ሙሴና ሙሐመድ የማይመሳሰሉባቸው 50 ነጥቦች

ሙሴና ሙሐመድ የማይመሳሰሉባቸው 50 ነጥቦች

ሙስሊም ወገኖች ስለ ሙሐመድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ ተተነበየ ይናገራሉ፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ከሚጠቅሷቸው ጥቅሶች መካከል ዘዳግም 18፡18 ላይ የሚገኘው የእግዚአብሔር ባርያ ሙሴ የተናገረው ትንቢት ዋነኛው ነው፡፡ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፡-

እግዚአብሔር አለኝ ፡– የተናገሩት መልካም ነው፡፡ ከወንድሞቻቸው መካከል እንደአንተ ያለ ነቢይ አስነሳላቸዋለሁ፡፡ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፡፡ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል፡፡ በስሜም የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀልለታለሁ፡፡”

ይህንን ጥቅስ ለሙሐመድ የተነገረ በማስመሰል የሚያቀርቡት ሙስሊም ወገኖች ቁጥር 15-16 ላይ የሚገኘውን “አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳልሃል” የሚለውን ቃል ባላየ ያልፉታል፡፡ በዚህ ጥቅስ መሠረት “ከወንድሞችህ” የሚለው 12ቱን ነገደ እስራኤልን የተመለከተ እንጂ የእስራኤል የአጎት ልጆች (የእስማኤል ልጆች) እንደሆኑ የተነገረላቸውን አረቦችን የሚጠቅስ አለመሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ጥቅሱ “ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ” በማለት ለእስራኤላውያን ብቻ የተነገረ መሆኑን አስረግጦ ሳለ ስለ ሌላ ሕዝብ የተነገረ እንደሆነ በማስመሰል መተርጎም አላዋቂነት አለበለዚያም አታላይነት ነው፤ ተቀባይነት የለውም፡፡ ለእውነት ግድ የሚለውና እውነተኛውን አምላክ እንደሚከተል የሚያምን ሰው እንዲህ ላለ ሃቀኝነት ለራቀው ሙግት ቦታ አይሰጥም፡፡

ይህንን ትንቢት ለሙሐመድ የተነገረ በማስመሰል የሚያቀርቡት እስላማዊ ጽሑፎች ሙሴና ሙሐመድ እንደሚመሳሰሉ ለማሳየት አንዳንድ “መመሳሰሎችን” ይጠቅሳሉ፡፡ ሆኖም የሚጠቅሷቸው ነጥቦች ማንኛውም ተራ ሰው ከሙሴ ጋር ሊመሳሰልባቸው የሚችላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሁለቱም በተፈጥሯዊ መንገድ ተወልደዋል፣ ሁለቱም አግብተዋል፣ ሁለቱም መሪዎች ነበሩ፣ ሁለቱም ሞተዋል፣ ወዘተ. የሚሉ ተራ መመሳሰሎችን ይጠቅሳሉ፡፡ አንዳንድ ጸሐፊያን እንዲያውም የሁለቱም ስም M በሚል የእንግሊዘኛ ፊደል የሚጀምር በመሆኑ ይመሳሰላሉ ብለው እስከ መሟገት ወርደዋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሙሴና ሙሐመድ ከሚመሳሰሉባቸው ነጥቦች ይልቅ የሚለያዩባቸው ነጥቦች በእጅጉ ይበዛሉ፡፡ ልዩነቶቹ እጅግ በርካታ ቢሆኑም በዚህ ጽሑፍ 50ዎቹን ከማስረጃ ጋር እንጠቅሳለን፡፡

  1. ሙሴ ከሌዊ ነገድ የሆነ እስራኤላዊ ነበር (ዘጸአት 2፡1-2)፤ የሙሐመድ የዘር ሐረግ “ቁረይሽ” ከተሰኘው የአረብ ጎሣ ይመዘዛል (ሱራ41:44፣ Sahih Bukhari 4፡698)፡፡
