ስለሙሐመድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተተንብዮአልን?

ስለሙሐመድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተተንብዮአልን?



ቁርኣን ስለሙሐመድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተተነበየ ይናገራል (ሱራ 7፡157-158፤37፡6)፡፡ ሙስሊም ዐቃቤ እምነታውያን እነዚህን ትንቢቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳገኙ በርግጠኝነት እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ ክርስቲያኖችና አይሁዶችም ሆነ ብለው ትንቢቶቹን እንደሚደብቁ በማስመሰል ወቀሳ ሲሰነዝሩ እያደመጥን ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ወገኖች ስለሙሐመድ የተነገሩ ትንቢቶች ናቸው በማለት የሚያቀርቧቸውን ጥቅሶች በትክክል ብንመረምራቸው የሙሐመድን ነቢይነት በመጽሐፍ ቅዱስ ለማረጋገጥ መሞከራቸው “ላም ባልዋለበት…” እንደሚባለው ምሳሌ ዓይነት ከንቱ ምኞት መሆኑን በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡

ሙስሊም ዐቃቤ እምነታውያን የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅሶች ሲጠቅሱ የራሳቸውን ሐሳብ እንዲደግፉላቸው ከሚጠቀሟቸው ዘዴዎች መካከል በጣም የተለመደው ጥቅሱን ከአጠቃላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ብሎም ከተጻፈበት አውድ ገንጥሎ ማውጣት ነው፡፡ ነገር ግን ከጥቅሱ ጋር አብረው የተቀመጡትን ከላይና ከታች ያሉትን ሐሳቦች ብናነባቸው እነርሱ ከሚፈልጉት አላማ ጋር ፈፅሞ የማይሄዱ መሆናቸውን በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡ ሌላው የተሳሳተ ዘዴያቸው በቦታው ላይ የሌለን እንግዳ ሐሳብ ወደ ጥቅሱ በመጨመር ማንበብ ሲሆን የራሳቸውን አላማ እስከደገፈ ድረስ በግድየለሽነት የሚፈልጉትን ትርጓሜ ሲሰጡ እየታዘብን ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ታማኝነትና ሚዞናዊነት የጎደለው አካሄድ ትዝብት ላይ የሚጥልና በእግዚአብሔር ዘንድም የሚያስጠይቅ ነው፡፡ በእርግጥ ሙስሊም ዳዒዎች በእንዲህ ዓይነቱ ከእውነት የራቀና ደካማ መሠረት ላይ አስተምህሮአቸውን መትከላቸው ለኛ ለክርስቲያን ዐቃቤ እምነታውያን እስልምና መሠረት የለሽ ሃይማኖት መሆኑን ለማሳየት ጥሩ አጋጣሚን በመፍጠር ሥራችንን አቅልሎልናል፡፡

ሙስሊም ሰባክያን ስለሙሐመድ እንደተተነበዩ በማስመሰል የሚከራከሩባቸው ሁለት አበይት ጥቅሶች አሉ፡፡ እነርሱም ዘዳግም 18:18 እና የዮሐንስ ወንጌል 14:16 ናቸው፡፡ ጥናታችንን ከነዚህ በመጀመር መለስተኛ ግምት ወደሚሰጧቸው ጥቅሶች  እንዘልቃለን፡

ማሳሰብያየሙስሊም ወገኖች የመከራከርያ ነጥቦች የተወሰዱት በዑመር አርሲታላቅ ምክር ለአዲሱ ትውልድበሚል ርዕስ ተፅፎ 1999 .. በሱና አሳታሚ ድርጅት ከታተመው ሦስተኛ ዕትም መጽሐፍ ላይ ነው፡፡ በመሆኑም ድግግሞሽ እንዳይኖር ከመጽሐፉ የተወሰዱ ሐሳቦች ሲኖሩ ገፁን ብቻ በመጥቀስ እናልፋለን፡፡

ሙሴን የሚመስለው ነቢይ ማን ነው?

ዘዳግም 18፡18 እግዚአብሔር አለኝ የተናገሩት መልካም ነው፡፡ ከወንድሞቻቸው መካከል እንደአንተ ያለ ነቢይ አስነሳላቸዋለሁ፡፡ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፡፡ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል፡፡ በስሜም የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀልለታለሁ፡፡

ሙስሊም ዐቃቤ እምነታውያን ከዚህ ጥቅስ በመነሳት እንደ ዋና መከራከርያ የሚያቀርቡት ነጥብ አረቦችና እስራኤላውያን “ወንድማማች ሕዝቦች” በመሆናቸው ሳብያ “ከወንድሞቻቸው መካከል” የሚለው ቃል በቀጥታ የሚመለከተው ሙሐመድን ነው የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ፈጥነን ወደ ድምዳሜ ከመድረሳችን በፊት የዘዳግም መጽሐፍ “ወንድሞች” የሚለውን ቃል በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚጠቀምበት ማየቱ ተገቢ ነው፡፡

የዘዳግም መጽሐፍ “ወንድሞች” የሚለውን ቃል አሥራ ሁለቱን የእስራኤል ነገዶች ለማመልከት ይጠቀማል፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፦

ዘዳ. 17፡14-15 “… አምላክህ እግዚአብሔር የመረጠውን በላይህ ታነግሳለህ ከወንድሞችህ የሆነውን በአንተ ላይ ንጉስ ታነግሳለህ፡፡ ወንድምህ ያልሆነውን ከሌላ ወገን ሰው በላይህ ንጉሥ ታደርግ ዘንድ አይገባህም ፡፡”

