የሙሐመድን ነቢይነት የማልቀበልባቸው 12 ምክንያቶች

የሙሐመድን ነቢይነት የማልቀበልባቸው 12 ምክንያቶች

ሙስሊም ወገኖች ክርስቲያኖች ሙሐመድን እንደ እውነተኛ ነቢይ ለምን እንደማይቀበሉ በመገረም ይጠይቃሉ፡፡ ምናልባትም ክርስቲያኖች “የተሳሳቱ ህዝቦች በመሆናቸው” እውነትን ለመቀበል ዝግጁዎች አይደሉም ብለው ያስቡ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እኔ በግሌ እንደ አንድ ክርስቲያን ሙሐመድ በሙሴና በሌሎች ነቢያት አምላክ እንደተላከ የሚያረጋግጥልኝን ማስረጃ ባገኝ ኖሮ ነቢይነቱን የማልቀበልበት ምክንያት አልነበረም፡፡ እውነቱን ለመናገር ግን በእስልምና የመጨረሻው ነቢይ እንደሆነ የሚታመንበት ሙሐመድ እንኳንስ በመጽሐፍ ቅዱስ የነቢይነት መስፈርት ተመዝኖ ይቅርና በእስልምና መጽሐፍት ውስጥ በሰፈረው የግል ታሪኩ እንኳ ነቢይነቱን አምኜ እንዳልቀበል የሚያስገድዱኝ ብዙ ዘገባዎች አሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሙሐመድን እንደ እውነተኛ ነቢይ የማልቀበልባቸውን ምክንያቶች በዝርዝር አቀርባለሁ፡፡

  1. ለነቢይነቱ ተጨባጭ ማስረጃ አለመስጠቱ

የሙሐመድን ነቢይት የማልቀበልበት መሠረታዊው ምክንያት ለነቢይነቱ የሚሆን የረባ ማስረጃ አለማቅረቡ ነው፡፡ ሙሐመድ በመካ ከተማ ስብከቱን ሲጀምር ለነቢይነቱ ማረጋገጫ የሚሆን ምልክት እንዲያሳይ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ጠያቂዎቹን በገሃነም ከማስፈራራትና ጥያቄዎቻቸውን በዘዴ ከማለፍ በዘለለ ምንም ዓይነት ምልክት ማሳየት አልቻለም ነበር፡፡ በሐዲስ መጻሕፍት የተመዘገቡ ብዙ የተዓምራት ታሪኮች ቢኖሩም በቁርኣን ውስጥ ሙሐመድ እንዳደረገው የተመዘገበ ምንም ዓይነት ማስረጃ አለመኖሩ በሐዲሳት የተመዘገቡት ታሪኮች ከክፍለ ዘመናት በኋላ የተጻፉ ተረታ ተረቶች መሆናቸውን ያስገነዝበናል፡፡ በቁርኣን ውስጥ ሙሐመድ ተዓምር ማድረጉን የሚገልፅ ምንም ዓይነት ማስረጃ ካለመኖሩም በላይ ተዓምራትን ማድረግ መቻሉ በገሃድ ተስተባብሏል፡፡ ለአብነት ያህል፡-

ሱራ 2:118 “እነዚያም የማያውቁት (አንተ መልክተኛ ስለመኾንህ) አላህ አያናግረንም ኖሮአልን? ወይም (ለእውነተኛነትህ) ታምር አትመጣልንም ኖሮአልን? አሉ፡፡ እንደዚሁ እነዚያ ከነሱ በፊት የነበሩት እንደ ንግግራቸው ብጤ ብለዋል፡፡ ልቦቻቸው (በክሕደት) ተመሳሰሉ፡፡ ለሚያረጋግጡ ሕዝቦች አንቀጾችን በእርግጥ አብራርተናል፡፡”

ሙሐመድ የመጨረሻውና ታላቁ የፈጣሪ ነቢይ አድርጎ ራሱን ከማቅረቡ አንፃር የአድማጮቹ ጥያቄ ተገቢና ትክክል ነበር፡፡ ከፈጣሪ ነቢያት ሁሉ የላቀ ደረጃና አስፈላጊነት እንዳለው የተናገረ ሰው ቢያንስ ከእነርሱ ጋር የሚስተካከል ተዓምራትን እንዲያደርግ መጠበቅ በከሃዲነት አያስፈርጅም፡፡ ከነቢያት ሁሉ የላቀ ደረጃ አለኝ፣ የመጨረሻው ነቢይ ነኝ፣ ገነት እንድትገቡ ተከተሉኝ፣ ከገዛ ነፍሳችሁ ይልቅ ውደዱኝ፣ ለእኔ ተጋደሉ፣ ለእኔ ሙቱ፣ እኔን መታዘዝ ማለት ፈጣሪን መታዘዝ ማለት ነው፣ ወዘተ. እያለ ራሱን ከፍጥረት በላይ ከፈጣሪ ጥግ አድርሶ የሚጓደድ ጀብራሬ “እንደ ቀደሙት ነቢያት ተዓምር ባለማድረጌ ካላመናችሁብኝ ከሃዲያን ናችሁ” ብሎ ማለቱ ትዝብት ላይ ይጥለዋል፡፡

ሱራ 6:37 “«ከጌታውም በእርሱ ላይ ለምን ተዓምር አልተወረደም» አሉ፡፡ «አላህ ተአምርን በማውረድ ላይ ቻይ ነው» በላቸው፡፡ ግን አብዛኞቻቸው አያውቁም፡፡”

ጠያቂዎቹ እውነተኛው አምላክ ለነቢያቱ ተዓምራትን የማድረግ ኃይል ሊሰጣቸው እንደሚችል ባያምኑ ኖሮ ሙሐመድ ተዓምራትን እንዲያደርግ ባልጠየቁት ነበር፡፡ ስለዚህ “አብዛኞቻቸው አያውቁም” የሚለው የሙሐመድ ወቀሳ ተራ ውንጀላ ነው፡፡

ሱራ 6:109 “ተዓምርም ብትመጣላቸው በእርሷ በቁርጥ ሊያምኑ ጥብቅ መሐሎቻቸውን በአላህ ማሉ፡፡ «ተዓምራት ሁሉ አላህ ዘንድ ናት» በላቸው፡፡ እርሷ በመጣች ጊዜም አለማመናቸውን (ወይም ማመናቸውን) ምን አሳወቃችሁ፡፡”

ሱራ 13:27 “እነዚያም የካዱት፥ በርሱ ላይ ከጌታው ታምር ለምን አልተወረደም ይላሉ፤ አላህ የሚሻውን ያጠማል፤ የተመለሰውንም ሰው ወደርሱ ይመራል፥ በላቸው።”

ሱራ 17:59 “ታምራቶችንም ከመላክ የቀድሞዎቹ ሰዎች በርሷ ማስተባበልና (መጥፋት) እንጂ ሌላ አልከለከልንም፤ ለሠሙድም ግመልን ግልጽ ታምር ሆና ሰጠናቸው፤ በርሷም በደሉ፤ታምራቶችንንም ለማስፈራራት እንጂ አንልክም።”

በዚህ ጥቅስ ደግሞ አላህ በሙሐመድ በኩል ተዓምር ከማድረግ የታቀበበትን ምክንያት ሲገልፅ የቀድሞ ሰዎች ክደው ስለጠፉ ነው የሚል ሰበብ ይሰጣል፡፡ ፈጣሪ በነቢያቱ በኩል ተዓምራትን እየሠራ ብዙ ክፍለ ዘመናትን ካሳለፈ በኋላ “የመጨረሻው፣ ታላቁና የነቢያት አለቃ” ጋር ሲደርስ ማቆሙ አስገራሚ ነው፡፡ ለነዚያ ሁሉ ክፍለ ዘመናት ተዓምራትን እየላከ “ሰዎችን እያጠፋ መኖሩን” ልክ የሙሐመድ ዘመን ላይ ሲደርስ ተገንዝቦት ይሆን? ምን የሚሉት ስላቅ ነው!

ሱራ 28:48 “እውነቱም ከእኛ ዘንድ በመጣላቸው ጊዜ «ለሙሳ የተሰጠው ብጤ አይስሰጠውም ኖሯልን» አሉ፡፡ «ከዚህ በፊት ሙሳ በተሰጠው አልካዱምን የተረዳዱ ሁለት ድግምቶች ናቸው» አሉ፡፡ «እኛ በሁሉም ከሓዲዎች ነንም» አሉ፡፡”

ሙሐመድ ተዓምራትን ማሳየት ባለመቻሉ ምክንያት የሙሴን ተዓምራት አስፈላጊነት አሳንሶ ለማሳየት ሲጣጣር ይታያል፡፡ ሙሴ ያንን ሁሉ ተዓምር ባያሳይ ኖሮ እስራኤላውያንን ከባርነት ነፃ ማውጣት ባልቻለ ነበር፡፡ ሙሐመድም የእውነተኛ ነቢያት ምልክቶችን ማሳየት ቢችል ኖሮ አረቦችን ለማስለም ሰይፍ መምዘዝ ባላስፈለገው ነበር፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች ሁሉ እንደሚያሳዩት ሙሐመድ ተዓምራትን እንዲያደርግ በተጠየቀ ጊዜ ሁሉ ጠያቂዎቹን ከመውቀስ በዘለለ ለጥያቄዎቻቸው ተገቢውን ምላሽ መስጠት አልቻለም፡፡ ከዚህም አልፎ ሙሐመድ ተዓምር ማድረግ እንደማይችልና አስፈራሪ (በቃላት የሚያስፈራራና የሚያስጠነቅቅ) ሰው ብቻ መሆኑን ቁርኣን እንዲህ ሲል የማያወላዳ ማረጋገጫ ይሰጣል፡-

ሱራ 13:7 “እነዚያም የካዱት፥ በርሱ ላይ ከጌታው ታምር ለምን አልተወረደለትም ይላሉ፤ አንተ አስፈራሪ ብቻ ነህ ለሕዝብም ሁሉ መሪ አላቸው።”

