የመካው ሙሐመድ – መካን አምላክ ያስተዋወቀ መካን ሰው

የመካው ሙሐመድ – መካን አምላክ ያስተዋወቀ መካን ሰው

 

ሙሐመድ በትምህርቱ አጥብቆ ከተቃወማቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የአላህን አባትነት ነው (ሱራ 4፡171፣ 19፡92-93፣ 23፡91፣ 25፡2)፡፡ የነቢያትን ትምህርት ስንመለከት ሕዝበ እግዚአብሔር የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆች መሆናቸውን አስተምረዋል (ዘጸአት 4፡22-23፣ ዘዳግም 32፡6፣ ኤርምያስ 31፡9)፤ ስለ እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ስለ መሲሁም ተንብየዋል (መዝሙር 2፡7፣ ምሳሌ 30፡4)፡፡ ይህ ጉዳይ ከእግዚአብሔር መለኮታዊ ልጅ መምጣት ጋር ተያይዞ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በስፋት ተገልጿል (ሉቃስ 1፡35፣ ዮሐንስ 3፡16፣ 5፡18፣ ሮሜ 1፡4-5)፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና ከተዘጋ ከ600 ዓመታት በኋላ የመጣው ሙሐመድ ግን ይህንን የነቢያትና የሐዋርያት ትምህርት በመጻረር አላህ ልጅ እንደሌለው አስተማረ፡፡ አልፎም አባትነትን በየትኛውም መልክና ቅርፅ ከፈጣሪ ጋር ማያያዝና ፈጣሪን በዚያ ስም መጥራት የከፋ ኃጢአት መሆኑን አስተምሯል፡፡ በእስልምና አላህ 99 ስሞች እንዳሉት የሚነገር ሲሆን አንዱን በማጉደል 100 እንዳይሞላ ተደርጓል፤ የአላህን ስሞች ጎደሎ እንዲሆን ያደረገው “አባት” የሚለው ከዝርዝሩ ውስጥ አለመገኘቱ ነው፡፡ ሙሐመድ የክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅነት የካደ እንዲሁም ገሃነም ከሚያስገቡ “የክህደት ንግግሮች” መካከል አንዱ እንደሆነ ያስተማረ ሲሆን አይሁድና ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆች መሆናቸውን መናገራቸውን በመጥቀስ ሲሳለቅባቸው በቁርኣን ውስጥ ይታያል (ሱራ 5፡18)፡፡ የሙሐመድ አምላክ ባርያ አሳዳሪ ቁጡ ጌታ እንጂ አፍቃሪ አባት አይደለም፡፡ ሙስሊሞች ለጸሎት በፊቱ የሚቀርቡት ወለም ዘለም በማያስብል የባርነት ሥርኣትን በሚያሳይ አቋቋምና አሰጋገድ እንጂ እንደ ክርስቲያኖች አፍቃሪ አባታቸውን ለማመስገንና ልመናቸውን ለማቅረብ በልጅነት መንፈስ አይደለም፡፡ ሙሐመድ የእግዚአብሔርን አባትነት እንዲህ መቃወሙና ቃሉ በየትኛውም መልክና ቅርፅ ከእርሱ ጋር መያያዙን እንደ ክህደት መቁጠሩ ለምን እንደሆነ በእጅጉ ከሚገርሙኝ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነበር፡፡ ጉዳዩ የተገለጠልኝ ግን በቅርብ ጊዜ ነው፡፡ የሙሐመድ አስተምህሮ የሕይወቱ ነፀብራቅ ነው፡፡ በማስከተል በማስረጃዎች አስደግፌ እንደማሳየው የመካው ሙሐመድ ኢብን አብደላህ አምላኩ ልጅ አልባ መካን መሆኑን ያስተማረው ራሱ መካን ስለነበረ ነው፡፡

