የሙሐመድን ታሪክ ተዓማኒነት የተመለከቱ ወሳኝ ጥያቄዎች

የሙሐመድን ታሪክ ተዓማኒነት የተመለከቱ ወሳኝ ጥያቄዎች

  1. ስለ ሙሐመድ የምናውቃቸው አብዛኞቹ ነገሮች የተጻፉት ከህልፈታቸው ከክፍለ ዘመናት በኋላ መኾኑ የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ዋና ዋና የሚባሉትን እስላማዊ ትውፊቶች ብንመለከት ሳሂህ አል-ቡኻሪ (870 ዓ.ም.)፣ ሳሂህ ሙስሊም (875 ዓ.ም.)፣ ሱናን ኢብን ማጃህ (887 ዓ.ም.)፣ ሱናን አቡ ዳውድ (888 ዓ.ም.)፣ ጃሚ አት-ቲርሚዚ (892 ዓ.ም.)፣ ሱናን አን-ነሳዒ (915 ዓ.ም.) የተጻፉ ናቸው፡፡ የሙሐመድ ሕይወት ለሙስሊሞች እጅግ ወሳኝ ከመኾኑ አንጻር በጽሑፍ ለመስፈር ይህን ያህል ዘመን መዘግየቱ ለምንድነው? ይህን ያህል የጊዜ ክፍተት የሚያሳዩ ጽሑፎችስ ተዓማኒነታቸው ምን ያህል ነው?
  2. የሙሐመድን ግለ ታሪክ በቀዳሚነት እንደከተቡ የሚነገርላቸው ኢብን ኢስሐቅ የተሰኙት የኢራቅ ሰው ነበሩ፡፡ “ሲራት ረሱል አላህ (የአላህ መልእክተኛ ግለ ታሪክ)” የሚል ርዕስ ያለው ይህ ድርሳን በ765 ዓ.ም. እንደተጻፈ የሚነገር ሲሆን በሁለት የእርማት ሥራዎች ውስጥ አልፏል፡፡ የመጀመርያውን እርማት ያደረጉት አል-ባካኢ የተሰኙ ደቀ መዝሙራቸው ነበሩ፡፡ በማስከተል ደግሞ ኢብን ሒሻም የተሰኙ ሰው በ833 ዓ.ም. በማረም አሁን ያለውን መልክ ሰጥተውታል፡፡ ጉዳዩን ያጠኑ ሊቃውንት የኢብን ኢስሐቅ ሥራ ከሞላ ጎደል በኢብን ሒሻምና በአል-ጦበሪ ጽሑፎች ውስጥ እንደሚገኝ የሚናገሩ ሲሆን ነገር ግን ዋናው ጽሑፍ ጠፍቷል፡፡ ይህንን ግለታሪክ በማረም አሁን ያለውን መልክ ያስያዙት ኢብን ሒሻም በመቅድሙ ላይ የሙሐመድን ታሪክ ሆነ ብለው መቀየራቸውን እንደሚከተለው ይናዘዛሉ፡- “ለመነጋገር አሳፋሪ የሆኑ ነገሮች፣ አንዳንድ ሰዎችን ሊያስጨንቁ የሚችሉ ጉዳዮችና በአል-ባካኢ [የኢብን ሒሻም መምህር] ተዓማኒ ተደርገው እንደማይቆጠሩ የተነገሩኝ ጉዳዮች እንዲወገዱ አድርጌያለሁ፡፡”[1] እንዲህ ካሉት ምንጮች እውነተኛ ታሪክ እንዴት ሊጠበቅ ይችላል?
  3. ቡኻራ ከተሰኘችው የኡዝቤኪስታን ከተማ የመጡት ኢማም አል-ቡኻሪ ዋነኛ የሐዲስ ሰብሳቢ ነበሩ፤ 600,000 ትረካዎችን ሰብስበው የነበረ ሲሆን ከነዚህ መካከል ተኣማኒ ናቸው ያሏቸውን 7397 የሚሆኑትን ብቻ በመምረጥ የተቀሩትን አስወግደዋል (የስብስቦቹን ትክክለኛ ቁጥር በተመለከተ የተለያዩ መጻሕፍት የተለያዩ ቁጥሮችን ይጠቅሳሉ)፡፡ የተደጋገሙ ትረካዎች ሳይቆጠሩ የተጣራው ቁጥር 2602 ብቻ ነው የሚኾነው፡፡ ይህ ማለት ከጠቅላላው ስብስብ በአል-ቡኻሪ የተመዘገቡት ከአንድ ከመቶ ያነሱ ናቸው (0.43%)፡፡ 99.5% የሚኾነው ታሪክ የት ገባ? ስለ አንድ ግለሰብ ይህን ያህል የሐሰት ታሪክ ፈጥሮ ያወራ ሕዝብ በዓለም ታሪክ ይኖር ይኾን? በዘመኑ የነበረው ሕዝበ ሙስሊም የፈጠራ ታሪክ ከማውራት ውጪ ሥራ አልነበረው ማለት ነው? የማይታመን ነው!
