የሙሐመድ ኩረጃ
ሙሐመድ እውነተኛ ነቢይ እንዳልሆነ ከሚያሳዩ ማስረጃዎች መካከል አንዱ በዙርያው ከነበሩ ባሕሎችና ሃይማኖታት የተለያዩ ሐሳቦችን በመቅዳት ከሰማይ የመጣለት መገለጥ አስመስሎ ማቅረቡ ነው፡፡ የእስልምና ጀማሪ የሆነው ሙሐመድ ምንም ዓይነት ኦሪጅናል መልእክት ያላመጣ ሲሆን ከተለያዩ ምንጮች የቃረማቸውን ነባር አስተምህሮዎች፣ ታኮችና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች መለኮታዊ መገለጥ በማስመሰል ሲያስተምር ነበር፡፡ በዘመኑ የነበሩት አረቦች እንኳ ይህንን እውነታ በመገንዘብ የሙሐመድን ትምህርት “…የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ተረቶች ናቸው” ይሉ እንደነበር በቁርአን ውስጥ በተደጋጋሚ ተጽፏል (ሱራ 83፡13፣ 68፡15፣ 46፡17)፡፡ ይህንን የሙሐመድ የመቅዳት ተግባር እስላማዊ ምንጮች እንዲህ ሲሉ ይናዘዛሉ፡-
ኢብን አባስ እንዳወራው ነቢዩ ከአላህ ዘንድ ትዕዛዝ በሌለባቸው ጉዳዮች ላይ የመጽሐፉን ሰዎች (አይሁድና ክርስቲያኖች) የሚያደርጉትን ቀድተው ያደርጉ ነበር… (ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 7፣ መጽሐፍ 72፣ ቁጥር 799)
አል-በራ እንዳወራው ለአስራ ስድስት ወይንም አስራ ሰባት ወራት ያህል ወደ ኢየሩሳሌም ዞረን እንሰግድ ነበር፡፡ ከዚያም አላህ ፊቱን ወደ ቂብላ (መካ) እንዲያዞር ነገረው፡፡ (ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 6፣ መጽሐፍ 60፣ ቁጥር 19)
ሁለተኛው ሐዲስ በመለኮታዊ መገለጥ ቢሳበብም ሙሐመድ በመለኮታዊ መገለጥ ሳይሆን በገዛ ስሜቱ ይመራ የነበረ ሰው መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ታሪካዊ አውዱን ስንመለከት ሙሐመድ ወደ መዲና በገባባቸው የመጀመርያዎቹ ዓመታት አይሁድን ወደ እስልምና ለመሳብ ያልተሳኩ ጥረቶችን አድርጎ እንደነበር እንገነዘባለን፡፡ እንደ አይሁድ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ ዞሮ ከመስገድ በተጨማሪ የአሹራ (የፋሲካ) ፆምን እንዲፆሙ ለተከታዮቹ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር (ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 3፣ መጽሐፍ 31፣ ቁጥር 222)፡፡ አይሁድ በአላህ የተመረጡ ሕዝቦች መሆናቸውንም ያስተምር ነበር (2፡47)፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ጥረት አይሁድ እንዲቀበሉት አላደረገም፡፡ በዚህም ስለተከፋ ወደ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ የነበረውን ስግደት ወደ መካ እንዲዞር አደረገ (ሱራ 2:142-145)፡፡ የአሹራንም ፆም በሮመዳን እንዲተካ አደረገ፡፡ (ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 3፣ መጽሐፍ 31፣ ቁጥር 116)፡፡ እዚህ ጋ መነሳት ያለበት ትልቁ ጥያቄ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ዞሮ መስገድ የአላህ ትዕዛዝ ከነበረ ካዕባ በጣዖታት ተሞልቶ በነበረበት ሁኔታ ወደዚያ ፊትን አዙሮ መስገድ ለምን አስፈለገ? የሚል ነው፡፡ ምላሹ ቀደም ሲል እንደተባለው ሙሐመድ በመለኮታዊ መገለጥ ሳይሆን በገዛ ስሜትና ፍላጎቱ ይመራ የነበረ ሰው መሆኑ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ እስላማዊ የታሪክ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፡-