እስኪ ልጠይቃችሁ፡፡ ሙሐመድ ስንት ሚስቶች ነበሩት? በወጣትነቱ ያገባትን የ40 ዓመቷን ኸዲጃን ጨምሮ 13 እንደሚሆኑ ይነገራል፡፡ በአንድ ወቅት 9 ሚስቶችን አንድ ላይ ያኖር እንደነበርና ከአንዲቱ በስተቀር ከሁሉም ጋር ወሲብ ይፈፅም እንደነበር ተነግሯል (Sahih al-Bukhari, Volume 7, Book 62, Number 5)፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የወሲብ ባርያዎች በእስልምና ስለተፈቀዱ የተወሰኑ ቅምጦች ይኖሩታል፡፡ ከነዚህ መካከል ግብፃዊቷ ማርያህ በስም ተጠቅሳለች (Ibn Sa’d, Al-Tabaqaat al-Kubra, 1/134-135)፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ ሁሉ ሴቶች ጋር ወሲብ እየፈፀመ ነገር ግን “ልጆች መውለድ የቻለው” ከመጀመርያ ሚስቱ ከኸዲጃና ከግብፃዊቷ ባርያ ከማርያህ ብቻ ነበር፡፡ በአብዛኞቹ እስላማዊ ምንጮች መሠረት ከኸዲጃ 6 ልጆችን እንደወለደና ሁሉም ወንድ ልጆቹ በህፃንነታቸው እንደተቀጩ ይነገራል፡፡ (አልጠበሪ 8 ልጆችን የሚጠቅስ ሲሆን ቀዳሚውን የሙሐመድ ግለ ታሪክ የከተበው ኢብን ኢስሐቅ ደግሞ 7 ይዘረዝራል)፡፡አብዛኞቹ  ሱኒዎች ሁሉም ልጆች የሙሐመድ እንደሆኑ ቢያምኑም በአብዛኞቹ ሺኣዎች እምነት መሠረት ግን ከሁለተኛ ልጁ ከፋጢማ በስተቀር ሁሉም ልጆች የሙሐመድ አይደሉም፡፡ በሺኣዎች መሠረት የተቀሩት ልጆች ከባሏ በመፋታት በቤታቸው ትኖር የነበረችው የኸዲጃ እህት የሓላ ቢንት ኹዋይሊድ ልጆች ነበሩ፡፡ ከመጀመርያ ጋብቻዎቿ የወለደቻቸው እንደሆኑም የሚናገሩ አሉ፡፡

የኸዲጃን የዕድሜ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ስናስገባ ይህ የሺኣዎች አመለካከት ለእውነት የቀረበ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ኸዲጃ ከሙሐመድ በፊት ሁለት (ወይም ሦስት ጊዜ) ጋብቻ ፈፅማ የነበረ ሲሆን ልጆችንም ወልዳለች፡፡ በአርባ ዓመቷ የሃያ አምስት ዓመቱን ወጣት ሙሐመድን ካገባች በኋላ በጥቂቱ 6 ልጆችን እንደወለደች በሱኒ ምንጮች ተነግሮላታል፡፡ ጋብቻው የተፈጸመው በ595 ዓ.ም. ሲሆን በሱኒ ምንጮች መሠረት 598 ዓ.ም የመጀመርያ ልጃቸውን “ቃሲምን” ወልደዋል፤ ሙሐመድ “አቡል ቃሲም” ተብሎ መጠራቱ በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የመጨረሻ ልጃቸውን አብደላን በ615 ዓ.ም የወለዱ ሲሆን በዚህ ጊዜ ኸዲጃ ዕድሜዋ 60 እንደሚሆን ይገመታል፡፡ አንዲት 40 ዓመት ያለፋትና ከዚያ ቀደም ልጆችን የወለደች ሴት የሴትነት ወጓ ከመቆሙ በፊት 6 ልጆችን አከታትላ ወልዳለች ማለት የማይመስል ነው፡፡ የሆነው ሆኖ በስሙ የተጠሩት ልጆች የእውነት ከእርሱ ተወልደዋል ወይ በሚለው ጥያቄ ዙርያ ሙስሊሞች እስከ ዛሬ ድረስ አልተግባቡም፡፡

ሙሐመድ ከኸዲጃ በኋላ ብዙ ሚስቶችን አግብቷል፤ ነገር ግን ልጅ መውለድ የቻለው ማርያህ አል-ቅብጥያ ከተባለችው አንዲት ግብፃዊት ባርያ ብቻ ነበር፡፡ የልጁ ስም ኢብራሂም ተብሎ የተሰየመ ሲሆን በአራስነቱ ተቀጭቷል (Sahih Bukhari 2:18:153)፡፡ ሙሐመድ ከማርያህ ጋር እንደማይተኛ የገባውን ቃል አፍርሶ አብሯት በመተኛቱ ምክንያት ሐፍሳና አይሻ እንዳፋጠጡት የሚናገሩ ሐዲሳትም አሉ (Sahih Bukhari 3:43:648, See also: Sahih Muslim 9:3511 & Sahih Bukhari 7:62:119)፡፡ በዚህም ምክንያት የሙሐመድ አገልጋይ የሆነው አላህ ሱራ 66:1-5 ላይ የሚገኘውን “በማውረድ ሚስቶቹን ገስጿቸዋል፤ ሙሐመድንም ከቃል ኪዳኑ ነፃ አድርጎታል፡፡ ይህንን ሌላ ጊዜ በስፋት እንመለከታለን፡፡

