ሙሐመድ በኢሳያስ 29፡12?  መጽሐፉን መንበብ ለማያውቅ፡- ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ ፡- ማንበብ አላውቅም ይላቸዋል

ሙሐመድ በኢሳያስ 29፡12? 

“መጽሐፉን መንበብ ለማያውቅ፡- ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ ፡- ማንበብ አላውቅም ይላቸዋል”

ሙስሊም ሰባኪያን የሙሐመድ መምጣት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሰ በማስመሰል ከሚሞግቱባቸው ክፍሎች መካከል አንዱ ኢሳይያስ 29፡12 ነው፡፡ በተለይም ዶ/ር ዛኪር ናይክ የተሰኙ ሕንዳዊ ሰው ይህንን ጥቅስ በተደጋጋሚ ሲጠቅሱ ይደመጣሉ፡፡ ጥቅሱ እንደሚከተለው ይነበባል፡-

“ደግሞም መጽሐፉን ማንበብ ለማያውቅ ፡- ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ፡- ማንበብ አላውቅም ይላቸዋል፡፡”

በሙስሊም ሰባኪያን መሠረት ይህ ጥቅስ ሙሐመድ በሒራ ዋሻ ውስጥ ጂብሪል ተገልጦለት “አንብብ” ባለው ጊዜ “ማንበብ አልችልም” ብሎ የመለሰበትን ክስተት የሚተነብይ ነው፡፡ ይህ አባባላቸው ሰባኪያኑ ምዕራፉን ጭራሹኑ ገልጠው አለማንበባቸውን ሲከፋም አንብበውት ሳሉ የዋኀንን ለማወናበድ የቆረጡ መሆናቸውን ያሳብቅባቸዋል፡፡ በማስከተል እንደምንመለከተው ይህ ክፍል ስለ ሙሐመድም ሆነ ስለ ሌላ ስለማንኛውም ነቢይ የተተነበየ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሙስሊም ሰባኪያን እንደሚሉት ስለ ነቢያቸው የተተነበየ ቢሆን ኖሮ እውነተኛ ነቢይነቱን ሳይሆን ሐሰተኛነቱን የሚተነብይ በሆነ ነበር፡፡ የምዕራፉን ሙሉ አውድ ያገናዘበ ማብራርያ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ምዕራፉ “ዳዊት ለሰፈረባት ከተማ ለአርኤል ወዮላት!” በማለት ጀምራል፡፡ (አርኤል በዕብራይስጥ መቃጠያ ወይም ምድጃን የሚያመለክት ነው፡፡) ከቁጥር ሁለት እስከ ስምንት እጅግ የሚያስፈራ የቁጣ ቃላትን ለእስራኤል ይናገራል፡፡ ከቁጥር ዘጠኝ ጀምሮ ደግሞ እስራኤል መንፈሳዊ ዕውርነት ውስጥ መሆኗን ይናገራል፡፡ 9 “ተደነቁ ደንግጡም፤ ተጨፈኑም ዕውሮችም ሆኑ፤ በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ሰከሩ፤ በሚያሰክር መጠጥ አይሁን እንጂ ተንገዳገዱ፡፡ 10 እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስ አፍስሶባችኋል ዓይኖቻችሁን ነቢያትንም ጨፍኖባችኋል ራሶቻችሁን ባለ ራዕዮችን ሸፍኖባችኋል፡፡ 11 ራዕዩም ሁሉ እንደ ታተመ መጽሐፍ ቃል ሆኖባችኋል፤ ማንበብንም ለሚያውቅ፡- ይህን አንብብ ብለው በሰጡት  ጊዜ እርሱ፡- ታትሞአል አልችልም ይላቸዋል፤ 12 ደግሞ መጽሐፉን መንበብ ለማያውቅ፡- ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ ፡- ማንበብ አላውቅም ይላቸዋል፡፡” ከአውዱ በግልፅ እንደሚታየው ይህ ክፍል የሚነግረን እስራኤል የእግዚአብሔርን ቃል አለመታዘዟንና አለመረዳቷን ነው፡፡ መንፈሳዊ ዓይናቸው ስለታወረ መጽሐፉ ውስጥ ያለው መልእክት ተሰውሮባቸዋል፡፡ ማንበብ በሚችል ሰው የተመሰሉት የሕግ መምህራን ሲሆኑ ማንበብ በማይችለው የተመሰሉት ደግሞ ሕዝቡ ናቸው፡፡ ማንበብ የሚችሉቱ (መምህራኑ) “መጽሐፉ ምስጢር ነው መረዳት አንችልም” ብለው ሲያሳብቡ ማንበብ የማይችሉቱ (ሕዝቡ) ደግሞ “እኛኮ ማንበብ አንችልም” ብለው ሕጉን ለመተላለፋቸው ማስተባበያ ይሰጣሉ፡፡ ለዚህም ነው ማንበብ የሚችሉትም (መምህራንም) ሆኑ ማንበብ የማይችሉት (ሕዝቡ) የመጽሐፉን ቃል ለመረዳት ዳተኞች በመሆናቸውና ባለመታዘዛቸው የተወቀሱት፡- 13 “ጌታም፡- ይህ ህዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና በከንፈሮቹም ያከብረኛልና ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛልና፡፡”

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ሙስሊም ሰባኪያን ሙሉ ክፍሉን ሳያነቡ ዘልለው ቁጥር 12 ላይ ደርሰው ሙሐመድን ያመለክታል ይሉናል፡፡ ከላይ እንዳየነው ክፍሉ ስለእስራኤል መንፈሳዊ ዕውርነት የተነገረ እንጂ ሙሐመድ ዋሻ ውስጥ እየተመሰጠ እያለ የሆነ አካል መጥቶ እያጋጨው “አንብብ” እያለው መጽሐፍን እንደሚሰጠው የተተነበየ አይደለም፡፡ ሙስሊም ሰባኪያን እንደሚሉት ጥቅሱ ሙሐመድን የሚያመለክት ከሆነ ሙሐመድ ነቢይ ሆኖ እንደሚነሳ ሳይሆን “ማንበብ አልችልም” እያለ የፈጣሪን ሕግ በመተላለፉ ምዕራፉ ውስጥ የተጠቀሱ መቅሰፍቶች በሙሉ እንደሚደርሱበት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሐሰተኛ ነቢይ ነው ማለት ነው፡፡ ሙስሊም ሰባኪያን እንደሚሉት “ማንበብ አልችልም” ያለው ሙሐመድ ነው ከተባለ ማንበብ እየቻለ “መጽሐፉ ታትሞአል” ብሎ ያላነበበው “ነቢይ” ማን ነው? መቼስ የመጣ ነው? ከሙሐመድ በፊት ነው ወይስ በኋላ? የሚሉ ጥያቄዎች ሊመለሱ ይገባል፡፡

በስተመጨረሻም የጥቅሱን ትክክለኛ ማብራርያ ባለመቀበል ሙስሊም ሰባኪያን “ስለ ነቢያችን የተተነበየ ነው” በማለት አሻፈረን የሚሉ ከሆነ ልንከራከራቸው አንወድም፤ በደስታ እንቀበላቸዋለን! በገዛ እጃቸው ነቢያቸው በመንፈሳዊ ዕውርነት የተያዘና ታላቁ የእግዚአብሔር ቁጣ የሚጠብቀው ሰው እንደሆነ ስላረጋገጡልን ልናመሰግናቸው እንወዳለን!


ነቢዩ ሙሐመድ