ሙሐመድ ተዓምራትን ማድረግ የማይችልበት ምክንያት አስፈራሪ ብቻ ስለሆነ መሆኑን ይህ ጥቅስ በግልፅ ይናገራል፡፡ ቁርኣን እንዲህ በግልፅ ሙሐመድ ተዓምር የመሥራት ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ችሎታ እንደሌለው በተናገረበት ሁኔታ ሐዲሳትና ሌሎች እስላማዊ መጻሕፍት ሙሐመድ ብዙ ተዓምራትን ማድረጉን መናገራቸው ትክክል አይደለም፡፡

ሌላው የእውነተኛ ነቢያት መታወቂያ ትክክለኛና ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚፈፀሙ ትንቢቶችን መናገር ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትክክል የተፈፀሙ እጅግ በርካታ ትንቢቶች ተመዝግበዋል፡፡ ነገር ግን በቁርኣንም ሆነ በእስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ የረባ ትንቢታዊ መልእክት አይደገኝም፡፡ አንዳንድ ሙስሊሞች እንደ ትንቢት የሚጠቅሷቸው ይዘቶች እጅግ አሻሚና አንዳንዶቹ እንዲያውም የሐሰት ትንቢቶች መሆናቸው የተረጋገጡ ናቸው፡፡

ሙስሊም ወገኖች ለሙሐመድ ነቢይነት ማረጋገጫ አድርገው በዋናነት የሚያቀርቡት ቁርኣንን ነው፡፡ ሥነ ጽሑፋዊ ውበቱ እጅግ የላቀ መሆኑ የፈጣሪ መጽሐፍ መሆኑን ያረጋግጣል ይላሉ፡፡ ዳሩ ግን ውበት እንደ ተመልካቹ በመሆኑ እንዲህ ካለው ግላዊ መመዘኛ በመነሳት የዘላለም መኖርያዬን የሚወስነውን እርምጃ መውሰድን ከሞኝነት እቆጥረዋለሁ፡፡

የሙሐመድን ነቢይነት ለመቀበል ሰበብ የሚሆን አዎንታዊ ነገር አለመኖሩ እውነተኛ ነቢይ አለመሆኑን ለማረጋገጥ በራሱ ብቻውን በቂ ቢሆንም በማስከተል ደግሞ ነቢይነቱን እንዳልቀበል ምክንያት የሆኑኝን አሉታዊ ምክንያቶች አቀርባለሁ፡፡

  1. ከቀደሙት ነቢያት ጋር የሚጋጭ ትምሕርት ማስተማሩ

ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ጀምሮ እስከ ጌታ ሐዋርያት ድረስ የሚገኙትን ቅዱሳን ሰዎች ስንመለከት መልእክታቸው ተያያዥና ተደጋጋፊ መሆኑን እናስተውላለን፡፡ አንዱ በሌላው ላይ የተገነባ ከመሆን ባለፈ አንዱ የሌላውን መልእክት ሲጣረስና ሲያፈርስ አይታይም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ገዢ የሆነው ትራኬ የእግዚአብሔር ፍጥረቱን የመዋጀት ሒደት ሲሆን ከዘፍጥረት መጽሐፍ ጀምሮ የዓለም ፍፃሜን እስከሚያሳየው እስከ ራዕይ መጽሐፍ ድረስ ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ በዚህ ሰንሰለት እርስ በርሳቸው ተሳስረውና ተጋምደው እንመለከታለን፡፡ ይህንን ገዢ ትራኬ የነገረ መለኮት ሊቃውንት The Crimson Thread በማለት የሚጠሩት ሲሆን እግዚአብሔር አንድያ ልጁን በመላክ ከእርሱ ተለይቶ የወደቀውን ፍጥረት ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ያቀደውን ዕቅድና ፍጻሜውን የሚያመለክት በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ከመጀመርያው አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ የተዘረጋ የታሪክና የአስተምሕሮ ሰንሰለት ነው፡፡

የሙሐመድ ቁርኣን ይህንን የነቢያት ሁሉ መልእክት የሚጻረርና ዓላማውንም የክርስቶስን መልእክትና ተልዕኮ መቀልበስ ያደረገ ነው፡፡ የሙሐመድ ቁርኣን ይህንን የቅልበሳ ግብ ከዳር ለማድረስ የተጠቀመው ዘዴ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ወደ ክርስቶስ የሚያመለክቱ ክስተቶችን፣ ስብዕናዎችን፣ ሥርዓቶችንና አስተምህሮዎችን ከእንደገና መተርጎም ነው፡፡ ቁርኣን ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሰንሰለት (የክሪምሰን ሰንሰለት) ለማስወገድ የነቢያትን መልእክት በመከለስና አቅጣጫን በማስለወጥ አማራጭ እስላማዊ ሰንሰለትን አዘጋጅቷል፡፡ ይህም የቅዱሳን ነቢያት ሁሉ መልእክት ሙሐመድ የመጨረሻው ነቢይ መሆኑን መጠቆም ነው የሚል ነው፡፡[1] ይህ ግን ፍፁም ሐሰትና የነቢያትን መልእክት የሚጻረር ነው፡፡

ሙሐመድ የፈጠረው ሃይማኖት የአንድ አምላክ ካባን የለበሰና የነቢያትን ታሪኮች የሚጠቃቅስ እንዲሁም የቀደሙትን ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያረጋግጥ መሆኑን የሚለፍፍ ቢሆንም ቅሉ የቅዱሳት መጻሕፍት ዋና መልእክት የሆነውን የክርስቶስን ተልእኮ ስለሚክድ ፈፅሞ ከእግዚአብሔር ሊሆን አይችልም፡፡ ሙሐመድ እውነተኛ ነቢይ እንደሆነ ከተቀበልን የቀደሙት ነቢያት ሁሉ ሐሰተኞች ይሆናሉ፡፡ የቀደሙት ነቢያት እውነተኞች ከሆኑ ደግሞ ሙሐመድ እውነተኛ ነቢይ የሚሆንበት ምንም ዓይነት ዕድል ሊኖር አይችልም፡፡

ይህንን ርዕሰ ጉዳይ በማንሳት ከሙስሊም ወገኖቼ ጋር በምወያይበት ጊዜ ሁሉ የሚሰጡኝ የተለመደ ምላሽ “የቀደሙት ቅዱሳት መጻሕፍት በሙሉ ስለተበረዙ እንጂ የሙሐመድ መልእክት ከቀደሙት ነቢያት መልእክት ጋር አንድ ነው” የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍት ስለመበረዛቸው ማስረጃዎችን እንዲሰጡኝ በምጠይቅበት ጊዜ ሁሉ የረባ ምላሽ አግኝቼ አላውቅም፡፡ ይህ ምላሽ ለምን እንደማያስኬድና የሙስሊሞች ብሒል እውነት ከሆነ እስልምና ሐሰት መሆኑን ከማረጋገጥ የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ለማወቅ እስላማዊ አጣብቂኝ በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁትን ጽሑፍ ታነቡ ዘንድ እጋብዛለሁ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳልተበረዘ የሚያረጋግጡ የጥንታውያን መዛግብት ማስረጃዎችን ለማየት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች  በሚል ርዕስ ያሰባሰብኳቸውን መረጃዎች ትመለከቱ ዘንድ አበረታታችኋለሁ፡፡

  1. የክርስቶስን ስቅለት መካዱ

የክርስቶስን ስቅለት በተመለከተ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-

“እኛ የአላህን መልክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲህ ዒሳን ገደልን በማለታቸው (ረገምናቸው) ፡ አልገደሉትም አልሰቀሉትምም ነገር ግን ለነሱ (የተሰቀለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ፡፡ እነዝያ በሱ ነገር የተለያዩት ከርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡ ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በሱ ነገር ምንም እውቀት የላቸውም፡፡ በእርግጥም አልገደሉትም፡፡ ይልቁንስ አላህ ወደርሱ አነሳው፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡” (አል-ኒሳ 4፡157-158)

የክርስቶስ ስቅለት ከነገረ መለኮታዊ ሙግት በመለስ የታሪክ ሃቀኝነት ጉዳይ ነው፡፡ ሙስሊም ወገኖች የክርስቶስን ስቅለት በተመለከተ የሚያቀርቧቸው ነገረ መለኮታዊ ሙግች ክርስቲያኖች ለክርስቶስ ስቅለት የሰጡትን ትርጓሜ ለማስተባበል ያገለግል ይሆናል፤ ነገር ግን ክርስቶስ እንዳልተሰቀለ በማስተባበል ቁርኣንን ከታሪካዊ ስህተቱ መታደግ አይችልም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የክርስቶስ ስቅለት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ በሚገኙ ዓለማውያንና መንፈሳውያን መዛግብት ውስጥ የሰፈረ መሆኑ ነው፡፡ የኢየሱስን ስቅለት በተመለከተ ከአራቱ ወንጌላት በተጨማሪ በዘመኑ በነበሩት የታሪክ ምሑራን የተጻፉ ብዙ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-

  1. ሮማዊው ጸሐፌ ታሪክ ቆርኖሌዎስ ታሲተስ የኢየሱስን ስቅለት ጽፏል፡፡[2]
  2. አይሁዳዊው ጸሐፌ ታሪክ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን የኢየሱስን ስቅለት በማያሻማ ቃል ጽፏል፡፡[3]
  3. የባቢሎናውያን ታልሙድ ኢየሱስ በፋሲካ ዋዜማ መሰቀሉን ይናገራል፡፡[4]
  4. ኢስጦኢክ ፈላስፋ የነበረው ማራ በር ሰራፒዮን ለልጁ በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ የኢየሱስን ሞት ጠቅሷል፡፡[5]
  5. ሉሺያን የተሰኘ ግሪካዊ ጸሐፊ ኢየሱስ መገደሉን ጽፏል፡፡[6]
  6. ፍሌጎን የተሰኘ ሮማዊ ጸሐፊ ስለ ኢየሱስ መሰቀል ብቻ ሳይሆን በስቅለቱ ወቅት በምድር ላይ ስለወደቀው ጨለማና ስለ ምድር መናወጥ እንዲሁም ስለ ትንሣኤው ጽፏል፡፡[7]

