ሙሐመድ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰችውን አይሻን ስለ ማግባቱ – ለሙስሊሞች ምላሽ የተሰጠ ምላሽ

ሙሐመድ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰችውን አይሻን ስለ ማግባቱ 

ለሙስሊሞች ምላሽ የተሰጠ ምላሽ

የሙሐመድን ሐሰተኛ ነቢይነት ከሚያሳዩ ተግባራቱ መካከል አንዱ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰችን ህፃን ማግባቱ ነው፡፡ ሙስሊም ወገኖች ይህንን የነቢያቸውን አስደንጋጭ ተግባር ለማብራራትና ለሰዎች ህሊና ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ብዙ ርቀት ሔደዋል፡፡ አንዳንዶች በሙሐመድ ታሪክ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ክስተቶችን በመጥቀስ የአይሻ ዕድሜ ከተነገረው በላይ እንደሆነና ሙሐመድ ለአቅመ ሔዋን ያልበቃችን ሴት እንዳላገባ ለማስረዳት ጥረት ቢያደርጉም አሳማኝ ሙግት ማቅረብ ተስኗቸዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ሙሐመድ አይሻን በ 6 ዓመቷ አጭቷት በ 9 ዓመቷ ማግባቱ በግልፅና በማያሻማ አገላለፅ ብዙ ጊዜ በመደጋገም በሐዲስና በሲራ መጻሕፍት ውስጥ መነገሩ ነው፡፡[1]

ይህንን ዘገባ ማስተባበል እንደማይቻል የተረዱት ሙስሊም ሊቃውን ዘገባውን ከመካድ ይልቅ የተለያዩ ሰበቦችን በመስጠት የሙሐመድን ጋብቻ ለማፅደቅ ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ ዳሩ ግን ምንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ ይህ ታሪክ በሙሐመድ እውነተኛ ነቢይነት ላይ የሚፈጥረውን ችግር ለመቅረፍ አልተቻላቸውም፡፡ በዚህ ጽሑፋችን ሙስሊም ወገኖች ለዚህ የነቢያቸው ተግባር እንደ ማፅደቂያ የሚጠቅሷቸውን ነጥቦች አንድ በአንድ እንፈትሻለን፡፡

የመጀመርያው ሙስሊም ወገኖቻችን የሚሰጡት ምላሽ የማርያምና የዮሴፍን እጮኝነት የተመለከተ ነው፡፡ የካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ ውስጥ የማርያም ዕድሜ 12 እንደነበረና የዮሴፍ ዕድሜ ደግሞ 90 እንደነበረ ተጠቅሷል ይሉናል፡፡

ይህ አስተያየት ከመቶ ዓመታት በፊት የተነገረ ሲሆን ማስረጃ አልባ ግምት ነው፡፡ በክርስቲያናዊ ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር አይገኝም፡፡ እኛ ስለ አይሻ ዕድሜ ጠቅሰን የምንሟገተው የሙስሊሞች ሃይማኖታዊ መመርያ ከሆኑት የሐዲስ መጻሕፍት ውስጥ እንጂ ከኢንሳይክሎፒድያ መጻሕፍት አይደለም፡፡ ከመቶ ዓመታት በፊት በ 1913 ዓ.ም. የተጻፈውን ኢንሳይክሎፒድያ ጠቅሰው ከሚሟገቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ የማርያምን ዕድሜ የሚገልፅ ማስረጃ ቢጠቅሱልን በተቀበልናቸው ነበር፡፡