“ዩኑስ ኢብን አብድ አል-ዐላ ኢብን ዋህብ ኢብን ዘይድ እንዳስተላለፈው፡ ነቢዩ ወደ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ ለአስራ ስድስት ወራት ያህል ዞረው ከሰገዱ በኋላ አይሁድ ‹‹በአላህ እንምላለን መሐመድና ተከታዮቹ እኛ እስክንመራቸው ድረስ ቂብላ ወዴት አቅጣጫ እንደሆነ አያውቁም ነበር›› ብለው መናገራቸውን ሰሙ፡፡ ይህም ነቢዩን አስቆጣቸው ስለዚህም ፊታቸውን ወደ ሰማይ ገልብጠው ተመለከቱ፡፡ አላህ እንዲህ አለ፤ “የፊትህን ወደ ሰማይ መገላበጥ በእርግጥ እናያለን፡፡ [ወደምትወዳትም ቂብላ እናዞርሃለን፡፡]” (The History of Al-Tabari: The Foundation of the Community; Volume VII, pp. 24-25)
ሙሐመድ የስግደት አቅጣጫ ከኢየሩሳሌም በጣዖታት ወደተሞላው የመካ ካዕባ እንዲዞር ያደረገው መለኮታዊ ምሪት አግኝቶ ሳይሆን የአይሁድ ነቀፋ ስላበሳጨው ነበር፡፡ ሁለተኛውም የስግደት አቅጣጫ ቀደም ሲል በአረብ ፓጋኖች ይተገበር የነበረ መሆኑ የሙሐመድ ሽግግር ከኩረጃ ወደ ኩረጃ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ተከታዩ ሐዲስ ደግሞ ሙሐመድ የቁርአንን መገለጥ ሳይቀር ከሰው ይወስድ እንደነበር ያረጋግጣል፡-
“አነስ እንዳወራው እስልምናን የተቀበለ አንድ ክርስቲያን ነበረ፤ ይህ ሰው ምዕራፍ 2 እና 3ን ያነብ የነበረ ሲሆን ለነቢዩ (የቁርአን) ጸሐፊ በመሆን ያገለግል ነበር፡፡ ኋላ ላይም ወደ ክርስትናው በመመለስ እንዲህ ሲል አወራ፡- “ሙሐመድ እኔ ከጻፍኩለት ነገር ውጪ ምንም ነገር አያውቅም፡፡” ከዚያም አላህ ገደለው… (ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 4፣ መጽሐፍ 56፣ ቁጥር 814)
ይህ ክርስቲያን የነበረና የሰለመ የሙሐመድ ጸሐፊ “ከሰማይ የመጣ” የተባለውን መገለጥ ከራሱ ከነቢዩ እየሰማ በመጻፍ ለኑሮው የሚያስፈልጉትን ነገሮች እያገኘ “የፈጣሪን መገለጥ” መጻፍን የመሰለ “መንፈሳዊ በረከት” እያጣጣመ ከመኖር ይልቅ ሙሐመድ ሐሰተኛ መሆኑን በመናገር ምድራዊ ጥቅማ ጥቅሞችንና “መንፈሳዊ በረከቶችን” ከማጣትም በተጨማሪ ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ከሙሐመድ እንዲነጠል ያደረገው አንድ ትልቅ ምስጢር መኖር አለበት፡፡ ይህ ሰው በሕይወቱ ቆርጦ ይህንን ከባድ ውሳኔ እንዲወስን ያደረገው ሙሐመድ ከመለኮት ከመስማት ይልቅ መገለጡን እርሱ እየፈጠረ እንዲጽፍለት ማድረጉ ነበር፡፡ ሰውየው እንዲህ ያለ የሐሰትና የማጭበርበር ኖሮን ከመግፋት ይልቅ በሕይወቱ ቆርጦ ከሙሐመድ ለመለየት ወስኗል፡፡ ይህ ታሪክ በእስላማዊ ምንጮች ውስጥ ተጽፎ የሚገኝ በመሆኑ ምክንያት የሰውየውን ተፈጥሯዊ ሞት ተዓምራዊ በማስመሰል “አላህ ገደለው” የተባለው አደገኛውን ሁኔታ ለማለባበስ (Damage Control) የታለመ የሙሐመድ ተከታዮች ፈጠራ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ የሰውየውን ውንጀላ ለማስተባበል ያገኙት ብቸኛ አማራጭ ሞቱን ተዓምራዊ ማስመሰል መሆኑ እሙን ነው፡፡
በሌሎች ዘገባዎች ደግሞ አብዱላህ ኢብን አቢ ሳርህ የተባለ ሌላ የሙሐመድ ጸሐፊ መገለጦችን ሲጽፍ ሳለ በየመሃሉ የማሻሻያ ሐሳቦችን ጣል ያደርግ እንደነበርና ሙሐመድም ብዙ ጊዜ በመስማማት በጽሑፉ ውስጥ እንዲካተት ይፈቅድ እንደነበር ተነግሯል፡፡ ሙሐመድ የሚናገረው መገለጥ ከፈጣሪ ዘንድ ቢሆን ኖሮ የሰው ሐሳብ እንዲጨመርበት ሊፈቅድ እንደማይችል ስለገባው ይህ ጸሐፊ እስልምናን በመተው ወደ መካ ከተማ ሸሸ፡፡ ኋላ ላይ ሙሐመድ መካን ድል ነስቶ በያዘ ጊዜ ኢብን አቢ ሳርህ እንዲገደል አዘዘ፡፡ ነገር ግን በኡሥማን ተማፅኖ ከመገደል ተርፎ እንደገና ወደ እስልምና ተመለሰ፡፡
ኢብን አቢ ሳርህ እስልምናን ስለመካዱና ሙሐመድ ስላስተላለፈበት የሞት ብይን ኢብን ኢስሐቅ፣ አልጦበሪና ኢብን ሰዓድን በመሳሰሉት የሙሐመድ ግለ ታሪክ ጸሐፍት የተዘገበ ሲሆን የቁርአንን መገለጦች እየጨመረና እየቀነሰ ስለመጻፉ ደግሞ አል-ኢራቂና ባይዳዊን የመሳሰሉት ሙስሊም ሊቃውንት ዘግበዋል፡፡ (Al-Wahidi Al-Naysaboori. Asbaab Al-Nuzool; p. 126 Beirut’s Cultural Libary Edition “Tub’at Al-Maktabah Al-thakafiyyah Beirut”)
