ነው። ይህም እውነት በቀጣዩ ሀረግ በይበልጥ ተረጋግጦ እናገኘዋለን

“..የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን?...” (ቁ.13)። አጋር ኤልሮኢ በማለት የጠራችው ያየችውን ነው። የሚያያትን እርሱን አየችው። ለእርሷ ግን የተገለጠው መልአኩ ነበር። ይህ ያለ ምንም ውዥንብር “የሚያየው አምላክ” ብላ የጠራችው መልአኩን እንደሆነ ያረጋግጣል።

  1. አጋር መልአኩን “የሚያየኝ” በማለት ጠርታዋለች

አጋር እርሷን ያነጋገራት አካል እርሷን የሚያያት መሆኑን መስክራለች። እርሷን ሁሌም ሲያያት የነበረውን አሁን ስላየችው ነው አልሮኢ ብላ ሰይማው “የሚያየኝን አየሁት” ያለችው።

መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስናጠና፤ የሰውን ልጅ አኗኗርና መንገድ የሚመለከተው፥ እግዚአብሔር መሆኑን እንረዳለን

ዓይኖቹ በሰው መንገድ ላይ ናቸው፥ እርምጃውንም ሁሉ ያያል።” (መጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ 3421)

ይህ ማለት ይህ መልአክ ሁሌም እርሷን ያያት እንደነበርና ከእርሱ እይታ ውጪ ሆና እንደማታውቅ ያሳያል። ያንን የሚያያትን አየችው። ስለዚህ ይህ መልእክተኛ እግዚአብሔር ነው ማለት ነው

  1. ስፍራ በመለኮታዊ ስም (theophoric name) ተጠርቷል

ስለዚህም የዚያ ጕድጓድ ስም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ ተጠራ፤ እርሱም በቃዴስና በባሬድ መካከል ነው።” (ኦሪት ዘፍጥረት 16:14)

መልአኩ ለአጋር ከተገለጠላት በኋላ፤ ያ ስፍራ “ብኤርለሃይሮኢ” ተብሎ ተጠርቷል። የስያሜውም ትርጉም “ተመልካቼ የሆነው የሕያዉ ምንጭ” ማለት ሲሆን መለኮታዊ ስያሜ ወይንም theophoric name ይባላል።

መለኮታዊ ስም፥ በአንድ ስፍራ አምላክ ሲገለጥ ያ ስፍራ የሚጠራበት ስያሜ ነው። ሁሌም የእግዚአብሔርን ስም ወይንም ባህርይ የያዘ ቃል ሲሆን፥ እግዚአብሔር በዚያ ስፍራ ተገልጦ የሰራውን ስራ የሚገልጽ ስም ነው።

ለምሳሌ

“አብርሃምም ያንን ቦታ ያህዌ_ይርኤ ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእግዚአብሔር ተራራ ይታያል ይባላል።” (ኦሪት ዘፍጥረት 22:14)

አብርሃም ልጁን ሊሰዋ በየነበረበትን ስፍራ “ያህዌ ይርኤ” በማለት በመለኮታዊ ስም ሲጠራው እንመለከታለን። ያህዌ ይርኤ ማለት እግዚአብሔር ያያል ማለት ሲሆን፥ እግዚአብሔር በልጁ በይስሐቅ ፈንታ የመስዋዕቱን በግ ስላዘጋጀለት ቦታውን እንዲህ ብሎ ሊሰይመው ችሏል

ሌላ ምሳሌ:-

ያዕቆብም። እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፥ ሰውነቴም ድና ቀረች ሲል የዚያን ቦታ ስም ጵኒኤል ብሎ ጠራው።” (ኦሪት ዘፍጥረት 32:30)

በዚሁ ስፍራም ያዕቆብ እግዚአብሔር የተገለጠለትን ቦታ “ጵኒኤል” በማለት በመለኮታዊ ስም ሲጠራው እንመለከታለን። ጵኒኤል ማለት የእግዚአብሔር ፊት ማለት ሲሆን፥ እግዚአብሔርን ስላየ (ቁ.30) ደግሞም ስለታገለው እንዲህ በማለት ቦታውን ጠርቶታል።