ከነዚህ በተጨማሪ ከአዲስ ኪዳን ውጪ የኢየሱስ ሞት ተዘግቦ የምናገኘው በጥንት የቤተ ክርስቲያን አበው ጽሑፎች ውስጥ ነው፡፡ የሐዋርያው ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረው ፖሊካርፕ የክርስቶስን ሞት ደጋግሞ የጻፈ ሰው ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ከጽሑፎቹ መካከል በአንዱ ውስጥ “ስለ ኃጢአታችን እስከ ሞት ድረስ መከራን የተቀበለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ…” በማለት አስፍሯል፡፡ የፖሊካርፕ ወዳጅ የነበረው የእስክንድርያው ኢግናጢዎስ በበኩሉ “በእውነት መከራን ተቀብሎ ከሞተ በኋላ ተነስቷል… ጌታችንን የሰቀሉት ፈሪሃ እግዚአብሔር የሌላቸው ሰዎች ነበሩ” በማለት ጽፏል፡፡[8] የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያን ጸሐፊ የነበረው ዮስቶኒዮስ ሰማዕትም ትሪፎ ለተሰኘ አይሁዳዊ በሰጠው ምላሽ በእርሱ ዘመን የነበሩት አይሁድ ኢየሱስን “የተሰቀለ ገሊላዊ” በማለት ይጠሩት እንደነበር ጽፏል፡፡[9]

እነዚህ ሁሉ ታሪካዊ ማስረጃዎች በአንደኛው ክፍለዘመንና በሁለተኛው ክፍለዘመን መጀመርያ ላይ የተጻፉ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ጌታችን ከመወለዱ ከብዙ ክፍለ ዘመናት በፊት ስለ ስቅለቱ ቅዱሳን ነቢያት ተንብየዋል (ኢሳ. 53፡1-12፣ ዳን. 9፡24-25፣ መዝ. 22፡12-18)፡፡

ይህ ሁሉ ስፍር ቁጥር የሌለው ማስረጃ ባለበት ሁኔታ ከ600 ዓመታት በኋላ፣ ከምድረ እስራኤል ቢያንስ በ1000 ኪሎሜትሮች ርቆ ይኖር የነበረ አረብ ነጋዴ ወደ ዋሻ ገብቶ በመውጣት ክርስቶስ እንዳልተሰቀለ መልአክ እንደነገረው ተናገረ፡፡ የነጋዴው ንግግር ግልፅ ባለመሆኑም ምክንያት ሙስሊም ተርጓሚዎች ከሰማይ ወረደ የተባለውን ቃል ትርጉም እንዲሰጥ ለማድረግ የግል ማብራርያዎቻቸውን በቅንፍ ለማስገባት ተገድደዋል፡፡ በክርስቶስ ምትክ ተሰቅሏል የተባለው ሰው ማንነትም ስላልተጠቀሰ ሙስሊም ሊቃውንት ለክፍፍል ተዳርገዋል፡፡ አንዳንዶች ከአይሁድ መካከል አንዱ ተሰቅሏል በማለት ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ የተሰቀለው ከሮማውያን ወታደሮች መካከል አንዱ ነው ይላሉ፡፡ ከዒሳ ተከታዮች መካከል አንዱ በፍቃደኝነት መሞት ስለፈለገ አላህ የዒሳን መልክ ሰጥቶት ተሰቀለ የሚሉም አሉ፡፡ ‘‘የበርናባስ ወንጌል’’ በሚል ስም በመካከለኛው ዘመን በአንድ ሙስሊም የተጻፈ መጽሐፍ ደግሞ በምትኩ የሞተው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነው ይላል፡፡

በዚህ ዘመን የሚገኙት የታሪክ ሊቃውንት በክርስቶስ ስቅለት ዙርያ አንዳች ልዩነት የላቸውም፡፡ የክርስቶስን ስቅለት ለማስተባበል መሞከር በዓለም የታሪክ ሊቃውንት ፊት መሳቂያና መሳለቂያ የሚያደርግ በመሆኑ በዘመናችን የሚገኙት የተማሩ ሙስሊሞች የቁርአኑን ቃል በተለየ መንገድ በመተርጎም የክርስቶስን ስቅለት ወደ መቀበል እየመጡ ነው፡፡ ዒሳ እንደተሰቀለ ነገር ግን በመስቀል ላይ በነበረ ጊዜ እንዳልሞተና ራሱን እንደሳተ የሚናገር ትወራ በአሁኑ ወቅት በተለይም በተማሩት ሙስሊሞች ዘንድ በስፋት ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል፡፡ ይህ አስተሳሰብ “ራስን የመሳት ትወራ” (Swoon Theory) በመባል የሚታወቅ ሲሆን ቬንቹሪኒ በተሰኘ ሰው በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የተጀመረ ነው፡፡ ግንባር ቀደም ሙስሊም ዐቃቤ እምነት የነበሩት ሼኽ አሕመድ ዲዳት እና የዘመናችን ስመጥር ተሟጋች የሆኑት ዶ/ር ሻቢር አሊን የመሳሰሉት ሙስሊሞች ያቀነቅኑታል፡፡ ከእስላማዊ ቡድኖች መካከል የኔሽን ኦፍ ኢስላም (NOI) እና የአሕመዲያ ጎራዎች እንደ እምነት አቋም ይዘውታል፡፡

እንግዲህ የተማሩት ሙስሊሞች ሙሐመድ ስለ ክርስቶስ ስቅለት የፈፀመው የታሪክ ቅጥፈት አሳፍሯቸው ከስህተቱ ራሳቸውን እያሸሹ በሚገኙበት ዘመን አንዴት ብዬ እንደ እውነተኛ ነቢይ ልቀበለው? የክርስቶስን ስቅለት በተመለከተ ሙሐመድ የፈፀመውን ስህተት በስፋት ያብራራሁበትን እስልምናና የመሲሁ ስቅለት በሚል ርዕስ የተጻፈውን ጽሑፍ አንብባችሁ የራሳችሁን ፍርድ ስጡ፡፡

  1. የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት መተላለፉ

እግዚአብሔር አምላክ በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ የሰጣቸው ትዕዛዛት ከሞላ ጎደል ሁሉም ሊባል በሚቻልበት ሁኔታ በሙሐመድ ተጥሰዋል፡፡ እነዚህ ትዕዛዛት በዘጸአት 20 ላይ ይገኛሉ፡፡ እስኪ አንድ በአንድ እንመልከት፡፡

የመጀመርያው ትዕዛዝ፡- “ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም…”

ሙሐመድ አንዱና እውነተኛ የሆነውን የእስራኤልን አምላክ ሰብኳልን? በፍፁም! የሙሐመድ አምላክ ከአረብ ጣኦታውያን የተኮረጀ እንጂ ለአብረሃምና ለሙሴ የተገለጠው ያሕዌ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ የዚህ አምላክ ማንነት የጣዖታት ከተማ ከነበረችው ከመካ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑ ከቁርኣንና ከሌሎች እስላማዊ ጽሑፎች ግልፅ ነው፡፡ ሙሐመድ የእውነተኛው አምላክ የግል ስም የሆነውን ያሕዌ የሚለውን ስም ከመጠቀም ይልቅ አረብ ጣዖታውያን ሲጠቀሙበት የነበረውን አላህ የሚለውን ቃል የፈጣሪ ትክክለኛ ስም በማስመሰል አቅርቧል፡፡ ከሙሴ ዘመን ጀምሮ የነበሩት እውነተኛ ነቢያት ሁሉ ያሕዌ በሚለው የእግዚአብሔር የግል ስም የተናገሩና ያስተማሩ ቢሆንም ሙሐመድ ግን ይህንን ስም ጭራሽ አያውቀውም፡፡

በተጨማሪም በመጀመርያው ትዕዛዝ ውስጥ ያሕዌ እግዚአብሔር የተቀረፁ ምስሎችን በመስራት ለእነርሱ መስገድን አጥብቆ ቢከለክልም ሙሐመድ ግን አረብ ጣዖታውያን ሲሰግዱለት ለኖሩት ጥቁር ድንጋይ በመስገድ፣ እርሱን በመሳምና በመተሻሸት በመላው ዓለም የሚገኙት ሙስሊሞች የእርሱን ፈለግ በመከተል አምልኮተ ጣዖትን እንዲለማመዱ ምክንያት ሆኗል፡፡[10] ሙስሊም ወገኖች ጥቁሩን ድንጋይ እንደማያመልኩትና እንደማይሰግዱለት ቢናገሩም በተግባር ግን ወደ ድንጋዩ ዞረው በመስገድ፣ ድንጋዩን በመዞር፣ በመሳምና በመተሻሸት አምልኮተ ጣዖትን ይለማመዳሉ፡፡ ይህንን ጥያቄ ለሙስሊም ወገኖቼ ሳቀርብ ተግባራቸው በብሉይ ዘመን ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ዞረው ከመጸለያቸው ጋር አንድ እንደሆነና የሚፈፅሙትም ሥርኣት በመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ ያለው መሆኑን ይገልጹልኛል፡፡ ዳሩ ግን አይሁድ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ዞረው የሚጸልዩበት ምክንያት እግዚአብሔር አምላክ በገሃድ ክብሩን በቤተመቅደሱ ውስጥ ስለገለጸ የእግዚአብሔር ክብር መገኛና መገለጫ ቦታ መሆኑን ስለሚያውቁ ነው (1ነገሥት 8፡10)፡፡ ነገር ግን የመካ ካዕባ ቀደም ሲል በ360 ጣዖታት የተሞላ አረማውያን ብዙ ርኩስ ተግባራትን የሚፈፅሙበት የረከሰ ቦታ እንጂ የእግዚአብሔር ክብር የተገለጠበት ቦታ አይደለም፡፡ የሚገርመው ነገር ሙሐመድ መጀመርያ አካባቢ እንደ አይሁድ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ዞሮ ይሰግድ የነበረ ቢሆንም ኋላ ላይ ግን አይሁድ ስለ ተዘባበቱበት በመበሳጨት የስግደት አቅጣጫውን ወደ መካ እንዲዞር አድርጓል፡፡ በጊዜው ደግሞ 360 ጣዖታት በቦታው ይመለኩ ነበር (ሱራ 2፡150)፡፡