ሙሐመድ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስንና የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን አባባሎች ልክ የራሱ ቃል በማስመሰል ለተከታዮቹ ያስተምር እንደነበር ከእስላማዊ ምንጮች እንገነዘባለን፡-
ጌታችን ያስተማረውን ጸሎት እንዴት አድርጎ አስልሞ እንዳቀረበ እንመልከት፡-
“አቡ ደርዳ እንዳስተላለፈው፡ የአላህ ምልእክተኛ (ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁንና) እንዲህ ሲሉ ሰምቼዋለሁ፤ ከናንተ መካከል የሚታመም ቢኖር ወይንም ወንድሙ የሚታመም ቢኖር እንዲህ ይበል:- በሰማይ የምትኖር ጌታችን አላህ ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ ትእዛዝህ በሰማይና በምድር የበላይ ሆኖ ይገዛል፤ ምህረትህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን፤ ኃጢኣታችንንና ስህተቶቻችንን ይቅር በለን፤ አንተ የመልካም ሰዎች ጌታ ነህ፤ ይህ በሽታ እንዲፈወስ ከምህረትህ ምህረትን ከፈውስህ ፈውስን አውርድ፡፡” (ሱናን አቡ ዳውድ መጽሐፍ 28፣ ቁጥር 3883)
እስኪ ይህንን ጌታችን ኢየሱስ ካስተማረው ጸሎት ጋር አነጻጽሩ፡-
“እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ፡- በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤ ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን፤ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን።” ማቴዎስ 6፡9-13
የእስልምና ጀማሪ የሆነው ሙሐመድ ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፈውን ከጠቀሰ በኋላ የአላህ ቃል መሆኑን በመመስከር እንዲህ ተናግሯል፦
“አቡ ሁረይራ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አላህ እንዲህ አለ ‹እኔ ለታማኝ ባርያዎቼ ዓይን ያላየችውን፣ ጆሮ ያልሰማውን የሰው ልብ ሊያስበው የማይችለውን (አስደናቂ ነገሮች)› አዘጋጅቻለሁ፡፡››” (Sahih Al-Bukhari, Vol. 9, Book 93, Number 589)
ይህ ቃል በሐዋርያው ጳውሎስ መልእክት ውስጥ እንዲህ ተጽፏል፡-
“ነገር ግን፦ ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንደተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን” (1ቆሮንቶስ 2፡9)፡፡
ከላይ የተጠቀሰው ሐዋርያው ጳውሎስ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱትን የእግዚአብሔርን ተስፋዎች በራሱ አባባል ጨምቆ ያስቀመጠበት ዓረፍተነገር ሲሆን ከእርሱ በሚቀድም በየትኛውም ምንጭ ውስጥ በዚህ መልኩ ተጽፎ አይገኝም፡፡ ይህንኑ ቃል ሙሐመድ “አላህ እዲህ አለ…” በማለት ከአላህ የሰማው መገለጥ በማስመሰል አቅርቦታል፡፡
በሌላ ሐዲስ እንዲሁ ሙሐመድ የሐዋርያው ጳውሎስን ሐሳብ በመቅዳት እንዲህ ሲል ተናግሯል፡-
“ኑዕማን ቢን በሺር እንዳስተላለፈው የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡- የአማኝ ፍቅር፣ መዋደድና መተሳሰብ ልክ እንደ አንድ አካል ነው፡፡ አንዱ የአካል ክፍል እንቅልፍ በማጣትና በትኩሳት ምክንያት ሲታመም መላው አካል አብሮት ይታመማል፡፡” (ሳሂህ ሙስሊም መጽሐፍ 45፣ ሐዲስ ቁጥር 84)
የአማኞች ፍቅርና አንድነት በአካል በመመሰል አስቀድሞ የተናገረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነው፡-
“ክብር ያላቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፥ ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው። አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ።” (1ቆሮ. 12፡24-27)