ዘዳ. 18፡1-2 ለሌዋውያን ካህናት ለሌዊም ነገድ ሁሉ ከእስራኤል ጋር ድርሻና ርስትአይሆንላቸውም፡፡ በእሳት ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መስዋእቱንና ርስቱን ይበላሉ፡፡በወንድሞቻቸውም መካከል ርስት አይሆንላቸውም፡፡ እርሱ እንደተናገራቸው ርስታቸውእግዚአሔር ነው፡፡

ዘዳ. 15፡7 አምላክህ እግዚአብሔር በሰጠህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ከሚኖሩ ከወንድሞችህ አንዱቢደኸይ ልብህን አታፅና፡፡ በድሃው ወንድምህ ላይ እጅህን አትጨብጥ፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ጥቅሶች ውስጥ ወንድሞች ተብለው የተጠሩት የእስራኤል ነገዶች መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ ዘዳ. 18፡18 በዙርያው ካሉት ከነዚህ ጥቅሶች በተለየ ሁኔታ ወደሌላ ወገን ያመለክታል ተብሎ መታሰብ የለበትም፡፡

ሌላው ይህ ጥቅስ ወደ ሙሐመድ እንደሚያመለክት የሚናገሩት ሙስሊሞች ቆርጠው የሚያስቀሩትና ክርክራቸውን ሁሉ ከስር መሠረቱ የሚንድ ሐሳብ እዚያው ምዕራፍ 18 ቁጥር አስራ አምስትና አስራ ስድስት ላይ ይገኛል፡፡

አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳልሃል፡፡

አሁን ሙስሊም ሰባኪያን ይህንን ጥቅስ ለምን ቆርጠው ከወገቡ መሃል ማንበብ አንደሚጀምሩ ግልፅ ነው፡፡ ይኸውም ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ የሚለውን ቃል መስማትም ሆነ ማየት ስለማይፈልጉ ነው፡፡ ፈለጉም አልፈለጉም እውነቱ ይኸው ነው! “ከአንተ መካከል” የሚለው ቃል ሌላ ምንም አማራጭ ሳያስቀር ወደ እስራኤላውያን ብቻ የሚያመለክት መሆኑን የሚክድ በእኩለ ቀን ሜዳ ላይ ቆሞ ፀሐይ አይታየኝም እንደሚል የታወረ ሰው ነው!

ሌላው ሙስሊም ዐቃቤ እምነታውያን ሊጠቅሱት የማይወዱት የቃሉ ተከታይ ክፍል እንዲህ ይነበባል፦

ዘዳ 18፡20-22 ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝሁትን ቃል በድፍረት የሚናገር ወይም በሌላ አማልክትስም የሚናገር ነቢይ እርሱ ይገደል፡፡ በልብህም፡እግዚአብሔር ያልተናገረውን ቃል እናውቅ ዘንድእንዴት ይቻለናል? ብትል ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው፡፡ ነቢዩ በድፍረት ተናግሮታል እርሱን አትፍራው፡፡

ሙሐመድ ይህንን መለኪያ ያልፍ ይሆን? “ሰይጣናዊ ጥቅሶች” በመባል ስለሚታወቁ መገለጦች በጥንታዊያን እስላማዊ ድርሳናት ውስጥ እናነባለን፡፡ ሙሐመድ እስልምናን በጀመረበት ወቅት ለረጅም ዘመናት ሲመለኩ የኖሩ አል-ላት፤ አል-ኡዛ እና አል-መናት በመባል የሚታውቁ ጣዖታትን ትቶ የርሱን ትምህርት መከተል ለብዙዎች ፈተና ሆኖ ነበር፡፡ ስለዚህ ሙሐመድ እነዚህ ጣዖታት እንደሚያማልዱ እንደ ተገለጠለት በመናገር ቁረይሾችን አስደሰተ፤ ብዙ ተከታዮችንም አገኘ፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ እንደተሳሳተ ገባው፡፡ እናም መገለጡ ከአላህ ዘንድ ሳይሆን ከሰይጣን ዘንድ እንደነበር ተናገረ፡፡ (ይህ ታሪክ በኢብን ኢስሃቅና በአልጠበሪ በተጻፉ የሙሐመድ ግለ-ታሪኮች ውስጥ በስፋት የተዘገበ ሲሆን ኢማም ቡኻሪ በከፊል ጽፈውታል። የበለጠ ለማወቅ እዚህ ጋ ጠቅ ያድርጉ)፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን ከእውነተኛ ነቢያት መካከል መገለጥ ተናግሮ መልሶ ደግሞ መገለጡ ከሰይጣን ዘንድ እንደሆነ የተናገረ ነቢይ የለም!

ሙስሊሞች ሙሴና ሙሐመድ እንደሚመሳሰሉ ለማሳመን ብዙ ጥረቶችን አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ይመሳሰሉባቸዋል በማለት የሚያነሱአቸው ነጥቦች ማንኛውም ተራ ሰው ሊመሳሰልባቸው የሚችላቸው ናቸው። ለምሳሌ ያህል ዑመር አርሲ ከአሕመድ ዲዳት በመቅዳት የወሠዷቸውን “መመሳሰሎች” እንደሚከተለው በመጽሐፋቸው ውስጥ አስፍረዋል፡-

“- ሁለቱም እናትና አባት ነበሯቸው

– አግብተው ልጆች ወልደዋል

– ተፈጥሮአዊ ሞት ሞተዋል

– ተዋግተዋል

– በሕዝባቸው ላይ መሪዎች ነበሩ” (ገፅ 59)

እነዚህ ተራ “መመሳሰሎች” ዋጋ የሚሠጣቸው ከሆነ አቶ ዑመርን ለመርዳት ያህል ጥቂት ነጥቦችን መጨመር እንችላለን፡-

  • ሁለቱም ሰዎች መሆናቸው
  • ሁለቱም ወንዶች መሆናቸው
  • ሁለቱም ጢም ያላቸው መሆናቸው
  • የሁለቱም ስም “M” በሚለው የእንግሊዘኛ ፊደል መጀመሩ ወዘተ.