ሁለተኛው ትዕዛዝ፡- “የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና።”

ሙሐመድ እውነተኛ አምላክ ብሎ የሚጠራውን የአላህን ስም በከንቱ በመጥራት ይህንን ትዕዛዝ በተደጋጋሚና በተለያዩ መንገዶች ተላልፏል፤ ሙስሊሞችም እንዲተላለፉ ምክንያት ሆኗል፡፡ የመጀመርያው የጣሰበት መንገድ በአላህ ስም የማላቸውን መሀላዎች ማፍረስ እንደሚቻል በማስተማር ነው፡፡

ሱራ 66:1-2 “አንተ ነቢዩ ሆይ አላህ ለአንተ የፈቀደልህን ነገር ሚስቶችህን ማስወደድን የምትፈልግ ስትሆን (ባንተ ላይ) ለምን እርም ታደርጋለህ፤ አላህ እጅግ መሐሪ አዛኝ ነው። አላህ ለናንተ የመሐሎቻችሁን መፍቻ ደነገገላችሁ፤ አላህም ረዳታችሁ ነው፤ እርሱም ዐዋቂው ጥበበኛው ነው።”

“Allah has already ordained for you [Muslims] the dissolution of your oaths. And Allah is your protector, and He is the Knowing, the Wise.”

ሙስሊም ሊቃውንት ይህ ጥቅስ ለምን “እንደ ወረደ” ሲናገሩ ሙሐመድ የሚስቶቹን ተራ ላለማጠፍ በመሀላ ቃል የገባ ቢሆንም የአይሻን ወይንም የሐፍሷን ተራ በማጠፍ ግብፃዊቷ መርየም ከተሰኘችው ሚስቱ (የጭን ገረዱ) ጋር ወሲብ በመፈፀሙ ምክንያት አላህ ከመሀላው ነፃ መሆኑን ለመግለፅ ያወረደለት መገለጥ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ፍፁምና ቅዱስ በሆነው አምላክ ላይ መሳለቅ አይደለምን?

ሌላው ሙሐመድ የአምላክን ስም በከንቱ በመጥራት ያቀለለበት መንገድ ሙስሊሞች በረባው ባልረባው በአላህን ስም በመጥራት እንዲምሉ ምሳሌ በመሆን ነው፡፡ በእስላማዊ ሐዲሳት ውስጥ ብዙ ጊዜ ሙሐመድ “ወሏሂ” (በአላህ እምላለሁ) የሚለውን አባባል የንግግሩ ማጀቢያ አድርጎት እንመለከታለን፡፡ ዛሬም ሙስሊሞች በትንሽ በትልቁ “ወሏሂ” እያሉ ሲምሉ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ሃይማኖታቸውን እንደሚያውቁ የሚናገሩ ብዙ ሙስሊሞች ለሃይማኖታቸው ግድ ከሌላቸው ደካማ ክርስቲያኖች በከፋ ሁኔታ የአምላካቸውን ስም በረባው ባልረባው እየጠሩ በመማልና በመገዘት ሲያቃልሉት ማየት የተለመደ ነው፡፡

ሦስተኛው ትዕዛዝ፡- “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ። ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፡፡”

ሙሐመድ እግዚአብሔር ለክብሩ ከመረጠው ዕለተ ሰንበት ይልቅ የመዲና የገበያ ቀን የሆነውን ዕለተ አርብን በመምረጥ የእስልምና ቅዱስ ቀን እንዲሆን አድርጓል፡፡ በዚህም እስልምና ከቀደሙት ነቢያት ጋር ተያያዥነት እንደሌለውና የአረቦችን ሁኔታ ብቻ ያገናዘበ መሆኑን አረጋግጧል፡፡[11]

የሆነው ሆኖ ሰንበትን ማክበር ከሥርዓታዊ ሕግጋት የሚመደብና ግብረ ገባዊ ሕግ ባለመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ማጥበቅ አልሻም፡፡ እስኪ ቀጣዩን ትዕዛዝ እንመልከት፡፡

አራተኛው ትዕዛዝ፡- “አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም።”

የሙሐመድ አባት ከልደቱ በፊትና ወላጅ እናቱ በህፃንነቱ በመሞታቸው ምክንያት  ይህንን ትዕዛዝ የመተግበር ዕድል አላገኘም፡፡ ሆኖም ሙሐመድ በዕድሜ ከእርሱ የሚበልጡትን ንፁሀን ወንዶችና ሴቶችን መዝረፉ፣ መግደሉና ማሳደዱ እናትና አባቱን ካለማክበር ይቆጠራል፡፡ እናም ይህንንም ትዕዛዝ እንዳልጠበቀ መናገር ይቻላል፡፡

አምስተኛው ትዕዛዝ፡- “አትግደል፡፡”

እስልምና የሰላም ሃይማኖት ነውን? በሚል ርዕስ ባዘጋጀሁት ጽሑፍ ውስጥ በስፋትና በጥልቀት እንዳሳየሁት ሙሐመድ ብዙ ንፁህ ደም በማፍሰስ ይህንን አምላካዊ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡ ከእርሱ ትምሕርትና ምሳሌነት የተነሳም በክፍለ ዘመናት ሁሉ ሙስሊሞች ላፈሰሱት ንፁህ ደም በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ ይሆናል፡፡

ስድስተኛ ትዕዛዝ፡- “አታመንዝር፡፡”

ምንዝርና ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈፀም ነው፡፡ ሙሐመድ ምንዝርናን ከመፈፀሙም በላይ አመንዝራነትን ፈቅዷል፡፡ ቁርኣን ከጋብቻ ውጪ ከሴት ባርያዎች ጋር ወሲብ መፈፀም እንደሚቻል እንዲህ ይናገራል፡-

ሱራ 70፡29-30 “እነዚያም እነሱ ብልቶቻቸውን ጠባቂዎች የሆኑት። በሚስቶቻቸው ወይንም እጆቻቸው በያዙዋቸው (ባሮች) ላይ ሲቀር። እነሱ (በነዚህ) የማይወቀሱ ናቸውና።

ሱራ 23፡5-6 “እነዚያም እነርሱ ብልቶቻቸውን ጠባቂዎች የሆኑት (አገኙ)፡፡ በሚስቶቻቸው ወይም እጆቻቸው በያዟቸው (ባሪያዎች) ላይ ሲቀር፡፡ እነርሱ (በነዚህ) የማይወቀሱ ናቸውና፡፡

እነዚህ ጥቅሶች ሙስሊም ወንዶች በጋብቻ ከተጣመሯቸው ሚስቶቻቸውና ከሚያገለግሏቸው ሴት ባርያዎቻቸው ጋር ወሲብ ቢፈፅሙ ወቀሳ እንደሌለባቸው ይናገራሉ፡፡ በሐዲስ መጻሕፍት ውስጥ ሙስሊም ወንዶች ይህንን ተግባር በሙሐመድ ይሁንታ ይፈፅሙ እንደነበር ተጽፏል፡-

…አቡ ሲርማ ለአቡ ሰዒድ አለ-ኹድሪ እንደነገረው፡ “አቡ ሰዒድ ሆይ የአላህ መልእክተኛ ስለ አዝል (የዘር ፈሳሽ ሳይፈስስ ብልትን ከሴት ማህፀን ስለማውጣት) ሲናገር ሰምተህ ታውቃህን?” ብሎ ጠየቀው፡፡ “አዎን” በማለት መለሰ፤ እንዲህ ሲልም አከለ “ከአላህ መልእክተኛ ጋር ወደ አል ሙስጠሊቅ በዘመትን ጊዜ ውብ የሆኑ የአረብ ሴቶችን ማርከን ነበር፤ ሚስቶቻችን ከኛ ጋር ስላልነበሩ የፍትወት ፍላጎት እጅግ አይሎብን የነበረ ቢሆንም በተመሳሳይ እነርሱን የማስለቀቂያ ወጆ መቀበልም ፈልገን ነበር፡፡ ስዚህ አዝል እያደረግን (እንዳይፀንሱ የዘር ፈሳሻችንን ውጪ በማፍሰስ) ከእነርሱ ጋር ወሲብ ለመፈፀም ወሰንን፡፡ ነገር ግን እንዲህ አልን፡ ‹‹የአላህ መልእክተኛ ከኛ ጋር እያለ ይህንን ነገር እየፈፀምን ነው፡፡ ለምን አንጠይቀውም?›› ስለዚህ የአላህን መልእክተኛ በጠየቅነው ጊዜ እንዲህ ሲል መለሰልን፡ “እስከ ዕለተ ትንሣኤ ድረስ የሚወለዱ ነፍሶች ሁሉ መወለዳቸው ስለማይቀር እንደርሱ ባታደርጉ ምንም ችግር የለውም፡፡”[12]

ከዚህ ሐዲስ እንደምንረዳው ሙሐመድ ወታደሮቹ ከጋባቻ ውጪ እንዲዘሙቱ ከመፍቀዱም በላይ እነዚህ ምርኮኛ ሴቶች መፀነሳቸው የወታደሮቹን ያህል አላሳሰበውም፡፡ እንዲህ ያለውን ሰው ነቢይ ብሎ መከተል ምንኛ መታወር ነው!