  2. ሙሴ ወገኖቹ እስራኤላውያን በባርነት ምድር ሳሉ ነበር የተወለደው (ዘጸ. 1፡9-14)፤ በሙሐመድ ዘመን አረቦች ነፃ ሕዝቦች ነበሩ፡፡
  3. ሙሴ በልጅነቱ ከሞት አዋጅ በመለኮታዊ እርዳታ ተርፏል (ዘጸ. 1፡15-16፣ 2፡2-10)፤ ሙሐመድ እንዲህ ያለ ታሪክ አልነበረውም፡፡
  4. የፈርዖን ልጅ ሙሴን ታጠባው ዘንድ ለወላጅ እናቱ ሰጠችው (ዘጸአት 2፡7-8)፡፡ የሙሐመድ ወላጅ እናት ራሷ ከማጥባት ይልቅ ሐሊማ ለተባለች ሴት እንድታጠባው ሰጠችው (Ibn Ishaq, Sirat Rasulullah, p.72)፡፡
  5. ሙሴ በምድረ ግብፅ ኖሯል (ዘጸአት 2፡10)፤ ሙሐመድ ግብፅን አልረገጠም፡፡
  6. ሙሴ በልጅነቱ አጠራጣሪ ወይም አነጋጋሪ መንፈሳዊ ልምምድ አልነበረውም፤ ሙሐመድ በልጅነቱ ወድቆ በመንፈራገጡ ምክንያት ሐሊማ ጋኔን እንዳደረበት ስላሰበች ለእናቱ መልሳዋለች (Ibn Ishaq, Sirat Rasulullah, p. 72)፡፡
  7. ሙሴ ጣዖታትን አላመለከም፤ ሙሐመድ በልጅነቱ ለጣዖት ሰውቷል (Hisham Ibn Al-Kalbi, The Book of Idols (Kitab al-Asnam), pp. 17-18; A. Guillaume, Islam, pp. 26-27)፡፡
  8. ሙሴ የግብፅን ዕውቀት የተማረ ማንበብና መጻፍ የሚችል ምሑር ነበር (ሐዋ. 7፡22፣ ዘጸ. 24፡4፣ ሌዋ. 1፡1፣ 4፡1፣ 5፡14፣ ዘኁ. 1፡1፣ 33፣2፣ ዘዳ. 1፡1፣ 4፡44፣ 29፡1)፤ ሙሐመድ ማንበብና መጻፍ የማይችል መሃይም ነበር (ሱራ 7:157-158፣ Sahih Muslim Vol. 1, p. 97)፡፡
  9. ሙሴ እግዚአብሔር የሰጠውን ሕግ በገዛ እጁ ጻፈ (ዘጸ. 24፡4፣ ሌዋ. 1፡1፣ 4፡1፣ 5፡14፣ ዘኁ. 1፡1፣ 33፣2፣ ዘዳ. 1፡1፣ 4፡44፣ 29፡1)፤ ሙሐመድ መሃይም ስለነበር ጸሐፊዎች ነበሩት፤ አንዳንዴም የገዛ ሐሳባቸውን እየጨመሩ ይጽፉ ነበር (Al-Wahidi Al-Naysaboori. Asbaab Al-Nuzool; p. 126 Beirut’s Cultural Libary Edition “Tub’at Al-Maktabah Al-thakafiyyah Beirut”)፡፡
  10. ሙሴ አሮንና ማርያም የተሰኙ ወንድምና እህት ነበሩት (ዘኁልቁ 26፡59)፤ ሙሐመድ ብቸኛው የአብደላና የአሚና ልጅ ነበር (Ibn Sa’d. Kitab al-Tabaqat al-Kabir Volume I Parts I & II, p. 107)፡፡
  11. ሙሴ እግዚአብሔርን ከሚያውቅ እስራኤላዊ ቤተሰብ ነበር የተወለደው (ዘጸአት 2፡1-3፣ ዕብራውያን 11፡23)፤ የሙሐመድ ወላጆችና ዘሮች ጣዖታውያን ነበሩ፡፡ አባቱና እናቱም ገሃነም ውስጥ መሆናቸውን ሙሐመድ ተናግሯል (Sahih Muslim Vol. 2, Book 4, Hadith 2130)
  12. የሙሴ ወንድ ልጆች ጌርሳምና ዓልአዛር ለአቅመ አዳም ደርሰው አግብተው ወልደዋል (1ዜና 23፡15-17)፤ ሙሐመድ ሦስት ወንድ ልጆች የወለደ ሲሆን (ከኸዲጃ የወለዳቸው አልቃሲምና አብዱላህ፣ ከግብፃዊቷ ባርያው የወለደው ኢብራሂም) ሦስቱም በህፃንነታቸው ሞተዋል፡፡ (Ibn Ishaq, Sirat Rasulullah, p.83)
