“የበርናባስ ወንጌል” እውነተኛ ወንጌል ነውን?

“የበርናባስ ወንጌል” እውነተኛ ወንጌል ነውን?

ሙስሊም ወገኖች የኢየሱስን ስቅለት ለማስተባበል ከሚጠቀሙባቸው ምንጮች መካከል አንዱ “የበርናባስ ወንጌል” የተሰኘው ሲሆን ብዙዎቹ በጳውሎስ ወዳጅ በበርናባስ እን

ደተጻፈ ያምናሉ፡፡ ነገር ግን ይህ መሰረት የለሽና ተስፋ የመቁረጥ ሙግት ነው፡፡ የበርናባስ ወንጌል በመካከለኛው ዘመን በጣልያን አገር በአንድ ሙስሊም የተጻፈ የፈጠራ ጽሑፍ ሲሆን ከአንደኛው ክፍለ 

ዘመን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም፡፡ ሙስሊም ወገኖች ብዙ ጊዜ “የበርናባስ ወንጌል” የተሰኘውን ጽሐፍ ከበርናባስ መልዕክት ጋር ሲያም

ታቱ ይስተዋላል፡፡ የበርናባስ መልዕክት ተብሎ የተሰየመው መጽሐፍ በበርናባስ የተጻፈ ባይሆንም ነገር ግን “ከበርናባስ ወንጌል” በተፃራሪ ፍፁም ክርስቲያናዊ ነው፡፡[1] የበርናባስ ወንጌል የአንደኛው ክፍለ ዘመን ጽሑፍ አለመሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ነጥቦች በውስጡ ይገኛሉ፡-

  • “ክርስቶስ” የሚለው የግሪክ ቃል እና “መሲህ” የሚለው የእብራይስጥ ቃል “የተቀባ” የሚል ተመሳሳይ ትርጉም ያላቸው ሲሆን በአንደኛው ክፍለ ዘመን የኖረ የትኛውም አይሁዳዊ ሁለቱ ቃላት ተመሳሳይ ትርጉም እንዳላቸው ያውቃል፡፡ በርናባስን የመሰለ የግሪክ ቋንቋ ከሚነገርባት ከአሌክሳንደርያ የመጣ አይሁዳዊ ይህንን ቀላል እውነታ ይዘነጋል ተብሎ በፍፁም ሊታሰብ አይችልም፡፡ ነገር ግን የበርናባስ ወንጌል ገና ሲጀምር ኢየሱስን “ክርስቶስ” ብሎ የጠራው ሲሆን (ገፅ 2) ነገር ግን ምዕራፍ 42 ላይ ኢየሱስ መሲህ መሆኑን መካዱን ይነግረናል፡፡
  • ምዕራፍ 3 ላይ ሄሮድስ እና ጲላጦስ በአንድ ዘመን የይሁዳ ገዢዎች እንደነበሩ ይናገራል፡፡ ነገር ግን ሄሮድስ ከ37-4 ዓ.ዓ. ይሁዳን ብቻውን የገዛ ሲሆን ጲላጦስ ደግሞ ከ26-36 ዓ.ም. ነበር የገዛው፡፡[2] በርናባስ ይህንን የታሪክ ቅጥፈት ሊፈፅም የሚችልበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም፡፡
  • በምዕራፍ 20-21 ላይ ኢየሱስ በጀልባ ወደ ናዝሬት ከተማ እንደሄደና የከተማይቱ ጀልባ ቀዛፊዎች እንደተቀበሉት ይናገራል፡፡ ነገር ግን ናዝሬት ከገሊላ ባሕር 14 ኪ.ሜ. ርቃ በተራሮች ተከባ የምትገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡[3] በዚሁ ቦታ ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ሽቅብ እንደወጣ የሚናገር ሲሆን ይህም ሌላ ጂኦግራፍያዊ ስህተት ነው፡፡ የቅፍርናሆም ከተማ አቀማመጥ ከናዝሬት በላይ ከፍታ ላይ ሳይሆን ታች የገሊላ ባሕር አጠገብ ነው፡፡ ኢየሱስ በተደጋጋሚ ወደ እነዚህ ከተሞች በመሄዱ ምክንያት ደቀ መዛሙርቱ በሚገባ ያውቋቸዋል (ማቴዎስ 2:23፣ 4:13፣ 8:5፣ 11:23፣ 17:24፣ 21:11፣ 26:71፣ ሉቃስ 4:16 )፡፡ ነገር ግን የበርናባስ “ወንጌል” ጸሐፊ ይህንን ስህተት በመስራት አጭበርባሪነቱን ይፋ አውጥቷል፡፡

የበርናባስ ወንጌል የእስልምናን ትምህርቶች የሚደግፍባቸው ብዙ ቦታዎች ቢኖሩም ነገር ግን ደግሞ ሙስሊሞች በእርሱና በቁርአን መካከል እንዲመርጡ የሚያስገድዱ የሚጣረስባቸው ብዙ ነጥቦች በውስጡ ይገኛሉ፡፡