አጋርም እንዲሁ መልአኩ ስለተገለጠላት፥ ያ ቦታ “ብኤርለሃይሮኢ” ተብሎ ተጠራ። የተመልካቹና የሕያዉ ምንጭ ማለት ነው። ተመልካችነትና ሕያውነት ደግሞ የእግዚአብሔር ባህርያት ስለሆኑ (ኢዮ 24:23 ዘኁ 14:28) ለአጋር የተገለጠው አካል እግዚአብሔር ነው ማለት ነው። ይህ ከምንም በላይ የመልአኩን እግዚአብሔርነት የሚያረጋግጥ ነው። የተገለጠበት ስፍራ በመለኮታዊ ስም ተጠርቷልና

 ሁሉን ተመልካችነት የእግዚአብሔር ባሕርይ ነው። ከእርሱ እይታ ውጪ የሚሆን ወይንም ከእርሱ ቁጥጥር የሚያመልጥ ምንም አይነት ነገር የለም። ይህ ባሕርይ የመለኮት ባህርይ ብቻ ሲሆን እርሱን ከፍጥረት ሁሉ ልዩ ያደርገዋል

እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር *ሁሉ* ይመለከታሉና። አሁንም ስንፍና አድርገሃል። ስለዚህም ከዛሬ ጀምሮ ሰልፍ ይሆንብሃል። “ (መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 16:9) ተጓዳኝ አንቀጽ፦ ምሳ. 15፥3 ምሳ 5:21

 ታዲያ እንዴት መልአኩ “የሚያየው አምላክ” ሊባል ቻለ? ይህ የመለኮት ብቻ ባህርይ ሆኖ ሳለ?

መልአኩ የሚያየው አምላክ ሊባል የቻለው የእግዚአብሔር ስም (መለኮት) በውስጡ ስላለ ነው (ዘጽ 23:21) ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ባሕርይ ስለሆነ ነው። በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር በህላዌው የሆነውን ነገር በሙሉ እርሱም ነው። ይህ ማለት ልክ እንደ እግዚአብሔር ሁሉን ተመልካች ነው ማለት ነው

አጋር ስለ መልአኩ የተናገረችው ነገር በራሱ በመልአኩ ተረጋግጦ እናገኘዋለን:-

የእግዚአብሔርም መልአክ በሕልም። ያዕቆብ ሆይ አለኝ፤ እኔም። እነሆኝ አልሁት። እንዲህም አለኝ። ዓይንህን አቅንተህ እይ፤ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ናቸው፤ ላባ በአንተ ላይ የሚያደርገውን ሁሉ አይቼአለሁና። ሐውልት የቀባህበት በዚያም ለእኔ ስእለት የተሳልህበት የቤቴል_አምላክ እኔ_ነኝ፤ አሁንም ተነሥተህ ከዚህ አገር ውጣ፥ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመለስ።” (ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 31፡11-13)

በዚህ ስፍራ የእግዚአብሔር መልአክ ለያዕቆብ በሕልም ተገልጦ የተናገረውን ነገር እንመለከታለን። በወቅቱ የላባ ልጆች “ያዕቆብ የበለጸገው የአባታችንን ሀብት ነጥቆ ነው” ይሉ ነበር። በዚህም ምክንያት የላባና የያዕቆብ ግንኙነት እንደበፊቱ አልሆን አለ

ከዚያም ያዕቆብ ሚስቶቹን ወደ ሜዳው ጠርቶ እንዴት አባታቸው በየግዜው ደመወዙን እየለዋወጠ እንደበደለው ካስታወሳቸው በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ በህልም ተገልጦለት የነገረውን ነገራቸው። እርሱም ላባ በእርሱ ላይ ያደረገውን ሁሉ የተመለከተው የቤቴል አምላክ መሆኑን ነገረው

 ይህ ክስተት አጋር ከብዙ አመታት በፊት የተናገረችውን ነገር የሚያረጋግጥ ነው። መልአኩን “የሚያየው_አምላክ” በማለት ነበር የጠራችው። መልአኩ ይህንኑ ሀሳብ በማጽናት፥ ላባ በያዕቆብ ላይ ያደርገውን ሁሉ የተመለከተው የቤቴል አምላክ መሆኑን ተናገረ