  4. ለሙሐመድ ታሪክ በኹሉም ረገድ ቅርበት የነበራቸው አረቦች እያሉ አብዛኞቹ ጸሐፊያን በእስልምና ከተወረሩት አካባቢዎች የመጡ አል-ቡኻሪ፣ ሙስሊም፣ ኢብን ማጃህ፣ አቡ ዳውድ፣ አት-ትርሚዚ እና አን-ነሳዒ የመሳሰሉት አረብ ያልኾኑ ግለሰቦች መኾናቸው ለምንድነው? ይህ ኹኔታ በጽሑፎቹ ተዓማኒነት ላይ ጥርጣሬን አያጭርምን?
  5. የሐዲስ ስብስቦችን በተመለከተ በሱኒዎችና በሺኣዎች መካከል ስምምነት አለመኖሩ የታወቀ ነው፡፡ የሺኣ ሙስሊሞች በነቢዩ ሙሐመድ የሥጋ ዘሮች ወይንም በኢማም አሊይ ደጋፊዎች የተዘገቡትን ብቻ የሚቀበሉ ሲኾን ከሱኒዎች የተለዩ የሐዲስ ጥራዞች አሏቸው፡፡ “አሥራ ሁለቱ” በመባል የሚታወቀው ዋና የሺኣ እስልምና አንጃ ኪታብ አል ካፊ፣ መን ላ ያህዱሩሁ ፊቅህ፣ ታህዚብ አል-አህካም እና አል-ኢስቲብሳር የተሰኙ አራት ስብስቦችን በመቀበል ስድስቱን የሱኒ ሐዲሶች የፈጠራ ሥራዎች እንደኾኑ ይገልጻል፡፡ ማንን እንመን? የቱን እንቀበል? መጻሕፍቱ በተጋጁበት ዘመን የነበሩ ወገኖች በመጽሐፍቱ ዙርያ ይህን ያህል የከረረ አለመግባባት ከነበራቸው በዚህ ዘመን የምንገኘው እኛ እንዴት እርግጠኞች ልንኾን እንችላለን? ኹሉንም የሐዲስ መጻሕፍት ሙሉ በሙሉ የማይቀበሉ እስላማዊ ቡድኖች በዚህ ዘመን መፈጠራቸው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡
  6. ነቢዩ ሙሐመድ ከቁርኣን ውጪ ሌላ ነገር እንዳይጻፍ አጥብቀው መከልከላቸውን እነዚሁ የሐዲስ ስብስቦች ይናዘዛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ሳሂህ አል-ቡኻሪ መጽሐፍ 42 ቁጥር 7147 ላይ ነቢዩ ሙሐመድ ምንም ዓይነት ሐዲስ ስለ እሳቸው መጻፍ ክልክል መኾኑንና የጻፈም ካለ እንዲሰርዝ አዘዋል፡፡ ሱናን አቡ ዳውድ ሐዲስ ቁጥር 3640 ላይ እንደተዘገበው ዘይድ የተሰኘው የሙሐመድ ጸሐፊ አንድ ሰው ከነቢዩ ሙሐመድ የሰማውን ሐዲስ ጽፎ ባገኘው ጊዜ ነቢዩ ሙሐመድ ምንም ዓይነት ሐዲስ ስለ እሳቸው መጻፍ ክልክል መኾኑን እንደተናገሩ አስታውሶት የጻፈውን እንዲያጠፋ ነግሮታል፡፡ ታድያ ሙስሊሞች የሙሐመድን ትዕዛዝ በመጣስ ስለምን ጻፉ?

ጥያቄዎቻችን ይቀጥላሉ። ለነዚህ ጥያቄዎች አሳማኝ ምላሽ የሚሰጠን ሙስሊም ከተገኘ በዚሁ ገጽ ላይ እንደምናሰፍር ቃል እንገባለን።

_______________________________________________________

[1] Alfred Guillaume. The Life of Muhammad, A Translation of Ibn Ishaq’s Sirat Rasul Allah; 1955, p. 691

 

ነቢዩ ሙሐመድ