  13. ሙሴ ለአገልግሎት የተጠራው በ 80 ዓመቱ ነበር (ዘጸአት 7፡7)፤ ሙሐመድ ግን ጂብሪል ታየኝ ያለው በ 40 ዓመቱ ነበር (Sahih Bukhari 5፡242)፡፡
  14. ሙሴ ነቢይነቱን ለማረጋገጥ የሚስቱ ማረጋገጫ አላስፈለገውም (ዘጸአት 4፡1-18)፤ ሙሐመድ ነቢይ መሆኑን ያሳመነችው ሚስቱ ኸዲጃ ናት (The History of Tabari, translated by W. Montgomery Watt, vol. 6, p. 72)፡፡
  15. ሙሴ ነቢይነቱን ያረጋገጠው እግዚአብሔር ተዓምራዊ በሆነ መንገድ ስለተገለጠለት ነው (ዘጸአት ም. 3-4)፤ ሙሐመድ ነቢይነቱን ያወቀው ኸዲጃ ቀሚሷን ገልጣ ሸፍናው ነው (Ibn Ishaq’s “Sirat Rasul Allah”, The Life of Muhammad, translated by A. Guillaume, p. 107)፡፡
  16. ሙሴ እግዚአብሔር ሲገለጥለት የተገለጠለት እግዚአብሔር መሆኑን አመነ እንጂ “ሰይጣን ታየኝ” አላለም (ዘጸአት ም. 3-4)፤ ሙሐመድ የተገለጠለት አካል ሰይጣን ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት አድሮበት ነበር (Ibn Ishaq’s “Sirat Rasul Allah,” The Life of Muhammad translated by A. Guillaume, p. 106)፡፡
  17. እግዚአብሔር ለሙሴ ሲገለጥ በንግግርና በምልክት አሳመነው እንጂ አላስገደደውም (ዘጸአት ም. 3-4)፤ “ጂብሪል” ሙሐመድን ከመሬት ጋር አጣብቆ በማስገደድ ቁርአንን አስነብቦታል (Sahih Muslim Vol. 1, p. 97)፡፡
  18. ሙሴ 40 ቀን በሲና ተራራ ላይ ከቆየ በኋላ ፊቱ አበራ (ዘጸአት 34፡30)፤ ሙሐመድ በሒራ ዋሻ ውስጥ ከደረሰበት ሁኔታ የተነሳ በፍርሃትና በመርበትበት ውስጥ ሆኖ ወደ ሚስቱ ተመለሰ (Ibn Sa`d, Kitab al-Tabaqat al-Kabir, Vol. 1, p. 225)፡፡
  19. ሙሴ ብዙ ተዓምራትን አድርጓል (ዘጸ. ም. 7፣ 8፣ 14፣ 17፣ ሱራ 2፡50፣ ሱራ 2፡57)፤ ሙሐመድ አንድም ተዓምር አላደረገም (ሱራ 28:48፣ ሱራ 6:109፣ ሱራ 13:27፣ ሱራ 17:59፣ ሱራ 13:7)፡፡ በሐዲስ መጻሕፍት ሙሐመድ ተዓምራትን እንዳደረገ ቢዘገብም ከቁርአን ጋር ስለሚጋጩ ከክፍለ ዘመናት በኋላ የተጻፉ የፈጠራ ታሪኮች መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡
  20. ሙሴ በቀጥታ ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋግሯል (ዘጸ. 33፡11፣ ሱራ 4፡164)፤ ሙሐመድ አልተነጋገረም (ሱራ 42፡51፣ Bukhari Vol. 6, Book 60, No. 378)፡፡ መገለጥንም ይቀበል የነበረው በተዘዋዋሪ በጅብሪል አማካይነት ነበር (ሱራ 2፡97)፡፡
  21. ሙሴ በጣም ትሁትና ለግል ጥቅሙ የማይከራከር ሰው ነበር (ዘኁልቁ 12፡3)፤ ሙሐመድ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግና ያስቀየሙትን ሰዎች በነፍሰ ገዳዮች የሚያስገድል ቂመኛ ሰው ነበር (ሱራ 33፡57፣ Bukhari vol 5 No. 369; Ibn Sa`d, Kitab al-Tabaqat al-Kabir, Vol. 2, p. 31; Ibn Ishaq’s “Sirat Rasul Allah,” The Life of Muhammad translated by A. Guillaume, pp. 675, 676)፡፡
