ቁርኣን ጨረቃ የራሷ ብርሃን እንደሌላት ይናገራልን?
ሙስሊም ወገኖቻችን ቁርአናቸው ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ ሳይንስን ዋቢ ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ የሳዑዲ ንጉሣዊ ቤተሰብ የግል ኃኪም የነበረው መውሪስ ቡካይሌ የተባለ የፈረንሳይ ዜጋ ከሙስሊሙ ዓለም ዶላር ለማጋበስ ሲል ከጻፈው The Bible, The Qur’an, and Science: The Holy Scriptures Examined in the Light of Modern Knowledge የሚል ርዕስ ካለው መጽሐፍ ወዲህ ሙስሊሞች ይህንን ሙግት ለሃይማኖታቸው እውነተኛነት እንደ ዋነኛ ማረጋገጫ አድርገው ይዘውታል፡፡ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ተጠቅሞ የቁርኣንን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ሙግት “ቡካይሌኢዝም” የሚል መጠርያ የተሰጠው ሲሆን ስያሜውን ያገኘው ከዚህ ሰው ነው፡፡ ቡካይሌ ለቁርኣን ትክክለኛነት በመጽሐፉ ውስጥ ከጠቀሳቸው ነጥቦች መካከል አንዱ የጨረቃን ብርሃን የተመለከተ ነው፡፡ በዚህ ዘመን የሚገኙት ሙስሊም ወገኖቻችን ይህንን ሙግት ምንም ማሻሻያ ሳያደርጉለት በተደጋጋሚ ሲጠቅሱት እየታዘብን ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ይህንን ሙግት እንፈትሻለን፡፡
ጨረቃ የራሷ ብርሃን እንደሌላትና የብርሃኗ ምንጭ ፀሐይ መሆኗን በተመለከተ ቁርኣን ውስጥ ይገኛል የተባለው ሳይንሳዊ እውነታ በተከታዮቹ ጥቅሶች ላይ የተመሠረተ ነው፡-
“አላህ ሰባትን ሰማያት አንዱ ካንዱ በላይ ሲሆን እንዴት እንደፈጠረ አታዩምን? በውስጣቸውም ጨረቃን አብሪ (ኑር) አደረገ ፀሐይንም ብርሃን (ሲራጅ) አደረገ።” (ሱራ 71፡15-16)
“ያ በሰማይ ቡርጆችን ያደረገና በርሷም አንጸባራቂን (ሲራጅ) (ፀሐይ) አብሪ (ሙኒር) ጨረቃንም ያደረገ ጌታ ክብሩ በጣም ላቀ።” (ሱራ 25፡61)
በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የጨረቃን ብርሃን ለመግለፅ የገቡት ቃላት “ኑር” እና “ሙኒር” የሚሉ ሲሆን የፀሐይን ብርሃን ለማመልከት የገባው ደግሞ “ሲራጅ” የሚል ነው፡፡ ሙስሊም አፖሎጂስቶች “ኑር” እና “ሙኒር” የሚሉት ቃላት በቁርኣን ውስጥ የጨረቃን ብርሃን ለመግለፅ ቢውሉም ፀሐይን ለመግለፅ ስላልዋሉ የጨረቃ ብርሃን ከፀሐይ የተንጸባረቀ መሆኑን ያመለክታሉ የሚል ሙግት ያቀርባሉ፡፡
ቁርኣን የፀሐይና የጨረቃን ብርሃን ለመግለፅ የተለያዩ ቃላትን መጠቀሙ የቁርኣን ደራሲ የጨረቃ ብርሃን ከፀሐይ የተንጸባረቀ መሆኑን ስለተረዳ ሳይሆን የብርሃናቸውን መጠን (Intensity) ለመግለፅ ብቻ ነው፡፡ “ኑር” የሚለው ቃል “ብርሃን” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን የቁርኣን ደራሲ ፀሐይን “ሲራጅ” (መብራት – lamp) በማለት መግለፁ የፀሐይን የብርሃን ኃይል ለመግለፅ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡፡፡
“ኑር” የሚለው ቃል የተውሶ ብረሃንን ያመለክታል ከተባለ አላህ በቁርኣን ውስጥ “ኑር” ስለተባለ አላህ ከሌላ አካል ብርሃን ተውሶ ነው የሚያንፀባርቀው ማለት ነው?