ደቡብ አፍሪካዊው አሕመድ ዲዳት በተለያዩ ጽሑፎቻቸውና የቪዲዮ ሰበካዎቻቸው ሙሴና ሙሐመድ እንደሚመሳሰሉ ለማሳየት በዑመር አርሲ የተጠቀሱትን ነጥቦች ከኢየሱስ ጋር በማያያዝ በእነዚህ ነገሮች ሙሴና ኢየሱስ እንደማይመሳሰሉ በመግለጽ ሙሐመድና ሙሴ ይመሳሰላሉ ለሚለው ነጥባቸው ጥንካሬን ለመስጠት ይታገላሉ፡፡ አሕመድ ዲዳት ፡፡ ሙሴና ሙሐመድን ብቻ ማመሳሰል ሚዛን የማይደፋ ከንቱ ልፋት መሆኑን የተረዱ ይመስላል፡፡ እንደ አሕመድ ዲዳት ብልጠትና ማጭበርበርን ያልተካኑት የአገራችን ጸሐፊ ዑመር አርሲ ግን ኢየሱስን ከሁለቱ በመነጠል የሙሴና የሙሐመድ መመሳሰል ተራ መሆኑን በበቂ ሁኔታ አሳይተዋል፡፡ ግሩም ሥራ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ሙሴን የሚመስለው ነብይ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ይናገራል (ሐዋ. 3፡17-26)።

ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው መመሳሰል የጠለቀና መንፈሳዊ ገፅታ ያለው እንጂ ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት ተራ መመሳሰል እንዳልሆነ መረዳት ተገቢ ነው፡፡

ሙሴና ኢየሱስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንፅፅር (ከብዙ በጥቂቱ)

  1. ሙሴና ኢየሱስ የተወለዱት ወገኖቻቸው በባዕድ አገዛዝ ሥር በነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡ ዘጸ. 1፡9-14፣ ሉቃ. 2፡1
  2. ሁለቱም በተወለዱ ጊዜ የሞት አዋጅ ታውጆባቸው ነበር፡፡ ዘጸ. 1፡15-16 ማቴ. 3፡13-18
  3. ሁለቱም በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ከሞት ተርፈዋል፡፡ ዘጸ. 2፡ 2-10 ማቴ. 2፡13-18
  4. ሁለቱም በግብፅ ተጠልለው ኖረዋል፡፡ ዘጸ 2፡10 ማቴ. 2፡14-15
  5. ሁለቱም በድንቅና በተአምራት ተገልጠዋል፡፡ ዘጸ. ም. 7፤8፤14፤17 ማቴ 8፡14-17ሉቃ 7፡11
  6. ሁለቱም አርባ ቀንና ሌሊት ፆመዋል፡፡ ዘጸ. 32፡ 31 ማ ቴ. 4፡2
  7. ውሃ ለሁለቱም ሥልጣን ተገዝቷል፡፡ ዘጸ. 14፡21 ማቴ. 14፡ 22-23
  8. ሙሴ የብሉይ ኪዳን መካከለኛ ሲሆን ኢየሱስ ደግሞ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው፡፡ ዘጸ. ም. 19-20 ዕብ 12፡24
  9. ሙሴ እስራኤላዊያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ እንዳወጣ ሁሉ ኢየሱስም በስሙ ያመኑትን ከኃጥያት ባርነት ነፃ ያወጣል፡፡ ኢሳ. 53 ዮ ሐ 8፡32-36 ሉቃ 4፡17-19
  10. ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ ተነጋግሯል፡፡ ኢየሱስም እንደዚሁ፡፡ ዘጸ. 33፡11 ማቴ. 17፡3
  11. ሁለቱም ሕዝብ እየሠማ እግዚአብሔር ተናግሯቸዋል፡፡ ዘጸ. 19:19 ዮሐ 12:28
  12. በሲና ተራራ ላይ በነበረው ክብር ምክንያት የሙሴ ፊት ሲያበራ በተራራው ሕብረት ምክንያት እንዲሁ የክርስቶስ ሁለንተና አብርቷል፡፡ ዘጸ 34፡29 ማቴ 17፡2
  13. ሁለቱም ተከታይ ለማግኘት ሰይፍ አላነሱም፡፡ ዘጸ. 7፡8፤ 14፡25 ማር 1፡21-25
  14. የሙሴ መቃብር በመላእክት ይጠበቅ እንደነበረ ሁሉ የክርስቶስም እንዲሁ ነበር፡፡ ይሁዳ 1፡9 ማቴ 28፡2
  15. ሙሴ ከሞተ በኋላ ለነ ጴጥሮስ ታይቷል፡፡ ኢየሱስም እንደዚሁ ከሙታን ተነስቶ ለነ ጴጥሮስ ታይቷል፡፡ ማቴ 17፡1-5፣ ዮሐ 20፡19

ክርስቲያኖች ሙሴና ኢየሱስ ይመሳሰላሉ በማለት ሲናገሩ ከላይ በቀረበው መልኩ ነው፡፡ ከላይ በተጠቀሱት በአብዛኞቹ ነጥቦች ላይ ሙሴና ሙሐመድ ይቃረናሉ እንጂ አይመሳሰሉም፡፡ ስለዚህ ሙስሊሞች ከላይ የተጠቀሱት ዓይነት የጠለቀ አንድምታ ያላቸው መመሳሰሎች በሙሴና በሙሐመድ መካከል መኖራቸውን ሊያረጋግጡልን ይችላሉን?

