ዲቃላ በመጽሐፍ ቅዱስ እና በቁርኣን

ዲቃላ በመጽሐፍ ቅዱስ እና በቁርኣን

ሙስሊም ወገኖች ብዙ ጊዜ እስራኤላውያን በዙርያቸው ከሚገኙት ሕዝቦች ጋር እንዳይቀላቀሉና እንደ ልዩ ሕዝብ ያላቸው መታወቂያ እንዳይጠፋ ለመከላከል እግዚአብሔር የሰጠውን ትዕዛዝ ሲተቹ እንሰማቸዋለን፦
“ዲቃላ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ፤ እስከ አሥር ትውልድ ድረስ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ።”
— ዘዳግም 23፥2
ይህ ጥቅስ ሕዝበ እስራኤልን ከባዕዳን ጋር እንዳይቀላቀሉና ሕልውናቸው እንዳይከስም ለመከላከል የተሰጠ protective ሕግ እንጂ ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ የተወለዱትን ሰዎች ለመጨቆን የተሰጠ አይደለም። “መምዜር” የሚለው የእብራይስጥ ቃል ከእስራኤላዊ አባትና ከሌላ ዘር እናት የተወለደን ሰው የሚያመለክት ነው። እግዚአብሔር አምላክ ይሁዲን ከተቀበሉ ከአሕዛብ ወገን ከሆኑት ሰዎች ጋር ጋብቻ እንዲፈፀም የፈቀደባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውን ስናስተውል ደግሞ ሕጉ የእስራኤል ሕዝብ በጋብቻ ከአሕዛብ ጋር ተቀላቅሎ ህልውናው እንዳይጠፋ የታለመ ብቻ መሆኑን እንገነዘባለን። (ለምሳሌ የሩትን ታሪክ መመልከት ይቻላል።)
ነገር ግን ሙስሊም ወገኖቻችን እንዲህ ያለ ቃል በመንፈሳዊ መጽሐፍ ውስጥ መጠቀስ የለበትም በማለት ነገሮችን በማጋነን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን። የገዛ መጽሐፋቸው ይህንን መስፈርት ያልፍ ይሆን? ሱራ 68:13 እንዲህ ይላል፦
عُتُلٍّ بَعْدَ ذَٰلِكَ زَنِيمٍ
“ልበ ደረቅን፣ ከዚህ በኋላ ዲቃላን (ሁሉ አትታዘዝ)፡፡”
በዚህ ጥቅስ ውስጥ “ዲቃላ” የሚለው ቃል ስድብ ነው ወይስ እውነታዊ ንግግር (statement of fact)? ስድብ ከሆነ አምላክ እንዲህ ያለ ስድብ እንዴት ይሳደባል? እውነታዊ ንግግር ከሆነ ሙሐመድ እነዚህን ሰዎች እንዳይሰማ የተነገረው ዲቃላ በመሆናቸው ነው ወይስ ሐሳባቸው መጥፎ ስለሆነ? ሐሳባቸው መጥፎ ስለሆነ ነው ከተባለ አወላለዳቸውን መጥቀስ ለምን አስፈለገ? የአንድን ግለሰብ አወላለድ ከሐሳቡ ጋር ምን አገናኘው? ለኔ በዚህ ጥቅስ ውስጥ የሙሐመድ ቁጣና ብስጭት እንጂ የአምላክ ንግግር አይታየኝም። ሙስሊም ወገኖች መጽሐፍ ቅዱስን ከመተቸታችሁ በፊት የገዛ መጽሐፋችሁን ችግሮች ብታፀዱ መልካም ነው።

አንድ ሙስሊም ሰባኪ ከላይ ለሚገኘው ጽሑፍ ፌስቡክ ላይ ምላሽ ሊሰጠኝ ጥረት ያደረገ ሲሆን ተከታዩን ምላሽ ሰጥቼዋለሁ

ሰሞኑን ሙስሊም ኡስታዞች በገዛ መጽሐፋቸው ላይ የማይጠቀሙትን መስፈርት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መጠቀማቸው ስህተት መሆኑን የሚያሳይ አጭር ጽሑፍ ለንባብ አብቅቼ ነበር፡፡ በዚህም መነሻ አንድ አብዱል ምላሽ የሚመስል ነገር ጽፏል፡፡ (ይህንን ሰው “አብዱል” ብዬ የምጠራው “ሚሽነሪ” በሚል በአረቦች ዘንድ ከስድብ በሚቆጠር ቃል ስለጠቀሰኝ መሆኑ ይታወቅ፡፡) የጽሑፉ ማጠንጠኛ “ዲቃላ” የሚል ቃል ሲሆን ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ በዘዳግም 23፡2 እንዲሁም በቁርኣን በሱራ 68፡13 ላይ ይገኛል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ ሐሳብ ድብልቅ ዘርን ለማመልከት የታለመ እንጂ ከጋብቻ ውጪ ስለተወለደ እስራኤላዊ አለመሆኑን በመግለፅ ምክንያቱን በአጭሩ አብራርቻለሁ፡፡ በጽሑፌ መቋጫም የቁርአኑ የቃል አጠቃቀም ስድብ ስለመሆን አለመሆኑ ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ ስድብ ከሆነ አምላክ እንዴት ይሳደባል? ስድብ አይደለም ከተባለ ደግሞ የአንድን ሰው አወላለድ ከሐሳቡ ጋር ምን አገናኝቶት ነው አላህ “ዲቃላ” የሚለውን ቃል የተጠቀመው? የሚሉ ጥያቄዎችንም አንስቼ ነበር፡፡