ከነዚህ በተጨማሪ ጌታችን ኢየሱስ በምፅዓቱ ዕለት የሚሰጠውን ፍርድ በተመለከተ የተናገረውን ሙሐመድ በመቅዳት ለአላህ አድርጎታል፡፡ በሐዲስ ቁድሲ ውስጥ እንዲህ ሲል ተጽፏል፡-
“አቡ ሁረይራ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ማለታቸውን ተናግሯል፡- በዕለተ ትንሣኤ አላህ እንዲህ ይላል፡- የአዳም ልጅ ሆይ፣ ታምሜ አልጠየቅኸኝም፡፡ እርሱም እንዲህ ይለዋል፡- ጌታዬ ሆይ አንተ የዓለማቱ ጌታ ስትሆን እኔ አንተን ጥየቃ እንዴት እመጣለሁ? እርሱም ይለዋል፡- እገሌ የተባለው ባርያዬ በታመመ ጊዜ እንዳልጠየቅኸው ታስታውሳለህን? ብትጎበኘው ኖሮ እኔን እርሱ ዘንድ ታገኘኝ እንደነበር ታውቃለህን? የአዳም ልጅ ሆይ ምግብ ለምኜህ አላበላኸኝም፡፡ ጌታዬ ሆይ አንተ የዓለማቱ ጌታ ስትሆን እኔ ላበላህ እንዴት እችላለሁ? እርሱም ይለዋል፡- እገሌ የተባለው ባርያዬ ምግብ ለምኖህ እንዳላበላኸው ታስታውሳለህን? ብታበላው ኖሮ ምንዳህን ከእኔ ዘንድ ታገኝ እንደነበር ታውቃለህን? የአዳም ልጅ ሆይ እንድታጠጣኝ ለምኜህ አላጠጣኸኝም፡፡ እርሱም እንዲህ ይለዋል፡- ጌታዬ ሆይ አንተ የዓለማቱ ጌታ ስትሆን እኔ የሚጠጣ ነገር ልሰጥህ የምችለው እንዴት ነው? እርሱም ይለዋል፡- እገሌ የተባለው ባርያዬ የሚጠጣ ነገር እንድትሰጠው ለምኖህ ከልክለኸዋል፡፡ ብታጠጣው ኖሮ ምንዳውን ከእኔ ዘንድ ታገኝ ነበር፡፡” (ዘገባው የሙስሊም ሲሆን ሐዲስ ቁጥር 18 ላይ ይገኛል)
ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ ማለቱ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ተጽፏል፡-
“የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፥ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል። ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። ጻድቃንም መልሰው ይሉታል፦ ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን? ንጉሡም መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል። በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል፦ እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። እነርሱ ደግሞ ይመልሱና፦ ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም? ይሉታል። ያን ጊዜ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል። እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።” (ማቴ. 25፡31-46)
ሙሐመድ ከቀኖናዊ ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ሳይሆን ከአፖክሪፋ ወንጌላትና ከአይሁድ ትውፊትም ይቀዳ እንደነበር ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ የቁርአን ብዙ ክፍሎች ከነዚህ መጻሕፍት የተቀዱ መሆናቸው ሊታበል የማይችል ሃቅ ነው፡፡ ለበለጠ መረጃ በርዕሱ ላይ የጻፍነውን ጽሑፍ ያንብቡ፡፡
ውድ ሙስሊም ወገኖቼ፤ ሙሐመድ ከእርሱ ቀደም የተጻፉትን ሐሳቦች በማገጣጠም ከሰማይ የመጣ መገለጥ አስመስሎ ሲናገር እንደነበር ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች ያስረዳሉ፡፡ በቁርአንና በሐዲስ ውስጥ የምታነቧቸው ብዙ ሐሳቦችና የምትተገብሯቸው ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ከሰማይ የመጡ መገለጦች ሳይሆኑ ከሙሐመድ ዘመን በፊት የሚታወቁና ብዙዎቹ ደግሞ ባልታመኑ ምንጮች ውስጥ ሰፍረው የሚገኙ ሰው ሰራሽ አስተምህሮዎችና ሥርዓቶች ናቸውና ንቁ!