የጥንት አይሁድ ሴቶችን በጨቅላነታቸው እንደሚድሩ የታወቀ ሲሆን የመጨረሻው ዝቅተኛ ዕድሜ 12 መሆኑን ሕጋቸው ያስቀምጣል፡፡[2] ዶ/ር ጂም ዌስት የተሰኙ የነገረ መለኮት ምሑር የአይሁድ ሴቶችን የጋብቻ ዕድሜ ሲገልፁ ወደ ጉርምስና ከገቡ በኋላ ወይንም 13 ዓመት አካባቢ ሲሆናቸው መሆኑን ጽፈዋል፡፡[3] የጥንት አይሁድ ሴቶቻቸውን በጨቅላነታቸው ቢድሩም የወር አበባን ከማየታቸው በፊት በ 9 ዓመት ዕድሜያቸው አልነበረም፡፡ ሙስሊሞች የሚጠቅሱት የማርያምና የዮሴፍ እጮኝነት ዕድሜ ትክክል ነው ቢባል እንኳ የ 9 ዓመትና የ 12 ዓመት ዕድሜ ሴቶችን ማነፃፀር አይቻልም፡፡ የ 12 ዓመት ሴት ልጅ ለጋብቻ ብቁ ባትሆንም ከ 9 ዓመት አንፃር ቢያንስ የመጀመርያ የወር አበባዋን የያች በመሆኗ የሚደርስባት ጉዳት እንደ 9 ዓመቷ የከፋ አይሆንም፡፡ የኛ ተቃውሞ በሙሐመድና በአይሻ መካከል የዕድሜ ልዩነት ለምን ኖረ ሳይሆን ለአቅመ ሔዋን ሳትደርስ ለምን አገባት ነው፡፡ የ50 ዓመት ጎልማሳ የ 5 ዓመት ህፃን ቢያገባና የ 70 ዓመት አዛውንት የ 25 ዓመት ሴት ቢያገባ የሁለቱም ልዩነት 45 ዓመት ቢሆንም ከባዮሎጂና ከግብረገብነት አንፃር የ 50 ዓመቱ ጎልማሳ ተግባር ይኮነናል፡፡ ስለዚህ የዕድሜ ልዩነት ችግር እንደሌለው ሊያስረዱን የሚደክሙት ሙስሊም ወገኖቻችን ምላሽ ከመስጠታቸው በፊት የሙግታችንን ነጥብ ቢረዱት መልካም ነው፡፡

ሁለተኛው የሙስሊሞች ምላሽ  ከባሕል አንፃር የሚቀርብ ሙግት ነው፡፡ በዘመኑ በነበረው ባሕል መሠረት የሙሐመድና የአይሻ ጋብቻ ተቀባይነት ስለነበረው ትክክል ነበር ይሉናል፡፡ ባሕል እንደየዘመኑ የሚለያይና ተነፃፃሪ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን በሙስሊሞች እምነት መሠረት የሙሐመድ ስብዕና ዘመን ተሻጋሪ በመሆኑ ይህ ሙግት ተቀባይነት የለውም፡፡ ሙሐመድ ለሰው ልጆች ሁሉ ምርጡ ምሳሌ እንዲሆን የተላከ ከሆነ ስነ ምግባሩ መመዘን ያለበት በሰባተኛው ክፍለ ዘመን ባሕል ሳይሆን የሰው ልጆች በደረሱበት የላቀ ስነ ምግባር ነው፡፡ ለሰው ልጆች ሁሉ ምሳሌ እንዲሆን በፈጣሪ የተላከ ሰው በእርሱ ዘመን ከነበረው ኋላ ቀር ባሕል የላቀ ስብዕና ሊኖረው ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን ለሁሉም የሰው ልጆች የሚመጥን ምሳሌ መሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሙስሊም ወገኖች ሙሐመድ ከነቢያት ሁሉ የላቀ ሥነ ምግባር የነበረውና የእርሱን ምሳሌነት መከተል ለጀነት እንደሚያበቃ ማመናቸው ስህተት ይሆናል፡፡ እነ ሙሴ፣ ዳዊት፣ ኢሳይያስና ሌሎች ነቢያት የኖሩበት ዘመን ከሙሐመድ በብዙ መቶ ዓመታት የሚቀድም ቢሆንም አንዳቸውም እንዲህ ያለ አስነዋሪ ተግባር አልፈፀሙም፡፡

ሦስተኛው የሚሰጡት ምላሽ አይሻ በወቅቱ በነበረው ሁኔታ ለአቅመ ሔዋን ደርሳለች የሚል ነው፡፡ ለዚህም የአየር ፀባይን እንደ ምክንያት ይጠቅሳሉ፡፡ የአየር ፀባይ በዕድገት ላይ መጠነኛ ተፅዕኖ እንዳለው ያስማማናል፡፡ በዚህም ምክንያት በበረሃማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶች ቶሎ የወር አበባ ሊያዩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የወር አበባ ስላዩ ብቻ ለጋብቻና ለግብረ ሥጋ ግንኙነት ብቁ ሆኑ ማለት አይደለም፡፡ አመጋገብና ሌሎች ጉዳዮችም ከዚህ ጋር ስለሚታዩ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን በችጋር በተመታው የአረብያ በረሃ ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች ዕድገታቸውን የሚያፋጥን የተመጣጠነ ምግብ እንደማያገኙ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ሲታይ አንዲት ሴት በ 9 ዓመቷ ለአቅመ ሔዋን ስለማትበቃ አይሻ ለአቅመ ሔዋን እንዳልበቃች መረዳት ይቻላል፡፡ የሆነው ሆኖ እስላማዊ ሐዲሳት ለሙስሊም ተሟጋቾች መፈናፈኛ በማይሰጥ ሁኔታ በግልፅ አይሻ ለአቅመ ሔዋን ያልበቃች ጨቅላ እንደነበረች ስለሚናገሩ ክርክሩ በአራት ነጥብ የተዘጋ ነው፡፡ ሳሂህ አልቡኻሪ እንዲህ ይላል፡-