  22. ሙሴ በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ሚስት አላገባም፣ በጋብቻውም ላይ አላመነዘረም፤ ሙሐመድ መድብለ ጋብቻን ፈፅሟል(Bukhari, volume 7, No. 142)፣ በጋብቻው ላይም አመንዝሯል (Kitab al-Tabaqat al-Kabir, p. 151)፡፡
  23. ሙሴ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች ህፃን አላገባም፤ ሙሐመድ አይሻ የ 6 ዓመት ህፃን ሳለች በማጨት በ 9 ዓመቷ አብሯት ተኝቷል (Sahih Al-Bukhari, Volume 5, Book 58, Number 234; Volume 5, Book 58, Number 236; Volume 9, Book 87, Number 140; see also Number 139; Volume 7, Book 62, Number 64; see also Numbers 65 and 88; Sahih Muslim, Book 008, Number 3309; see also 3310; Book 008, Number 3311; Sunan Abu Dawud, Number 2116; Book 41, Number 4915; Book 13, Number 2380)፡፡ ሙሐመድ በዳዴ የሚሄዱትን ህፃናት እንኳ ሳይቀር ለጋብቻ ይመኝ እንደነበር በእስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ ማንበብ በእጅጉ አስደንጋጭ ነው፡፡ “የአባስ ልጅ ኡም ሐቢባ ጡት በመጥባት እድሜ ላይ በነበረች ጊዜ በፊታቸው በዳዴ ስትሄድ ነቢዩ ተመልክተዋት እንዲህ አሉ፡ ‹እኔ በሕይወት እያለሁ የምታድግ ከሆነ አገባታለሁ፡፡›” (Musnad Ahmed, Number 25636)
  24. ሙሴ የማደጎ ልጁን ሚስት ቀምቶ አላገባም፤ ሙሐመድ የማደጎ ልጁ የዘይድን ሚስት ዘይነብን አግብቷል (ሱራ 33:37፣ Sahih Muslim Book 8, Number 3330)፡፡
  25. ሙሴ እስራኤላውያንን ወደ ተስፋይቱ ምድር መርቷል (ኦሪት ዘጸአት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቁ፣ ዘዳግም)፤ ሙሐመድ እስራኤላውያንን በሰይፍ ጨፍጭፏል፣ ዘርፏል፣ ባርያ አድርጓል፣ ከአገር አባሯል ((Ibn Ishaq’s “Sirat Rasul Allah,” The Life of Muhammad translated by A. Guillaume, pp. 363, 437, 461, 510)፡፡ በመጨረሻው ዘመንም ሙስሊሞች አይሁድን በሙሉ እንደሚጨፈጭፉ ተናግሯል (Sahih al-Bukhari Volume 4, Book 52, Number 177; Sahih Muslim, Book 041, Number 6981)፡፡
  26. ሙሴ ጋኔን እንዳደረበት አስቦ አያውቅም፤ ሙሐመድ ጋኔን እንዳደረበት ተናግሯል (Sirat Rasulallah p. 106, 121, 130, 136)፡፡