ሙስሊሙ ወገን በሁለተኛ ምላሹ “ዘኒሚን” የሚለው በቁርኣን ውስጥ የተጠቀሰው ቃል “ዲቃላ” የሚል ትርጉም እንዳለው ያመነ ሲሆን ጥቅሱ በእውነትም ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ የተወለደን አል-ወሊድ ኢብን አል-ሙጊራ የተባለን ሰው የተመለከተ መሆኑን የተናገሩ ሙፈሲሮች መኖራቸውን ገልጿል፡፡ አል-ወሊድ ኢብን አል-ሙጊራ የእውነትም ዲቃላ በመሆኑ “ዲቃላ” በሚለው ቃል መጠራቱ እንዴት ቁርኣንን ያስተቻል? የሚል ዓይነት ጥያቄም ያነሳል፡፡ ይህ ወገናችን ይህንን ምላሽ መስጠቱ በቁርኣን ላይ ያነሳናቸው ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውን ያረጋግጣል፡፡ አላህ (እንደ እውነቱ ከሆነ ሙሐመድ) የሙሐመድ ተቃዋሚ የነበረውን ሰው አወላለዱን በመጥቀስ በዚህ ቃል መጥራቱ ሰውየውን ለመሳደብ ያለመ ነው ማለት ነው፡፡ ባይሆን ኖሮ የሰውየውን አወላለድ ከሐሳቡ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር ባለመኖሩ አወላለዱን በመጥቀስ “ዲቃላ” ባላለው ነበር፡፡ ሙሐመድ አባቱ ከልደቱ በፊት በመሞቱ ምክንያት በዘመዶቹና በማሕረሰቡ እየተገፋ ከማደጉ አንጻር ይህ ቃል የሚያስከትለውን ህመም ከእርሱ በላይ የሚያውቅ አልነበረም፡፡ በስብከቱ ላይ ተቃውሞ በማሰማቱ ብቻ ሰውየውን በዚህ ቃል መጥራቱ ለስድብ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
ሙስሊሙ ወገን በሁለተኛው ምላሹ የአረብኛው ቃል ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ የተወለደን ሰው ለማመልከት ጥቅም ላይ መዋሉን የገለጸ ቢሆንም በመጀመርያ ምላሹ “ዘኒም” የሚለው ቃል “ዲቃላ” ከሚለው ቃል የሰፋ ትርጉም እንዳለው በመናገር የቁርአኑን ሐሳብ ለማድበስበስ ሞክሯል፤ አንድ ሁለት ምንጮችንም ጠቅሷል፡፡ ይህ ወገናችን ያልተገነዘበው ነገር ቢኖር በየትኛውም ቋንቋ ቃላት የተለያየ ትርጉም ሊኖራቸው ቢችልም በአንድ ንባብ ውስጥ ያላቸው ትርጉም በአውድ የሚወሰን መሆኑን ነው፡፡ ሁለቱ ጃለሎች በተፍሲራቸው እንደገለፁት ቃሉ በእውነትም ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ የተወለደውን አል-ወሊድ ኢብን አል-ሙጊራ የተባለን ሰው ለመጥቀስ ነበር ጥቅም ላይ የዋለው፡፡ ስለዚህ በመዝገበ ቃላትም ሆነ በሌሎች ምንጮች ውስጥ “ዲቃላ” ከሚለው ቃል የሰፋ ትርጉም ያለው መሆኑ በቁርኣን ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለበት አገባብ ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ የተወለደን ሰው ለመጥቀስ የመሆኑን እውነታ አይለውጥም፡፡ ለዚህ ነው ዕውቁ የቁርኣን ሙፈሲር ሰይድ አቡል ዓላ ማውዱዲ ይህ ቃል ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ የተወለደን ሰው እንደሚያመለክት የተናገሩት፡፡ ይህ ሙስሊም ወገናችን ቃሉ በቁርኣን ውስጥ የተጠቀሰው “ዲቃላ” የሆነን ሰው ለማመልከት መሆኑን አምኖ ሳለ መልሶ ደግሞ ቃሉ “ዲቃላ” ከሚለው የሰፋ ትርጉም ስላለው የቁርኣን አጠቃቀም “ዲቃላን” ለማመልከት አይደለም የሚል ሙግት ማቅረቡ አስቂኝ ነው፡፡ ይህ ወገናችን ምን እያወራ ነው? የሎጂክ ያለህ!