“በመስጂድ ቅጥር ውስጥ የሚጫወቱ ኢትዮጵያውያንን ስመለከት ሳለሁ ነቢዩ በሪድዓው (ከላይ በሚለበስ ልብስ) ይከልለኝ ነበር፡፡ እስኪበቃኝ ድረስ አየኋቸው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ክስተት (ለአቅመ ሔዋን ያልበቃች) ትንሽዬ ልጅ እንዴት መያዝ እንዳለባት መረዳት ትችላላችሁ፡፡”[4]

“አይሻ እንዳወራችው፡- ነቢዩ ባሉበት ቦታ ከሴት ጓደኞቼ ጋር በአሻንጉሊቶች እጫወት ነበር፡፡ የአላህ መልእክተኛ ወደ ቤት ሲገባ ጓደኞቼ ይደበቁ ነበር ነገር ግን እርሱ ይጠራቸውና ከእኔ ጋር እንዲጫወቱ ይነግራቸዋል፡፡”[5]

ፈትህ አል-ባሪ ውስጥ እንዲህ ተብሏል፡- “በአሻንጉሊቶችና በተመሳሳይ ምስሎች መጫወት የተከለከለ ነው፤ ነገር ግን አይሻ ለአቅመ ሔዋን ያልበቃች ትንሽ ልጅ ስለነበረች ተፈቅዶላታል፡፡”[6]

ሙስሊም ተሟጋቾች አይሻ በ 9 ዓመቷ ለአቅመ ሔዋን ደርሳለች የሚሉን በሐዲሳቱ መሠረት በወቅቱ በአሻንጉሊቶች ትጫወት እንደነበር መገለጹን እንዴት ቢያዩት ነው? በእስልምና ለአቅመ ሔዋን የደረሰች ሴት በአሻንጉሊት እንድትጫወት አይፈቀድላትም!

በአራተኛ ደረጃ ጋብቻው ኋላ ቀር ባሕሎችን ከማስቀረት አንፃር ጠቃሚ ስለነበር ትክክል ነው የሚል አስገራሚ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ለዚህም በሸዋል ወር ማግባትንና የወዳጅን ልጅ ማግባትን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ፡፡ በአረቦች ባሕል መሠረት በሸዋል ወር ማግባትና የወዳጅን ልጅ ማግባት እንደ ነውር ስለሚቆጠር ነቢዩ ሁለቱንም ክልከላዎች በመጣስ ጥሩ ምሳሌ ሆነዋል ይላሉ፡፡ ይህ ሚዛን የሚደፋ ሙግት አይደለም፡፡ ሙሐመድ ኋላ ቀር ባሕልን ለማስቀረት ህፃን ልጅን የማግባት ሌላ የከፋ ኋላ ቀር ተግባር መፈፀም የለበትም፡፡ በሸዋል ወር ማግባት እንደሚቻል ለማስተማር ከፈለገ ለምን በአሻንጉሊት የምትጫወትን ህፃን ልጅ አገባ? ለምንስ የምትመጥነውን ሌላ ሴት አላገባም? የወዳጅንስ ልጅ ማግባት ከፈለገ አቡበከር ብቸኛ ወዳጁ ስላልነበረ የሌሎች ወዳጆቹን ልጆች ማግባት ይችል አልነበር? ደግሞ እኮ የወዳጁን የዑመርን ልጅ ሐፍሷን በማግባት የወዳጅን ልጅ ማግባት እንደሚቻል አሳይቷል፡፡ እርሱ በቂ አልነበር? ሲጀመር በአረቦች ባሕል መሠረት የወዳጅን ልጅ ማግባት አይቻልም ነበር የሚለው ምክንያት ማስረጃ የሌለው ፈጠራ ነው፡፡ ሙሐመድ አይሻን ለጋብቻ ሲጠይቅ አባቷ አቡበከር ሙሐመድ የእምነት ወንድሙና ወዳጁ መሆኑን በመጥቀስ እምቢታውን ገልፆ ነበር፡፡ የወዳጅን ልጅ ማግባት አይቻልም ነበር የሚለው ምክንያት ከዚህ የአቡበከር ምላሽ በመነሳት የቀረበ እንጂ የእውነት በአረቦች ባሕል ውስጥ እንዲህ ያለ ልማድ ስለነበረ አይደለም፡፡ አረቦች ከወዳጅ ልጅ አልፈው የሥጋ ዘመዶቻቸውን እንኳ ሲያገቡ የነበሩና አሁንም ከዚያ ልማድ ያልወጡ ሕዝቦች ናቸው፡፡