ኢብራሂም የእውነት የሙሐመድ ልጅ በመሆኑ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ አለ፡፡ በኢብን ሳዓድ “ጠበቃት” መጽሐፍ መሠረት ሙሐመድ ህፃኑ ኢብራሂምን አይሻ ዘንድ በመውሰድ እርሱን እንደሚመስል በነገራት ጊዜ አይሻ ልጁ በፍፁም እርሱን እንደማይመስል በአፅንዖት ነግራዋለች፡፡ ለምን? (Tabaqat, Vol. 1, P. 368):: ከልጁ ልደት በፊት ማርያህ ከእርሷ ጋር ከግብፅ የመጣ ለስሙ ጃንደረባ የሆነ ሰው ፆታዊ ጥቃት እንደፈፀመባት ለሙሐመድ በመናገሯ ምክንያት ሙሐመድም አሊ እንዲገድለው እንደላከውና ሰውየው ግን ዛፍ ላይ በመውጣት ብልቱ ሙሉ በሙሉ የተቆረጠ መሆኑን ለአሊ በማሳየቱ ምክንያት አሊ ሳይገድለው እንደተመለሰ ተዘግቧል፡፡ (The History of al-Tabari, the Last Years of the Prophet, Vol. 9, p. 147)፡፡ ሰውየው ማርያህን ደፍሯት ባይሆን ኖሮ እንዴት ልትወነጅለው ቻለች? ሙሐመድስ እንዴት ሊገድለው ወሰነ? አሊ ሰውየው ዛፍ ላይ ሆኖ ብልቱን ሲያሳየው በትክክል የተቆረጠ መሆኑን አረጋግጦ ይሆን የተወው ወይንስ ሰውየው አታሎታል? ወይንም ደግሞ ራርቶለት ትቶት ይሆን? ግራ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ኢብራሂም የሙሐመድ ልጅ መሆኑን መናገር አይቻልም፡፡

በዘመኑ የነበሩት ሰዎች የሙሐመድን ሁኔታ በመታዘብ ዘሩን መተካት የማይችል ሰው እንደሆነ እንደተገነዘቡ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል አል-ዓስ ኢብን ዋዒል የተባለ ሰው ሙሐመድን “የተቆረጠ ሰው” በማለት ይጠራው እንደነበር ተዘግቧል፡፡ በአረብኛ “አብታር” ሚለው ጭራው የተቆረጠን እንስሳ የሚያሳይ ሲሆን በአማርኛ አቻ ትርጉሙ “ቆንጤ” የሚል ነው፡፡ አረቦች ወራሽ ወንድ ልጅ የሌለውን ሰው በዚህ ስም ይጠሩ የነበረ ሲሆን ሙሐመድንም በዚህ ስም ይጠሩት እንደነበር በእስላማዊ ምንጮች ውስጥ ተዘግቧል፡፡ ከዚህ የተነሳም ለሙሐመድ ሱረቱ አል-ከውሠር የተሰኘው 108 ሱራ እንደወረደለትና አላህ በገነት ከማር የጣፈጠ ከውሠር የተሰኘ የነጭ ፈሳሽ ነገር ወንዝ እንዳዘጋጀለት እንደነገረው እስላማዊ ምንጮች ይናገራሉ (የኢብን ከሢር ተፍሲር፡- https://sunnahonline.com/library/the-majestic-quran/761-tafsir-of-chapter-108-surah-al-kauthar )፡፡ ሙሐመድ ዘሩ የተቆረጠ እንደሆነ በመናገር ኢ-አማንያን ስለተሳለቁበት አላህ የነጭ ፈሳሽ ነገር ወንዝ በገነት እንዳዘጋጀለት መናገሩ ምንን ሊያመለክት ይችላል ለሚለው መልሱን እናንተ ስጡ፡፡