(ከላይ የተጠቀሱትን ተፍሲሮች በዚህ ገፅ ላይ ታገኛላችሁ https:// quranx . com/tafsirs/68.13 ወደ ገጹ ለመሄድ ክፍተቶቹን ማቀራረብ እንዳትረሱ፡፡)
በመጨረሻም “መምዜር” የሚለው የእብራይስጥ ቃል የሚያመለክተው ከጋብቻ ውጪ የተወለደን ሰው እንጂ የእስራኤላዊና የአሕዛብ ድብልቅ አለመሆኑን ጽፏል፡፡ የቃሉ ትርጉም ይህ መሆኑን የሚያመለክት የመዝገበ ቃላት ማስረጃ ያልጠቀሰ ሲሆን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ “illegitimate birth, bastard, born of a forbidden marriage” በማለት እንደሚያስቀምጥ ጠቅሷል፡፡ ነገር ግን የብሮውን፣ ድሪቨር፣ ብሪግስ የእብራይስጥ መዝገበ ቃላትነን ስንመለከት የተዳቀለ (bastard)፣ ድብልቅ ሕዝብ (mixed population) ወይም ደግሞ በዳህራይ እብራይስጥ ከሥጋ ዘመድ ግንኙነት የተወለደ (Child of incest) የሚሉ ትርጉሞች እንዳሉት ይገልጻል፡፡ የስትሮንግ ኮንኮርዳንስ ደግሞ መለያየት (to alienate)፣ የሁለት ወገን ድቅል (a mongler)፣ ከአይሁድ አባትና አሕዛብ እናት የተወለደ (Born of a Jewish father and heathen mother) በማለት ያስቀምጠዋል፡፡ ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁለት ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ዘካርያስ 9፡6 ላይ የተደባለቀ ሕዝብ ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ስለዚህ ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው ከሁለት ወገን ማለትም ከእስራኤላዊና ከአሕዛብ ወገን የተደባለቀን ሰው ለማመልከት ነው፡፡
በመጨረሻም በቀደመው ልጥፍ እንደገለጽኩት ይህ ጥቅስ ሕዝበ እስራኤልን ከባዕዳን ጋር እንዳይቀላቀሉና ሕልውናቸው እንዳይከስም ለመከላከል የተሰጠ protective ሕግ እንጂ ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ የተወለዱትን ሰዎች ለመጨቆን የተሰጠ አይደለም። እገዳውም እንዲህ ያሉ ሰዎች ወደ ጉባኤ እንዳይገቡ ብቻ እንጂ ሌሎች መብቶቻቸውን የተመለከተ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ይሁዲን ከተቀበሉ ከአሕዛብ ወገን ከሆኑት ሰዎች ጋር ጋብቻ እንዲፈፀም የፈቀደባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውን ስናስተውል ደግሞ ሕጉ የእስራኤል ሕዝብ በጋብቻ ከአሕዛብ ጋር ተቀላቅሎ ህልውናው እንዳይጠፋ የታለመ ብቻ መሆኑን እንገነዘባለን። (ለምሳሌ የሩትን ታሪክ መመልከት ይቻላል።) ሕዝበ እስራኤል የሰው ልጆችን ለማዳን ለሚመጣው መሲህ መንገድ ይሆን ዘንድ በእግዚአብሔር የተመረጠ ሕዝብ በመሆኑ ከአሕዛብ ጋር ተደባልቆ ሕልውናው እንዲጠፋና የአሕዛብን መንገድ እንዲማር እግዚአብሔር አልፈቀደም፤ ስለዚህ እንዲህ ያለ ጥብቅ ትዕዛዝ መስጠት አስፈላጊ ነበር፡፡ ሆኖም የሕዝቡን ህልውና ለአደጋ የማያጋልጡ የተወሰኑ ጋብቻዎች አዎንታዊ ምላሽ ማግኘታቸው ሕጉ የተሰጠው የሕዝቡን ህልውና ለማረጋገጥ እንጂ አድልዎ ለመፈፀም አለመሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡ ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው እውነታን ለማንፀባረቅ እንጂ እንደ ቁርኣን ለስድብ አለመሆኑም ሊሰመርበት ይገባል፡፡