“አላህ የሰማያትና የምድር አብሪ (ኑር) ነው…” (ሱራ 24፡35)
“ኑር” የተውሶ ብርሃን ከሆነ ቁርኣን ሙሐመድን ለፀሐይ የሚጠቀመውን “ሲራጅ” የሚለውን ቃል በመጠቀም ስለሚገልፀው አላህ የሚያበራው ከሙሐመድ ብርሃን ተቀብሎ ይሆን?
“አንተ ነቢዩ ሆይ! እኛ መስካሪ አብሳሪና አስፈራሪም አድርገን ላክንህ። ወደ አላህም በፈቃዱ ጠሪ፣ አብሪ ብርሃንም፣ (ወሲራጀን ሙኒረን) (አድርገን ላክንህ)፤ አማኞችንም ከአላህ ዘንድ ለነርሱ ታላቅ ችሮታ ያላቸው መሆኑን አብስራቸው።” (ሱራ 33፡45-47)
“አብሪ ብርሃንም” ተብሎ የተተረጎመው በአረብኛ “ወሲራጀን ሙኒረን” የሚል ሰሆን “ሙኒር” የሚለው ቃል “ሲራጅ” ለሚለው ቅፅል ሆኖ ነው የገባው፡፡ “ሙኒር” የሚለው ቃል active participle ነው፤ ስም ሲሆን ደግሞ “ኑር” (ብርሃን) እንዲሁም “ናር” (እሳት) የሚሉ ቃላትን እናገኛለን፡፡ ቃሉ ማንኛውንም ብርሃን የሚገልፅ እንጂ የተንጸባረቀ ብርሃንን (reflected light) ለይቶ የሚያሳይ አይደለም፡፡ አረብኛ በቃላት የበለፀገ ቋንቋ በመሆኑ ለዚያ የሚሆን ሌላ ቃል አለው፤ እርሱም انعكاس (ኢንዒካስ) የሚል ነው፡፡
ከላይ የሚገኘው እንዳለ ሆኖ ቁርኣን የጨረቃ ብርሃን የተውሶ መሆኑን ቢናገር እንኳ አስገራሚና ተዓምራዊ የማይሆንበት አንድ ትልቅ ምክንያት አለ፤ እርሱም ጨረቃ የራሷ ብርሃን እንደሌላትና የፀሐይን ብርሃን እንደምታንፀባርቅ ከእስልምና በፊት በነበሩት የአይሁድና የግሪክ ጽሑፎች ውስጥ መገለፁ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በክርስቶስ ዘመን የኖረ ፋይሎ የተባለ አይሁዳዊ መምህር ጨረቃ የራሷ ብርሃን እንደሌላትና ከፀሐይ ወስዳ እንደምታንፀባርቅ ጽፏል (PHILO: From Questions on Genesis (92) http://www.christian-thinktank.com/baduseot.html ) ከክርስቶስ ልደት በፊት 384-322 ዓ.ዓ የኖረው ግሪካዊው ፈላስፋ አርስጣጣሊስ (አርስቶትል) በበኩሉ በጨረቃ ግርዶሽ ወቅት ምድር በጨረቃ ላይ ከምታሳርፈው ጥላ ተነስቶ የምድርን ቅርፅ ሲገልፅ ይህንን እውነት መረዳቱን አሳይቷል http://aerospace.wcc.hawaii.edu/Curriculum_Voyagers/shadows.html ስለዚህ ቁርኣን የጨረቃ ብርሃን የፀሐይ ነጸብራቅ መሆኑን ቢገልፅ እንኳ ቀደም ሲል የታወቀውን እውነታ ከመድገም የዘለለ ስለማይሆን አስገራሚና ተዓምራዊ የሚያስብል ምንም ነገር የለውም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጨረቃ ብርሃን ምን ይላል?