  • ቁርአን መርየም ዒሳን የወለደችው በምጥ እንደሆነ የሚናገር ሲሆን (ሱራ 19፡22-23) የበርናባስ ወንጌል ግን ያለ ምንም ምጥ እንደወለደችው ይናገራል (ም. 3)፡፡
  • ቁርአን ዒሳ መሲህ መሆኑን በተደጋጋሚ የሚናገር ሲሆን (ሱራ 3፡45) የበርናባስ ወንጌል ግን ዒሳ መሲህ መሆኑን መካዱን (ም. 42) እና መሐመድ መሲህ መሆናቸውን መመስከሩን ይናገራል (ም. 97)፡፡ በቁርአን ውስጥም ሆነ በየትኛውም እስላማዊ ጽሑፍ ውስጥ መሐመድ መሲህ መሆናቸው አልተጻፈም፡፡
  • ቁርአን አንድ ሙስሊም ወንድ እስከ አራት ሚስቶች እንዲያገባ የሚፈቅድ ሲሆን (ሱራ 4፡3) የበርናባስ ወንጌል ግን ድርብ ጋብቻን አጥብቆ በመቃወም አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያንጸባርቃል (ም. 115)፡፡
  • ቁርአን ሰባት ሰማያት ብቻ እንዳሉ የሚናገር ሲሆን (ሱራ 17፡44) የበርናባስ ወንጌል ግን ዘጠኝ መኖራቸውን ይናገራል (ም. 178)፡፡

የበርናባስ ወንጌል የመካከለኛው ዘመን ፈጠራ መሆኑን የሚያሳዩ ጠቋሚ ምልክቶች በውስጡ ይገኛሉ፡፡

  • በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ኢዮቤ ልዩ በየ ሃምሳ ዓመቱ እንዲከበር ትዕዛዝ የተሰጠ ሲሆን (ዘሌዋውያን 25፡10-11) በ1300 ዓ.ም. የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ የነበሩት ቦኒፌስ ስምንተኛ በየ መቶ አመቱ እንዲከበር አውጀው ነበር፡፡ ነገር ግን ቀጣዩ ጳጳስ ክሌመንት አራተኛ አዋጁን በመሻር ተመልሶ በየ ሃምሳ ዓመቱ እንዲከበር ስላወጁ በ1350 ዓ.ም. ተከብሯል፡፡[4] የበርናባስ ወንጌል ግን ይህንን የጳጳሱን የተሳሳተ አዋጅ በመቀበል በምዕራፍ 82 ላይ የኢዮቤ ልዩ በዓል በየ መቶ ዓመቱ እንደሚከበር ይናገራል፡፡ ይህም መጽሐፉ በመካከለኛው ዘመን የተጻፈ ስለመሆኑ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡
  • ይህ መጽሐፍ የመካከለኛው ዘመን ፈጠራ መሆኑን የሚያመለክተው ሌላው ነጥብ ከዘመኑ ጸሐፊ ከዳንቴ ሥራዎች ላይ የተቀዱ ሐሳቦች በውስጡ መገኘታቸው ነው፡፡[5] ለምሳሌ ያህል ከገነት በፊት ዘጠኝ ሰማያት መኖራቸውን ጸሐፊው ከዳንቴ ልበ ወለድ ላይ መውሰዱ ግልፅ ነው (ም. 178)፡፡
  • የበርናባስ ወንጌል ቀዳሚያን የእጅ ጽሑፎች በጣልያንኛና በእስፓኒሽ የተጻፉ ሲሆኑ ምርመራ ተደርጎባቸው ከአሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ የተጻፉ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡[6] እውነተኛው በርናባስ ጽፎት ቢሆን ኖሮ በእብራይስጥ፣ በግሪክ ወይንም ደግሞ በአረማይክ ነበር መጻፍ የነበረበት፡፡

የጠለቀ ዕውቀት የሌላቸው ሙስሊሞች ይህንን መጽሐፍ እንደ ተዓማኒ ወንጌል ቢያራግቡትም ነገር ግን ጉዳዩን በጥንቃቄ ያጠኑ ሙስሊም ሊቃውንት ሳይቀሩ ሐሰተኛ መጽሐፍ መሆኑን ዕውቅና ይሰጣሉ፡፡[7]


ማጣቀሻዎች

[1] ማንኛውም ፍላጎቱ ያለው አንባቢ ተከታዩን አስፈንጣሪ በመጠቀም የበርናባስን መልዕክት ማንበብ ይችላል፡- http://answeringislam.net/Barnabas/epistleb.html

[2] FF Bruce. Israel and the Nations, Exeter: Paternoster Press, 1973, p. 240.

[3] “Nazareth”, New Bible Dictionary, England: IVP, 1987, p. 819

[4] Herbert Thurston. The Holy Year of Jubilee, London: Sands & Co., 1900, p. 5

[5] Dante Alighieri. The Divine Comedy, section: Paradiso

[6] Geislere. Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 67

[7] “የበርናባስ ወንጌል” የተጭበረበረ ጽሑፍ ስለመሆኑ ሙስሊም ምሑራን እንዲህ ብለዋል:- As regards the “Gospel of Barnabas” itself, there is no question that it is a medieval fnetery … It contains anachronisms which can date only from the Middle Ages and not before, and shows a garbled comprehension of Islamic doctrines, calling the Prophet the “Messiah”, which Islam does not claim for him. Besides it farcical notion of sacred history, stylistically it is a mediocre parody of the Gospels, as the writings of Baha Allah are of the Koran. (Cyril Glassé, The Concise Encyclopedia of Islam, San Francisco: Harper & Row, 1989, p. 65)

ነቢዩ መሐመድ