የሚሰጡት አምስተኛ ምክንያት በሐዲሳት መሠረት ጋብቻቸው የተሳካ እንደነበር መገለፁን ነው፡፡ አይሻም ብዙ ሐዲሶችን መዘገብ መቻሏ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንዳልደረሰባት ያሳያል ይላሉ፡፡ ይህኛውም ሙግት ምንም አሳማኝ አይደለም፡፡ የሙሐመድን ስብዕና ለማጉላት ከ250-350 ዓመታት ዘግይተው የተጻፉት አፈታሪኮች ጥሩ ጥሩውን ብቻ መርጠው መጥፎ መጥፎውን የመደበቃቸው ሁኔታ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ምንጮች ጋብቻው የተሳካ ነበር ስላሉ የተሳካ አይሆንም፡፡ በ 9 ዓመት ህፃን ልጅና በ 54 ዓመት ጎልማሳ መካከል በሚደረግ ጋብቻ ውስጥ ሴቷ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሊደርስባት መቻሉ የሚያከራክር አይደለም፡፡ አይሻ ብዙ ሐዲሶችን መዘገቧ ጥሩ ትውስታ የነበራት ሴት መሆኗን እንጂ በጋብቻው ምክንያት ሥነ ልቦናዊ ጫና እንዳልደረሰባት የሚያሳይ አይደለም፡፡ ይህ ጋብቻ የተፈጸመው በዚህ ዘመን ቢሆን ኖሮ ሙሐመድ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተከስሶ ፍርድቤት ይቆም ነበር፡፡

ስድስተኛው ምክንያታቸው ወላጆቿ ጋብቻውን አልተቃወሙም የሚል ነው፡፡ ነገር ግን የአይሻ አባት አቡበከር፤ ሙሐመድ የእምነት ወንድሙና ወዳጁ መሆኑን በመጥቀስ  አይሻን ሊድርለት እንዳልፈለገ በጨዋ መንገድ ገልፆ ነበር፡፡ ይህ እምቢታ የአይሻን ዕድሜ በማገናዘብ የመገለፁ ሁኔታ ዝቅተኛ ቢሆንም ቢያንስ አቡበከር በጋብቻው ደስተኛ አለመሆኑና በግልፅ ያልተነገረ ቅሬታ እንደነበረው መገንዘብ ይቻላል፡፡ መታወቅ ያለበት ሌላው ጉዳይ ወላጆቿ ተቃውሞን አለማቅረባቸው በዘመኑ እንደነበረው ኋላ ቀር ማሕበረሰብ ሁሉ ያለዕድሜ ጋብቻ ስላለው ጉዳት ግንዛቤ የጎደላቸው ሰዎች መሆናቸውን እንጂ ጋብቻው ትክክል መሆኑን አያሳይም፡፡ ነቢይ የተባለው ሙሐመድ ቢያንስ ከእነርሱ ተሽሎ መገኘት ነበረበት፡፡

ሙስሊም ወገኖቻችን የሚሰጡት የመጨረሻው ምላሽ አላህ ለነቢዩ ፈቅዶለታል የሚል ነው፡፡ ሙሐመድ እንደ ማንኛውም ሰው ሰው በመሆኑ ሊሳሳት መቻሉን በማወቅ ይህንን የተኮነነ ተግባር መፈፀሙ ሰብኣዊ ድካሙን የሚያሳይ መሆኑን ተቀብሎ ማለፍ ሲቻል እንዲህ ያለውን ቅሌት በፈጣሪ ማሳበቡ ከሁሉም የከፋ ስህተት ነው፡፡ በእርግጥ ፈጣሪ እንደፈቀደለት የተናገረው ሙሐመድ ራሱ በመሆኑ ነቢይነቱን የሚቀበሉ ወገኖች ይህንን ወንጀል በፈጣሪ ለማሳበብ ይገደዳሉ፡፡ ሙሐመድ እንዲህ ብሎ ነበር፡-