ሙሐመድ እራሱ ግብፃዊቷ መርየም ከተሰኘች ባርያው ጋር ወሲብ ይፈፅም እንደነበር እስላማዊ መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡[13]

የሙሐመድ የወሲብ ፍላጎት እጅግ ከፍ ያለ ከመሆኑ የተነሳ በአንድ ሌሊት ከ 9 ሚስቶቹ ጋር ወሲብ ይፈፅም እንደነበር እስላማዊ ሐዲሳት ይዘግባሉ፡፡[14] በሌላ የሐዲስ ዘገባ ደግሞ በአንድ ቀን 11 ሚስቶቹን ይጎበኝ እንደነበርና የ30 ወንዶች ያህል የወሲብ ጉልበት እንደነበረው ተነግሮለታል፡፡[15] ይህ ልማዱ እንደ ጀግንነት ቢነገርለትም ሴሰኝነት ጀግንነት ሳይሆን ደካማነት መሆኑን አእምሮው በትክክል የሚያስብ ሰው ሁሉ የሚያውቀው እውነታ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ቁርኣን ሙስሊም ወንዶች በሰማይ ቤት ከደናግላን ጋር ወሲብ እንደሚፈፅሙ ይናገራል፡-

ሱራ 44፡54 “(ነገሩ) እንደዚሁ ነው፤ ዓይናሞች የሆኑን ነጫጭ ሴቶች እናጠናዳቸዋለን።”

ሱራ 55፡56 “በውስጣቸው ከበፊታቸው (ከባሎቻቸው በፊት) ሰውም ጅንም ያልገሠሣቸው ዓይኖቻቸውን (በባሎቻቸው ላይ) አሳጣሪዎች (ሴቶች) አልሉ።”

ሱራ 55፡70-74 “በውስጣቸው ጠባየ መልካሞች መልከ ውቦች (ሴቶች) አልሉ። ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ? በድንኳኖች ውስጥ የተጨጐሉ፥ የዓይኖቻቸው ጥቁረትና ንጣት ደማቅ የሆኑ ናቸው። ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ? ከነሱ በፊት፥ ሰውም ጃንም አልገሠሣቸውም።”

ሱራ 56፡34-37 “ከፍ በተደረጉ ምንጣፎችም፣ (ሴቶችም፣ መካከል)። እኛ አዲስ ፍጥረት አድርገን (ለነሱ) ፈጠርናቸው። ደናግሎችም አደረግናቸው። ለባሎቻቸው ተሽሞርሟሪዎች፣ እኩያዎች (አደረግናቸው)።”

ሱራ 78፡31-33 “ለጥንቁቆቹ መዳኛ ስፍራ አላቸው። አትክልቶችና ወይኖችም። እኩያዎች የሆኑ ጡተ ጉቻማዎችም።”

ሙሐመድ ሙስሊም ወንዶች በገነት 72 ደናግላንን እንደሚሸለሙ መናገሩ በሐዲስ መጻሕፍት ተዘግቧል፡፡[16] ሙሐመድ አመንዝራነት በምድር ብቻ ሳይሆን በሰማይም እንደተፈቀደ በማስተማር በእውነተኛው አምላክ ላይ የተሳለቀ ሰው ነው፡፡

ሰባተኛው ትዕዛዝ፡- “አትስረቅ።”

የሙሐመድን ዘራፊነት ማስተባበል አይቻልም፡፡ ከመካ ወደ መዲና ከተሰደደ በኋላ ያደረገው የመጀመርያው ነገር ሽምቅ ተዋጊዎችን በመላክ የመካ ነጋዲያንን ማስገደልና ማስዘረፍ እንደነበር ከእስላማዊ ጽሑፎች መረዳት ይቻላል፡፡

በቁርኣን ውስጥ ሱረቱ አል-አንፋል (የጦር ዘረፋዎች ምዕራፍ) ተብሎ በተሰየመው ምዕራፍ የመጀመርያው ቁጥር ላይ እንዲህ ተብሏል፡-

ሱራ 8:1 “ከጦር ዘረፋ ገንዘቦች ይጠይቁሃል፤ የዘረፋ ገንዘቦች የአላህና የመልክተኛው ናቸው፤ ስለዚህ አላህን ፍሩ፤ በመካከላችሁ ያለችውንም ሁኔታ አሳምሩ፤ አማኞችም እንደሆናችሁ፣ አላህንና መልክተኛውን ታዘዙ በላቸው።”

ሙሐመድ ተከታዮቹ በትጋት በመሥራት የገዛ እንጀራቸውን እንዲበሉና ሃይማኖታቸውን እንዲጠቅሙ ከማስተማር ይልቅ ዝርፍያን በማበረታታት ራሱና ተከታዮቹ የግፍ ሐብትን እንዲያከማቹ አድርጓል፡፡ በሙሐመድ ዘመን የነበሩት አረቦች ወደ እስልምና በብዛት እንዲጎርፉ ካደረጓቸው ነገሮች መካከል አንዱ በአላህ መንገድ እየተጋደሉ ቢሞቱ ገነትን እንደሚወርሱና በሕይወት ቢተርፉ ደግሞ በዘረፋ ገንዘብ እንደሚበለፅጉ የተሰጣቸው ተስፋ ነበር፡፡[17]

ስምንተኛው ትዕዛዝ፡- “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።”

ሙሐመድ በመዋሸትና ውሸትን በመፍቀድ ይህንን አምላካዊ ትዕዛዝ አፍርሷል፡፡ በዚህ ዝርዝር 7ኛው ቁጥር ላይ እናየዋለን፡፡

ዘጠነኛው ትዕዛዝ፡- “የባልንጀራህን ሚስት … አትመኝ፡፡”

ሙሐመድ ይህንን ትዕዛዝ በመተላለፍ የማደጎ ልጁን ሚስት አግብቷል፡፡ ይህንንም በተራ ቁጥር 9 ላይ እንመለከተዋለን፡፡

አሥረኛው ትዕዛዝ፡- “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ።”

ሙሐመድ የኸይበር አይሁድ ብዙ ያከማቹት ኃብት መኖሩን በመስማቱ ምክንያት ወረራ እንደፈፀመባቸው እስላማዊ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ የኃብት ክምችታቸው የት እንደሚገኝ ለማውጣጣት የጎሣ መሪውን በሚዘገንን ሁኔታ አሠቃየው፡፡ በአል-ጠበሪ የተጻፈው ታሪክ እንዲህ ይላል፡-

“ነቢዩ ኪናና የተባለውን ሰው በተመለከ ለዙባይር እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጡ ‹በውስጡ የደበቀውን ሁሉ እስኪያወጣ ድረስ አሰቃየው፡፡› ስለዚህ ዙባይር ኪናና ለሞት እስኪቃረብ ድረስ ደረቱ ላይ እሳት አስቀመጠበት፡፡ ከዚያም ነቢዩ ለመስለማህ አሳልፈው ሰጡት፡፡ እርሱም አረደው፡፡”[18]

ከዚህ ታሪክ እንደምንረዳው ሙሐመድ የጎረቤቶቹን ኃብት መመኘቱ አሣቃቂ ግድያዎችን እንዲፈፅም አድርጎታል፡፡ እናም የጎረቤቶቻችንን ኃብት እንዳንመኝ የሚከለክለውን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ከመተላለፉም በተጨማሪ ንፁህ ደምን ማፍሰስን የሚከለክለውን ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡

  1. የአምላኩን ስም የግል ጥቅሞቹን ለማስከበር መጠቀሙ

ሙስሊሞች ሙሐመድ የአላህ መልእክተኛና አገልጋይ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ዳሩ ግን ቁርኣንንና ሌሎች እስላማዊ መጻሕፍትን ያነበብን እንደሆን እውነታው የተገላቢጦሽ ነው፡፡ አላህ የሙሐመድ አገልጋይና ጉዳይ አስፈፃሚ፣ ቁርኣንም ደግሞ የሙሐመድ የግል ሰነድ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ሙሐመድ የግል ምኞቱን ለማሳካት የአላህን ስም ሲጠቀምና ዘላለማዊ የአላህ ቃል እንደሆነ የሰበከውን ቁርኣንን እንደ መሣርያ ሲጠቀም እናስተውላለን፡፡

ለምሳሌ ያህል ሙሐመድ ብዙ ሴቶችን የማግባት ፍላጎቱን ከግብ ለማድረስ በአላህ ሽፋን እንዲህ ሲል ተናግሯል፡-

ሱራ 33:50 “አንተ ነቢዩ ሆይ! እኛ እነዚያን መህሮቻቸውን የሰጠሃቸውን ሚስቶችህን፣ አላህ ባንተ ላይ ከመለሰልህም እነዚያን እጅህ የጨበጠቻቸውን ምርኮኞች፣ እነዚያንም ከአንተ ጋር፣ የተሰደዱትን የአንጎትህን ሴቶች ልጆች፣ የአክስቶችህንም ልጆች፣ የየሹማህንም ሴቶች ልጆች ፣ የየሹሜዎችሕንም ሴቶች ልጆች (ማግባትን) ለአንተ ፈቅደንልሃል፤ የአመነችንም ሴት ነፍሷን (ራሷን) ለነቢዩ ብትሰጥ ነቢዩ ሊያገባት የፈለገ እንደ ሆነ፣ ከምእምናን ሌላ ላንተ ብቻ የጠራች ስትሆን፣ (ፈቀድንልህ)፤ በነርሱ (በምእምናን) ላይ በሚስቶቻቸውና እጆቻቸውም በጨበጧቸው (ባሮች ነገር) ግዴታ ያደረግንባቸው በእርግጥ አውቀናል፤ ባንተ ላይ ችግር እንዳይኖር፣ (ያለፉትን ፈቀድንልህ)፤ አላህም መሐሪ አዛኝ ነው።”