መልአኩ ልክ አጋር እንደጠራችው፤ እኔ አምላክ ነኝ ከማለቱ ባሻገር ግፍን አይቻለሁ ማለቱ እግዚአብሔር መሆኑን ያሳያል። ምክኒያቱም ግፍን ወይንም በደልን “አይቻለሁ” ሊል የሚችለው ወይንም፥ “ይይ” የሚባልለት እግዚአብሔር ብቻ ነው። ይህ የእርሱ ልዩ ባሕርይ ነው

አሁንም እነሆ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ወጣ፤ ግብፃውያንም የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ።” (ኦሪት ዘጸአት 3:9)

እንዲሁም ንጉሡ ኢዮአስ ዮዳሄ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፥ ልጁንም ዘካርያስን አስገደለው፤ እርሱም ሲሞት። እግዚአብሔር ይየው፥ ይፈልገውም አለ። “ (መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 24:22) ተጓዳኝ አንቀጽ፦ ዘጸ። 3:16

ስለዚህ መልአኩ እንዲህ ማለቱ መለኮት መሆኑን ከማረጋገጡ ባሻገር አጋር ስለ እርሱ የተናገረችው ነገር በሙሉ እውነት መሆኑን ያሳያል።

ይህ መልእክተኛ ክርስቶስ መሆኑን በምን ማረጋገጥ እንችላለን?

ይህ መልእክተኛ ክርስቶስ መሆኑን የምናውቅበት አንድ ተጨባጭ ማስረጃ አለ። እርሱም ክርስቶስ ሁሉን ተመልካች መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማሩ ነው።

በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፥ ሰባትም ቀንዶችና ሰባት_ዓይኖች ነበሩት እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።” (የዮሐንስ ራእይ 5:6)

በዚህ ስፍራ ክርስቶስ ሰባት አይን እንዳለው እንደታረደ በግ ተመስሎ እንመለከተዋለን። ሰባት የፍጹምነት፥ የምሉዕነት ምልክት ነው። አንድም ሳይቀር ሙሉ ለሙሉ ማለት ነው።

በጉ ሰባት አይኖች አሉት ማለት ሙሉ እይታ፥ ሙሉ ቁጥጥር አለው ማለት ነው። እርሱ የማያየው፥ ከእርሱ ቁጥጥር ውጭ የሆነ አንድም ነገር በሰማይም ሆነ በምድር የለም ማለት ነው።

ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ፤ አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ።” (የዮሐንስ ራእይ 2:23)

በዚህ ስፍራም ጌታ ኢየሱስ፥ ልብና ኩላሊትን እንደሚመረምር ይናገራል። ልብና ኩላሊትን እመረምራለሁ ያለው እግዚአብሔር ብቻ ሲሆን (ኤር 17:10) የሰውን ማንነት ሙሉ በሙሉ የሚመረምርና የሚያውቅ መሆኑን ያሳያል። ይህ በግልጽ ሁሉን ተመልካቹ እሱ መሆኑን ያሳያል

ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ። ቀኝ እጁንም ጫነብኝ እንዲህም አለኝ። አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥” (የዮሐንስ ራእይ 1:17)

እዚህ ጋርም ጌታ ኢየሱስ ራሱን “ሕያው” በማለት ሲጠራ እንመለከታለን። ሕያው ማለት ለዘላለም የሚኖር ማለት ሲሆን፥ ለአጋር መልአኩ ስለተገለጠላት ያ ቦታ የተሰየመበት መለኮታዊ ስም ነው። ጌታ ኢየሱስ ራሱን “ሕያው” ብሎ መጥራቱ ለአጋር የተገለጠው አምላክ እርሱ መሆኑን በግልጽ ያሳያል

 መደምደሚያ

ከላይ በቀረቡት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች መሰረት፥ ያ በብሉይ ኪዳን ሲገለጥ የነበረው መለኮታዊ መልእክተኛ ክርስቶስ ኢየሱስ መሆኑን እናረጋግጣለን።



መሲሁ ኢየሱስ