“ሁለት ጊዜ በህልም ታየሽኝ፡፡ በሐር ጨርቅ ላይ ሆነሽ አየሁሽ፡፡ ‹‹ይህቺ ሚስትህ ናት፤ ግለጣት›› ተባልኩኝ፡፡ ስገልጥ አንቺ ነበርሽ፡፡ ይህ ህልም ከአላህ ከሆነ ይፈፀማል አልኩኝ፡፡”[7]

ይህ ህልም የሙሐመድን የልብ ምኞት የሚገልፅ እንጂ የፈጣሪን ፈቃድ የሚያሳይ አይደለም፡፡ ሙሐመድ አይሻን በጨቅላነቷ በማግባት በሙስሊሙ ዓለም ለሚገኙት ብዙ ሕፃናት የሰቆቃ ምንጭ ሆኗል፡፡ የእርሱን ምሳሌነት በመከተል ብዙ ሙስሊም ወንዶች ተመሳሳይ ተግባር ይፈፅማሉ፡፡ እንዲህ ያለውን አውዳሚ ተግባር በፈጣሪ ማሳበብ ትልቅ ድፍረት ነው!

አንዳንድ ሙስሊሞች ሙሐመድ ከአይሻ ጋር በ 9 ዓመቷ የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዳልፈፀመ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን በሐዲሳቱ ውስጥ “በ 9 ዓመቷ ጋብቻውን አሟላ” በተባለው ውስጥ “አሟላ” (consummated) ለሚለው ቃል የገባው የአረብኛ ቃል “ደኻላ” የሚል ሲሆን Hans-Wehr Arabic-English Dictionary  ገፅ 273 ላይ በተጠቀሰው መሠረት የቃሉ ትርጉም “ወደ ውስጥ መግባት፣ መውጋት፣ (ወሲብን በሚገልፅ መንገድ) ማስገባት፣ የጋብቻን ወግ መፈፀም፣ ከሴት ጋር (ወሲብ ለመፈፀም) መተኛት” የሚሉ ትርጉሞች አሉት፡፡ ስለዚህ ሙሐመድ ከአይሻ ጋር አልተኛም የሚለው ግምት የማያስኬድ በመሆኑ የዕውቀት እጥረት ያለባቸው ሙስሊሞች ካልሆኑ በስተቀር ሙስሊም ሊቃውንት እንኳ የሚቀበሉት ሐሳብ አይደለም፡፡ በእስላማዊ የሐዲስ መጻሕፍት መሠረት አይሻ ልጅ መውለድ አልቻለችም፡፡ ሙሐመድ ሲሞት ዕድሜዋ ገና 18 የነበረ ቢሆንም ሙሐመድ ሚስቶቹ ከእርሱ ሞት በኋላ እንዳያገቡ በቁርኣን ክልከላን በማስቀመጡ ምክንያት ሌላ ሰው የማግባት ዕድል አላገኘችም (ሱራ 33፡53)፡፡ ይህም የሙሐመድን ራስ ወዳድነት የሚያሳይ ሲሆን  ልጅ አለመውለዷ ለአቅመ ሔዋን ሳትደርስ በማግባቷ ምክንያት የደረሰባት ጉዳት ውጤት ሊሆን ይችላል፡፡

በመጨረሻም ሙስሊም ወገኖቻችን እንዲያስቡበት የምንፈልገው ጉዳይ ሙሐመድ ህፃናትን ለጋብቻ ሲመርጥ የመጀመርያው ያለመሆኑን እውነታ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሙስናድ አህመድ ኢብን ሐንበል ሐዲስ ቁጥር 25636 ላይ እንዲህ ተፅፏል፡-

“የአባስ ልጅ ኡም ሐቢባ ጡት በመጥባት ዕድሜ ላይ ሳለች በዳዴ ስትሄድ ተመልክቷት ነቢዩ እንዲህ አለ፡- ወሏሂ እኔ በሕይወት እያለሁ የምታድግ ከሆነ አገባታለሁ፡፡” [8]