ሙሐመድ ወሲብ ላይ ደካማ መሆኑ በሰዎች ዘንድ መታወቁ ምቾት የሰጠው አይመስልም፡፡ በዚህም ምክንያት አላህ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ ወሲባዊ ኃይሉን እንደጨመረለት ተናገረ፡፡ በግለ ታሪኩ ውስጥ እንደተዘገበው ገብርኤል ከሰማይ በትንሽ ማሰሮ ምግብ እንዳመጣለትና ያንን ምግብ ከበላ በኋላ የ 40 ወንድ ጉልበት እንዳገኘ ገልጿል፡፡ (Tabaqat, Vol. 8, p. 200)፡፡ በሳሒህ ሐዲሳት ደግሞ ሙሐመድ የ 30 ወንድ ያህል ጉልበት እንደነበረውና በአንድ ቀን ሁሉንም ሚስቶቹን ይጎበኝ እንደነበር ተነግሯል  (Sahih al-Bukhari, Volume 1, Book 5, Number 268)፡፡ መሰል ታሪኮች የሙሐመድን ወሲባዊ ችግር ለመሸፈን የተነገሩ ፈጠራዎች መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ሙሐመድ ሚስቶቹን እየዞረ እንዲሁ በእጁ ይነካካቸው እንደነበር፤ ይህም ተግባር ራሱን መቆጣጠር በመቻሉ እንደተሳበበ በሐዲስ ውስጥ እናነባለን  (Sahih al-Bukhari, Volume 1, Book 6, Number 299)፡፡ አይሻ ደግሞ የሙሐመድን ሐፍረተ ሥጋ ዓይታ እንደማታውቅ ተናግራለች (Tabaqat, Vol. 8, p. 368)፡፡ እንዴት ቢሆን ነው ሚስት የባሏን አካል የማታየው? የማይታመን ነው!

ስናጠቃልል ሙሐመድ ከኸዲጃ ቢያንስ 6 ልጆችን እንደወለ ቢነገርም ሙስሊሞች የትኞቹ የእርሱ እንደሆኑና እንዳልሆኑ ከስምምነት አልደረሱም፡፡ የሱኒ ሙስሊሞች ሁሉም የእርሱ እንደሆኑ ቢናገሩም የሺኣ ሙስሊሞች ግን ከፋጢማ በስተቀር ሁሉም የእርሱ እንዳልሆኑ ይናገራሉ፡፡ ከኸዲጃ ህልፈት በኋላ ሙሐመድ ቢያንስ 12 ሚስቶችን ያገባና ከተለያዩ ሴቶች ጋር ወሲባዊ ግንኙነት ይፈፅም እንደነበር ቢታወቅም ልጅ መውለድ እንደቻለ የተነገረው ከግብፃዊቷ ባርያ ከማርያህ ብቻ ነበር፡፡ የተወለደው ህፃን የእርሱ ይሁን የሌላ ሰው ጥርጣሬን የሚያጭሩ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከሌሎች ወጣት ሚስቶቹና እቁባቶቹ መውለድ ያልቻለው ሙሐመድ ከአንዲት ማንም ወንድ ሊተነኩሳት ከሚችል ባርያ ብቻ እንደወለደ መነገሩ አሳማኝ አይደለም፡፡ በመጨረሻም መካንነቱ ግልፅ ሆኖ መታወቅ ሲጀምር አላህ ተዓምራሲ የሆነ ወሲባዊ ጉልበት እንደሰጠው በመናገር ስነ ልቦናውን ለማከም ሞክሯል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች በመነሳት ሙሐመድ ቢያንስ ቢያንስ ከኸዲጃ ወዲህ የመካንነት ችግር እንደገጠመው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

በመጨረሻም ይህ የመካንነት ችግር ሙሐመድ ብዙ ጊዜ ከራሱ ማንነት ጋር ስለሚምታታበት አላህ ስለተባለው አምላክ ባለው አስተምህሮ ላይ ተፅዕኖን ያሳደረ ይመስላል፡፡ አላህን በየትኛውም መንገድ “አባት” ብሎ መጥራት ኃጢአት መሆኑን በማስተማር ከእርሱ በፊት የነበሩትን ነቢያት ትምህርት ተፃረረ፡፡

ነቢያት ያሕዌ እግዚአብሔር ልጁን እንደሚልክ ተንብየዋል፡፡ ሐዋርያት የልጁን መምጣት መስክረዋል፡፡ ልጁ ከመጣ ከ 600 ዓመታት በኋላ መካ ውስጥ የኖረ ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀት ያልነበረው በመካንነት ስነ ልቦና ሲቸገር የነበረ ሰው እግዚአብሔር ልጅ እንደሌለው ስለተናገረ ይህ እውነት አይለወጥም፡፡ እኛ ሕያው የሆነውን በባሕርይ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መንፈሳውያን ልጆቹ ያደረገንን አምላከ እስራኤልን እንጂ መካን አምላክ ስለማንከተል እንዲህ ያለውን ክህደት አንቀበልም!

ነቢዩ ሙሐመድ