የነቢይነት ማሕተም ወይንስ የጤና ችግር?

የነቢይነት ማሕተም ወይንስ የጤና ችግር?

የእስልምና ቅዱሳት መጻሕፍት ለሙሐመድ ነቢይነት ማረጋገጫ ብለው የሚያቀርቧቸው ነገሮች በእጅጉ አስገራሚ ናቸው፡፡ ሙሐመድ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት ለነቢይነት የሚያበቃ ማስረጃም ሆነ ማረጋገጫ ስለሌለው ጥንታውያን ሙስሊሞች ያዩትን ነገር ሁሉ ለነቢይነቱ ማረጋገጫ ምልክት አድርገው ይተረጉሙ እንደነበር መረዳት ይቻላል፡፡

ሙሐመድ ራሱን የነቢያት መደምደምያ ወይንም ማሕተም አድርጎ ይቆጥር እንደነበር ቁርኣንም ሆነ የሐዲስ መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡-

“ሙሐመድ ከወንዶቻችሁ የአንድንም ሰው አባት አይደለም፤ ግን የአላህ መልክተኛና የነቢዮች መደምደሚያ ነው፤ አላህም በነገሩ ሁላ ዐዋቂ ነው።” (ሱራ 33፡40)

Muhammad is not the father of any of your men, but (he is) the Apostle of God, and the Seal of the Prophets: and God has full knowledge of all things. (33:40 Yusuf Ali)

ይህ ዓይነቱ ንግር ሙሐመድን ከነቢያት ሁሉ የበላይ በማድረግ ለሰው ልጆች ሁሉ አስፈላጊ ስለሚያደርገው በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ስለዚህ የነቢያት ማሕተም ስለመሆኑ ማሳያ የሚሆን የማረጋገጫ ምልክት ያሻዋል፡፡ ነገር ግን ለዚህ የሚሆን አንዳችም ልዕለ ተፈጥሯዊ ምልክት ባለመኖሩ ሳብያ ጥንታውያን ሙስሊሞች “ምልክት” ሆነው ሊተረጎሙ የሚችሉ ነገሮችን ለማግኘት ቀቢፀ ተስፋ ውስጥ የገቡ ይመስላል፡፡ በዚህም ሒደት በሙሐመድ ጀርባ ላይ የሚገኝ እብጠት እንዴት ሆኖ የነቢይነቱ ምልክት ተደርጎ እንደተተረጎመ ተዓማኒ የተባሉት የሐዲስ ስብስቦች እንዲህ ይነግሩናል፡-

አስ ሳዒብ ቢን ያዚድ እንዳስተላለፈው፡- አክስቴ ነቢዩ ዘንድ ወሰደችኝና እንዲህ አለች፣ “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ይህ የእህቴ ልጅ እግሩ ላይ ህመም አለበት፡፡” ከዚያም እጁን በላዬ አሳልፎ የአላህን በረከት ለመነልኝ፤ ከዚያም ትጥበት ፈፀመና ከተረፈው ውኀ ጠጣሁ፡፡ ከዚያም ከበስተጀርባው ቆሜ የነቢይነት ማሕተምን በትከሻው መካከል አየሁ፤ ልክ እንደ “ዚር አል-ሒጅላ” ይመስላል (የትንሽ ድንኳን ቁልፍ፣ ነገር ግን አንዳንዶች የቆቅ እንቁላል፣ ወዘተ. ይመስላል ይላሉ)፡፡ (Sahih al-Bukhari Volume 1, Book 4, Number 189)

አስ ሳዒብ እንዳስተላለፈው፡- አክስቴ ወደ አላህ መልእክተኛ ወስዳኝ እንዲህ አለች፡- “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! የእህቴ ልጅ ታሟል፡፡” ነቢዩ ጭንቅላቴን በመንካት የአላህን በረከት ለመነልኝ፡፡ ከዚያም ትጥበት ከፈፀመ በኋላ ከትጥበቱ የተረፈውን ውኀ ጠጥቼ ከጀርባው በመቆም “ኸተም አን-ኑቡዋ” (የነቢይነት ማሕተም) በትከሻዎቹ መካከል ልክ እንደ ድንኳን ቁልፍ የሚመስል አየሁ፡፡ (Sahih al-Bukhari Volume 7, Book 70, Number 574)

ጃቢር ቢን ማሙራ እንደዘገበው፡- የእርግብ ዕንቁላል የሚመስለውን ማሕተሙን ጀርባው ላይ አየሁ፡፡ (Sahih Muslim Book 030, Number 5790)

አብዱላህ ቢን ሰርጂስ እንደዘገበው፡- … ከዚያም ተከትዬው ሄድኩና በትከሻዎቹ መካከል የሚገኘውን የነቢይነት ማሕተም ተመለከትኩ፤ ወደ ግራ ጎኑ አቅጣጫ የቆዳ ትርፍ ሥጋ የሚመስሉ ምልክቶች አሉበት፡፡ (Sahih Muslim Book 030, Number 5793)

ቁራህ ኢብን ኢያስ አል-ሙዛኒ እንዳስተላለፈው፡- ከሙዛይናህ ጋር ሆነን ወደ አላህ መልእክተኛ (ሰላም በሳቸው ላይ ይሁንና) መጣንና ቃል ኪዳን ገባን፡፡ የሸሚዙ ቁልፍ ክፍት ነበር፡፡ የታማኝነት ቃል ኪዳን ገባሁለትና በሸሚዙ አንገት ጌ እጄን አስገብቼ ማሕተሙን ስነካው ተሰማኝ… (Sunan of Abu Dawud Book 32, Number 4071)

ተመሳሳይ ዘገባዎች በሌሎች በርካታ እስላማዊ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ሙሐመድ የነቢያት መደምደሚያ የመሆኑ ምልክት በጀርባው ላይ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ ይህም ምልክት “የነቢያት ማሕተም” (ኸተም አን-ኑቡዋ) የተባለ ሲሆን ሱራ 33፡40 ላይ “የነቢዮች መደምደሚያ” ተብሎ ከተተረጎመው ጋር ተመሳሳይ የሆነ የአረብኛ ሐረግ ነው፡፡ ከዘገባዎቹ እንደምንገነዘበው ጥንታውያን ሙስሊሞች “የነቢያት ማሕተም” ብለው የተረጎሙት ምልክት በሙሐመድ ጀርባ ላይ የሚገኝ ትርፍ ሥጋ፣ እባጭ ወይንም ዕጢ ነው፡፡ እንዲህ ያለ የጤና ችግር በምን መንገድ የነቢይነት ምልክት ተደርጎ እንደተወሰደና ለሙሐመድ ነቢይነት ማረጋገጫ ሆኖ እንደቀረበ ማሰብ በእጅጉ ይቸግራል፡፡ ውድ ሙስሊሞች፤ ምን እያላችሁ ነው? እስኪ አስረዱን?


 

ነቢዩ ሙሐመድ