ውድ ሙስሊሞች ነቢያችሁ የእውነት እንዲህ ያለ አስተሳሰብ የነበረው ሰው ከሆነ ጤናውን ብንጠራጠር ልትፈርዱብን የሚገባ አይመስለኝም፡፡ ሙሐመድ ለነቢይነት የሚያበቃ ስብዕና አልነበረውም፡፡ በፍፁም ፈጣሪን የሚያውቅና የሚፈራ ሰው አልነበረም፡፡

—————————

ቁርኣን ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ህፃናትን ማግባትን ይፈቅዳልን?
በቁርኣን ውስጥ ገና የወር አበባን ያላዩ (ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ) ሴቶችን መፍታት ስለሚቻልበት ሁኔታ መመርያን የሚሰጥ አንድ ጥቅስ ይገኛል፡-
“እኒያም ከሴቶቻቸው ከአደፍ ያቋረጡት (በዒዳቸው ሕግ) ብትጠራጠሩ ዒዳቸው ሦስት ወር ነው፡፡ እኒያም ገና አደፍን ያላዩት (ዒዳቸው እንደዚሁ ነው)፡፡ የእርግዝና ባለቤቶችም ጊዜያቸው እርጉዛቸውን መውለድ ነው፡፡ አላህንም የሚፈራ ሰው ከነገሩ ሁሉ ለርሱ መግራትን ያደርግለታል፡፡” (የፍች ምዕራፍ 65፡4)
ይህንን ጥቅስ ግልፅ ለማድረግ ያህል አንድ ሙስሊም ወንድ አንዲትን የወር አበባዋ የተቋረጠ ሴት ለመፍታት ቢፈልግ ለሦስት ወር ያህል የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሳይፈፅም ይቆያል፡፡ ለአቅመ ሔዋን ባለመድረሷ ምክንያት የወር አበባ ያላየችን ሴት ለመፍታት ቢፈልግ እንዲሁ ሦስት ወር ያህል የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሳይፈፅም ይጠብቃል፡፡ ይህ የቁርኣን ሐታቾች ሁሉ የሚስማሙበት እስላማዊ መመርያ ሲሆን ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 7፣ መጽሐፍ 62፣ ቁጥር 63 ላይ በዚሁ መንገድ ተብራርቷል፡፡[9]ይድ አቡል ዓላ ማውዱዲ የተሰኙ ፓኪስታናዊ ሙስሊም ሊቅ ይህንን ጥቅስ በተመለከተ እንዲህ ይላሉ፡-
“ገና አደፍን ያላዩትን (የወር አበባ ያላዩትን) መፍታት የሚቻልበትን መመርያ የሚሰጠው ይህ የቁርኣን ጥቅስ ባሎች ከእንዲህ ያሉ ሴቶች ጋር የጋብቻ ወግ መፈፀም እንደሚችሉ በግልፅ የሚያሳይ ነው፤ በመሆኑም ቁርኣን ያፀደቀውን ይህንን ተግባር ማንም የመከልከል መብት የለውም፡፡”[10]
ማውዱዲ በሙስሊሙ ዓለም እጅግ የተከበሩ የቁርኣን ተንታኝ ናቸው፡፡

———————

[1] Sahih Al-Bukhari, Volume 5, Book 58, Number 234; Volume 5, Book 58, Number 236; Volume 9, Book 87, Number 140; see also Number 139; Volume 7, Book 62, Number 64; see also Numbers 65 and 88; Sahih Muslim, Book 008, Number 3309; see also 3310; Book 008, Number 3311; Sunan Abu Dawud, Number 2116; Book 41, Number 4915; Book 13, Number 2380;

[2] Baker Ency. of the Bible volume 2, page 1407

[3] Jim West. Ancient Israelite Marriage Customs; http://www.theology.edu/marriage.htm

[4] Sahih Al-Bukhari, Volume 7, Book 62, Number 163)

[5] Sahih Al-Bukhari, Volume 8, Book 73, Number 151

[6] Fateh-al-Bari page 143, Vol.13

[7] Sahih al-Bukhari, 3606

[8] Musnad Ahmed, Number 25636

[9] Sahih al-Bukhari, Volume 7, Book 62, Number 63

[10] Sayid abul A’La maududi, The meaning of the Qur’an Vol. 5 pp. 599 & 617

ነቢዩ ሙሐመድ