አፅናኙ ሙሐመድ ነውን?

ዮሐንስ 14፡16 “እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እን ዲኖር ሌላ አፅናኝይሰጣችኋል”

በቁርአን 61፡6 ላይ እንዲህ የሚል ቃል ተፅፎ እናገኛለን “የመርየም ልጅ ኢሳም፡– የእስራኤል ልጆችሆይ እኔ ከተውራት በፊቴ ያለውን የማረጋገጥና ከኔ በኋላ የሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድበሆነው የማበስር ሲሆን ወደእናንተ (የተላክሁ) የአላህ መልክተኛ ነኝ፡፡” ይህንን ቃል የሚደግፍ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማግኘት ካላቸው ጉጉት የተነሳ ሙስሊም ሰባኪያን ስለ አፅናኙ የተተነበየውን ትንቢት ስለ ሙሐመድ ነው የሚል መከራከርያ ያቀርባሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ክርስቲያኖች ይህንን እውነታ በማጣመም መንፈስ ቅዱስ ነው በማለት እንደሚያስተምሩ በማማረር ይወነጅላሉ፡፡ እንደሌሎቹ እስላማዊ ክርክሮች ሁሉ ይህኛውም ፍፁም የተሳሳተና መሠረተ ቢስ መሆኑን እንደሚከተለው እንገልጣለን፡፡

ሙስሊም ዳዒዎች አሕመድ የሚለው የአረብኛ ቃል በግሪክ ቋንቋ “ፔሪክሉቶስ” (በአማርኛ አነባበብ ጴሪቅሉጦስ) እንደሆነና ክርስቲያኖች “ፐራክሊቶስ” (በአማርኛ አነባበብ ጰራቅሊጦስ) ወደሚለው እንደቀየሩት ይናገራሉ፡፡ “ፐራክሊቶስ” በግሪክ ቋንቋ አፅናኝ ማለት ሲሆን ወደ “ፔሪክሉቶስ” ሲቀየር “የተመሰገነ” (በአረብኛ አሕመድ) የሚል ትርጓሜን ይሰጣል፡፡ ነገር ግን ሙሐመድ ከመወለዱ በፊት ብዙ ዘመናትን ካስቆጠሩ በሺዎች ከሚቆጠሩ የአዲስ ኪዳን መዛግብት መካከል አንዱም እንኳ “ፔሪክሉቶስ” የሚለውን ቃል ይዞ አይገኝም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ላይ ተፅፎ የሚገኘው “ፐራክሊቶስ” የሚለውና አፅናኝ የሚል ትርጉም ያለው ቃል ነው፡፡ በመሆኑም ይህ የሙስሊም ሰባኪያን ክስ መሠረተ ቢስ አሉባልታ ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

ብዙ ጊዜ ሙስሊም ወገኖቻችን ሊያነቡ የማይወዱትና ክርክራቸው ትክክል እንዳልሆነ የሚገልጥ የክፍሉ ቀጣይ ቁጥር እንዲህ ይላል፦

“እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለሆነ ሊቀበለው የማይችለው የእውነት መንፈስ ነው፡፡ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውስጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቁታላቸሁ” ዮሐ. 14፡17፡፡

ኢየሱስ ይህንን ቃል የተናገረው ለሐዋርቱ ነበር፡፡ አፅናኙም ይመጣል እያለ ያለው ወደ እነርሱ ነው፡፡ በማስከተል ደግሞ እንዲህ በማለት የአፅናኙን ማንነትና ይሥራ ድርሻ ግልፅ አድርጓል፦

“አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አፅናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔምየነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” ዮሐ. 14፡26

“እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል፡፡ እኔ ባልሄድ አፅናኙ ወደ እናንተአይመጣምና፡፡ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ ፡፡ እርሱም መጥቶ ስለኃጢዓት ስለፅድቅምስለፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፡፡ ስለኃጢዓት በኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለፅድቅም ወደ አብ ስለምሄድከዚህ በኋላ ስለማታዩኝ ነው ስለፍድም የዚህ ዓለም ገዢ ስለተፈረደበት ነው፡፡ የምነግራችሁ ብዙነገር አለኝ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም፡፡ ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደእውነት ሁሉ ይመራችኋል፡፡ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይናገርምና የሚመጣውንምይነግራችኋል፡፡ እርሱ ያከብረኛል ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና፡፡ ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው ፡፡ስለዚህ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ” ዮሐ. 16፡8-16፡፡

አፅናኙ ሙሐመድ ነው ከተባለ ተከታዮቹን ነጥቦች ሙስሊም ዐቃቤ እምነታውያን እንዴት ይመለከቱአቸዋል?