  27. ሙሴ ራሱን ለመግደል ሞክሮ አያውቅም፤ ሙሐመድ ከተራራ ላይ ራሱን ወርውሮ ለመግደል ብዙ ጊዜ ሞክሯል (History of Tabari, translated by W. Montgomery Watt, vol. 6, p. 69-70; Ibn Ishaq’s “Sirat Rasul Allah,” The Life of Muhammad, translated by A. Guillaume, p. 106)፡፡
  28. ሙሴ እስከ መጨረሻው ድረስ ጤናማ አእምሮና አስተሳሰብ ነበረው (ዘዳግም 34፡1-7)፤ ሙሐመድ ለሞት ሲቃረብ የአእምሮ መታወክ ደርሶበት ነበር (Sahih al-Bukhari Volume 2, Book 23, Number 471)፡፡
  29. ሙሴ ከሰይጣን የሆነ ቃል አልተናገረም፤ ሙሐመድ ሰይጣናዊ ጥቅሶችን ተናግሯል (History of Tabari, vol. 6, pp. 108-110)፡፡
  30. ሙሴ በያሕዌ ስም እንጂ በሌላ አምላክ ስም አልተናገረም (ዘዳግም 18፡20)፤ ሙሐመድ በአል-ላት፣ አል-ኡዛና መናት ስም ተናግሯል (History of Tabari, vol. 6, pp. 108-110)፡፡
  31. ሙሴ በእግዚአብሔር ስም ሐሰትን ተናግሮ አያውቅም (ዘዳግም 18፡20)፤ ሙሐመድ በአምላኩ ስም ሐሰትን መናገሩንና አምላኩ ያልተናገረውን የተናገረ በማስመሰል እንደተናገረ ተናዟል (Al-Tabari, The History of Al-Tabari, vol. vi, p. 111; Ibn Sa’d, Kitab Al-Tabaqat Al-Kabir, vol. 1, p. 237)፡፡
  32. ሙሴ አስማት ሊሠራበት አልቻለም (ዘኁልቁ 23፡23)፤ ሙሐመድ በአስማት ቁጥጥር ስር ሆኖ ለአንድ ዓመት ያህል ሲሠቃይ ነበር (Al-Bukhari, vol. 7, no. 660; Al-Bukhari, vol. 7, no. 658)፡፡
  33. የሙሴ አምላክ ለሕዝቡ አባት ነው (ዘዳግም 32፡6)፤ የሙሐመድ አምላክ ለማንም አባት ሆኖ አያውቅም (ሱራ 5:18)፡፡
  34. ሙሴ የገዛ መገለጡን ሽሮ አያውቅም፤ ሙሐመድ መገለጦቹን በተደጋጋሚ ይሽር ነበር (ሱራ 13፡39፣ 16፡101፣ 2፡106፣ 17፡86)፡፡
  35. ሙሴ የግል ብቀላን ከልክሏል (ዘሌዋውያን 19፡18)፤ ሙሐመድ ግን ይቅርታ ተመራጭ መሆኑን ቢናገርም ብቀላን ፈቅዷል (ሱራ 16፡126)፣ እራሱም ተበቃይ ነበር (Bukhari vol 5 No. 369; Ibn Sa`d, Kitab al-Tabaqat al-Kabir, Vol. 2, p. 31; Ibn Ishaq’s “Sirat Rasul Allah,” The Life of Muhammad translated by A. Guillaume, pp. 675, 676)፡፡
  36. ሙሴ በተሳተፈባቸው ጦርነቶች ላይ አንድም ጊዜ አልተሸነፈም፤ ሙሐመድ በኡሁድ ጦርነት ላይ ክፉኛ ተሸንፏል፡፡ በዚህ ጦርነት ላይ አጎቱ ሐምዛ የሞተ ሲሆን ሙሐመድ ራሱ ከንፈሩ ተሰንጥቆ የፊት ጥርሶቹ ረግፈዋል፡፡ የሙሐመድ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሁለት ጥርሶች ዛሬ በኢስታንቡል ሙዚየም ውስጥ ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ (Paul Fregosi. Jihad in the West, Muslim Conquest from 7th to 21st Centuries; 1998, p. 53)