ሙሐመድ መልከ መልካም እንደሆኑ ያሰባቸውን ዘመዶቹን ጨምሮ በዙርያው የሚገኙትን ሴቶች አግበስብሶ የማግባት ምኞት ስላደረበት እንጂ ከአላህ ዘንድ ሰምቶ እንዳልተናገረ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፡፡ እውነተኛና ቅዱስ የሆነው አምላክ የአንድን ሰው የፍትወት ጥማት ለማርካት እንዲህ ያለውን ትዕዛዝ የዘላለማዊ ቃሉ አካል አድርጎ ምድር ከመፈጠሯ በፊት ጽፎ አስቀምጧል ማለት ትልቅ የስድብና የክህደት ንግግር ነው፡፡

በአንድ ወቅት ደግሞ ሙሐመድ ሰዎች ሳያስፈቅዱ ወደ ቤቱ ዘው ብለው በመግባታቸው ምክንያት ተበሳጨ፤ የሚስቶቹንም ልብ እንዳይሰርቁ ሰጋ፤ እናም አገልጋዩ አላህን እንዲህ ሲል አናገረው፡-

ሱራ 33:53 “እላንተ ያመናችሁ ሆይ መድረሱን የማትጠባበቁ ስትሆኑ ወደ ምግብ ካልተፈቀደላችሁ በስተቀር የነቢዩን ቤቶች (በምንም ጊዜ) አትግቡ፤ ግን በተጠራችሁ ጊዜ ግቡ በተመገባች ሁም ጊዜ ወዲያውኑ ተበተኑ፤ ለወግ የምትጫወቱ ኾናችሁም (አትቆዩ) ፤ ይሃችሁ ነቢዩን በእርግጥ ያስቸግራል፤ ከናንተም ያፍራል፤ ግን አላህ ከውነት አያፍርም ዕቃንም (ለማዋስ) በጠየቃችኋቸው ጊዜ፣ ከመጋረጃ ኋላ ኾናችሁ ጠይቋቸው፤ ይሃችሁ በልቦቻችሁ፤ ለልቦቻቸውም የበለጠ ንጽሕናን ነው፤ የአላህም መልክተኛ ልታስቸግሩ ሚስቶቹንም ከርሱ በኋላ ምንጊዜም ልታስቡ ለናንተ አይገባች ሁም፤ ይሃችሁ አላህ ዘንድ ከባድ (ኅጢአት) ነው።”

በአንድ ወቅት ደግሞ ሙሐመድ የቤቱ ደጅ ላይ ሆነው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሚጠሩት ሰዎች ምክንያት ተበሳጨ፤ እናም አገልጋዩ አላህ እንዲህ ሲል እንዲናገርለት አደረገ፡-

ሱራ 49:4 “እነዚያ ከክፍሎቹ ውጭ ሆነው የሚጠሩህ አብዛኞቻቸው አያውቁም። ወደነርሱም እስክትወጣ ድረስ እነርሱ በታገሡ ኖሮ ለነርሱ በላጭ በሆነ ነበር፤ አላህም እጅግ መሐሪ አዛኝ ነው።”

ሙሐመድ የአምላኩን ስም የግል ጥቅሙን ለማስከበር በእንቶ ፈንቶ ጉዳዮች ሲጠቀም የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንዲህ ያሉ የአንድን ግለሰብ ጊዜያዊና ግላዊ ጥቅም ለማስከበር የታለሙ መንፈሳዊ ርባና የሌላቸውን ነገሮች ፈጣሪ በዘላለማዊ ቃሉ ውስጥ እንዲካተቱ አድርጓል ብሎ ለማመን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ዐይንን ጨፍኖ በዚያ ላይ በወፍራም ጨርቅ ተሸፍኖ ለማየት ከመሞከር ጋር ሊነፃፀር የሚችል ጭፍንነት ይጠይቃል፡፡

  1. ባስተማረው ትምሕርት አለመኖሩ

ማራ በር ሰራፒዮን የተሰኘ ፈላስፋ በ70 ዓ.ም. ገደማ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲጽፍ እንዲህ አለ፡-

“ሶቅራጥስን በመግደል የአቴንስ ሰዎች ምን አተረፉ? ድርቅና ወረርሽኝ ለሰሩት ወንጀል እንደ መቀጣጫ መጣባቸው፡፡ የሳሞስ ሰዎች ፓይታጎረስን በማቃጠላቸው ምን አተረፉ? በቅጽበት መሬታቸው በአሸዋ ተሸፈነ፡፡ አይሁድ ጥበበኛ ንጉሣቸውን በመግደላቸው ምን አተረፉ? ልክ ከዚያ በኋላ መንግሥታቸው አከተመለት፡፡ አምላክ ለነዚህ ሦስት ሰዎች በትክክለኛ ፍረድ ተበቀለለላቸው፡፡ አቴናውያን በረሃብ ሞቱ፡፡ ሳሞሳውያን በባህር ሰጠሙ፡፡ አይሁድ ተፍረክርከው ከምድራቸው ላይ በመባረር ሙሉ በሙሉ ተበትነው ኖሩ፡፡ ነገር ግን ሶቅራጥስ መሞቱ ለበጎ አልሆነም፡፡ በፕላቶ ትምህርት ኖሯልና፡፡ ፓይታጎረስ መሞቱ ለበጎ አልሆነም፡፡ በሄራ ሐውልት ውስጥ ኖሯልና፡፡ ጥበበኛውም ንጉሥ መሞቱ ለበጎ አልሆነም፡፡ ራሱ ባስተማረው ትምህርት ኖሯልና፡፡[19]

የእውነተኛ የእግዚአብሔር ሰው አንዱ መገለጫ ባስተማረው ትምሕርት መኖሩ ነው፡፡ ነገር ግን ሙሐመድ ቀደም ሲል ከአምላኩ ዘንድ እንደተሰጡ ያስተማራቸውን ትዕዛዛት በመተላለፍ የወደደውን ሲያደርግ እንመለከታለን፡፡ ለምሳሌ ያህል ቁርኣን ለአንድ ሙስሊም ወንድ እንዲያገባ የሚፈቅደው እስከ አራት ሚስቶች ብቻ ነው (ሱራ 4፡3)፡፡ ነገር ግን በታሪክ እንደሚታወቀውና ሙስሊም ምሁራን እንደተስማሙበት ከሆነ ሙሐመድ ወደ አሥራ ሦስት ሚስቶችን በማግባት በቁርኣን ከተፈቀደው ከሦስት እጥፍ በላይ ሚስቶች ነበሩት፡፡ ታዲያ ሙሐመድ ይህንን ትዕዛዝ ተላልፎ ነው ይህን ያደረገው ወይስ ትእዛዙ እርሱን የማይመለከት ሆኖ ነው? ይህ ትዕዛዝ እርሱን አይመለከትም ካልን ለምን? የሚል ጥያቄ ማስከተል ተገቢ ነው፡፡ አንድ ነቢይ እውነትኛነቱ የሚታወቀው በተናገረው መልዕክት መኖር ሲችል ነው፡፡ እርሱ ያላደረገውን (ማድረግ የማይችለውን) ትዕዛዝ በሌላው ላይ የሚጭን መምህር ጥሩ ሞዴል ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም፡፡ ሙሐመድ ለራሱ አሥራ ሦስት ሚስቶችን አግብቶ ሌሎችን ግን “አላህ የፈቀደላችሁ እስከ አራት ማግባት ብቻ ነው” ማለቱ የሚናገራቸውን መገለጦች ሲፈልግ ለራሱ ጥቅም እንደሚገለገልባቸው ማሳያ ነው፡፡

  1. ውሸትን መፍቀዱ

በዓለም ላይ ከሚገኙት ታላላቅ ሃይማኖታት መካከል እስልምና ውሸትን የሚፈቅድ ብቸኛው ሃይማኖት ነው፡፡ በእስልምና ውስጥ ብዙ የተፈቀዱ የውሸት ዓይነቶች አሉ፡፡ የሱኒ ሙስሊሞች “ሙደራት” የተሰኘ የአታላይነት አስተምህሮ አላቸው፡፡ በሺኣ ሙስሊሞች ዘንድ ደግሞ “ታቂያ” በመባል ይታወቃል፡፡ ከኡላማ (ከእስልምና ሊቃውንት) ክበብ ውጪ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ስለዚህ አስተምህሮ ብዙም አያውቁም፡፡ “ሙደራት” ማለት ማደናነቅ፣ የግብዝነት አድናቆት፣ ማታለል፣ ቆዳን ማስወደድ፣ ማጭበርበር፣ እኩል መራመድ፣ መሸፈን፣ መደበቅ ወይንም መሰወር ማለት ነው፡፡ ይህ የማታለል ጠባይ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ሰዓት ሁሉ በማንም ላይ ተግባራዊ ሊደረግ ይችላል፡፡ ነገር ግን የሱኒ ምሑራን  በቋሚነት የሙደራት ዒላማ ውስጥ መግባት አለባቸው ያሏቸውን አሥር ዓይነት ሰዎች ለይተው አስቀምጠዋል፡፡ ካፊር (ሙስሊም ያልሆነ ሰው)፣ “ክፉ” የሆነ መሪ፣ አዲስ የሰለሙ ሰዎች፣ ከእስልምና ልቡ ያፈነገጠውን ሰው ወደ እስልምና ለመመለስ፣ አማኞች ያልሆኑትን በመምሰል የሳተን ሙስሊም ለመመለስ፣ የተማረን ሰው ወይንም ሳይንቲስት ከዕውቀቱ ለመጠቀም፣ ጓደኛን ለማስደሰት፣ ከጠላት ለማምለጥ ወይም ለመጉዳት፣ የትዳር አጋርን ለማስደሰት፣ የታመመ ሰው (ለምሳሌ ያህል ደህና እንደሚሆን ወይንም ደህና መምሰሉን በመንገር)፡፡ የሱኒ ሊቃወንት ይህንን አመለካከት ለማፅደቅ የተለያዩ የቁርኣን ጥቅሶችን ይጠቅሳሉ፡፡[20]