  1. አፅናኙን ዓለም ሊያየው ሊያውቀውና ሊቀበለው አይችልም፡፡ ሙሐመድ ግን ሥጋ ለባሽ እንጂ መንፈስ ስላልነበረ በዓለም ታይቷል ፤ ማንነቱም በታሪክ ይታወቃል፡፡
  2. አፅናኙ “የእውነት መንፈስ” እንጂ ሰው አይደለም፡፡
  3. አፅናኙ ከኢየሱስ ሐዋርያት ዘንድ ስለሚኖርና በውስጣቸውም ስለሚሆን እነርሱ ያውቁታል፡፡ ሙሐመድ ግን የመጣው እነዚህ ሰዎች ከሞቱ ከብዙ አመታት በኋላ ስለሆነ ከእነርሱ ጋር መኖር አይችልም፤ መንፈስ ስላልሆነም በውስጣቸው ሊያድር አይችልም፡፡
  4. አፅናኙ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ በግልጥ ተፅፏል፡፡
  5. አፅናኙ የሚመጣው በኢየሱስ ስም ነው። ሙሐመድ ግን በማን ስም ነው የመጣው?
  6. አፅናኙ ለኢየሱስ ሐዋርያት ሁሉን ያስተምራቸዋል ኢየሱስ የነገራቸውንም ሁሉ ያሳስባቸዋል፡፡ ሙሐመድ ግን በእነርሱ ዘመን ስላልነበረ ይህን ሁሉ ነገር ማድረግ አይቻለውም፡፡
  7. አፅናኙ ኢየሱስን ያከብረዋል፡ ከኢየሱስ ካለውም ወስዶ ለሐዋርያቱ ይነግራቸዋል፡፡ ምክንያቱም የአብ የሆነው ሁሉ የኢየሱስ ነውና፡፡ ሙስሊሞች የአብ የሆነው ሁሉ የኢየሱስ መሆኑን ያምናሉን?
  8. አፅናኙን ወደ ሐዋርያቱ የሚልከው ራሱ ኢየሱስ ነው፡፡ ሙስሊሞች ሙሐመድ በኢየሱስ እንደተላከ ያምናሉን? አፅናኙ ሙሐመድ ነው ከተባለ ተከታዩ አመክንዮአዊ ድምዳሜ አይቀሬ ነው፦
  • ሙሐመድን የላከው አላህ ነው።
  • ሙሐመድ አፅናኙ ነው።
  • አፅናኙን የላከው ኢየሱስ ነው።
  • ስለዚህ አፅናኙ ሙሐመድን የላከው አላህ ኢየሱስ ራሱ ነው።

በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ እንደምናነበው ጌታ ኢየሱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ወደ ሐዋርያቱ መምጣት በድጋሜ የተስፋ ቃሉን አጽንቷል (ሐዋ. 1፡5)፡፡ ይህም የተስፋ ቃል በጥቂት ቀናት ውስጥ ፍፃሜን አግኝቷል፡፡ (የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ሁለትን ያንብቡ፡፡)

ሙስሊሙ ጸሐፊ ዑመር አርሲ “ታላቅ ምክር ለአዲሱ ትውልድ” በሚለው መጽሐፋቸው ገፅ 57 እና 58 ላይ ዮሐ. 16፡5-8 ላይ ያለውን ቃል ሲጠቅሱ “እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ” የሚለውን ዐረፍተ ነገር በግልፅ ይዘሉታል፡፡ ይህ የኢየሱስ ንግግር አፅናኙ ሙሐመድ ነው የሚለውን ነጥባቸውን የእምቧይ ካብ እንደሚያደርግባቸው ስለሚገነዘቡ እንደ አቶ ዑመር ሁሉ ሙስሊም ሰባኪያን በንግግሮቻቸውና በጽሑፎቻቸው ውስጥ ይህንን ቃል ላለመጥቀስ ይጠነቀቃሉ፡፡

አቶ ዑመር በመጽሐፋቸው ውስጥ መንፈስ ቅዱስ “ዓለምን ሲወቅስ አልታየም” በሚል ልፍስፍስ ምክንያት አፅናኙ እርሱ እንዳልሆነ ለማሳመን ይጥራሉ (ገፅ 57)፡፡ ነገር ግን በሐዋርያት ውስጥ ሆኖ ዓለምን ሲወቅስ የነበረው ማን ነበር? ራሱ መንፈስ ቅዱስ አልነበረምን? መንፈስ ቅዱስ ዓለም ባያየው፣ ባያውቀውና ባይቀበለው እንኳ በሐዋርያት ውስጥ ሆኖ ሥራውን ሲሠራ ነበር፡፡ በእርሱ ምሪት በተጻፈልን በቅዱስ ቃሉም አማካይነት ሥራውን ቀጥሏል፡፡ ዛሬም ቢሆን በእውነት በክርስቶስ ኢየሱስ ባመኑት ክርስቲያኖች ውስጥ ይኖራል፡፡

መንፈስ ቅዱስ በሁሉ ስፍራ በመገኘት ችሎታው ከሐዋርያት ጋር ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚያ ባለፈ ሊጠቀምባቸውና ሥራውን ሊሠራ በውስጣቸውም ሊኖር በታላቅ ክብር ወደ እነርሱ የመጣው ኢየሱስ የተስፋ ቃሉን ለሐዋርያቱ ካፀናላቸው ከጥቂት ቀናት በኋላ ነበር፡፡ ዑመር አርሲ “መንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር አብና ከእግዚአሔር ወልድ ጋር እኩል ከሆነ ከማነው የሚሰማውን የሚናገረው?” የሚል ጥያቄ ይሰነዝራሉ (ገፅ 58)፡፡ በእግዚአብሔር አካላት (በሥላሴ) መካከል እኩልነት መኖሩ እንደይከባበሩ እንዳይደማመጡና አንዱ ለአንዱ እንዳይታዘዝ አያደርግም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ የሚሰማውን መናገሩ፤ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ለአብ መገዛቱና በመንፈስ ቅዱስ መመራቱ፤ አብ ኢየሱስን ማክበሩ ለኛ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን የፍቅርና የትህትና መገለጫ እንጂ የበላይነትና የበታችነትን አያሳይም፡፡ አቶ ዑመርና ሌሎች ሙስሊም ተሟጋቾች የክርስቲያኖች አምላክ በቁርኣን ውስጥ ከተገለጠው አምላካቸው ፈፅሞ የተለየ መሆኑን ሊረዱልን ይገባል፡፡