ሙስሊም ሰባኪያን የጨረቃ ብርሃን ከፀሐይ የተንጸባረቀ መሆኑ በቁርኣን እንደተገለጸ ለማሳየት ከላይ ባለው መንገድ ቁርአናቸውን በማጣመም ካቀረቡ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት 1፡16 ላይ ከዚህ በተቃራኒ እንደሚናገር በመጥቀስ ትችር ሲሰነዝሩ ይደመጣሉ፡-
“እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ፡፡”
ሙስሊም ሰባኪያን ፀሐይና ጨረቃ በተመሳሳይ ቃል “ብርሃን” (በእብራይስጥ “ሐመኦር”) ተብለው መገለጻቸው ስህተት ነው ይላሉ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ሁለቱን አካላት የጠቀሰበት መንገድ ክስተታዊ (phenomenal) እንጂ ሳይንሳዊ ባለመሆኑ በስህተትነት የሚፈረጅ አይደለም፡፡ በዓለም ላይ የሚገኝ የትኛውም ሰው በዕለት ተዕለት የመግባቢያ ንግግሩ ውስጥ “ጨረቃ ከፀሐይ ተቀብላ የምታንፀባርቀው ብርሃን” ከማለት ይልቅ “የጨረቃ ብርሃን” በማለቱ ሳብያ የሳይንስ ዕውቀት እንደጎደለው እንደማይቆጠር ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስም ጨረቃን “ብርሃን” ብሎ መጥራቱ እንደስህተት ሊቆጠር አይገባውም፡፡ ለምሳሌ ያህል የሳይንስ ምሑራንን ጨምሮ በዓለም ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ፀሐይ “ወጣች” “ገባች” የሚሉትን ዓይነት ንግግሮች ይጠቀማሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ንግግሮች ከሳይንስ አኳያ ሲታዩ ትክክል አይደሉም፡፡ ፀሐይ የወጣችና የገባች የሚመስለን ለኛ እንጂ እንደ እውነቱ ከሆነ በራሷ ዛብያ ላይ በመዞር የተለያዩ ገፆቿን ወደ ፀሐይ የምታዟዙረው መሬናት፡፡ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ክስተታዊ ንግግሮች ሳይንሳዊ ስላልሆኑ በስህተትነት አይፈረጁም ወይንም ደግሞ ከዕለት ተዕለት የመግባቢያ ንግግራችን ውጪ አይደረጉም፡፡ በክስተታዊ ንግግሮች ምክንያት የትኛውም ማሕበረሰብ ሳይንሳዊ ዕውቀት የጎደለው እንደሆነ እንደማይታሰብ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የትኛውም ሃይማኖታዊ መጽሐፍ እንደዚህ ዓይነት ንግግሮችን በመጠቀሙ ምክንያት ሳይንሳዊ ስህተት እንዳለበት በመቆጠር ሊነቀፍ አይገባውም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የጨረቃ ብርሃን ከፀሐይ የመጣ መሆኑን የሚያመለክት አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል፡-
“የሰማይም ከዋክብትና ሠራዊቱ ብርሃናቸውን አይሰጡም፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፥ ጨረቃም በብርሃኑ አያበራም።” (ኢሳይያስ 13፡10)
“ባጠፋሁህም ጊዜ ሰማዮችን እሸፍናለሁ፥ ከዋክብቶችንም አጨልማለሁ ፀሐዩንም በደመና እሸፍናለሁ ጨረቃም ብርሃኑን አይሰጥም።” (ሕቅኤል 32፡7)
“በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም” (ማርቆስ 13፡24)፡፡
በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የፀሐይ መጨለምና የጨረቃ ብርሃኗን ያለመስጠት እንደ ሳብያና ውጤት ነው የተቀመጠው፡፡ የነዚህን ዓረፍተ ነገሮች አወቃቀር ስናጤን የጨረቃ ብርሃኗን ያለመስጠት ምክንያቱ የፀሐይ መሸፈንና መጨለም እንደሆነ በሚያሳይ መልኩ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
እኛ ክርስቲያኖች ከሳይንስ ጋር ተስማሚ የሆኑ ብዙ እውነታዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ መሆናቸውን ብናውቅም ለመጽሐፍ ቅዱስ እውተኛነት ማረጋገጫ አድርገን ማቅረብ እንደሚያስፈልገን አናምንም፡፡ ለዚህም የመጀመርያው ምክንያታችን ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛነት ከዚህ የላቁ የተፈፀሙ ትንቢቶችን የመሳሰሉ ማስረጃዎች ስላሉን ነው፡፡ ሌላው ምክንያታችን ደግሞ በየጊዜው የሚለዋወጠውን ሳይንስ ከቅዱሳት መጻሕፍት በላይ በማስቀመጥ ሥልጣን ልንሰጠው አለመፈለጋችን ነው፡፡ ሙስሊሞች ሳይንስን የቁርአናቸው አረጋጋጭ አድርገው በማቅረብ ከፍ ያለ ሥልጣን አጎናፅፈውታል፡፡ ስለዚህ ሳይንስ የቁርኣንን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ከቻለ ውድቅ የማያደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