  37. ሙሴ ወንድ የሴት ልብስ እንዳይለብስ ከልክሏል (ዘዳግም 22፡5)፤ ሙሐመድ የሚስቱ የአይሻን ቀሚስ ሲለብስ ነበር (Sahih al-Bukhari Number 2442; 2393; 3941; Sahih Muslim, Book 031, Number 5984)፡፡
  38. ሙሴ የሰው ሚስት መመኘትን ከልክሏል (ዘጸአት 20፡17)፤ ሙሐመድ የሰው ሚስት ከመመኘት አልፎ ቀምቶ አግብቷል (ሱራ 33፡37፣ Sahih Muslim Book 8, Number 3330)፡፡
  39. ሙሴ የጦር ምርኮኛ ሴቶችን መድፈርን ከልክሏል (ዘዳግም 21፡10-14)፤ ሙሐመድ ፈቅዷል፣ ለዚያውም የምርኮኞች ባሎች በሕይወት እያሉ! (Sahih Al-Bukhari 62:137; Bukhari 34:432; Abu Dawud 2150; Sahih Muslim volume 2, No. 3371; ሱራ 70፡29-30፣ 23፡5-6)፡፡
  40. ሙሴ ለኃጢአት ስርየት የመሥዋዕት ሥርዓትን ሲፈፅም ነበር (ኦሪት ዘሌዋውያን በሙሉ)፤ ሙሐመድ ለኃጢአት ሥርየት ስለሚሆን መሥዋዕት አላስተማረም፡፡ በሙሴ ሕግ ለመብል እንኳ የተከለከለውን ግመልን ሲሠዋ የነበረ ሲሆን ከሙሴ የመሥዋዕት ትርጉም ጋር ጭራሽ አይገናኝም፤ ከአረብ ጣዖታውያን የተኮረጀ ነው (ሱራ 22፡32-36፣ 2፡196)፡፡
  41. ሙሐመድ ከሙሴ መጽሐፍ ሲጠቅስ የገዛ ቃሉን ጨምሮ ጠቅሷል፤ ይህም የሙሴን መጽሐፍ አለማወቁን ያሳያል፡- “በነርሱም ላይ በውስጧ ነፍስ በነፍስ፣ ዓይንም በአይን፣ አፍንጫም በአፍንጫ፣ ጆሮም በጆሮ፣ ጥርስም በጥርስ (ይያዛል)፣ ቁስሎችንም ማመሳሰል አለባቸው ማለትን ጻፍን” (ሱራ 5፡45)፡፡ ነገር ግን ትዕዛዙ በተሰጠባቸው ቦታዎች ሁሉ “አፍንጫም በአፍንጫ፣ ጆሮም በጆሮ” የሚል የለም (ዘጸአት 21፡24፣ ዘሌዋውያን 24፡20፣ ዘዳግም 19፡21)፡፡
  42. ሙሴ የግመል ሥጋ መብላትን ከልክሏል (ዘሌዋውያን11:1-4፣ ዘዳግም 14:3-7)፤ ሙሐመድ የግመል ሥጋ መብላትን ብቻ ሳይሆን የግመል ሽንት መጠጣትንም ፈቅዷል (Sahih Bukhari 8፡796; ሱራ 22:36)፡፡
  43. ሙሴ ስለ ንፅህና አጠባበቅ ጥሩ ትምህርቶችን አስተምሯል (ሌዋውያን 11፡25፣ 13:47–58፣ 14፡8፣ 15፡5-13፣ ዘዳግም 23:12–14፣ )፤ ሙሐመድ ጤናን ለአደጋ የሚያጋልጡ ትምሕርቶችን አስተምሯል፤ ለምሳሌ፡- ዝንብ በመጠጫ ውስጥ ከወደቀች ወደ ውስጥ እንድትጠልቅ ማድረግ በሽታን እንደሚከላከልና የሞቱ እንስሳት የሚጣሉበትንና ሴቶች የወር አበባ ጨርቅ የሚያጥቡበትን ውኀ መጠጣት ጤናን እንደማይጎዳ ተናግሯል (Sahih Al-Bukhari Volume 4, Book 54, Number 537; Sunan Abu Dawud 67; Sunan Ibn Majah 520; Sunan Ibn Majah 521)፡፡
  44. ሙሴ ለአምልኮ አገልግሎት የሚውል ምንም ዓይነት ድንጋይ ማቆምን ከልክሏል (ዘጸአት 26፡1፣ ዘዳግም 16፡22)፤ ሙሐመድ አረብ ጣዖታውያን ሲያመልኩት የነበሩትን ጥቁር ድንጋይ ስሟል፣ ተሻሽቷል፣ ተከታዮቹ በቀን አምስቴ ወደ እርሱ ዞረው እንዲሰግዱ አዟል (Sahih al-Bukhari, Volume 2, Book 26, Number 673; ሱራ 2፡150)፡፡