አምስቱ ጥቅሶች

በማስከተል ሙስሊም ዐቃቤ እምነታውያን ስለሙሐመድ እንደተተነበዩ በማስማሰል የሚጠቅሷቸውንና መለስተኛ ግምት የሚሰጧቸውን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንመለከታለን፡፡

  1. ዘዳ. 33፡2-3 “እግዚአብሔር ከሲና መጣ ከሴይርም ተገለጠ ከፋራን ተራራ አበራላቸውከአእላፋትም ቅዱሳኑ መጣ፡ በስተቀኙ የእሳት ህግ ነበረላቸው ፡፡ ህዝቡንም ወደዳቸውቅዱሳኑ ሁሉ በእጅህ ናቸው፡፡”

ሙስሊም ዐቃቤ እምነታውያን ለዚህ ጥቅስ ማብራሪያ ሲሰጡ “እግዚአብሔር ከሲና ሲመጣ በሙሴ በኩል መጣ ከሴይር ሲገለጥ በኢየሱስ በኩል ተገለጠ ከፋራን ተራራ ሲያበራ በሙሐመድ በኩል አበራ” በማለት ነው፡፡ ነገር ግን “እግዚአብሔር” የሚል እንጂ “ነቢይ” የሚል አንድም ቃል በቦታው ላይ አይገኝም፡፡ ሙስሊሞች ይህንን ቃል ለነቢያቸው እንደተነገረ ትንቢት የሚቆጥሩበት ምክንያት የፋራን ተራራ መካ አጠገብ ይገኛል ከሚል የተሳሳተ ግምት በመነሳት ነው፡፡ የፋራን ተራራ የሚገኘው በሰሜን ምዕራብ ሲና በሚገኘው በፋራን ምድረበዳ ውስጥ ነው፡፡ ይህም ከመካ ቢያንብ 1000 ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ እስራኤላውን በጉዟቸው ወቅት በፋራን ምድረበዳ ውስጥ እንዳለፉ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልፅ ሰፍሯል (ዘኁ. 10፡12፤ 12፡16፤ 13፡3፤13፡26 ዘዳ. 1፡1)፡፡ መቼም እስራኤላውያን ወደ መካ እንዳልተጓዙ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ለራስ ዓላማ ሲባል የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል እንደፈለጉ መተርጎም ትክክለኛ አካሄድ እንዳልሆነ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

2. ራዕይ 19፡11 “ሰማይም ተከፍቶ አየሁ እነሆም አምባ ላይ ፈረስ የተቀመጠበትም የታመነናእውነተኛ ይባላል፡ በፅድቅም ይፈርዳል ይዋጋልም፡፡ ”

ሙስሊም ዐቃቤ እምነታውያን ስለነቢያቸው እንደተተነበዩ በማስመሰል በድፍረት ከሚያቀርቧቸው ጥቅሶች መካከል በጣም አስገራሚው ይኸኛው ነው፡፡ ሙስሊሙ ጸሐፊ ዑመር አርሲ የዚህን ጥቅስ ቀጣይ ክፍል ቆርጠው በማስቀረት ከላይ የተጠቀሰውን ብቻ በመውሰድ ለሙሐመድ የተነገረ ነውና እመኑ ይሉናል (ገፅ 58)፡፡ ምናልባት የሳቸውን መጽሐፍ የሚያነቡ አብዛኞቹ ሙስሊሞች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ለማመሳከር እድሉ እንደሌላቸው ስለሚያውቁ እነርሱን ለማታለል ካልሆነ በስተቀር መጽሐፍ ቅዱስ በእጁ እያለለት የሚታለል ክርስቲያን እንደማይኖር ልቦናቸው ሳያውቅ ቀርቶ አይመስለንም፡፡ ቀጣዩ ክፍል እንዳህ ይነበባል፡-

“ዓይኖቹ እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፡፡ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶቸ አሉ፡፡ከእርሱ በቀር አንድስንኳየማያውቀው የተፃፈ ስም አለው፡፡ በደምም የተረጨ ልብስ ተጎናፅፏል ስሙም የእግዚአብሔርቃል ተብሎአል፡፡ … በልብሱና በጭኑ ላይ የተፃፈበት፡– የነገስታ ንጉስና የጌታዎች ጌታ የሚል ስምአለው፡፡” ራዕ. 19፡12-16

በቁርኣንም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የእግዚአብሔር ቃል” መሆኑ የተመሠከረለት ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ (ዮሐ. 1፡11 ከሱራ 4፡171 ጋር ያነፃፅሩ፡፡)