ሙሐመድ አንድ ሙስሊም በአደጋ ውስጥ በሚሆንበት ሰዓት ሃይማኖቱን እስከ መካድ የሚደርስ ውሸትን መዋሸት እንደሚችል በማስተማር ሙስሊም መሆንን ርካሽ አድርጎታል (16፡106)፡፡ ነገር ግን እውነተኛ አማኞች የሆኑት ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብድናጎ አምላካቸውን ክደው ለጣዖት እንዲሰግዱ በንጉሥ ናቡከደነፆር በታዘዙ ጊዜ እንዲህ የሚል ምላሽ በመስጠት እሳት ውስጥ መጣልን መርጠዋል፡-

“ናቡከደነፆርም፦ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ሆይ፥ አምላኬን አለማምለካችሁ፥ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም መለሱ ንጉሡንም፦ ናቡከደነፆር ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም። የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ! ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት።” (ዳንኤል 3፡16-18)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃልም ሆነ በተግባር በእምነት ፀንቶ ስለመገኘት እንዲህ ብሏል፡-

“ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ። ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ ተቈጥሮአል። እንግዲህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ። ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።” (ማቴዎስ 10፡28-33)

ክርስትና የሕይወት መንገድ ስለሆነ ክርስቲያን መሆን ውድ ነው፡፡ እስልምና ሰው ሰራሽ ሃይማኖት ስለሆነ ሙስሊም መሆን ቀላልና ርካሽ ነው፡፡ ነገሮች ሲከብዷችሁ ትክዱታላችሁ፤ ሲመቻችሁ አብራችሁ ትጎርፋላችሁ፡፡

ሙሐመድ በአንድ ወቅት ከኣብ ኢብን አል-አሽራፍ የተሰኘውን ሰው ለመግደል የእርሱ ወዳጅ የነበረው ሙሐመድ ቢን መስለማ የተሰኘ ሰው ውሸትን እንዲጠቀም ፈቃድ ሰጥቶት ነበር፡፡[21]

በእስልምና የሸሪኣ መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ተብሏል፡- it is permissible to lie if attaining the goal is permissible. የሚፈለገው ግብ የተፈቀደ ከሆነ (ትክክል ከሆነ) መዋሸት የተፈቀደ ነው እንደ ማለት ነው፡፡[22] ስለዚህ በዚህ ረገድ ያለው እስላማዊ አስተምሕሮ “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” ዓይነት ነው፡፡ እስልምና በምንም መስፈርት እውነተኛና ቅዱስ ከሆነው አምላክ ዘንድ ሊሆን አይችልም፡፡

  1. ከ 9 ዓመት ህፃን ጋር መተኛቱ

ሙሐመድ ከፈፀማቸው አስደንጋጭ ተግባራት መካከል አንዱ አይሻ የተሰኘችውን ጨቅላ ሚስቱን በ6 ዓመቷ አጭቷት በ9 ዓመቷ አብሯት መተኛቱ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ማስተባበል በማይቻልበት ሁኔታ በእስላማዊ ሐዲሳትና የሙሐመድ ግለ-ታሪኮች ውስጥ በግልፅ የሰፈረ ሲሆን ሙስሊም ወገኖች ድርጊቱን ለማፅደቅ እንጂ ለማስተባበል ሲጨነቁ እምብዛም አይታዩም፡፡[23] ድርጊቱ ትክክል መሆኑን ለማሳየት ሙስሊሞች የሚጠቅሷቸው ምክንያቶች በሙሉ ለምን ሊያስኬዱ እንደማይችሉ ሙሐመድ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰችውን አይሻን ስለ ማግባቱ – ለሙስሊሞች ምላሽ የተሰጠ ምላሽ በሚል ርዕስ በጻፍኩት ጽሑፍ በቂ ምላሽ ሰጥቻለሁ፡፡

ሙሐመድ ለጨቅላ ህፃናት ፆታዊ ፍላጎት እንደነበረው የሚያሳዩ ሌሎች ታሪኮች በእስላማዊ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ሙስናድ አህመድ ኢብን ሐንበል ሐዲስ ቁጥር 25636 ላይ እንዲህ ተፅፏል፡-

“የአባስ ልጅ ኡም ሐቢባ ጡት በመጥባት ዕድሜ ላይ ሳለች በዳዴ ስትሄድ ተመልክቷት ነቢዩ እንዲህ አለ፡- ወሏሂ እኔ በሕይወት እያለሁ የምታድግ ከሆነ አገባታለሁ፡፡”[24]

እንዲህ ያለውን ሰው እንደ እውነተኛ ነቢይ መቀበል እንደ እውነቱ ከሆነ የጤና ምልክት አይደለም፡፡ ብዙ ሙስሊሞች ይህንን ሚስጥር ካወቁ በኋላ ሙሐመድን ከመከተል እንደሚመለሱ ጥርጥር የለኝም፡፡

  1. የማደጎ ልጁን ሚስት መንጠቁ

ሙሐመድ “የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ” የሚለውን አምላካዊ ትዕዛዝ በመተላለፍ የማደጎ ልጁ የዘይድ ሚስት የነበረችውን ዘይነብን ተመኝቷታል፤ ስለ ውበቷም ባልተገባ መንገድ በመናገር ትዳሯን ካናጋ በኋላ አግብቷታል፡፡ ይባስ ብሎ ይህንን አስነዋሪ ተግባሩን ለማፅደቅ በቁርኣን ውስጥ አገልጋዩ አላህን እንዲህ ሲል እንዲናገርለት አድርጎታል፡-

ሱራ 33:37 “ለዚያም አላህ በርሱ ላይ ለለገሰለትና (አንተም ነጻ በማውጣት) በርሱ ላይ ለለገስክለት ሰው (ለዘይድ)፥ አላህ ገላጩ የኾነን ነገር በነፍስህ ውስጥ የምትደብቅና አላህ ልትፈራው ይልቅ የተገባው ሲኾን፣ ሰዎችን የምትፈራ ሆነህ ፦ ሚስትህን ባንተ ዘንድ ያዝ፤ (ከመፍታት) አላህንም ፍራ፤ በምትል ጊዜ፥ (አስታውስ) ዘይድንም ከርሷ ጉዳይን በፈጸመ ጊዜ በምእምናኖች ላይ፣ ልጅ አድርገው ባስጠጉዋቸው (ሰዎች) ሚስቶች፥ ከነሱ ጉዳይን በፈጸሙ ጊዜ (በማግባት) ችግር እንዳይኖርባቸው፥ እርሷን አጋባንህ፤ የአላህም ትእዛዝ ተፈጻሚ ነው።”

በዚህ የቁርኣን ጥቅስ መሠረት ሙሐመድ ዘይነብን ተመኝቷት ነበር፡፡ ነገር ግን ሰዎች ምን ይሉኛል በሚል እፍረት ዘይድ ሚስቱን እንዳይፈታ ግብዛዊ በሆነ መንገድ ይመክረው ነበር፡፡ ዳሩ ግን አላህ ጉዳዩን አደባባይ በማውጣት ዘይነብን ዳረለት፡፡ ለዚህም ሙስሊሞች የማደጎ ልጆቻቸውን ሚስቶች ከፍቺ በኋላ ማግባት እንደሚችሉ ምሳሌ ለመሆን ነው የሚል ደካማ ምክንያት ቀርቧል፡፡ ነገር ግን ሙሐመድ ዘይነብን የተመኛት ባለትዳር በነበረችበት ጊዜ በመሆኑና ስለ ውበቷ ባልተገባ መንገድ መናገሩ ለትዳሯ መናጋትና ለፍቺ ምክንያት መሆኑ በእስላማዊ ሐዲሳት ውስጥ በግልፅ ተጽፎ ስለሚገኝ “ምሳሌ ለመሆነ ነው” የሚለው ሰበብ አሳማኝ አይደለም፡፡[25]

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ አለ፡-

“አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።” (ማቴዎስ 5፡27-28)

ሙሐመድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የላቀ የሥነ ምግባር ልኬት መሠረት አመንዝራ ነው፡፡

  1. ለጥቁሮች የነበረው ዝቅተኛ አመለካከት

ሙሐመድ ለጥቁሮች ከፍተኛ ንቀት እንደነበረውና የሰዎችን ሰብዓዊ ዋጋ በቆዳ ቀለም የሚለካ ሰው እንደነበር እስላማዊ መጻሕፍት ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ሙሐመድ እንዲህ በማለት ሰይጣንና ጥቁር ሰውን አመሳስሏል፡-

“ነቢዩ እንዲህ አሉ፡- ‹‹ሰይጣንን ማየት የሚፈልግ ሰው ነብጣል ኢብን አል-ሐሪሥን ይመልከተው!›› ጥቁር ሰው ሲሆን የተንጨባረረ ረጅም ፀጉርና ጥቁር መንጋጋዎች አሉት፡፡”[26]

የጥንት ሙስሊሞች ሙሐመድ ጥቁር መሆኑን የሚናገር ሰው ይገድሉ ነበር፡-

“የሰህኑን ወዳጅ የነበረው አሕመድ ኢብን አቢ ሱለይመን እንዲህ አለ፡- ‹‹ማንኛውም ነቢዩ ጥቁር እንደሆኑ የሚናገር ሰው ይገደላል፡፡ ነቢዩ ጥቁር አልነበሩም››፡፡”[27]

ሙሐመድ ጥቁር ባርያዎች እንደነበሩት በብዙ እስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ በተደጋጋሚ ተዘግቧል፡፡[28] ጥቁር ባርያዎችንም በስጦታ ይቀበል እንደነበር ተነግሯል፡፡[29]

በአንድ ወቅት አንድ ባርያ በሁለት ጥቁር ባርያዎች እንደለወጠ እስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ ተጽፏል፡-