  45. የሙሴ አምላክ ውሸትና ማታለልን የማያውቅ ቅዱስ ነው (ዘኁልቁ 23፡19)፤ የሙሐመድ አምላክ አታላይ ተብሎ ተጠርቷል፡- ሱራ 3፡54፡- “አላህም ከአድመኞች ሁሉ በላጭ ነዉ።” ومكروا ومكر الله والله خير الماكرين “ወአላሁ ኸይሩ አል-መክሪን” ማለት አላህ ከአታላዮች ሁሉ የበለጠ አታላይ ነው” ማለት ነው፡፡ Allah (is) the best (of) the cheaters/deceivers. ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸው በርካታ የቁርአን አናቅፅ ይገኛሉ (ሱራ 7፡99፣ 8:30፣ 10:21፣ 13:42)፡፡ ነገር ግን የአማርኛ ቁርአን ተርጓሚዎች የተለያዩ ቃላትን በመተካትና በማዛባት ቢተረጉሙም ቀጥተኛው ትርጉም አላህ ከአታላዮች ወይም አጭበርባሪዎች ሁሉ የከፋው አታላይ ወይም አጭበርባሪ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ከአላህ 99ኙ ስሞች መካከል አንዱ “አል-መክር” ወይም “አታላዩ” የሚል ነው፡፡ ብዙ የአረብኛ ዲክሺነሪዎችም ቃሉን “አታላይ፣ አጭበርባሪ፣ ተንኮለኛ፣ ወዘተ.” በማለት ይተረጉማሉ፡፡
  46. ሙሴ አንድም ጊዜ የግል ጥቅሙን ለማስከበር መገለጥ ተናግሮ አያውቅም፤ ሙሐመድ በመገለጥ ሽፋን የገዛ ጥቅሙን ሲያሳድድ ነበር (ሱራ 33:51፣ ሱራ 33:37፣ ሱራ 33:50፣ ሱራ 33:53፣ ሱራ 49:4)፡፡
  47. ሙሴ ኢትዮጵያዊትን ሴት አግብቷል (ኦሪት ዘኍልቍ 12፡1)፤ ሙሐመድ ለኢትዮጵያውያን፣ ብሎም ለጥቁሮች ከፍተኛ ንቀት ነበረው፣ ባርያም አድርጓቸዋል (Sahih Muslim, Book 10, Number 3901; Sahih Bukhari, Volume 9, Book 91, Number 368)፡፡ ኢትዮጵያውያንን “ዘቢብ ጭንቅላት” ብሎ ተሳድቧል (Sahih al-Bukhari Book Number 89 Hadith Number 256)፡፡ ሰይጣንና ጥቁሮችን አመሳስሏል (Ibn Ishaq, Sirat Rasulallah, translated as, The Life of Muhammad by A. Guillaume, page 243)፡፡ ጥቁር ሴት የበሽታ ወረርሽኝ ምልክት መሆኗን ተናግሯል (Sahih Bukhari, Volume 9, Book 87, Number 161)፡፡ ለበለጠ መረጃ መሐመድ ለጥቁሮች የነበረው ንቀት የሚለውን ጽሑፍ ያንብቡ፡፡
  48. ሙሴ በአካሉ ላይ ምንም ዓይነት እንከን እንዳልነበረው እስላማዊ ሐዲሳት ይናገራሉ (Sahih Al-Bukhari Volume 4, Book 55, Number 616; Volume 1, Book 5, Number 277) ፤ ሙሐመድ በጀርባው ላይ እባጭ ወይም ዕጢ ነበረበት፤ የቀደሙት ሙስሊሞች ይህንን የጤና ችግር “የነቢያት ማሕተም” አድርገው ተርጉመውታል (Sahih al-Bukhari Volume 1, Book 4, Number 189; Volume 7, Book 70, Number 574; Sahih Muslim Book 030, Number 5790)፡፡ ለበለጠ መረጃ የነቢይነት ማሕተም ወይንስ የጤና ችግር? በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ጽሑፍ ያንብቡ፡፡
  49. ሙሴ ረጅም ዕድሜ ኖሮ በእግዚአብሔር ፈቃድ መሠረት ሞቷል፣ አስከሬኑም በመላእክት ይጠበቃል (ዘዳግም 34፣ ይሁዳ 1፡9)፤ ሙሐመድ መርዝ በልቶ ሞቷል፣ መቃብሩም በመዲና ከተማ ይገኛል (Sahih al-Bukhari, Volume 5, Book 59, Number 713)፡፡