አቶ ዑመር የክርስትና መመርያ መዋጋትን ስለሚከለክል ይህ ጥቅስ ኢየሱስን አይመለከትም ይሉናል፡፡ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ በዳግም ምፅዓቱ ጊዜ ለሁሉም እንደየሥራው ዋጋን እንደሚሰጥና በፅድቅ እንደሚፈርድ እንዲሁም የሰይጣንን ኃይል እንደሚደመስስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጥ ተጽፏል (ራዕ. 22፡12 ፤19፡19-21)፡፡ ኢየሱስ መጀመርያ የመጣው ሰዎችን ለማዳን ሲል ራሱን ዝቅ አድርጎ ክብሩን ጥሎ ቢሆንም ነገር ግን በዳግም ምፅዓቱ ጊዜ በታላቅ ግርማና ሞገስ ጠላቶቹን ለመደምሰስና በፅድቅ ሊፈርድ ይገለጣል፡፡ ዮሐንስም በራዕዩ ያየው ይህንኑ ነው፡፡

3. ዕንባቆም 3፡3 “እግዚአብሔር ከቴማን ቅዱሱም ከፋራን ተራራ ይመጣል፡፡ ክብሩም ሰማያትንከድኗል፡፡ ምስጋናውም ምድርን ሞልቷል፡፡”

አሁንም የሙስሊም ጸሐፊያን ግራ መጋባት የመነጨው ቴማን መዲና ፋራን ደግሞ መካ ነው ከሚል የተሳሳተ ግምት ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ ፋራን ከመካ ርቆ የሚገኝ ቦታ እንሆነ ቀደም ሲል ገልፀናል፡፡ ቴማን ደግሞ ከመካ ቢያንስ በ400 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ወደ ሰሜን አቅጣጫ የሚገኝቦታ ነው።

ይህ ቃል የሚናገረው እግዚአብሔር በታላቅ ግርማ እንደሚገለጥ ነው፡፡ ይመጣል የተባለውም ራሱ እግዚአብሔር ሲሆን ወደ ሌላ ወደ ማንኛውም ነቢይ አያመለክትም፡፡ ይህ ዓይነቱ አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለመደ፤ የእግዚአብሔርን ክብር እንዲሁም ቁጣውን ለመግለጥ የሚነገር ተምሳሌታዊ ንግግር ነው፡፡ መካና መዲና ከቴማንና ፋራን ጋር በፍፁም አንድ ስላልሆኑ ይህ የሙስሊሞች መከራከርያ ስፍራ የሚሰጠው አይደለም፡፡

4. ኢሳያስ 21፡7 “በከብት የሚቀመጡትን ሁለት ሁለት እየሆኑ የሚሄዱት ፈረሰኞች በአህዮችየሚቀመጡትንና በግመሎች የሚቀመጡትን ባየ ጊዜ በፅኑ ትጋት አስተውሎ ተግቶም ያዳምጥ”

ሙስሊም ጸሐፊያን በግመሎች የሚቀመጡት ነቢዩ ሙሐመድና ተከታዮቹ ሲሆኑ በአህዮች የሚቀመጡት(!?) ደግሞ ኢየሱስ እንደ ሆነ ይነግሩናል፡፡ እኛ ደግሞ በፈረሶች የሚቀመጡትስ እነማን ሊሆኑ ይችላሉ? ብለን እንጠይቃቸዋለን፡፡ ኢየሱስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ብቻውን በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ እንጂ ሌሎች ሰዎች ከርሱ ጋር በአህዮች ተቀምጠው አላጀቡትም ሉቃ. 19፡28-40፡፡ ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ ነቢያት ሳይሆን ስለባቢሎን መጥፋት ነው፡፡ ይህንንም እዚያው ላይ ከተጻፈው ቃል መረዳት ይቻላል፡፡ “ባቢሎን ወደቀች …” (ቁ. 9)፡፡ የባቢሎንን መጥፋት የሚያውጁ መልእክተኞች በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚመጡ የሚገልጥ ትንቢት መሆኑን ከአውደ ንባቡ መገንዘብ እንችላለን፡፡ ስለዚህ ይኸኛውም የሙስሊም ጸሐፊያን የመከራከሪያ ነጥብ እንደሌላው ሁሉ ሚዛን የሚደፋ አይደለም፡፡

5. ኢሳያስ 21፡13-17 “ ስለ ዓረብ የተነገረ ሸክም፡– የድዳው ያን ነጋዴዎች ሆይ በአረብ ዱር ውስጥታድራላችሁ፡፡ በቴማን የምትኖሩ ሆይ ወደ ተጠሙ ሰዎች ውሃ አምጡ እንጀራ ይዛችሁየሸሹትን ሰዎች ተቀበሏቸው፡፡ከሰይፍ ከተመዘዘው ሰይፍ ከተለጠጠውም ቀስት ከፅኑምሰይፍ ሸሽተዋልና፡፡ ጌታ እንዲህ ብሎኛልና፡– እንደምንደኛ ዓመት በአንድ ዓመት ውስጥ የቄዳርክብር ሁሉ ይጠፋል ከቀስተኞች ቁጥር የቀሩት የቄዳር ልጆቸ ኃያላን ያንሳሉ፡፡ የእስራኤልአምላክ እግዚአብሔር ተናግሯልና፡፡”