“ጃቢር ኢብን አብዱላህ እንዳስተላለፈው፡- አንድ ባርያ ወደ አላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) በመምጣት ቃል ኪዳን ያዘ፡፡ ነቢዩም ባርያ መሆኑን አላወቁም ነበር፡፡ አሳዳሪው በመምጣት ባርያው እንዲመለስለት በጠየቀ ጊዜ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ‹‹ሽጥልኝ›› አሉት? በሁለት ጥቁር ባርያዎችም ገዙት፡፡”[30]

ለኢትዮጵያውያን ያለውን ንቀትና ዘረኛ አመለካከት እንዲህ በማለት ገልጧል፡-

“የእናንተ መሪ ዘቢብ (የደረቀ የወይን ፍሬ) የመሰለ ጭንቅላት ያለው ኢትዮጵያዊ ቢሆን እንኳ ታዘዙት፡፡”[31]

እንዲህ ያለ የዘረኝነት አመለካከት የነበረው ሰው እውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢይ ሊሆን አይችልም፡፡

  1. ፍቺን መፍቀዱ

እንደ እስልምና ፍቺን ያቀለለ ሃይማኖት ያለ አይመስለኝም፡፡ ሙሐመድ የፈለገውን እንዲፈታና የፈለገውን እንዲያስጠጋ አላህ ፈቃድ እንደሰጠው ቁርኣን እንዲህ ሲል ይናገራል፡-

ሱራ 33:51 “ከነሱ የምትሻትን ታቆያለህ፤ ይምንሻትንም ወደ አንተ ታስጠጋለህ፤ (በመፍታት) ከአራቅሃትም የፈለግሃትን፥ (በመመለስ ብታስጠጋ)፥ በአንተ ላይ ሐጢያት የለብህም፤ ይህ ዓይኖቻቸው ወደ መርጋት፣ ወደ አለማዘናቸውም፥ ለሁሉም በሰጠሃቸው ነገር ወደ መውደዳቸውም በጣም የቀረበ ነው፤ አላህም በልቦቻችሁ ውስጥ ያለውን ሁሉ ያውቃል፤ አላህም ዐዋቂ ታጋሽ ነው።”

የፍቺ ነፃነት ለሙሐመድ ብቻ ሳይሆን ለሙስሊም ወንዶች ሁሉ የተሰጠ ነው፡-

ሱራ 4፡20 “በሚስትም ስፍራ ሚስትን ለመለወጥ ብትፈልጉ፣ ለአንደኛዪቱ (ለምትፈታው) ብዙን ገንዘብ የሰጣችኋት ስትሆኑ ከርሱ ምንንም አትውሰዱ። በመበደልና ግልጽ በሆነ ኃጢያት ትወስዱታላችሁን?”

በዚህ ጥቅስ መሠረት ሙስሊም ወንዶች ሚስት መለወጥ ቢፈልጉ ማድረግ ያለባቸው ለተፈቺዋ ብዙ ገንዘብ መስጠት ነው፡፡ ፍቺ ያን ያህል ቀላል ነው፡፡ ነገር የእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡-

“ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ ሌላይቱንም የሚያገባ ያመነዝራል፡፡ ከባልዋም የተፋታችውን የሚያገባ ያመነዝራል፡፡” (ሉቃስ 16፡18)

“ሚስትህ ባልንጀራህና የቃልኪዳንህ ሚስት ሆና ሳለች እርስዋን አታለሃታልና እግዚአብሔር ባንተና በልጅነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለሆነ ነው፡፡እግዚአብሔር የህይወትን መንፈስ አንድ አዱርጎ ጠብቆልን የለምን? እርሱም የሚፈልገው ምንድ ነው? ዘር አይደለምን? ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ፡፡ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል፡፡ መፋታትን እጠላለሁ ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፡፡ ልብሱንም በግፍ ስራ የሚከድነውን ሰው እጠላለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፡፡ ስለዚህ እንዳታታልሉ መንፈሳችሁን ጠብቁ፡፡” (ሚልክያስ 2፡14-16)

ሙሐመድ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላውን ተግባር ያፀደቀና አቅልሎ ያቀረበ ሰው በመሆኑ እውነተኛ ነቢይ ሊሆን አይችልም፡፡

  1. በድግምት ቁጥጥር ስር መውደቁ

አይሻ እንደዘገበችው ላቢድ ቢን አል-አስማ የተባለ ሰው በሙሐመድ ላይ ድግምት በመሥራቱ ሳብያ ሙሐመድ ሚስቶቹ በሌሉበት ከሚስቶቹ ጋር እየተኛ እንደሆነ ይመስለው ነበር፡፡ እንኳንስ በእግዚአብሔር ነቢይ ላይ ይቅርና በእግዚአብሔር በእውነት ባመነ በማንኛውም ሰው ላይ አስማት እንዴት ሊሠራ ይችላል? የበለአም አስማት እንኳንስ በሙሴ ላይ ሊሠራ ይቅርና በሙሴ ከሚመራው ህዝብ መካከል በአንዱ ላይ እንኳ ሊሠራ አልቻለም፡፡ ይልቅስ ይህንን የተረዳው አስማተኛው በለአም “በያዕቆብ ላይ አስማት የለም በእስራኤልም ላይ ሟርት የለም” በማለት መስክሯል (ዘኁልቁ 23፡23)፡፡

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ ጌታ ኢየሱስ የአጋንንት ኃይል በስሙ ባመኑት ሰዎች ላይ እንደማይሠራና ይልቁኑ በስሙ አጋንንትን ከሰዎች ውስጥ እንዳሚያስወጡ ተናግሯል፡፡ ይህ ተስፋ በሐዋሪያት ዘመን ሲሠራ ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን እየሠራ እንደሆነ ማንም አይቶ መመስከር ይችላል (ማርቆስ 16፡17-18)፡፡

ማጠቃለያ

እኔ እንደ አንድ ሰው ከላይ በተጠቀሱትና ወደፊትም በተከታታይ በማቀርባቸው በሌሎች ብዙ ምክንያቶች ሙሐመድን እንደ እውነተኛ ነቢይ ልቀበለው ከቶ አልችልም፡፡ ብዙ ሙስሊም ሰባኪያን እነዚህ የነቢያቸው እውነተኛ ገፅታዎች አደባባይ እንዲወጡባቸው አይፈልጉም፡፡ ይህ ሀቀኝነት የጎደለው አካሄድ ነው፡፡ አሁን ግን ይህ አካሄዳቸው ፈፅሞ እንደማያዋጣቸው ሊያውቁት ይገባል፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ለመረጃ ቅርብ ሆኗልና፡፡ ስለዚህ የሚያዋጣቸው እውነትን መደበቅ ሳይሆን ተጋፍጠው ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መልስ መስጠት አለበለዚያ ደግሞ ለእውነት እጅ ሰጥቶ አቅጣጫን ማስተካከልና ሌሎችንም ማስተማር ነው፡፡

ጌታ እግዚአብሔር የሙስሊም ወገኖቼን የልብ ዓይኖች በመክፈት ወደ ልጁ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን ይመራቸው ዘንድ የዘወትር ጸሎቴ ነው፡፡

———————————-

[1] ሳም ሰለሞንና አጢፍ ደብስ፣ ያሕዌ እግዚአብሔርና አላህ  አንድ ናቸውን? ገፅ 10

[2] Josh McDowell, Evidence that Demands a Verdict, New and Revised, 1999, pp. 122-123

[3] Ibid., p. 125

[4] Ibid., pp. 123-124

[5] Ibid., p. 123

[6] Norman L. Geislere, Encyclopedia of Christian Apologetics, 1999, p. 128

[7] Ibid.

[8] Ibid.

[9] Ibid.

[10] Sahih al-Bukhari, Volume 2, Book 26, Number 673

[11] https://www.answering-islam.net/Books/MW/friday.htm

[12] Sahih Al-Bukhari Vol 3 Book 46 Hadith 718

[13] Kitab al-Tabaqat al-Kabir, p. 151

[14] Sahih Al-Bukhari Vol 7 Book 62 Hadith 142

[15] Sahih Al-Bukhari, volume 1 Book 5 Hadith 268

[16] Sunan Ibn Majah, Vol 5 Book 37 Hadith 4337

[17]  Sahih Al-Bukhari, Vol. 4, Book 52, Hadith 46

[18] Al-Tabari; Vol. 8, p. 122

[19] Josh McDowell, Evidence that Demands a Verdict, New and Revised, 1999, p. 123

[20] Sam Solomon & E. Al-Maqdisi. Al-Hijra, Islamic Migration: Accepting Freedom or Imposing Islam?; 2009, pp. 72-79

[21] Sahih Bukhari Vol 5 Book 59 Hadith 369

[22] Ahmad ibn Naqib al-Misri, The Reliance of the Traveller, translated by Nuh Ha Mim Keller, amana publications, 1997, section r8.2, page 745

[23] Sahih Al-Bukhari, Volume 5, Book 58, Number 234; Volume 5, Book 58, Number 236; Volume 9, Book 87, Number 140; see also Number 139; Volume 7, Book 62, Number 64; see also Numbers 65 and 88; Sahih Muslim, Book 008, Number 3309; see also 3310; Book 008, Number 3311Sunan Abu Dawud, Number 2116; Book 41, Number 4915; Book 13, Number 2380;

[24] Musnad Ahmed, Number 25636

[25] Sahih Muslim, Book 008, Number 3330

[26] Ibn Ishaq, Sirat Rasulallah, translated as, The Life of Muhammad by A. Guillaume, page 243

[27] Qadi ‘Iyad Musa al-Yahsubi, Muhammad Messenger of Allah (Ash-Shifa of Qadi ‘Iyad), translated by Aisha Abdarrahman Bewley [Madinah Press, Inverness, Scotland, U.K. 1991; third reprint, paperback], p. 375 & 387

[28] Sahih Bukhari, Volume 9, Book 91, Number 368

[29] Malik’s Muwatta, Book 21, Number 21.13.25

[30] Sahih Muslim, Book 10, Number 3901

[31] Sahih al-Bukhari Book Number 89 Hadith Number 256

 

ነቢዩ ሙሐመድ