  50. ሙሴ እንደ እርሱ ያለ ነቢይ ከእስራኤላውያን መካከል እንደሚነሳ ተናግሯል (ዘዳግም 18፡18)፤ ሙሐመድ በአምስት ነገሮች ከነቢያት ሁሉ የተለየ መሆኑን ተናግሯል ስለዚህ በራሱ ቃል መሠረት ከሙሴ ጋር አይመሳሰልም (Sahih al-Bukhari Volume 1, Book 7, Number 331)፡፡

ውድ ሙስሊሞች! ከነዚህ እውነታዎች አንፃር ሙሴን የሚመስለው ነቢይ ሙሐመድ መሆኑን ለመናገር የሚያስችል ምን ማስረጃ ማቅረብ ትችላላችሁ? ይህንን ዝርዝር ካነበባችሁ በኋላስ ኡስታዞቻችሁ በሚያቀርቡት ሙግት ላይ ያላችሁ መተማመን ምን ያህል ነው? በሙሐመድ ዘመን የነበሩ ሰዎች እንኳ ሙሴና ሙሐመድ እንደማይመሳሰሉ ተገንዝበው ጥያቄን አንስተው እንደ ነበር በቁርአናችሁ ውስጥ ተጽፏል፡- ሱራ 28:48 “እውነቱም ከእኛ ዘንድ በመጣላቸው ጊዜ «ለሙሳ የተሰጠው ብጤ አይስሰጠውም ኖሯልን» አሉ፡፡ «ከዚህ በፊት ሙሳ በተሰጠው አልካዱምን የተረዳዱ ሁለት ድግምቶች ናቸው» አሉ፡፡ «እኛ በሁሉም ከሓዲዎች ነንም» አሉ፡፡”

ነቢያችሁ ሙሐመድ ተዓምራትን ማሳየት ባለመቻሉ ምክንያት የሙሴን ተዓምራት አስፈላጊነት አሳንሶ ለማሳየት ሲጣጣር ይታያል፡፡ ሙሴ ያንን ሁሉ ተዓምር ባያሳይ ኖሮ እስራኤላውያንን ከባርነት ነፃ ማውጣት ባልቻለ ነበር፡፡ ሙሐመድም የእውነተኛ ነቢያት ምልክቶችን ማሳየት ቢችል ኖሮ አረቦችን ለማስለም ሰይፍ መምዘዝ ባላስፈለገው ነበር፡፡ ዛሬ እናን እስልምናን እየተከተላችሁ ያላችሁት ሙሐመድ እውነተኛ ነቢይ መሆኑን አረጋግጣችሁ ነው ወይንስ በጭፍን? ሰይፍ ፈርታችሁ ነው ወይንስ በገዛ ፈቃዳችሁ? ከእስልምና በመውጣታችሁ የሚደርስባችሁን መገለልና ጊዜያዊ ፈተና ፈርታችሁ ነው ወይንስ የዘላለምን ሕይወት አገኛለሁ ብላችሁ? ከሚመጣው ፍርድ ያድናችሁ ዘንድ ሙሐመድ ብቁ ነውን? እስኪ ሕይወቱን ተመልከቱና ለገዛ ልቦናችሁ እውነትን ተናገሩ! እንደ ሙሐመድ ኃጢአትና ክፋት ያልተገኘበትን አንድ አዳኝ እንጠቁማችሁ፡፡ ስሙ ኢየሱስ ይባላል! በእብራይስጥ ዬሹዋ መሺያኽ ብለው ይጠሩታል፣ ዓረብ ክርስቲያኖች የሱዋ አል-መሲህ ይሉታል፣ እናንተ ደግሞ አል-መሲህ ዒሳ ትሉታላችሁ፡፡ እርሱ ፍፁም ጻድቅ፣ ንፁህና ኃጢአት የሌለበት መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ እርሱ የሰው ልጆችን ከኃጢአታቸው ለማዳን ከሰማይ የመጣ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ እንዲህ ይላችኋል፡-

“እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” (ማቴዎስ 11፡28)

ይህ ቅዱስ ጌታ እናንተ በገዛ ሥራችሁ ልታገኙት ያልቻላችሁትን የዘላለምን ሕይወት በነፃ ይሰጣችኋል፡፡ ኃጢአትን ድል የምትነሱበትንም ቅዱሱን መንፈስ ይልክላችኋል፡፡ ዛሬውኑ በስሙ በማመን ከዘላለም ጥፋት ትድኑ ዘንድ ጥሪን እናቀርብላችኋለን! እግዚአብሔር አምላክ ይርዳችሁ!

 

ስለመሐመድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተተንብዮአልን?

ነቢዩ መሐመድ