ከላይ የተጠቀሰው ጥቅስ የሙሐመድን ከመካ ወደ መዲና መሰደድ የሚያመለክት እንደሆነ ሙስሊም ሰባኪያን ይነግሩናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠው ቴማን መዲና እንዳልሆነ ቀደም ሲል ተመልክተናል፡፡ ቄዳር ተብለው የሚታወቁት ደግሞ የእስማኤል ዝርያዎች ናቸው፡፡ (ሙሐመድ የእስማኤል ዘር ስለመሆኑ እስላማዊ ምንጮች እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ መርጃዎችን ያቀርባሉ። ገሚሶቹ የእስማኤል ዘር እንደሆን የሚናግሩ ሲሆን ገሚሶቹ ግን ይህንን ሐሳብ ያፈርሳሉ። ሙሐመድን ከእስማኤል ጋር ማያያዝ ከአብርሃም ጋር እርሱን በማገናኘት ለነቢይነቱ ሕጋዊ መሠረት ለመስጠት በኋለኞቹ ሙስሊሞች የተፈጠረ የፈጠራ ታሪክ እንጂ ማስረጃ ያለው አይደልም። ለበለጠ መረጃ እዚህ ጋር ጠቅ ያድርጉ።)

ኢሳይያስ በትንቢቱ ውስጥ እየተናገረ ያለው ሕዝቦች ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ስለሚሰደዱበት ሁኔታ ነው፡፡ በዚሁም መሠረት ኢሳይያስ ትንቢቱን በተናገረ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በ732 ዓ.ዓ ላይ አሦራውያን መካከለኛውን ምስራቅ በመውረር ብዙ ሕዝቦችን ፈጅተዋል፡፡ በዚህም ወረራ በአረብና በሲና በረሃ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ህዝቦች ከአንዱ ወደ ሌላው ቦታ ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ውስጥ በግልፅ እንደተናገረው የመፈፀምያ ጊዜው በአንድ አመት ውስጥ ነው፡፡ ትንቢቱም በትክክል ተፈጽሟል፡፡

ዑመር አርሲ ሙሐመድ ከመካ ወደ መዲና ከተሰደደ ከአንድ ዓመት በኋላ የመካን ክብር ስላጠፋ ትንቢቱ በዚያ ተፈጽሟል በማለት ጽፈውልናል (ገፅ 46)፡፡ ይህ ፍጹም ሀሰት ነው፡፡ ሙሐመድ መካን ለመቆጣጠር ድፍን ስምንት ዓመት ፈጅቶበታል፡፡ “የበድር ጦርነት የተካሄደውና ሙሐመድና ተከታዮቹ የመካን ነዋሪዎች ያሸነፉት ከስደቱ በኋላ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነበር” የሚለው የአቶ ዑመር አባባል ዐይን ያወጣ ቅጥፈት ነው፡፡ እኚህ ጸሐፊ “አንድ ዓመት” የሚለውን የትንቢት ቃል ከሙሐመድ ታሪክ ጋር ለማገናኘት የበድር ጦርነት የተደረገው በ 623 ዓ.ም. እንደነበር ነግረውናል፡፡ ነገር ግን ሙሐመድ ከመካ ወደ መዲና የተሰደደው በ622 እ.ኤ.አ ሲሆን የበድር ጦርነት ደግሞ የተካሄደው በ624 እ.ኤ.አ (በሁለተኛው ሂጅራ) ነው፡፡ በድር ላይ ካሸነፈ ከአንድ ዓመት በኋላ በ625 ዓ.ም በእሁድ ጦርነት ላይ ከባድ የሆነ ሽንፈት ገጥሞታል፡፡ በዚህ ጦርነት ላይ አጎቱ ሐምዛ የሞተ ሲሆን ሙሐመድ እራሱ ከጠላት ወገን በተወረወረ ድንጋይ ከንፈሩ ተሰንጥቆ ሁለት የፊት ጥርሶቹ ረግፈዋል፡፡ የሙሐመድ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሁለት ጥርሶች ዛሬ በኢስታንቡል ሙዚየም ውስጥ ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ (Paul Fregosi, Jihad in the West, 1998, p. 53 ይመልከቱ፡፡)

ሙስሊሞች መካን ከተቆጣጠሩ በኋላም ቢሆን የመካ ክብር ጠፍቷል የሚያስብል ምንም ምክንያት የለም፡፡ የመካ ነዋሪዎች ለሙሐመድ እጅ መስጠታቸው በብዙ መልኩ ጥቅማቸውን አስጠብቆላቸዋል፡፡ ከካዕባ ያገኙ የነበሩትም ገቢ ቀደም ሲል ቢቀዛቀዝም ነገር ግን ለአምልኮ ወደዚያ በሚመላለሱ ሙስሊሞች ሳቢያ ተፈላጊነታቸው ጨመረ እንጂ አልቀነሰም፡፡ ከሙሐመድ ሞት በኋላም ቢሆን በኸሊፋዎች አማካይነት የመሪነቱን ስፍራ በመቆናጠጥ የበላይነታቸውን አረጋግጠው ኖረዋል፡፡ ታዲያ የመካና የነዋሪዎቿ የቁረይሾች ክብር ሁሉ ጠፍቷል የሚያስብል ምን ሁኔታ ተፈጠረ? ሙስሊሙ ጸሐፊ ዑመር አርሲ የሙሐመድን ነቢይነት በመጽሐፍ ቅዱስ ለማረጋገጥ ያላቸው ጉጉት ታሪክን እንኳ እንዲጠመዝዙ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡

ሙስሊም ዳዒዎች ለሙሐመድ የተተነበየ በማስመሰል የሚያቀርቡትን ሌላ ትንቢት የተመለከተ ጽሑፍ ያንብቡ:- የሙሐመድ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ?

እግዚአብሔር አምላካችን የሙስሊም ወገኖቻችንን የልብ ዐይኖች በመክፈት እውነትን ወደማወቅ ይመራቸው ዘንድ የዘወትር ጸሎታችን ነው፡፡

ሙሐመድ